
የኮልፌ እና የለሚኩራ የገበያ ማዕከላት ለ3ተኛ ወገን ተላልፈዋል
አዲስ አበባ፦ ባለፉት አራት ወራት በመዲናዋ መግቢያ በሮች በሚገኙ የገበያ ማዕከላት ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ነዋሪዎች ግብይት መፈጸማቸውን የአዲስ አበባ ከተማ ንግድ ቢሮ አስታወቀ። ቢሮው በከተማ አስተዳደሩ የተገነቡትን የኮልፌና የለሚኩራ የገበያ ማዕከላትን ለሦስተኛ ወገን አስተላልፏል።
የገበያ ማዕከላቱን እንዲያስተዳድሩ ለሁለት የግል ድርጅቶች የተሰጠ ሲሆን “ሀብ ቢዝነስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር” የአስተዳደሩን ሥራ “ኢትዮ ጥበቃ አገልግሎት” ደግሞ የፅዳትና የጥበቃ ሥራውን ለመሥራት ጨረታ አሸንፈው የተመረጡ ድርጅቶች መሆናቸውን ቢሮው ትናንት ገልጿል።
የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ኃላፊ አቶ ቢኒያም ምክሩ በወቅቱ እንደተናገሩት፤ ድርጅቶቹ ከሐምሌ አንድ ቀን 2016 ዓመተ ምሕረት ጀምሮ ወደሥራ እንደገቡ እና ለሦስት ወር የሚቆይ መሆኑን ገልጸው የግብይት ሥርዓቱ በየሳምንቱ ንግድ ቢሮ በሚያወጣው ተመን እንደሚካሄድ ተናግረዋል። ይህም ማለት አጠቃላይ ሂደቱን ቢሮው የሚቆጣጠር መሆኑን ነው የገለጹት።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ በውስጥ አቅም የሚሠሩ ሥራዎችን ለ3ተኛ ወገን በማስተላለፍ መሥራት የሚያስችል ውሳኔ በዚህ ዓመት ኅዳር ወር ላይ ማስተላለፉ ይታወሳል ያሉት አቶ ቢኒያም፤ በዚህ መሠረት ቢሮው በከተማ አስተዳደሩ የተገነቡትን የኮልፌና የለሚኩራ የገበያ ማዕከላትን ለሦስተኛ ወገን አስተላልፏል ብለዋል።
በአሁኑ ጊዜ በመዲናችን እየተስተዋለ ላለው የኑሮ ውድነት ዋነኛ ምክንያቱ የምርት አቅርቦትና ፍላጎት አለመጣጣም ነው ያሉት አቶ ቢኒያም፤ ይህንን ለመቅረፍ ከተማ አስተዳደሩ ስትራቴጂካዊ ሥራዎች እየሠራ ይገኛል። ለአብነትም በከፍተኛ በጀት በመዲናዋ መግቢያ በሮች ግዙፍ የገበያ ማዕከላትን በመገንባት አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ ነው ያሉት።
የገበያ ማዕከላቱ በአቃቂ ቃሊቲ፣ በለሚ ኩራ እና በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተሞች የተገነቡ ሲሆን እነዚህም እየተስተዋለ ያለውን የኑሮ ውድነት ለመቀነስ ከፍተኛ አስተዋፅዖ ይኖራቸዋል ያሉት አቶ ቢኒያም፤ ባለፉት አራት ወራት በመዲናዋ መግቢያ በሮች በሚገኙ የገበያ ማዕከላት ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ነዋሪዎች ግብይት ፈጽመዋል ሲሉ ተናግረዋል።
በእነዚህ የገበያ ማዕከላት የሚቀርቡ ምርቶች የመሸጫ ዋጋ ውጪ ካለው የምርቶች መሸጫ ዋጋ ከ 10 እስከ 15 በመቶ ቅናሽ ይኖራቸዋል ያሉት አቶ ቢኒያም፤ አገልግሎቶቹን ለ3ተኛ ወገን ማስተላለፍ ያስፈለገው ንግድ ቢሮ የሚያስቀምጠውን የዋጋ ተመን፣ የፅዳትና የጥበቃ ሥራዎች ላይ ጠንካራ ቁጥጥር ለማድረግ መሆኑን ገልጸዋል።
ይህም ሸማቹ ጥራት ያለው ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኝ ያስችላል ያሉት አቶ ቢንያም፤ ሥራው እየተጠናከረ ሲሄድ በከተማዋ የሚታየውን የዋጋ ንረት በእጅጉ ለመቀነስ ያስችላል ብለዋል።
ሳሙኤል ወንደሰን
አዲስ ዘመን ሐምሌ 6 ቀን 2016 ዓ.ም