“የአዲስ አበባን ሸክም ሊካፈሉ የሚችሉ፤ ከአዲስ አበባ የተጠጋ አገልግሎት እና ኢኮኖሚ ያላቸው ከተሞች መፈጠር አለባቸው” – ወይዘሮ ሄለን ደበበ – የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ሚንስትር ዴኤታ

ከተማና ከተሜነት በአለም አቀፍ ደረጃ እያደገ ያለና የሚኖር ጉዳይ ነው። የበርካታ ከተሞች አመሰራረትም ከንጉሳውያ የንግስና መቀመጫ ቦታነት የመጡ መሆናቸውም ይነገራል። ከተሞች የመንግስታት መቀመጫ ሲሆኑ በስራቸው በርካታ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች እንዲከፈቱና በዛም ዜጎች እንጀራ ፍለጋ በሚል ካሉበት ወደ ከተሞቹ እንዲተሙ ይሆናል።

ከዚህ አንጻር በኢትዮጵያም በተለያዩ ጊዜያት የመንግሥታት መቀመጫ በመሆናቸው የተፈጠሩ ከተሞች አሉ። አክሱም፤ ላሊበላ፤ ሸዋ እና ጎንደር ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ናቸው። አሁን ላይ ከእነዚህ ሁሉ ከተሞች በእድሜ ልጅ የሆነችው አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ እና የሀገሪቱ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ማዕከል በመሆን እያገለገለች ትገኛለች።

በ19ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ ላይ የተመሰረተችው አዲስ አበባ ዘመናዊ የመሠረተ ልማቶች፣ ህንጻዎች፣ የገበያ ማዕከሎች እና ደማቅ የባህል ትእይንት ያላት ከተማ ሆናለች። ከተማዋ እንደ የአፍሪካ ህብረት ዋና መስሪያ ቤት እና የተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ያሉ አለም አቀፍ ተቋማት መገኛ ነች። ይህም ሆኖ ግን ከተማዋ ከቤት አቅርቦትና ከመሰረተ ልማት ጋር የተያያዙ በርካታ ጥያቄዎች በየጊዜው ይነሱባታል።

በዛሬው የተጠየቅ አምዳችንም የከተማና መሰረተ ልማት ሚንስቴር ሚንስትር ዴኤታ እና የቤቶችና የከተማና ልማት ዘርፍ ኃላፊ ከሆኑት ወይዘሮ ሔለን ደበበ ጋር በአዲስ አበባ እና በሌሎች ከተሞች እየተከናወኑ ያሉ አጠቃላይ የመሰረተ ልማት እንቅስቃሴዎች የተመለከተ ቆይታ አድርገናል። መልካም ንባብ።

አዲስ ዘመን፡- እንደተቋም በባለፈው ዘጠኝ ወራት ምን አቅዳችሁ ምን አሳካችሁ?

ወይዘሮ ሄለን፡- ባለፈው ዘጠኝ ወራት በቤቶች ልማት ዘርፍ ላይ በተለያዩ አማራጮች የቤት አቅርቦትን ለማሳደግ አቅደን ነበር። ዕቅዱ በአጠቃላይ በ9 ወራት ወደ 126ሺ 500 ቤቶች በተለያዩ አማራጮች ይቀርባሉ የሚል እቅድ አቅደን አፈጻጸሙን ስናይ፤ በራስ አገዝ ህብረት ስራ ማህበራት ተደራጅተው ለዜጎች መንግስት መሬት አቅርቦላቸው እነሱ ቆጥበው ሰርተው የቤት ባለቤት የሚሆኑበት አንዱ አማራጭ ነው።

በዚህ እቅድ በ10 ዓመቱ እቅድ ውስጥም እንዳካተትነው በአጠቃላይ ከሚሰራው ቤት ላይ 35 በመቶ የሚሆነው ቤት በማህበር የቤት አማራጭ ይሸፈናል የሚል ነው። ከዚያ አንጻር በማህበራት የቤት አማራጭ ወደ 25 ሺ 400 ቤቶች ቀርበዋል።

የቤት ባለቤትነት ጥያቄን ለመመለስ የመሬት አማራጭ ማስፋት እና ተደራሽነቱ ላይ መስራት ያስፈልጋል። ከዚህ አንጻር በተያዘው ዓመት 50ሺ 500 ቤቶች ይገነባሉ ተብሎ ታስቦ ከ50ሺ በላይ ቤቶች ተሰርተዋል።

