አለም በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ብዙ ርቀት እየተጓዘ ነው። የሰው ልጅ የየዕለት ተግባሩ መከወኛና የአኗኗር ዘይቤውን ማቅለያ መሳሪያዎቹ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ግኝት የሆኑ የምርምር ውጤቶች ናቸው። በየጊዜው አዳዲስ ምርምሮችና ፈጠራዎች ይከወናሉ። እነዚህ የምርምርና ፈጠራ ስራዎች አለም አሁን ለምትገኝበት ለውጥና ሁነት የጎላ ሚና አላቸው። መነሻቸው የገጠመ ችግር መድረሻቸው የችግሩ ማቅለያና መፍቻ መፍትሄ የሆኑት የምርምርና የፈጠራ ስራዎች ከዘመን ጋር እየዘመኑ ዛሬ ላይ ደርሰዋል። የምርምርና የፈጠራ ስራዎች ችግር ፈቺነት ውስብስብነትና አስደማሚነት ስንመለከት የሰው ልጅ የአይምሮን ምጥቀት ምን ደረጃ እንደደረሰ ማሳያዎች ናቸው። በእነዚህ የፈጠራና የምርምር ስራዎች በመገረም ደጋግመን “አጀብ ብለናል።
የሳይንስና ቴክኖሎጂ ውጤቶች የአለም አጠቃላይ ገፅታን በመቀየርና በራሱ በመቅረፅ ለሰው ልጆች መልካም አጋጣሚ መፍጠር ችለዋል። የምርምር ስራዎች መበራከት ለሀገር ሁለንተናዊ ለውጥ ወሳኝ ጉዳይ ነው። ለዚህ ነው ሀገራት ትኩረታቸውን ሁሉ የምርምርና የፈጠራ ስራ ላይ በማድረግ ዘርፉን በማጠናከርና በመደገፍ ላይ የሚገኙት።
ዛሬ ላይ በሀገራችን ወጣት ተመራማሪዎች እዚያም እዚህም መመልከታችን ሀገራችን በዘርፉ ወደፊት የምትደርስበትን ደረጃ መተንበይ ያስችላል። ወጣቶቹ በግል ተነሳሽነት የተለያዩ የምርምርና የፈጠራ ስራዎች በማበርከት ላይ ይገኛሉ።
ያለ ሙያዊና ቁሳቁሳዊ ድጋፍ በግል ተነሳሽነት በዘርፉ ያለውን ፈተና ተቋቁመው የማህበረሰብን ችግር ሊፈቱ የሚችሉ የምርምር ስራዎችን በማድረግና ለማህበረሰቡ በማበርከት የዜግነት ግዴታቸውን በመወጣት ላይ የሚገኙ ወጣት የፈጠራ ባለሙያዎች ዛሬ ላይ በርክተዋል። የፈጠራ ስራቸው ከግብ መድረስ እንዲችል እና ለምርምር ስራቸው እውቅና ለመስጠት አዳዲስ ተመራማሪዎችን ለማበረታታት ያግዛልና ዛሬ በምርምርና ፈጠራ ስራ ስኬታማ የሆነች ወጣት የፈጠራ ባለሙያ አነጋግረን የፈጠራ ስራዋን የተመለከተ ፅሁፍ በዚህ መልክ አቀረብንላችሁ።
ወደ ፊት ብዙ መስራትን የምታስብ በምርምር ስራዎች ለሀገርዋ ትልቅ ነገርን ማበርከት የምትፈልግ አሁንም በመስራት ላይ ያለች ወጣት የፈጠራ ባለሙያ ናት:: ፀደይ ሚካኤሌ ትባላለች። በ2010 በቆዳ (ሌዘር) ኢንጅነሪንግ የመጀመሪያ ዲግሪዋን በጥሩ ውጤት አጠናቃለች። የስኳር እና የካንሰር ህመምተኞች የሚሆን የጫማ ዲዛይን በመስራት ህመምተኞቹ በህመማቸው ምክንያት የእግር መቁሰልና ሰፍቶም ለጋንግሪን መጋለጥን የሚከላከል የፈጠራ ስራ አበርክታለች።
የፈጠራ ስራው ምንነት፡–
የስኳር ህመምተኞች ብዙውን ጊዜ የሚገጥማቸው የእግር ቁስለት ወይም የጋንግሪን በሽታ ዋነኛ መንስኤ የሚያደርጉት ጫማ ምቹ አለመሆን ነው። የወጣት ፀደይ የፈጠራ ስራ ለስኳር ህመምተኞች መፍትሄን ይዞ የመጣ ያለባቸውም ችግር መቅረፍ የሚችል ነው። የወጣትዋ የፈጠራ ስራ ለስኳርና ለካንሰር ህመምተኞች የሚሆን ጫማ በእግር መቁሰል ምክንያት የሚከሰት ጋንግሪን እንዳይከሰት የሚከላከልና ለህመምተኞቹ ምቹ ሆኖ የተዘጋጀ ነው።
