ክላስተር እርሻ – አዋጩ የግብርና መንገድ

በዚህ ዓመት ከ24 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት ለማረስ እቅድ መያዙንና ይህንን እቅድ ለማሳካት ከዝናቡ ጋር መሸቀዳደም ቀዳሚ ተግባር መሆን አለበት ሲሉ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሰሞኑን በማኅበራዊ ትስስር ገፃቸው መግለጻቸው ይታወሳል፡፡ የዘንድሮውን የክረምት እርሻ እቅድ ለማሳካት ሰፊ እንቅስቃሴ መጀመሩንና ይህም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ ከጊዜ ወደ ጊዜ ኩታ ገጠም እርሻ እየተስፋፋ መሆኑንም ጠቅሰው፣ እርሻውን ኩታ ገጠም ማድረግ ብቻ ሳይሆን ዘመናዊ መንገድ መከተል እንደሚገባም አስታውቀዋል፡፡ ይህም በምግብ ራስን ለመቻል የሚደረገውን ጥረት ለማሳካት እንደሚያስችል አስታውቀዋል፡፡

ኩታ ገጠም እርሻ እየተስፋፋ መሆኑንና ይህን ተከትሎ ለውጦች እየተመዘገቡ ስለመሆናቸው የዘርፉ ባለሙያዎችም አረጋግጠዋል፡፡ ኩታ ገጠም እርሻ ለሀገሪቱ ወሳኝ መሆኑን በመጥቀስም ይበልጥ ሊሠራበት እንደሚገባም አመልክተዋል፡፡

አቶ ኢሳያስ ለማ በግብርና ሚኒስቴር የሰብል ልማት ዘርፍ ሥራ አስፈፃሚ ናቸው፡፡ ኩታ ገጠም እርሻ ሲባል ማሳቸው ወይም ድምበር የሚዋሰኑ አርሶአደሮች መሬታቸውን በማጣመር በአንድ ላይ የሚያርሱበት ሥርዓት መሆኑን ይገልጻሉ፤ በእንግሊዘኛው ‘cluster Farming’ የሚለውን ቃል ለመተካት ሲባል የሚውል ነው›› በማለትም ያብራራሉ፡፡ በኢትዮጵያ ኩታ ገጠም እርሻ በተለያዩ ጊዜ ተሞክሮ እንደነበር አስታውሰው፤ በአርሶአደሩ ዘንድ ከመሬት ጋር በተያያዘ በነበረው ምልከታና በአግባቡ ካለመመራቱ ጋር ተያይዞ ውጤታማ የሚባል እንዳልነበር ያመለክታሉ፡፡

ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ ግን አርሶአደሩን በማሳመንና ከግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር በሙከራ /በፓይለት/ ደረጃ የክላስተር እርሻ (ኩታ ገጠም) መጀመሩን ጠቅሰው፣ መንግሥትም ልዩ ትኩረት ሰጥቶት እየተሠራ መሆኑን በዚህም በአጭር ጊዜ ውስጥ ውጤት ለማየት መቻሉን ያስረዳሉ፡፡

እሳቸው እንዳሉት፤ የዚህ መርሐ ግብር ዋና ዓላማ በአርሶአደሩ ዘንድ በገዛ ምርቱ የመወሰን፣ በገበያም የመደራደር አቅም እንዲሁም ደግሞ በጋራ ሠርቶ መኖርን፤ ተባብሮ የማደግ እሴቶችን ሊያጎለብት የሚችልበትን አሠራር መፍጠር ነው፡፡ በሌላ በኩል አንድ አርሶአደር ብቻውን ሆኖ ዘር ወይም ትራክተር አልያም ሌሎች ግብዓቶችን ቢጠይቅ ለእሱ ብቻ ድጋፍ ለማድረግ አዳጋች ነው፣ ጨርሶ ላያገኝበት የሚችልበት ዕድልም አለ፤ ሆኖም በጋራ ሆኖ ሲጠይቅ መንግሥትም ሆነ ባለሀብቱ ለአሠራር ቀላልና አዋጭ ስለሚሆንላቸው አፋጣኝ ምላሽ መስጠት የሚችሉበትን ሁኔታ መፍጠር ያስችላል፡፡