ሌላኛው ደግሞ ሪል ስቴት ነው። ዘርፉ በሀገራችን በስፋት በዋና ከተማዋ እና በሌሎች ከተሞች ላይ እየሰፋ ያለ ነው። በአጠቃላይ ዘርፉም የእቅዳችንን 10 በመቶ እንዲሸፍን አቅደን ነበር። ከዚህ አንጻር ወደ 35ሺ 850 ቤቶች በሪል ስቴት አልሚዎች ተገንብተው ወደ ገበያ ገብተዋል።

በመንግሥት በኩል እንዲሁ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎች በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች የተሰሩ የቤት አማራጮች አሉ። ባሳለፍነው የዘጠኝ ወራት ወደ 8ሺ ቤቶች ይገነባሉ የሚል እቅድ ነበረን ሲሆን ከ10ሺ 200 በላይ ቤቶች በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ለዜጎች ተላልፈዋል።

ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከቤት ግንባታው በተጨማሪ ቤቶችን ማስተዳደር ስራዎችም ተከናውነዋል። በመሆኑም የቤት ኪራይ ዋጋን ከማስተካከል አንጻር ምን እርምጃ መወሰድ አለበት በሚል በእኛ የውስጥ ጥናቶች እንዲሁም ከሌሎች አጋር ተቋማት ጋር በመሆን ጥናቶች ተደርገዋል። በጥናቶችም ደንብ (regulation) ማዘጋጀት እንደሚገባ ተጠቁሟል። ከተደረጉት የጥናት ግኝቶች በመነሳት እና የሌሎች ሀገራትን ተሞክሮ በመውሰድ ደንብ (regulation) በማዘጋጀት በ2016 በጀት አመት ሥራ ተሰርቶ የመኖሪያ ቤቶች ኪራይ ቁጥጥርና አሰራር አዋጅ ጸድቆ ወደ ስራ ገብቷል። ይህም እንደሚኒስቴር መስሪያ ቤት የተመዘገበ ትልቅ ስኬት ነው።

እንደሚኒስቴር መስሪያ ቤት ለመስራት ከታቀዱ ሌሎች እቅዶች መካከል ደግሞ የከተማና መሰረተ ልማት ዝርጋታዎችን ማከናወን የሚለው ይገኝበታል። ከተሞቻችን ላይ እንደሚታወቀው ደረጃቸውን የጠበቁ መንገዶች፤ የመንገድ ዳር መብራቶች፤ የጎርፍ ማፋሰሻዎች፤ አረንጓዴ ፓርኮች ያስፈልጓቸዋል። ይህም በከፍተኛ ደረጃም እየተሰራ ነው።

ባለፉት ዘጠኝ ወራትም መንገዶች ይሰራሉ ብለን አቅደን፤ ትግበራው ከእቅዱ አንጻር ሲገመገም ተስፋ ሰጭ ነው የሚል ግምገማ አለን። በበጀት ዓመቱም የተለያዩ የመንገድ አይነቶች ሊገነቡ ችለዋል። ለአብነትም በዘጠኝ ወራት ውስጥ የተለያዩ የጠጠር መንገዶች፤ የአስፓልት እና የኮብል ስቶን መንገዶችን መገንባት ችለናል።

ከጠጠር መንገድ ግንባታ አንጻር ወደ አንድ ሺህ 250 ኪሎ ሜትር ለመገንባት አቅደን አንድ ሺህ 563ኪሎ ሜትር ለመገንባት ችለናል። 29ኪሎ ሜትር የአስፓልት መንገድ ለመገንባት አቅደንም 67ኪሎ ሜትር የአስፓልት መንገድ ለመገንባት ተችሏል። የውሃና የመብራት ስራዎችን ጨምሮ በከተማ ልማት ዘርፍ ላይ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ተስፋ ሰጭና ውጤታማ ናቸው።

አዲስ ዘመን፡- በከተሞች ያለውን የቤት ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ምን አቅዳችኋል? ምንስ ሰርታችኋል?

