ባለፉት ዓመታት የለውጡ መንግሥት ስር የሰደዱ ችግሮችን ለመፍታትና የተረጋጋ ዘላቂ ሰላም ለመፍጠር አልሞ ሲሠራ ቆይቷል፡፡ በተለይ በቀድሞ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ይነሱ የነበሩ በክልልነት እንደራጅ ጥያቄዎች በዴሞክራሲያዊ መንገድ ምላሽ ማግኘታቸው ይታወሳል፡፡ ታዲያ በለውጡ መንግሥት የክልልነት ጥያቄዎችን ምላሽ ካገኙት መካከል የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ተጠቃሽ ነው፡፡ እኛም ከክልልነት አደረጃጀት እና አጠቃላይ ከለውጡ ጋር ተያይዞ በተሠሩ ሥራዎች ዙሪያ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግሥት ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደን እንግዳ አድርገን ይዘንላችሁ ቀርበናል መልካም ንባብ፡
አዲስ ዘመን፡- ከለውጡ በኋላ በአደረጃጀት ጥያቄ በኩል ምላሽ ካገኙ ክልሎች መካከል አንዱ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መሆኑ ይታወቃል፡፡ የክልልነት አደረጃጀት ጥያቄ የተመለሰው በምን መልኩ ነው?
አቶ ጥላሁን፡- ከለውጡ በፊት በቀድሞ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በነበርንበት ጊዜ በእጅጉ በጣም በርካታ ችግሮች ሲስተዋሉ እንደነበር ይታወቃል፡፡ ቀደም ሲል የሕዝብ ጥያቄ የሚመለስበት አግባብና እውነተኛ የሕዝብ ጥያቄዎች ምንጭ ምንድን ናቸው? በማለት የመለየት ተግባር አልነበረም፡፡ ብልጽግና እንደፓርቲ ተዋህዶ ወደ ሥራ ስንገባ በዋናነት የሕዝብ ጥያቄ መነሻዎች ምንድን ናቸው? በማለት ተለይተዋል። ሕዝብ ጥያቄዎቹን በራሱ እንዲመልስ በማድረግ እውነተኛ ዴሞክራሲን ማሳየት አለብን በማለት መድረክ እንዲፈጠር ተደርጓል፡፡
በሁሉም አካባቢ የውይይት መድረኮች ተፈጥረው በመዋቅር ጥያቄ ምክንያት አንድም ሰው መሞት የለበትም የሚለውን ከጫፍ ጫፍ ተግባብተን ወደ ተግባር መግባት ችለናል፡፡ በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት በግጭት፣ እጅ በመጠምዘዝ ሳይሆን ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ጥያቄችን እንዲመለሱ መግባባት ተፈጥሯል፡፡ በተለይም መሠረታዊ የሆኑ የዞንና የወረዳ ጥያቄዎች በጥናት እንዲመለሱ ማድረግ ተችሏል፡፡
ሕገመንግሥታዊ መብታቸውን ተጠቅመው ዞኖች ለብቻቸው በክልልነት እንደራጅ የሚል ጥያቄ ለሚመለከተው አካል አቅርበዋል፡፡ ሠራተኛው ከሥራና ከተለያዩ ተግባራት ሳይነጠል ገዢው ፓርቲ በዴሞክራሲያዊ መንገድ ይመልስልናል በሚል መድረኮች ተፈጥረዋል፡፡ በፓርቲ ደረጃ ሕዝብን በማሳተፍ የክልልነት ጥያቄን ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ልንመልስ ይገባል የሚል ውሳኔ ተወስኖ፤ ከሕዝብ ጋር ውይይት በማድረግ ክልሎችን ማደራጀት ተችሏል፡፡
የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝብ ከጫፍ ጫፍ ለውጡ ሰላማዊ፣ዴሞክራሲያዊና ሕጋዊ በሆነ መልኩ እንዲካሄድና ሀገሪቱ ወደ ሌላ ጦርነት እንዳትገባ በሰከነ ሁኔታ የሕዝብ ጥያቄን የሚመልስ መንግሥትና ፓርቲ እንዲኖር ልባዊ መሻት ነበረው፡፡ ሆኖም የውስጥና የውጭ የጠላት ሃይሎች ለውጡን ለመቀልበስ በከፍተኛ ሁኔታ አቅደው የሕዝብን ስሜት ኮርኳሪ አጀንዳዎችን በመልቀም ለውጡን ለማደናቀፍ ሲሞክሩ መቆየታቸው አይዘነጋም፡፡ ነገር ግን ለውጡን ወደ ኋላ ለመመለስ የተሸረበውን ሴራ አልፈናል፡፡
ለውጡን ለመቀልበስ የመጀመሪያ ትልቁ አጀንዳ ተደርጎ የተወሰደው በአደረጃጀት መልክ የሚነሱ ጥያቄዎች መልካቸውን ወደ ግጭት፣ ሰዎችን ወደ መግደል፣ ዜጎችን ወደ ማፈናቀል፣ ንብረት እንዲወድም ሀገር እንድትጎሳቆል በማድረግ ለውጡን ለማጨናገፍ የተደረገው ሙከራ በጣም በርካታ ዋጋ አስከፍሏል፡፡ ከስሜት ኮርኳሪ አጀንዳዎች መካከል ዋነኛው በክልልነት እንደራጅ ጥያቄ ብቻ ሳይሆን በዞን፣ በወረዳ ደረጃ እንደራጅ የሚሉ ጥያቄዎችም ነበሩ። በለውጡ መንግሥት እምነት ላይ በመመስረት የሕዝብን ጥያቄ በማዳመጥ፣ ቀረብ ብለን መነሻ ጉዳዮችን በሰከነ ሁኔታ ተረድተን፣ ምላሽ በጊዜ መስጠት ስለሚገባን በዋናነት ምላሹ ምን ይሁን? የሚለው ላይ አተኩረናል፡፡ በሚፈልጉት መልኩ ይሁን ወይስ አይሁን የሚለውንም ለመወሰን፤ ከጠያቂው ሕዝብ ጋር መግባባት አለብን በሚል መርህ በፓርቲ ደረጃ ተይዞ በመግባባት ተግባራዊ ተደርጓል፡፡
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሲመሠረት እውነተኛ ዴሞክራሲ የታየበት ትክክለኛ የብልጽግና ቱሩፋት ብለን ተቀብለነዋል፡፡ ክልሉ የፖለቲካ ተሳትፎ ፍትሃዊነትን ለማረጋገጥ በሚያስችል መንገድ ተመሥርቷል፡፡
አዲሱ ክልል በዞን እና በወረዳ ደረጃ እንደራጅ የሚሉ ጥያቄዎችን መመለስ በሚያስችል መልኩ ተደራጅቶ ወደ ሥራ ማስገባት ተችሏል፡፡ የክልልነት ጥያቄ ጫና ሳይደረግ ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ መካሄዱ እንደሀገር ለውጡን የተሳካ አድርጎታል፡፡ እናም ክልሉ የሰላም፣ የብልጽግና እና የመቻቻል ተምሳሌት እንዲሆን ራዕይ ተይዞ ተደራጅቶ የሕዝብን ይሁንታ አግኝቷል፡፡ የክልል አደረጃጀቱ በተጨባጭ እውነተኛ ዴሞክራሲ የታየበት እንዲሆን የተሠራው ሥራ የተሳካ ሆኗል ማለት ይቻላል፡፡
ይህም ሆኖ በሂደቱ በርካታ የውጭና የውስጥ ሃይሎች በተደራጀ መንገድ ሕዝብን ሲቀሰቅሱ ነበር፡፡ ነገር ግን ሕዝብ በነቂስ ወጥቶ ውሳኔ በማድረግ ስኬታማ ጉዞ ማድረግ ተችሏል። በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በዴሞክራሲያዊ መንገድ ሕዝብ በራሱ በነቂስ ወጥቶ የራሱን ክልል፣ ሕገ መንግሥት፣ አርማ፣ ሰንደቅ ዓላማ መርጠው በውሳኔ ተግባራዊ እንዲሆን ተደርጓል። በአጠቃላይ ባለፉት ስድስት ዓመታት ከተሠሩት አንዱና ትልቁ የለውጡ ትሩፋትና ስኬት መካከል ሕዝቡን ባለቤትና አሳታፊ ያደረገ እውነተኛ ዴሞክራሲ የተረጋገጠበት የክልል አደረጃጀት ሥራ ተሠርቷል። በለውጡ እውነተኛ ዴሞክራሲ፣ ሕዝብ የወደደውን የፈቀደውን የተገነዘበውን ሊወስን ይገባል የሚል አቋም ተይዞ ተግባራዊ ተደርጓል፡፡
ከክልል ምስረታ በኋላ ሕዝቡ ያለውን በመስጠት ድጋፉን በተጨባጭ አሳይቷል፡፡ የመረጥኩት የወሰንኩት ክልል ወደ ሥራ ሲገባ መደገፍ አለብኝ በሚል ድጋፍ አድርጓል፡፡ የክልሉ መንግሥት ዜጎች የሰጡትን የቤት ሥራ በመገንዘብ ባለፉት ጊዜ ያልተሰሩትን ሥራዎች በሚያካክስ መልኩ የሕዝብን ጥያቄዎች መመለስ በሚያስችል አግባብ ወደ ተግባር ተገብቷል፡፡
በተለይም የሽግግር ጊዜ እቅድ በማውጣት የክልል ማዕከላትን የማደራጀት፣ የሰው ሃይል ማሰማራት፣ የአሠራር ሥርዓቶችን ለማሳለጥ 54 አዋጆችን ፣ ሕጎችን፣ ደንቦችን መመሪያዎችን ማውጣት ተችሏል፡፡ እንደክልል ሊከናወኑ የሚችሉ የእቅድ ክለሳ በማድረግ በግብርና፣ በቱሪዝም፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በማዕድን በሥራ እድል ፈጠራ ቁልፍ ተግባራትን በመለየት ወደ ተግባር ተገብቷል፡፡
አዲስ ዘመን፡- እንደ ሀገር በምግብ ራስን ለመቻል ሰፋፊ ኢኒሼቲቮች ተቀርጸው በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛል፡፡ በተለይም በግብርና፣ በሌማት ትሩፋት እንደክልል ያለው እንቅስቃሴ እንዴት ይገለጻል?
