ካለፈው ስህተቱ መማር ያልቻለው ፌዴሬሽን የስፖርት ቤተሰቡን ተስፋ እንዳያጨልም

የተያዘው የውድድር ዓመት መቋጫ የሆነው ኦሊምፒክ ጥቂት ሳምንታት ብቻ ቀርተውታል። እንደሚታወቀው በዚህ ወቅት ሀገራት የባንዲራን ክብር ለማስጠበቅ ጠንክረው በአንድ ዓላማ የሚሠሩበት ነው። በመርህና የሁሉ የበላይ በሆነው ሕግ እየተመሩም የአትሌቶችን ምርጫና ዝግጅት ያካሂዳሉ።

በአንጻሩ በኢትዮጵያ፤ ኦሊምፒክ እና የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮናን መሰል ውድድሮች ሲቃረቡ ውዝግብና አለመግባባት መከተላቸው የተለመደ ሆኗል። የፓሪሱ ኦሊምፒክ መቃረቡን ተከትሎም የኢትዮጵያን አትሌቲክስ ፌደሬሽን የተጣባው በሽታ ዳግም አገርሽቶበታል።

በርግጥ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ ብሄራዊ ቡድንን አደራጅቶና አዘጋጅቶ ማቅረብ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ኃላፊነት እንደሆነ ይታወቃል። ሃላፊነቱን በአግባቡ ለመወጣትም ተቋማዊ አሠራሮች ፣ ዓለም አቀፍ ሕጎችን እና አሠራሮችን ተከትሎ መንቀሳቀስ ይጠበቅበታል።

ከዚህ አንጻር ፌሬሽኑ ዓመታት ባስቆጠሩ ችግሮች ተሳስሮ ስፖርቱን በሚጎዳ መንገድ ላይ እንደሚገኝ የአደባባይ ሚስጥር ነው ። ራሱ ያወጣውን ሕግ በራሱ ከመጣስ ጀምሮ በሥራ አስፈጻሚው ጣልቃ ገብነት የሚፈጠሩ ጣልቃ ገብነቶች ዛሬም የውዝግብ እና የችቅጭቅ ምክንያት እንደሆኑ ነው ።

ባለፈው ዓመት የሃንጋሪዋ ቡዳፔስት የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ማዘጋጀቷን ተከትሎ ኢትዮጵያን እንዲወክል የተደረገው ብሄራዊ ቡድን ውስጥ በተፈጠረው አለመግባባት በተፈጠሩ አሳዛኝ ክስተቶች የስፖርት ቤተሰቡ በብዙ ማዘኑ የሚታወስ ነው ።

በወቅቱ ለቻምፒዮናው የሚሆን የሰዓት ማሟያ ጊዜ ተጠናቋል ያለው ፌዴሬሽኑ፣ ሕጉን የጣሱ አትሌቶችን ሰዓት በመመዝገብ በስፖርቱ ላይ ትልቅ ወንጀል መፈጸሙ ፤ በአንጻሩ ይኸው ጉዳይ እንደ ወንጀል የተቆጠረበት ሌላ አትሌት ከቡዳፔስት እንባውን እያዘራ እንዲመለስ መደረጉ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው።

በተመሳሳይ በረጅም ርቀት ሰዓት የምታሟላ አትሌት ‹‹በስህተት ነው›› በሚል በቻምፒዮው እንዳትሳተፍ ተደርጋም ነበር። የሥራ አስፈጻሚዎች ፍላጎት እንጂ ምክንያታዊ ያልሆነ ምርጫ እንደሆነ በተነገረበት በዚያ ውድድር ላይም ብዙዎች አስቀድመው እንደገመቱት ስፖርቱ ከውጤትም ከፍትህም ሳይሆን ቀርቷል።

ይህንን ተከትሎም አዲስ ዘመን ጋዜጣ ከፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ ጋር ቆይታ አድርጎ ነበር። በወቅቱም ፕሬዚዳንቷ ‹‹ፌዴሬሽኑ ሕግ ሲጣስ ዝም ማለቱ መዘናጋት ነው። ያስቀመጠውን ሕግ ካላከበሩ ሀገርን ለመወከል አይበቁም በሚል ጠበቅ ያለ አሠራር አለመቀመጡ የፌዴሬሽኑ ድክመት ነው ብለው ነበር።