ወይሮ ሄለን፡- እንደ ሃገር በዘላቂነት ያሉብንን የቤት ችግሮች ለመፍታት በጥናት ያየነው እና እኛም በፈጸምነው የተቀናጀ የቤት ፕሮግራም ላይ የወሰድናቸው በርካታ ተሞክሮዎች አሉ። ከእነዚህ ተሞክሮዎች በመነሳት የቤት ፍላጎትን በዘላቂነት ለመፍታት በመንግሥት የቤት አቅራቢነት ብቻ ችግሩ እንደማይፈታ አይተናል።

በፍላጎትና በአቅርቦት በኩል ሰፊ ልዩነት አለ። የቤት ፈላጊው ማህበረሰባችን ቁጥር ደግሞ በየጊዜው እየጨመረ ነው። በቤት አቅርቦት እና በማህበረሰባችን ፍላጎት መካከል ያለውን ክፍተት ለመሙላት በተለያዩ አማራጮች ቤቶችን መገንባት ያስፈልጋል። አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ደግሞ ቤቶችን መገንባት በጣም ትልቅ ወጭን የሚጠይቅ ነው። እዚህ ላይ የመንግስት ሚና ከፍተኛ መሆን አለበት። መንግሥት ለማን ነው ቤት ማቅረብ ያለበት? የሚለውም በደንብ መታየት አለበት።

በሀገራችን የሚስተዋለውን የቤት ችግር ለመቅረፍ እና በቤት አቅርቦት እና በማህበረሰባችን ፍላጎት መካከል ያለውን ክፍተት ለመሙላት ከመንግሥት ቀጥሎ የግሉ ዘርፍ የራሱን አስተዋጽኦ ማበርከት አለበት። የግል ባለሃብቶች ከመንግሥት ጋር በመተባበር ግንባር ቀደም በመሆን ተዋናይ መሆን ካልቻለ ከቤት ጋር ተያይዞ የሚስተዋለውን ክፍተት መሙላታ አይቻልም።

ሌላው በቤት አቅርቦት እና በማህበረሰባችን ፍላጎት መካከል ያለውን ክፍተት ለመሙላት መጠቀም ያለብን አማራጭ ደግሞ “ራስ አገዝ ማህበራት” ማስፋፋት ነው። ይህ አካሄድ በምዕራባውያን፤ በሩቅ ምስራቅ፣ አፍሪካ እና ኤሽያ ሀገራት ላይ ትልቅ ችግር እየፈታ ያለ ነው።

በቤት አቅርቦት እና በማህበረሰባችን ፍላጎት መካከል ያለውን ክፍተት ለመሙላት እነዚህን እና መሰል ሁሉ አማራጮች መጠቀም ያስፈልጋል። ነገር ግን እንደ መንግሥት ከእኛ የሚጠበቀው ከላይ የተጠቀሱትን አመራጮች መስራት የሚችል ስርዓት መዘርጋት ነው።

አዲስ ዘመን፡- እንደሀገር ከቤት አቅርቦት ጋር ተያይዞ ለሚፈጠሩ ችግሮች አብይ ምክንያቶች ምንድን ናቸው?

ወይዘሮ ሄለን፡- አሁን ላይ እንደ ሀገር ያለው አንዱ እና ዋነኛው ችግር ለቤቶች ግንባታ የሚሆን የፋይናንስ አቅርቦት ያለመኖር ነው። ቤት መሰረታዊ ነገር ነው። ነገር ግን ሁሉም ሰው የቤት ባለቤት መሆን አይችልም።

የቤት አቅርቦቱን ለማስፋት በተለያየ አመራጭ የቤት ክምችቱን ማስፋት ይጠበቅብናል። ይህ ሲባል አቅሙ የፈቀደለት በባለቤትነት፤ አቅሙ ያልፈቀደለት ደግሞ በኪራይ ሊሆን ይችላል። ከዚህ አንጻር ስርዓት መገንባት ያስፈልጋል። ስርዓት መገንባት ሲባል አንደኛው የፋይናንስ ስርዓት መገንባት ነው። እንደ ሀገር ረዘም ላለ ጊዜ ብድር መመቻቸት ቢቻል በእድሉ መጠቀም የሚችል በርካታ የማህበረሰብ ክፍሎች አሉ። ለዚህ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር እንደመንግሥት በርካታ ስራዎች እየተከናወኑ ነው።

እንደሀገር የሆነ ጊዜ ተጀምሮ ያልዘለቀ የፋይናንስ ስርዓት አለ። እሱን እንደመንግሥት ለመፈታት በከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር የተጀመሩ ጥናቶች አሉ። ጥናቶች ተጠቃለው ለመንግሥት ይቀርባሉ። መንግሥትም ጥናቶችን መሰረት አድርጎ ስርዓቶችን ከተገነባ፣ ህጎችን እና ፖሊሲዎችን መቅረጽ ከቻለ ስርዓቱ በራሱ ቤት ፈላጊው የማልማት አቅም እንዲኖረው ያስችለዋል።