አቶ ጥላሁን፡- እንደመንግሥት የልማት እቅድ ተይዞ ወደ ተግባር ሲገባ ኢትዮጵያን የአፍሪካ የብልጽግና ተምሳሌት ማድረግ አለብን የሚል ራዕይ ተይዟል፡፡ በእኛ ክልልም የሰባት ዓመት ፍኖተ ብልጽግና ሊያረጋግጡ የሚችሉ ተግባራት ተለይተው ወደ ሥራ ተገብቷል፡፡ በዋናነት በግብርና ዘርፍ የቤተሰብ ብልጽግናን በማረጋገጥ ክልሉን የብልጽግና ተምሳሌት ለማድረግ እየተሠራ ነው። ጸጋዎችን የመለየትና እንደሀገር የተለዩ የአረንጓዴ ዐሻራ፣ የበጋ ስንዴ፣ የሌማት ትሩፋት ኢኒሼቲቮችን ተግባራዊ እየተደረጉ ይገኛል፡፡
በአረንጓዴ ዐሻራ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ‹‹ኢትዮጵያን አረንጓዴ እናልብሳት›› ብለው በጀመሩት ንቅናቄ መሠረት ተግባራዊ እየተደረገ ነው፡፡ ችግኞችን መትከል ብቻ ሳይሆን የተተከሉትን የመንከባከብ ሥራ ይሠራል። የሚተከሉት ችግኞች ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው የደን ዛፎች፣ ፍራፍሬዎች፣ ቀርከሀ፣ የእንስሳት መኖና የመሳሰሉት ናቸው፡፡
ትልቁ የክልሉ ፈተና ለሥራ አጥ ወጣቶች ሥራ ማግኘት ነው፡፡ ስለዚህ አረንጓዴ ዐሻራን ከሥራ እድል ፈጠራ ጋር በማቀናጀት ችግሩን ለማቃለል የሚያስችል ሥራ እየተሠራ ነው፡፡ በመሆኑም በአረንጓዴ ዐሻራ ተራራዎችን በማልማት፣ የለሙትን ተራሮች ወጣቶችን በንብ ማነብ፣ በከብት ማርባት፣ በቱሪዝም ዘርፍ በማቀናጀት ማሰማራት ይቻላል፡፡
ምርትና ምርታማነትን የማሳደግ፣ የሥራ እድል የመፍጠር፣ የአየር ንብረትን የመቀየር፣ የከርሰ ምድር ውሃን አቅም በመጨመር ረገድ የአረንጓዴ ዐሻራ ሥራ ወሳኝ ነው፡፡ ለእዚህም በተቀናጀ መንገድ የችግኝ ዝግጅት፣ የመንከባከብ፣ የመትከያ ቦታ የማዘጋጀትና የተተከሉትን የመጠበቅ ሥራ በብቃት እንዲመራ እየተሠራ ነው፡፡
በክልሉ በበልግ እና በመኸር በሁለት ዙር የችግኝ ተከላ ይካሄዳል፡፡ በበልግ ለአብነት ቡና፣ አግሮ ፎረስተሪ ችግኞች የሚተከሉ ሲሆን፤ በመኸር በደን ልማት ላይ ያተኮሩ ችግኞች ይተከላሉ፡፡ በስንዴ ልማት በኩል ምርትና ምርታማነት በማሳደግ ከውጭ የሚገባው የስንዴ ምርት በማቆም ወደ ውጭ መላክ አለብን የሚል ውሳኔ ተወስኖ በአጭር ጊዜ ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ ታሪክ ተመዝግቧል፡፡
ስንዴ በዓመት አንዴ ብቻ ይመረት ነበር፡፡ በዓመት ሁለት እና ሦስት ጊዜ ማምረት የሚያስችል ሀገር እንደሆነ ማሳየት ተችሏል፡፡ የማምረትና የመሥራት ባህልን በመቀየር ስንዴን በየትኛውም ቦታ ላይ ማምረት እንደሚቻል ታይቷል፡፡
ከውጭ የሚገባን ስንዴ በማስቆም ወደ ውጭ ስንዴን መላክ ተጀምሯል፡፡ እንደሀገር እቅማችን ከፍ ያለ መሆኑንና የጋራ ስኬት መሆኑን ያሳየንበት ነው፡፡ በክልሉም በዚህ ልክ በጋ ላይ በመስኖ ለምቶ የማያውቅ ስንዴ ማልማት ጀምረናል። እንደ ክልል የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ምርታማነትን ማሳደግ የሚያስችሉ ሥራዎች እየተሠሩ ናቸው፡፡ በግብርናው ዘርፍ ምርትና ምርታማነት ማሳደግ ለምርጫ የሚቀርብ ጉዳይ አይደለም፡፡
ከአርሶ አደር ማሠልጠኛ ጀምሮ እስከ ክልል ባለው መዋቅር በመናበብ የግብርና ማነቆዎችን በመፍታት በተለያዩ ሰብሎች ላይ ምርት የማሳደግ ሥራ ተሠርቷል፡፡ በተለይም ቦቆሎ፣ ስንዴ፣ ማሽላ እና የጤፍ ሰብሎች ላይ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስችል የግብዓት ፣ የኬሚካል፣ ማዳበሪያ፣ የዘር አቅርቦት ላይ ተሠርቷል፡፡
እንደ ክልል ሁሉንም የአርሶ አደር ማሳ በዘር የመሸፈን ሥራ የተሠራ ሲሆን፤ የሰብል ጥበቃ፣ የተባይ፣ የአረም፣ የማዳበሪያ አጠቃቀምና የግንዛቤ አቅም እየተሻሻለ መጥቷል፡፡ ለድጋፍ እና ለክትትትል በሚመች መልኩ በኩታ ገጠም ሰፋፊ እርሻዎች ምርት ማምረት ተጀምሯል።
በሌማት ትሩፋ እንደሀገር የተጀመረው በእኛ ክልል አርባ ምንጭ ከተማ ነው፡፡ በመሆኑም የሌማት ትሩፋት የአንድ ዓመት ተኩል ጉዞን በቅርቡ ገምግመናል፡፡ በርካታ ስኬቶችን ያስመዘገብን ሲሆን፤ በክልላችን በእጅጉ የተሳካ መሆኑን አረጋግጠናል፡፡ በተለይ የወተት፣ የንብ፣ የዶሮ፣ የስጋ መንደሮች ተፈጥረዋል፡፡ የተበታተነ የእንስሳት ምርት ከማምረት ለገበያም፣ ለግብዓት አቅርቦትም በሚመች መልኩ ሰብሰብ ብለው በአባወራ ደረጃ የሚያመርቱበት ሂደት ተፈጥሯል፡፡
የሌማት ትሩፋት ለአርሶ አደርና ለከተማ ነዋሪ ብቻ ሳይሆን ከሥራ እድል ፈጠራ አኳያ በጣም በርካታ ወጣቶች ተሰማርተዋል፡፡ በተለይም እንደክልል እንቁላል፣ ዶሮ፣ ሥጋ ከማቅረብ አኳያ በጣም በከፍተኛ ሁኔታ አመርቂ ውጤት እየተመዘገበ ነው፡፡ የሌማት ትሩፋት ልዩ ትኩረት ከተሰጠው በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ማርሽ ቀያሪ ተግባር ነው። በዋናነት የግብዓት አቅርቦት፣ መኖ፣ የመሠረተ ልማት፣ የፋይናንስ፣ የገበያ ትስስር፣ የመሥሪያ ቦታዎች ችግሮች አሉ። በየከተሞቻችን የገበያ ትስስር፣ ማምረቻ ቦታ፣ የመኖ፣ የጤና ችግር ለመቅረፍ ከግሉ ባለሀብት ጋር በቅንጅት እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ካደረግን በጣም በአጭር ጊዜ ውስጥ የተቀመጠውን ግብ አሳክቶ ሀገራዊ የብልጽግና ተምሳሌት ራዕይ ማሳካት የሚያስችል መንገድ ላይ እንዳለን አመላካች ነው፡፡
