የመስኖ ልማቱ የ30 ዓመት ፍኖተ ካርታ

የኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይ በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ከፍተኛ መጠን ያለው የስንዴ ምርት እያገኘች ነው። ለአብነትም ዘንድሮ ከ100 /ከአንድ መቶ/ ሚሊዮን ኩንታል በላይ ስንዴ በበጋ መስኖ ልማት ብቻ ማግኘት ተችሏል። ይህ የተገኘውም በሶስት ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ ልማቱን በማካሄድ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ። በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት በኩልም እንዲሁ የመስኖ ልማቱ በስፋት እየተካሄደ ይገኛል።

ይህ ልማት ግን ሀገሪቱ ካላት የውሃና በመስኖ ሊለማ ከሚችል ሀብት አኳያ ሲታይ ብዙ የሚባል እንዳልሆነ የዘርፉ ባለሙያዎች ያመለክታሉ። በመስኖ መሠረተ ልማት የተከናወነው ተግባር ዜሮ ነጥብ አምስት በመቶ ብቻ መሆኑን ይጠቁማሉ።

ሀገሪቱ ያላትን ከፍተኛ ለመስኖ ልማት ሊውል የሚችል አቅም በመጠቀም የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚረዳ የመስኖ ፍኖተ ካርታ እያዘጋጀች ትገኛለች። ለቀጣይ 30 ዓመታት ሥራ ላይ ሊውል የሚችለው ይህ ፍኖተ ካርታ በየ10 ዓመቱ በተከፋፈሉ ፕሮግራሞች ተግባራዊ እንደሚደረግ ፍኖተ ካርታውን አስመልክቶ በቅርቡ ከተካሄደ መድረክ መረዳት ተችሏል።

ፍኖተ ካርታው ሀገሪቱ የግብርና ክፍለ ኢኮኖሚዋን የበለጠ በማሳደግ ከዘርፉ ተጠቃሚ ለመሆን እንደሚያስችላት ታምኖበታል። በመስኖ እና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስቴር በኩል የሀገራዊ መስኖ ልማት ተግዳሮቶችን በመለየት እና ባልተቀናጀ መልኩ ይደረጉ የነበሩ የመስኖ ልማት ጥረቶችን የሚያቀናጁ ፣ የዘርፉን አቅም የሚያሳድጉ ፕሮግራሞች በእቅድ ተይዘዋል። ፕሮግራሞቹ ተፈፃሚ የሚሆንባቸው እና በተለይ የግሉን አቅም የሚያሳድጉ ሥራዎችም እየተዘጋጁ ናቸው።

ከሰሞኑ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ቴክኖሎጂ እና ማኔጅመንት ባለሙያዎች ማህበር ከመስኖ እና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር ጋር በመሆን በዋነኛነት አሁን ያለውን የመስኖ ልማት ካለበት ደረጃ ወደ ተሻለ የመስኖ ትራንስፎርሜሽን ለማሳደግ ያለመ ኮንፍረንስ ተካሂዷል። በመድረኩ ጥናታዊ ፅሁፎች የቀረቡ ሲሆን፤ ከአማካሪ ድርጅቶች፣ ኮንትራክተሮች፣ የምርምር ተቋማት እና ዩኒቨርሲቲዎች የመስኖ ዘርፉን መሠረተ ልማት ለማሳደግ የሚያግዙ ገንቢ ሃሳቦች እና ጥናቶች ቀርበዋል።

በመስኖና እና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር የመስኖ ምርምር ዴስክ ኃላፊ አቶ ያሬድ ሙላቱ ፣ በሀገሪቱ እየጨመረ የመጣውን የሕዝብ ብዛትና የተመጣጠነ ምግብ /ዳያትሪ/ ፍላጎት ለማሟላት በፈረንጆቹ 2050 በአውሮፓውያን አቆጣጠር በ2022 የተመረተውን እህል መጠን በአራት እጥፍ ማሳደግን የግድ እንደሚል ይገልጸሉ። ለእዚህም በዝናብ ላይ ተመስርቶ የሚመረተውን የእህል መጠን በከፍተኛ ደረጃ ለማሳደግ መሥራቱ እንዳለ ሆኖ፣ የመስኖ መሠረተ ልማትን በከፍተኛ ደረጃ ማስፋፋት ያስፈልጋል።

