ዓለማችን ከመቼውም ጊዜ በላይ በቴክኖሎጂ ትሩፋት አነስተኛ መንደር ሆናለች። ዓለማችን ይበልጥ በኢኮኖሚያዊ፣ በማኅበራዊና በፖለቲካዊ ጉዳዮች ተሳስራለች። አሜሪካ ስታስነጥስ የተቀረው ዓለም ጉንፋን ይይዘዋል የሚለው ይትበሀል አድጎ ቻይና፣ ሕንድ፣ ራሽያና ሌሎች ሀገራት ሲያስነጥሱ ጉንፋን ይይዘን ጀምሯል። ዩክሬን በአቅሟ አስነጥሳ እንኳ የስንዴ፣ የምግብ ዘይትና የማዳበሪያ ጉንፋን ይዞን የለ። አያርገውና 3ኛው የዓለም ጦርነት ቢቀሰቀስ ዳፋው የከፋ ስለሆነ አበክረን እንድናስብበት ይቺን አሳሳቢና አብሪ መጣጥፍ ለመጫጫር ተነሳሁ። አበባሉስ አይመጥንም ትተሽ ይመጣልን ባሰብሽ፤ እማይደል።
ከ2ኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ በአውሮፓም በሌሎች ክፍለ አኅጉራት ለ80 ዓመታት ያህል የሰፈነው አንጻራዊ ሰላም ቢደፈርስ ከቀዝቃዛው የዓለም ጦርነት አያልፍም ተብሎ ይታመን ነበር። ራሽያ በፋሺስትነት የፈረጀችውን የዜሌኒስኪ አገዛዝ በኃይል ለመቀየር ወረራውን ሲጀምር በቀናት ግፋ ቢል በሳምንታት ውስጥ ኪየቭን ከዛ ዩክሬን በሞላ ትቆጣጠራለች ተብሎ ተጠብቆ የነበር ቢሆንም ጦርነቱ ዓመታትን እያስቆጠረ፣ ተዋንያንን እያበዛ ሌሎች ሀገራትን ስቦ እያስገባ እየተባባሰ ይገኛል።
ኔቶ፣ እነ ፈንሳይና አሜሪካ በብዙ መቶዎች ቢሊየን የሚያወጡ የጦር መሳሪያዎችን ለዩክሬን እያጎረፉ፤ ስልጠና እየሰጡ፣ በጀት እየደገፉ በጦርነቱ በተዘዋዋሪ እየተሳተፉ ይገኛል። የዩክሬን ጦር በተዋጊ አውሮፕላን፣ በክሩዝ ሚሳየል፣ በመድፍ በአጠቃላይ በትጥቅና ስንቅ እየደገፉ የፈለጉትን ያህል ድል ማግኘት ባለመቻላቸው ሰሞኑን ዩክሬን ራሽያ ውስጥ ያሉ የጠላት ኢላማዎችን እንድታጠቃ ፈቅደዋል ። በዚህ መሠረት ዩክሬን ራሽያ ውስጥ ያሉ ወታደራዊ ኢላማዎች መደብደብ ጀምራለች። የራሽያ አጸፋ የከፋ ስለሚሆን መዘዙ ከወዲሁ ስጋት ፈጥሯል።
የእስራኤል የጋዛ ወረራ ይሄን ተከትሎ ከኢራን ከዮርዳኖስ ከሶሪያና ከእነ ሁቲ አማጽያን ጋር የተፈጠረው ውጥረት፤ በቻይናና በእነ ፊሊፒንስ የተፈጠረው ግብግብ እና ታይዋንን የምትወር ከሆነ አሜሪካ በቀጥታ ወደ ጦርነት እንደምትገባ መዛቷ 3ኛው የዓለም ጦርነት አይቀሬ አስመስሎታል። የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ለ3ኛው የዓለም ጦርነት ዝግጅት ከጀመረ ሰነባበተ። አባላቱም እንደዚሁ። የብሪታንያ የቀድሞው መከላከያ ሚኒስትር ግራንት ሻፕስ በዚያ ሰሞን ባደረጉት ንግግር ሀገራቸው በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ውስጥ ከቻይና፣ ሩሲያ፣ ኢራን እና ሰሜን ኮሪያ ጋር ለሚደረገው ጦርነት መዘጋጀት አለባት ብለዋል።
