«ከአንድ ብርቱ ሁለት መድኃኒቱ» የሚለው የሀገራችን ብሂል ለብቻ ከመሥራት ተባብሮ መሥራት ለስኬት እንደሚያበቃ ያመለክታል። አሁን ባለንበት ዘመን ደግሞ በጋራ መስራት ይበልጥ የህግ መሰረት ይዟል፡፡ በገጠርና በከተማ የሚኖሩ ማህበረሰቦች በተለያዩ ዘርፎች በህብረት ሥራ ማህበራት እየተደራጁ አብረው ለማደግ እየሰሩ ይገኛሉ።
በጋራ ወይንም በማህበር መሥራት ብዙ ፋይዳዎች አሉት። በዋናነት ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር ከመንግሥት ጋር በቅርበት ለመሥራት፣ የገበያ ድርሻ ከፍ እንዲል የአባላቱ ተጠቃሚነት እንዲያድግ ብሎም የአገር ዕድገት እንዲፋጠን ከፍተኛ ሚና ይጫወታል።
በዚህ ዓይነት መንገድ የሠሩ የህብረት ሥራ ማህበራት ከትንሽ ካፒታል ተነስተው ዛሬ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ካፒታል ለማፍራት ችለዋል። በምሳሌነት ከሚጠቀሱት መካከል የበቾ ወሊሶ ህብረት ሥራ ማህበር አንዱ ነው። ማህበሩ የአስር መሰረታዊ የህብረት ሥራ ማህበራትን የ140 ሺ ብር ካፒታል በመያዝ ነው በ1992 ዓ.ም የተቋቋመው፡፡
በአሁኑ ወቅትም የአባላቱ መጠን 90 እንዲሁም ካፒታሉ 126 ሚሊዮን ብር ደርሷል። በዚህም አባላቱን ተጠቃሚ እያደረገና በአገር ኢኮኖሚያዊ ግንባታ ላይም የራሱን ድርሻ እየተወጣ ይገኛል።
የህብረት ሥራ ማህበሩ ሥራ አስኪያጅ አቶ ኡርጌሳ አቶማ እንደሚሉት፤ ማህበሩ በተለይ የግብርና ግብዓቶችን ለአባላት በማቅረብ በኩል ሰፊ ሥራ እየሠራ ሲሆን፣ የኢንዱስትሪ ውጤቶችንም በአባላቱ ፍላጎት መሰረት ያቀርባል። ማህበሩ በአግሮ ፕሮሰሲንግ ዘርፍ ላይ እሴት ጨምሮ ለመሥራትና ተጠቃሚነቱን ይበልጥ ለማጠናከር በርካታ ተግባሮችን እያከናወነ ነው።
በዚህም አንድ የፕላስቲክ ማምረቻ ፋብሪካ በማቋቋምና ማህበራቱ ለምርቶቻቸው ማሸጊያ የሚያስፈልጓቸውን ከረጢቶች በማምረት እያቀረበ ነው። ይህንን ምርቱን የዓለም የምግብ ፕሮግራም (wfp) ጨምሮ የተለያዩ ድርጅቶች እየገዙ ይገኛሉ። ማህበሩ 360 ለሚሆኑ የአባል አርሶ አደሮች ልጆችም የሥራ እድል ፈጥሯል።
የአገሪቱ የግብርና ዘርፍ ችግር ሆኖ የቆየውን ዝቅተኛ ምርታማነት ለመፍታትም የምጥን ማዳበሪያ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ በ56 ሚሊዮን ብር ካፒታል በማቋቋም ቀድሞ በዘልማድ ይመረት የነበረውን ማዳበሪያ ወደ በዘመናዊ መንገድ እንዲከናወን በማድረግ አፈሩን መርምሮ ትክክል ይዘት ያለውን ማዳበሪያ እያመረተ ይገኛል። በዚህም የአባላቱ ምርታማነት እንዲጨምር እያደረገ ነው፡፡
«የሁሉንም ህብረተሰብ ፍላጎት በመንግሥት ብቻ ማሟላት አይችልም» የሚሉት አቶ ኦርጌሳ፣ ህብረት ሥራ ማህበሩ በተለይም መንግሥት ሊደርስባቸው ባልቻለባቸው አካባቢዎች ላይ የሰውና የእንስሳት የጤና ኬላዎችን በመገንባት፣ የተፈጥሮ ሀብት እንክብካቤ በማድረግ እንዲሁም ችግረኛና አካል ጉዳተኛ ሰዎችን የትምህርት ዕድል እንዲያገኙ በማድረግ ማህበራዊ ኃላፊነቱንም እየተወጣ መሆኑን ያብራራሉ።