በክልሉ በሚገኙ በሁሉም ከተሞች ላይ የእንቁላል ዋጋ በተሻለ ሁኔታ እየቀረበ ይገኛል፡፡ የኑሮ ውድነትንና የዋጋ ግሽበትን ለማረጋጋት እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች ተጨባጭ ለውጥ እያመጡ ይገኛሉ፡፡ ሌላው የደቡብ ኢትዮጵያ ትልቁ አቅም ፍራፍሬ ልማት ነው፡፡ ማምረት ለገበያ ማቅረብ ብቻ ሳይሆን ተጨማሪ እሴት ጨምረን ለገበያ ማቅረብ አለብን የሚል እሳቤ ይዘናል፡፡ በሙዝ፣ በማንጎ፣ አቦካዶ፣ አፕል፣ ብርቱካን እና ሎሚ በሁሉም አካባቢዎች ላይ በምርምር የተረጋገጠ ምርት ለማቅረብ እየተሠራ ነው፡፡
ደቡብ ኢትዮጵያ የፍራፍሬ ቋት ነው፡፡ አርሶ አደሩ ብቻ ሳይሆን የግሉ ባለሀብት በለውጡ መንግሥት በብላቴን ተፋሰስ ወደ ልማት እንዲገቡ ተደርጓል፡፡ ቡናና ቅመማ ቅመም በተደራጀ መንገድ እንዲለማ በማቀድ በምርምር የተረጋገጡ ሥራዎች እየተሠሩ ናቸው፡፡ በሥራ ስር እንሰት፣ ጎደሬ፣ ስኳር ድንች ማምረት ለምግብ ዋስትና የቤተሰብ ብጽግናን ለማረጋገጥ ወሳኝ በመሆናቸው፤ እንሰትን የማስፋት የመጠበቅ የመንከባከብ ሥራ በልዩ ሁኔታ ለመምራት የተጀመረው ዘመቻ ውጤት እያመጣ ነው፡፡ ሥራ ሥር የአፈር ለምነትን ለመጠበቅ፣ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ወሳኝ ነው፡፡
ክልሉ በልዩ ሁኔታ የእንሰት፣ የፍራፍሬ፣ የአሳ ኢኒሼቲቮች ላይ እየሠራ ነው፡፡ በተለይም አሳን በአባያ፣ ጫሞ፣ ኦሞ የተፈጥሮ ሀይቆች ላይ ከፍተኛ የሆነ አሳ ምርት እየተመረተ ነው፡፡ በሰው ሰራሽ ሀይቅ ግድቦች ጊቤ ሦስት ከፍተኛ የሆነ የአሳ ምርት ያለበት ነው፡፡ አሳን በሀይቆችና ግድቦች ማምረት ብቻ ሳይሆን በገንዳዎችና በኩሬዎች በግለሰብ ደረጃ ማምረት በሚያስችል መልኩ አቀናጅተን እየሠራን ነው፡፡ አሳ በክላስተር ተቀናጅቶ በመሥራት ክልሉን የብልጽግና ተምሳሌ ለማድረግ
እየተሠራ ነው፡፡ በአጠቃላይ በግብርና ዘርፍ እጅግ በጣፍ ከፍተኛ ውጤቶች እየተመዘገቡ ይገኛሉ፡፡
አዲስ ዘመን፡- አምራች ኢንዱስትሪዎችን ወደ ሥራ ከማስገባትና የሥራ እድል በመፍጠር፣ የግብርና ምርቶች ላይ እሴት በመጨመር ወደ ገበያ በማቅረብ በኩል የተሠሩ ሥራዎች ምንድን ናቸው?
አቶ ጥላሁን፡- አምራች ኢንዱስትሪውን የማስፋፋት የነበሩትን መሠረታዊ ማነቆዎች የመፍታትና የማበረታታት ተግባር በልዩ ሁኔታ እየተመራ ነው፡፡ በተለይም የግብርና ምርት ባለባቸው አካባቢዎች ምርትን የማቀነባበር፣ ተጨማሪ እሴትን የመጨመር በርካታ የኢንቨስትመንት ጥያቄዎች ቀርበዋል፡፡ በፍራፍሬ እንስሳት ተዋጽኦ ተጨማሪ እሴት ጨምሮ አሽጎ ለማዕከላዊ ገበያ ማቅረብ ለሚችሉ ባለሀብቶች ፍቃድ ተሰጥቷል፡፡
በዲላ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ የአቦካዶን ምርትን ወደ ዘይት በመቀየር ፣ በይጋጨፌ ቡናን ቆልቶ በማሸግ ለማቅረብ ወደ ሥራ ገብተዋል፤ እንዲሁም በሥጋ ምርት የተሰማሩ ባለሀብቶችም ወደ ሥራ ገብተዋል፡፡ በመካከለኛና አነስተኛ ኢንዱስትሪ የምግብ ማቀነባበር፣ የወተት፣ የውሃ ማሸጊያ ፍቃድ አግኝተው ወደ ሥራ የገቡ አሉ፡፡ በአዲስ መልክና ነባር ሆነው ማነቆዎች አጋጥመዋቸው ወደ ሥራ ሳይገቡ የቆዩትን ችግሮች በመፍታት በወላይታ ሶዶ፣ አርባምንጭ፣ ዲላ ከተሞች ወደ ማምረት ሂደት ውስጥ እንዲገቡ ተደርጓል፡፡
በኢትዮጵያ ታምርት የንቅናቄ መድረክ 750 በመካከለኛና አነስተኛ አምራች ኢንዱስትሪዎች የመሥሪያ ቦታ የግብዓት፣ የገበያ ችግሮቻቸውን የመፍታት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ በጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪ ከእደ ጥበብ ጀምሮ በማዘመን ወደ ውጪ እስከመላክ የደረሱ ባለሀብቶች ተፈጥረዋል። በተለይም የአርባምንጭ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ጭምር ልብስ እያመረተ ይገኛል። በተጨማሪም በጨርቃጨርቅ ስምንት ከፍተኛና ሰባት መካከለኛ ባለሀብቶች ወደ ሥራ የገቡ ሲሆን፤ የድንጋይ ከሰል ተመርቶ ለሲሚንቶ ፋብሪካዎች እየቀረበ ነው፡፡
በማዕድን ዘርፍ ለጌጣጌጥነት፣ ለግንባታ የሚያገለግሉ የግራናይት ሀብቶች አሉ፡፡ አምራች ኢንዱስትሪውን ከማዕድን ጋር በማገናኘት የተለያዩ ባለሀብቶች እንዲሳተፉ ማስተዋወቅ፣ ሕጎችን የማስተካከል ሥራ እየተሠራ ነው፡፡ በተለይም የአምራች ኢንዱስትሪውን የፋይናንስ ችግሮች ለመፍታት ከልማት ባንክ ጋር እየተሠራ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- በአምራቾች የሚነሱ የመሠረተ ልማት ጥያቄዎች በምን መልኩ እየተመለሱ ናቸው?
