የዘንድሮው የኢትዮጵያ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ማጠናቀቂያ ሰርተፍኬት ፈተና ባለፈው ከማክሰኞ ሀምሌ 3 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ለተከታታይ አራት ቀናት ሲሰጥ ቆይቶ ተጠናቋል፡፡ ፈተናው ከመሰጠቱ በፊት የተለያዩ ውዥንብሮች ሲናፈሱ ቆይተዋል። በማህበራዊ ድረገፆች ፈተናው በበይነ መረብ እንደማይሰጥ በስፋት ሲሰራጭ መቆየቱ ይታወሳል፡፡ በተለይ በአዲስ አበባ ያሉ አንዳንድ ትምህርት ቤቶች ለተማሪዎች ” የበየነ መረብ (ኦንላይን) ፈተና ቀርቷል ” እያሉ ለተማሪዎች መናገራቸውና የጽሁፍ መልዕክት በቴሌግራም ላይ መለጠፋቸው የተማሪ ወላጆችንና ተማሪዎችን ይበልጥ ውዝግብ ውስጥ ከቶ ነበር፡፡
እንዲህ ያለው ውሳኔ የሚተላለፈው ከማዕከል ከትምህርት ሚኒስቴር ሆኖ ሳለ ትምህርት ቤቶቹ ውሳኔውን ማን እንዳሳለፈ በይፋ ያሉት ነገር ሳይኖር በደፈናው የበይነ መረብ ፈተናው ‹‹ቀርቷል›› የሚል ነገር ለተማሪዎቻቸው መናገራቸው ግራ አጋቢ ነበር፡፡ ኋላም እራሳቸው ትምህርት ቤቶቹ ቀድሞ ያሰራጩትን ያልተረጋገጠ መረጃ በማጥፋት የበይነ መረብ ፈተናው እንዳልቀረ መልሰው መግለፃቸውም ውዥንብሩን አስቀርቷል፡፡
በዚህም ቀላል የማይባሉ የአስራ ሁለተኛ ክፍል ተፈታኝ ተማሪዎች ግራ መጋባት ውስጥ ገብተው የነበረ ቢሆንም ትምህርት ሚኒስቴር በጉዳዩ ላይ የተጣራ መረጃ ይዞ በመቅረቡና ፈተናው በበይነ መረብና በወረቀት እንደሚሰጥ በማስታወቁ ተፈታኞች በወረቀትም በበይነ መረብም ፈተናውን እንዲወስዱ ተደርጓል፡፡
የትምህርት ሚኒስትሩ ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና በአብርሆት ቤተ-መጽሃፍት በመገኘት የ12ኛ ክፍል የማህበራዊ ሳይንስ ብሄራዊ ፈተናን ባስጀመሩበት ወቅት፣ በዚህ ዓመት እየተተገበረ ያለው የወረቀትና የኦን ላይን ፈተና (hybrid exam) መሆኑን አመልክተዋል። ለወደፊቱ ተማሪዎችን ሙሉ በሙሉ በኦን ላይን መፈተን ሲቻል የበለጠ ፈተናውን ከስርቆትና ከመኮራረጅ ከመታደጉም በላይ ለትምህርት ጥራት የበኩሉን ድርሻ እንደሚያበረክትም ገልፀዋል፡፡ በተጨማሪም ፈተናውን ለማስተዳደር፣ ለቁጥጥር፣ ለህትመት፣ ለማጓጓዝ፣ ለደህንትና መሰል ወጪዎችን ለመቀነስ እንደሚያስችል ተናግረዋል።
ሚኒስትሩ በመጨረሻም የፈተናውን ድባብ ለማበላሸት ሀሰተኛ መረጃዎች በማህበራዊ ሚዲያዎች ስለሚንሸራሸሩ ሁሉም የማህበረሰብ ክፍል ከሀሰተኛ መረጃዎች ራሱን እንዲጠብቅ አሳስበው ተማሪዎችም ተረጋግተው ፈተናቸውን እንዲሠሩ መክረዋል፡፡
ፈተናው ከዚህ ቀደም እንደተገለጸው በበይነ መረብ (ኦንላይን) እና በወረቀት እንደተማሪዎች የቀደመ ምርጫ መሠረት የተሰጠ ሲሆን አስቀድመው በወረቀት ለመፈተን የመረጡ ተማሪዎች ወደተመደቡበት ዩኒቨርሲቲ፤ በበይነ መረብ (ኦንላይን) ለመፈተን የመረጡ ተማሪዎች ደግሞ በተመደቡበት የፈተና ጣቢያ ተገኝተው ፈተናውን ወስደዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የ2016 ዓ.ም የትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ሀገር አቀፍ ፈተና ተማሪዎች በተመደቡባቸው የኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ /ዋናው ግቢ/፣ በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲና በኢፌዴሪ ቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ተፈትነዋል፡፡