አበው ‘ድር ቢያብር አንበሳ ያስር’ እንደሚሉት ሁሉ ኩታ ገጠም ወይም የክላስተር እርሻ እንደሀገር አርሶአደሮቹ መሬታቸውን በአንድ ላይ በማጣመር፣ ተመሳሳይና አዋጭ ያሉትን አዝርዕት በመዝራትና በጋራ በመንከባከብ መሥራት የሚችሉበት ዕድል ተፈጥሯል። ሞዴልና ጠንካራው አርሶአደር ደካማውን እየደገፋና እያበረታ በተሻለ ሁኔታ ምርታማ መሆን ጀምረዋል፡፡

‹‹አርሶአደሮቹ ከእቅድ ጀምሮ እስከ ሽያጭ ድረስ በጋራ የሚያቅዱበትን ገበያን ያካተተ ወይም ገበያ መር የግብርና ሥርዓት እንዲከተሉ በማድረግ ረገድ ያመጣው ለውጥ እንደተጠበቀ ሆኖ ጊዜ፤ ሀብትና ጉልበትን በመቆጠብ የክላስተር እርሻ መጀመሩ ከፍተኛ አስተዋፅዖ እያበረከተ ነው›› ሲሉም አቶ ኢሳያስ ይጠቅሳሉ፡፡

‹‹ኩታ ገጠም ሲጀመር በተወሰኑ ቦታዎችና ሰብሎች ላይ ነበር፤ አሁን ግን ክልሎችም በራሳቸው እያሰፉ በመምጣታቸው ከፍተኛ እምርታ እየተመዘገበ ነው›› ሲሉም ይገልፃሉ፡፡ አብነት አድርገውም በየክልሉ ለምግብ ዋስትና፣ ለኤክስፖርትና ለኢንዱስትሪ ጠቀሜታ ያላቸውን የተለያዩ ሰብሎችን እንደየአካባቢው ነባራዊና ምቹ ሁኔታ ተለይቶ በክላስተር ማረስ መጀመሩን ይጠቅሳሉ፡፡ አንዳንድ ክልሎችም የየራሳቸውን የምርጥ ዘር አቅርቦት እስከማሟላት የደረሱበት ሁኔታ እንዳለም ያስረዳሉ፡፡ በክላስተር የማረሱ ባሕል ገና በጅምር ደረጃ የሚታይ እንደሆነና እያንዳንዱ ክላስተር ኢንተርፕራይዝ ሆኖ ራሱን ችሎ እንዲቆም በማድረግ ረገድ በርካታ የቤት ሥራዎች እንደሚጠብቁም ነው ሥራ አስፈፃሚው የተናገሩት፡፡

በኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት የአግሪካልቸር ኮሜርሻላይዜሽን ክላስተር ዳይሬክተር ዳኛቸው ሉሌ (ዶ/ር) እንዳስረዱት፤ ከ80 በላይ የሚሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሕይወቱ በግብርና ላይ የተመሠረተ ነው፤ የሀገሪቱም የኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት ግብርና እንደመሆኑ የግብርና ሥርዓቱን ማዘመን አጠያያቂ ጉዳይ አይደለም፡፡ በተለይ ደግሞ አብዛኛው አርሶአደር በተበጣጠሰ መሬት ላይ የሚያርስ እንደመሆኑና በቤተሰብ ደረጃ ያለው የመሬት ይዞታም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ በመምጣቱ የክላስተር እርሻ መከተል በብዙ መልኩ አዋጭ ነው፡፡

‹‹የመሬት ይዞታ የሚቀንስ እንዲሁም በሌላ በኩል የሕዝብ ብዛት የሚጨምር ከሆነ ያለው አማራጭ በሄክታር የሚገኘውን ምርታማነት መጨመር ነው፤ ለዚህ ደግሞ በተበጣጣሰ መልኩ የሚደረገውን የእርሻ ሥርዓት አቀናጅቶ መምራት ይገባል›› ሲሉም ያብራራሉ፡፡ በተለይ አብዛኛው የሃገሪቱ ሕዝብ የኑሮ መሠረት ግብርና መሆኑን ጠቅሰው፣ ከእጅ ወደአፍ የሆነውን የአርሶአደሩን ሕይወት መቀየር የሚያስችል ሥርዓት መፍጠር ይገባል ይላሉ፡፡ ‹‹ከዚህ በኋላ ግብርናችን ከእጅ ወደ አፍ ከመሆን አልፎ ለትርፍ ማምረት የሚችል አርሶአደር ማፍራት ግድ ይላል›› ሲሉም አስታውቀዋል፡፡