ሌላኛው ከቤት ጋር ተያይዞ ያለው ችግርና ቤት በጣም ውድ እንዲሆን እያደረገ ያለው የቴክኖሎጂ አቅርቦታችን እጅግ ኋላ ቀር በመሆኑ ነው። ስለዚህ ይህንን ዘርፍ

በቴክኖሎጂ መደገፍ ያስፈልጋል። ከዚህ አንጻር ከተለመዱት ብዙ የሲሚንቶ ፍጆታ ካላቸው ግንባታዎች ለመውጣት እና በሌሎች ሀገራት በምናያቸውን ተሞክሮዎች ወደሀገራችን ለማምጣት በመንግሥት በኩል በርካታ ስራዎች እየተከናወኑ ነው።

ሶስተኛው ችግር ደግሞ ከመሬት አቅርቦት ጋር የተገናኘ ነው። ስለሆነም ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የመሬት አቅርቦትን ማሻሻል ያስፍልጋል።

እነዚህ እና መሰል ችግሮችን መቅረፍ ከተቻለ ከቤት ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ ችግሮችን በዘላቂነት ችግሩን መፍታት ይችላል።

የግል አልሚዮችም ለዝቅተኛ፤ ለመካከለኛ እና ከፍተኛ ገቢ ላላቸው የማህበረሰብ ክፍሎች ገንብተው ማስረከብ የሚችሉባቸው ሁኔታዎችን ለማመቻቸት የተለያዩ ህጎች እየወጡ ነው።

አዲስ ዘመን፡- በቅርቡ ከጸደቀው ከቤት ኪራይ ቁጥጥርና አሰራር አዋጅ ምን ትጠብቃላችሁ?

ወይዘሮ ሄለን፡- የመንግሥት ሚና ቤት ማቅረብ ብቻ አይደለም። ህግና ደንቦችን በማውጣት መቆጣጠርም ነው። የጸደቀው የመኖሪያ ቤቶች ኪራይ ቁጥጥርና አሰራር አዋጅ ይፈታቸዋል ተብሎ ከሚጠበቃቸው ችግሮች መካከል ዋጋ ላይ ያለውን ያልተገመተ እና የሀገሪቱን ኢኮኖሚ እድገት ያላገናዘበ መሰረት ያላደረገ የዋጋ ጭማሪን ይቆጣጠራል። ነገር ግን አዋጁ ብቻውን ይህንን አያደርግም። የእኛ ሀገር ያለው አጠቃላይ የገበያ ሁኔታ ለህግ ተገዥነት በራሱ ሌላ ችግር ነው።

አዋጁ የወጣው ተከራዩን ለመጥቀም አከራዩ ደግሞ ለመጉዳት ታስቦ አይደለም። አከራዩ ለሀገሪቱ ግብር ከፋይ እና የቤት አቅራቢ መሆኑን መዘንጋት አይገባም። ቤት እያቀረበ ስለሆነ መበረታታትና መደገፍ ነው ያለበት። ስለሆነም አዋጁ የወጣው አከራይን ጎድቶ ተከራይን ለመጥቀም ሳይሆን የሁለቱንም ፍላጎት ህጋዊና ሚዛናዊ በሆነ መንገድ አስታርቆ ለመሄድ ነው። አከራዩም ለንብረቱ ተገቢውን ዋጋ ማግኘት አለበት። ተከራዩም እንዲሁ ባወጣው ገንዘብ ልክ ተገቢውን አገልግሎት ማግኘት አለበት። ከዚህ አንጻር መንግስት አዋጁ እንዲተገበር ማድረግ ከቻለ አሁን ያለውን የተጋነነ የቤት ኪራይ ዋጋ ለመቆጣጠር ያስችለዋል።

አሁን ያለው ዋጋ በትክክል ከኢኮኖሚው ጋር አብሮ የሚሄድ አይደለም። ያንን ማስተካከል ከቤት ኪራይ ያለፈ እድምታ ያለው ነው። በማስፈጸም በኩል ትልቅ ቁርጠኝነትን የሚፈልግ እና የህብረተሰቡን ትብብር የሚጠይቅ ነው። ችግሩን በመፍታና ዋጋውን በማረጋጋት በኩልም ትልቅ ችግር ፈች ነው።

አዲስ ዘመን፡- የቤቶች ግንባታን ከማስተር ፕላኑ ጋር አቀናጅቶ ለማስኬድ በእናንተ ተቋም በኩል ምን እየተሰራ ነው?