ሚኒስቴሩ የመስኖ ልማትን ለማስፋፋት ፕሮጀክቶችን እየነደፈ ሲሠራ መቆየቱን አስታውቀው፣ የመስኖ ፍኖተ ካርታ እያዘጋጀ መሆኑንም አመልክተዋል። ሀገሪቱ በመስኖ መልማት የሚችል አስር ሚሊዮን ሄክታር ያህል መሬት እንዳላት ጠቅሰው፣ እስካሁን የለማው ግን እጅግ ዝቅተኛው መሆኑን ጠቁመዋል።

ለእዚህ ምክንያት ከሆኑት መካከል ተቀናጅቶ አለመሥራት አንዱ መሆኑን ጠቅሰው፣ የመስኖ ልማት ዲዛይንና ጥናት፣ ኮንስትራከሽን ሥራዎች፣ ምርምሮችና የመሳሰሉት ተቀናጅተው በእቅድ ካልተመሩ በስተቀር የሚፈለገውን ለውጥ ማምጣት አይቻልም ሲሉ አቶ ያሬድ አስታውቀዋል። በዘርፉ ውጤታማ ለመሆን ኢትዮጵያ በመስኖ ልማቷ የዛሬ አምስት ዓመት የት ትድረስ? የዛሬ 10 ዓመት የት ትድረሰ የሚለውን በመያዝ መጓዝ ያስፈልጋል። ከዚህ አኳያ ፍኖተ ካርታ መዘጋጀቱ የጎላ ሚና እንደሚኖረውም አመልክተዋል።

ከመስኖ ልማት አኳያ ያለንን የተፈጥሮ ሀብት በመረዳት ረገድ ክፍተቶች አሉብን ያሉት አቶ ያሬድ፣ ሀገሪቱ ከፍተኛ የገፀ ምድር የውሃ ሀብት ቢኖራትም በመስኖ መሠረተ ልማቱ ላይ ሰፊ ተግዳሮቶች እንደነበሩ ጠቅሰዋል። አብዛኛዎቹ ተግዳሮቶችም በሀገሪቱ ከዝናብ ከሚገኘው ውሃ 70 በመቶው በሶስት ወራት ውስጥ ፈሶ እንደሚያልቅ ጠቁመዋል። ይህን ተከትሎም ለዘጠኝ ወራት ያህል የውሃ እጥረት ይከሰታል ብለዋል።

እሳቸው እንዳሉት፤ የሀገሪቱ የተፈጥሮ አቀማመጥ ከፍያለ ስለሆነም ከምታገኘው የዝናብ ውሃ 96 በመቶ ያህሉ ወደ ጎረቤት ሀገራት ይሄዳል። ይህም ትልቁ ተግዳሮት ነው። በመሆኑም በመስኖ ዘርፉ የጎረቤት ሀገራትን ተጠቃሚነት ታሳቢ ባደረገ መልኩ ውሃውን መጠቀም ያስፈልጋል።

በሀገሪቱ በመስኖ ዘርፉ ባሉ ባለድርሻ አካላት በኩልም የግንዛቤ ክፍተቶች መኖራቸውን አቶ ያሬድ ያመላከታሉ። የግብርና ዘርፉ አሁን በያዝነው መንገድ የት ያደርሰናል የሚለው ሲታሰብ እጥረት እንዳለም ጠቅሰው፣ መስኖ የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን የግድ አስፈላጊ ነው በሚለው ላይ ትልቅ የግንዛቤ እጥረት አለ ሲሉ ይጠቁማሉ። የተቋማት እና ባለድርሻ አካላት የአቅም እጥረት ሌላው ተግዳሮት መሆኑን ገልጸው፣ ከመንግሥት ተቋማት ጀምሮ መስኖ ላይ እየሠሩ የሚገኙ የልማት ድርጅቶች የአቅም እጥረት እንዳለባቸው ጠቁመዋል። የግል ዘርፉ ተሳትፎ አነስተኛ መሆኑን አመልክተዋል።

