ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ኢትዮጵያ በቱሪዝም ዘርፍ በተለይ ደግሞ በመዳረሻ ልማት ከፍተኛ መሻሻል እያሳየች መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ። ዘርፉ ከአምስቱ ዋና ዋና የኢኮኖሚ ምሰሶዎች ውስጥ እንደ አንዱ ተደርጎ መወሰዱና ይህን ተከትሎም በተለይ በመንግስት የተሰጠው ከፍተኛ ትኩረት ለውጤታማ አፈፃፀሙ ምክንያት መሆኑ ይገለጻል።
በቱሪዝም ዘርፍ እንደ በጎ ጅምር ከሚወሰዱ የመዳረሻ ልማት ስራዎች ውስጥ ግንባታቸው ተጠናቆ ለጎብኚዎች ክፍት የተደረጉት በአዲስ አበባ ተገንብተው ወደ ስራ የገቡት የገበታ ለሸገሮቹ የእንጦጦ፣ አንድነትና ወዳጅነት ፓርኮች፤ የገበታ ለሀገር ፕሮጀክት አካላት የሆኑት እንደ ሀላላ ኬላና ጨበራ ጩርጩራ የዝሆን ዳና ሎጅ እንዲሁም የወንጪ ደንዲ ኢኮ ሎጅ እና ሌሎች መሰል የመስህብ ስፍራዎች በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ።
ከመዳረሻ ልማት ባሻገር የቱሪዝም ሚኒስቴርና የሚመለከታቸው የዘርፉ ባለድርሻዎች በማስታወቂያና ገበያ ልማት በኩል የመስህብ ሀብቶቹን ለዓለም ገበያ ለማቅረብ አዳዲስ ስልቶችን በመከተል እየሰሩ መሆናቸው፣ ከእነዚህ የማስታወቂያና የቱሪስት ፍሰትን ከሚጨምሩ የገበያ ልማት ስራዎች ውስጥ ዓለም አቀፍ ፌስቲቫሎች እንዲሁም ኮንፍረንሶች ላይ መሳተፍ እንዲሁም የቱሪዝም ዲፕሎማሲ ስራዎችን መተግበርም ሌሎች ለአፈጻጸሙ ውጤታማነት አስተዋጽኦ ያደረጉ ምክንያቶች በሚል ሊወሰዱ ይችላሉ።
የቱሪዝም ሚኒስቴር በቅርቡ ይፋ እንዳደረገው፤ ከላይ የተጠቀሱትን ተግባራት ተከትሎ የዓለም አቀፍና የአገር ውስጥ ጎብኚዎች ቁጥር እያደገ መጥቷል። ይህ ቁጥር በዓለም አቀፍ ተፅእኖዎችና በአገሪቱ አንዳንድ ቦታዎች ከሚታየው ግጭት እና አለመረጋጋት አንፃር ተስፋ ሰጪ መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎችም ይናገራሉ። በ2016 በጀት ዓመት፣ በአስር ወራት ውስጥ ብቻ 982 ሺህ ዓለም አቀፍ ጎብኚዎች አንዲሁም 37 ሚሊዮን የአገር ውስጥ ቱሪስቶች ልዩ ልዩ የቱሪዝም መስህቦችን እንደጎበኙ የሚኒስቴሩ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቅርቡ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሲሰጡ፣ በ2016 በጀት ዓመት በቱሪዝም ዘርፍ ስኬታማ ውጤቶች መመዝገባቸውን ተናግረዋል። ከእነዚህ ውጤታማ ተግባሮች ውስጥ አንዱ በአዲስ አበባ እየተተገበረ ያለው የኮሪደር ልማት መሆኑ ተመልክቷል። የአገር ውስጥ ቱሪዝም እድገት እያሳየ መምጣቱንም እንደ በጎ ጅምር ጠቅሰውታል።
እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ፤ የኮሪደር ልማቱ የአዲስ አበባን ገፅታ በማራኪ መልኩ ከመቀየሩም ባሻገር ነዋሪዎች መዝናኛና መናፈሻዎችን በበቂ ሁኔታ እንዲያገኙ እያስቻለ ነው። በቀጣይ አምስትና ስድስት ዓመታት ውስጥ መሰል ስራዎች ተጠናክረው ሲቀጥሉ የአገሪቱ ብሎም የከተማዋን አጠቃላይ ገፅታ ሊሻሻል ይችላል።
በኮሪደር ልማቱ፣ በአዲስ አበባ የተገነቡ አዳዲስ የመዳረሻ ልማቶችን ተከትሎም፣ የአገር ውስጥ ቱሪዝም ከፍተኛ እድገት ማስመዝገቡን ጠቅሰው፣ በበጀት ዓመቱ ብቻ 37 ሚሊዮን ገደማ የአገር ውስጥ ጎብኚዎች የመስህብ ስፍራዎቹን እንደጎበኙ ገልፀዋል። የዜጎች የመዝናናት እና አዳዲስ ቦታዎችን የመመልከት ባህላቸው እየጨመረ መምጣቱንም የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በልዩ ልዩ አካባቢዎች የሚስተዋለው አለመረጋጋት ሲወገድና የተሟላ ሰላም ሲመጣ ከዚህ በበለጠ መልኩ ቱሪዝም በአገር ውስጥም ሆነ በውጪ ጎብኚዎች ትልቅ ገበያ ሊሆን እንደሚችል አመልክተዋል።
መንግስት ሁሉን አቀፍ የቱሪዝም ለውጥ እንዲመዘገብ እየሰራ መሆኑን ተናግረው፣ ተስፋ ሰጪ ጅምሮች መኖራቸውን ገልፀዋል። የተፈጥሮ ቱሪዝምንም ሆነ መሰል መስህቦችን ለመጎብኘት እንዲያስችሉ ተደርገው በአገር ውስጥ መኪኖች መገጣጠማቸው ከእነዚህ ውስጥ አንዱ መሆኑን አመልክተዋል። ይህም መንግስት ባለሀብቶችን ለመደገፍ በሰጠው አቅጣጫ መሰረት ተከናውኖ ለስኬት የበቃ መሆኑን ጠቅሰው፣ የመጀመሪያዎቹ ለሳፋሪ ጉብኝት የሚያገለግሉ መኪኖች መመረታቸውንም ገልፀዋል። ይህ ስኬት ሁሉን አቀፍ ለውጥ ለማምጣት እንደሚረዳም አስገንዝበዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በየካቲት 2016 በተካሄደ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የ100 ቀናት ግምገማ ወቅት ለቱሪዝም አገልግሎት የሚሰጡ የሳፋሪ ተሽከርካሪዎች እንዲመረቱ ለኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የሰጡትን አቅጣጫ ተከትሎ ሚኒስቴሩ በሀገር ውስጥ ለሳፋሪ አገልግሎት ተሽከርካሪነት የተቀየሩ ባለአንድ ጋቢና ፒክ አፕ መኪናዎችን በናሙናነት ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አስረክቧል። መኪናዎቹን ለሳፋሪ አገልግሎት እንዲመቹ አድርጎ በመለወጥ ሂደት ውስጥ አምራቾች በሀገር ውስጥ በስፋት የመለወጥ ልምድ እና አቅም ለማዳበር እንደቻሉም ተመልክቷል።
ለቱሪዝም እድገት የሚረዱ አዳዲስ ተግባራትን ከመከወን ባሻገር ዓለም አቀፍ ጎብኚዎችን ለመሳብ የሚረዱ የማስተዋወቅ ተግባራት በባለድርሻ አካላት እየተከናወኑ መሆናቸውን የሚያስገነዝቡ በርካታ መረጃዎችም እየወጡ ይገኛሉ። ከእነዚህ ውስጥ ታዋቂ የእግር ኳስ ተጫዋቾችን ወደ ኢትዮጵያ በመጋበዝ እንዲሁም የመስህብ ስፍራዎችንና የኢትዮጵያን ገፅታ የሚቀይሩ እውነታዎችን በማስተዋወቅ ዓለም አቀፍ የገበያ ድርሻን ለማስፋት የሚደረገው ጥረት ይገኝበታል። ከሰሞኑም በዚህ ረገድ ስኬታማ ስራዎች መከናወናቸውን የቱሪዝም ሚኒስቴር ያወጣው መረጃ ያመለክታል።