እሳቸው እንዳስታወቁት፤ የክላስተር እርሻ በተስፋፋባቸው አንዳንድ ቦታዎች ላይ ሞዴል አርሶአደሮች በጣም ብዙ ምርት የሚያገኙበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ግን ደግሞ ቁጥሩ ቀላል የማይባለው አርሶአደር አሁንም በተበጣጠሰው መሬቱ ላይ ምንም አይነት የቴክኖሎጂ ድጋፍ ሳያገኝ የሚያርስ በመሆኑ የሚያገኘውም ምርት አነስተኛ ነው፡፡ እንደ ሀገርም ሲታይ በየትኛውም የግብርና ምርት ማግኘት የሚገባውን ያህል ምርት እየተገኘ አይደለም፡፡

‹‹አንዳንድ በክላስተር የተጀመሩ የአቦካዶ ክላስተሮች አሁን ወደ አውሮፓ ወደ ስፔንና ወደ ሌሎች ሃገሮች ኤክስፖርት ማድረግ ጀምረዋል፤ እንደሃገር ያለውን ምርታማነት በአማካኝ ስናየው ግን የሚፈለገውን ያህል አይደለም›› በማለት ዳኛቸው (ዶ/ር) ይገልፃሉ።

ዳኛቸው (ዶ/ር) በቆሎን አብነት አድርገውም ሲያብራሩም ‹‹በቆሎ በሄክታር 90ና ከዚያ በላይ ኩንታልን የሚያገኝ ሞዴል ገበሬ አለ፤ እንደሃገር ደግሞ የማዕከላዊ ስታስቲክስ አገልግሎት ያስቀመጠው 42 ኩንታል ነው›› ይላሉ፡፡ አሁን እንደሃገር ትርፍ አምራች የምንለው ገበሬ ከሚያመርተው ውስጥ በግሉ ተጠቅሞ ለገበያ የሚያቀርበው በጣም ትንሽ መሆኑን ጠቅሰው፣ አሁን እየተመረተ ያለው ምርት በተለይ ከተማ አካባቢ እየጨመረ ያለውን የሕዝብ ብዛት ሊመግብ አይችልም፡፡ በመሆኑም አሁን ባለው ሁኔታ የሃገሪቱ መሬት ይዞታ አኳያ ክላስተር እርሻ መሥራት ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡

እንደ እሳቸው ገለጻ፤ ሀገሪቱ እምቅ የተፈጥሮ ሃብት አላት፣ አየሩም ሆነ መሬቱ ለእርሻ ሥራ ምቹ ነው፤ የሚሠራ ሰፊ የሰው ኃይልም አለ፤ እነዚህን በመጠቀም ምርታማነትን ማሳደግና የአርሶአደሩንና የሃገርንም ተጠቃሚነት ማሳደግ ይገባል፡፡

በተለይ የክላስተር እርሻው መስፋፋቱ የግብርና ኤክስቴንሽን ሥርዓቱን በማሳለጥ፣ አርሶአደሮች አግባብነት ያለው ግብዓት ተጠቅመው እንዲያመርቱ፤ ያመረቱትንም ከገበያ ጋር ለማስተሳሰር ያግዛል፡፡ እንደአጠቃላይ ግብርናውን እንደቢዝነስ ተጠቅሞ ኩባንያ ለመፍጠር የሚያስችል አርሶአደር ሊኖር የሚችለው የክላስተር እርሻ ሲስፋፋ እንደሆነ ነው ሲሉ ዶክተር ዳኛቸው ያስረዳሉ፡፡

‹‹ግብርና ለሃገር ውስጥ ዓመታዊ እድገት 33 በመቶ፣ ለወጭ ንግድ 76 በመቶ አስተዋፅዖ ያበረከታል፤ ለሃገሪቱ ሰፊ የሥራ እድል በመፍጠር ግንባር ቀደሙ ነው›› ብሎ መናገር ብቻ ሳይሆን በተግባር መሬት ላይ ከዚህ የተሻለ አስተዋፅዖ እንዲያበረክት ማድረግ ይገባል›› ይላሉ፡፡

