ኢትዮጵያ ከአጠቃላይ ምድራዊ ስፋቷ 60 በመቶ በደን ሀብት የተሸፈነ እንደነበር ታሪክ ያስረዳል። በሂደት ግን በብዝኃ-ሕይወት መመናመን ምክንያት ጥቅል የደን ሽፋን ወደ ሶስት በመቶ መውረዱ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተደረጉ ጥናቶች ደግሞ የኢትዮጵያ የደን ሽፋን ወደ 17 በመቶ ማደጉ ይነገራል። በቅርቡ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ይፋ በሆነበት ዕለትም የኢትዮጵያ የደን ሽፋን 23 ነጥብ 6 በመቶ መድረሱ ተነግሯል፡፡
ይህም ኢትዮጵያ በአካባቢ ጥበቃ ዘርፍ ከምትከናውናቸው ተግባራት መካከል አንዱ በሆነው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ-ግብር የተገኘ አመርቂ ውጤት ነው፡፡ በተለይም ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ በሀገር አቀፍ ደረጃ ተግባራዊ እየተደረገ ያለው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ-ግብር እምርታ የታየበትና እንደአፍሪካም በምሳሌነት የሚጠቀስ ተግባር ሆኗል፡፡
የመጀመሪያው ምዕራፍ አረንጓዴ ዐሻራ በ2011 ዓ.ም ክረምት ወቅት መባቻ ተጀምሮ እስከ 2014 ዓ.ም ድረስ ዘልቋል። በመጀመሪያው ምዕራፍ የመጀመሪያ ዙር መርሃ-ግብር በ2011 ዓ.ም በይፋ ሲጀመር አንድ ሰው 40 ችግኞችን እንዲተክል ተሰልቶ በድምሩ አራት ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ ነበር። በዚህ እቅድ መሠረትም ከታለመው በላይ ማሳካት ተችሏል። ሐምሌ 22 ቀን 2011 ዓ.ም በአንድ ጀምበር 200 ሚሊዮን ችግኞች የመትከል ዕቅድ ግቡን አልፎ በቀን 354 ሚሊዮን ገዳማ ችግኞች በመትከል አዲስ ክብረ ወሰን ማስመዝገብ ተችሏል። በመጀመሪያው ዙር የአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብር 20 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ዐሻራቸውን ማኖር ችለዋል።
በሁለተኛው ዙር የአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብር በ2012 ዓ.ም አምስት ቢሊዮን ችግኞች ለመትከል ታቅዶ ከዕቅድ በላይ ተሳክቷል። በተለይ የፍራፍሬ ተክሎች ትኩረት ተሰጥቷቸው ነበር።
ሦስተኛው ዙር አረንጓዴ ዐሻራ “ኢትዮጵያን እናልብሳት” በሚል መሪ ሃሳብ ተተግብሯል። ይህም ዙር ችግኞችን ለጎረቤት ሀገራት በመስጠት ኢትዮጵያን የአረንጓዴ ዐሻራ አርዓያ እንድትሆን በማስቻል ለየት ያለ ባህሪ ነበረው። ድንበር ዘለል የአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብር ነበር። ኢትዮጵያ ለጎረቤት ሀገራት ችግኞችን መለገሷ ቅቡልነትን አስገኝቶላታል፡፡ ደንን በማልማት ጤናማ አካባቢ በመፍጠር ከጎረቤት ሀገራት ጋር የሚኖረንን ሰላም ለማረጋገጥም ያግዛል። ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም በተጀመረው ሦስተኛ ዙር መርሃ-ግብር ስድስት ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ የነበረ ሲሆን ከታቀደው በላይ ተከናውኗል።
አራተኛው ዙር አረንጓዴ ዐሻራ መርሃ-ግብር “ዐሻራችን ለትውልዳችን” በሚል መሪ ሃሳብ ስድስት ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ ነበር። ሰኔ 14 ቀን 2014 ዓ.ም በይፋ የተጀመረው በዚህ መርሃ-ግብር ከዕቅድ በላይ መሳካቱ ይታወሳል።
ሁለተኛው ምዕራፍ አረንጓዴ ዐሻራ መርሃ-ግብር መሪ ሃሳብ ‘ነገን ዛሬ እንትከል’ የሚል ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በአፋር ክልል የሁለተኛው ምዕራፍ የመጀመሪያ ዙር ባስጀመሩበት ወቅት እንዳሉት በቀጣይ አራት ዓመታት በሚተገበረው ሁለተኛው ምዕራፍ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ-ግብር 25 ቢሊዮን ችግኞች ይተከላሉ በማለት ገልፀው ነበር፡፡ ይህንን እቅድ ከግብ ለማድረስም በተጠናከረ መልኩ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በመተባባር እየሠሩ ይገኛሉ፡፡
