ኢትዮጵያ ካሏት የማዕድን ሀብቶች መካከል የከበሩ ማዕድናት ይጠቀሳሉ። ከ40 በላይ የከበሩ ማዕድናት አይነቶች እንዳሏት መረጃዎች ይጠቁማሉ። ከእነዚህ የከበሩ ማዕድናት መካከልም ኦፓል፣ ሳፋየር፣ አማዞናይት፣ ኳርትዝ፣ ኤምራልድ፣ ሩቢ፣ አጌት ፣አኳመሪን፣ ቶርመሪን እና ሌሎችም ይገኙበታል። ይሁን እንጂ በባሕላዊ መንገድ ተቆፍረው እየወጡ ጥቅም ላይ የሚውሉበት ሁኔታ ከመኖሩ በስተቀር እስካሁን ድረስ በሳይንሳዊ መንገድ ተጠንተው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታቸው በሚገባ ተለይቶ አይታወቅም።
ሀገሪቷ ያሏትን የከበሩ ማዕድናት በሚገባ ማወቅና መለየት ላይ ብቻ አይደለም ያልተሠራው። እነዚህ ሀብቶች ልክ እንደ ወርቅ ማዕድን ሁሉ ታምኖባቸው ትኩረት ተሰጥቷቸው እምብዛም ሲሠራባቸው አይስተዋልም። ይህም ዘርፉን በእውቀት የመምራትና ሀብቱን በሚገባ አውቆና ለይቶ መጠቀም ላይ ክፍተቶች መኖራቸው ያሳያል። የከበሩ ማዕድናት ዘርፉ እውቀትና ክህሎት ያለው ብቁና የሠለጠነ የሰው ኃይል የሚጠይቅ ቢሆንም፣ አሁን ያለው የሰው ኃይል በጣም ጥቂት የሚባል መሆኑን መረጃዎች ያመላክታሉ።
ከዚህ ሀብት በሚገባ ለመጠቀም በሳይንሳዊ መንገድ የከበሩ ማዕድናትንና ጌጣጌጦችን የሚለይ፣ የሚያጠና፣ የሚቆርጥና እሴት የሚጨምር ባለሙያ ያስፈልጋል። አሁን ባለው ሁኔታ በዚህ ዘርፍ ሀገሪቱ ያለቻት አንዲት ባለሙያ /ጂሞሎጂስት/ ብቻ መሆኗን መረጃዎች ይጠቁማሉ። ይቺ ባለሙያ እውቀቱ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጣና ለሌሎችም እንዲተርፍ ከዓለም የከበሩ ማዕድናት ማኅበር ጋር በመተባበር እየሠራች ትገኛለች። ይህን ተከትሎም በባለፈው ሳምንት መጨረሻም በከበሩት ማዕድናት ዘርፍ በሀገሪቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የሠለጠኑ 12 ጂሞሎጂስት ባለሙያዎች ተመርቀዋል።
በምረቃ ፕሮግራሙ ላይ የተገኙት የማዕድን ሚኒስትር ኢንጂነር ሀብታሙ ተገኝ፤ ተመራቂዎቹ ኢትዮጵያ ከከበሩ ማዕድናት የሚገባትን ጥቅም እንድታገኝ በማድረግ ወደ ቀጣይ ምዕራፍ እንዲያሸጋገሩ ተስፋ የተጣለባችሁ መሆናቸውን አስገንዝበዋል።
ኢትዮጵያ በከበሩት ማዕድናት ዘርፍ ከ40 ያላነሱ ድንቅ የሚባሉ፣ እጅግ ብዙ ዋጋ የሚወጡ ማዕድናት እንዳሏት ይናገራሉ፤ ይሁን እንጂ ሀብቱን በቅጡ አላወቅነውም፣ አልተጠቀምንበትም ሲሉ ሚኒስትሩ ይናገራሉ። እስካሁን በዚህ ዘርፍ እውቅና ያላቸው ሀብቱን የሚያወቁ ማዕድናቱን በዓለም ደረጃ የሚያቀርቡ ደረጃውን የሚያወጡ ባለሙያዎች አልነበሩም ብለዋል። በዚህ ምክንያት ያላለቀለትና እሴት ያልተጨመረበትን የከበረ ድንጋይ ለተለያዩ ሀገራት ስናቀርብ ኖረናል ነው ያሉት ሚኒስትሩ። ይህም እንደ ሀገር ማግኘት ያለብን ዋጋ ሳናገኝ፤ በብዙ ሺዎች ቶን እየላክን ከ10 ሚሊዮን ዶላር ያለበለጠ ገቢ ብቻ ስናገኛ ቆይተናል ሲሉ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ እጅግ በጣም ውድ የሆኑ ኦፓል፣ ሳፋየር እና ኤምራልድ የመሳሰሉት የከበሩ ማዕድናት እንዳሏት አመልክተው፣ በዘርፉ እውቀትና በኢንዱስትሪ ደረጃ የሚያመርቱ ተቋማት እንደሌሉ አስታውቀዋል። በዚህ የተነሳም ሀብቱ በከንቱ እንዲባክን ሆኖ መቆየቱን ጠቅሰው፣ በዚህ ዘርፍ ጥቂቶችም ቢሆኑ ለመጀመሪያ ጊዜ መመረቃቸው ትልቅ ትርጉም እንዳለው ገልጸዋል። እነዚህ ምሩቃን በሚቀጥሉት ዓመታት ራሳቸው እያባዙ በመቶዎች እና በሺዎች የሚቆጠሩ ባለሙያዎች ያፈራሉ ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል።
እንደ ሚኒስትሩ ማብራሪያ፤ በከበሩ ማዕድናት ዘርፍ ከወርቅ ባልተናነሰ ሁኔታ ኢትዮጵያ በቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ ምርት ለውጭ ገበያ ማቅረብ ትችላለች። በማዕድን ዘርፉ በዋንኛነት ለውጭ ገበያ የሚቀርብ ተደርጎ የሚቆጠረው ወርቅ ነው። ይሁንና በሥነሥርዓቱ የተሠራ የአንድ ኦፓል ዋጋ ከወርቅ በላይ ያወጣል። ይህን የሚያወቁና በዚህ ደረጃ ቆርጠው ለክተው ለዓለም ገበያ ተወዳዳሪ የሆነ ምርት የሚልኩ ባለሙያዎች መመረቃቸው ትልቅ ትርጉም ይኖረዋል። እነዚህ ወጣቶች ደግሞ ለሌሎች ወጣቶች ትምህርቱን ይሰጣሉ፤ ለራሳቸውም ሌሎች አዳዲስ ንግዶችም ይከፍታሉ ።
በሚቀጥሉት ዓመታት በከበሩት ማዕድናት /በጂሞሎጂ/ ዘርፍ ከሚመጡ አዳዲስ የሥራ ፈጠራ ሀሳብ ባለቤቶች /startup/ በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር የኤክስፖርት መጠን ያላቸው ሀብቶች ይገኛሉ ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል።
ወጣቷ ወይዘሪት ሃይማኖት ሲሳይ በዚህ ሙያ የመጀመሪያ ተመራቂ ናት። አብረዋት ከሚሠሩ አጋሮቿ ድጋፍ ጠይቃ ትምህርት ቤቱ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲከፈት፣ የተሟላ ላብራቶሪ እንዲቋቋም በማድረግ ሕልሟን እውን አድርጋለች ያሉት ሚኒስትሩ፤ ለዚህም ኢንዱስትሪ የሚሆን በዘርፉ አይን ከፋች የሆኑ ወጣቶች ለማፍራት ላደረገችው ጥረት አመስግነዋታል።
የዓለም የከበሩ ማዕድናት ማኅበር መሥራችና ሊቀመንበር ሚስተር ጆፍሪ ዶሚኒ በበኩላቸው፤ ጂሞሎጂስት ሲባል የከበሩ ማዕድናትን ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ የሚያወቅ፣ የሚያጠና፣ ለዘርፉ አስፈላጊ ሥራዎችን የሚሠራ መሆኑን ይናገራሉ። ጂሞሎጂስት የከበሩ ማዕድናትን ከመሬት ከማውጣት አንስቶ ለተጠቃሚ እስከሚደርስ ድረስ ያለውን ሥራ በሚገባ አውቆና ተንትኖ መሥራት እንዳለበት ይገልጻሉ።
