“የውስጥ ችግሮቻችንን በውይይት ፈትተን ሙሉ አቅማችንን ለልማት ካዋልን ከበለፀጉት ሀገራት መካከል ለመሆን እንችላለን” ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ርዕሰመስተዳድር

ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል እራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄው በሕዝበውሳኔ ምላሽ አግኝቶ 11ኛው ክልል ሆኖ ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ከገባ ሁለት ዓመት ተኩል ጊዜ ተቆጠረ። ክልሉ በዚህ አጭር ጊዜ በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ የተከናወኑትን ተግባራት የጋዜጠኞች ቡድን በክልሉ ተገኝቶ ቃኝቷል። ቅኝቱን መሠረት በማድረግ ከክልሉ ርዕሰመስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) ጋር ቆይታ አድርገናል።

አዲስ ዘመን፡- ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል እራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ መልስ ያገኘው ከሀገራዊ ለውጥ በኋላ መሆኑ ይታወሳል። ሀገራዊ ለውጡ ለክልሉ ምን አይነት ዕድሎች ይዞለት እንደመጣና ቱሩፋቶች ናቸው የሚሏቸውን ይግለጹልን።

ኢንጂነር ነጋሽ (ዶ/ር)፡-ሕዝቡ መሠረታዊ የሆኑ ጥያቄዎችን በማንሳት ትግል ሲያደርግ እንደነበር ይታወሳል። ይህን አዲስ ክልል የወለደው፤ የነበሩት የሕዝብ ጥያቄዎች ናቸው የሚል እምነት አለኝ። የፍትሀዊ ተጠቃሚነት፣ በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ ውክልና፣ በመሠረተልማት፣ ፍትሐዊ የሆነ የመልማት አቅምን መሠረት ያደረገ ድጋፍ አልተደረገልንም፣ ሌሎች በሚገኙበት ደረጃ ልንገኝ አልቻልንም፣ በተፈጥሮ የተሰጠን ሰፊ ፀጋ የአካባቢውን ሕዝብ ተጠቃሚ በሚያደርግ መልኩ ጥቅም ላይ አላዋልንም፣ ይህንንም ማድረግ ያልቻልነው በኢፍትሀዊነት ምክንያት ነው የሚሉ ጥያቄዎች ነበሩ።

በመልካም አስተዳደር ደግሞ፤ ፍትህ፣ ልማት፣ የተለያዩ ወቅታዊና ተከታታይ የሆኑ ድጋፎችና እገዛዎች ለማግኘት ከመኖሪያቸው አካባቢ እስከ አንድ ሺ ኪሎ ሜትር ለመጓዝ እንደሚገደዱ፣ ወደእነርሱ ለመምጣት የሚፈልጉትም በተመሳሳይ ረጅም እንደሚጓዙ፣ በዚህ የተነሳም የአካባቢው ሀብት ማህበረሰቡን ተጠቃሚ በማያደርጉ ወጪዎች ይባክናል የሚል ነበር።

የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎቻችንም በጊዜውና በተገቢው መንገድ እየተፈቱልን አይደሉም፤ ተመጣጣኝ የሆነ የፖለቲካ ውክልና የለንም ሲልም ሕዝቡ ያነሳ ነበር። በእነዚህ ተደራራቢ ምክንያቶች ኢፍትሀዊነት ሰፍኗልና ኢፍትሀዊነትን መፍታት የሚችል፣ ፍትሀዊ የሕዝብ የልማት ተጠቃሚነት፣ የፖለቲካ ውክልና፣ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል መዋቅር ያስፈልገናል የሚል ጥያቄ ነበር።

ጥያቄዎች ለሶስት አስርት ዓመታት ሲነሱ ቆይተዋል። ጥያቄ የሚያነሳ በሌላ መንገድ ይፈረጅ ነበር። ሀገራዊ ለውጥ እንደተደረገም ቀደም ሲል ይቀርቡ የነበሩ ጥያቄዎች የቀረቡት ገንነው ነበር። መንግሥትም ጥያቄው የሕዝብ ከሆነ ምላሽ ማግኘት እንዳለበት አምኖበት ትኩረት ሰጥቶ ሥራውን ሰርቷል። ጥያቄው የሕዝብ ስለመሆኑና የጥቂት ፖለቲካ ልሒቃን አስተሳሰብ ነው የሚለውን ለመለየት በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የሚመራ ከአካባቢው የተመረጡ አካላት የተሳተፉበት የሰላም አምባሳደር ተቋቁሞ የውይይት መድረኮች ተዘጋጅተው መረጃ የማሰባሰብ ስራ ተሰርቷል። በተጨማሪም መንግሥት የራሱን የአሰራር ሥርዓት ዘርግቶ ፍተሻ አድርጓል።