ይህንን ግብ ለማሳካት መላው ህብረተሰብ እና ተቋማት ጭምር ተሳትፎ እያደረጉ ናቸው። ሐምሌ 10 ቀን 2015 በአንድ ጀምበር 500 ሚሊዮን ችግኞችን በመትከል በሀገራችን የተያዘውን ሪከርድ ለመስበር በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የተሰጠውን ጥሪ በመከተል ከ567 ሚሊዮን በላይ ችግኞች መተከላቸውም አንዱ የስኬት ማሳያ ነው፡፡ በዚህም 34 ሚሊዮን ሕዝብ በመሳተፍ ታሪክ መጻፍ ተችሏል፡፡
አረንጓዴ ዐሻራ በሁሉም ዘርፍ ያለው ጠቀሜታ የሚያጠያይቅ አይደለም፡፡ ተለይም ደግሞ በብዝሀ ሕይወት ጥበቃ ረገድ የሚጫወተው ሚና ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ በሀገር በቀል እፅዋት ብዝሃ ሕይወት ሀብት በግንባር ቀደምነት የምትጠቀስ ሀገር ናት፡፡ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ፤ የሀገሪቱን የአየር ሁኔታ የተላመዱ እና ድርቅና ከባድ የአየር ሁኔታን በቀላሉ የሚቋቋሙ የእፅዋት ዝርያዎች በብዛት ይገኛሉ፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የእነዚህ ተክሎች ጥቅማቸው በማህበረሰቡ ዘንድ እየታወቀ በመምጣቱ ትኩረት እየተሰጣቸው ይገኛል፡፡ ነገር ግን ጅማሮው የሚበረታታ ቢሆንም ይህ ብቻውን በቂ ነው ለማለት አያስደፍርም፡፡
በአረንጓዴ ዐሻራ በአማካይ በየአመቱ እስከ አምስት ቢሊዮን ችግኝ ይተከላል፡፡ ከዚህ ውስጥ ሀገር በቀል ተክሎች ከሶስት ሚሊዮን የሚበልጡ አይደሉም፡፡ ስለዚህ ሀገርን አረንጓዴ ከማልበስና ከማስዋብ ባሻገር ለሀገር በቀል እፅዋት በተለየ መልኩ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሠራበት ይገባል፡፡ ምክንያቱም ሀገር በቀል እፅዋትን በአረንጓዴ አሻራ አማካይነት በብዛት መትከል ከቻልን በጂን ባንክ መቀመጥ የማይችሉ ዝርያዎችን በመሩት ላይ በመትከል ማህበረሰቡ ከተረፈ ምርታቸው እየተጠቀመ እንዲጠብቃቸው ከፍተኛ እድል ይፈጥራል፡፡
በሀገር በቀል እፅዋት ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሠራው የኢትዮጵያ ብዝሃ ሕይወት ኢንስቲትዩት በየዓመቱ በሀገር በቀል ችግኞችን ለአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብር ያበረክታል፡፡ ባሳለፍነው የ2015 ዓ.ም የአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብር ሁለት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ሀገር በቀል ችግኞችን ለማዘጋጀት አቅዶ ሶስት ሚሊዮን ችግኝ ለማዘጋጀት ተችሏል።
ለዘንድሮ አረንጓዴ ዐሻራ ሀገር በቀል የሆኑ ችግኞችን ኮሶ፣ ብርብራ፣ የሀበሻ ጽድ፣ ቀርቀሃንና መሰል የደን ተክሎችን ጨምሮ ለምግብነት የሚያገለግሉ ችግኞችን ጨምሮ አራት ሚሊዮን ሀገር በቀል ችግኞች መዘጋጀታቸውን ኢንስቲትዩቱ አሳውቋል፡፡ ታዲያ ይህን ቁጥር አሁንም በቂ የሚባል አይደለም፡፡ ሀገር በቀል እፅዋትን መትከል የአካባቢ ሥነ-ምህዳርን ከመጠበቅ ባለፈ በመጥፋት ላይ ያሉ ዕፅዋቶች መልሰው እንዲያገግሙ ሰፊ እገዛ ያደርጋል፡፡ ከሚያስገኙት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ በመነሳት ፊታችንን ወደ ሀገር በቀል ተክሎች በመመለስ እየተመናመኑ ያሉ የእፅዋት ዝርያዎችን አረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብር በሚደረገው ሰፊ ተሳትፎ አማካይነት ልንታደጋቸው እና ልንጠብቃቸው ይገባል፡፡
ቲሻ ልዑል
አዲስ ዘመን ሐምሌ 5 ቀን 2016 ዓ.ም