ብሔራዊ ትያትር ምን ነካው?!

መንግሥት አዲስ አበባን በሁለንተናዊ መንገድ ለነዋሪዎቿ የተመቸች የመኖሪያ አካባቢ ለማድረግ በስፋት እየሠራ ነው። ከተማዋን እንደ ስሟ አዲስ ለማድረግ እየተደረገ ባለው እንቅስቃሴም አሁን ላይ የከተማዋ ገጽታ በብዙ መልኩ እየተለወጠ ነው። መሽቶ ሲነጋ ለዓይን እና ለመንፈስ ማራኪ የሆኑ አዳዲስ ነገሮችን ማየትም እየተለመደ ነው።

የከተማዋ የመለወጥ ፍጥነት እንኳን ከከተማዋ ርቀው ለሚገኙ፣ በውስጧ ለሚኖሩ ነዋሪዎቿም ጭምር አስገራሚ እና አስደማሚ እየሆነ ነው። በዚህም ከሁሉም በላይ በቁርጠኝነት፣ በቁጭት እና በይቻላል መንፈስ ለለውጥ መሥራት ከተቻለ መለወጥ፤ የሩቅ ሳይሆን በእጅ ላይ ያለ የቅርብ ጊዜ ተስፋ መሆኑን በተጨባጭ ያመላከተ ነው።

በርግጥ መንግሥት ከተወሰኑ ወራት በፊት ስለ ኮሪደር ልማት እና የከተማ እድሳት ማውራት ሲጀምር፤ ከቆየው ልምምዳችን ጋር በተያያዘ እውነታውን መቀበል በብዙዎች ዘንድ ከባድ ነበር፤ ለተለመደ የፖለቲካ ፍጆታ የቀረበ ሸቀጥ አድርገው የወሰዱትም ነበሩ፤ ከዚያም አልፎ አጋጣሚውን የፖለቲካ አጀንዳ አድርገው ለመጠቀም የሞከሩም ጥቂት አልነበሩም።

እዚህ ግባ የማይባሉ ፕሮጀክቶች ዓመታት በሚያስቆጥሩበት፤ ለዓመታት የመሠረት ድንጋይ ማስቀመጥ እንጂ ተግባራዊ አፈጻጸም በማይታይበት ሀገር፤ ለዓመታት አስታዋሽ አጥቶ፤ በአሮጌ ፍርስራሽ ቤቶች ውስጥ ያለን ሰፋፊ የከተማ ክፍል ዘመኑን በሚመጥን ደረጃ ለማደስ መነሳት በብዙዎች ዘንድ ጥያቄ መፍጠሩ ብዙም ለውይይት የሚቀርብ አይደለም።

ገና ከምሥረታዋ ጀምሮ ዘመናዊ ከተማ የመሆን መነሻዋ በብዙ ተግዳሮቶች የተፈተነው አዲስ አበባ፤ በደርግ 17 የሥልጣን ዓመታት ዘመኑን የሚመጥን የከተማ ልማት ሳታይ አልፋለች። በዘመነ ኢሕአዴግም ቢሆን አዳዲስ የከተማ አካባቢዎችን ከማስፋት ባለፈ አዲስ አበባን አዲስ አበባ አድርገዋት የነበሩ መሐል አካባቢዎች /Downtown/ አስታዋሽ አጥተው ዓመታትን አስቆጥረዋል።

የእነዚህ አካባቢዎች የእርጅናቸው መጠን ለግምት በሚያዳግት መልኩ ነዋሪዎቿን አንገት ያጎበጠ እንደነበርም ከነዋሪዎቿ የትናንት ሕይወት በላይ ሊናገር የሚችል አይኖርም። በእርጅናቸው ላይ በየዘመኑ የደራረቧቸው አሮጌ ነገሮች፤ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሆነውባቸው፤ ለተመልካችም፤ ለሰሚም የሚመች ትርክት አልነበራቸውም።

በእርጅና ብዛት የከተማነት ውበት ያጡትን እነዚህን አካባቢዎች፤ በማደስ ለከተማዋ አዲስ ውበት አድርጎ ለመሥራት የሚደረገው ጥረት አሁን ላይ ከሞላ ጎደል ከቋንቋ ያለፈ ትርጉም ያለው የልማት ንቅናቄ መሆን ችሏል። በመላው ሕዝባችን አመኔታ እያገኘ፤ የተጠናከረ ድጋፍም እየተቸረው ነው። በዚህም የከተማዋ ነገሮች ብሩህ ስለመሆናቸው ተስፋ ሰጭ ጅማሪ እየታየ ነው።