እሳቸው እንዳስታወቁት፤ እነዚህን ተግዳሮቶች ለመፍታት ፕሮግራም ነድፎ፣ ፍኖተ ካርታ ቀርጾ መሥራት ያስፈልጋል። በሌላ በኩል የሙያ ብቃት እጥረት አለ። ይሄንንም ችግር ለመፍታት ከልማት ድርጅቶች /የልማት ተቋማት/ ጋር በመናበብ ባለሙያዎችን ብቁ በማድረግ በተለይ ተግባር ተኮር እውቀት እና ክህሎት እንዲኖራቸው በማድረግ በኩል ክፍተቶች ይታያሉ። በአሁኑ ወቅትም እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ባለድርሻ አካላትን የማቀናጀት ተግባር እየተከናወነ ይገኛል።

በመስኖ ልማት አንዱ ትልቁ ተግዳሮት ያለውን የመስኖ ሀብት በቁጥር አለማወቅ ነው ያሉት ኃላፊው፣ በዘርፉ ላይ በመንግሥት ተቋምም ሆነ በተለያዩ አካላት የተደረጉ ጥናቶች የተለያዩ ሆነው መቆየታቸውን ተናግረዋል። ያልተቀናጁ መረጃዎችን በመያዝ በተደረገው ግምታዊ ዳታ መሠረት የመስኖ ልማቱ በኢትዮጵያ በዚህ ዓመት አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ሄክታር ያህል መድረሱን አስታውቀዋል።

የሀገሪቱ የመስኖ አቅምን አስመልክቶ ሶስት ሚሊዮን እና አራት ሚሊዮን የሚሉ ብዙ ግምቶች እንደሚሰጡ አስታውሰው፣ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ባካሄዳቸው ጥናቶች ግን ይህ አቅም ወደ 10 ሚሊዮን ሄክታር አካባቢ እንደሆነ ጠቁመዋል። በመስኖ የለማው ግን የዚህ ከሩብ በታች መሆኑን ጠቅሰዋል።

እንደ አቶ ያሬድ ገለጻ፤ ሌላው ትልቁ ተግዳሮት ሥራ ላይ ያሉ ፕሮጀክቶች በሙሉ አቅም እየሠሩ አለመሆናቸው ነው። አብዛኛዎቹ ከመቶ በታች ናቸው። የውሃ እና የመስኖ ዘርፍ ሌላው አንዱ ትልቁ ክፍተት ቀደም ሲል በየራሳቸው ይካሄዱ የነበሩ ኮንፍረንሶች ያስከትሉት የነበረው የሀብት ብክነት ነው። በመሆኑም የተናበበ ውጤት በማስመዝገብ በኩል ክፍተት አለ።

የአሁኑን ወርክሾፕ ልዩ የሚያደርገውም መሬት ላይ ያለውን ሥራ እየሠሩ ያሉ የልማት ድርጅቶችን፣ አማካሪዎች፣ የግል ዘርፎች፣ ኮንትራክተሮች እንዲሁም የህንፃ እና የመንገድ ግንባታ ሲቪል ሥራ ላይ ያሉ እና የመስኖ ዘርፉንም ማገዝ የሚችሉ ባለድርሻ አካላትን ያሰባሰበ በመሆኑ ነው። የሚቀርቡት ጥናቶችም ተግባር ተኮር የሆኑና አማካሪ ድርጅቶችም ከራሳቸው እይታ በራሳቸው ጫማ ውስጥ ሆነው ለማየት ያስችላቸዋል። የመስኖ መሠረተ ልማት ፍኖተ ካርታ ዝግጅቱም በዋነኛነት እየተሠራ ያለው በሚኒሰቴር መሥሪያቤቱ ነው።

አሁን የሚኒስትሩ አማካሪዎች ፕሮጀክቱን እየመሩ እና ባለሙያዎችን እያስተባበሩ በእቅድ ደረጃ እየተሰራ ይገኛል ያሉት አቶ ያሬድ፣ ባለሙያዎችም ተሳትፎ ያደርጋሉ ብለዋል። በአቅም ግንባታ እና ቴክኖሎጂን ተግባራዊ ማድረግ ላይ ትኩረት ተሠጥቶታል ነው የሚሉት።

እሳቸው እንዳሉት፤ ቀደም ሲል ትኩረት ላልተሰጠው የግሉ ዘርፍም አቅም ይፈጥር ዘንድ አንድ ፕሮግራም ከዚህ ፍኖተ ካርታ ይመጣል ተብሎ ይጠበቃል። ይህም በዲዛይን፣ በኮንስትራክሽን፣ መስኖ ላይ ኢንቨስት በማድረግ፣ ፋብሪካዎችን በማቋቋም ጭምር የሚገለጽ ይሆናል። ይህም በፍኖተ ካርታው ይመጣሉ ተብለው ከሚጠበቁትና እንደ ንድፈ ሃሳብ ከተያዙት አምስት ፕሮግራሞች መካከል አንዱ መሆኑን አመላክተዋል።