አቶ ጥላሁን፡- በክልላችን የግብርና ምርቶችን ወደ ገበያ ለማቅረብ በሚደረገው ጥረት የመሠረተ ልማት ችግር አለ፡፡ የሁሉም አርሶ አደሮችና ባለሀብቶች መሠረታዊ ጥያቄ ከሚያመርቱበት ማሳ እስከ ገበያ ለማድረሰ የሚያስችል መሠረተ ልማት በሚፈለገው ደረጃ የለም የሚል ነው። ከአርባምንጭ ደልበና፣ ከደልበና ጂንካ ያለው መንገድ ተበላሽቷል፡፡ መንገዱን የፌዴራል መንገዶች ባለሥልጣን ለማሠራት በእቅድ ይዞ እየተቀሳቀሰ ነው፡፡ ከቀይ አፈር እስከ ቱርሚ ድረስ ያለው መንገድም አልተሠራም፡፡ ስለዚህ በፌዴራል የሚሠሩ የመንገድ ሥራዎችን ልዩ ትኩረት እንዲሰጣቸው እየተነጋገርን ነው።
የኦሞ ኩራዝ ስኳር አምስት ፍብሪካዎች ከ250 ሺህ ሄክታር በላይ ለሸንኮራ አገዳ ማሳ ተሰጥቶ እያለሙ ይገኛሉ። ከአምስት ፋብሪካዎች ሦስቱ ቁጥር አንድ ፣ ሁለት እና ሶስት ምርት እየሰጡ ናቸው፡፡ ባለቤትነቱ የኢትዮ ስኳር ግሩፕ የሆነው የኦሞ ኩራዝ ስኳር ፋብሪካ በሙሉ አቅሙ እያመረተ አይደልም፡፡ በሙሉ አቅሙ የማያመርትበት ዋነኛ ምክንያት የመሠረተ ልማት ችግር ነው፡፡
እንደሀገር ከፍተኛ የስኳር ፍጆታ ፍላጎት ያለ በመሆኑ፤ የፌዴራል መንግሥት ችግሩን ለመቅረፍ አቅዶ እየሠራ ነው። በክልሉ የተቀናጀ የመሠረተ ልማት የሚያስፈልግ በመሆኑ በተለይም የግብርና ምርት በስፋት በሚገኝባቸው አካባቢዎች ላይ ለማሟላት ከልማት ባንክ፣ ከፌዴራል መንግሥት እና ከግብርና ሚኒስቴር ጋር እየሠራን ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- በክልሉ በማህበራዊ ዘርፎች ላይ ያሉ እንቅስቃሴዎች ምን ይመስላሉ?
አቶ ጥላሁን፡- እንደሀገር የትምህርት ስብራት ላይ እንደመሆኑ መጠን፤ በክልል ደረጃም የትምህርት ስብራትና የውጤት መበላሸትን፣ የትምህርት ጥራትና የተደራሽነት ችግር፣ የትምህርት ቤቶች ደረጃቸውን አለመጠበቅ፣ የግብዓት ችግር፣ የተማሪና መምህራን ጥምረት አለመመጣጠን ችግሮች አሉ፡፡ በመንግሥት አቅም የሚፈቱትን ከፍተኛ ወጪ በማድረግና ሕዝብን በማስተባበር ችግሩን መቀየር እንደሚያስፈልግ አቋም ተይዞ ወደ ተግባር ተገብቷል፡፡ በራስ አቅም ስብራቶችን ለመቅረፍ የሚያስችሉ ንቅናቄዎች በክልል ደረጃ ተጀምረዋል። በዋናነት ጥራት ያለው የትምህርት ተደራሽነት ላይ እየተሠራ ነው፡፡ ዜጎች በቂና የተሟላ ትምህርት እንዲያገኙ ከመዋለ ህጻናት ጀምሮ በልዩ የማስፋት፣ መምህራንን የማብቃት፣ ግብዓት የማቅረብ፣ ሥራ ማህበረሰብ በማሳተፍ ትምህርት ቤቶች የማስፋፋት ሥራ እየተሠራ ነው፡፡
በሁሉም አካባቢዎች ላይ መዋዕለ ህጻናትን ማስፋፋት ብቻ ሳይሆን፤ አዳሪ ትምህርት ቤቶች ላይ በተሠራው ሥራ ውጤት ማምጣት ተችሏል፡፡ ከለውጡ ወዲህ ጥሩ ውጤት ለማምጣት የሚያስችል በወላይታ ሊቃና በአርባምንጭ ጋሞ በማስተማር ዙሪያ ሰፊ ሥራ ተሠርቷል፡፡
ማህበረሰቡን በማስተባበር በስድስት ዞኖች ላይ ሞዴል ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት እየተሠራ ነው። በአሁኑ ጊዜ በዲላና ጎፋ ላይ የአዳሪ ትምህርት ቤቶች የግንባታ ሂደት ተጀምሮ እየተሠራ ይገኛል፡፡
የአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ከ1ኛ እስከ 8ኛ ክፍል መጽሐፍቶችን በክልሉ መንግሥት የሚቀርቡ በመሆናቸው ለተማሪዎች ተደራሽ ለማድረግ የህትመት ጨረታ ተዘጋጅቷል፤ ለዚህም 2 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ይጠይቃል፡፡ ችግሩን ለማቃለል የአንድ ተማሪ መጽሐፍ በአንድ ቤተሰብ በሚል ንቅናቄ የተጀመረ በመሆኑ፤ በመጪው ክረምት መጽሀፍትን ተደራሽ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡
በትምህርት ዘርፍ የሚታየውን ስብራት ለማከምና ለመጠገን የሚያስችሉ ሥራዎች እየተሠሩ ናቸው፡፡ በክረምቱ መማሪያ ክፍሎችን የመጠገን፣ የትምህርት ግብዓት የማቅረብና አዳዲስ ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሠራ ነው፡፡ ብልጽግናን ማረጋገጥ የሚቻለው ጤናማና አምራች ዜጋ ሲኖር ነው ፡፡ ስለዚህ በጤናው ዘርፍ የጤና ኬላዎችን ደረጃ ከፍ የማድረግ፣ የባለሙያዎችን ብቃት አቅም ማሳደግ፣ በሽታን መከላከል፣ የማህበረሰብ አቅምን የመገንባት፣ የጤና መድህን ሽፋን ማሳደግ ተግባር በልዩ ሁኔታ እየተመራ ነው፡፡
የጤና ጣቢያዎችንና የሆስፒታሎችን ግንባታና ማስፋፊያ፣ ግብዓትና ባለሙያዎችን የማሟላት ተግባራት እየተሠራ ሲሆን፤ በሁሉም የክልሉ ከተሞች ላይ 18 የማህበረሰብ መድኃኒት መሸጫዎች ተገንብተው ወደ ሥራ ገብተዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ የጤና መድህን ሽፋንም በጥሩ ሁኔታ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ በሚያደርግ መልኩ ተግባራዊ እየተደረጉ ነው፡፡
በክልሉ የሚስተዋሉትን የወባ፣ ኩፍኝ፣ ኮሌራ ወረርሽኞች የመከላከልና የመቆጣጠር አቅምን የማሳደግ ተግባር እየተከናወነ ይገኛል፡፡ ወረርሽኞች ሲከሰቱ ሰብዓዊ ቀውስ ሳያስከትሉ መከላከል የህብረተሰቡ ቋሚ ተግባር መሆን እንዳለበት የማስገንዘብ ሥራ እየተሠራ ነው፡፡ እስካሁን እንደ ክልል ስጋት ላይ የጣለንና የከፋ ችግር የተፈጠረበት አግባብ የለም፡፡
በአጠቃላይ በሥራ እድል ፈጠራ ዙሪያ ከአካባቢው ለሥራ ፍለጋ የሚወጡ ወጣቶች እንዲሄዱ የሚያደርጉ ገፊና እንዲወጡ የሚያደርጉ በሌሎች አካባቢዎች ያሉ ሳቢ ጉዳዮችን እዚሁ እንዲያገኙ በልዩ ሁኔታ እየተሠራ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- የዜጎችን ሰላምና ጸጥታ ለማስጠበቅ በደቡብ ኢትዮጵያ እየተሠሩ ያሉ የሰላምና የጸጥታ እንቅስቃሴዎች ምን ይመስላሉ?
አቶ ጥላሁን፡- የመጀመሪያውና ቁልፉ ሥራ ሰላምና ጸጥታን ማስከበር በመሆኑ የጸጥታውን መዋቅር ሪፎርም በማድረግ ሰላምን ማስከበር የሚያስችል የአሠራር ሥርዓት ተዘርግቷል፡፡ ለውጡን እንደ ሀገር ለማደናቀፍ የፈለጉ ሃይሎች በየአካባቢው ስሜት ኮርኳሪ ጥያቄዎችን በማንሳት ሕዝብን ከሕዝብ ለማጋጨት አቅደው በጣም በርካታ ሙከራዎችን አድርገዋል፡፡ ብሔርን ከብሔር፣ ሃይማኖትን ከሃይማኖት ጋር፣ በሌሎችም ውስን ምክንያቶች ዜጎችን በማጋጨት ያልተረጋጋና ሰላም ያልሰፈነበት ክልል እንዲሆን ብዙ ሙከራዎች ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡
ነገር ግን ሀገር በቀል እውቀቶችና ልማዶች ለውጡን ለማጽናትና የተጀመረውን የብልጽግና ራዕይ እውን ለማድረግ ያላቸው ሚና ከፍተኛ በመሆኑ እንዳቀዱት አልሆነላቸውም፡፡ በተለይም የሰላምና ጸጥታ ሁኔታዎችን ለማጽናት ሀገር በቀል የግጭት አፈታት ሥርዓቶችን ተግባራዊ ማድረግ ተችሏል፡፡
የሕዝብን ደህንነት፣ ሰላም ከማስፈን አኳያ በየአካባቢው ያሉ ሀገር በቀል ልማዶች፣ ሥርዓቶችን እውቅና በመስጠት ለመጠቀም የሚያስችል አካሄድ ተጀምሯል፡፡ እንደ ሀገር ከለውጡ ወዲህ ሰላምን ለማጽናት የጋሞ አባቶች ሚና ከፍተኛ በመሆኑ ለሀገርም የሰላም አምባሳደር መሆን የቻሉበትን እውቅና አስገኝቷል፡፡
