ከመንግሥት ሠራተኝነት እስከ ኢንቨስተርነት

ቲቶን እንደተረዳሁት

ቲቶ ሐዋርያት ይባላል፤ ጋምቤላ ክልል፣ ማጃንግ ዞን፣ ጎደሬ ያበቀለችው ቁመተ መለሎ ጎልማሳ ነው። ይህ ሰው የባሮ ዳር ፈርጥ፤ የጋምቤላ ከተማ ተምሳሌት ነው። በተምሳሌትነቱም በርካቶች ያውቁታል። በአካባቢው በሚገኘው በማርና በወተት ተቀማጥሎ ያደገ ስለመሆኑ ተክለ ቁመናው በግልፅ ያሳብቃል፤ ንግግሩ ደግሞ ሩቅ አሳቢ ስለመሆኑ ይመሰክራል።

በነበረን አጭር ቆይታ ትህትናው እና ተግባቢነቱ ረጅም መንገድ ለመጓዝ ያሰበ፤ ሩቅ የተለመ ስለመሆኑ ፍንትው አድርጎ ያሳያል። ቲቶ፣ ሥራው ማር- ንግግሩም ማር ነው። ስለሚናገረው ይጠነቀቃል፤ ማር ይበላል፤ እንግዳ ወደ ቤቱ ሲሄድ ማር ያቀርባል። አማርኛ ይቀኛል፤ የማጃንግ ቋንቋ አፍ መፍቻው ነው፤ በአፋን ኦሮሞ ይግባባል፤ ከፍኛ ቋንቋም እንዲሁም የራሱ ነው። እንግሊዘኛን በሥራ እና በትምህርት አግኝቶታል። የቋንቋ እና ተግባቦት ሃብታም ነው።

የቲቶ መንደር

የቲቶ መንደር ይለያል። ተፈጥሮ ለእርሱ ሰፈር ያደላች ይመስላል። ዞኑ ሙሉ በሙሉ ጫካ ነው። እልፍ ሲሉ ውሃ ነው፤ እንደገና እልፍ ሲባል ደን፣ ውሃ፣ ፍራፍሬ፣ ንብ ነው፤ ጥቅጥቅ ያለ ጫካ ከመሆኑ የተነሳ አካባቢውን ዝቅ ብሎ ለተመለከተ ሰው አረንጓዴ ስጋጃ የለበሰ ይመስላል። ቀና ሲሉ ደግሞ እርስ በእርስ ተቆልፈው ሰማይን የጋረዱ ዛፎች ቅርንጫፋቸውን አጣምረው የጥዋት ጀንበር በጭላንጭል ብቻ ምድሪቱን እንድትሞቅ አስገድደዋል። ተፈጥሮ ተፈጥሮን ሲገድብ የጫካው እና የጥዋት ጀንበር አሙቂኝ አላሞቅም ግብግብ በማጃንግ ምድር አንዱ ለአንዱ ምስክር ናቸው።

በጫካው ያሉ ጦጣዎች በነፃነት ከአንዱ ዛፍ ወደሌላኛው ዛፉ ይንጠላጠላሉ። ማጃንግ ዞን በተባበሩት መንግስታት የትምህርትና ባህልና ቅርስ ድርጅት (ዩኒስኮ) የተመዘገበ ደን ያለበት ሲሆን፣ በዚህ ውስጥም በርካታ አዕዋፍ እና የዱር እንስሳ ይገኙበታል። በጫካው ውስጥ በቅርብ ርቀቱ ባህላዊ ቀፎዎች ተሰቅለዋል። በእርግጥ በማጃንግ ብሄረሰብ ዞን ደን እና ሰው በእጅጉ ተስማምቶ የሚኖርበት፤ አንዱ ለአንዱ የሚጨነቅበት ነው ቢባል ማጋነን አይደለም።