ወይዘሮ ሄለን፡- በእኛ ሀገር ከከተሞች ልማት ጋር ተያይዞ ትልቁ ችግር የመሰረተ ልማት ቅንጅት ችግር ነው። መሰረተ ልማት ስንል ቤትም መሰረተ ልማት ነው። በተለይ የጋራ መኖሪያ ቤቶች በየትኛውም አልሚ የሚገነቡ ቢሆኑም የሚገነቡት ቤቶች መንደር እና ከተማ ነው የሚሆኑት። ዜጎች ወደዚያ እንዲሄዱ ሲደረግም ከእቅድ ጀምሮ በሚገባ መቀናጀት አለበት።

አካባቢዎችን ስንፈጥር መሰረተ ልማቶቹን በተቀናጀ መንገድ ተናበው እንዲሄዱ በማድረግ በኩል ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ኃላፊነቱን ወስዶ መሰረተ ልማት ቅንጅት ካርታ እያስጠና ነው። በዘላቂነት አፍርሰን ገንብተን ማፍረስ ሳይሆን ሳንሰራው የምንቀናጅበት መንገድ እውን ይሆናል ብለን እናስባለን።

እንደሚታሰበው ግን ቀላል አይደለም ብዙ አድካሚ ነው። የቅንጅት ባህላችንም ብዙም ጠንካራ አይደለም። ይሄንን በመቀየር በርግጠኝነት ወደ ውጤት እናመጣዋለን።

አዲስ ዘመን፡- በ2017 የጋራ መኖሪያ ቤቶችን በመገንባት እና ለተጠቃሚዎች በማድረስ በኩል ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ምን አቅዷል? ተገንብተው ለነዋሪዎች የተላለፉና በቂ የመሰረተ ልማት ዝርጋታ የሌላቸውን የመሰረተ ልማት ዝርጋታውን ለማሟላትስ ምን ታስቧል?

ወይዘሮ ሄለን፡- እንደ ፌዴራል መንግስት ያለን ሚና ህግ እና ፖሊሲዎችን ማውጣት እንዲሁም ስትራቴጂዎችን ማመላከት ነው። ስለዚህ ከቤት ልማት አንጻር ያወጣነው ስትራቴጂ ሶስት አመታት አልፈውታል። በቤት አቅርቦትና ፍላጎት መካከል ያለውን ልዩነት እንዲሞላ በመንግሥት የሚቀርበው ቤት አንዱ አማራጭ ነው። “የፐብሊክ ፕራይቬት ፓርትነርሽፕ” ሌላኛው አማራጭ ነው። በተጨማሪም በማህበር የሚገነቡ የቤት አማራጮች እንዲተገበሩና የእቅዱ አካል እንዲሆኑ እየሰራን ነው።

እንግዲህ ከተሞች እና ክልሎች በራሳቸው ነባራዊ ሁኔታ በማቀናጀት ውጤት ሊያመጣላቸው የሚችለውን አማራጭ በመውሰድ በ2017 ወደ ትግበራ የሚገቡባቸው ሁኔታዎች አሉ። እነዚህ ጉዳዮች እውን እንዲሆኑ ደግሞ እንደ ፌዴራል መንግሥት በጋራ ተቀናጅተን ለመስራት ያለውን የህብረተሰብ ችግር እንዲፈታ በጋራ የምንሰራበት ሁኔታ ይኖራል።

ከመሰረተ ልማት አቅርቦት አንጻር ቀደም ሲል በተላለፉ ቤቶች ላይ የአቅርቦት ክፍተት እንዳለ ገምግመናል። ችግሮችን ለመቅረፍ በጣም ብዙ ስራዎች እየተሰሩ ነው። ለውጦችም እንዲሁ እየመጡ ነው። ለመኖር ምቹ አይደሉም የሚል ቅሬታ አለ፤ እውነትም በተጨባጭ ስናይ የውሃ እና የመብራት ችግር ያለባቸው አሉ። አሁን ላይ ግን የአብዛኛዎቹ ችግር እየተፈታ ነው። መብራት እንዲገባላቸው በርካታ ወጭ ወጥቶ የትራንስፎርመር ግዥዎች ተፈጽመዋል። ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በመቀናጀትና የፋይናንስ አማራጮችን በመፈለግ።

አዲስ ዘመን፡- በሥራችሁ ከሚገኙ ተጠሪ ተቋማትና ክልሎች ጋር ያላችሁ ግንኙነት ምን ይመስላል? በአጋርነት የሚሰሩ ተቋማትን አስተሳስሮና አናቦ ለመሄድ ምን አይነት ስራዎችን እየሰራችሁ ነው?