በተለያየ መንገድ ለማጣራት የተሰሩት ሥራዎች ያሳዩት አንድ ውጤት ነው። ሕዝቡ ከነባሩ ክልል ተነጥሎ በተለየ የክልል የመንግሥት አስተዳደር ሥርዓት እራሱን ማስተዳደር ይፈልጋል። ስለዚህ ይሄ ምላሽ ማግኘት አለበት የሚል ነው። እዚህ ደረጃ ላይ ከተደረሰ በኋላም በቂ አይደለም ተብሎ ጥያቄው የአብላጫው ሕዝብ ስለመሆኑ የማጣራት ሥራ ተሰርቷል። ይሄ መረጋገጥ የሚገባው በቀጥተኛ ዴሞክራሲ ሥርዓት በሪፈረንደም መሆን አለበት የሚል ድምዳሜ ላይ ተደረሰ። ድምጽ መስጠት የሚችል ሁሉ ድምጽ እንዲሰጥ ተደረገ። 98 በመቶ የሚሆን ሕዝብ ድምጽ ሰጥቶ በተሰጠው ድምጽ መሠረት 11ኛው የፌዴሬሽን አካል ሆኖ ተደራጅቷል።

በክልል መደራጀት ያስገኘው ጥቅም፤ አንደኛው እራስን በራስ ማስተዳደር በሕገመንግሥቱ የተቀመጠውን የዴሞክራሲ ሥርዓት መገለጫ የሆኑ፣ መብት የማስከበር፣ የሕዝብ ድምጽ የሚሰማበት አውድ መፍጠር፣ በዚህ ሂደት ደግሞ የዴሞክራሲ ሥርዓትን የመለማመድ፣ የሕዝቦች ድምጽ የሚከበርበት አብላጫ ድምጽ የሚገዛበት አሰራር ሥርዓት ለመፍጠር የተደረገው፣ ትልቅ ትምህርት አስገኝቷል የሚል እምነት አለኝ። ያለምንም ግጭት፣ ጦርነት ሳይኖር፣ ሰዎች ከአካባቢያቸው ሳይፈናቀሉ፣ የሰው ሕይወት ሳይጠፋ፣ ንብረት ሳይወድም፣ በሰላማዊ መንገድ መሸጋገር ትልቁ ፋይዳ ነው።

ክልል ሆኖ ከተደራጀ በኋላ፣ የሕዝባችን አንገብጋቢ የሆኑ ጥያቄዎችን ወደ ሕዝቡ ወርዶ የመፍታትና ምላሽ የመስጠት ጉዳይ አንዱ ትልቁ ውጤት ነው ብለን እንወስዳለን። ክልሉ ከመቋቋሙ በፊት ሸካ ዞን፣ ምእራብ ኦሞ ዞን አካባቢ የሰዎች ሰላማዊ እንቅስቃሴ የተገደረገበት፣ ጥቂት ቡድኖች ወጥተው አካባቢውን ለመቆጣጠር ሙከራ ያደረጉበት፣ በአንዳንድ ቦታዎችም የሰው ሕይወት የጠፋበት፣ ንብረትም የወደመበት፣ በአጠቃላይ የማህበረሰቡ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ የተገታበት ጊዜ ነበር።

ክልል ከሆነ በኋላ ግን በአፋጣኝ፣ የችግሩን መንስኤ ለማወቅና መፍትሄም ለመስጠት የተደረገው ከማህበረሰቡ ጋር የጋራ ምክክር ነው። ከምክክሩ በኋላ መሣሪያ አንግበው ጫካ የገቡ፣ ሕገወጥ ቡድን ሆነው ሲዘርፉ የነበሩ፣ መሣሪያቸውን አውርደው እንዲመለሱና ከሕዝብ ጋር እንዲቀላቀሉ የማድረግ፣ አንዳንዶቹ ደግሞ የሕግ ፍርደኛ ሆነው ለረጅም ዓመታት ተፈርዶባቸው እያሉ ከእስርቤት አምልጠው መሣሪያ ይዘው ጫካ በመግባት ጥቃት ሲያደርሱ የነበሩ ናቸው።

እነርሱም ወደ ሕግ አግባብ እንዲመለሱ የማድረግ፣ መጠነኛ የወንጀል ተሳትፎ ያላቸውንና በሂደት ውስጥ ተባባሪ ናቸው የተባሉትንም ለይቶ በማህበረሰባዊ የፍትህ ሥርአት ለተበዳይ ወገን የሚገባውን ካሣ እንዲክሱ በማድረግ፣ ማህበረሰቡም፣ ተበዳዩም እራሱ ምህረት እንዲያደርግ በማድረግ በወንጀል ምክንያት ተጠርጥረው የሕግ ሂደት እየተከታተሉ የነበሩትን አካላት ምህረት ሰጥቶ የመልቀቅ ሥራ ተሰርቷል።

ይሄ ትልቁ በሰላምና ፀጥታ ዙሪያ አካባቢን ለማረጋጋት የተከናወነ ነው። በዚህ ሂደት ውስጥ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የኃይማኖት አባቶች፣ ወጣቶች ከፍተኛ ተሳትፎ አድርገዋል። ሂደቱ ግን ቀላል አልነበረም። ከሕገወጥ ቡድን ጋር ልታጣሉን ነው። እገሌ ነው መሣሪያ ይዞ ጫካ የገባው ብለን ብንጠቁም መልሰው እኛኑ ያጠቁናል፤ መንግሥት አቅሙን ያሳይ የሚል ከሕዝቡ ይነሳ ነበር። የተረጋጋ አካባቢ መፍጠር የቻልነው መንግሥት ሕግ የማስከበር ኃላፊነቱን መወጣት አለበት የሚል አቋም ይዘን፣ የፀጥታ መዋቅራችንን እንደገና የማደራጀትና በተለያየ መንገድ የማብቃት ሥራ በመሥራትና ወደ ማህበረሰቡም በመቅረብ ተከታታይ ተግባራትን በማከናወን ነው። ይሄ ትልቁ ውጤትና ቱሩፋት ተደርጎ ይወሰዳል።

