ሕገ ወጥ ፍልሰትን መከላከልና መቆጣጠር በተግባር

የሰው ልጆች ምድር ላይ መኖር ከጀመሩበት ጊዜ ጀምሮ ስደት አብሯቸው የኖረ ክስተት ነው። ሰዎች በተፈጥሮም ሆነ በሰው ሰራሽ አስገዳጅ ምክንያቶች አልያም በፍላጎት ከተወለዱበት ወይም ከሚኖሩበትን አካባቢ ወይም ሀገር ለቀው ድንበር አቋርጠው ወደ ሌሎች አካባቢዎች ወይም ሀገራት ይሰደዳሉ፡፡

በተለይ በሕጋዊ መንገድ ወደ ሌሎች ሀገሮች የሚፈልሱ ዜጎች በራሳቸው ፍቃድ ከሀገር የሚወጡና የሚሄዱበትን ሀገር ሕጋዊ ፍቃድ ያገኙ በመሆኑ ያን ያህል አስከፊ ጉዳት ሲያጋጥማቸው አይስተዋልም። በሕጋዊ መንገድ የሚሄዱት ደህንነታቸው ተጠብቆና መብታቸው ተከብሮ በሚሠሩት ሥራ የራሳቸውና የቤተሰቦቻቸውን ኑሮ ከማሳደግ አልፎ ለሀገርም ያላቸው ጠቀሜታም ከፍተኛ ነው፡፡ ደህንነቱ በተጠበቀ መንገድን መሄድ እያለ ሕገወጥና ደህንነቱ ያልጠበቀ መንገድን መምረጥ በአንፃሩ ትሩፋቱ ጥቃት፣ ስቃይ እና ሞት ነው፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሕገ ወጥ ፍልሰት መንስኤ ከሆኑ ምክንያቶች መካከል ጦርነት፣ የኢኮኖሚ ቀውስ፣ ድህነት፤ ሥራ አጥነት ፣ የሕገወጥ ደላሎች ቅስቀሳ፣ የቤተሰብና የጓደኛ ግፊት፣ ጥቂት ተሳክቶላቸውና ገንዘብ ይዘው የተመለሱ ሰዎችን እንደ ምሳሌ ማየት በምሳሌነት የሚጠቀሱ ናቸው።

ወጣቶችን ለሕገ ፍልሰትን ከሚገፋፉ ምክንያቶች መካከልም የግንዛቤ ማነስ፣ የሀገር ውስጥ የሥራ አማራጮችን ያለማየት፣ ሥራን ማማረጥ፣ ኑሮን ማሻሻል የሚቻለው በስደት ብቻ ነው ብሎ ማመን፣ ስራ አጥነትና ድህነት፣ ጎልተው ይጠቀሳሉ።

ሕገ ወጥ ፍልሰት የአንድ ሀገር ብሎም አሕጉር ችግር አይደለም፡፡ በሁሉም የዓለማችን ክፍል የሚታይ ነው፡፡ ይሁንና በታዳጊ አገሮች በተለይ ደግሞ ከሳሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራት ችግሩ ገዝፎ ይታያል። ኢትዮጵያም በሕገ ወጥ ፍልሰት እጅጉን ከሚፈተኑና ከሚሠቃዩ ሀገራት አንዷ ናት፡፡

በሐገሪቱ የሕገ ወጥ ፍልሰት መነሻ የሚባሉት አካባቢዎች ሞያሌ፣ አሳሶ፣ መተማ፣ አፋርና ድሬዳዋ ሲሆኑ መድረሻቸው ደግሞ ሰላም ያልሰፈነባቸው ለራሳቸው ዜጎችም ቢሆን ለመኖር አስቸጋሪ የሆኑት ደቡብ አፍሪካ፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ ሊቢያ፣ ሱዳንና የመን መሆናቸውን ጥናቶች ያመለክታሉ።

ሕገ ወጥ ፍልሰትን ምርጫ ያደረጉ በርካታ ኢትዮጵያውያም ተስፋ ያሳደሩበትን ያህል ሕይወታቸውን ሊለውጥ የሚችል ገንዘብ ሊያገኙ ቀርቶ፤ ላልተጠበቀ አደጋ እየተጋለጡ ወደ ማይወጡት ማህበራዊ ቀውስ ሲገቡ ማየት እጅጉን የተለመደ አሳዛኝ ትእይንት ነው፡፡ እንደዚህ ዓይነቱ የ“አተርፍ ባይ አጉዳይ” ክፉ እጣ የሚገጥማቸውን ኢትዮጵያውያን ቤት ይቁጠራቸው ሲሉ የዓይን ምስክርነት የሚሰጡ ወገኖች ጥቂቶች አይደሉም፡፡

