ከኢትዮጵያ በበለጠ ለሶማሊያ ሕዝብ ዋጋ የከፈለ ማን አለ ?

ሶማሊያ ባለመረጋጋትና በግጭት ውስጥ የምትኖር ሀገር ነች። ከዚያም አልፎ መንግስት አልባ ሆና ዘመናትን ተሻግራለች። በእነዚህ የመከራ ዓመታት ግን የኢትዮጵያ ሕዝብ ከሶማሊያ ሕዝብ ጎን ተለይቶ አያውቅም።

በፊት ‘AMISOM’ አሁን ደግሞ ‘ATMIS’ እየተባለ በሚጠራው የአፍረካ ኅብረት የሶማሊያ ሰላም ማስከበር ተልዕኮ በኩል ኢትዮጵያ ለሶማሊያ ሰላም ጉልህ አስተዋጽኦ ስታደርግ ቆይታለች። በዚህ ተልኮም አብዛኛውን የሶማሊያ መሬት በመሸፈንና ከጥቃት በመከላከል የሶማሊያ ሕዝብ በሰላም ወጥቶ እንዲገባ፤ የሶማሊያ መንግስትም ተረጋግቶ መንግስታዊ ስራዎችን እንዲያከናውን በማድረግ ላይ ይገኛል።

በአንድ ወቅት የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ እንደተናገሩት 60 በመቶ የሚሆነውን የሶማሊያ ክፍል የሚጠብቀውና ከአልሻባብ ጥቃት የሚከላከለው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ነው። ኢትዮጵያ በሶማሊያ ጠንካራ መንግሥት እንዲፈጠር መስዋዕትነት ስትከፍል ቆይታለች። አልሻባብ የሁለቱም የጋራ ጠላት መሆኑ ደግሞ ሁለቱ ሀገራት በጋራ እንዲቆሙ የሚያስገድድ ነው።

የኢትዮጵያን የሶማሊያ ግንኙነት ከዚህም በላይ ነው። የሁለቱ አገሮች ሕዝቦች በሁለት አገሮች የሚኖሩ አንድ ሕዝቦች ናቸው። ዕጣ ፈንታቸው የተሳሰረ ነው። ወደ 16 ሚሊዮን ሕዝብ ያላት ሶማሊያ እ.ኤ.አ. በ2020 ወደ 294 ሚሊዮን ዶላር የሚገመት ሸቀጣ ሸቀጥ ከኢትዮጵያ አስገብታለች። የንግድ ልውውጡም እያደገ እንደሚሄድ ይታመናል።

ሆኖም አሁን ያለው የሶማሊያ መንግስት ይህን ሁሉ የተመለከተ አይመስልም። የኢትዮጵያ መንግስት ወደብና የባህር በር ለኢትጵያ ወሳኝ መሆኑንና የጎረቤት ሀገራትም ኢትጵያን እንዲተባበሯት ተደጋጋሚ ጥያቄ ቢያቀርብም በግልጽ የተቀበለ ሀገር የለም። ስለዚህም በርካታ አማራጮችን በማማተር ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ መንግስት የጋራ ተጠቃሚነትን መርህ በመንተራስ ከሶማሊ ላንድ ጋር የጋራ መግባቢያ ሰነድ ተፈራርሟል። ይህ ስምምነት ደግሞ ከወዲሁ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት እያገኘ መጥቷል። በታዋቂ ሰዎች፤ በዲፕሎማቶችና በፖለቲከኞች ጭምር ተገቢነቱ እየተነገረ ነው።

የኢትዮጵያ ወደብ አልባ መሆንም ከስነልቦናዊ ቀውስ ባሻገር ለበርካታ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ጫና ሕዝቡ እንዲጋለጥ አድርጎታል። የኢትዮጵያን ክብር እና ዝና ዝቅ እንዲል ከማድረጉም ባሻገር በኢኮኖሚ ረገድም ተጎጂ እንድትሆን አድርጓታል። ለበርካታ መሰረተ ልማቶችና ለድህነት መቀነሻ ልማቶችን ይውል የነበረውን ከ1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር በላይ በየዓመቱ ለወደብ ብቻ በማዋል በድህነት ውስጥ እንድትማቅቅ አድርጓታል።