ዓለም የደረሰችበትን ዘመናዊ የሆነ ግብርና ማማተር ይገባል፤ እንደከዚህ ቀደሙ በበሬና ገበሬ ወይም በሞፈር ብቻ የሚሠራ ሳይሆን በሜካናይዜሽን ቴክኖሎጂ ወይም ደግሞ ዲጂታላዜሽን መንገድ የሚመራ ግብርና መፍጠር ይገባል፡፡ በተጨማሪም ቤት ቁጭ ብሎ መረጃ አግኝቶ ሊሠራ የሚችል ትውልድና አርሶአደር ማፍራት ይጠበቃል። ለዚህ ደግሞ የክላስተር ሥርዓቱ በተለይ አሁን ባለው የኢትዮጵያ ሁኔታ አማራጭ የለውም፤ ወቅታዊ ነው፡፡

ዳኛቸው (ዶ/ር) ‹‹አሁንም ቢሆን እየተከናወነ ያለው ሥራ በጅምር የሚጠቀስ ነው፤ ግብዓት አቅርቦት ላይ አሁንም ክፍተት አለ፤ መሬትና ዝናብ ስላለ ብቻ ምርታማነትን መጨመር አንችልም፣ በተለይ ማዳበሪያና ዘርን በአግባቡ መጠቀም ወሳኝ ነው›› ይላሉ፡፡ በጊዜው መዝራት፣ ማረምና ክትትል ማድረግና በሽታን መከላከሉ እንዳለ ሆኖ ግብዓትና ጊዜው የሚጠይቀውን ቴክኖሎጂ መጠቀም ግድ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡

አሁን ባለው ሁኔታ በክላስተር የተደራጀው አርሶአደር በአግባቡ መጠቀም ያለበትን ዘር ተጠቅሞ እያረሰ አለመሆኑን ጠቅሰውም፤ ‹‹የምርምር ተቋማት የተለያዩ ዝርያዎችን ቢያወጡም አርሶአደሩ ግን በሚገባ እየተጠቀመ አይደለም፡፡ በርካታ የተሻሻሉ ዝርያዎች ቢወጡም አርሶአደር ሲጠቀምና ሲለወጥበት አይታይም›› ሲሉም ጠቁመዋል፡፡

ለአርሶአደሩ የሚሰጠውም የማማከር አገልግሎት በዚሁ ልክ መሻሻል እንደሚገባውም ያስገነዝባሉ፡፡ ዘርና ሌሎች ግብዓቶች እጥረትን ለመፍታት ደግሞ የግሉን ዘርፍ ማሳተፍ እንደሚገባ አመልክተው፣ ‹‹በዘርፉ ያለውን ሁሉንም ችግር ለመፍታት በመንግሥት አቅም የሚቻል ባለመሆኑ የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ወሳኝ ነው›› ሲሉም ነው የገለፁት፡፡

በሌላ በኩል ትክክለኛ የግብርና ትራንስፎርሜሽን እንዲመጣ ከተፈለገ እንደሃገር ያለውን የገበያ ሥርዓት ማዘመን እንደሚገባ ይናገራሉ፡፡ በተለይም በደላሎችና በሕገወጥ ተዋናዮች የገበያ ሰንሰለቱ የተያዘ መሆኑን ተናግረው፣ አሠራሩን ዲጂታላይዝድ በማድረግ ቁጥጥርና ክትትሉን ማሻሻል፣ እንደ መንገድ ያሉ መሠረተ ልማቶችን ማስፋፋት እንደሚገባም ያመለክታሉ፡፡ ‹‹በተለይ የአርሶአደሩን አመለካከት በመቀየር ምርታማነትን የሚጨምሩለትን ግብዓቶች እንዲጠቀም፤ እርሻውን በመካናይዜሽን እንዲመራ ማድረግ ላይ መሥራት ያስፈልጋል›› ይላሉ፡፡

እሳቸው እንዳሉት፤ ከዚህም ባሻገር የፋይናንስ ተቋማትም ለአርሶአደሩ አሁን የሚያደረጉትን አነስተኛ ድጋፍ በከፍተኛ ደረጃ ሊያሳድጉ ይገባል፡፡ ‹‹ዛሬ በክላስተር ያለው ገበሬ ነገ ኩባንያ መክፈት እንዲችልም የብድር አገልግሎትን ማሻሻል ይገባል›› በማለት ይገልፃሉ።