በሀገሪቱ የፀረ – ሕገ ወጥ ፍልሰት ዘመቻ ዘግይቶ በመጀመሩም በተለያዩ ዓለማት ላይ በሚገኙ ዜጎች ላይ አሰቃቂ የግድያና የሞት አደጋ እንዲደርስ ምክንያት ሆኗል። በተለይም ሴቶች ላይ በሕጋዊነት ጥያቄዎችና በጸጥታ ችግሮች ምክንያት ድብደባ፣ ስድብና አስገድዶ መደፈር፣ ከፎቅ መገፍተር፣ የጉልበት ብዝበዛ፣ እንዲሁም የሞት አደጋ ደርሷል፡፡

ከችግሩ አሳሳቢነት አንፃር ኢትዮጵያ ሕገ ወጥ ፍልሰት ለመከላከልና ለመቆጣጠር አጠቃላይ ድንጋጌ አስተላልፋለች። የመከላከልና ቁጥጥር ሥራውንም በጠንካራ ሕግ አስደግፋለች፡፡ በሀገር አቀፍ ደረጃም ሕገ ወጥ ፍልሰትና የሰዎች ዝውውርን ለመከላከልና የተጎጂዎችን ሠብዓዊ መብት ለማስከበር፣ መደበኛ ያልሆነ ፍልሰት የወንጀል ድርጊት መሆኑንና አስከፊነቱን ለህብረተሰቡ ለማስገንዘብ፣ የሕገ ወጥ ሰዎች ዝውውር ተጎጂዎችና የስደት ተመላሾች ማህበራዊና ሥነ-ልቦናዊ ድጋፍ በመስጠት ረገድ የተለያዩ ተቋማትን ባቀፈ መልኩ ዘርፈ ብዙ ተግባራት በመከናወን ላይ ናቸው፡፡

በሀገር አቀፍ ደረጃ የተደራጀው ግብረ ሃይልም በሀገራቸውም ሆነ ወደ ውጭ ሀገር በሕጋዊ ተንቀሳቅሰው መሥራት የሚፈልጉ ዜጎችን በቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች በማስገባት በተለያዩ የሥራ መስኮች የአጭር ጊዜ ሥልጠና መስጠት እንዲሁም ከሥልጠናው በኋላ በሠለጠኑበት ሙያ በሀገር ውስጥ በመደራጀት ወደ ሥራ መሰማራት የሚፈልጉ ዜጎችን ከሥራ ጋር ለማስተሳሰር ዘርፈ ብዙ ጥረት እያደረገ ይገኛል።

ከዚህ በተጨማሪም ተጎጂዎችን ለመደገፍና መልሶ ለማቋቋም፣ የመሥሪያና የመሸጫ ቦታ አቅርቦት ለሚፈልጉ ዜጎች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት አገልግሎቱን እንዲያገኙ ማድረግ፣ ለሥልጠና እና መሰል ሥራዎች ድጋፍ የሚውል ሀብት ማስገኛ ፕሮጀክቶችን ማዘጋጀትና ሀብት የማፈላለግ ተግባራት ገቢራዊ ሆነዋል።

ከዚህ ጎን ለጎንም የሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር መነሻ፣ መተላለፊያና መዳረሻ ቦታዎችን በመለየት በዚህ ትውልድን ለአደጋ በሚዳርግ ተግባር የተሠማሩ ደላሎች ላይ የሕግ ማስከበር ሥራዎች አልተቋረጡም፡፡ በሀገሪቱ የሚገኙ የውጭ ሀገር የግል ሥራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች ላይ ክትትልና ቁጥጥር በማድረግም በአመዛኙ ሕግን መሠረት አድርገው እንዲንቀሳቀሱ ማድረግም ተችሏል።

የሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ተራማጆችን የሚመለምሉና የሚያዘዋውሩ ደላላዎችን፣ ተባባሪና ቤት አከራዮችን እንዲሁም አጓጓዦችን መረጃ ማሰባሰብና በመለየት በሕግ ተጠያቂ የሚሆኑበትን አሠራር ተግባራዊ በመደረግ ላይ ይገኛል፡፡ በዚህም ለሕገወጥ የሰዎች ዝውውር መባባስ ዋነኛ መንስኤው የሆኑትንና ቁጥራቸው እንደአሸን ፈልቶ የነበረው የሕገወጥ አዘዋዋሪዎችና ኤጀንሲዎችን ቁጥር በእጅጉ መቀነስ ተችሏል።