ኢትዮጵያ ወደብ አልባ በመሆኗ ለኪራይና ለመጓጓዣ ከፍተኛ ዶላር ስለምታወጣ የሸቀጦች ዋጋ እንዲንርና የኑሮ ውድነትም እንዲባባስ ምክንያት ሆኗል። በዲፕሎማሲ እና በተጽዕኖ ፈጣሪነትም ረገድ የኢትጵያ ሚና አሽቆልቁሏል። በዚህ ሁኔታ ውስጥ መቀጠል ስለማይቻል መንግስት ሰላምን መሰረት ያደረገ አዲስ የባህር በር አማራጭ ይፋ አድርጓል።

ይህ የመግባቢያ ሰነድ ሲተገበር አካባቢያዊ መረጋጋት የሚያመጣና ኢትዮጵያም በቀጣናው ላይ አለኝ የምትለውን የባለቤትነት ጥያቄ መልስ እንዲገኝ በር የሚከፍት ነው። ቀጣናዊ ሰላምን በማስፈን የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ የተረጋጋ እንዲሆን በር ይከፍታል። የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊስ ቅድሚያ ትኩረት የሚሰጠው ለጎረቤት ሀገሮች ነው። በተለይም ለቀጠናዊ ግንኙነት የመጀመሪያውን ትኩረት በመስጠት ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር የጠበቀ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዲኖራት ተደርጓል።

የኢትዮጵያ ልማት በአስተማማኝ መሠረት የሚቆመው የኢትዮጵያ የውስጥ ሰላምና መረጋጋት ሲረጋገጥ እንደሆነ እና ይኸው ሰላምና መረጋጋት የሚጸናው ደግሞ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ሰላማዊ ግንኙነትን በማዳበርና የአገራቱ ሰላምና መረጋጋት ሲረጋገጥ ነው። ለዚህም ከጎረቤት አገራት ጋር በወዳጅነት፣ በትብብርና ኢኮኖሚያዊ ትስስርን በሚያመጣ መልኩ የተቃኘ ዲፕሎማሲ ኢትዮጵያ በመከተል ላይ ትገኛለች።

ኢትዮጵያ ለሶማሊ ላንድ የሰጠችውን ዕድል ለሌሎች የሰጠች ቢሆንም የተጠቀመችበት ግን ሶማሊላንድ ብቻ ነች። ዋናዋ ሶማሊያም የዚህ ዕድል ተጠቃሚ የመሆን ዕድል አላት። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሰሞኑን በፓርላማ ተገኝተው እንዳሉት ‹‹የሶማሊያ መንግስት በአንድ ሰዓት በረራ እና በአንድ ሰዓት ውይይት ይህን ነገር መልክ ማስያዝ ይችላል። በጣም ቀላል ነገር ነው።

ምክንያቱም ከሶማሌ መንግስት ጋር ምንም ጸብ የለንም። የሶማሌ መንግስት የመረጠው ግን እኛን ከማናገር በየሰፈሩ እየዞረ እኛን መክሰስ ነው። ያለኝ ምክር ብር አታብክኑ ነው። በየ ሀገሩ ስንሄድ፤ በጣም ብዙ ወጪ ይወጣል፤ ብር ከምናባክን እሱን ሰብሰብ አድርገን አንድ ኪሎ ሜትር ዎክ ዌይ ብንሰራበት፤ አንድ ትምህርት ቤት መቋዲሾ ብንሰራበት ሕዝብ ይጠቅማል።

እኛን ለመክሰስ ሀገር ለሀገር መሄድ አያስፈልግም። አዲስ አበባ መምጣት ይቻላል። ለመነጋገር ዝግጁ ነን። ሶማሊያ እንድትጎዳ፤ እንድትፈራርስም፤ እንድትበተንም የሚፈልግ መንግስት አይደለም። ቢሆን ልጆቹን ልኮ አይሞቱም። የኢትዮጵያ መንግስት ጥያቄ የባህር በር ጥያቄ ነው። ይህ ህጋዊ ጥያቄ ነው። ይህን በሰላማዊ እና በንግግር መልኩ እንደማንኛውም /ኮሚዲቲ/ ሸቀጥ ለመቀበል ኢትዮጵያ ዝግጁ ነች።