ለፈጠራ ስራው ያነሳሳት ምክንያት፡–
የፈጠራ ስራዎች መነሻ የሚሆን ችግር ነውና ወጣት ፀደይ በአሳዳጊ አያትዋ ላይ የደረሰ ህመም ለምርምር ስራዋ መነሻ እንደሆናት ትናገራለች። በወቅቱ አሳዳጊዋ (አያትዋ) በስኳር ህመም ምክንያት እግራቸው ይቆስላል፤ ቁስሉም ከመሻር ይልቅ ከፍ ወዳለ ደረጃ ይደርስና እግራቸው ይቆረጣል። ያኔ የምትወዳቸው አያትዋ የደረሰባቸው ጉዳት በስኳር በሽታቸው መነሻነት እግራቸው ላይ በተፈጠረ ቁስል መሆኑ የተረዳችው ወጣት ፀደይ የውስጥ ቁጭት ተፈጠረባት።
አያትዋ የገጠማቸውን ትልቅ ጉዳት ለማስቆም ባትችልም ሌሎች ወገኖችዋ ተመሳሳይ ችግር እንዳይገጥማቸው መፍትሄን ማፈላለግ ለችግሩ መግቻ የሚሆን መላን ማውጠንጠን ያዘች። ተደጋጋሚ ሙከራዎችንና ጥረቶችን ማድረግ ተያያዘች። ሳታሰልስ ያደረገችው ጥረት ደግሞ የተሻለ ውጤት ያስገኝላት ጀመር። በመጨረሻም ያሰበችው ተሳክቶ ውጥንዋ ሰምሮ የስኳርና የካንሰር ህመምተኞች ምቹ የሆነና እግር ከመቁሰል የሚከላከል ጫማ ለመስራት በቃች። ሙሉ በሙሉ የራስዋ የፈጠራ ውጤት የሆነው ጫማ የስኳርና የካንሰር ህመምተኞችን ከችግር የሚከላከል መሆኑን ትናገራለች።
በፈጠራ ስራው የተገኘ እውቅናና ሽልማት
ወጣት ፀደይ የምርምር ስራዋ ብዙ እውቅናና ሽልማት ከተለያዩ ተቋማት አስገኝቶላታል። ከኢትዮጵያ አዕምሮዋዊ መብት ፅህፈት ቤት የፈጠራ ባለቤትነት መብት ሰርተፍኬት፣ ከአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲና ከባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የአመቱ ምርጥ የምርምር ስራ በመሰኘት፣ ከስኳር ህመምተኞች ማህበር ፣ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እና ከተለያዩ ተቋማት በምርምር ስራዋ ሽልማቶችን አግኝታለች።
የፈጠራ ስራው አሁን ያለበት ደረጃ :-
የፈጠራ ስራዎች ተግባራዊ ሆነው ህብረተሰቡ ጋር እንዲደርሱ ማድረግና ጥቅም ላይ ማዋል ወሳኙ ጉዳይ ነው። ነገር ግን በምርምር ተገኙ፤ በተደጋጋሚ በሚደረግ ጥረትም ተፈጠሩ የሚባሉት የፈጠራና ምርምር ስራዎች በተመራማሪው የገንዘብና የቁሳቁስ አቅም ውስንነት የተነሳ ብዙ ጊዜ ማህበረሰቡ ጋር ሳይደርሱ ይቀራሉ። የወጣት ፀደይ የምርምር ውጤት የሆነውና ለስኳር ህመምተኞች መፍትሄን ይዞ የመጣው የፈጠራ ስራ ወደ ገበያ ለመግባትና ለህብረተሰቡ በበቂ መጠን ለማቅረብ የወጣት ተማራማሪዋ አቅም ውስን መሆን እንቅፋት ሆኗል።
አሁን ላይ በተመራማሪዋ የሚሰሩት ውስን ጫማዎች በፋብሪካ ደረጃ ተዘጋጅተው ለህብረተሰቡ በስፋት የሚቀርብበት እድል ቢመቻች አንድም የፈጠራ ስራውን ማበረታታትና ጥቅም ላይ ማዋል ሲሆን በዘርፉ ተሰማርቶ ስራውን ለመስራት ላለመም ሰፊ የገበያ እድል ማግኛ መንገድ መሆኑ እሙን ነው። ወጣት ፀደይ ከጫማ ፋብሪካዎች ጋር ለመስራት የተለያዩ ጥረቶች በማድረግ ላይ ትገኛለች።