ኢትዮጵያ 125 ቢሊዮን ኩዩቢክ ሜትር አካባቢ በገፀ ምድሯ ላይ የሚፈስ የውሃ ሀብት አላት፤ አንድ ትሪሊዮን ኩዩቢክ ሜትር ውሃም ከዝናብ ታገኛለች። ከዚያ ውስጥ በወንዞቿ 124 ቢሊዮን ሜትር ኩዩቢክ አካባቢ ውሃ ይፈሳል። ከዚህ ውስጥም 96 ቢሊዮን ኪዩቢከ ሜትር ውሃ ወይም 80 በመቶው ውሃ ወደ ውጭ ሀገሮች ይሄዳል።

ከዝናብ ከሚገኘው ውሃ አንፃር በመስኖ የምንጠቀመው ከ10 ቢሊዮን ኪዩቢከ ሜትር በታች ነው ያሉት አቶ ያሬድ፣ ይህም ከዝናብ ውሃ ከአንድ በመቶ በታች ነው ይላሉ። የዓለም የምግብና ግብርና ድርጅት /ፋኦ/ 2016 እ. አ.አ በመስኖ ላይ ያካሄደውን ጥናት ዋቢ አድርገው ሲያብራሩም፣ በሀገሪቱ ወንዞች ከሚፈሰው 124 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ፣ ዘጠኝ ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትሩ ብቻ ጥቅም ላይ እንደሚውል አመልክተዋል። ይህም እስካሁንም 10 በመቶ አይሞላም። ከዝናብ የሚገኘውን ውሃ በመያዝ ለመስኖ ልማት ማዋል ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ተግባር ነው ሲሉ ያስገነዝባሉ።

የመስኖ እና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስቴር ልዩ አማካሪ ዶክተር ኢንጂነር ውብሸት ዠቅአለ በኮንስትራክሽን ዘርፉ በተለያየ ዘርፎች ይሠራሉ። የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለሙያዎች ማህበር የአማካሪ ቦርድ ሰብሳቢም ናቸው። ማህበሩ በዋናነት ከመስኖ እና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስቴር ጋር በመተባበር እንደሚሠራ ጠቅሰው፣ መድረኩ የመስኖ ልማቱ በፍኖተ ካርታ ታግዞ እንዲመራ ለማድረግ እንደሚረዳ አስታውቀዋል።

ፍኖተ ካርታው ለቀጣይ 30 ዓመታት የመስኖ መሠረተ ልማቱን ማምጣት የሚያስችል መስመር የሚቀረፅበት ነው ሲሉም ጠቁመዋል። በኢትዮጵያ የመስኖ ልማት ላይ እምርታዊ ለውጥ ለማምጣት የተቀረጸ ስትራቴጂክ ፍሬምወርክ መሆኑን ጠቅሰው፣ አራት ዋና ዋና ክፍሎች እንዳሉትም አመልክተዋል። የሀገሪቱ የመስኖ ልማት ዘርፍ ያለበትን አጠቃላይ ሁኔታ፣ ዓለም አቀፍ ምርጥ የመስኖ ልማት ተሞክሮዎችን፣ በቀጣዮቹ 30 ዓመታት በዘርፉ ሊከናወንና ሊደረስበት የታሰበው በዝርዝር የተመላከተበት መሆኑን አብራርተዋል።

እሳቸው እንዳሉት፤ በሀገሪቱ ለሶስት ወራት የዝናብ ውሃ ይኖራል፤ ለስድስት ወራት ውሃ ያለባቸው፣ የሌለባቸው ቦታዎችም አሉ። ውሃ በሌለባቸው አካባቢዎች መስኖን እና ውሃ የሚቆጥቡ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ምርታማነትን መጨመር በሚቻልበት መንገድ ላይ በመሥራት ምርታማነቱን በአራት እጥፍ ማሳደግ ይገባል። ፍኖተ ካርታውም በዓመት አራት ጊዜ በማምረት ምርታማነትን ማሳደግ የሚቻልበት አቅም እንዳለ ለማሳየት ያግዛል። የአፈር ባህሪ ሲታይም ውሃ ቶሎ የሚለቅ፣ ውሃ የሚይዝም አለ። ከሚለሙት አትክልቶች አኳያ ሲታይም እንዲሁ ውሃ በጣም የሚፈልጉና የማይፈልጉ አሉ።