ህብረት ሥራ ማህበሩ አገሪቱ የሚያስፈልጋትን የመካናይዜሽን የግብርና ፕሮግራም መጀመሩን የሚገልጹት ሥራ አስኪያጁ፣ በዚህም ውጤታማ እየሆነ መምጣቱን ይጠቁማሉ። ይህንን በማስፋት በሁሉም አካባቢዎች ግብርናው እንዲዘምን የሚያስችሉ ሥራዎችን እንደሚሠራም ያብራራሉ። እስከ አሁን ሲሠራ የነበረውን የዘር ብዜት ሥራም በቀጣዮቹ ዓመታት አስፍቶ ለመሥራትም መታቀዱን ይጠቁማሉ።
በቾ በምርታማነታቸው ከሚታወቁ የአገሪቱ አካባቢዎች አንዱ ነው የሚሉት ሥራ አስኪያጁ፣ በአካባቢው በብዛት በሚመረተው ሽምብራ ላይ እሴት በመጨመር የውጭ ገበያውን ለመቀላቀል ከፍተኛ ፍላጎት አለው ይላሉ።
እንደ ሥራ አስኪያጁ ማብራሪያ፤ ማህበሩ አባላቱ የተሻለ አምራች እንዲሆኑ ድጋፍ ያደርጋል። ምርታቸውንም ይሰበስባል፤ ምርቱ ወደ ገበያ እንዲገባ ለማድረግም በአዲስ አበባና በሌሎች የክልል ከተሞች ከሚገኙ የሸማች ማህበራት ጋር በህብረት ሥራ ማህበራት ኤጀንሲ አማካይነት ትስስር ይፈጥራል።
በደቡብ ክልል ጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ የሚገኘው አድማስ የህብረት ሥራ ማህበርም እንዲሁ አርሶ አደሩን ተጠቃሚ እያደረገ ይገኛል። ማህበሩ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ፣ የኢንዱስትሪ ውጤቶችን ለአርሶ አደሩ በማድረስ ተጠቃሚነታቸውን እያሳደገ ነው፡፡ በሥሩም 134 መሰረታዊ ማህበራት እንዲሁም ከ 50 ሺ በላይ የተናጥል አባላት ያሉት ሲሆን፣ በአስር ወረዳዎች ይንቀሳቀሳል።
ማህበሩ በ1995 ዓ.ም በ 153 ሺ ብር የተመሰረተ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ገቢው 23 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር ደርሷል። ሁለት ሠራተኞችን ይዞ ቢሮ በመከራየት ሥራውን አሀዱ ብሎ የጀመረው ማህበሩ፣ አሁን 54 ቋሚና 20 ጊዜያዊ ሠራተኞች አሉት።
የማህበሩ ሥራ አስኪያጅ ተወካይ አቶ አበበ ወርቅነህ እንደሚሉት፤ ለአባላት ምርጥ ዘር ማቅረብ፣ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች ማስተዋወቅና እንዲጠቀሙ ማድረግ ትምህርትና ሥልጠና መስጠት፣ የመጋዘን አገልግሎት ማመቻቸት፣ በየጊዜው ተለዋዋጭ የሆኑ ቴክኖሎጂዎችን እንዲላመዱ እንዲሁም አባላት የአካባቢ የገበያ መረጃ እንዲያገኙ ማስቻል ከሥራዎቹ ጥቂቶቹ ናቸው።
እንደ ተወካዩ ገለጻ፤ ማህበሩ የኑግ አምራች አባላትን ኑግ በመረከብና በማዘጋጀት «ቸምና» የተጣራ የኑግ ዘይት በጥራት እያመረተ ለአባላቱ እንዲሁም ለህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ ያቀርባል፡፡ ከዘይቱ ተረፈ ምርት ፋጉሎ በማምረት ከብት ለሚያደልቡ አባል አርሶ አደሮች በማከፋፈል ተጠቃሚነቱን ዘርፈ ብዙ እያደረገም ነው።
የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት በማሳደግ ኑሮው እንዲሻሻል ለማድረግም ምርቶቹን በፋብሪካ ለማቀነባበር እንዲቻልም ፋብሪካዎችን እንደሚገነባም ነው ተወካዩ የጠቆሙት። በአካባቢው ቡና አምራች አርሶ አደሮች እንደሚገኙ ገልጸው፣ ምርታቸውን ቆልተውና አሽገው በአጠቃላይ እሴት ጨምረው ለውጭ ገበያ እንዲያቀርቡ በአሁኑ ወቅት ፋብሪካ እየተተከለ መሆኑን አመልክተው፣ የፋብሪካው ግንባታ ሲጠናቀቅም የመኖ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ለማቋቋም ዝግጅቱ መጠናቀቁን አስረድተዋል።
አቶ አበበ እንደሚሉት፤ ማህበሩ የመጀመሪያውን የዘይት መጭመቂያ ፋብሪካ ሲያቋቁም ከፍተኛ ውጣ ውረድ ያገጠመው ቢሆንም ትልቅ ትምህርት ተቀስሞበታል፡፡
በወቅቱ አባላት ለፋብሪካ ያላቸው ግንዛቤ ዝቅተኛ በመሆኑ የተነሳ፣ ለፋብሪካው የሚያስፈልገውን ገንዘብ በማሰባሰብ ላይ ችግሮች ማጋጠማቸውን በአብነት ጠቅሰው፣ ይህ ግን ለቀጣዮቹ ፋብሪካዎች ግንባታ ትምህርት እንደተቀሰመበት ይገልጻሉ።
በ40 ዩኒየኖች የተቋቋመው የኦሮሚያ ሁለገብ የግብርና ፌዴሬሽን ሌላው የህብረትና የአብሮ መሥራትን ስኬታማነት ማሳያ ነው። ፌዴሬሽኑ በ2000ዓ.ም የተቋቋመው 1 ነጥብ 1 ሚሊዮን አርሶ አደሮችን አባል አድርጎ ነው። አሁን የአባላቱን መጠን ከ 3 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ አድርሷል። አባል የዩኒየኖቹም ወደ 65 ከፍ ብለዋል፡፡ ሲቋቋም 15 ሚሊዮን ብር ካፒታል የነበረው ፌዴሬሽኑ ይህን ካፒታሉን አሁን 90 ሚሊዮን ብር አድርሷል።
የፌዴሬሽኑ የግብይት ኃላፊ አቶ ንጉሴ ለገሰ እንደሚናገሩት፤ ፌዴሬሽኑ ሲቋቋምም ትንሽ የሚባል ባይሆንም፣ አሁን ግን ከትልልቆቹም በላይ ትልቅ ሆኗል። ትልቅ ለመሆኑ ዋናው ምስጢር ጠንክሮ መሥራቱ ሲሆን፣ የበቆሎ ዱቄት ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ተክሎ በስፋት እየሠራ ይገኛል። በቅርቡም የአሰላ ብቅል ፋብሪካን በ1ነጥብ 36 ሚሊዮን ብር በመግዛት የትልቅነት ጉዞውን አፋፍሟል።
የብቅል ፋብሪካው መገዛት በራሱ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚያሳድገው ተናግረው፣ የቢራ ገብስ አምራቾች ምርታቸውን ቀጥታ ወደ ፌዴሬሽኑ በማምጣት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማስቻሉን ያመለክታሉ። ፌዴሬሽኑ ፋብሪካውን በተረከበ በ6 ወራት ጊዜ ውስጥ ከ140 ሚሊዮን ብር በላይ የተጣራ ትርፍ ማስገኘቱን ይናገራሉ።
እንደ አቶ ንጉሴ ገለጻ፤ ፌዴሬሽኑ በገላን ከተማ ላይ ቀድሞ ከነበረው በተጨማሪ ሌላ የምግብ ምርቶች ማቀነባበሪያ ኮምፕሌክስ ግንባታ እየተጠናቀቀ ነው፡፡ ከአንድ ቢበዛ ከሁለት ወራት በኋላ ወደ ሥራ ይገባል። ይህ በራሱ ከ 500 በላይ ሠራተኞችን በመቅጠር ሰፊ የሥራ ዕድል ይፈጥራል፡፡
በዚህም ፌዴሬሽኑ ሀገሪቱ የተያያዘችውን ኢኮኖሚውን ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ የማሸጋገር ራእይ ለማሳካት የሚጠበቅበትን እየተወጣ ነው ያሉት አቶ ንጉሴ፣ ፌዴሬሽኑ ትኩረት አድርጎ እየሠራ ያለው በማህበራዊ አቅም ግንባታ ላይ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ በዚህም ብዙ ማትረፍ ላይ ሳይሆን ትኩረቱ ዩኒየኖችና የህብረት ሥራ ማህበራቱ ባመረቱት ልክ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እንደሚደረግም ይጠቁማሉ፡፡