የ2016 በጀት ዓመት የ10 ወራት የማክሮ ኢኮኖሚ የዘርፎች ዋና ዋና አፈፃፀም እና የ2017 የትኩረት አቅጣጫዎችን አስመልክቶ የተደረገውን ውይይት ተከትሎም የቱሪዝም ሚኒስትር አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ የቱሪዝም ዘርፉን አፈፃፀም የሚመለከት ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት እንደተናገሩት፤ የቱሪዝም ዘርፉ በሁለት ንኡስ ዘርፎች ተከፍሎ ዋና ዋና ስራዎችን እንዲያከናውን እንደሚጠበቅበት ተናግረዋል። እነዚህም የመዳረሻ ልማት እና የማስተዋወቅና የገበያ ልማት መሆናቸውን ይገልፃሉ።
እንደ ሚኒስትሯ ገለፃ፤ በተጠናቀቀው የ2016 በጀት ዓመት ከገበያና ማስተዋወቅ ተግባር አንፃር ሰፋፊ ስራዎች በአገር ውስጥና በውጪ ሀገሮች ተከናውነዋል። በውጪ ከተሰሩት ተግባራት ውስጥ ዓለም አቀፍ የቱሪዝምና ንግድ አውደርእዮች (trade fair) ላይ ለመሳተፍ፣ ዓለም አቀፍ ገበያ ውስጥ ለመግባት እድል መክፈት የሚችሉ ቱር ኦፕሬተሮችን ወደ አገር ውስጥ ለማምጣትና የትውውቅ መድረኮችን ለመፍጠር (familiarization trip) ተሰርቷል፤ በዚህም ዓለም አቀፍ ተደራሽነትንና ተቀባይነትን ለማግኘት ጥረት ተደርጓል።
እርምጃውን ተከትሎ በተለይ ወደ ኤዢያ አገራት (በተለይ ቻይና)፣ ወደ መካከለኛው ምስራቅ አገራትና ደቡብ አሜሪካ አገራት በመሄድ የትውውቅና የገፅታ ግንባታን የሚያፋጥኑ መድረኮች መፈጠራቸውን ሚኒስትሯ ጠቅሰዋል። ይህም የዓለም አቀፍ ቱሪስቶችን ቁጥር በመጨመር ረገድ የበኩሉን አስተዋፆ እንደሚያበረክት ይገልፃሉ።
ሚኒስትሯ በሶስተኛው ሩብ ዓመትም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ያቀደውን ያህል ዓለም አቀፍ ቱሪስት ወደ አገር ውስጥ መሳብ መቻሉን ጠቅሰው፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ካለው ፍላጎት እንዲሁም ካለው አቅም አንፃር ሲታይ በቀጣይ ብዙ ስራዎች እንደሚቀሩ አመላክተዋል። ቀሪ ስራዎችን አስመልክተው ሲያብራሩም በአንዳንድ አገራት ወደ ኢትዮጵያ ጎብኚዎች እንዳይገቡ የሚያደርጓቸው የጉዞ ክልከላዎች መኖራቸውን ጠቁመው፣ ይህንን ገፅታ መቀየር እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል። የጉዞ ክልከላውን አልፈው የመጡ ጎብኚዎች መኖራቸውን አስታውቀው፣ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም ካስቀመጠው እቅድ አንፃር በቂ የቱሪስት ቁጥር ወደ አገር ውስጥ መግባቱን አመልክተዋል።