ወይዘሮ ሄለን፡- ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከክልሎች ጋር ብቻ ሳይሆን በከተማ አስተዳደር ካሉ መዋቅሮች ጋር በጋራ በመሆን ስራዎችን ይከውናል። ከነሱ ጋር ያለን መስተጋብርም እቅድ በጋራ እናቅዳለን፤ እቅዱም እንዲፈጸም “በሴክቶሪያል ጉባኤ” ተማምነን በመፈራረም ተከታታይ የሆነ ድጋፍና ክትትል እናደርጋለን።

የፋይናንስ፣ የቴክኒክ እና የስልጠና ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል የሚለውን እየለየን እንደፌዴራል ተቋም የክልሎቻንን እና የከተሞቻችንን አቅም እየገነባን ሥራ ወደ መሬት እንዲወርድ እናደርጋለን። ክልሎች እና ከተሞች ደግሞ በዚሁ መሰረት ሪፖርት ያደርጉልናል ሪፖርቱ በተጨባጭ መሬት ላይ አለ የሚለውን በአመራር ደረጃ እና ከፍተኛ ባለሙያ ሱፐርቪዥን ይደረጋል። ባገኘናቸው ሱፐርቪዥኖች እንዲሁ የጋራ ግምገማ እናደርጋለን።

ከክሎች ጋር በየስድስት ወሩ ግምገማ እናደርጋለን። ከእኛም ከእነሱም የሚታረሙ ነገሮች ላይ እየተማማርን የተሻለ አፈጻጸም እንዲኖር እያደረግን ነው። በዚህ ባለፉት ሁለት እና ሶስት አመታት ከክልሎች እና ከከተሞች ጋር የፈጠርነው መስተጋብር እጅግ በጣም ጠንካራ ሥራን ማዕከል ያደረገ ውጤት የሚያመጣ ተናባቢ በመሆኑ አመራሩም በልዩ መንገድ እስከ ክልል ከተሞች ድረስ ወርዶ ችግሮች እንዲፈቱ በማድረጉ ከፍ ያሉ ውጤቶች እና ለውጦች እየመጡ ነው።

ለመሰረተ ልማት ሚኒስቴር ተጠሪ የሆኑ በርካታ ተቋማት አሉ። ከእነዚህ ተቋማት ጋር ተቀናጅተን ነው የምንሰራው፤ በሁሉም ጉዳዮቻችን ላይ አንድ እቅድ እና አንድ ሪፖርት ነው ያለን። እንደ ተቋም መስራት ያለባቸው ጉዳዮች ላይ ራሳቸውን ችለው ይሰራሉ። እንደሚኒስቴር መስሪያ ቤት ደግሞ አንድ ሆነን ተቀናጅተን መስራት ያለብን ጉዳዮች ላይ በጋራ ሆነን እንሰራለን። የተለያዩ ተቋማት ተቀናጅተው ወደ እኛ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት መጥቷል። አሁን ባለው ቅንጅትም በርካታ ችግሮች ትርጉም ባለው መንገድ ተፈቷል። ሥራው ወደ እኛ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት መምጣቱ ትልቅ ጥቅም አለው።

አሁን የመሰረተ ልማት ጉዳይ በአንድ የመጣ ስለሆነ ቅንጅቱን በመምራት እና በመስተባበር ሂደት የእኛ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ስራውን ወስዶታል። አጠቃላይ ደግሞ የቅንጅት ማስተር ፕላን እየተዘጋጀ ነው። ማስተር ፕላኑ ሲተገበር ከፍ ባለ ሁኔታ ችግሮች ተቋማዊ በሆነ መንገድ የሚፈቱበት ይሆናል። አሁን ባለው ሁኔታ ግን ችግሮች ሙሉ በሙሉ ጠፍተዋል ባይባልም በጣም ጠበዋል። ስንመዝናቸውም በከፍተኛ ሁኔታ ለውጥ እያመጡ ችግሮች ሲያጋጥሙም በቸልተኝነት የምናልፋቸው ሳይሆኑ ቶሎ ብለን ተቋማት ተገናኝተው እንዲፈቱት በማድረግ ምሳሌያዊነት ያለው ሥራ እየተሰራ ነው።

አዲስ ዘመን፡- አዲስ አበባ ላይ የሚስተዋለው የቤት ችግር መንስኤው ከተማዋ መሸከም ከሚገባት የህዝብ መጠን በላይ ተሸክማ ነው ወይስ ባለን የመሬት አጠቃቀም ክፍተት የመጣ ነው?

