ብክለትና ብክነት የወቅቱ የህልውና ስጋት

የሰው ልጆች ኑሮን ለማዘመን በካይ የአኗኗር ዘይቤን በመከተላቸውና ከተፈጥሮ ጋር በገጠሙት ጦርነት ምድራችን ለመኖሪያነት የነበራትን ምቹነት እያጣች ትገኛለች። አለማችንም ከአየር ንብረት ቀውስ ለመፋታት ልጆቿን እየተማጸነች፣ ፍቱን የሆነ መድሃኒት እንኳን ባይገኝ ጊዜያዊም ቢሆን ማስታገሻ የሚሠጣትን አጥብቃ መሻቷን ቀጥላለች፡፡

ቀውሱ

ሰዎች በተለያየ መንገድ ተፈጥሮን እያራቆቱ መሄዳቸው እየዋለ ሲያድር በየፈርጁ ዋጋ እያስከፈላቸው ይገኛል። ቀውሱም ድሃም ሆኑ ሃብታም የሚባሉ ሃገራትን ሳይለይ የጥፋት በትሩን ሁሉም ላይ እያሳረፈ ይገኛል። የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ድንበር ዘለል እንደመሆኑ በተለይም ለቀውሱ ያላቸው ድርሻ እጅጉን ዝቅተኛ የሆኑ ታዳጊ ሀገራት በተደጋጋሚ ድርቅና ጎርፍ የተነሳ ለምግብ እጥረት፣ ለበሽታዎች መስፋፋት፣ ለሥርዓተ ምህዳርና ብዝሀ ህይወት መመናመንና ውድመት ሲዳረጉ ማየት የተለመደ ሆኗል፡፡

በእርግጥ የአየር ንብረት ለውጥ እሳት የበላቸውም ሆነ ቀጣዩ ቀውስ የሚያሰጋቸው የተለያዩ ሃገራት የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ልዩ ትኩረት ሰጥተው መስራትና አጀንዳቸው ብሎም የፖሊሲያቸው አካል አድርገው በመንቀሳቀስ ላይ ናቸው። ምንም እንኳን እነዚህ ተግባራት ቀውሱ ከዚህም ላይ ቅጣቱን እንዳያስመለክት አስተዋፅኦ ማድረጋቸው የማይካድ ቢሆን ውጤታማነታቸው ሲፈተሸ ግን ብዙ እንደሚቀር የሚያከራክር አይደለም፡፡

ኢትዮጵያ

ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ እያስከተለ ላለው ተፅዕኖ በከፍተኛ ሁኔታ ተጋላጭ ናት። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህም ከችግሩ አሳሳቢነት አንፃር ህዝብን ባሳተፈ መልኩ የተፈጥሮ ሀብትና እንክብካቤ ዘዴዎችን በመጠቀም የአየር ንብረት ለውጥ የሚፈጥራቸውን ተጨማሪ ስጋቶችና አደጋዎችን ለመቀነስና ተፅእኖዎቹን ለመቋቋም አስደናቂ ሊባሉ የሚችሉ ተግባራት እያከናወነችም ትገኛለች።

በተለይ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) መሪነት፣ የአካባቢ ጥበቃን በማጠናከር ለሁሉም የምትመች፣ ፅዱና አረንጓዴ ኢትዮጵያን እንዲሁም ውብ ከተሞችን የመፍጠር ዓላማን ያነገቡ ኢኒሼቲቮችን ማስጀመራቸው የሚታወስ ሲሆን፤ የአረንጓዴ አሻራ፣ ጽዱ ኢትዮጵያን የመሳሰሉ ንቅናቄዎችም አስደናቂ የሚባሉ ውጤቶች ለማስመልከት አልተቸገሩም፡፡

በተለይም በደን ልማት ላይ በመከናወን ላይ የሚገኙ ተግባራት በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ የሚደርሰውን የደን መራቆት በመቀነስ በኩል ትልቅ ተጨባጭ ውጤት የተገኘባቸው ናቸው። ሀገሪቱ ባለፉት አምስት ዓመታት 32 ቢሊዮን ችግኞችን በመትከል ቀውሱን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የራሷን አስተዋጾኦ ከማበርከቷም በተጨማሪ እንደ ሀገር ብቻ ሳይሆን ዓለምን ከካርቦን ልቀት ለመታደግ ለተያዘው ዓለም አቀፍ ጥረትም ጉልህ ፋይዳ እያበረከተች ትገኛለች፡፡

መረጃዎች እንደሚያመላክቱትም፣ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ-ግብር የተከናወኑ የደን ማልማት ሥራዎች በአየር ንብረት ሥርዓቱ ላይ ተጨባጭ ለውጥ ከማምጣት ባሻገር የኢትዮጵያ የደን ሽፋን እንዲጨምርና ከ2 ነጥብ 8 ቢሊየን ቶን በላይ ካርበን ማከማቸት አስችሏል። ይህም ከሀገር አልፎ ለዓለም አቀፉ የአየር ንብረት ሥነ-ምኅዳር ጉልህ ድርሻ እንዳለው እሙን ነው፡፡፡