ከኢኮኖሚ ተጠቃሚነት አኳያም፤ አካባቢው በተፈጥሮ ፀጋ የታደለ ለግብርና ሥራ ምቹ ነው። ክልሉ ወደ አስር ወር ዝናብ ያገኛል። ከቆላ አስከደጋ ማንኛውም አይነት ምርት ይመረታል። ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታቸው ከፍተኛ የሆኑ ቡና፣ ሰሊጥ፣ ቅመማቅመምና የማር ምርቶች ይመረታሉ። ይሁን እንጂ የማህበረሰቡ ኑሮ በዚህ ልክ አልተለወጠም። በአካባቢው ሀብት የኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲሆን ምን መሰራት አለበት የሚለው ዋና የትኩረት አቅጣጫ ነው። በግብርና፣ በኢንደስትሪው፣ በአገልግሎት ዘርፍ፣ በቱሪዝም፣ በማዕድንና በሌሎችም የመለየት ሥራ ሰርተናል። የክልሉን አጠቃላይ የልማትና የኢኮኖሚ የ10 ዓመት ፍኖተ ካርታ አዘጋጅተናል።

በተለይም በግብርናው ዘርፍ ክልሉ በሚታወቅበት በቡና፣ በቅመማቅመም፣ በሰሊጥ፣ ከምግብ ፍጆታ ባለፈ ለገበያ በሚቀርቡ ምርቶች ላይ መሥራት እንደሚገባና ለዚህም ዘመናዊ የግብርና አስተራረስና አመራረት ዘዴ፣ ሜካናይዜሽንን የምናለማምድበት መንገድ መከተል አለብን ብለን ባደረግነው ሙከራ በግብርናው ከ182 በላይ የተለያዩ ኢንቨስትመንቶችን መሳብ ችለናል። ወደ 16 ቢሊዮን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ ናቸው።

በሰራነው ሥራ የቡና ምርታማነትንም የመጨመር አቅም ፈጥረናል። ቡና ላይ ምርታማነትን የሚጨምሩ አሰራሮችን በመከተል ከአንድ ሄክታር ከስድስትና ሰባት ኩንታል ያልበለጠ ምርት ይገኝ የነበረውን ወደ አስር ኩንታልና ከዚያም በላይ ከፍ ማድረግ ተችሏል። በመሥኖ የማልማቱ ልምድ መዳበሩም ምርታማነቱን ከፍ እያደረገው ነው። ቅመማቅመም በስፋት እንዲመረት እድል ተፈጥሯል። ለውጭ ገበያ የማር ምርት የሚያቀርቡ ባለሀብቶች ማፍራት ተችሏል። በሰሊጥ ምርትም ሜካናይዜሽንን አለማምደናል። ወደ 66 የእርሻ ትራክተሮች ተገዝተው ለአርሶ አደሩና ለወጣቱ ተሰራጭተዋል።

የሌማት ቱሩፋት ከተጀመረ በኋላ ደግሞ፣ ለግብርናው አጋዥ የሆነ ነገር መገኘቱን ግምት ውስጥ በማስገባት፣ በዶሮ እርባታ፣ በከብት ማድለብ፣ በወተት ላሞች፣ በንብ ማነብ፣ በአሣ ምርት ሰፊ ልማት እየተከናወነ ነው። ባለፈው በጀት ዓመት ወደ አንድ ነጥብ አራት ሚሊዮን የዶሮ ጫጩት ተሰራጭቷል። በተያዘው በጀት ዓመትም በአስር ወራት አንድ ነጥብ ሰባት ሚሊዮን የዶሮ ጫጩት ተሰራጭቷል። በዚህ በኩል በአርሶ አደርና በቤተሰብ ደረጃ ፍላጎት ተፈጥሯል። የዶሮ እርባታው የእንቁላል ገበያን አረጋግቷል። በዚህ በኩል በደንብ የተሰራበትንና ያልተሰራበትን አካባቢ በመለየት ልማቱን ለማጠናከር፣ በተለይም ወጣቶች ተደራጅተው በስፋት እንዲሰሩ ጥረት እየተደረገ ነው። በግብርና ሥራ ወቅት አርሶ አደሩን በተከታታይ የመደገፍ ሥራም ተጠናክሯል።

ከመሠረተ ልማት አኳያ የመንገድ፣ የትምህርት ቤትና የጤና፣ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኮሌጆች ግንባታዎች ሥራ ላለፉት ዘጠኝና አስር ዓመታት አልነበሩም። በዚህ በኩል ቅድሚያ የሚሰጣቸውን በመለየትና የክልሉን ሀብት መሠረት በማድረግ ሆስፒታሎች፣ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኮሌጆችን፣ አንዱን ወረዳ ከሌላው ጋር የሚያገናኙ መንገዶች ላይ ትኩረት ሰጥቶ በመሥራት ወደ ሕዝብ የመቅረብ እድል ፈጥረናል። በዚህ ሂደት ውስጥ ልምምድ መሆን አለበት ብለን የምንወስደው የማህበረሰብ ተሳትፎ ነው። የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል በተጀመረ ሥራ ማህበረሰቡ በአንድ ዓመት ብቻ አራት መቶ አስራ አራት ሚሊዮን ብር ለግንባታ ሰጥቷል። ለመማሪያ መጽሐፍት ማሟያም 65 ሚሊዮን ብር ማህበረሰቡ አዋጥቷል። እንዲህ ያለው ድጋፍ የመጽሐፍት ጥምርታን የተሻለ ለማድረግ ያስችላል።