ከገቢም አንፃር አመርቂ ውጤት መታየቱን የጠቀሱት አምባሳደር ናሲሴ፣ በአገር ውስጥ የጉብኝት ባህል እየዳበረ መምጣቱን፤ በተለይ ወጣቱ የተለያዩ የጉብኝት ጉዞዎችን (የተራራ መውጣት፣ በቡድን ጉዞ ማድረግን የመሳሰሉ) እንደሚያደርግ አንስተዋል። ከዚህ ባሻገር በማይስ (ስብሰባና አውደ ርዕይ) ቱሪዝም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከእቅድ በላይ ዓለም አቀፍ ስብሰባዎችን (በጤና፣ በኢንዱስትሪ፣ በማኑፋክቸሪንግና በልዩ ልዩ ዘርፎች ላይ) ያተኮሩ አውደ ርእዮችንና መሰል መድረኮችን ማዘጋጀት መቻሉንም ይገልፃሉ። እነዚህ ሁሉ ኢትዮጵያ በማይስ ቱሪዝም ዘርፍ ስኬታማ ዓመት እንድታሳልፍና ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሁነቶች እንዲዘጋጁ ምክንያት መሆናቸውን ያስረዳሉ።
ሚኒስትሯ በሰጡት ማብራሪያ እንዳስታወቁት፤ በቱሪዝም ዘርፍ ከሚጠበቁ ተግባራት መካከል አንዱ የመዳረሻ ልማት ነው። ከዚህም አኳያ የገበታ ለሀገር ፐሮጀክቶች ወደ ስራ እየገቡ ያሉበት ሁኔታ እንዲሁም የገበታ ለትውልድ ፕሮጀክቶች ግንባታ መጀመሩ በዘርፉ ከተመዘገቡ ስኬቶች መካከል ናቸው። አፈፃፀማቸውም በመልካም ሁኔታ እየሄደ መሆኑም ሌላው ስኬት ነው።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በበላይነት የሚያከናውናቸው የመዳረሻ ልማት ስራዎች መኖራቸውን የሚገልፁት ሚኒስትሯ፣ ለእዚህም በምሳሌነት የጅማ አባጅፋር ቤተመንግስት የጥገና ስራና አዳዲስ የመዳረሻ ልማት ስራዎች በተፋጠነ ሁኔታ እየተሰሩ መሆናቸውን ጠቅሰዋል። አብዛኛዎቹ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሚያከናውናቸው ፕሮጀክቶች በቀጣዩ ዓመት መጀመሪያ ወራት ላይ ተጠናቅቀው ለአገልግሎት እንደሚበቁ እንደሚጠበቅም ጠቁመዋል።
‹‹ነባር መዳረሻዎች ደረጃቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ እየተሰራ ነው›› የሚሉት ሚኒስትሯ አምባሳደር ናሲሴ፤ በተለይ ከመፀዳጃና ከተለያዩ መሰረተ ልማቶች አንፃር ደረጃቸውን ከፍ ለማድረግ እንደሚሰራ ይናገራሉ። ይህንንም ለመፈፀም የመዳረሻ ልማቶቹ ምን አይነት ደረጃ ሊኖራቸው ይገባል በሚለው ላይ ደረጃ የማውጣት እና ሰነድ የማዘጋጀት ስራ መዘጋጀቱን ጠቅሰው፣ ከዚህም ባሻገር ወደ ተግባራዊ ስራ ለመግባት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም አመልክተዋል። ክልሎቹም የመዳረሻዎቻቸውን ጥራትና ደረጃ እንዲያሻሽሉ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጥረት እያደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።