ሌሎች ወገኖች ደግሞ ከኢኮኖሚያዊ ዕድገት ይልቅ ለወታደራዊ አቅም ግንባታ ትኩረት መስጠት አርቆ የማየት ችግር ነው ብለው ያምናሉ። ይሁንና አሜሪካና ብሪትን ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎችን ተማምነው ከእነ ቻይና ጋር ወደ ጦርነት ቢገቡ ለእያንዳንዱ አሜሪካዊ ወይም ብሪትናዊ ወታደር ስምንት የጠላት ወታደር ይገጥመዋል ወይም አሰላለፉ አንድ ለስምንት ይሆናል ማለት ነው። ብሪታንያ ለጦርነት እየተዘጋጀች ባለችበት አየርላንድ ደግሞ ከቻይና ጋር ጥብቅ የኢኮኖሚና የዲፕሎማሲ ግንኙነት በመመስረት ላይ መሆኗ ጂኦ ፖለቲካ ምን ያህል ውስብስብና ባለብዙ ፍላጎት መሆኑን ያመለክታል።
ኔቶ ባለፈው ሳምንት ለሦስተኛው የዓለም ጦርነት ልምምዶችን እንደሚጀምር አስታውቋል። ለዛውም ወደ ኒውክሌር ጦርነት ሊያድግ እና ዓለምን ሊያጠፋ ለሚችለው ጦርነት። የብሪታኒያ የመከላከያ ሚኒስትር ሻፕስ በጠላትነት የፈረጇቸው ሀገራት አንድ ላይ ሲደመር፣ 8.2 ሚሊዮን መደበኛ ወታደሮችና ተጠባባቂዎች አሏቸው። ከዚህ አንጻር ብሪታኒያ 73ሺህ፣ አሜሪካ ደግሞ ከ1 ሚሊየን ብዙም ያልተሻገረ ወታደርና ተጠባባቂ ኃይል ብቻ እንዳላቸው ይነገራል። ለዚህ ነው አሰላለፉ አንድ ለስምንት ነው የተባለው።
ችግሩና ጥያቄው እነዚህን ወታደሮች ከማሰልጠኛና ከካምፕ ወደ ግምባር በምንና እንዴት እናጓጉዛቸው ነው። የብሪትን ባሕር ኃይል ሰሞኑን ወደ ቀይ ባሕር ሊያደርገው የነበረውን ጉዞ በባሕርተኞች እጥረት የተነሳ ሰርዟል። እንደ አሜሪካ ሁሉ የእንግሊዝ ጦርም በከፍተኛ የወዶ ገብ ምልምል እጥረት የተነሳ የሰው ኃይሉ እየተመናመነ ይገኛል። የብሪትን የመከላከያ ሚኒስትር ሻፕስ በአምስት ዓመታት ውስጥ 3ኛው የዓለም ጦርነት ሊቀሰቀስ ስለሚችል መዘጋጀት አለብን ባሉት መሠረት ታዲያ በእነዚህ አጭር ዓመታት በጦሩ የሚስተዋለውን የሰው ኃይሉ ችግር መቅረፍ ይቻላል። በቻይናና በሕንድ በራሽያና በሰሜን ኮሪያ ግን በአንድ የክተት አዋጅ ሚሊየኖችን መመልመል ይችላሉ።
ኔቶ በዩክሬን አማካኝነት ከራሽያ ጋር በሚያካሂደው የውክልና ጦርነት አቅሙን አይቷል። ዛሬ በዩክሬን እየሆነ ያለው በአንድ የኔቶ አባል ሀገር ላይ ነገ ቢሆን ኔቶ እንደተጠቃ ስለሚቆጠር ወደ ጦርነት መግባቱ ስለማይቀር በዘወርዋራ ከራሽያ ጋር እየተፈታተሸ ነው። የዩክሬን ማፈግፈግ በመጨረሻም ከተሸነፈች ለኔቶና ለአጋር ሀገራት የሚያስተላልፈው አንድምታ ከባድ ከመሆኑ ባሻገር ፑቲን የልብልብ ተሰምቷቸው ሌላ ሀገር እንዳይወሩ ጦርነቱ በዩክሬን አሸናፊነት እንዲደመደምና ለሌሎች አምባገነን አገዛዞች መቀጣጫ እንዲሆን ስለሚፈልግ ከዩክሬን ጎን መቆምን መርጧል።
ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ ከቻይና ጋር የሚፈጠሩ ዲፕሎማሲያዊ መቆራቆሶች፣ የቃላት ጦርነቶች እና በደቡባዊ ቻይና ባሕርና በታይዋን በሚስተዋሉ የውክልና መጎሻሸሞች ብዙዎችን እያሳሰበ ይገኛል። ቁጥራቸው ቀላል ያልሆነ ተንታኞችም ምዕራባውያን ለማይቀረው ዘርፈ ብዙ ጦርነት ተዘጋጁ እያሉ ይገኛል። የ3ኛው የዓለም ጦርነት ይህን ይመስላል፤”This Is What World War III Will Look Like”በሚል ርዕስ በTIME መጽሔት ፒ ደብሊው እና ኦገስት ኮል በጋራ ባስነበቡን መጣጥፍ፤ በነገራችን ላይ የሳይንሳዊ ልቦለድ ማለትም፤”Ghost Fleet: A Novel of the Next World War.”