በርካቶችም መንግሥት ባመቻቸው ሁኔታ በሀገራቸው ውስጥ ሠርተው ማደግና መለወጥ ብቻ ሳይሆን፣ ሀብት ማፍራትና ጥሪት መቋጠር እንዲሁም ራሳቸውንና ሀገራቸውና ለሌሎች ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚቻል በማስመስከር ላይ ናቸው።

በተለይ የለውጡ መንግሥት ወደ ሥልጣን ከመጣ ወዲህ ችግሩን ለመከላከል ከላይ በጠቀስናቸው መልኩ ዘርፈ ብዙ ጥረቶች እየተደረጉ ውጤቶችንም መመልከት እየተቻለ ነው፡፡ ሕገ ወጥ ፍልሰትን ከመከላከልና ከመቆጣጠር ባሻገር በተለይ ለዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ በቀውስ ሰለባ ሆነው በተለያዩ ሀገራት የሚገኙ ዜጎችን ወደ ትውልድ ሀገራቸው መመለስ ሥራ እየተሠራም ይገኛል፡፡

የመኖሪያ ፈቃድና ሰነድ የሌላቸው ኢትዮጵያውያንን ወደ ሀገራቸው ለመመለስ ብሔራዊ ኮሚቴ ተቋቁሞ ወደ ሥራ ከገባ ወዲህ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ወደ ሀገራቸው የመመለስ ሥራ ተሰርቷል፡፡ እየተሠራም ይገኛል፡፡ እየተከናወነ በሚገኘው ዜጎችን ወደ ሀገር የመመለስ ሥራም ለአብነት በዚህ ዓመት ከጥቅምት ወር ወዲህ ብቻ ከሳዑዲ ዓረቢያ፣ ከሱዳን፣ ከየመንና ኦማን 105 ሺህ 602 ዜጎች ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል፡፡ ከሚያዚያ 04 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ እስካሁን ከ58 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያንን መመለስ ተችሏል።

መንግሥት እየተከተለ ባለው ዜጋ ተኮር ፖሊሲው አማካኝነት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ በነበረችበት ጊዜ እንኳን መደበኛ ባልሆነ ፍልሰት ወደ ተለያዩ ሀገራት ሄደው ለችግር የተጋለጡ ዜጎችን ወደ ሀገራቸው የመመለስ ሥራዎችን በስፋት ሲያከናውን መቆየቱም የሚታወስ ነው፡፡ የመኖሪያ ፈቃድና ሰነድ የሌላቸውን ኢትዮጵያውያንን ወደ ሀገራቸው የመመለስ ተግባር መንግሥት ለዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ የሰጠውን ልዩ ትኩረት እንደሚያሳይም የሚያከራክር አይደለም፡፡

በመንግሥት በኩል ችግሩን ለመከላከልና ከመቆጣጠር የሚደረጉ ጥረቶች እንደተጠበቁ ሆነው፣ አሁንም በሀገር ውስጥ ሰርቶ ማደግና መለወጥ የሚቻልበት መንገድ እያለ ሕገ ወጥ ፍልሰትና ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን እንደ አማራጭ የሚወስዱ ዜጎች መኖራቸው የሚታበይ አይደለም።

የሕገ ወጥ ሰዎች አዘዋዋሪዎቹ ብዛትና ዓይነት፣ የመረቡ ውስብስብነት፣ የቤተሰብ ገፋፊነትን ጨምሮ በተለያዩ ምክንያቶች የሕገ ወጥ ጉዞው ቀውስ አሁንም በበቂ ሁኔታ ተፈትቷል ለማለት አያስደፍርም፡፡ በሕገ ወጥ ደላሎችና አፈ ቅቤዎች ተታልለው በተሳሳተ ቅስቀሳ ሰለባ ሆነው ውጪውን እንዲያማትሩ የተገደዱ ዜጎችም ዛሬም ድረስ በርካታ ናቸው።