በክልሉ የተረጋጋ የፖለቲካ አካባቢ መፍጠር ተችሏል። በተለይም በኢመደበኛና ሕገወጥ በሆነ አደረጃጀት ይደረግ የነበረ እንቅስቃሴን ለመከላከል ተጠቃሽ ነው። የመንግሥትን ሚና መጫወት የሚችል ሥልጣንና ኃላፊነት ያለው የመንግሥት መዋቅር የኃላፊነት ሚናውን እንዲወጣ፣ በፖለቲካውም በተመሳሳይ ኃላፊነት የተሰጠው አካል እንዲወጣ፣ ደጋፊ አባሉም በዚሁ ማእቀፍ ውስጥ እንዲያልፍ የሚል አቋም ተይዟል። ከዚህ ውጭ ያለው የራሱን ፍላጎትና ስሜት በሕዝብ ላይ በማንፀባረቅ ሕዝብን ከሕዝብ፣ ብሄረሰብን ከብሄረሰብ፣ ሕዝብን ከመንግሥት ጋር የሚያጋጭ የፖለቲካ አስተሳሰብ መራመድ የለበትም በሚል ተከታታይ የምክክር መድረኮችን በማዘጋጀት የፖለቲካ አመለካከት በሀሳብ የማሸነፍ ልምምድ እንዲሰፋ የማድረግ ሥራ ተሰርቷል። ገዥው መንግሥትና ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች መደጋገፍ ባለባቸው ሁሉ የሚደጋገፉበት ሁኔታ መፍጠር የሚቻልበት እድል መኖሩም ግምት ውስጥ ገብቷል።

በክልል መደራጀት ውስጥ አዲስ አስተሳሰብ ይዘን የመጣነው፤ ቀደም ሲል ባለው ተሞክሮ ክልሎች ያላቸው አንድ ማእከል ነው። ሁሉም የመንግሥት ተቋማት፣ የፓርቲ መዋቅርም እንደ ክልል ምክር ቤቶችና የፍትህ ተቋማት የሚገኙት አንድ ማእከል ውስጥ ነው። አንድ ቦታ በመሆኑ ምክንያትም የለማው ወይም ያደገው አንድ አካባቢ ነው። ሁሉም አካባቢ ተመጣጣኝ የሆነ ልማትና እድገት በከተሞቻችን ላይ ሊረጋገጥ አልቻለም። ከዚህ ትምህርት ወስደን ተቋሞቻችን ክላስተር ብናደረግ ብለን ምክክር አደረግን። መግባባት ላይ ከደረሰን በኋላ የአካባቢውን መልማትና ፀጋዎቹን መሠረት ያደረገ ልየታ በማድረግ በአራት ክላስተር በመከፋፈል ወደ ሥራ ገብተናል። በዚህ መልኩ መንቀሳቀሱ በማህበረሰቡ ዘንድ ክልሉ የኔ ነው የሚል ስሜት ፈጥሯል። በዚህም ብዝሀነት አስተሳሰብ ወደመሬት ወርዷል ብለን እናስባለን።

አዲስ ዘመን፡- በክልሉ በክላስተር የሙዝ ልማት ማከናወን ያመጣው ውጤት እንዴት ይገለጻል?

ኢንጂነር ነጋሽ (ዶ/ር)፡– ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር የምንከተላቸው ስልቶች አሉ። አንዱ ማዳበሪያና ሌሎችም የግብርና ግብአት ሲሆን፣ በቴክኖሎጂ የታገዘ የውሃ አማራጭ ሌላው ነው። መስኖ ባይቻል እንኳን በባህላዊ መንገድ ውሃ ጠልፎ ወደማሳ በማስገባት ለእርሻ ልማት ማዋል ነው። አርሶአደሮች በኩታገጠም ወይንም በክላስተር የግብርና ዘዴ መጠቀማቸው በተለያየ መንገድ ተጠቃሚ ያደርጋቸዋል። በአንድ አቅራቢያ ላይ ሆነው ተመሳሳይ የሆነ ምርት ቢያመርቱ የዘር ጊዜያቸውን ለመወሰን፣ ወጥ በሆነ መንገድ ግብአት ለማግኘት ያስችላቸዋል። ምርት ሲደርስም የግብይት ስርአቱን ለማሳለጥ ያግዛል።