ይህም ሆኖ ግን ይህ የሕዝብ እና መንግሥት ጥረት ትርጉም ያለው ፍሬ እያፈራ ባለበት ወቅት፤ አንዳንድ ተቋማት፤ ከተኙበት መንቃት እና ከቀደመው ዘመን አስተሳሰብ መሻገር ተስኗቸው በላያቸው ላይ የደረቡትን አሮጌ ማራገፍ አቅቷቸው፤ በአንድ ወቅት የከተማዋ ዓይን ማረፊያ የነበሩ ስፍራዎቻቸውን የድሪቶ ማራገፊያ አድርገዋቸዋል፡፡

ለዚህ ደግሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ትያትርን እንደማሳያ አድርጎ መጥቀስ የሚቻል ይመስለኛል። ብሔራዊ ትያትር በኪነጥበቡ ዘርፍ እንደ ሀገር ያበረከተው አስተዋፅዖ በመላው ሕዝብ፣ በተለይም በሙያው መስክ ለሚገኙ ባለሙያዎች እና ለሙያው አድናቂዎች የሚነገር አይደለም። በብዙ መንገድ ባለውለታ ነው። ብዙ አንጋፋ የጥበብ ሰዎችን በማፍራትም ግንባር ቀደም ነው።

ከዚህም ባለፈ የብሔራዊ ቲያትር አረንጓዴ የመናፈሻ ስፍራዎች እንደዛሬ የከተማ መሐል አረንጓዴ የመናፈሻ ስፍራዎች ባልተስፋፉበት ወቅት የብዙዎችን ዓይን እና ቀልብ የሚስብ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው፤ የመናፈሻው ልምላሜ እና ፋውንቴን ለአካባቢው ሞገስ እንደነበርም ለማስታወስ አይከብድም።

የመናፈሻው ልምላሜ ቁጭ ብሎ ከራስ ጋር ለማውራትና ለመጫወት የሚያስችል ነበር። ነፍሱን ይማር እና ታላቁ ገጣሚ እና ጸሐፊ ተውኔት ሎሬት ፀጋዬ ገብረመድኅን፤ ብዙውን ጊዜ በዛች መናፈሻ የመገኘቱ ሚስጢርም ይኸው ይመስለኛል ።

መናፈሻው ለአካባቢው የሚሰጠውን ውበት ሆነ፤ ለነዋሪዎቿ የሚያጎናጸፈውን መንፈሳዊ መታደስ ታሳቢ ባላደረገ መንገድ፤ ከሁሉም በላይ ለቲያትር ቤቱ ሞገስ የሆነውን ይህን የመናፈሻ ስፍራ፣ በሬስቶራንት ስም ወደ ተጎሳቆለ ጎጆ ከተለወጠ ዓመታት ተቆጥረዋል።

የአካባቢውን አሁናዊም ሆነ ቀደምት ውበት በማይመጥን መልኩ በሬስቶራንት ስም፣ እዚህ ግባ የማይባል የውስጥ ገቢ ለመፍጠር የተደረገው ጥረት በየትኛውም መመዘኛ አሁናዊ የከተማ እሳቤን የሚሸከም አይደለም። ከዚህ ይልቅ የተቋሙ አመራሮች የት ጋር ቆመው እያሰቡ እንዳለ የሚያሳብቅ ይመስለኛል።

የተቋሙ አመራሮች የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ኃላፊነት ወስዶ መናፈሻውን እንዲያድስ የሚጠብቁ አይመስለኝም፤ ይህን እየጠበቁ ከሆነ የመጨረሻ አሳፋሪ ጠባቂነት እንደሆነ መናገር ተገቢ ነው። እንደሀገር ከጠባቂነት ለመውጣት ብዙ እየተሠራ ባለበት ሁኔታ እጅን አጣጥፎ በጠባቂነት መንፈስ ውስጥ ሆኖ መገኘት ተገቢ፣ የለውጥ አመራርም መገለጫ አይደለም።

ፈጥኖ ወደ ሥራ በመግባት መናፈሻው ከቀደመው በተሻለ መንገድ ለአካባቢው ግርማ ሞገስ የሚሆንበትን፣ ለከተማዋ ተጨማሪ ውበት የሚፈጥርበትን፣ ለትያትር ቤቱ ባለሙያዎች ማሰላሰያ፤ ፀጥታና አረንጓዴ ስፍራ ለሚፈልገው የከተማዋ ነዋሪ ማረፊያ የሚሆንበትን አማራጭ የቲያትር ቤቱ ኃላፊዎች ሊያስቡበት ይገባል። ይህ ተግባር ለነገ የሚሉት የቤት ሥራ ሊሆንም አይገባም!።

ከመርደክዮስ

አዲስ ዘመን ሐምሌ 8 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You