ይህ እንደመሆኑም አሁንም ዜጎችን ከሕገ ወጥ ፍልሰትና ጉዞ አስተሳሰብ፣ ከሄዱም በኋላ ከስቃይ ታዳጎ ለመመለስ፣ በዜጎች የሚነግዱትንም በመታገልና ፍትህ ፊት ቀርበው ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ ለማድረግ ይበልጥ መትጋን የግድ ይላል፡፡

ይህ ትጋት በአንድ ወገን ሩጫ ብቻ የሚፈለገውን ለውጥ ያመጣል ብሎ ማሰብም አላዋቂነት ነው፡፡ መሰል ተግባራትን ይበልጥ ውጤታማ በሆነ መልኩ ለማስፈፀም፣ የተለያዩ አጋር አካላትን ቅንጅትና የጋራ ርብርብን የግድ ይላል፡፡ የሕገ ወጥ ፍልሰት ዋነኛ ምንጩ ከታወቀና አስከፊ ውጤቱ በተግባር ከታየ ለዘላቂ መፍትሄ መረባረብ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ኃላፊነት መሆን አለበት።

በዚህ ረገድ ከቀናት በፊት የተሰማው ዜና በተለይም የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የፍልሰት ተመላሾችን መልሶ ማቋቋምና የቴክኒክ ድጋፍ መስጠት በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ በጋራ ለመሥራት ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችና ከተቋማት ጋር በጋራ መሥራት የሚያስችለውን ስምምነት መፈራረሙም እጅጉን አስደሳችና ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡

በተለይም ጥምረቱን የፈጠሩት፣ የኢንፎርሜሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣ የፕላንና ልማት ሚኒስቴር፣ የትምህርት ሚኒስቴር፣ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር፣ ጤና ሚኒስቴር፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የኢንፎርሜሽንና መረብ ደህንነት አስተዳደር፣ የፌደራል ፖሊስ ኮምሽን፣ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎትና የስደተኞችና ተመላሽ አገልግሎት የመሳሰሉ ወሳኝ ተቋማት መሆናቸው ሕገ ወጥ ፍልሰት ስደትን ለመከላከልን ለመቆጣጠር የሚደረጉ ጥረቶችን ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ እጅጉን ወሳኝ ስለመሆኑም ሊሰመርበት ይገባል፡፡

በአጠቃላይ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሕገ ወጥ ፍልሰትና የሰዎች ዝውውርን ለመግታት የሚደረጉ ጥረቶች ይበልጥ ውጤታማ መሆን እንዲችሉ ከመሰል ቅንጅታዊ ሥራዎች ባሻገር የሕገ ወጥ ፍልሰት አስከፊነት በቤተሰብ፣ በማህበረሰብና በሀገር ላይ የሚያስከትለውን ጉዳት ማስተማርና ወጣቶች በሀገራቸው ሠርተው መለወጥ እንዲችሉ ቀጣይነት ያላቸው የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን መሥራትም ይገባል። ሕግን በአግባቡ የማስከበር ርምጃዎች ባሻገር በተለይ ከትንሽ ነገር ተነስተው ለስኬት የበቁ ጠንካራ ወጣቶችን ምሳሌ ማድረግም ያስፈልጋል፡፡

የሕገ ወጥ ፍልሰትና ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን ለማስቀረት በየደረጃው ያሉ የህብረተሰብ ክፍሎች ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ሊወጡም ይገባል። ዜጎች ሕገ ወጥ ደላሎችን ተከታትሎ በማጋለጥ ሕግ ፊት እንዲቀርቡ የማድረግ ግዴታም አለባቸው።

የመኖሪያ ፈቃድና ሰነድ የሌላቸውን ኢትዮጵያውያንን ወደ ሀገራቸው የመመለስ ተግባር ቀጣይ ማድረግ እንደተጠበቀ ሆኖ ወደ ሀገር ውስጥ ከመጡ በኋላም ተደራጅተው ሥራ መፍጠር የሚችሉበትን መንገድ ማሳየት ብሎም የሥራ እድል ተጠቃሚ ማድረግም ይገባል፡፡ ሕጋዊ ጉዳዮችን ይበልጥ ማጠንከርና የሕገ ወጥ ፍልሰትን ለመከላከል በሕጋዊ ፍቃድ የተደራጁ ነገር ግን ሕገ ወጥ ሥራ የሚሠሩ ኤጀንሲዎችን መቆጣጠርም መቼም ቢሆን ችል ሊባል አይገባም፡፡

ታምራት ተስፋዬ

አዲስ ዘመን ሐምሌ 8 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You