እንደአጠቃላይ ግብርናውን ማዘመን አሁን ያለው ትውልድም ወደ ዘርፉ እንዲሳብ ያስችላል ባይም ናቸው። ‹‹ይህንን ማድረግ ስንችል የበለጠ አመለካከቱ የተቀየረ ማኅበረሰብ እንፈጥራለን፡፡ አርሶ አደሮችም ወደኋላ የማይመለስ ደረጃ እንዲደርሱ ያደርጋል፡፡ የግብርና አስተዳደራቸው ሥልጡንና ከዘመኑ ጋር የዘመነ እንዲሆን በር ይከፍታል፤ ከዚህ በመነሳትም ሌላ ቢዝነስ መሥራት የሚችል አርሶአደር መፍጠር እንደሚቻልም ያስገነዝባሉ።

ይህ መሆን ሲችል ልክ እንደ ስንዴና ቢራ ገብስ ሁሉ ከውጭ በከፍተኛ ምንዛሪ ይመጡ የነበሩ ሰብሎችን በማስቀረት በራስ አቅም በማምረት ምንዛሪውን መታደግ፤ አግሮ ኢንዱሰትሪውን ማጠናከርና ሃገርንም ማበልፀግ ይቻላል፡፡ በተለይ ደግሞ ሰፊውን የወጣት ኃይል የሥራ እድል ተጠቃሚ ማድረግ ያስችላል፡፡

አቶ ኢሳያስ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ የክላስተር እርሻ ከተጀመረ በጣት የሚቆጠሩ ዓመታት ብቻ ነው ያሳለፈው፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ ስርነቀል የሆነ ለውጥ ይመጣል ተብሎ አይታሰብም፡፡ ይሁንና መንግሥት ኃላፊነቱን ወስዶ፣ መዋዕለንዋይ መድቦና ያለውን አቅም ተጠቅሞ የክላስተር እርሻ በጀመረባቸው ቦታዎች የሚበረታታ ውጤት ተገኝቷል፤ ሥራው ይህንን ማስፋትን ይጠይቃል፡፡

በተለይ አርሶአደሩ በተበጣጣሰ መሬት ላይ የሚሠራ መሆኑ የግብርና ዘርፉ የሚገባውን ያህል ምርታማ እንዳይሆን አድርጎት ቆይቷል ያሉት አቶ ኢሳያስ፣ ‹‹አሁንም ቢሆን አንድ አርሶ አደር ባለው 0 ነጥብ 5 ሄክታር መሬት ላይ የሚደረገው ሥራ ለውጥ አያመጣም›› ብለዋል፡፡

አርሶ አደሮች መሬታቸውን አጣምረው በጋራ ቢሠሩ ግብዓትን ከመጠቀም ጀምሮ እስከ ገበያው ድረስ የመደራደር አቅማቸው እንደሚጠናከር ጠቅሰው፣ በሁለተኛ ደረጃ ሃገሪቱም ተመሳሳይ የሆነና ጥራቱን የጠበቀ ምርት ከአንድ ቦታ ለማግኘት ያስችላታል ብለዋል።

እሳቸው እንዳሉት ይህ መሆኑ ለአግሮ ኢንዱስትሪው ማደግም ለውጭ ንግዱ መሳለጥ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል። ይሁንና የተናጠል እርሻው ሥራ የሚቀጥል ከሆነ 18 ሚሊዮን የሚደርሰውን አርሶአደር በምንም መልኩ መደገፍ አዳጋች ነው፡፡ በመሆኑም ሃገሪቱ የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ አልፎ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለመፍጠር እያደረገች ላለችው ሁለንተናዊ ጥረት የክላስተር እርሻ ወሳኝ ሚና ያለው በመሆኑ የኩታ ገጠም እርሻን የተገኘውን ምርጥ ተሞክሮ በመጠቀም በሁሉም ክልሎች ማስፋፋት ይገባል፡፡

መረጃዎች እንዳመለከቱት ፤በሀገሪቱ በኩታ ገጠም እርሻ የሚሳተፉ አርሶ አደሮች ብዛት በየዓመቱ እየጨመረ መጥቶ ስምንት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ደርሷል፡፡

ማሕሌት አብዱል

አዲስ ዘመን ሰኞ ሐምሌ 8 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You