የኢትዮጵያ በአፍሪካ የከበሩ ማዕድናት በስፋት ከሚገኙባት ሀገራት ውስጥ አንዷ መሆኗን ያነሱት ሚስተር ጆፍሪ ዶሚኒ፤ በዘርፉ የሠለጠነ የሰው ሀብት በማፍራት ሀገሪቱ ያላትን የማዕድን ሀብት በአግባቡ ለመጠቀም የሚያስችል መሆኑን ያመላክታሉ። ማኅበሩ በዚህ ዙሪያ የጀመረውን ሥራ አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በዓለም የከበሩ ማዕድናት ማኅበር የአፍሪካ ዳይሬክተር ወይዘሪት ሃይማኖት ሲሳይ እንዳለችው፤ የኢትዮጵያ የማዕድን ዘርፍ ገና ምንም ያልተነካና ብዙ መሥራት የሚጠይቅ እንደመሆኑ በዘርፉ በርካታ ሰዎችን ማስተማር፣ ማሠልጠን፣ ማሳወቅና ማብቃት ያስፈልጋል። በዚህ ዘርፍ የዓለም የከበሩ ማዕድናት ማኅበር አማካይነት ባለፉት 11 ወራት 12 ተማሪዎች አሠልጥኖ ማስመረቅ ተችሏል። በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በምሥራቅ አፍሪካ የመጀመሪያዎቹ ለሆኑት ለእነዚህ ተመራቂዎች ወደፊት ምን ይሠራሉ? ለሀገራቸውም ምን ይጠቅማሉ? የሚለውን ታሳቢ ያደረገ ትምህርትም ተሰጥቷቸዋል።
ይህ ፕሮጀክት ተግባራዊ እንዲሆን ብዙ ጥረት መደረጉን ጠቅሳ፣ የዓለም የከበሩ ማዕድናት ማኅበር ትምህርቱን ስፖንሰር በማድረግ፣ ተማሪዎች ደግሞ 12 በመቶ ያህሉን ከፍለው እንዲማሩ መደረጉን ገልጻለች። ‹‹ላለፉት 11 ወራት እኔን የማኅበሩን ፕሬዚዳንት ጨምሮ በነፃ ስናስተምር ቆይተናል። በዚህም ሠልጣኞቹ ልምድና በቂ እውቀት ያገኙ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪና ብቁ ባለሙያዎችን አብቅተናል። ›› ትላለች።
እንደ ወይዘሪት ሃይማኖት ማብራሪያ፤ ይህ ፕሮጀክት የተለያዩ ዙሮች አሉት። የመጀመሪያው ዙር የጂሞሎጂ ትምህርት በስኬት ተጠናቋል። ሁለተኛው ዙር ደግሞ እሴት መጨመር ሲሆን፣ በዚህም 10 ተማሪዎች እንዲሠለጥኑ ማድረግ ተችሏል። በቀጣይ ደግሞ አሠልጣኝ የማሠልጠን ፕሮግራም ይከናወናል። በዚህም በአንድ ክፍል ውስጥ አስር ተማሪዎች በሙከራ ሥራ በነፃ እንዲሠለጥኑ ይደረግና፣ ቀጥታ ወደ ሥራ እንዲገቡ ይደረጋል። ከዚህ ቀጥሎም ልዩ የሆኑ ጌጣጌጦች እንዲመረቱ ይደረጋል።
ማዕድኖቹን የሚያወጣው አካል ዋጋውን ማወቅ አለበት የምትለው ዳይሬክተሯ፤ በባሕላዊ መንገድ እየቆፈሩ ያሉ ሰዎችን ሳይቀር በተናጠል ማሠልጠን ቀጣይ ሥራ እንደሚሆንም ጠቁማለች። የመጀመሪያው ሂደት የሚሆነው ማዕድኖቹን እንዴት አድርገን እናውጣው? እንዴትስ እሴት እንጨምርበታለን? ባሕላዊውን አመራረትስ እንዴት አድርገን እንቀይረው? በሚሉት ላይ ግንዛቤ ካስጨበጥን፣ እንዲህ አይነት ምርት አለን ብለን፣ ለዓለም ካስተዋወቅን ገበያው ይመጣል ብላለች።
ወይዘሪት ሃይማኖት ‹‹የእኔ ሕልም ትምህርቱን በአማርኛ ማዘጋጀት ነው። ይህን ለማሳካት ጥረት እያደረኩ ነው›› ትላለች። አሁን ትምህርቱ በእንግሊዘኛ የሚሰጥ በመሆኑ ተማሪዎች ዘርፉን ለማወቅ ፍላጎቱ ያላቸው እና እንግሊዘኛ በቀላሉ አንብበው መረዳት የሚችሉ በመሆናቸው ታይተው እንደተመረጡም ታስረዳለች።