በቲቶ መንደር በርካታ ቀፎች ተሰቅለዋል። የአካባቢው ነዋሪም የቲቶ ቀፎ እያለ ይጠራቸዋል። ይህ ሰው በተወለደበት አካባቢው የሚወደድ ነው፤ ብዙ በጎ ተፅዕኖም የፈጠረ እና የእርሱን እግር ተከትለው ወደተሻለ ሕይወትም እያመሩ ያሉ ወጣቶች አሉ። እናም ቲቶ በዚህ መንደር የበጎ ሰዎች ተምሳሌት ነው።

ብቸኛው ልጅ

ለእናቱ ብቸኛ ልጅ ነው። በአጋጣሚ ደግሞ የትዳር አጋራቸውም ለእናታቸው ብቸኛ ልጅ ናቸው። ሁለቱም ለእናታቸው ብቸኛ ልጅ መሆናቸውን ያወቁት ግን በትዳር አብሮ መኖር ከጀመሩ ዓመታት በኋላ ከዕለታት በአንድ ቀን በተነሳ ጨዋታ ነው። በአባታቸው በኩል ደግሞ በተመሳሳይ መልኩ በርከት ያሉ እህቶች እና ወንድሞች አሏቸው – አቶ ቲቶ እና ባለቤታቸው።

ትምህርት እና ልጅነት

ቲቶ እናት አንድ ልጃቸውን ከአጠገባቸው እንዲርቅ ባይፈልጉም ከቀለም ትምህርት ግን ማናጠብ አልፈለጉም። ይልቁንም ተምሮ በሀገሬው ዘንድ የተከበረ ይሆን ዘንድ የዘወትር ምኞታቸው ነው። አንድ ልጃቸውን በእጅጉ ይሳሱለታል። በአካባቢው ሸክላ ሥራ ተለመደ ነው። እናም አንዳንድ ጊዜ ልጃቸው ብቸኛ መሆኑን፤ ሲሰሩ ‹‹አንተ ሸክላ ብትሆን እዚሁ አቡክቼ እዚሁ ሰርቼ ብዙ አደርግህ ነበር›› እያሉም ይቀልዱበታል። ግን ደግሞ ገና በማለዳቸው ሲመርቁት፤ “አንተ አንድ ሆነህ እንደ ሺህ ታፈራለህ፤ ዘር ይለመልማል” እያሉ ነው። ቲቶም ደስ ይለዋል፤ ቲቶ ያደገው ይህን በአእምሮ እያሰላሰለ እና ደጋግሞ እያሰበም ነው። በተቻለ መጠን ለተወለደበት አካባቢ አርዓያ ለመሆንም ያልፈነቀለው ድንጋይ የለም፤ ያልቧጠጠው ተራራ አልነበረም። ታዲያ ያሰበው ነገር እንዲሁ መና አልቀረም፤ የእናቱ ምኞትምና ምርቃትም አልባከነም። በአካባቢው በርካቶች ትምህርት ላይ ብዙ ባያተኩሩም እርሱ ግን ትምህርቱን በተቻለ መጠን ገፍቶበታል።

ቲቶ የትምህርትን ጥቅም ብዙ ባያውቅም ገና በልጅነቱ መማር ይፈልግ ነበር። በተለይ ደግሞ ወላጅ እናቱ ለትምህርት በጣም ጉጉት ነበራቸው። በልጅነቱም መርቀው ወደ ትምህርት ቤት ሸኙት። እርሱም ቦርሳውን አንግቶ ከመንደሩ ጥቂት ተማሪዎች ጋር ወደ አስኳላ ትምህርት አቀና። ጎሽኔ፣ ገለሻ እና አካሺ በሚባሉ ትምህርት ቤቶች እየተዘዋወሩ ከአንደኛ ክፍል እስከ ስምንተኛ ክፍል ተምረዋል።