የተለያዩ የአቅም ግንባታ ሥራዎችን እንደሚያከናውን፣ አመልክተው፣ አንድ ፀረ አረም ኬሚካልና ሌሎችንም በማስመጣት ገበያው ላይ ካለው ዋጋ በሚቀንስ መልኩ በመሸጥ አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ማድረግም ሌላው ኃላፊነቱ መሆኑን ይናገራሉ።
«ፌዴሬሽኑ በአንድ ጊዜ አርሶ አደሩን ሀብት በሀብት አያደርገውም፤ ከዝርፊያ ያድነዋል፤ ገንዘቡም ሲጠራቀም ኑሮውን ደረጃ በደረጃ ከፍ ያደርግለታል፤ ምርት በሚሰበስብበት ወቅት ደግሞ ነጋዴዎች ሊገዙት ከተዘጋጁበት ዋጋ በላይ በመግዛት ተጠቃሚ እንዲሆን እየተሠራ ነው» ሲሉ ያብራራሉ። አዲስ ዘመን ታህሣሥ 2/2011 እፀገነት አክሊሉ
የተጣራ ትርፍ ሲገኝ ወደ ዩኒየን፣ ከዛም ወደ መሰረታዊ የህብረት ሥራ ማህበራት እንደሚወርድ ጠቅሰው፣ ማህበሩ ለእያንዳንዱ አባል አርሶ አደር እንደሚያከፋፍል ይጠቁማሉ፡፡ ይህን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለውን ፌዴሬሽን ሌሎች አርሶ አደሮችም አባል እንዲቀላቀሉ ለማድረግ ከፍተኛ ተግባር እንደሚከናወንም ይጠቁማሉ።
የፌዴራል ህብረት ሥራ ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዲ ሙመድ እንዳሉት፤ የህብረት ሥራ ማህበራት በመደራጀት ለውጥን የሚያመጡ ናቸው። ከጊዜ ወደ ጊዜ ራሳቸውን እያበቁና በገጠርም ሆነ በከተማ የህብረተሰቡን ፍላጎት የሚያረኩ ተግባራትን እየፈጸሙም ይገኛሉ። በአሁኑ ወቅት የመደራጀት ፍላጎቱም በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ነው።
በአሁኑ ወቅትም 85 ሺ መሰረታዊ የህብረት ሥራ ማህበራት እንዲሁም 388 የሚሆኑ ዩኒየኖች በሀገሪቱ ይገኛሉ፡፡ ሦስት ፌዴሬሽኖችም አሉ። የእነዚህ ማህበራት አባላት መጠንም 19 ሚሊዮን ደርሷል፡፡
«በአንዳንድ አገሮች የሚገኙ የህብረት ሥራ ማህበራትን ብናይ ከህዝብ ቁጥራቸው በላይ ከመሆኑ አንጻር ሰፊ ተደራሽነት ያለውም ነው» ያሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፣ እነዚህ ማህበራት ወደ 22 ቢሊዮን ብር ካፒታል እንዳላቸው፣ የቁጠባ መጠናቸውም 15 ቢሊዮን ብር መድረሱን ያብራራሉ፡፡
እንደ አቶ አብዲ ገለፃ፤ የህብረት ሥራ ማህበራቱ ከ1ነጥብ 5 ሚሊዮን ለሚሆኑ ዜጎችም ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል ፈጥረዋል፤ይህም ህብረት ሥራ ማህበራት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደጉ መምጣታቸውን ያመለክታል።
«የቁጥራቸውን ያህል ተጽዕኖ የመፍጠር አቅማቸው ገና ይቀረዋል» የሚሉት አቶ አብዲ ፣ አቅማቸውን አጠናክረው በተቻለ መጠን በገበያው እንዲሁም በአገር ኢኮኖሚ ግንባታው ላይ የራሳቸውን ሚና እንዲጫወቱ ሆነው ሊጠነክሩ እንደሚገባም ያሳስባሉ።
አዲስ ዘመን ታህሣሥ 2/2011
እፀገነት አክሊሉ