ክልሉ በግጭት አፈታት ሂደት ሀገር በቀል የማህበረሰብ እውቀት፣ ሥርዓት፣ ባህል፣ እሴት ያሉበት ነው፡፡ በጌዲዮ፣ በአሪ ዞን፣ ወላይታን ጨምሮ በሁሉም አካባቢዎች ላይ የክልሉን ሰላምና ጸጥታ ለማስከበር በሚደረገው ጥረት ሀገር በቀል እውቀቶችና ሥርዓቶች ከፍተኛ ሚና እየተጫወቱ ነው። አባቶች ከወጣቶች ጋር የሚናበቡበት ሥርዓት፤ ጠንካራ ሆነው ከሚስተዋሉባቸው አካባቢዎች አንዱ በመሆኑም ሀገር በቀል እውቀት በክልሉ ያለውን ሰላምና ጸጥታ ለማስከበር አቅም ሆኗል፡፡
ባህላዊ የግጭት አፈታት ሥርዓቶች የጸጥታና የፍትህ ሥርዓቱ ላይ ጫና እንዳይኖር ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡ ከለውጡ ወዲህ ሀገራዊ ችግርን ሀገር በቀል መፍትሄዎች ሊሰጥባቸው ይገባል የሚል አቅጣጫ ተቀምጦ ሲሠራ ቆይቷል፡፡ ክልላዊና አካባቢያዊ ችግሮችን በዘለቄታው ለመፍታት ባህላዊ ግጭት መፍቻ ሥርዓቶችን መጠቀም፣ እውቅና መስጠት ተቀዳሚ ተግባር በማድረግ ተሠርቷል ማለት ይቻላል፡፡
አዲስ ዘመን፡ – እንደሀገር ከተሞችን ለነዋሪዎች ምቹ ለማድረግ የኮሪደር ሥራዎች እየተሰሩ ነው፡፡ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምን እየተሠራ ነው?
አቶ ጥላሁን ፡- ትልቁ እንደሀገር የመጣው ለውጥ ከተሞቻችን የብልጽግና ተምሳሌት መሆን አለባቸው፣ ለነዋሪዎቻቸው ምቹ ለኢንቨስትመንት ማራኪ፣ ጽዱ ከተሞች ማድረግ የሚል ነው፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ከቤተ መንግሥት የተጀመሩት የገበታ ለሸገር፣ ለሀገር፣ ለትውልድና ከተሞችን ለመቀየር ደግሞ የኮሪደር ልማት ምን ያክል ውጤታማ እንደሆነ በአዲስ አበባ ላይ ታይቷል፡፡ ልማቱ አዲስ አበባ ላይ ብቻ የሚቀር ሳይሆን በሁሉም አካባቢ ሊሰፋ ስለሚገባ በደቡብ ክልል በወላይታ ሶዶ፣ አርባምንጭና ዲላ ከተሞች ላይ የኮርደር ልማት፣ አረንጓዴ ፓርኮች፣ ቤተመጽህፍትና መዝናኛ ቦታዎች በተቀናጀ መልኩ እየተሠራባቸው ነው፡፡
ከተሞቻችን የብልጽግና ተምሳሌት በመሆን ለኢንቨስትመንት፣ ለነዋሪዎች ምቹ አረንጓዴ፣ ጽዱ መሆን አለባቸው፡፡ በከተሞች የሚስተዋሉ የቤት አቅርቦት፣ የቆሻሻ አወጋገድ፣ ውሃ፣ መብራት የአቅርቦት ችግሮችን ለመፍታት የተጀመሩ ሥራዎች ተስፋ ሰጪ ናቸው፡፡ በአሁኑ ጊዜ በወላይታ ሶዶ፣ አርባ ምንጭና ዲላ ከተሞች ላይ ቀደም ሲል ቆሻሻ ሲጣልባቸው፣ ለመቆም አጸያፊ የነበሩ ቦታዎች ጸድተው መቀመጫ ተዘጋጅቶላቸው ማራኪ ቦታዎች ሆነዋል፡፡ ልማቱ የሥራ እድል ፈጠራም እየሆነ ሲሆን፤ ሕዝቡን በማስተባበር ሥራውን ማስፋት ያስፈልጋል፡፡
የተሟላ ዘመናዊ የመንገድ ዳር ሽንት ቤቶችን ባለሀብቶች በማስተባበር ለመገንባት እንቅስቃሴ ተጀምሯል። በቀጣይ ዓመት የኮሪደር ልማቱን በሳውላ፣ ካራትና ጂንካ ከተሞች ላይ የማስፋፋት ሥራ ይሠራል፡፡ ከተሞቻችን ጽዱ፣ አረንጓዴ፣ ለነዋሪዎች ምቹ የሆኑና የብልጽግና ተምሳሌት ለማድረግ እቅድ ተይዞ እየተሠራ ይገኛል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ጠቅላይ ሚኒስትሩ ካስጀመሯቸው ተግባራት አንዱ የአቅመ ደካሞችን ቤት ማደስ ማዕድ ማጋራት አንዱ ነው፡፡ በመሆኑም እንደ ክልል በክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት ምን ያህል ታቅዶ እየተሠራ ነው?