የመስኖ ሥራዎችንና ቴክኖሎጂዎችን ስናይ ውሃ በጣም በሚፈለግባቸው ቦታዎች ላይ የምንጠቀማቸው ቴክኖሎጂዎች አሉ። ውሃ በጣም የሚያጥርባቸው ቦታዎች ላይ ደግሞ ለውሃ ቁጠባ የሚረዱ የውሃ መስኖ ቴክኖሎጂዎች አሉ ሲሉም አመልክተው፣ እነዚህን አራት ነገሮች በማቀናጀት ምርታማነታችንን ከፍ በማድረግ በምግብ፣ ራስን ለመቻል የተጠቃሚውን ህብረተሰብ ገቢ ለመጨመር፣ የግብርና ምርቶችን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ እንደሚቻል አስታውቀዋል።

ኢንጂነር ውብሸት ዘርፉ ከባድ የሚባሉ ተግዳሮቶች እንዳሉበትም ጠቁመዋል። ተግዳሮቶቹንም በቅድመ ፕሮጀክት በዲዛይን፣ በማልማት /ዴቨሎፕመንት/ በትግበራ /በኤክስኪዩሽን/ እና በአቅርቦት ማኔጅመንት በኩል የሚታዩ መሆናቸውን ጠቅሰዋል። የኤስያ፣ አፍሪካ፣ የመካከለኛው ምስራቅ፣ የአሜሪካ፣ የእንግሊዝ ተሞክሮዎችን በመጥቀስም ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን በሰነዱ ለማሳየት መሞከሩን ተናግረዋል።

ከዚህም በአንደኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠችው ባንግላዴሽ 82 በመቶ ውሃዋን ለመስኖ ተጠቅማለች። ፓኪስታን ሁለተኛ ነች፤ 52 ነጥብ 56 በመቶ ተጠቅማለች። ከዚያ በኋላ ያሉት 40፣ 30 ውስጥ ያሉ ናቸው። የእኛዋ ሀገር ዜሮ ነጥብ አምስት ደረጃ ላይ ትገኛለች፤ ይህም ያስቆጫል።

በመስኖ ልማት በፍጥነት በመጠቀም ከችግር ለመውጣት እና ሕዝቡ የሚጠቀምበትን የመስኖ ዘርፍ ከሕዝብ፣ ከባህል እና ከማህበረሰቡ ጋር አቀናጅቶ መሥራት ይገባል ሲሉም መክረዋል። ሳይንሱም አንዳንድ ጊዜ አርሶ አደሩ ለረጅም ጊዜ ሲጠቀምበት የኖረውን አብሮ አገናዝቦ በተጨባጭ ሥራ ተሰናስሎ እንዲሄድ ካልተደረገ ውጤታማ ላይሆን ይችላል ሲሉም አስገንዝበዋል።

በመቀጠልም ልማቱ ወደ ንግድ በሚሄድበት ጊዜም ወደ ሕዝብ፣ ሕዝባዊ የግል ዘርፍ ፣ እንዲሁም ወደ ግሉ ዘርፍ በደረጃ መግባት አለበት ሲሉ ጠቁመው፣ ይሄንን በየደረጃው በማሳደግም በመጀመሪያው 10 ዓመት፣ በሁለተኛው 10 ዓመት፣ በ3ኛው 10 ዓመት ምን መሥራት እንደሚገባ በዝርዝር በመቅረፅ አምስት ፕሮግራሞች እና 26 ፕሮጀክቶች መቅረባቸውን አመልክተዋል።

ይሄንንም የመስኖና እና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር ተመልከቶ እና ቅድሚያ የሚሰጠውን ለይቶ እስከ ታህሳስ ወር 2017 ዓ.ም ድረስ እንደሚያጠቃልለውና ይፋ እንደሚያደርግ ግምታቸውን አስቀምጠዋል።

በኃይሉ አበራ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሐምሌ 6 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You