‹‹ማዕድን አላቂ ነው፤ ሁልጊዜ አይገኝም፤ ተፈጥሮም አትሰጠንም፤ ኢትዮጵያ በዘርፉ ገና ብዙም ያልተነካች እንደመሆኗ፣ እንደ አፍሪካም መንቃት አለብን›› በማለት፤ ሀብቱን በራስ አቅም አውጥቶ መቶ በመቶ ተጠቃሚ መሆን አስፈላጊነቱን በአፅዕኖት ትገልፃለች። የውጭ ሰዎች ማዕድኑን አውጥተው የሚከፍሉት ታክስና የመሳሰሉት ገቢዎች ብቻቸውን በቂ እንዳልሆኑም አስገንዝባለች። የአሕጉሪቱን የከበሩ ማዕድናት የማልማቱ ሥራ መታገዝ ያለበት ትክክለኛ መንገድ በአፍሪካና በአፍሪካ ብቻ መሆን እንዳለበትም አስታውቃለች።
ወጣት ዳዊት ታደገ ከዕለቱ ተመራቂዎች አንዱ ነው። ዳዊት የማዕድን መሐንዲስ ሲሆን፣ ማዕድን ለውጭ ገበያ በማቅረብ /ኤክስፖርት/ ላይ ተሰማርቶ እየሠራ ይገኛል። በማዕድን ማውጣት ሥራ ላይም ከዓለም አቀፍ ተቋም ጋር አብሮ እንደሚሠራ ይገልጻል።
በአንድ ወቅት ወደ ታይላንድ በሄደበት አጋጣሚ የሀገሪቱ የከበሩ ማዕድናት በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገሮች ያላቸውን የዋጋ ልዩነት እና በዘርፉ የሚታዩ ክፍተቶችን መረዳት ችሏል። ‹‹ለምሳሌ በላብራቶሪ የበለጸጉ፣ መለየት የማንችላቸው ድንጋዮች አሉ›› ይላል። ከዚሁ ጋር የተያያዙ ብዙ አይነት ግድፈቶች እና ሌብነቶች እንዳሉም ይጠቁማል። እነዚህና መሰል ነገሮችን ለማወቅ የከበሩት ማዕድናትን የተመለከተ እውቀት እንደሚያስፈልገው መረዳቱን ያነሳል አጋጣሚውን አግኝቶ የመጀመሪያው ተመራቂ ለመሆን መብቃቱንም ይናገራል።
ትምህርቱን ለመከታተል 11 ወራት ያህል መፍጀቱንና ‹‹ኬረር ጂሞሎጂ›› የሚባል ኮርስ መውሰዳቸውን የሚገልፀው ወጣት ዳዊት ‹‹ኬረር ጂሞሎጂ›› ቀለም ያላቸው ድንጋዮች እና ዳይመንድን ጭምር የሚያካትት ትምህርት የሚሰጥበት መሆኑን ያነሳል። ሥልጠናው በአብዛኛው በተግባር ተደግፎ በኦንላይን እንደተሰጣቸው ይገልጻል። የከበሩ ድንጋዮችን እንዴትና በምን አይነት መንገድ መለየት ይቻላል? በሚለው ላይ በቂ እውቀት እንዳገኙበትም አስታውቋል።
ወጣት ዳዊት እንደተናገረው፤ በማዕድን ምሕንድስና ለሰባት ዓመታት፣ በማዕድን የውጭ ገበያ /ኤክስፖርት/ ላይ ደግሞ ለሦስት ዓመታት ያህል ሠርቷል። በዚህ ዘርፍ በጣም የበዛ የእውቀት ክፍተት እንዳለ ያውቃል። ሥልጠናው ይህን ክፍተት እንደሞላ አስችሎታል። ንግዱንም በምን አይነት መንገድ መሄድ እንዳለበት በደንብ ለመገንዘብ መቻሉን ያመለክታል። በሥልጠናው ያገኘውን በቂ እውቀት በመጠቀም የተወሰኑ የላብራቶሪ እቃዎችን ከውጭ በማስመጣት ለመሥራት ዝግጅት ማድረጉን ይናገራል። ያገኘውን እውቀት ለሌሎች በማጋራት ዘርፉ የተሻለ እንዲሆን እንደሚሠራ ቃል ገብቷል።
‹‹በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በተሰጠው በዚህ ሥልጠና ይህን እውቀት በማግኘቴ ላቅ ያለ ደስታ ተሰምቶኛል። ወደፊት በዘርፉ ያለኝን ልምድና እውቀት ተጠቅሜ ለራሴም ለሀገሬም አስተዋፅዖ አበረክታለሁ ። ይህን እድል የሰጡትን አካላትም አመሰግናለሁ›› ሲል ሀሳቡን ቋጭቷል።