ደራሲም ናቸው። የአሜሪካ እና የቻይና የጦር መርከቦች ከመድፍ እስከ ክሩዝ ሚሳኤሎች እና ሌዘር ድረስ እየተታኮሱ በባህር ላይ ይዋጋሉ። ስውር የሆኑ የሩሲያ እና የአሜሪካ ተዋጊ ጄቶች በሮቦት እየበረሩ በአየር ላይ ይተናነቃሉ። ወይም ዶግፋይት ያደርጋሉ።
የበይነ መረብ ሰርሳሪዎች ወይም ሰርጎ ገቦች በቻይና ሻንጋይ እና በአሜሪካ ሲሊኮን ቫሊ መሽገው የሳይበር ውጊያውን ያጧጡፋሉ። ለነገሩ ማታ ነው ድሌ ብሎ ግዳይ ለመጣልና ለመጨፈር በህዋ ላይ የሚደረጉ ውጊያዎች ወይም ስፔስ ዎርስ ይወስናሉ። ይህ ልቦለድም ነገ በገሀዱ ዓለም ሊከሰት የሚችል በዓለማችን ላይ ያንዣበበ አደጋ ነው። የኃያላን ሀገራት ጦርነት የ20ኛውን መቶ ክፍለ ዘመን ዕጣ ፈንታ ይወስናል። በነገራችን ላይ ሁለቱ የዓለም ጦርነቶች በአስር ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት የቀጠፉ ሲሆን፤ በእግራቸው የተተካው የዓለማችን የቀዝቃዛው ጦርነት ደግሞ ከጂኦፖለቲካ እስከ ስፖርት ድረስ ያለውን መልካዓ በየነ። ቀረፀ። በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ ደግሞ የ3ኛው የዓለም ጦርነት ፍርሃት ቆፈን መጣሁ መጣሁ እያለን ነው።
ሆኖም ያ የገፈፈ የመሰለን የጦርነት ዳመና እንደገና መዳመን ጀምሯል። ራሽያ የዩክሬንን መሬት መውረሯ። በቀይ ከዋክብት ያጌጡ የራሽያ አውሮፕላኖች ያለማቋረጥ የአውሮፓን ድንበሮች መቃኘት፤ ኔቶን ከምንጊዜም በላይ ጥንቃቄ እንዲያደርግና ራሽያን በጥርጣሬ እንዲመለከት አስገድዶታል። ከ1980ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ ኔቶ አይኑን ከራሽያ ላለማንሳት ወስኗል። እያንዳንዱን እርምጃዋን በንቃት ይከታተላል። በፓስፊክ ውቅያኖስ ውስጥ አሜሪካ እና አዲሷ ኃያል ሀገር ቻይና እልህ አስጨራሽ የጦር መሳሪያ ውድድር ላይ ተፋጠዋል። ቻይና ባለፉት ዓመታት ውስጥ ከየትኛውም ሀገር በበለጠ ብዙ የጦር መርከቦችን እና የጦር አውሮፕላኖችን የሰራች ሲሆን፤ ፔንታጎን ግን ትኩረቱን የተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎችን መታጠቅ ላይ አድርጓል።
ቻይና ከዚህ መሳ ለመሳ የሳይበር ጦርነት ልምምድ እያደረገች ይመስላል። በዚህ ዘርፍ በስፋት እየታጠቀችም ነው። በቅርቡ በአሜሪካ የሰው ኃይል አስተዳደር የመረጃ ቋት ላይ የፈፀመችው የበይነ መረብ ስርሰራና የመረጃ ምንተፋ የሳይበር ጦርነት አዲሱ አውደ ግንባር መሆኑን የሚያመላክት ነው። አሳሳቢው የ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የቀዝቃዛ ጦርነት በአንድ ወገን ቻይናን እና አጋሯን ሩሲያ በሌላ ወገን አሜሪካንና ምዕራባውያንን ወደለየለት ጦርነት ሊወስድ ይችላል። ቻይና ደይሊ በዚያ ሰሞን እትሙ ያረጋገጠልን ይሄን ነው። “የአሜሪካ-ቻይና ጦርነት የማይቀር ነው”ሲል እቅጩን እስከ ዶቃ ማሰሪያችን ነግሮናል።