ማህበረሰቡ የግብርና ሥራውን ሲያከናውን የቆየው ቤቱን በአጥር አጥሮ፣ የእርሻ ማሳውንም ከልሎ ድንበር አበጅቶ ነው። ይህ በመሆኑ ኩታገጠም የግብርና ዘዴ የተለመደ አይደለም። አርሶአደሩ ከነበረው አስተሳሰብ ወጥቶ በኩታገጠም የአስተራረስ ዘዴ ልምምድ እንዲያደርግ በተከናወነው ተግባር ውጤታማ መሆን ተችሏል። አርሶአደሩም ጥቅሙን ተገንዝቧል። የኩታገጠም የግብርና ዘዴ በሙዝ ብቻ ሳይሆን አቮካዶ፣ ቡና እና ስንዴ፣ በቆሎ ላይም በተመሳሳይ አርሶአደሩ ተቀናጅቶ እያመረተ ይገኛል።

በተወሰኑ አርሶአደሮች የታየው ውጤትም ወደሌሎች እየሰፋ ይገኛል። በመንግሥት መዋቅርም ትኩረት ያደረግነው ኩታገጠሙ ለሜካናይዜሽንም ሆነ ለሌሎች ግብአቶች አቅርቦትና ክትትል ሥራ ምቹ መሆኑ የማሳየትና የማስረጽ ሥራ ተሰርቷል። የኩታገጠም የሙዝ ልማት በቆላማ አካባቢዎች ቤንች ሸኮ፣ ኮንታና ዳዎሮ ዞኖች በስፋት እየተከናወነ ነው።

በበልግ የግብርና ወቅት በአብዛኛው የበቆሎ ልማት ስለሚከናወን በኩታገጠም የአስተራረስ ዘዴ በቆሎ እስከ ሰባት መቶ ሄክታር መሸፈን ተችሏል። ይሄ ትልቅ ልምምድ ነው። ቀደም ሲል አንዱ በቆሎ ይዘራል፣ ሌላው ድንች ይተክላል፣ ወይንም መሬቱን ጠፍ ያሳድረዋል። አሁን ላይ በኩታገጠም በቆሎ የመዝራት ሁኔታ ተፈጥሯል።

ምርቱ ሲደርስም በጋራ ለገበያ ማዘጋጀት ተለምዷል። አርሶአደሩ ማልማት ብቻ ሳይሆን፣ በጋራ ተደራድሮ ገበያ ለመወሰንም ተደራጅቶ የሕብረት ሥራ ማህበርም እያቋቋመ ይገኛል። ሕብረት ፈጥሮ ደላላን ከመካከል በማውጣት ተጠቃሚነቱን ለማሳደግ ጥረት እያደረገ ነው። እንዲህ ያሉ መልካም ነገሮች እየታዩ ቢሆንም በቂ ነው ተብሎ አይወሰድም። ተጠናክሮ መቀጠልና መስፋት ይኖርበታል። የኩታገጠሙ ከሌማት ቱሩፋት ጋርም ተቀናጅቶ እንዲሰራም አስፈላጊው ክትትልና ድጋፍ ይደረጋል።

በተለይም የገበያ ትስስሩ ላይ የተጠናከረ ሥራ እንደሚያስፈልግ ግንዛቤ ተይዟል። በገበያ ማጣት፣ በመንገድ መሰረተልማት አለመሟላትና የተበላሹ መንገዶች በቶሎ ባለመጠገናቸው አርሶአደሩም ሸማቹም ሳይጠቀም ምርት ይባክናል። አርሶአደሩም በተደጋጋሚ የሚያነሳው ጉዳይ በመሆኑ የመንገድ መሠረተልማት በማሟላት በኩል የክልሉም የፌዴራል መንግሥትም የትኩረት አቅጣጫ መሆን ይኖርበታል። የኩታገጠም የግብርና ዘዴ ጠቃሚ መሆኑን አርሶአደሩ እየተገነዘበው የመጣ በመሆኑ ወደኋላ መመለስ የለበትም።

አዲስ ዘመን፡- የአካባቢውን የተፈጥሮ ፀጋ መሠረት አድርጎ ለወጣቶች የሥራ እድል ከመፍጠር አኳያ ክልሉ የሰራቸውንና በስኬት የሚያነሳቸውን ቢገልጹልን።

ኢንጂነር ነጋሽ (ዶ/ር)፡– ድጋፍና ክትትል ይሻሉ ብለን ከለየናቸው ተግባራት መካከል የሥራ ዕድል ፈጠራና የኑሮ ውድነት ጫናን መቀነስ ይጠቀሳሉ። ባለፉት ሁለት ዓመት ተኩል ከሰራናቸው ዋና ዋና ተግባራት ሥራ ፈላጊ ማነው የሚለውን መለየት ነው። የልየታ ሥራውን በቅርቡ ከሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ጋር በጋራ በመተባበር በአንድ ማዕከል በቴክኖሎጂ የታገዘ የልየታ ሥራ ተሰርቷል። ከዩኒቨርሲቲና ኮሌጆች የተመረቁ፣ በቂ የእርሻ መሬት የሌላቸው የአርሶአደር ልጆች፣ በከተማ የሚኖሩ በዛ ያሉ ስራ ፈላጊዎች መኖራቸውን ለይተናል።