ሌላኛዋ ተመራቂ ወጣት ጵንኤል ፋሲካ ስትሆን፤ መጀመሪያ ዲግሪዋን ከአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በጂኦሎጂ ትምህርት ዘርፍ ያገኘች ናት። የዓለም የከበሩ ማዕድናት ማኅበር ፕሮጀክቱን ሲያስተዋወቅ ስትሰማ አጋጣሚውን ተጠቅማ ወደ ሥልጠና መምጣቷን ትናገራለች።
ወጣት ጵንኤል፤ ‹‹ትምህርቱ 95 በመቶ ተግባር ላይ ያተኮረ በመሆኑ ማዕድናትን መለየት የሚያስችሉ መሣሪያዎች እንዴት መጠቀም እንዳለብን ተምረናል። የማዕድናቱን ጥራት ማወቅ፣ ከቀለም፣ ከአቆራረጥ እና ከመሳሳሉት አንጻር እንዴት ዋጋውን ማወቅ እንደምንችል ተምረናል። አልማዝን /ዳይመንድን/ በተመለከተ ተገቢውን ትምህርት አግኝተናል›› ትላለች።
በሀገራችን የከበሩ ማዕድናትን ለይቶ የማወቅ ክፍተቶች እንደነበሩ የምታነሳው ተመራቂዋ፤ ማዕድናቱ የሚለዩት በልማዳዊ መንገድ እንደሆነም ትጠቁማለች። ቀይ ድንጋይ ያየ ሰው ሁሉም ቀይ ድንጋይ ሩቢ ይመስለው እንደነበር ጠቅሳለች። ማዕድናቱን መለየት ራሱን የቻለ ትምህርት እንዳለው ገልጻ፤ ይህን ትምህርት ከወሰድን በኋላ ማዕድናቱን የመለየትና ጥራቱ ምን ያህል እንደሆነ ምን ያህል ዋጋ እንደሚያወጣ ማወቅ ችለናል ብላለች። ሥልጠናው በዘርፉ ያሉ ክፍተቶችን እንደሚሞላ ጠቁማለች።
በዘርፉ የተማረ ሰው ኃይል እንዲበዛ መደረጉ ሀገሪቱ እስከዛሬ ስታጣ የነበረውን ሀብት በአግባቡ አውቃ እንድትጠቀምበት ያስችላል የምትለው ጵንኤል፤ የኢትዮጵያ የከበሩ ማዕድናት አሁን በሀገር ውስጥ እየተሸጡ ያለበትና በዓለም ገበያ ላይ ያለው ዋጋቸው ሲታይ ትክክለኛው ዋጋ በጣም እንደሚለያይ ጠቁማለች። ይህን ትክክለኛ ዋጋ ከማወቅ አንጻር ሥልጠናው ብዙ ችግሮችን ይቀርፋል ስትል አስገንዝባለች።
‹‹ትምህርቱ ለመጀመሪያ ጊዜ በመሰጠቱና እኔም በመውሰዴ እድለኛ ነኝ፤ ወጣት እንደ መሆኔ በቀጣይ ያሉትን መልካም አጋጣሚዎችን በመጠቀም በዚህ ዘርፍ በሰፊው እንቅስቃሴ በማድረግ ዘርፉ አንድ እርምጃ ወደፊት እንዲመጣ እሠራለሁ›› ብላለች። አጋጣሚው በከበሩ ማዕድናት ዘርፍ ለመሠማራት ለሚፈልጉ በር ከፋች መሆኑን ጠቁማ፣ በተለይ ሴቶች በሙያው በብዛት እንደሚያስፈልጉና በዘርፉ ቢሰማሩ ውጤታማ እንደሚሆኑ ትገልፃለች።
ከሥልጠናው በፊት ስለከበሩት ማዕድናት ያለኝ እውቀት ውስን ነበር ያለችው ጵንኤል፤ ከሥልጠናው በኋላ ያለኝ አመለካከትም ሆነ እውቀት በእጅጉ የተለየ ሆኗል ብላለች። ‹‹የከበሩ ማዕድናትን ለማግኘት ብዙ ጥረት ማድረግን እንደሚጠይቅ ጠቁማ፣ ‹‹ማዕድኑ በመከራ ተገኝቶ ውበትን የሚሰጥ የክብር እቃ ነው›› ብላለች።
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ሐምሌ 5/2016 ዓ.ም