ሕይወት ቀያሪ ድጋፍ ለእናቶች

ወይዘሮ መሠረት በሻዳ ትባላለች። ምትኖረው እዚሁ አዲስ አበባ ጠመንጃ ያዥ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነው። ባለትዳርና የአራት ልጆች እናት ነበረች። ባሏ መጠጥ ጠጥቶ እየመጣ ይደበድባታል። ለልጆቿ ስትል ሁሉን ችላ ብትኖርም በመጨረሻ አንገሽግሿት ከባሏ ተፋታች። ከፍቺ በኋላ ግን ሕይወት እንዳሰበችው አልሰመረላትም። ኑሮ በጣም ከበዳት። ልጆቿን ለማሳደግ ብርቱ ጥረት ብታደርግም ብቻዋን አልቻለችም። ልጇን አዝላ እንጀራ እየጋገረች ገቢ ለማግኘት ሞክራለች።

በየኮንዲሚኒም ቤቱ እየተዟዟረች ልብስ በማጠብ ልጆቿን ለማሳደግ ጥረት አድርጋለች። በመጨረሻ ተስፋ ቆርጣ ልጇን ይዛ ጎዳና ወጥታ በልመና ሕይወቷን ለመምራት ተገዳለች።

አንድ ቀን የወረዳ ሰዎች መንገድ ላይ ስትለምን አዩዋት። ‹‹ላይፍ ሴንተር›› ከተሰኘና መበለቶችንና /ባሎቻቸው የሞቱባቸው ወይም የተፋቱ ሴቶች/ ወላጅ አልባ ህፃናትን ከሚረዳ ድርጅት ጋር አገናኟት። የመጨረሻ ልጇ እዚህ ድርጅት ውስጥ ከገባች ሰባት ዓመት አስቆጥራለች። በዚህ ድርጅትም የተለያዩ የትምህርት መሣሪያዎችና የገንዘብ ድጋፍ ይደረግላታል። እርሷም በድርጀቱ የልብስ ስፌት ሥልጠና ተሰጥቷታል። ከድርጅቱ ፈሳሽ ሳሙና በቅናሽ እየወሰደች አትርፋ የምትሸጥበት እድል ተመቻችቶላታል። አሁን ደግሞ ድርጅቱ ባመቻቸው የልብስ ስፌት ሥለልጠና ላይ ተሳትፋ ተጨማሪ ሕይወቷን የምታሻሽልበት እድል ተመቻችቶላታል።

ወይዘሮ ሙሉ ግርማይ የላይፍ ሴንተር መስራችና ዳይሬክተር ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት ላይፍ ሴንተር የተመሰረተው ከአስራ አንድ አመት በፊት ነበር። የተመሰረተበት ዋና ዓላማ ደግሞ በተለያዩ ምክንያቶች ወላጅ አልባ የሆኑ ህፃናትንና ብቻቸውን ልጆቻቸውን በማሳደግ ላይ የሚገኙ እናቶች ለመደገፍ ነው። ለወላጅ አልባ ህፃናት በርካታ አገልግሎት ይ

የገንዘብ ድጋፍ ያገኛሉ። የውጭ ሀገራት በስፖንሰርሺፕ እንዲያግዟቸው ይደረጋል። ከገንዘብ በተጨማሪ በሕይወታቸው ለውጥ እንዲያመጡ ኮምፒዩተርን ጨምሮ የተለያዩ ሥልጠናዎች ይሰጧቸዋተል። ትምህርታዊ ድጋፍ ይደረግላቸዋል። የምክር አገልግሎት ያገኛሉ።

በተለያዩ ምክንያት ካባሎቻቸው ጋር የተለያዩ ሴቶች ደግሞ የብድር አገልግሎት እንዲያገኙ ይደረጋል። ሰጣል። ብድሩን ወስደው አነስተኛ ንግድ እንዲጀምሩና እንዲሠሩ ይደረጋል። በሚሰጣቸው አነስተኛ ሥልጠና አማካኝነት ሴቶቹ ንግድ አውቀውና ሰርተው ሕይወታቸውን ሲለውጡ ታይተዋል። እስካሁን ባለው ሂደትም ሥልጠና ወስደው አነስተኛ ንግድ የጀመሩ 500 እናቶች ሕይወታቸውን መቀየር ችለዋል። ቶሊ የተሰኘው የረድዔት ድርጅት ደግሞ ለእናቶች የብድር አገልግሎት ድጋፍ ያደርጋል።

ወይዘሮ ሙሉ እንደሚሉት ላይፍ ሴንተር ለእናቶች ያዘጋጀው ሥልጠና በምን ሁኔታ ላይ እንዳሉ ለማወቅ፣ እርስ በርሳቸው ልምድ እንዲለዋወጡ፣ እንዲመከሩ፣ እንዲማሩና እንዲሰለጥኑ ነው። ሥልጠናው መሪ ቃልም ‹‹ድል›› ነው። ድል ማሸነፍ እንደሚቻል፤ በተለይ እናቶች ልጆቻቸውን ብቻቸውን ሲያሳድጉ መከራና ስቃይ ይኖራል። ነገር ግን ደግሞ ከበረቱ መከራውና ስቃዩ አልፎ ባለድልና በኑሯቸው ሠርተው አሸናፊ ሊሆኑ እንደሚችሉ ለማበረታታትና ለመምከር ነው።