ሥራ ፈላጊዎቹን በምን አይነት የሥራ ዘርፍ ላይ ብናሰማራቸው ውጤታማ ይሆናሉ የሚለው ቀጥሎ ያለው ተግባር ነበር። ወደ ትግበራ የገባነው ሰፊ የሥራ ዕድል መፍጠር የሚቻለው በግብርናው ዘርፍ በመሆኑም ከሌማት ቱሩፋቱ ጋር በማያያዝና ለእርሻ የሚሆን መሬትም በማዘጋጀትና አስፈላጊ የሆኑ ግብአቶችንም በማመቻቸት ነው። ለ53 ሺ ዜጎች የሥራ ዕድል ፈጥረናል። ከነዚህ ውስጥም 28 ሺ የሚሆኑት በግብርና ዘርፍ በእርሻ፣ በእንስሳት እርባታ፣ በንብ ማነብና መሰል ጉዳዮች ላይ የተሰማሩ ናቸው። ሰብልና ፍራፍሬ ማምረቱ ሰፊውን ድርሻ ይይዛል። በትራክተር ታግዘው ያለሙ ወጣቶችም ሀብት ማፍራት ጀምረዋል።

ክልሉ በምእራብ ኦሞና ሱሩማ አካባቢዎች የወርቅ ማዕድን ሀብት አለው። አሁንም የደለል ወርቅ የሚያመርቱ ወጣቶች አሉ። ሆኖም ግን በተደራጀ መንገድና ከባለሀብት ጋር በማቀናጀት አነስተኛ የወርቅ አምራቾችን ለመፍጠርና በተሻለ ተጠቃሚ እንዲሆኑ መሰራት እንዳለበት በክልሉ ታምኖበታል። አምራቾቹ የወርቅ ማጠቢያ ማሽን በብድር ገዝተው እንዲጠቀሙ ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠር ጥረት እየተደረገ ነው።

የድንጋይ ከሰል ሀብት ዳውሮና ኮንታ ዞኖች ውስጥ በስፋት ይገኛል። ወጣቶች በማምረት፣ ትራንስፖርት በማቅረብ፣ በፋብሪካ ውስጥም በመሥራት የሚሳተፉበት እድል አላቸው። እንደ አሸዋ ያሉ ለግንባታው ዘርፍ ግብአቶችም አሉ። ምእራብ ኦሞ ዞን ዲማ በሚባል አካባቢ አሸዋ በስፋት ይገኛል። በቱሪዝም ኢንደስትሪው በገበታ ለሀገር እንደ ሀላላ ሎጅ፣ ጨበራ ሎጅ፣ ደንቢ ሎጅ ያሉ ፕሮጀክቶች ትልቅ ተስፋዎች፣ የቱሪስት ፍሰቱን የሚጨምሩ መዳረሻዎች ናቸው። ወጣቶቹ በቱሪዝሙ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተጠቃሚ ይሆናሉ። ከቡና ጋር ተያይዞ ቡና ማጠቢያና መቀሸሪያ የማምረቻ ኢንደስትሪዎች እንዲሁም በብረታ ብረትና እንጨት ውጤቶች ላይ መሰማራት ሌላው አማራጭ ነው።

በሌማት ትሩፋት ፕሮግራም የአንድ ቀን ጫጩት ለሚያቀርቡ ተዘዋዋሪ ፈንድ የማመቻቸት ሥራ ተሰርቷል። በ16 ከተማ አስተዳደሮች ላይ ሼድ በመሥራት ከግንቦት ወር አጋማሽ ጀምሮ በተደራጁ ወጣቶች አማካኝነት የማሰራጨት ሥራ ተጀምሯል። እቅዱ ወጣቶቹ ባገኙት ገንዘብ ገቢ አግኝተው የተጠቀሙበትን ገንዘብ ተመላሽ እንዲያደርጉ ነው። ዓላማው በዚህ መልኩ ገንዘቡን በማዘዋወር ብዙዎችን ተጠቃሚ ማድረግ ነው። በአሣ ማስገርም ስራ እየተሰራ በመሆኑ እንዲሁ ወደ ገበያ ማቅረብ ተጀምሯል። ወጣቱ የሥራ ባህሉን መቀየር ከቻለ የሥራ ዕድል ዘርፍ ሰፊ ነው። በኔ እምነት ወጣቱ ተቀጣሪ ለመሆን መመኘት የለበትም። መንግሥት የመሥሪያ ቦታ፣ የገንዘብ ብድር፣ ተዘዋዋሪ ፈንድ አቅርቦት ላይ ነው ትኩረት ማድረግ ያለበት።

አዲስ ዘመን፡- በክልሉ በገበታ ለሀገርና ለትውልድ የተከናወኑት የቱሪዝም ኢንደስትሪውን ከፍ የሚያደርጉ ፕሮጀክቶች ለክልሉ ምን አይነት እድሎችን ፈጥሯል ይላሉ?