ቻይና የግዛቴ አካል ነው በምትለው ደቡባዊ ባሕር ሰው ሰራሽ ደሴት መገንባቷና ከእነ ፊሊፒንስና ከአሜሪካ ጋር ከቃላት ጦርነት አልፈው ባሕር ላይ መተነኳኮሳቸው፤ ቻይና አንድ ቀን ታይዋንን ወርሬ እጠቀልላለሁ ስትል መዛቷና በቀጣናው ከፍተኛ ወታደራዊ ዕንቅስቃሴ እያደረገች መሆኗ ጦርነቱን አይቀሬ አስመስሎታል። እኤአ በ2014 በፐርዝ ዩኤስ-ኤሺያ ማእከል የተደረገ የሕዝብ አስተያየት እንደሚያሳየው 74 በመቶ ቻይናውያን ከአሜሪካ ጋር ጦርነት ቢደረግ ቻይና ታሸንፋለች ብለው ያምናሉ። ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ዩክሬን የአሜሪካ የጦር መሳሪያዎችን ተጠቅማ እንደ አዲስ ጥቃት በተከፈተባት የካርኪቭ የሰሜን ምዕራብ ግዛት አጎራባች የሚገኙ የራሽያን ወታደራዊ ኢላማዎችን እንድትመታ ፈቀዱ።
ኔቶ፣ እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመንና ፖላንድ አበክረው ዩክሬን ባስታጠቋት የጦር መሳሪያዎች የራሽያን ጥቃትና ወረራ ለመከላከልና ለመመከት ራሽያ ውስጥ ያሉ ወታደራዊ ኢላማዎች እንድትመታ የፈቀዱ ሲሆን፤ አሜሪካ ግን የጦር መሳሪያዎቿ ድንበር ተሻግረው ራሽያን እንዳይመቱ ገደብ ጥላ ቆይታለች። ራሽያ በካርኪቭ ግንባር ጦርነት ከፍታ በአጭር ጊዜ ውስጥ በርካታ ስትራቴጂያዊ ቦታዎችን መቆጣጠሯና ግስጋሴዋ መቀጠሉ ባይደን ሀሳባቸውን እንዲቀይሩ አስገድዷል ይለናል CNN። ለባይደን ቅርበት ያላቸው የኋይታውስ ባለስልጣናት ፕሬዚዳንቱ ዩክሬን የአሜሪካ ጦር መሳሪያዎችን ተጠቅማ በራሽያ ኢላማዎች ላይ አጸፋዊ ምት እንድታሳርፍ ይሁንታን ቢሰጡም ዩክሬን በካርኪቭ ድንበር አቅራቢያ በሚገኙ የራሽያ ኢላማዎች ላይ ብቻ እንድትወሰን ማዘዛቸውን ገልጸዋል።
ኪየቭ የራሽያ ጦር በካርኪቭ ግንባር እያደረገ ያለውን ግስጋሴ ለመግታት አሜሪካ የጣለችውን ገደብ እንድታነሳ ስትወተውት እንደነበር፤ በገደቡ የተነሳ ዩክሬን የራሽያ የጦር መሳሪያ መጋዘን፣ የሎጅስቲክ ማዕከሎች በካርኪቭ ድንበር የቅርብ ርቀት ላይ እንደሚገኙ እያወቀች አጸፋዊ እርምጃ ከመውሰድ መቆጠቧን ታወሳለች። ይሁንና የባይደን አስተዳደር ዩክሬን ከ320 እስከ 482 ኪሎ ሜትር የሚምዘገዘጉ የአሜሪካ “ATACMS”የተሰኙ ሚሳይሎችን ራሽያ ውስጥ ላሉ ኢላማዎች እንዳትጠቀም ገደብ መጣሉ ይታወሳል።