በ1990 ዓ.ም ደግሞ በወቅቱ ለታዳጊ ክልሎች በሚሰጠው የትምህርት ዕድል መሠረት ወደ አዲስ አበባ አምርቶ ከ8ኛ እስከ 12ኛ ክፍል የአዳሪ ትምህርት ቤት ትምህርቱን ተከታተለ። ከዚያም ወደ ጋምቤላ ክልል በመመለስ ኮሌጅ ሰልጥኖ አጠናቀቀ። የኮሌጅ ምረቃ ከተከናወነ በኋላ ያለአንዳች ቆይታ ሥራ ላይ ተመደበ፤ መምህርም ሆነ። ከተማሪነት ወደ አስተማሪነት በመሸጋገር አዲስ የሕይወት ምዕራፍ ጀመረ።

ሥራ

ፈርጣማው ወጣት አሁን ከትምህርት ዓለም ወደ ሌላኛው የሕይወት ምዕራፍ ተሸጋገሩ። ወደ ተወለዱበት ጎደሬ ወረዳ ተመልሰው በመምህርነት ለአንድ ዓመት አገለገሉ። ወርሃዊ ደመወዛቸውም 450 ብር ተወሰነላቸው። ታዲያ ታታሪ እና ጎበዝ ሰራተኛ ስለሆኑ በርካቶች ትኩረት ጣሉባቸው። ከወረዳ እስከ ዞን ብሎም ክልል ድረስ በአጭር ጊዜ ለመዝለቅ የሚያስችል ብቃት አሳዩ። ከአንድ ዓመት የሥራ ቆይታ በኋላ ማለትም በ1995 ዓ.ም በጋምቤላ ክልል ሹመት ተሰጣቸው። ከዚህ ቀን ጀምሮ በክልሉ የተለያዩ ቢሮዎች እና ጽህፈት ቤቶች በኃላፊነት አገልግለዋል።

ከ21 ዓመት የሥራ ዘመናቸው 20 ዓመታት ሙሉ የቆዩት በአመራርነት ላይ ነው። ከእነዚህም መካከል የፓርቲ ጽህፈት ቤት፣ ንግድ ቢሮ፣ ገቢዎች ቢሮ፣ በሕዝብ ተሳትፎ፣ ኮሌጅ ዲን፣ የክልሉ ዋና አፈ ጉባኤ እንዲሁም በአሁኑ ወቅት የክልሉ ምክር ቤት ውስጥ ቋሚ ኮሚቴ አባል ናቸው። እነዚህ የስልጣን እርከኖችን በአግባቡ ተጠቅመዋል፤ ሕዝብ የጣለባቸውን ኃላፊነትም በአግባቡ ተወጥተዋል።

የሥራ መልቀቂያ

አቶ ቲቶ በአሁኑ ወቅት የክልሉ ምክር ቤት ውስጥ ቋሚ ኮሚቴ አባል ቢሆኑም ሥራ መልቀቂያ ጠይቀዋል፤ ምክንያታቸው ደግሞ ኃላፈነት በቃኝ የራሴን ሥራ ልጀምር የሚል ነው። እንደ እርሳቸው አባባል፤ ‹‹እኔ በግል ጠንክሬ ከሠራሁ ራሴንም ሀገሬንም እለውጣለሁ ብዬ አምናለሁ፤ በተለይም እንደ ሀገር የተጀመረው የሌማት ትሩፋት እንቅስቃሴ በርካቶችን እያነቃቃ እና ለውጥም እየተመዘገበ በመሆኑ ይህ መልካም አጋጣሚ ነው። እኔም ከልጅነቴ ጀምሮ የግብርና ሥራን በጣም የምወድ በመሆኑ ወደምወደው ግብርና ለመግባት ወስኛለሁ። ›› ይላሉ።

“እኔ ይህን ውሳኔ ስወስን ወይንም ወደግል ሥራዬ ስገባ የመንግስት ሥራ ይበደላል። በመሆኑም ሙሉ ለሙሉ ወደ ግል ሥራ መዞር ስላለብኝ የመንግስት ሥራ ማቆም እንዳለብኝ ለራሴ ነገርኩት። በተለይም ሕዝባዊ ኃላፊነት ተሸክሞ በሙሉ ልብና ጊዜ በሥራው ላይ አለመገኘት ሕዝብን መበደል መስሎ እየተሰማኝ መጣ። በዚህ ሁኔታም መቀጠል ለእኔም፣ ለማኅበረሰቡም ብሎም ለሀገሬ የሚጠቅም አይደለም። ሥለዚህ ከሁለት አንዱን መምረጥ ግድ ይለኝ ስለነበር የሥራ መልቀቂያ አስገባሁ። ” ይላሉ- ቲቶ ሐዋርያት።