ቶሊ የተሰኘው የብድር አገልግሎት የሚሰጠው የርዳታ ድርጅት የእናቶቹን አነስተኛ ቢዝነስ ጎብኝቷል። እናቶች በሚሠሯቸው ሥራዎችም ተደምመዋል። ወንድ ብቻ ይሰራዋል ተብሎ የሚታሰብ ሥራም ሲሠሩ ነው የታዩት። በዚህም እናቶች ምንም ነገር መሥራት እንደሚቻል እያሳዩ ነው። በቀጣይም ያሳያሉ። ሥልጠናውም የእርስ በርስ ትውውቅ፣ የልምድ ልውውጥ እንዲያደርጉ አስችሏቸዋል። ችግር እንደሚታለፍ፣ ታልፎ መቆም እንደሚቻል ያዩበትም ጭምር ነው ሥልጠናው።

የላይፍ ሴንተር አጋርና መቀመጫውን አሜሪካን ሀገር ያደረገው ‹‹ቶሊ›› የተሰኘው ድርጅት መሥራች ዶክተር ኤዲ ያሳ በበኩላቸው እንደሚሉት ድርጅቱ በአጭሩ ‹‹touch of love›› ቶሊ ተብሎ ይጠራል። ተቀማጭንቱ በአሜሪካን ሀገር ኮሎራዶ ግዛት ሲሆን ከላይፍ ሴንተር ጋር በጋራ ይሠራል። በጥቃቅን ንግድና ቁጠባና ብድር እንዴት መሥራትና ራስን መለወጥ እንደሚቻል ማሳየት ነው የድርጅቱ ዋነኛ ዓላማ። ልክ

ቻይናውያን ‹‹አሳ ከምትሰጠው አሳ እንዴት ማስገር እንዳለበት አስተምረው›› እንደሚሉት የድርጅቱ ፍልስፍናም ይኸው ነው። በተመሳሳይ ላይፍ ሴንተርም ሴቶችን ለማበረታታትና ለማገዝ ቁርጠኝነት እንዳለው ለማየት ተችሏል።

ድርጅቱ ከላይፍ ሴንተር ጋር ለብዙ ዓመታት በአጋርነት ሠርቷል። የድርጅቱ ፍላጎትም ይህ አጋርነት ጤናማ ሆኖ ለረጅም ጊዜ እንዲጥል ነው። ሴቶች ራሳቸውን በራሳቸው ችለው እንዲኖሩ ማድረግ የድርጅቱ ሌላኛው ዓላማ ሲሆን ሴቶች ሥልጠና ወስደውና ራሳቸውን ችለው ንግድ መጀመር የሚችሉበትን ሁኔታ ያመቻቻል። ይህም ድጋፍ ሴቶች ሕይወታቸውን በብዙ መልኩ እንዲቀይሩ ያስችላቸዋል። በዚሁ ድጋፍ አማካኝነት ሴቶች ሥልጠና ወስደውና የገንዘብ ድጋፍ ተደርጎላቸው በአነስተኛ ቢዝነስ እንዴት ሕይወታቸውን መቀየር እንደቻሉ ለማየት ተችሏል።

ሴቶች ትንሽ እገዛ ቢደረግላቸው እንዴት ራሳቸውን እንደሚችሉና የቤተሰቦቻቸውን ፍላጎት እንደሚያሟሉ ድርጅቱ ለመረዳትም ተችሏል። ሴቶች ሥራ በመጀመራቸው ልጆቻቸውን ትምህርት ቤት መላክና ቤተሰቦቻቸውን ማገዝ ችለዋል። ይህን ግን ድርጅቱ ለብቻው አላደረግም። የሴቶቹ ሕይወት ሊቀየር የቻለው በላይፍ ሴንተር ድጋፍም ጭምር ነው። ሴቶች ትልቅ አስበው ሕይወታቸውን እንዲቀይሩም ነው የድርጅቱ ዓላማ።

የኢትዮጵያ ሴቶች ብልህና በትንሽ ነገር ራሳቸውን መቀየር የሚችሉ ናቸው። የድርጅቱም ምኞት ኢትዮጵያውያን ሴቶች ትልቅ እንዲመኙና በትልቁ እንዲቀየሩ ነው። ከዚህ አንፃር ድርጅቱ ላይፍ ሴንተር ሴቶችን ለመደገፍ እያደረገ ያለውን ጥረት በማድነቅ በቀጣይም አብሮ የሚሠራ ይሆናል። በተለያዩ ምክንያቶች ማለትም በጦርነት፣ ግጭትና ከኑሮ ውድነት ጋር በተያያዘ ችግር ውስጥ ያሉ ሴቶችን ለመደገፍ ድርጅቱ ዝግጁ ነው።

አስናቀ ፀጋዬ

አዲስ ዘመን ሐምሌ 4/2016 ዓ.ም

Recommended For You