ወ/ሮ ሄለን፡- አዲስ አበባም ሆነ በሀገሪቱ ባሉ ከተሞች የሚፈልሰው ህዝብ ቁጥር በጣም ፈጣን ነው። ነገር ግን ከተሜነቱ ምጣኔው ግን ገና ነው። እንደከተማና መሰረተ ልማት ችግሩን ለመፍታት የከተማ-የገጠር ግንኙነቱን ለማጠናከር እየተሰራ ነው። ከዚያ አንጻር ወደ ከተማ ያልመጡ ገጠር ላይ ያሉ ቦታዎች የገጠር ማዕከላትን በፕላን እንዲመሩ፤ ቤቶች እንዲሰሩባቸው፤ አገልግሎት ሰጭ ተቋማት እንዲገነቡባቸው እና እንዲሰበሰቡ በማድረግ የሥራ እድልን በመፍጠር ከገጠር ወደ ከተማ የሚመጣውን ፍልሰት እዚያው እንዲያዝ ለማድረግ እየተሰራ ነው። ይህንን መንገድ እስካልፈጠርን ድረስ ወደከተሞች የሚመጣውን ፍልሰት መቆጣጠር አይቻልም።

ጤናማ የሆነ እና ጤናማም ያልሆነ ፍልሰት አለ። ጤናማው ፍልሰት ለከተሞቹ የሚጨምረው ነገር አለ። ጤናማ ያልሆነ ፍልሰት ግን ውጤታማ ባለመሆኑ ከተሞች መያዝ ከሚገባቸው በላይ ሸክም ሌላ ሸክም ይፈጥራል። ይሄንን በመሰረታዊነት ለመፍታት በከተማና መሰረተ ልማት የተዘጋጀ ስትራቴጂ አለ። ትግበራውም ተጀምሯል።

ብዙዎቹ የገጠር ከተሞቹ “ስኬች ፕላን” አላቸው። በጣም ተራርቆ ያሉትን አንድላይ በመሰብሰብ ለወጣቶች የሥራ እድል መፍጠር የሚቻልበትን ሁኔታ መፍጠር ያስፈልጋል። ከሁሉም የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ጋር በመቀናጀት ችግሩን በዘላቂነት መፍታት ካልተቻለ አሁን የደረሰውን ችግር መፍታት አይቻልም። ጤናማ በሆነ መንገድ ባሉበት እንዲረጋጉና ዜጎች ከቄያቸው ወጥተው የሚደርስባውን ስቃይ እና መከራ መቀነስ ያስፈልጋል።

አዲስ አበባን ጉዳይ ስንመለከት ከተማ አስተዳደሩ በጥልቀት ያጠናው ጥናት አለ። እኛም እንደከተማና መሰረተ ልማት ፍልሰቱ ጤናማ ነው የሚል ግምገማ የለንም። በጣም ከፍ ያለ ወደ አዲስ አበባ የሚደረግ ጤናማ ያልሆነ ፍልሰት አለ። ያ ፍልሰት ጤና በሆነ መንገድ የሥራ እድል ተፈጥሮ መሸከም የሚችለውን ያክል እየተሸከመ አይደለም።

ከመሬት ጋር ተያይዞም ያለው ክፍተት አዲስ አበባ ያላት የቆዳስፋት ተወስዶ ቢታይ አብዛኛው ሰው እየኖረ ያለው ወደ ጎን በሆነ የአሰፋፈር ስርዓት ነው። ስለሆነም ትንሽ ሰው ብዙ መሬት ይዞ ነው የሚኖረው። የመሬት አጠቃቀም ባህላችንም በጣም ወደኋላ የቀረ በመሆኑ አሁን የማስተናገድ አቅማችን በዚያው ልክ እየተፈተነ ነው።