ለምሳሌ ወይ ሶማሌ፤ ወይ ጅቡቴ ወይም ሌሎቹ፤ የባህር በር አላቸው፤ ግን እንደ ኢትዮጵያ ሊያመርቱ አይችሉም። እኛ የተሻለ መሬት አለን፤ የተሻለ ውሀ አለን፤ ኢነርጂ ምግብም፤ ከኛ አቦካዶ ከእርነሱ፣ ከእነሱ ውሀውን ብንጋራ ምንም ችግር የለውም፤ ንግድ ነው። ተጠቅመው፣ ተጠቅመን፤ አድገው አድገን፣ ተባብረን አብረን ብንሄድ ለአካባቢው ለልጆቻችንም ጠቃሚ ነው። እናንተ እንዲህ ዓይነት ጥያቄ አታንሱ ቢባል ግን፤ ጥያቄ አታንሱ ብለህ የምታፍነው ጉዳይ አይደለም፤ እውነት እስከሆነ ድረስ ጊዜውን ጠብቆ ይወጣል።›› ሲሉ መልዕክት ማስተላለፋቸው የሚታወስ ነው።

ስለዚህም በአሁኑ ወቅት 120 ሚሊዮን ሕዝብ በ2050 አካባቢ ደግሞ በዕጥፍ የሚያድግ ሕዝብ ተይዞ ‹‹ስለቀይ ባህር እና ስለ ወደብ አታንሳ፤ ዝም ብለህ ተቀመጥ›› የሚል አፋኝ አመለካከት ሊኖር አይገባም። የሶማሊያ መንግስት ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የተፈራረመችውን የመግባቢያ ሰነድ ማክበር አሊያም ደግሞ የራሷን የባሕር በርና የወደብ አማራጮች ማክበር ይገባታል። ከሁለቱ ውጭ መሆን ግን በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያውያን የሚቀበሉት አይደለም።

ሶማሊያ በሺዎች ኪሎ ሜትር የሚቆጠር የባሕር በር አላት። ግን ይህ ሁሉ ኪሎ ሜትር ለሶማሊያ ወደብ ሆኖ ሊያገልግል የሚችል አይደለም። ስለዚህም ሶማሊያ ከኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ተጠቃሚ ለመሆን ከፈለገች ወደብ ከኢትዮጵያ ጋር ማልማት ትችላለች። ወይንም ደግሞ ለም መሬት ወስዳ በምትኩ ወደብ ልታቀርብልን ትችላለች። ብቻ አማራጩ ብዙ ነው።

ዘይላ ሶማሊያ እንደሀገር ከመፈጠሯ በፊት ኢትዮጵያ የምትጠቀምበት የባሕር በር ነው። ከዛግዌ መንግስት ጀምሮ ኢትዮጵያ በወደቡ ስትጠቀም ኖራለች። ለኢትዮጵያ ቅርበት አለው። ከሞቃዲሾ በርካታ ኪሎ ሜትሮችን የሚርቅ ስለሆነ ሶማሊያ ልትጠቀምበት አትችልም። ስለዚህም መነጋገር ከተቻለ በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኘውን የዘይላን ወደብ ኢትዮጵያ ብትጠቀምበት እና ሶማሊያም በምትኩ ጥቅም ብታገኝ ሁለቱም ሀገራት አሸናፊ መሆን ይችላሉ።

ከዚህ በተረፈ ግን የኢትዮጵያን ፍላጎት አፍኖ አሸናፊ መሆን አይቻልም። ለሶማሊያ ሕዝብ በርካታ ውለታ ለዋለችው ኢትዮጵያ በየስፍራው እየዞሩ ስም ማጥፋትና በኢትዮጵያን ላይ ሀገራት የተሳሳተ አቋም እንዲይዙ ለማድረግ የሚደረገው ጥረት የኢትዮጵያን ውለታ የዘነጋ ነው። ሰሞኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በፓርላማ ተገኝተው እንደተናገሩት የሶማሊያን ሕዝብ ለመታደግ ሲባል ኢትዮጵያ በርካታ ወታደሮቿን አጥታለች።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት የሶማሌ ሕዝብ፤ የሶማሌ ጎሳዎች በአብዛኛው በእኛ ውስጥ ስላሉ ጎረቤት ብቻ ሳይሆን ወንድሞቻችን ናቸው። ለሶማሊያ ሰላም ሞተናል፤ ለሶማሊያ አንድነት ሞተናል። ለሶማሊያ ያለንን ክብር፤ ብልጽግና ከማንም መንግስታት በላይ አሳይተናል።