ኢንጂነር ነጋሽ (ዶ/ር)፡– እንደማህበረሰብ ስናየው በልማት ወደኋላ የቀሩ፣ ያልታዩ፣ የተረሱ አካባቢዎችን እንድናስታውስ ያደረገ ነው። ይሄ ሕዝቡም የሚመሰክረው ነው። ተረስተናል ይል የነበረ ማህበረሰብ አለመረሳቱን ያረጋገጠበት ፕሮጀክት ነው። ሕዝብና መንግሥትን ያቀራረበ ነው። አሁን ፕሮጀክቱ የሚገኝባቸው አካባቢዎች ትልቅ ታሪክ ይዘው ግን ትኩረት የተነፈጋቸው ነበሩ። ዛሬ ላይ ከፍ ብለው መታየት ችለዋል። ይሄ ደግሞ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ቅርስ ብቻ ሳይሆን የመላው ኢትዮጵያ ሀብት ጭምር ሆኖ ጥቅም ላይ እንዲውል የታሰበበት ትልቅ ፕሮጀክት ነው የሚል እምነት አለኝ።

ፕሮጀክቶቹ ማረፊያ ብቻ ተደርገው የሚወሰዱ አይደለም። በአካባቢው ላይ የሚገኙ የባህል፣ የታሪክ፣ የተፈጥሮ መስህቦችና መሰል እምቅ የሆኑ ሀብቶችን ለማወቅ፣ ለማድነቅ፣ እንዲታወስም እድል ይሰጣል። በአጠቃላይ ታሪካዊ ዳራውን ይዞ የተቀረፀ ፕሮጀክት ነው። ከኢኮኖሚ አኳያም ሀብት በማመንጨት ፋይዳው ከፍተኛ ነው። የአካባቢው ማህበረሰብም ሀገርም ተጠቃሚ ይሆናል።

በገበታ ለትውልድ በግንባታ ላይ የሚገኘው ደንቢ ሎጅና ፏፏቴም ደንቢ ሐይቅ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ አካል ነው የነበረው። ሐይቁ የተመረጠው በአካባቢው ላይ የሚገኙ የእርሻ ልማት ድርጅቶች ኃይል እንዲያገኙ ታስቦ ነበር። ሌሎች የኃይል ማመንጫ አማራጮች ሲመጡ ኃይል ማመንጨቱ ለጊዜው ተቋረጠ። ለኃይል ማመንጫ ተብሎ ተዘርግተው የነበሩ ብረቶችና ሌሎች ቁሳቁስ ሳይነኩ ማህበረሰቡ ጠብቋቸው እስከ ዛሬ ድረስም አሉ። ማህበረሰቡ የጠበቀው ወደነበረበት ይመለሳል ወይንም ወደተሻለ ይሸጋገራል የሚል እምነት ስለነበረው ነው። አሁን ላይም በሐይቁ ላይ የተጀመረው የሎጅ ግንባታ ቀደም ሲል ከነበረው አገልግሎት ያላነሰ በመሆኑ ፕሮጀክቱ ትልቅ ተስፋን ያሳደረ ነው። በአጠቃላይ ፕሮጀክቶቹ የኢንቨስትመንት ፍላጎት በመጨመር ዕድል ፈጥረዋል።

አዲስ ዘመን፡- በክልሉ እየተገነባ ስላለው የአውሮፕላን ማረፊያ አጠቃላይ ሁኔታ በተመለከተ ቢገልጹልን።

ኢንጂነር ነጋሽ (ዶ/ር)፡- የተገነቡት ፕሮጀክቶች የቱሪዝም ኢንዱስትሪውን ከፍ ለማድረግ፣ ኢንቨስትመንት ለመጨመር የሚያግዙ በመሆናቸው፣ አሰተማማኝ የትራንስፖርት አገልግሎት ሊኖር ይገባል። የአየር ትራንስፖርት ደግሞ አንዱ አማራጭ ነው። ቀድሞ የነበረው የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ያለበቂ ምክንያት እንዲቋረጥ ተደርጓል። ክልሉ ለየብስ ጉዞም ቢሆን ምቹ የሆነ መንገድ የለውም። በእነዚህ ሁሉ ገፊ በሆኑ ምክንያቶችና መንግሥትም በሰጠው ትኩረት የሚዛን አማን የአየር ማረፊያ ግንባታ ሥራ ተጀምሯል። በጥሩ እንቅስቃሴ ላይም ይገኛል።

ክልሉም ካለው ጉጉት ወጪውን ለመጋራት ቃል ገብቷል። የግንባታ ጊዜውም ሁለት ዓመት ነው። ሆኖም የገንዘብ አቅም ፈትኖታል። ግንባታው ከሚከናወንበት አካባቢ ለሚነሱ ነዋሪዎች የካሣ ክፍያ ከክልሉ አቅም በላይ ነው። እንዲያውም ሕዝቡ ትብብር አድርጓል። ካሣ ሳይቀበሉ የተነሱም አሉ። ክልሉ ገና አዲስ በመሆኑ በብድርም ሆነ በተለያየ መንገድ የፌዴራል መንግሥት እገዛ ያስፈልገዋል። ዝናባማ አካባቢ ከመሆኑ ጋር ተያይዞም ግንባታው በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ ላይ እንዳይጠናቀቅ ምክንያትም እየሆነ ነው።

አዲስ ዘመን፡- አረንጓዴ አሻራ መርሃግብር ክልሉ ካለው የተፈጥሮ ፀጋ ጋር እንዲጣጣም የተሰጠው ትኩረትስ እንዴት ይታያል?

