የ2024 ፓሪስ ኦሊምፒክ ሊጀመር ከሁለት ሳምንት ያነሰ ጊዜ ቀርቶታል። በዚህ ዓለም በጉጉት በሚጠብቀው ትልቅ የስፖርት መድረክ ከመካከለኛ እስከ ረጅም ርቀት እንዲሁም ማራቶን ድረስ ስሟን የሚያስጠሩ ከዋክብት አትሌቶች አጥታ የማታውቀው ኢትዮጵያ ውጤታማ ይሆናሉ ተብለው ከሚጠበቁ አገራት ቀዳሚ ነች።
ሀገሪቱ በኦሊምፒኩ ከፍ ብላና በውጤት አሸብርቃ ለመታየት እንቁ አትሌቶችን ታድላ ያጣችው ነገር ባይኖርም በዚህ ወቅት ትኩረቷ ውድድሩ ላይ ሳይሆን ፤ ባለፉት ዓመታት እንደተስተዋለው በአስተዳደራዊ ንትርኮች ላይ መሆኑ ግን በብዙ መልኩ ዜጎችን እያነጋገረ ይገኛል ።
በአሁኑ ሰዓት በኦሊምፒክ የሚሳተፉ ከሁለት መቶ በላይ አገራት ድምፃቸውን አጥፍተው ውጤታማ የሚያደርጓቸው ስራዎች ተጠምደዋል። ከነዚህ አገራት መካከል በተለያዩ አስተዳደራዊ ጉዳዮች ላይ የሚነታረክና ውዝግብ ውስጥ የሚገኝ አንድም አገር ፈልጎ ማግኘት አይቻልም።
እኛ ግን ዓለም ሁሉ የሚቀናባቸው አትሌቶችን ታቅፈን ለዚህ አልታደልንም ። ትኩረቱ ሁሉ አገር በታላቁ የስፖርት መድረክ ከዚህ ቀደም ከነበራት የተሻለ ውጤት እንዴት ታስመዝግብ ሳይሆን ስፖርቱን የሚመሩ አካላት በፈጠሩት ዝርክርክ አሰራርና አስተዳደራዊ ጉዳይ ላይ ከሆነ ውሎ አድሯል።
ለችግሩ መነሻ የሆነው የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴና አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አመራሮች ከሕግና ከመርህ ባፈነገጠ አካሄድ የፈጠሩት ቀውስ ነው። ሁለቱን የስፖርት ተቋማት የሚመሩ ግለሰቦች ብዙ ነገሮችን ስተዋል። እያንዳንዱን ነገር በዝርዝር ለማየት ጊዜ አለ። አሁን ግን ውድድሩ በጣት የሚቆጠሩ ቀናት ቀርተውታልና በዚህ ሁሉ ውጥንቅጥ ውስጥ ሆነን አትሌቶቻችን እንዴት ውጤታማ ይሁኑ የሚለው ጉዳይ ላይ ማተኮሩ ተገቢ ነው።
ለዚህም አንገብጋቢ በሆነውና የበርካታ እንቁ አትሌቶቻችንን እንባ እያፈሰሰ ትልቅ የሞራል ጉዳትም እያደረሰ የሚገኘው የአትሌቶች ምርጫ ዋጋ እንዳያስከፍለን በጥንቃቄ ማየት ያስፈልጋል። እንደ አለመታደል ሆኖ ነው እንጂ በዚህ ወቅት አገራችንን በታላቁ መድረክ እንዴት አጉልተን እናሳይ እንጂ የአትሌቶች ምርጫ ጉዳያችን ሊሆን አይገባም ነበር።
ያም ሆኖ በመርህ ሳይሆን በግለሰቦች ፍላጎትና በጥቅም ትስስር የሚመራው ኦሊምፒክ ኮሚቴና አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በአንድ አትሌት ላይ የፈፀሙትን በደል ያስተካከሉ መስሏቸው የነካኩት ነገር ሁሉ ለሌሎች በርካታ አትሌቶች በደል ምክንያት እየሆነ ይገኛል። ወትሮም ከሕግና ደንብ ውጪ የሚሰራ ነገር አንዴ ከእጅ ካፈተለከ ውጤቱ የከፋ እንደሚሆን ለማንም የሚደበቅ አይደለም ።
የዚህ ጽሁፍ ዋነኝ ዓላማም ፤ አስራ አንደኛው ሰዓት ላይ ሆነን ቢሆን፤ ቢያንስ ከዚህ በኋላ ሌላ ቀውስ እንዳይፈጠር እና ችግሩ የአገርን ውጤት ገደል ይዞ እንዳይወርድ ምን ይደረግ የሚለው ላይ ነው።
አሁን ላይ ሁላችንም እንደምንሰማው፤ ቀደም ሲል በተለያዩ ውድድሮች ይሳተፋሉ ተብለው ይፋ የተደረጉ አትሌቶች ሁለቱ የስፖርት ተቋማት መሪዎች በሚፈጥሯቸው ችግሮች በየቀኑ እየተፐወዙ፣ ቦታ እየቀተቀያየሩ ይገኛሉ። ትናንት በቋሚነት ይወዳደራል የተባለ አትሌት ዛሬ ተጠባባቂ ሲሆን፣ አትወዳደርም የተባለ አትሌት ደግሞ ድንገት ነጭ ላቡን እያፈሰሰ ለወራት ሲዘጋጅ በቆየ ሌላ አትሌት ሲተካ እያየን ነው።
