ባለዘርፈ ብዙ ፋይዳው መርሀ ግብር

እንደ አብዛኛው ሕዝቧ አርሶ አደር የሆነው ኢትዮጵያ ሐምሌ ወር የተስፋ፣ የእምነትና የበረከት ወሯ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። አርሶ አደሩ ፈጣሪውን አምኖ ጥሪቱን አሟጦ ባለሰለሰው ማሳ ላይ የሚዘራበትና አንደ አረምና ኩትኳቶ ባሉት የእንክብካቤ ስራዎች የሚጠምድበት ወር ነው።

የአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብር የተጀመረበት ሐምሌ 2011 ዓ.ም ደግሞ ልዩ ወሩ መሆኑን አጠናክሮታል። ከዚህ ዓመት አንስቶ መላ ኢትዮጵያን አረንጓዴ የሚያለብሰውን የአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብር ከግብርና ስራው ጎን ለጎን ከመላ ኢትዮጵያውያን ጋር በመሆን በዚህ ወር በስፋት ያከናውናል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ሀገሪቱን አረንጓዴ ለማልበስ ያስጀመሩት ይህ መርሀ ግብር ይሄው ላለፉት ዓመታት በተጠናከረ መልኩ ተካሂዷል፤ ዘንድሮም ይበልጥ ተጠናክሮ ከሰባት ነጥብ አምስት ቢሊየን በላይ ችግኞች ይተከሉበታል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በ2011 ዓ.ም በተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) 75ኛ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር “የእኛ ዋነኛ ግብ የተራቆተውን መሬት በደን መሸፈንና የተሻለ ነገን መፍጠር ብቻ ሳይሆን ስራችንን ከአረንጓዴና ከአየር ጠባይ ለውጥ ጋር በተስማማ መልኩ ማከናወን ነው፤ ይህን እውን ለማድረግም አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ አለብን፤ ስለጉዳዩ የሚያሳስበን ሌላ አካል አያስፈልገንም። ምክንያቱም የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለውን አውዳሚ ጥፋት በመላው ዓለም በተለያዩ ቦታዎች ላይ በተጨባጭ አይተነዋል“ በማለት ለመርሃ ግብሩ ስኬታማነት ያላቸውን ቁርጠኝነታቸውን ባሳወቁት መሰረት ሀገሪቱን አረንጓዴ የማልበሱ ስራ ተጠናክሮ ቀጥሏል። በዚህም ጠቅላይ ሚኒስትሩም ቃላቸውን በተግባር አረጋግጠዋል።

እስከ አሁን 32 ነጥብ አምስት ቢሊየን ችግኞች ተተክለዋል። በአንድ ጀምበር በመቶ ሚሊየን ችግኞችን መትከል የተቻለበትም ነው። በ2011 ዓ.ም በአንድ ጀምበር ብቻ 200 ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል ግብ ተቀምጦ፣ ከዚያ የላቀ መትከል ተችሏል። በ2015 ዓ.ም እንዲሁ በአንድ ጀምበር 500 ሚሊየን ለመትከል ታቅዶ ከ567 ሚሊየን በላይ መትከል ተችሏል። ዘንድሮም በብዙ መቶ ሚሊየኖች የሚቆጠሩ ችግኞችን በአንድ ጀምበር በመትከል ስኬቱን በዩኔስኮ ለማስመዝገብ ታስቧል።

መርሃግብሩ ሀገራዊ እሳቤን ያነገበ በመሆኑም እንደ ሀገር ብዙ ለውጦችን እያመጣ ስለመሆኑ መርሃግብሩን በዋናነት የሚመራው አካል ሪፖርትም ያመላክታል። ኢትዮጵያ በመርሀ ግብሩ ያከናወነችውና እያከናወነች ያለችው የችግኝ ተከላ ዓለም አቀፍ አጀንዳ እስከመሆን ደርሷል። ሌሎች ሀገራትም ተሞክሮውን እንዲወስዱና እንዲተገብሩት አስከማስቻልም ተደርሷል።

የኢትዮጵያ የደን ሃብት ከግብርና፣ ከማገዶ፣ ከከሰል ማውጣት፣ ከልቅ ግጦሽ፣ ከግንባታና ከእንጨት ስራ ጋር በተያያዘ በማይታመን ፍጥነት መጠኑ መቀነሱ ይታወቃል። ይህን ሁኔታ መለወጥ ስለመጀመሩም እየተጠቆመ ነው።

በአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብሩ የሚተከሉ ችግኞች ጽድቀት እየጨመረ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ፤ ፊት 75 በመቶ የነበረው የጽድቀት መጠን 80 በመቶ የደረሰበት ሁኔታ ታይቷል። በመርሀ ግብሩ ከተተከሉ ችግኞች መካከል እንደ አቮካዶ፣ ቡና የመሳሰሉት ምርት እስከ መስጠት የደረሱበት ሁኔታም መርሀ ግብሩ ምድሪቱን አረንጓዴ ከማልበስ ባሻገር ለምግብ ዋስትናም አስተዋጽኦ ማድረግ ስለመጀመሩ ሌላው ማሳያ ነው።

በችግኝ ተከላው የፍራፍሬ ችግኞችን በስፋት የመትከሉ ስራ ዘንድሮም ተጠናክሮ ቀጥሏል። የችግኝ ተከላውን ከግብርና ስራ ጋር በማቀናጀት ማካሄድ እና አቮካዶን እንዲሁም ፓፓያን የመሳሳሉ ፍራፍሬዎችን ጨምሮ የተለያዩ ችግኞች እየተተከሉ ናቸው።

ችግኞቹን በጥናት ላይ ተመስርቶ በመለየት፤ ተገቢውን ችግኝና ዝርያ ለተገቢው አካባቢና ለትክክለኛው ዓላማ የመትከል ስራ እየተከናወነ ይገኛል። እንደ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ያሉት የማንጎ ችግኝ በስፋት ወደ መትከል የገቡበት ሁኔታም ይህንን ያመለክታል። ይህም ሀገሪቱ በመርሀ ግብሩ የተመናመነባትን የደን ሀብት በድጋሚ ከማልማት ጎን ለጎን ለምግብ ዋስትና ስራም እያዋለችው መሆኑን ያመለክታል።

የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብሩ ባለቤቱና ተጠቃሚው ሕዝቡና ሕዝቡ ብቻ እንዲሆን ያስቻለ መሆኑ መርሃ ግብሩ በመታገዝ በርካታ የስራ ዕድል እድሎች እንዲፈጠሩም እያደረገ ነው። በተለይ የገጠሩን ማህበረሰብ ሕይወት በማሻሻል በኩል ብዙ ለውጦች ማሳየት እየተቻለ ነው።

በችግኝ ማፍላትና ማዘጋጀት ስራ በርካቶች የተሰማሩበት ሁኔታ ለሥራ እድል ፈጠራ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ያመለክታል። በተለይ ወጣቶችና ሴቶች ችግኝ በማፍላትና በመንከባከብ በስፋት ተጠቃሚ እንዲሆኑ፤ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የማህበረሰብ ክፍሎች ራሳቸውን በገቢም በምግብም እንዲደጉሙ እያስቻለ ነው።

የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋም መልካምድርን መልሶ ከመፍጠር አንጻርም ለውጦች እየታዩ መሆናቸው እየተጠቀሰ ነው። አንዳንድ ጥብቅ ደኖች በዓለም አቀፉ የካርቦን ንግድ በኩል ለሀገሪቱ የውጭ ምንዛሬ ሊያስገኙ የሚችሉበት ሁኔታ እንዳለም እየተገለጸ ይገኛል።

እንደሚታወቀው የደን ልማት እና የግብርና ሥራ በሚከናወንባቸው ስፍራዎች የሚኖረው አርሶ አደርና ሌሎች የማህበረሰብ ክፍሎች ደረቃማው ወቅት ሲያበቃ ነው የአካባቢያቸው አፈር ርጥበታማ የሚሆነው። በዚህ ምክንያት ሁሌም ዝናብ ጠባቂ ናቸው። ይህም በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ አምራች እንዲሆኑ ሲያስ ገድዳቸው ኖሯል።

በአረንጓዴ ዓሻራ መርሃ ግብሩ የተፋሰስ ልማት በተሰራለቸው የተጎዱ አካባቢዎች ላይ ችግኞችን በመትከል በአረንጓዴ ልማት ላይ መስራት ውስጥ በስፋት መገባቱ ይህን ሁሉ ሁኔታ ይቀይራል ተብሎ ይጠበቃል። የከርሰ ምድር ውሃ አቅም እየጨመረ ሊመጣ ይችላል፤ ምንጮች ውሃ መስጠት የማይቸገሩበት ሁኔታ ይፈጠራል።

በአንዳንድ አካባቢዎችም ይሄው እየሆነ መሆኑ ይነገራል፤ ደርቀው የነበሩ ምንጮች ውሃ መስጠት ያቆሙበት፣ ደን በመመንጠሩ የተነሳ ተሰደው የነበሩ አንዳንድ የዱር እንስሳትና አእዋፋት ወደ ቀድሞ ቀዬቻው እየተመለሱ ስለመሆኑም ይገለጸል። መርሃ ግብሩ የውሃ አቅርቦትና ፍላጎታቸውን ማሟላት፣ አርሶ አደሮችም በዓመት አንዴ ብቻ ሳይሆን ሁለት ሶስቴ ማምረት ወደሚችሉበት ሁኔታም የሚገቡበት ሁኔታ እየተፈጠረ እንዲመጣም ያደርጋል።