አቶ ጥላሁን፡- የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በብሔራዊ ደረጃ ሲታወጅ ሀገራዊ ችግርን በሀገራዊ አቅም መፍትሔ ለመስጠት ነው፡፡ አንዳችን ለአንዳችን መድኃኒት በመሆናችን የለውጡ ትልቁ ትሩፋት በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተጀመሩና እንደሀገር የታወጀው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት አንዱ ነው፡፡
በአሁኑ ጊዜ የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት የቤት ጥገና፣ አረጋውያንን መንከባከብ፣ ደጋፊ ጧሪ የሌላቸው ወገኖችን መጠየቅ፣ ደም ልገሳ ሥራዎች ባህል ሆነዋል፡፡ በለውጡ መንግሥት አዲስ የመደጋገፍና የመረዳዳት ባህል ተተክሏል፡፡ በዚህም ሰው ሲሞት የሚያዝነውን ማህበረሰብ ሰው በቁሙ ሲቸገር እንዲያዝንና እንዲረዳ እየተቀየረ በመሆኑ አሁን ቤት ገንብቶ ለአቅመ ደካሞች የሚያስረክብ ባለሀብት እየተፈጠረ ነው፡፡
እንደክልል በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በባለፈው ዓመት በጌዲኦ ዞን በአንድ ጀምበር ብቻ 605 ቤቶች ተገንብተዋል፡፡ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች ተሳትፈውበታል፡፡ ዘንድሮም በጎነት ለኢትዮጵያ ከፍታ በሚል መሪ ሃሳብ የአቅመ ደካሞችን ቤቶች መገንባ፣ መጠገንን ጨምሮ ቁሳቁስ ማሟላት፣ የዘማች ቤተሰብ እንክብካቤ፣ የሥራ እድል በመፍጠር የተሟላ ድጋፍ ለማድረግ በስድስቱም የክልል ከተሞች ላይ ተጀምሯል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ችግሮችን በምክክር ለመቅረፍ የምክክር ኮሚሽን ተቋቁሞ እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል፡፡ በክልል ደረጃ ምክክሩ ውጤታማ እንዲሆን ምን እየሠራችሁ ነው?
አቶ ጥላሁን፡- የለውጡ መንግሥት አንዱና መሠረታዊ መለያው ዜጎች የመሰላቸውን ጥያቄ ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ማንሳትና መናገር እንዲችሉና ጥያቄዎች በውይይትና በመተማመን ሊፈቱ ይገባል የሚል አቋም ይዞ መሥራቱ ነው።
የነጠላ ትርክትና የሚያለያዩ፣ ሚዛን የማይደፉ ጉዳዮች እርስ በእርስ እንድንባላ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆናቸውን ተመልክተናል፡፡ ገዢ ትርክትና ወንድማማችነት ለኢትዮጵያ ወሳኝ ነው፡፡ ከሚለያዩን እርስ በእርስ ከሚያናቁረን፣ ከሚያጣሉን ጉዳዮች መካከል በቀላሉ መፍታት የምንችላቸው አሉ፡፡ ጉዳዮችን በሰከነ ሁኔታ ቁጭ ብለን መነጋገር ብንችል መልካም ነው፡፡ ለእዚህም ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ተቋቁሞ እንደሀገር የሚያለያዩን ጉዳዮችን ቁጭ ብለን መክረን ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓትን በተከተለ መልኩ ልንፈታቸው እንችላለን፡፡ የሚያለያዩ ጉዳዮችን በጦርነትና በጠመንጃ መፍታት ኋላ ቀርነት ነው፡፡ የሠለጠነ የዘመነ ሰው ችግርን ሊፈታ የሚችለው ቁጭ ብሎ ሃሳብ በማንሸራሸር ነው።
እንነጋገር እንመካከር እንወያይ ችግሮቻችንን መፍታት የምንችለው ተወያይተን ነው፡፡ ለእዚህም ብሔራዊ የምክክር ኮሚሽን ተቋቁሞ ወደ ሥራ ገብቷል፡፡ እንደክልል ሰዎች ነጻ ሆነውን እንዲወያዩና እንዲመካከሩ ለኮሚሽኑ ሁኔታዎችን እያመቻቸን ነው፡፡ መንግሥት ምክክሩ ወደ ተግባር እንዲገባ ምቹ ሁኔታን እየፈጠረ በመሆኑ ኢትዮጵያውያን በሠለጠነ መንገድ ተመካክረን፣ ተነጋግረን ችግሮቻችንን መፍታት አለብን፡፡ ችግራችንን በራሳችን ለመፍታት የሄድንበት አግባብ ትልቅ ታሪክ ነው፡፡ ይህ እንዲሳካና ግቡን እንዲመታ እንደ ደቡብ ኢትዮጵያ መንግሥት የሚጠበቅብንን እገዛ እናደርጋለን፡፡
በአጠቃላይ ኢትዮጵያ በለውጥ ጉዞ ውስጥ ናት፡፡ ብልጽግና ፓርቲ ፈተናን ወደ በለጠ አቅምና እድል በመቀየር ኢትዮጵያን አንበረክካለሁ የሚል ሃይል እንደማይሳካለት በተጨባጭ አሳይቷል፡፡ ይህ ከጊዜ ወደ ጊዜ ስኬቶችን እያስመዘገብን የመጣንበት ምስጢር ፓርቲው በትክክለኛው መንገድ ላይ ከሕዝባችን ጋር ተቀናጅቶ በመሥራቱ ነው፡፡ ትፈርሳለች የተባለችው ሀገር ከራሷ አልፋ ለምሥራቅ አፍሪካ ወሳኝ መሆኑዋን እያረጋገጠች ያለች ሀገር ናት፡፡
በኢትዮጵያ ታሪክ በችግሮች ውስጥ ሆኖ ትላልቅ ስኬት ያስመዘገበ ፓርቲ ቢኖር ብልጽግና ነው፡፡ እንደፓርቲ ታይቶ የማይታወቁ ድሎችን አስመዝግበናል፡፡ የገባነውን ቃል እየፈፀምን በስኬት ጎዳ ላይ መሆኑን መሬት ላይ ያለው እውነታ የሚያሳይ ሲሆን፤ በቀጣይም የተሻለ በመሥራት በአጭር ጊዜ ብልጽግና እንድናረጋገጥ ማድረግ የሚቻለውን አስተዋጽኦ እናበረክታለን፡፡
አዲስ ዘመን፡- ለሰጡን ሰፊ ማብራሪያ ከልብ አድርገን እናመሰግናለን፡፡
አቶ ጥላሁን፡-እኔም ለነበረን ቆይታ በእጅጉ አመሰግናለሁ፡፡
ማርቆስ በላይ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 8 ቀን 2016 ዓ.ም