ሚኒስትሯ እንዳብራሩት፤ የአገልግሎት ዘርፉን ጥራት ከማስጠበቅ አንፃር ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ልዩ ልዩ ተግባራትን እያከናወነ ነው። ከዚህ አንፃር በሆስፒታሊቲ ዘርፉ የቱሪስት አገልግሎትን የሚያሟሉና ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች ምደባ ተካሂዷል። ዘንድሮም በድጋሚ የባለኮኮብ ሆቴሎች ምደባ ተካሂዷል፤ በተመሳሳይ በቅርብ ጊዜያትም ሌሎች ተጨማሪ ሆቴሎችን የመመደብ ስራ የሚከናወን ይሆናል።
የሆቴሎች የደረጃ ምደባ የሚያስፈልግበት ዋንኛ ምክንያት ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንድትሆን ነው የሚሉት ሚኒስትሯ፤ ይህንን ተከትሎ ሆቴሎች አሊያም አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ከሌሎች መሰል ዓለም አቀፍ ሆቴሎችና ተቋማት ጋር ተመሳሳይ የሆነ የጥራትና አገልግሎት ደረጃ እንዲኖራቸው እንደሚያግዝ ያስረዳሉ።
እስካሁን ደረጃ ላልወጣላቸው ሬስቶራንቶች፣ አስጎብኚ ድርጅቶች፣ ሎጆችና ሪዞርቶች ደረጃ የማውጣት ሂደት እየተጠናቀቀ መሆኑን ይናገራሉ። በቅርቡም ልክ እንደሆቴሎቹ ሁሉ እነዚህም የቱሪዝም ዘርፍ የሆስፒታሊቲ አንቀሳቃሾች ደረጃ እንደሚወጣላቸው አስታውቀዋል። ይህም ስራ ከ2017 በጀት ዓመት እቅድ ከቀዳሚ ተግባራት መካከል አንዱ እንደሆነ ተናግረዋል።
ሚኒስትሯ አጠቃላይ የቱሪዝም ዘርፍ ተግባራት (ከመዳረሻ ልማት፣ ማስተዋወቅ፣ ደረጃ ማውጣት) አንፃር ሰፋፊ ስራዎች መከናወናቸውን ገልፀዋል። እነዚህ ተግባራት ኢትዮጵያ በቱሪዝም መዳረሻነት ከሌሎች አገራት ጋር ተወዳዳሪ እንድትሆን ከፍተኛ አስተዋፆ እንደሚኖራቸውም ጠቁመዋል። በቀጣይ ዓመትም የቱሪስት ፍሰቱ እንደሚጨምር ጠቅሰው፣ እስከ አንድ ነጥብ ሶስት ሚሊዮን ቱሪስቶች ወደ አገር ውስጥ እንደሚገቡ ጠቁመዋል።
የአዲስ አበባ የኮሪደር ልማት ስራን አስታክኮም የጊዜያዊነት ትራንዚት የሚያደርጉ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ተጓዦች የሚኖራቸውን አጭር ሰዓታት ቆይታ አዲስ አበባን የሚጎበኙበት (Stopover tourism) አጋጣሚ የሚጨምርበት፣ አገርም ከዚያ ተጠቃሚ የምትሆንበት ሁኔታ እንዲፈጠር እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።
የቱሪዝም ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያመለክተው፤ ከላይ ከተነሱት ተግባራት በተጨማሪ በዘንድሮው በጀት ዓመት ምቹና ደህንነቱ የተጠበቀ የትራንስፖርት አገልግሎት ከመስጠት፤ 60 የሚደርሱ ዓለም አቀፍ አስጎብኚዎች የኢትዮጵያን የመስህብ አቅም ተመልክተው ጎብኚዎችን እንዲያመጡ፣ በቅድሚያም ራሳቸው እንዲጎበኙ ከማድረግ፣ የገበያ ማስተሳሰር ስራን ከማከናወን፤ በውጪ አገራት ውጤታማ የግብይትና የማስተዋወቅ ስራን ከመስራት አንፃር አመርቂ ተግባራት ተከናውነዋል።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 7 ቀን 2016 ዓ.ም