ከዚህ ባለፈ መርሃ ግብሩ የተሻሻለ የግብርና አሰራርን በማስፈን፣ የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ፣ የአፈር፣ የውሃ ሃብትና የብዝሃ ህይወት ጥበቃን በማረጋገጥ ዘላቂ ተጠቃሚነትን ማስገኘት እየተቻለ ስለመሆኑም የተለያዩ ወገኖች ይናገራሉ።

ይህ መርሃግብር ከተሞችንና አካባቢያቸውን ከማስዋብ ባለፈ ነፋሻና ንጹህ አየር የሚገኝባቸው እንዲሆኑ የበኩሉን ሚና እየተጫወተ ይገኛል። የተበከሉ ወንዞችን ደህንነት በማስጠበቅ፣ የአረንጓዴ ስፍራዎች በስፋት በማልማት፣ ደኖች ተጠብቀውና ለምተው ለቱሪዝም አገልግሎት እንዲውሉ ምቹ ሁኔታንም ይፈጥራል።

ሀገሪቱ ይህን ተሞክሮ ወደ ጎረቤት ሀገሮች ለማስፋትም እየሰራች ትገኛለች። ለጎረቤት ሀገሮች ችግኝ በማቅረብ ጭምር እያከናወነች ያለችው ተግባርም ይህንኑ ያመለክታል። የደን ልማት በአንድ ሀገር ውስጥ ብቻ ታጥሮ መቀመጥ ያለበት እንዳለመሆኑ መንግስት ይህን ማድረግ ውስጥ መግባቱ በተለይ ለአካባቢውና ለአፍሪካ ሀገሮች በአጠቃላይ ለዓለም ፋይዳው ከፍተኛ ነው።

ስለዚህ ይህ ተግባር እንደ ሀገር ያለው ጥቅም እጅግ በርካታ ነው። ይህ መርሀ ግብር የያዘው ዓላማ እንዲሳካ እስከ አሁን በተከናወኑ ተግባሮች የተገኙ ልምዶችን ቀምሮ ስራ ላይ ማዋል ያስፈልጋል። በተለይ የፍራፍሬ ልማትን ከመርሀ ግብሩ ጋር የማስተሳሰሩ ተግባር ያለው ፋይዳ ዘርፈ ብዙ እንደመሆኑ ይበልጥ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል።

ለሀገር በቀል የዛፍ ዝርያዎች ልማትም ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑ ይታወቃል። ትኩረቱ ግን በልዩ ትኩረት ሊያዝ ይገባል። እነዚህ የዛፍ ዝርያዎች ለመሬት ለምነት፣ ለተያዘው የውሃ ሀብት ልማት ያላቸው አስተዋጽኦ ክፍተኛ ነው። ይህ ብቻውን ለዝርያዎቹ ትኩረት መስጠት እንደሚገባ ያስገነዝባል። ዝርያዎቹ እንዲጠበቁ ከማድረግም በላይ እንዲለሙ ማድረግም ይገባል።

በአረንጓዴ ዐሻራም ይሁን በተለይ በከተሞች የአረንጓዴ ስፍራዎች ልማት ውስጥ በተለይ እንደ ወይራ ዛፍ ላሉት ልማት ትኩረት መሰጠቱ ያስመሰግናል። እነዚህ ወይራና የመሳሰሉት የዛፍ ዝርያዎች ደርሰው ለተፈለገው ዓላማ ለመዋል ረጅም እድሜ የሚጠይቁና ልዩ እንከብካቤ የሚፈልጉ ቢሆኑም ያለምንም መታከት በልዩ ትኩረት ልማታቸው ላይ መሰራት ይኖርበታል። የአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብሩ እነዚህን ዝርያዎች ለመታደግ በወሳኝ ወቅት የደረሰ መሆኑንም ተገንዝበን እንጠቀምበት።

ይህ በሐምሌ ወር አሀዱ ተብሎ የተጀመረና በተለይ በዚሁ ወር በስፋት እየተካሄደ የሚገኝ መርሃ ግብር ከእነግለቱ እንዲቀጥልና ዓላማው እንዲሳካ በግልም፣ በማህበረሰብም እንዲሁም እንደ ኢትዮጵያ ሕዝብ ርብርባችን ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል። ሰላም !!

ይህ አምድ በተለያዩ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዜጎች ነፃ ሀሳባቸውን የሚሰጡበት ነው።በዓምዱ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የዝግጅት ክፍሉን አቋም አያመለክቱም።

ክብረ መንግስት

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሐምሌ 6 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You