በዚህ ርቀት ትሳተፋለህ ተብሎ ለወራት ሲዘጋጅ የቆየ አትሌትና አሰልጣኝ ድንገት የተዘጋጀበት ቀርቶ ባላሰበው ርቀት ትሮጣለህ ይባላል። የተቋማቱ አመራሮች ጩኸት ሲበዛባቸው የአንዱን እንባ አበስን ብለው የሌሎችን እያፈሰሱ ነው። በዚህም አትሌቶች፣ አሰልጣኞችና ክለቦች ቅሬታዎቻቸውን እየገለፁ ይገኛሉ።
አሁን ላይ በየትኛውም ርቀት ኢትዮጵያን በኦሊምፒክ ወክሎ ለመወዳደር እየተዘጋጀ የሚገኝ አትሌትም ይሁን አሰልጣኝ በተረጋጋ ሁኔታ ትኩረቱን ዝግጅቱ ላይ ብቻ አድርጎ እየሰራ አይደለም። ይህም አስፈላጊውን ዝግጅት ከማስተጓጎሉ በስነ-ልቦናም ረገድ ትልቅ ችግር መፍጠሩ አልቀረም።
የአትሌቶቹን ምርጫ በየጊዜው እየቀያሩ የሚገኙት የሁለቱ ተቋማት አመራሮች ችግር በዚሁ ቢያበቃ ጥሩ ነው። እንደ አያያዛቸው ግን አይመስልም፤ ድንገት ውድድሩ ሰዓታት ሲቀሩት የሚቀይሩት ሃሳብ ሊኖር እንደሚችሉ መገመት ሞኝነት አይመስለኝም። ለዚህ ደግሞ ባለፉት ዓመታት ውድድሮች ላይ የነበረውን ተሞክሮ ማስታወስ በቂ ነው።
ይህ አካሄድ በኦሊምፒኩ አገርን ዋጋ እንደሚያስከፍልና ውጤት እንደሚያሳጣ ለመናገር የስፖርት ተንታኝ መሆን አይጠይቅም። የሁለቱ የስፖርት ተቋማት አመራሮችም ይህን የሚያጡት አይመስለኝም። በዚህ ባለቀ ሰዓት ላይ ሆነው እንኳን ቢያንስ ተጨማሪ ስህተት ላለመስራት መቆጠብ ይጠበቅባቸዋል።
ባለፉት ዓመታት በተመሳሳይ የስፖርቱ አመራሮች ንትርክና ውዝግብ ውጤት ሲጠፋ “ኦሊምፒክ መድረክ ላይ መሳተፍ በራሱ ስኬት ነው፣ እኛ ነን የብርና የነሐስ ሜዳሊያ የምንንቀው፣ የእኛን ውጤት ያላገኙ ብዙ አገራት ይቀኑብናል” የሚል የስላቅ መልስ ከተጠያቂነት ማምለጫ ነበር።
ዘንድሮ ግን ይሄን መስማት የሚፈልግ ኢትዮጵያዊ ያለ አይመስለኝም ። እኛ መገለጫችን ወርቅ ነው። እኛ የአበበ ቢቂላ፣ ኃይሌ ገብረስላሴ፣ ቀነኒሳ በቀለ፣ ጥሩነሽና መሰረትን የመሳሰሉ ከዋክብቶች መፍለቂያ እንጂ ሌላ አይደለንም። አሁንም ኢትዮጵያ እነዚያን ዘመን የማይሽራቸው የኦሊምፒክ ፈርጦች ያፈራ ማህፀኗ ለምለም ነው።
አገራቸውን በደምና ላባቸው ውድ ዋጋ ከፍለው ከፍ ማድረግ የሚችሉ አቅሙም ብቃቱም ያላቸው ብዙ ወጣት ከዋክብት አላጣችም። ሳታጣ ያጣችው ከራሳቸው ጥቅም ይልቅ በቅንነት ስፖርቱን የሚመሩ ሰዎችን ነው። እነዚህ ሰዎች ኦሊምፒክ ለኢትዮጵያ ምን ማለት እንደሆነ በቅጡ የተረዱት አይመስልም፡፡
ኦሊምፒክ የኢትዮጵያውያን አልሸነፍ ባይነት፣ ጀግንነት የሚገለጥበት፣ በገንዘብ የማይተመን ገፅታ መገንቢያ፣ አንገታችንን ቀና እድርገን የምንሄድበት ሌላም ሌላም መሆኑን ስተዋል። ይድነቃቸው ተሰማን የመሳሰሉ ከኢትዮጵያ አልፈው ለአፍሪካ ስፖርት እንደ አባት የሚቆጠሩ በስፖርት አመራርነት የተከበሩ ሰዎችን ማፍራት በቻለች ሀገር እንዲህ አይነት የአመራር ጉራማይሌ መታየቱ ብዙዎችን የሚያሳዘን ነው።
እዚህ ላይ ሊታሰብበት የሚገባ ዋንኛ ጉዳይ ከየትኛውም ግለሰብ ማንነት በስተጀርባ የሚገኝ ለሀገር ጥቅም እና ብሄራዊ ክብር ያልተገዛ ስብእና በምንም መልኩ ተቀባይነት ሊኖረው እንደማይችል ነው። እንዲህ አይነቱ ስብእና ሊፈጥረው የሚችለው ጥፋት የታሪክ የሞራል እና የሕግ ተጠያቂት ይዞ እንደሚመጣም ማሰብ ተገቢ ነው።
አሜን ከካምቦሎጆ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 7 ቀን 2016 ዓ.ም