ንብ ማነብ

ሰውየው ከልጅነታቸው ጀምሮ የግብርና ፍቅር በአዕምሯቸው ውስጥ አለ። ይሁንና በመንግስት የስራ ኃላፊነት ላይ በመጠመዳቸው ሙሉ ለሙሉ ብለው አልገቡበትም። ግን ከአራት ዓመት በፊት ንብ ማነብ እና ማር ማምረቱን በሰፊው ተያያዙት፡ በጥቂት ቀፎ የተጀመረው ሥራ እያደገ በመምጣቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ቀፎዎችን ማስቆጠሩ ቻሉ። ይህም ብቻ ሳይሆን የቲቶ ቀፎ ያለበት ሁሉ የሰፈሩ መለያ እስከመሆንም ደረሰ። ሰዎች በዚያ መንደር ሲያልፉም በርከት ብለው ከጫካው ውስጥ የተደረደሩ ቀፎዎችን ከተመለከቱ የቲቶ ንብረት ስለመሆኑ ይናገራሉ። ቲቶ ሐዋሪያትና ቤተሰቡ ከባህላዊ ቀፎ ወደ ዘመናዊ ቀፎ በመሸጋገር ሥራውን አዘመኑት። ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ ደግሞ ንብ ከማነብና ማር ከማምረት ወደ ሌላ የግብርና ዘርፍ ተሸጋግረዋል። ሙዝ ላይ በሰፊው መሥራት ጀመሩ። በአሁን ወቅት ሦስት ሄክታር መሬት የሚጠጋ የሙዝ እርሻ አላቸው።

ሽግግር ወደ አረንጓዴው ወርቅ

የጀመርኩት አንዱ የሥራ ዘርፍ ብቻ ይበቃኛል ብለው የማይቀመጡት አቶ ቲቶ፣ ከአንዱ ስራ ወደ ሌላ ስራ በፍጥነት እየተሸጋገሩ ነው። ከንብ ማነብ ወደ ሙዝ እርሻ መሰስ ብለው ገብተዋል። ይህ አልበቃኝም ብለው አንገታቸውን በረጅሙ አስግገውና የሀገሪቱ ቀዳሚዎቹ የገቢ ምንጭ የሆነው አረንጓዴ ወርቅ ለማምረት በማለም ወደ ቡና እርሻ አማትረዋል። በአሁኑ ወቅት ደግሞ በሙሉ አቅም ወደ ቡና እርሻ ለመግባት እየተንደረደሩ ነው። የቡና እርሻ ኢንቨስትመንት ፈቃድ ወስደዋል። ለዚህም የሚሆን ተስማሚ ቦታ ለማግኘት ለጎደሬ ወረዳ ዞን እና ክልል በየደረጃ ለሚመለከታቸው አካላት አሳውቀው የኢንቨስመንት ይሁንታ አግኝተው አሁን የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ይገኛሉ።

 