እንደ የአዲስ አበባ ህዝብ በጣም ተጠጋግቶ ለሚኖር ህዝብ መሰረተ ልማቶችን በማዘመን በከተማዋ የሚሰጡ አገልግሎቶችን በማሳለጥ ለህዝቡ ተደራሽ መሆን ያስፈልጋል። ነገር ግን አዲስ አበባን በመለጠጥ ብቻ የነዋሪዋን ችግር መፍታት አይቻልም። ይሄንን ለማድረግ ደግሞ ሃብት እና ቴክኖሎጂ ይፈልጋል። አሰፋፈራችንንም መቀየር ይፈልጋል። ፍልሰቱም ልቅ ሆኖ መምጣቱ አዲስ አበባ እና ዙሪያዋ ላይ ያለውን ጫና ከፍ ያደርገዋል።

አዲስ አበባ ከተማ የሚስተዋለውን ጫና ለመቀነስ የእንደከተማና መሰረተ ልማት ሌሎች ሁለተኛ ከተሞች መፈጠር አለባቸው። የአዲስ አበባን ሸክም ሊካፈሉ የሚችሉ እና ወደ አዲስ አበባ የተጠጋ አገልግሎት እና ኢኮኖሚ ያላቸው፤ ለዜጎች የኑሮ ሁኔታ አመቺ እና ሳቢ የሆኑ ከተሞችን መፍጠር ያስፈልጋል። ከጠቅላይ ሚኒስቴሩ አቅጣጫ ተሰጥቷል። ይህን እውን ለማድረግ እየተሰራ ነው። ይህን እውን ማድረግ ካልተቻለ አሁን በአዲስ አበባ እና ሌሎች ከተሞች እየታየ ያለውን የመሸከም አቅም ችግር መግታት አይቻልም።

አዲስ ዘመን፡- ቅርስ የሆኑ ቤቶች ያሉባቸውን አካባቢዎች ከመጠበቅ አኳያ ምን እየሰራችሁ ነው? በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ ቅርሶች እየጠፉ እንዳሉ የሚወሰድበት ሁኔታ አለ፤ ለዚህ የናንተ ምላሽ ምንድነው?

ወ/ሮ ሄለን፡- ከተማ ሲባል ህንጻዎች ብቻ ያሉበት ማለታችን አይደለም። ከተሞች ህይወት አላቸው። ከተማ ልማት የምንለው ከተማው የሚመራበት “ስፓሻል ድስትሪቢዩሽን” ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ “ሶሾ ኢኮኖሚው” ጥናት ያለበት ትልቅ ሰነድ ነው። ከተማው ላይ ምንድነው ያለው? ምን አይነት ታሪክ አለው? ኢኮኖሚው ከየት ወደየት ይሄዳል? የህብረተሰቡ ትስስርስ ምን ይመስላል የሚለው በደንብ ጥናት ይወሰዳል።

በተጨማሪም ከተሞች ገቢ የሚያስገኙት የቱሪስት መዳረሻ ሲሆኑ ነው። ይህ የሚሆነውም ታሪካዊነት ያላቸውን ቅርሶች መጠበቅ ስንችል ነው። ለዚህ ደግሞ በስነስርዓት ዘርግተን እየሰራን ነው። እየጠበቅናቸውም ነው።

አንዳንድ ቦታ ላይ ስናይ ከተማዋን በማደስ ሂደት ቅርስ እየጠፋ እንዳለ ተደርጎ የሚወሰድበት ሁኔታ አለ። ሁሉ ነገር ቅርስ ነው ማለት አይቻልም። በትክክል ለትውልድ ተሻጋሪ የሆኑ ቅርሶች ተለይተው እንዲሻገሩ እየተደረገ ያለበት ሁኔታ አለ። እኛ ሀገር ትንሽ ከእድሜ አንጻር ብቻ እየታየ ሁሉንም ነገር ቅርስ ነው የማለት ዝንባሌ አለ። ሁሉም ቅርስ ነው ካልን አጠቃላይ ከተማችንን የማደስ እና የመቀየር አንችልም። የመሬት አጠቃቀማችንን ችግር ውስጥ እንጥላለን። በዘላቂነት የቱሪስት መዳረሻ የሚሆኑትን ለይተን ከታሪካዊ ዳራቸው አንጻር በአዲስ አበባም ሆነ በሌሎች ከተሞች የጥበቃ ሂደት ዘርፉን ከሚመራው ተቋም ጋር በመሆን እየሰራን ነው።

አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ እናመሰግናለን።

ወይዘሮ ሄለን፡- እኔም አመሰግናለሁ።

መክሊት ወንድወሰን

አዲስ ዘመን ሐምሌ 3 ቀን 2016 ዓ.ም

 

Recommended For You