ፈተናው በተጀመረበት ወቅት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኤ ፍ ቢ የፈተና መስጫ ጣቢያ የመጀመሪያውን ፈተና አጠናቀው የወጡ ተማሪዎችን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ሃላፊ ዶ/ር ዘላለም ሙላቱ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ ጋር በመሆን ስለፈተናው በመጠየቅ በትኩረት እንዲሠሩ አበረታተዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አምናም ካቻምናም የተፈታኞች ቁጥር ሳይቀንስ ፍፁም ሰላማዊ በሆነ መልኩ ዘንድሮም የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና በተሳካ ሁኔታ ተካሂዶ ተጠናቋል፡፡ በእርግጥ በሀገር አቀፍ ደረጃ አምና በ12ኛ ክፍል ደረጃ የተመዘገበው ውጤት እጅግ አስደንጋጭ ነበር፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ ተፈታኝ ተማሪዎችም ያመጡት ውጤት ዝቅተኛ ነበር፡፡ በዘንድሮው በጀት ዓመት ግን ገና ከጅምሩ ከትምህርት አመራሮች ጀምሮ አስከተማሪውና ወላጅ ድረስ በተማሪዎች ውጤት መሻሻል ዙሪያ ጠንካራ ሥራ በመሠራቱ የአምናው ውጤት ዘንድሮ የሚደገም አይመስልም፡፡
ግጭቶች በተከሰቱባቸው የአማራ፣ ትግራይና አፋር ክልሎች ከዚህ ቀደም በተለይ በአማራና አፋር ክልል በተወሰኑ አካባቢዎች ላይ ብቻ ፈተናው የተሰጠ ቢሆንም ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ በትግራይ ክልል ከዚህ ቀደም አስረኛ ክፍል የነበሩ ተማሪዎች ከአራት ዓመታት በኋላ የማካካሻ ትምህርት ወስደው የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና በሀገር አቀፍ ደረጃ ከሁሉም ተማሪዎች ጋር እኩል ወስደዋል፡፡ በተመሳሳይ በአፋር ሙሉ በሙሉ እንዲሁም በአማራ ክልል በአብዛኛዎቹ አካባቢዎች ተማሪዎች የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ መልቀቂያ ፈተናቸውን ወስደዋል፡፡
በትግራይ ክልል የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ መልቀቂያ ፈተና በሁለት ዙር ከሐምሌ 2 እስከ 12 2016 ዓ.ም በመቐለ፣ ራያ፣ አዲግራት እና አክሱም ዩኒቨርሲቲዎች የተሰጠ ሲሆን የመጀመሪያው ዙር ፈተና ከሐምሌ 2 እስከ 5 2016 ዓ.ም ተሰጥቷል፡፡ ከ31 ሺህ በላይ የማኅበራዊ እና የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች በዚህ ዙር ለፈተና እንደተቀመጡም ተገልጿል፡፡
በተመሳሳይ በአማራ ክልል ውስጥ የተፈታኞች ቁጥር ከታቀደው በግማሽ እንደሚያንስ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ማስታወቁ የተነገረ ሲሆን ለዚህም በክልል በአንዳንድ አካባቢዎች የሚታየው ግጭት ለቁጥሩ ማነስ አስተዋፅኦ ሳያደርግ እንዳልቀረ ተነግሯል፡፡ በዚህ ዓመት ከ200 ሺህ በላይ ተማሪዎች ለ12ኛ ክፍል ብሄራዊ መልቀቂያ ፈተና እንደሚቀመጡ ቢሮው አቅዶ እንደነበር የገለፀ ቢሆንም ፈተና ላይ የተቀመጡት ግን 96 ሺህ 408 ተማሪዎች መሆናቸውን አስታውቋል፡፡