 ሰዎች ደነገጡ

አቶ ቲቶ ሐዋርያት፣ ሹመት አልፈልግም ብለው ወደ ግል ሥራ ሲገቡ ያመነ የለም፤ ሰዎችም ደንግጠዋል። ‹‹ብዙ ሰዎች ደንግጠዋል። እውነት አልመሰላቸውም። አልተለመደም። በእኛ አካባቢ ብዙውን ጊዜ ሰዎች የሚጣሉት እና እንደ ክልልም የግጭት መንስኤ ከሆኑት ምክንያቶች አንዱ የወንበር ሽሚያ ጉዳይ ነው። በበርካቶች ዘንድ ስልጣን የመያዝ ፍላጎት አለ። ስልጣን ለመያዝ አንዱን በሌላ ላይ ማነሳሳትና ማደራጀት አለ›› ይላሉ ያለውን ሽኩቻ ሲገልፁ። በመሆኑም እኔ በተለየ መልኩ ሕይወት ምቾት የሚሰጠው በስልጣን ላይ ሳይሆን በሌላኛው ገጽታ መሆኑን ለማሳየት ስል ብሎም የምወደውን ሥራ ለመሥራት በማሰብ ማመልከቻ አስገባሁ ባይ ናቸው። የጀመሩት ሥራ አዳካሚ ቢሆንም በብዙ እጥፍ አትራፊ እንደሚሆኑም አይጠራጠሩም። ከገቢ አኳያም በመንግስት ሥራ ላይ ከሚያገኙት የሰማይ እና ምድር ያህል ልዩነት እንዳለው ይናገራሉ። በእርግጥ እኔ ኃላፊነት ትቼ ወደዚህ ስራ ስገባ በርካቶች ዘንድ አግራሞት ተፈጥሯል፤ ተገርመዋል፤ ለምን? ብለው ጠይቀዋልም። እኔ ደግሞ የተገነዘብኩት ነገር አለ። የምለፋው ዕድሜ ልኬን ሳይሆን በጣም ጥቂት ዓመታትን ነው። በጥቂት ዓመት ውስጥ በገንዘብ ደረጃም ሐብታም መሆን እንደሚቻል አይቻለሁ። ይህን ውሳኔ ስወስን ደጋግሜ አስቤ ነው ይላሉ።

ቤተሰብ

እኚህ ሰው በትዳራቸው ስኬታማ ከሚባሉት መካከል ናቸው። ከባለቤታቸው ጋር ከተጋቡ 26 ዓመታት ተቆጥረዋል። በጋ ሙቀቱን፤ ክረምት ደግሞ ብርዱን፤ በችግር ጊዜ ውጣ ውረዱን አብረው ተጋፍጠዋል። አምስት የአብራካቸው ክፋዮች አሏቸው፤ አንዲት ሴት እና አራት ወንዶች ናቸው። ልጆቻቸው በሙሉ ትምህርት ላይ ናቸው።

የቲቶ ትዳር አጋር ጠንቃቃ ወይዘሮ ናቸው። ወይዘሮዋ፣ የመንግስት ተቀጣሪ ቢሆኑም፤ ባለቤታቸውን በማገዝ ቀዳሚውን ድርሻ ይወስዳሉ። ይህም ብቻ ሳይሆን የንብ ማነብ ሆነ እርሻው የበለጠ እንዲስፋፋ ትልቅ ሚና ይጫወታሉ፤ ይመካከራሉ፤ በበጎ አንደበት ይነጋገራሉ። ስለነጋቸው ማማር አብረው ይወጥናሉ። ከዓይን ጥቀሻ በፈጠነ ሁኔታ ይናበባሉ፤ ይግባባሉ። ልጆቻቸውም ቢሆኑ አባታቸው ሥራ መልቀቂያ ማስገባቱን ሲረዱ ጠንክረን እንሰራለን ብለው አበረታትተዋል።

“እኔ 30 ቀን ሰርቼ አንድ ቀን ደመወዝ ከምቀበል፤ አንድ ቀን ሰርቼ 30 ቀን ደመወዝ የምቀበልበትን ዕድል መፍጠር እፈልጋለሁ። መሻቴ መቀጠር ሳይሆን ለብዙዎች የሥራ እድል መፍጠር ነው። ለአካባቢው ብሎም ለክልሉ በመልካም አርዓያነት መጠቀስን እሻለሁ። ” ይላሉ።

እናቴ ብትኖር…

አባቴ ከሌላ የወለዳቸው ሁለት ወንድሞች ከእኔ ጋር ይኖራሉ። ማር እያስተዋወቁና እና እየሸጡ ደመወዝ ይከፈላቸዋል። በአሁኑ ወቅት በዓመት ሁለት ሺ ኪሎ ግራም ማር እያመረትኩ ነው። በቅርቡ ይህን አምስት ሺ ኪሎ ግራም አደርሳለሁ። ሙዝ እና የቡና እርሻውም እያደገ እና እየሰፋ ሲመጣ በርካቶች ሥራ ዕድል ተጠቃሚ ይሆናሉ።