ሶማሌን እንደ ኢትዮጵያዊ ቆጥረን የደገፍነው እኛ ነን። በሶማሌ አንድነት የኢትዮጵያ መንግስት ጥያቄ የለውም። በእኛ እና በሶማሌ ላንድ መካከል የተደረገው የመግባቢያ ስምምነት ለሁሉም ጎረቤቶቻችን ያቀረብነው ጥያቄ፤ ሁሉን ጠይቀን ምላሽ ስናጣ ከመለሰልን አካል ጋር ተፈራረምን እንጂ፤ ከሶማሊያ አንድነት ጋር የተያያዘ ጥያቄ አይደለለም ብለዋል።

ሆኖም የሶማሊያ መንግስት ይህን ሁሉ በመዘንጋት ወይም ለኢትዮጵያ ውለታ ፊቱን በማዞር ከኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር አብሮ እየሰራ ነው። ከዚያም አልፎ ሰማሊያ ውስጥ ያለው የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ኃይል እንዲወጣ ጥያቄ አቅርቧል። ይህ ደግሞ አልሸባብ እንደገና እንዲያንሰራራ እና የሶማሊያ ህዝብ ዳግሞ ለስቃይ እንዲዳረግ መፍቀድ ነው። ከዚህም አልፎ የምሰራቅ አፍሪካ ቀጣና የአሸባሪዎች መናኸሪያ እንዲሆን በማድረግ የበለጠ የግጭትና የጦርነት ቀጣና እንዲሆን በር የሚከፍት ነው።

የሶማሊያ መንግስት ይህንን ባስታወቀ በጥቂት ቀናት ውስጥ፤ በሞቃዲሾ አካባቢ አምስት የሚሆኑ ወታደሮቹ ተገድለውበታል፤ በርካቶች ቆስለዋል። ስለዚህም የኢትዮጵያ ወታደሮች በሶማሊያ ውስጥ መቆየታቸው የሶማሊያን ሰላምና ጸጥታ አስተማማኝ ከማድረጉም ባሻገር ተሰማርቶ ለሚገኘው የሰላም አስከባሪ ኃይል ትልቅ አቅም የሚሆነው ነው።

ባለፉት 15 ዓመታት እንደታየውም የሶማሊያን ሰላምና ጸጥታ የማስከበር አቅም ያለው የኢትዮጵያ የጸጥታ ኃይል ብቻ ነው። የኢትዮጵያ የጸጥታ ኃይል በሶማሊያ ተልዕኮ ወስዶ ከተሰማራ በኋላ አሸባሪው አልሸባብ ክፉኛ ከመዳከሙም በላይ በአዲስ አበባ በተካሄዱ ተደጋጋሚ ውይይቶች ሶማሊያ አዲስ የሆነ መንግስት እንድትመሰርት አስችሏታል። እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስም የኢትዮጵያ የጸጥታ ኃይል 60 በመቶ የሚሆነውን የሶማሊያን ክፍል ከአልሻባብ ጠብቆ መንግስቷም የተሻለ መረጋጋት እንዲኖረው አስችሎ ቆይቷል።

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2008 የሶማሊያ መንግስት ሲቋቋም ቀድማ ኤምባሲ የከፈተችና ዕውቅና የሰጠችው ኢትዮጵያ ናች። በተለያዩ ጊዜያትም በሶማሊያ ሰው ሰራሽና ተፈጥሮ አደጋዎች ሲያጋጥሙ የሶማሊያ ሕዝብን በሯን ከፍታ የምትቀበለው ኢትዮጵያ ብቻ ነች። ታዲያ ይህንን ሁሉ ውለታ ለምትውለው ኢትዮጵያ የሶማሊያ መንግስት በተቃራኒው እየሰራ ያለው ኢትዮጵያን የማጠልሸት ዘመቻ እንቆቅልሽ ሆኖ ዘልቋል።

እስማኤል አረቦ

አዲስ ዘመን  ሐምሌ 7 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You