ቀሪ 106 ሺህ ያክል ተማሪዎች ፈተና እንደማይወስዱም የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮው የተናገረ ሲሆን አሁን ላይ ፈተናውን የማይወስዱ ተማሪዎች ተምረው በመስከረም 2017 ዓ.ም በሁለተኛ ዙር ለመፈተን እቅድ እንደተያዘ ገልጿል። በ2016 ዓ.ም ፈተናውን የወሰዱት ተማሪዎች ለፈተናው መቀመጥ የሚያስችላቸውን ትምህርት የተከታተሉ መሆናቸውንም ጠቁሟል፡፡ ባለፉት በርካታ ዓመታት የሀገሪቱ ከፍተኛው ውጤት የሚመዘገብበት እና እጅግ በጣም ጎበዝ ተማሪዎች የሚገኙበት አማራ ክልል ዘንድሮ የሚጠበቅበትን ያክል ተማሪ ባለማስተማሩ ሳቢያ በርካታ ተማሪዎች በመጀመሪያ ዙር ፈተና ላይ መቀምጥ እንዳልቻሉም ነው ቢሮው የጠቀሰው፡፡
በሌላ በኩል በአማራ ክልል ዘንድሮ ትምህርታቸውን መማር ከነበረባቸው 6 ነጥብ 2 ሚሊዮን ተማሪዎች መካከል መማር የቻሉት 3 ነጥብ 7 ሚሊዮን ተማሪዎች መሆናቸው ተነግሯል፡፡ 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ተማሪዎች ትምህርት እንዳላገኙም ተጠቁሟል፡፡ እስከ አሁን ድረስ ትምህርት ያልጀመሩ ዞኖች እና ወረዳዎች እንዳሉም ተጠቅሷል፡፡ ተማሪዎች ካልተማሩባቸው አካባቢዎች መካከል ሰሜን ጎጃም እና ምዕራብ ጎጃም ዞኖች ዋነኞቹ መሆናቸውም ተጠቅሷል፡፡ አንድም የ6ኛ ፣ የ8ኛ እና የ12ኛ ክፍል ተማሪዎችን እንደማያስፈትኑም ነው የተነገረው፡፡
የትግራይ ክልል ሙሉ በሙሉ ከግጭት አገግሟል ባይባልም በአንፃሩ ሰላም የሰፈነበት ክልል ሆኗል፡፡ በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት መሠረት ገቢራዊ ሊሆኑ የሚገባቸው ቀሪ ሥራዎች ቢኖሩም ክልልሉ ከግጭት ነፃ መሆኑ ቢዘገይም አልረፈደምና ነው ነገሩ ዘንድሮ በአብዛኛዎቹ የክልሉ አካባቢዎች ላይ የሚገኙ ተማሪዎች የ12ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተናን ወስደዋል፡፡ እነዚህ ተማሪዎች ጥሩ ውጤት አምጥተው የነገዋን ኢትዮጵያ መፃኢ ተስፋ ይወስናሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በአንፃሩ በአማራ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች ባሉ ግጭቶች ምክንያት በእቅዱ በተቀመጠው ልክ ተማሪዎችን ለፈተና ማስቀመጥ አልተቻለም። እንደውም ከዓምናው ጋር ሲነፃፀር ዘንድሮ ለ12ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና የተቀመጡ ተማሪዎች ቁጥር ዝቅተኛ መሆኑ ተነግሯል፡፡ ግጭቱ በዚሁ ከቀጠለ በቀጣዩ ዓመት 12ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና የሚወስዱ ተማሪዎች ቁጥር ከዚህም ሊያንስ እንደሚችል የብዙዎች ግምት ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ሰላምን ለማምጣትና የነገ ሀገር ተረካቢ ተማሪዎች ትምህርታቸውን በአግባቡ ተከታትለው ፈተናቸውን እንዲወስዱ መንግሥት፤ ሕዝብና ታጣቂ ሃይሎች በጠረጴዛ ዙሪያ ቁጭ ብለው እንዲነጋገሩ የሁሉም ፍላጎት፡፡
አምና ባጠቃላይ የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ከወሰዱ ተማሪዎች ውስጥ 3 ከመቶ የሚሆኑት ብቻ ነበሩ ፈተናውን ማለፍ የቻሉት፡፡ የዚህ ውጤት አንድምታ ከተለያዩ አንግሎች ሊታይ ይችላል፡፡ በመጀመሪያ ተማሪው በራሱ ለፈተናው በሚፈለገው ልክ እራሱን እንዳላዘጋጀ ያሳያል፡፡ ብዙ ጊዜ ‹‹ሰርገኛ መጣ በርበሬ ቀንጥሱ›› እንደሚባለው አባባል ተማሪዎች በአብዛኛው የፈተና ወቅት ሲቃረብ ብቻ ነው ትምህርታቸውን የሚያጠኑት፡፡ ይህም ጠለቅ ያለ እውቀት ይዘው ለፈተና እንዳይቀርቡ አደርጓቸዋል። የተጠበቀው ውጤትም ሊመጣ አልቻለም፡፡ ወላጆችም ቢሆኑ ልጆቻቸው በትምህርት እንዲበረቱ በሚፈለገው ልክ ድጋፍና ክትትል አድርገዋል ማለት አይቻልም፡፡