አሁን ላይ ግን አንድ ነገር ይቆጨኛል። በዚያን ጊዜ የአካባቢያችን ሰዎች ለትምህርት ብዙም ትኩረት በማይሰጡበት ወቅት እናቴ ብቸኛ ልጇን ወደ ትምህርት ቤት ሂድ ብላ የመከረችበትና የዕውቀት ጥማቷን የገለፀችበት ብሎም ስስቷን ያሳየችበት የሸክላው አባባል በአዕምሮዬ ይመላለሳል። ዛሬ ሁሉን ነገር የኋሊት አስባለሁ። እናቴ ብትኖር ብዬ እመኛለሁ። ያለፍኩበትን ሁሉን ነገር ታውቃለች፤ ለእኔ ብዙ ተመኝታለች፤ በብዙ ደክማለች፤ አሁን የደረስኩበትን ግን ሳታይ ከዚህ ዓለም አልፋለች። የልፋቷን ፍሬ ብትመለከተው ብዬ አስባለሁ፤ ግን ፈጣሪ አይሳሳትም ብዬ እጽናናለሁ።

ደን እና ማዣንግ

ደን እና ማዣንግ የማይለያዩ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽዎች ናቸው። ደን ጠፋ ማለት ማጃንግ ጠፋ ማለት ነው። ደን ለእኔ ብሄረሰብ፣ ዞን፣ ሕይወትም ጭምር ነው። ማንነታችን የተመሰረተው እዚህ ላይ ነው። እኔም ይህ የሕይወታችን መሰረት የሆነው ደን እንዳይነካ ሌት ተቀን አስተምራለሁ፤ ከማህበረሰቡም ጋር በቅርበት እሰራለሁ። እኔም ብቻ ሳልሆን በርካታ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ደን እንዳይመነጠር የአካባቢውን ማህበረሰብ በማሰልጠንና በተለያዩ የስራ ዘርፎች በማሰማራት ኃላፊነታቸውን እየተወጡ ነው።

የዞኑም ሆነ የክልሉ መንግስትም በማጃንግ ዞን ያለው ደን እንደተጠበቀ እንዲቀጥል የሚሰሩት ስራ ተስፋ ሰጪ ነው። ማህበረሰቡም ከጥንት ጀምሮ ያዳበረው ደን የመጠበቅ ባህል ከፍ ያለ ነው። ይህ በመሆኑ ማር፣ ውብ ተፈጥሮ እና የተፈጥሮ ፏፏቴ ብሎም በደኑ ውስጥ ያሉ በረከቶች ሁሉም ለዛቸውን ጠብቀው ውበታቸው ፈክቶ ይቀጥላሉ ሲሉ ተስፋቸውን ይገልፃሉ።

ካፒታላቸው

በጥሬ ገንዘብ ምንም የለኝም ማለት ይቻላል ይላሉ። በጋምቤላ ከተማ እያንዳንዳቸው 400 ካሬ ሜትር ላይ ያረፉ ሁለት ቤቶች በተመሳሳይ ማጃንግ ዞን ሁለት ቤቶች አሏቸው። በጎደሬ ወረዳም በተመሳሳይ ቤቶች አሏቸው። በተወለዱበት ሰፈርም እርሻ እና የገጠር ቤት አላቸው። ከ400 ያላነሰ ቀፎ ብሎም የቡና እና የሙዝ እርሻ አላቸው። እነዚህ ተደምረው በትንሹ ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታል አለኝ ይላሉ። ይህ በጥናት እና በትክክለኛ ሂሳብ አያያዝ ላይ ቢመሰረት ከዚህ በላይ ነው። እኔ ምኞቴ ካፒታል መቁጠር ብቻ ሳይሆን የማይሞት ራዕይ መትከል ነው። ከእኔ የተሻሉ ብዙ ሰዎች በአካባቢያችን፣ በዞናችንና በክልላችን እንዲኖሩ ነው። ሥራ ወዳድ ዜጋ ከተፈጠረ እና ጥረት ከታከለ ከካፒታል በላይ ደስታ ይሰጣል ሲሉ ይናገራሉ።