በቡዳፔስት ያጋጠመው ችግር አትሌትክሱ በጠንካራ ሕግ እና ዲሲፕሊን መመራት እንደሚኖርበት ጠንካራ መልእክት ያስተላለፈ ነው። ከዚህ በኋላ ውድድር ሲቃረብ መሰል ሁኔታ ውስጥ እንዳንገባ የሚያደርግ ሕግ በቅርቡ በሚደረገው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ በማጸደቅ፤ ክለቦችም ሆኑ ክልሎች በዚሁ መሠረት እንዲመሩ ለማድረግ ጥረት እናደርጋለን›› በሚል ቃል ገብተውም ነበር።

ይሁንና ይህ ሁኔታ ከዓመት በኋላ ተዘንግቶ ተመሳሳይ ችግር መፈጠሩ እየተስተዋለ ይገኛል። ካለፈው ጊዜ መማር ያልቻለው ፌዴሬሽኑ በድጋሚ ለአንዳንድ አትሌቶች አድልቶ ሌሎች አትሌቶችን ደግሞ በማስለቀስ ላይ ይገኛል። አስቀድሞ እጩዎችን በማሳወቅ ወደ ዝግጅት የገባው የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ብሄራዊ ቡድን የመጨረሻዎቹን ተሳታፊ አትሌቶችን ማሳወቅ ተከትሎ የተለመዱት ዓይነት ቅሬታዎችና የአትሌቶች ክስ በመሰማት ላይ ነው።

ፌዴሬሽኑ በሁለቱም ጾታ ከ800 ሜትር እስከ ማራቶን (ማጣሪያውን ማለፍ ካልቻለው የወንዶች 800ሜትር በቀር) ባሉት ርቀቶች ከእነተጠባባቂዎቹ 42 አትሌቶችን ስም አስታውቋል። ከዚህም ጋር ተያይዞ ከብሄራዊ ቡድኑ ጋር ለወራት ሲዘጋጁ ቆይተው ‹‹አለአግባብ ተቀንሰናል›› የሚሉ የአትሌቶች ድምጽ መሰማት ጀምሯል። ይህም ከወዲሁ የአትሌቲክስ ቤተሰቡን ቅሬታ እና እንደ ቶኪዮ ኦሊምፒክ የውጤት ስጋት ውስጥ እንዲገባ በማድረግ ላይ ነው።

የፌዴሬሽኑ ምርጫ አግባብ አይደለም ካሉት መካከል አትሌት ፍሬወይኒ ኃይሉ ትጠቀሳለች። በዓመቱ ጥሩ ሰዓት ያላት እና በ5ሺ ሜትር እንዲሁም በ 1 ሺህ 500 ሜትር የመሳተፍ አቅም ያላት አትሌቷ በአንዱ ርቀት ብቻ በተጠባባቂነት መካተቷ አስከፍቷታል። ምርጫው አድሏዊ አሠራርና ወቅታዊ አቋምን ያላገናዘበ ስትልም ስሜቷን በደብዳቤና በተንቀሳቃሽ ምስሎች አጋርታለች። በአንጻሩ ከእሷ የሚያንስ ውጤት ያላት አትሌት በኦሊምፒኩ ተሰላፊ መሆኗ ተረጋግጧል።

በሌላ በኩል ደግሞ አትሌት ጉዳፍ ጸጋይ በሶስት ርቀት እንደምትካፈል ፌዴሬሽኑ በምርጫው አመላክቷል። ምርጫው የተደረገውም ፌዴሬሽኑ ባስቀመጠው የጊዜ ገደብ በተመዘገበ ሰዓት ብቻ አለመሆኑም ተመላክቷል። ይህም ከፌዴሬሽኑ ባለፈ አትሌቶች እርስ በእርሳቸው ልዩነት እንዲፈጥሩም መንገድ እንደሚከፍት ግልጽ ነው።