በእስካሁኑ ሂደት በተከናወኑ ዘርፈ ብዙ ተግባራት ለዓለም ምሳሌ የሚሆኑ ተጨባጭ ውጤቶችና ለውጦችን ማስመልከት ቢቻሉም አሁንም ቢሆን ቀሪ ስራዎች ስለመኖራቸው የሚካድ አይደለም። ሀገሪቱም በአካባቢ ብክለትና ብክነት እየተፈተነች መሆኗም የሚያከራክር አይደለም::

የአካባቢ ደህንነትን የሚያስጠብቁ ህጎች እንዲከበሩ ከማድረግና የክትትል፣ ድጋፍና ቁጥጥር ስራዎች በየደረጃው እየተከናወኑ ቢሆንም ስራዎችን በቅንጅትና ወጥነት ባለው መልኩ ከመስራት ብሎም በባለቤትነት መንፈስ ከመፈፀም አንፃር ሲታይ በርካታ ክፍተቶች ይታያሉ፡፡

የዘርፉ ምሁራን እንደሚያስረዱት ከሆነም፣ ብክለት የአንድን አካባቢ አፈር፣ ውሃ፣ አየር፣ ድምፅ… ፊዚካላዊና ባዮሎጂካላዊ ይዘቶች ማጥፋት ወይም ማበላሸት ማለት ነው። ብክለት የተፈጥሮን ወይም ሰው ሰራሽ ሀብቶችን በመበከል በሰው፣ በእንስሳትና በሌሎች ህይወታዊ በሆኑ ነገሮች ላይ ጉዳት ማድረስንም ያጠቃልላል፡፡

መረጃዎች እንደሚያመላክቱት፣ ሶስት ዋና ዋና የሆኑ የብክለት አይነቶች አሉ። እነሱም የአየር ብክለት፣ የውሃ ብክለትና የመሬት/አፈር /ብክለት ናቸው፡፡የድምፅ ብክለት፣ የጨረር ብክለትና የፕላስቲክ ብክለትም በተጨማሪነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

የውሃ ብክለት ማለት ግልጽ በሆነና በሌላ አገላለጽ ሲታይ የተለያዩ የውሃ መገኛ አካላት ማለትም የከርሰ ምድር ውሃና የገጽ ምድር ውሃ ለምሳሌ የምንጭ፣ የሃይቅ፣ የባህር ወይም የውቅያኖስ አካላት ለሰውም ሆነ ለሌሎች እንስሳትና ዕጽዋት ለመጠጥ፣ ለማብሰያነት፣ ለመዋኛነትና ሌሎች አገልግሎቶች እንዳይውል ወይም ህይወት ላላቸው ፍጡራን ጉዳት በሚያደርሱ ነገሮች መበረዝ ወይም መበከል ነው፡፡

በአሁን ወቅትም የውሃ ብክለት የውሃን ጥራትና ንፅህና እንዲቀንስ በማድረግ በአካባቢ የጤና ሁኔታና በዓለማችን ምጣኔ ሀብታዊ እንቅስቃሴ ላይ የሚያስከትለው ጉዳት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ ይገኛል። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ‹‹አስጠንቼዋለሁ›› ሲል ይፋ ባደረገው መረጃም፣ በ2025 አንድ ነጥብ ስምንት ቢሊዮን ህዝቦች ውሃ ፍለጋ ከቀያቸው ርቀው እግራቸው ወደመራቸውው እንደሚሄዱ አመላክቷል፡፡

በ2030 ደግሞ የውሃ እጥረት ወይንም ጥማት ከ 24 እስከ 700 ሚሊየን ህዝብ ሙሉ በሙሉ ከቀየው ተፈናቅሎ ‹‹ተሰዳጅ›› እንደሚሆን አትጠራጠሩም ብሏል። በጥናቱ እንደተመላከተውም፣ አህጉራችን አፍሪካ በውሃ እጥረት ብሎም ብክለት ክፉኛ ከሚቆስሉት አንዷ ስትሆን 25 የሚሆኑ ሀገራት ደግሞ ሕመማቸው ከሌሎችም እጅጉን ፅኑ ይሆናል ተብለው ተለይተዋል።

በተለያዩ በአካባቢ ጉዳዮች ላይ ድንቅ ሀተታዎችን በመፃፍ የሚታወቁ ፀሃፍትና የዘርፉ ምሁራንም‹‹ችግሩን ለመፍታትና ተፈጥሮን መልሶ ወደ ነበረችበት ክብር ቦታዋ ለመመለስ ወፋፍራም ሕጎች፣ ደንቦችና መመሪያዎች፤ ፕሮቶኮሎችና ስምምነቶች ከማዥጎድጎድ በላይ ፈጣንና የጋራ ትብብን የግድ ይላል፣ሁሉም ለመፍትሄው እጁን ካልሰበሰበ አትጠርጠሩ ጥፋቱ ከዚህም ይከፋል›› እያሉ ናቸው፡፡፡