የደመወዝ ነገር

1994 ዓ.ም የወር ደመወዛቸው 450 ብር ነበር። 20 ዓመት አገልግለው በመጨረሻ የሥራ መልቀቂያ ሲያስገቡ ደመወዛቸው 15 ሺ ብር ነው። በአሁኑ ወቅት ደግሞ በቀን ከአንድ ሺ 500 እስከ ሁለት ሺ ብር አገኛለሁ። ይህን ሳነፃፅረው ይገርመኛል ይላሉ። ይሁንና ሕዝቤ አምስት ጊዜ መርጦኝ ምክር ቤት አገልግያለሁ። ምንም እንኳን ገንዘብ ባላገኝም ኃላፊነቴን ስለተወጣሁ ደስተኛ ነኝ፤ አልቆጭም። ፈጣሪ ይመስገን፤ ጎደለኝ የምለው የለም። አሁን የ43 ዓመት ጎልማሳ ነኝ። ከመጣሁት ይልቅ የምሄደው መንገድ ሩቅ እንደሆነ ስለሚሰማኝ ብዙ ጊዜ ማባከን አልፈልግም። በዕድሜዬ ብዙ ሮጬ፣ በብዙ ደክሜ ብዙ ሃብት ማፍራትና መለወጥ እፈልጋለሁ። እኔም ብቻ ሳልሆን ሌሎችም የእኔን አርዓያ ተከትለው የተሻለ እንዲሆኑ እጥራለሁ። ይህን የማደርገው ደግሞ አንድ ሰው ለመኖር እንደ ዜጋ አለፍ ሲል ደግሞ ሀገራዊ ኃላፊነቴን ለመወጣት እና ከሕሊና ወቀሳ ለመዳን ነው።

መልዕክት

ለጋምቤላ ክልል ብሎም ለአጠቃላይ ወጣቶች ምክር አለኝ ይላሉ – አቶ ቲቶ ሐዋርያት። ‹‹ወጣቶች በጊዜያችን እንጠቀም፤ ስራ መናቅ የለብንም፤ የሥራ ትንሽ የለም። አንድ ሰው ሩቅ መሄድ ካሰበ ጉዞው የሚጀመረው በአንዲት እርምጃ ነው። ለአንድ እርምጃም አንድ እግሩን የግድ ማንሳት አለበት›› ይላሉ። ተስፋ መቁረጥ፣ የተሸናፊነት ስሜት በወጣት ልብ ውስጥ መኖር የለበትም።

በከተማችን በርካታ ወጣቶች አልባሌ ቦታ እየዋሉ በመሆኑ ወደ ሥራ ማተኮር አለባቸው። ዓለም የምትቀየረው በሥራ እና በሥራ ፈጣሪ እጆች ነው። ለፈጠራ እና አዳዲስ ሃሳቦች በራችን ዝግ መሆን የለበትም። ሕይወት መስመሯ ብዙ ነው። በሮቿ ብዙ ናቸው። እነዚህን በሮች ማንኳኳት ይገባል። ሁሉም በር ባይከፍት በደንብ ደጋግመን ያንኳኳናቸው በሮች እንደሚከፈቱ እርግጠኛ መሆን አለብን። በመሆኑም ጥረት፣ እውቀትና ጥበብ ይዘን መስራት አለብን። እኔ ይህን ምክር ደጋግሜ መናገር የምፈልገው ለጋምቤላ ከተማ ወጣቶች ነው። በጊዜያችን ሰርተን፣ ለራሳችን ሰርተን፣ ራሳችንን እንጠቀም።

ክፍለዮሐንስ አንበርብር

አዲስ ዘመን ሐምሌ 7 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You