ሳይንስ የእድገት ማፍጠኛ የብልፅግና መቃረቢያ መንገድ፣ የችግር መፍቻ ዋንኛ ተግባርና ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን ተመራማሪ ፀደይ ትናገራለች። የፈጠራ ባለሙያዎችን በመደገፍ፣ የፈጠራ ስራቸው ጥቅም ላይ የሚውልበትን መንገድ ምቹ በማድረግና የፈጠራ ስራዎቹ ይበልጥ ተሻሽለው ከፍ ያለ ጠቀሜታን ማበርከት እንዲችሉ ማድረግ ደግሞ ሊሰራበት የሚገባ ወሳኝ ሀገራዊ ጉዳይ እንደሆነ ወጣት ፀደይ ትገለፃለች።
በምርምር ስራ ከባዱ ፈተና
የምርምር ስራን ከስኬት ለማድረስ እጅግ የበዛ ፈተናና ተስፋ አስቆራጭ ገጠመኞች እንዳሉት ተመራማሪዋ ትገልፃለች። ያለመሰልቸት ተደጋጋሚ ሙከራ ማድረግና ለምርምር ስራው የተሻለ ውጤት የማያለሰልስ ጥረት ማድረግ በምርምር ስራው ውስጥ ወሳኝ ጉዳይ ነው። ወጣት ፀደይ በምርምር ስራዋ ከዚህ ደረጃ ለመድረስ መንገዱ አልጋ ባልጋ ሆኖ አልጠበቃትም። የሚገጥማት ፈተና በመጋፈጥ ያለመችውን ለማሳካት ያላሰለሰ ጥረት አድርጋለች። ለምርምር ስራ ምቹ የሆነ አካባቢያዊ ሁኔታና ልምድ አለመኖር፣በሀገር ደረጃ ለፈጠራ ስራ የሚሰጠው ትኩረት የጠነከረ አለመሆንና ለምርምር ስራ የሚሰጠው ድጋፍ ማነስ በምርምሩ ውጤታማነት ላይ ተፅዕኖ አሳዳሪ ምክንያት እንደነበሩ ታስረዳለች። በመንግስት በኩል ለፈጠራ ስራዎች ተገቢውን ትኩረት መስጠትና ተግባራዊነታቸውን በመፈተሸ ሀገራዊ ጠቀሜታቸውን ማጉላት እንደሚገባም ትገልፃለች።
ለጀማሪ የፈጠራ ስራ ሙያተኞችና ተመራማሪዎች መልዕክት
የምርምር ስራ ላይ የተሰማራ ሰው ትዕግስት በተሞላበት መልኩ የምርምር ስራውን ማከናወንና የሚገጥሙት የበዙ ፈተናዎች ከተስፋ መቁረጥ በራቀ መንፈስ ሊጋፈጥ እንደሚገባ ትመክራለች። በተለይ አዲስ ለሆኑና የፈጠራ ስራ ላይ ለተሰማሩ ወጣቶች የምርምር ስራቸው መልካም ውጤት በመመኘት ተደጋጋሚ ጥረት ማድረግና ቆራጥነት በባህሪ መልክ ሊላበሱት እንደሚገባም ወጣት ፀደይ ምክርዋን ትለግሳለች። ከሌላ አካል ድጋፍን ከመጠበቅ ይልቅ አካባቢያዊ በሆነና የምርምር ስራ መስራት በሚያስችሉ ቁሳቁሶች በመጠቀም የፈጠራ ስራቸውን አጠንክረው ሊያስቀጥሉ እንደሚገባም ትገልፃለች።
ወጣት ፀደይ በሀገር ደረጃ ያሉትን ዘርፈ ብዙ ችግሮችን ለመግታት የምርምር ስራዎች ወሳኝ እንደሆኑና መንግስትና ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባም ትናገራለች። በተለይ የምርምር ስራዎች በሙሉ በተሻለ መልኩ ተጠንተውና ትኩረት ተሰጥቷቸው ለህብረተሰቡ ጥቅም መስጠት እንዲችሉ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል፤ እንደ ወጣት ፀደይ።
ወጣት ፀደይ ከዚህ የፈጠራ ስራዋ በተጨማሪ ሌሎች የምርምር ስራዎችም በመስራት ላይ ትገኛለች። “ወደፊት እጅግ የበዙ እቅዶች አሉኝ ለሀገሬ ኢትዮጵያ ጥሩ ነገርን ማበርከት እፈልጋለሁ” ትላለች ወጣትዋ፤ እኛም ስኬቷን ተመኘንላት፤ ቸር ይግጠመን።
አዲስ ዘመን ሰኔ 21/2011
ተገኝ ብሩ