
አዲስ አበባ፡- በዘንድሮው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር 558 ሚሊዮን 524 ሺህ 512 ችግኞች እንደሚተከሉ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ግብርና ቢሮ አስታወቀ፡፡
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የግብርናና ገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡስማን ሱሩር እንደገለጹት፤ በክልሉ በሁለት ሺህ 630 ጣቢያዎች የችግኝ ዝግጅት ሥራ ሲከናወን ቆይቷል፡፡ በዘንድሮው አረንጓዴ ዐሻራ መርሃግብር 558 ሚሊዮን 524 ሺህ512 ችግኞች ይተከላሉ፡፡
ከሚተከሉት ችግኞች ውስጥ ከ60 በመቶ በላይ የሚሆኑት ዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚዊ ጠቀሜታ ያላቸው እንደ ቡና፣ አትክልት፣ ፍራፍሬ፣ መኖና እንሰትን ተክሎች መሆናቸውን አመላክተዋል።
ለተከላ የሚያስፈልጉ ቅድመ ዝግጅቶች ተጠናቀዋል ያሉት ቢሮ ኃላፊው፤ ሁለት ሺህ 269 የተከላ ቦታ መለየቱን፣ 245 ሚሊዮን 341 ሺህ 46 ጉድጓዶችን መዘጋጀታቸውን እንዲሁም 40 ሺህ 902 ነጥብ 34 ሄክታር ካርታ የማዘጋጀትና ሥራ መከናወኑን ጠቅሰዋል።
እስካሁን ድረስ የዝናብ ስርጭት ባለባቸው አካባቢዎችም 78 ሚሊዮን 710 ሺህ 759 ችግኞች መተከላቸውንም ገልጸዋል፡፡
እንደ አቶ ኡስማን ገለጻ፤ በክልሉ የአረንጓዴ ዐሻራ ሥራው ውጤታማ ነው፤ ውጤታማ ያደረገው ደግሞ ሕብረተሰቡ አምኖበት በሰፊው እየተሳተፈበት በመሆኑ ነው፡፡
በወል መሬትና ተራሮች ባሉበት አካባቢ ለማገዶ፣ ለግንባታ፣ ለኢንዱስትሪ ግብዓት እንዲሁም ለአካባቢ ጥበቃ ሊውሉ የሚችሉ ደኖች እንደሚለሙ ገልጸው፤ በዚህም የተራቆቱና ከአገልግሎት ውጪ የነበሩ መሬቶች አገግመዋል፡፡ መሬቱ በመራቆቱ ምክንያት ስጋት ውስጥ የነበሩ የማህበረሰብ ክፍሎች ችግርም ተፈቷል፡፡
የተፋሰስ ሥራዎችን በማስቀደም እርከን የመሥራትና ችግኝ የመትከል ሥራውን በማከናወን ውሃው ባለበት እንዲቀር ማድረግ ተችሏል ያሉት አቶ ኡስማን፤ አፈሩም ባለበት እንዲቀር ከተደረገ በኋላ በወል መሬቶች ላይ የተደራጁ ወጣቶች ፍራፍሬና አትክልት እያለሙ ሀብት መፍጠር ችለዋል ሲሉ አስረድተዋል።
ከወል መሬት ውጭ ያሉ ቦታዎችንም በአብዛኛው ዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ባላቸው ተክሎች እንዲሸፈኑ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡
ክልሉ አንድ አርሶ አደር በመጀመሪያው ዓመት 30፣ በሁለተኛው ዓመት 40፣ እንዲሁም በሦስተኛው ዓመት 30 የፍራፍሬ ዛፎች መትከል ይኖርበታል ከሚለው የአረንጓዴ ዐሻራ ንቅናቄ ጋር በማስተሳሰር ህብረተሰቡ በባለቤትነት የችግኝ ተከላውን እያከናወነ እንደሚገኝም ጠቁመዋል፡፡
ጥቅምት መጀመሪያ ላይ የተቀናጀ የግብርና ልማት ንቅናቄ ተካሂዶ እንደነበር አስታውሰው፤ በበልግ ወቅት በተከናወነ ንቅናቄም 10 ሚሊዮን ቡና ጨምሮ 14 ሚሊዮን ችግኞች መተከላቸውን አንስተዋል። በንቅናቄው ከተካተቱ ሥራዎች አንዱ የአረንጓዴ ዐሻራ የተተከሉ ችግኞችን የመንከባከብና ለዘንድሮ ተከላ ዝግጅት ማድረግን እንደሚያጠቃልል አመላክተዋል።
የአረንጓዴ ዐሻራ የመኖርና ያለመኖር ጉዳይ በመሆኑ በቀጣይነትም ሁላችንም በባለቤትነት የምናከናውነውና አጠናክረን የምንቀጥለው ይሆናል ብለዋል፡፡
አቶ ኡስማን እንዳስታወቁት፤ በተያዘው ዓመት በተቀናጀ ተፋሰስ ልማት 147 ሺህ ሄክታር መሬት ለማልማት ታቅዶ ከእቅዱ በላይ 219 ሺህ ሄክታር መሬት የተፋሰስ ልማት ተከናውኗል፡፡ በሥራው አንድ ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን ዜጎች ተሳትፈዋል፤ ከዚህ ውስጥ ግማሽ ያክሉ ሴቶች ናቸው፡፡
ፋንታነሽ ክንዴ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 9 ቀን 2016 ዓ.ም