ኢንጂነር ነጋሽ (ዶ/ር)፡- አዎ እንደተባለው ክልሉ አረንጓዴ ነው። እድሜ ያስቆጠሩ የደን ዛፎች፣ የቡና፣ ቅመማቅመምና ሌሎችም ተክሎች ይገኛሉ። አረንጓዴ አሻራ ላይ ዋና ተግባራችን የነበረው በሳሱ ደኖች አካባቢ ችግኞችን በመትከል ወደነበረበት መመለስ፤ ደጋማው አካባቢ አቮካዶ፣ ቆላማው ሙዝና ማንጎ የሚመረትባቸው አካባቢዎች በመሆናቸው በስፋት እንዲመረት ማድረግ ነው። ባለፈው ዓመት ወደ 289 ሚሊዮን ችግኝ ተተክሏል። በዘንድሮ ክረምትና እስከ መስከረም ወር ባለው ጊዜ 404 ሚሊዮን ችግኞች ለመትከል ታቅዷል። ከነዚህ ውስጥም የተተከለው 44 ሚሊዮኑ የቡና ችግኝ ነው። የተከላ መርሃግብሩም ተጀምሯል። መርሃግብሩ የባህርዛፍ ተክልን በተለያዩ የዛፍ ችግኞች የመተካት ዓላማም አለው።

አዲስ ዘመን፡- ከጤና አኳያ ማህበረሰቡ የወባ በሽታ ጉዳት እያስከተለ መሆኑን እያነሳ ነው። በዚህ በኩል ምን እየተሰራ ነው?

ኢንጂነር ነጋሽ (ዶ/ር)፡- የወባ ወረርሽኝ ለክልሉ ተግዳሮት ሆኗል። በሽታውን ለመከላከል የተለያዩ ሥራዎች ቢሰሩም ችግሩ እየተባባሰ ነው እንጂ አልቀነሰም። በዚህ ዓመት ተባብሷል። አንድ ሰው በተደጋጋሚ በወባ ይያዛል። የታማሚውም ቁጥር ጨምሯል። የሞት ምጣኔውም ቢሆን ከፍ ብሏል። ከጤና ሚኒስቴርና የልማት አጋሮች ጋር በጋራ የንቅናቄ ሥራ ተሰርቷል። መፍትሄ ስለሚያስፈልገው ጥረቱ መጠናከር እንዳለበት ግንዛቤ ተይዟል። የእናቶችንና ሕፃናትን ሞት ለመቀነስ ስትራቴጅ ተቀርጾ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው።

አዲስ ዘመን፡- ቀሪ የቤት ሥራዎች ቢኖሩም እስካሁን የተከናወኑት ሥራዎች በስኬት የሚወሰዱ እንደሆኑ ገልጸውልናል። በጥቅሉ ሀገራዊ ለውጡ እንደ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች እንዴት ሊታይና ሊወሰድ ይችላል?

ኢንጂነር ነጋሽ (ዶ/ር)፡- ለውጡ እንደሀገር መቀጠል ጥያቄ ውስጥ ሊገባ ያለበትን የቀየረ፣ ልንበተን እንችላለን ብለን ስጋት ውስጥ ከገባንበት የወጣንበትና ኢትዮጵያን እንደሀገር ማስቀጠል የተቻለበት ትልቅ ምእራፍ ነው። በለውጡ ሂደት ውስጥ ተግዳሮቶች ነበሩ። ይሄ የዓለም ነባራዊ ሁኔታ ነው ብዬ እወስዳለሁ። በፈተናዎች ውስጥ በጥቂት ዓመታት ጊዜ በኢኮኖሚው ድሎች ተገኝተዋል። በሜጋ ፕሮጀክቶች ግንባታ፣ በበጋ መስኖ ስንዴ ልማትና በሌሎችም ሊጠቀሱ የሚችሉ ሥራዎች ተሰርተዋል። ሰላምን ለማረጋገጥም ሰፊ ርቀት ተኬዷል። ወደ ክልላችን ስመጣ የሚሆነው የዚሁ አካል ነው። እራስን በራስ የማስተዳደር መብት መከበሩ ትልቅ የፖለቲካ ድልም ጥቅምም ነው።

ከፌዴራል መንግሥት ጋር በተናበበ መልክ የልማት፣ የማህበራዊና ሌሎችንም ተግባራት ያለጣልቃገብነት በትብብር ማዕቀፍ ማከናወን እየተቻለ ነው። ወደ ሁለተናዊ ብልጽግና መሸጋገር አለብን ብለን ለዚያ የሚሆን መሠረት መጣል አለብን ብለን ያልናቸውን እንደክልልም እንደሀገርም እየጣልን እንገኛለን። በዚህ ከቀጠልን ከጥቂት ዓመታት በኋላ የምናስመዘግባቸው ውጤቶች ከፍተኛ ይሆናሉ። በኢኮኖሚ ጠንካራ የሆነች ሀገር እንገነባለን። ሩቅ አይሆንም። የውስጥ ችግሮቻችን በውይይት ፈትተን ሙሉ አቅማችንን ለልማት ካዋልን ከበለፀጉት ሀገራት መካከል ለመሆን እንችላለን። የተሻለች ኢትዮጵያን እንደምናይ ሙሉ እምነትና ተስፋ አለኝ።

አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ እናመሰግናለን።

ኢንጂነር ነጋሽ (ዶ/ር)፡- እኔም አመሰግናለሁ።

ለምለም መንግሥቱ

አዲስ ዘመን ሐምሌ 4/2016 ዓ.ም

Recommended For You