በዩክሬን እና በሩስያ የአየር ክልል ውስጥ የሚበሩትን የሩሲያ አውሮፕላኖች ስጋት ለማስወገድ ግን የአሜሪካ ፀረ-አይሮፕላን መሳሪያዎችን እንድትጠቀም የተፈቀደላት መሆኑንና በዚህም ውጤታማ መሆኗ የተመለከተ ሲሆን፤ የአሜሪካን ጸረ አውሮፕላን መሳሪያዎችን ተጠቅማ ራሽያ ውስጥ የሚገኙ ኢላማዎችን ግን ማጥቃት አትችልም ነበር። የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በዚህ ሳምንት ሀገራቸው የዩክሬንን ወቅታዊ ሁኔታ ከግምት በማስገባት አቋሟን ልታለዘብ እንደምትችል ፍንጭ ሰጥተው እንደነበር CNN ያወሳል።
አሜሪካ ለዩክሬን የምታደርገውን ድጋፍ እንደ ጦርነቱ ተለዋዋጭ ሁኔታ እንደምታጣጥመው ብሊከን ጠቁመው በቀጣይም ተጨማሪ የፖሊሲ ለውጦችን ለማድረግ መዘጋጀቷን ጠቁመዋል። በዚያ ሰሞን ከጀርመን ቻንስለር ኦላፍ ሾልስ ጋር በተደረገው ጋዜጣዊ ጉባኤ ላይ የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ዩክሬን ሀገራቸው የለገሰቻቸውን የረዥም ርቀት ተምዘግዛጊ ክሩዝ ሚሳኤሎችንና ሌሎች የጦር መሳሪያዎችን ተጠቅማ ራሽያ ውስጥ የሚገኙ የጦር ሰፈሮችን እንድታጠቃ ፈቅደዋል።
ማክሮን በብራንድንበርግ ጀርመን በሽሎስ ሜሴበርግ በጎበኙበት ወቅት “የዩክሬን ከተማዎችና መንደሮች ከራሽያ በሚተኮሱ ክሩዝ ሚሳየሎች ወደ ፍርስራሽነት እየተቀየሩ እየወደሙና ንጹሐንም በግፍ እየተገደሉ መሳሪያው እያላት እጇን አጣጥፋ እንድትመለከት ማድረግ የራሽያ ወረራ ከመደገፍ ተለይቶ አይታይም”ብለዋል። የጀርመኑ ቻንስለር ሾልዝ የማክሮንን አቋም በማስተጋባት ዩክሬን ዓለማቀፉን ሕግ አክብራ በታጠቀችው የጦር መሳሪያ ራሷን መከላከልና የአጸፋ መልስ እንድትሰጥ መፍቀድ መሬት ላይ ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ ከግምት ያስገባ ተገቢ ውሳኔ ነው ይላሉ።
የባይደን አስተዳደር ዩክሬን ከአሜሪካ የተሰጣት የጦር መሳሪያ በመጠቀም ራሽያ ውስጥ ያሉ ኢላማዎችን እንዳታጠቃ የከለከለው ጦርነቱ እንዳይስፋፋ በመስጋት ነበር። ስጋቱ እንዳለ ቢሆንም ዩክሬን ካርኪቭን የመከላከል ወታደራዊ ስትራቴጂ ጠቀሜታ ወሳኝ መሆኑን በመወትወቷና በእነ ኔቶና ፈረንሳይ ግፊት አሜሪካ ይዛው የቆየችውን አቋም እንድትቀይር መግፍኤ ሆኗል።
ብሊንከን በዚህ ወር መግቢያ ላይ ዩክሬንን በጎበኙበት ወቅት ዩክሬን ራሽያ ውስጥ ያሉ ወታደራዊ ኢላማዎችን ማጥቃት ስለሚኖረው ወታደራዊ ጠቀሜት ከተብራራላቸው በኋላ ዩክሬን ራሷን እንድትከላከል ገደቡ መነሳት እንዳለበት ስላመኑ ገደቡ በተወሰነ ደረጃ ሊነሳ ችሏል። ይህ ገደብ ተነሳ ማለት ራሽያ ራሷን ለመከላከል የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ተጠቀመች ማለት ነው። አሜሪካ የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ከተጠቀምሽ እጄን አጣጥፌ አልቀመጥም ባለችው መሠረት ሲፈራ ወደነበረው 3ኛው የዓለም ጦርነት ተገባ ማለት አይደለም። እንደ ሀገር ስለዚህ ስጋት አበክረን ልንዘጋጅ አይገባም።
ሻሎም ! አሜን ።
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን ሐምሌ 4/2016 ዓ.ም