ሁኔታው በየትኛውም አካሄድ ተገቢነት የሌለው ከመሆኑም በላይ በግልጽ የሥራ አስፈጻሚ ጣልቃገብነት ያለበት መሆኑን መረዳት ይቻላል። ሌሎች አትሌቶችም ይህንኑ ተከትሎ ፌዴሬሽኑ እስከመቼ ነው አትሌቶችን የሚያስለቅሰውና የሚያሳቅቀው በሚል በማህበራዊ ድረገጾች የጎረቤት ሀገር ኬንያን ተሞክሮ በማመላከት ሃሳባቸውን እያጋሩ ይገኛል።

በእርግጥ ጀግናዋ አትሌት ጉዳፍ ጸጋይ ሁሌም ሀገሯን በማኩራትና ሰንደቋን በማክበር በዚህ ወቅት በቀዳሚነት ስማቸው ከሚጠቀስ አትሌቶች መካከል አንዷ ናት። ይሁንና በሶስት ርቀቶች መሳተፏ ወቅታዊ አቋሟን ጥያቄ ውስጥ ከማስገባት ሳይሆን እንደ ሰው አቅምን ሊፈትን እንደሚችል በማሰብ ስጋት ማሳደሩ አይቀርም።

በውድድሩ ላይ ይህ ግምት እውን ሆኖ ሜዳሊያ ባይገኝ የስፖርት ቤተሰቡ በድጋሚ በፌዴሬሽኑ አሠራር ላይ ጣቱን መቀሰሩ አይቀሬ ነው። ታዲያ ይህንን ኃላፊነት ለመውሰድ ፌዴሬሽኑ ተዘጋጅቷል?። ወይስ በተመሳሳይ መንገድ ሊያጋጥም የሚችለውን ችግር ለመመለስ እየተዘጋጀ ነው?።

ስፖርቱን የሚመሩ አካላት እርስ በእርስ የገቡበት ቅራኔ ውጤቱ ላይ ተጽእኖ እንዳያሳድር ስጋት የማሳደሩ ነገር መፍትሄ ሳያገኝ ፌዴሬሽኑ በአትሌቶች ላይ ስህተት መሥራቱ ሌላኛው ይቅር የማያሰኝ ጥፋት ነው። በመርህና በሕግ ከመመራት ይልቅ ልምድና ስሜትን ማስቀደም ከስፖርቱም ከስፖርት ቤተሰቡም ጋር መቀያየም ብቻም ሳይሆን በታሪክም ተወቃሽ ያደርጋል።

ከዚህ ቀደም የውጤት መጥፋት መንስኤው ስፖርቱን በማያውቁ ሰዎች መመራቱ ነው ሲሉ የቆዩ የስፖርቱ ዓለም ሰዎች እድሉ በእጃቸው እያለ የሚፈጽሙት ስህተት ምናልባትም ከሠሩት ታሪክ ሊበልጥ እንደሚችል ማሰብ ይገባቸዋል።

እንደዛሬው ባልዘመነውና አስፈላጊው ሁሉ በቀላሉ በማይገኝበት በዚያን ዘመን ሀገር ያስከበሩ አትሌቶች ከምንም በላይ ሀገርን አስቀድመው እርስ በእርሳቸው ተከባብረው ማለፋቸውን መዘንጋት የለብንም።

ታላቁን የኦሊምፒክ መድረክ ሲያልሙ የኖሩና ለሀገራቸው ሁሉን ሊሰጡ የተዘጋጁ ወጣት አትሌቶችን ተስፋ ማጨለምም ያለፉትን የኦሊምፒክ ጀግኖች ታሪክ ማደብዘዝ ይሆናል። ስለዚህም የሚመለከታቸው ሁሉ በቀረው አጭር ጊዜ ስህተታቸውን አርመው ከቅሬታ የጸዳና ሀገርን ብቻ ባስቀደመ ቡድን ኢትዮጵያ እንድትወከል ቢያደርጉ መልካም ነው።

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን ሐምሌ 3 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You