ከወላጆች በበለጠ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች አብዛኛውን ጊዜያቸውን የሚያሳልፉባቸው ናቸው፡፡ ተማሪዎችን በእውቀት የሚቀርፁት ደግሞ መምህራን ናቸው፡፡ መምህራን ሁሉም ባይሆኑ በሚፈለገው መጠንና ችሎታ ለተማሪዎቻቸው አስፈላጊውን የትምህርት እውቀት ባለማስጨበጣቸው የሚጠበቀውን ያህል ውጤት ማምጣት አልተቻለም። ለዚህ ታዲያ መምህራን ብቻ ሳይሆኑ ርእሰ መምህራንም ጭምር ሃላፊነቱን ይወስዳሉ፡፡
ከዚህ ባለፈ ትምህርት ቤቶችን የሚቆጣጠሩ ከወረዳ ጀምሮ አስከ ከተማ አስተዳደር ያሉ የትምህርት ፅህፈት ቤቶችም በሚፈለገው ልክ ትምህርትና ትምህርትን ብቻ መሠረት አድርገው ድጋፍን ክትትል ባለማድረጋቸው ሀገር አቀፍ የአስራ ሁለተኛ ክፍል ፈተና ውጤት ደካማ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ የትምህርቱን ዘርፍ የሚመሩና በከፍተኛ የሥልጣን እርከን ላይ የሚገኙ አመራሮችም ለውጤቱ ማነስ በየደረጃው ሃላፊነት አለባቸው፡፡
ከሁሉ በላይ ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ከኩረጃ የፀዳ አዲስ የፈተና አሰጣጥ ሥርዓት በመዘርጋቱ ስንዴውን ከእንክርዳዱ መለየት ተችሏል፡፡ የፈተና አሰጣጥ ሥርዓቱ ጠንካራ በመሆኑ የተማሪዎች የውጤት ደረጃ የት ላይ እንዳለ ለማየት አስችሏል። ውጤቱ ለዘንድሮው ሀገር አቀፍ የአስራ ሁለተኛ ክፍል ተፈታኝ ተማሪዎች፣ ወላጆች፣ መምህራን፣ ርእሰ መምህራን፣ የትምህርት ባለሙያዎችና አመራሮች ትልቅ መልእክት አስተላልፏል፡፡
ስለዚህ ከአምናው ይልቅ የዘንድሮው የአስራ ሁለተኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና በብዙ መልኩ ይጠበቃል፡፡ የአምናውን ውጤት ያዩ ወላጆች ዘንድሮ ትምህርት ወስደው ልጆቻቸውን በመደገፍና በማበረታታት ለፈተና እንዳበቋቸው ይታመናል። በዚህም ከልጆቻቸው ጥሩ ውጤት ይጠብቃሉ። መምህራንም ከአምናው ስህተታቸው ተምረውና በቁጭት ተነሳስተው አመቱን ሙሉ ተማሪዎቻቸውን በሚገባ ሲያበቁ ቆይተዋል፡፡ ስለዚህ እነርሱም የዘሩትን ጥሩ ዘር ማጨድ ይፈልጋሉ፡፡ ርእሰ መምህራንም እንደዛው፡፡
ከወረዳ ጀምሮ እስከ ከፍተኛው የትምህርት ሚኒስቴር ደረጃ ያሉ አመራሮችም ቢሆኑ የአምናው ውጤት በእጅጉ ያስደነገጣቸው በመሆኑ አመቱን ሙሉ ለተማሪዎች ውጤት መሻሻል መፍትሄ ይሆናሉ የተባሉ ርምጃዎችን ሁሉ ሲወስዱ ቆይተዋል፡፡ እነርሱም በተመሳሳይ በዘንድሮው ሀገር አቀፍ የአስራ ሁለተኛ ክፍል ፈተኛ ጥሩ ውጤት እንዲመዘገብ ይፈልጋሉ፡፡ ፈተናው ሀገር አቀፍ ነውና አሁንም ቢሆን በግጭቶች ምክንያት አሁንም ፈተና ላይ ለመቀመጥ እድል ያልገጠማቸው ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች አሉና ግጭቶች ቆመው ሰላም እንዲሰፍንና ተማሪዎች ትምህርታቸውን ተምረውና ተፈትነው ቀጣይ እጣ ፈንታቸውን እንዲወስኑ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ሃላፊነት ነው፡፡
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 8 ቀን 2016 ዓ.ም