ኢትዮጵያም የውሃ ብክለትና ብክነት ችግር ከሚስተዋልባቸው አገራት አንዷ ናት። ይህ ከጊዜ ወደ ጊዜ አሳሳቢ እየሆነ የመጣና ለሰው ልጅ ህልውና ከባድ ፈተናን የደቀነ የውሃ ብክለትና ብክነት ቀውስ ለመከላከልን ለመቆጣጠር ከውትሮው በተለይ ፍጥነትና ርብርብ መትጋት የግድ ይላል፡፡

በተለይም በአንዳንድ አካባቢዎች አንቦጭን የመሳሰሉ የመጤ ወራሪ ዝርያዎች ስርጭት በውሃ አካላት ላይ ከባድ ጥፋትን የሚያስከትል እንደመሆኑም መሰል ችግሮችን ለመከላከል፣ ለመቆጣጠርና ለማጥፋት ከወትሮው በተለየ መልኩ ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ የግድ ይላል።

ሌላኛው የወቅቱ አንገብጋቢ የብክለት አይነት የፕላስቲክ ብክለት ነው። በተለይም ሊዮ ቤክላንድ በሚባለው ግለሰብ እኤአ በ1907 ከዓለም የተዋወቁት የፕላስቲክ ምርቶች፣ የአካባቢን ተፈጥሮአዊ ይዘት በማሳጣት በሰው፣ በእንስሳትና በእፅዋት ላይ ከፍተኛ ጉዳትን ማድረስ ከጀመሩም ውለው አድረዋል፡፡

የፕላስቲክ ብክለት በአሁኑ ወቅት ፈጣን ምላሽ የሚፈለግ ዓለማችንን በእጅጉ እየፈተነ ያለ ዓለም አቀፍ እና ድንበር ዘለል የምድራችንና የሰዎች ደህንነት ስጋት ሆኗል። በበርካታ ሀገራት የተጠቃሚዎች ፍላጎት በእጅጉ መጨመርና መልሶ ጥቅም ላይ የማዋል አቅምም ሆነ ቴክኖሎጂ ውስንነትም ለቀውስ መባባስ አይነተኛ ምክንያት ሆኖ ይቀርባል፡፡

ችግሮች በኢትዮጵያ

የኢትዮጵያ የፕላስቲክ አጠቃቀምና አጠቃላይ አያያዝ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መሆኑንና እንደ ሀገር ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ የሚገባ ደረጃ ላይ እንደምንገኝ ጥናቶች ያመላክታሉ። በሀገሪቱ ለአብነት እኤአ በ2015 እና በ 2020 የተደረገ ጥናት ነበር። ለአብነት እኤአ በ2015 እስከ 2020 ባለው ጊዜ ብቻ ከአራት መቶ ፐርሰንት በላይ ጭማሪ አሳይቷል። ከዚህ ውስጥ ደግሞ መልሶ ጥቅም እንዲሰጥ በመደረግ ላይ የሚገኘው ከ7 በመቶ በላይ የሚበልጥ አይደለም፡፡

ጥናቱ እኤአ 2015 በቀን 9ሺ 700 ቶን ፕላስቲክ በቀን እንደሚወጣ የሚያሳይ ሲሆን ይህ አሃዝ በ2020 ወደ 12 ሺ 200 ቶን ከፍ ብሏል። በአንድ አመት 386 ሺ ቶን ፕላስቲክ በተለያየ መልክ ለማሸጊያና መያዥያ ለሌሎችም አገልግሎቶች ወደ ሀገር እየገባ ነው፡፡

በአሁኑ ወቅት የከተማዋ የአየር ብክለት ተጋላጭነት በተለይም የፕላስቲክ ምርቶች አጠቃቀምና አወጋገድ ድክመት ልዩ ትኩረት የሚፈልግ ደረጃ ላይ ይገኛል። ከዚህ ባሻገር የነዋሪ ቁጥር መጨመር፣ ከህብረተሰብ ግንዛቤ ማነስ ጋር ተደምሮ በተለይም የፕላስቲክ ማሸጊያዎችና መያዣዎችን በስፋት የመጠቀም ልምድ ከተሞችን ለከፍተኛ የአካባቢ ብክለት እንዲጋለጡ አድርጓቸዋል፡፡

ሀገር አቀፍ ንቅናቄው

ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የዘላቂ ልማት ግቦችን ጨምሮ በርካታ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን ፈራሚና አፅዳቂ ሀገር ናት። ዜጎች በህገ መንግስቱ የተጎናፀፉትን ንፁህና ጤናማ አካባቢ የመኖር መብት ማረጋገጥ ጨምሮ አባል የሆንባቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ለመተግበር በሁሉም ቦታና ጊዜ ተገቢ ጥረቶችን ማድረግ የግድ ይላል፡፡

በእርግጥ ሀገሪቱን ከተለያዩ የብክለት ምንጮች ለመጠበቅ በተለይ በሕግና በአሰራር ችግሩን ለመፍታት ዘርፈ ብዙ ጥረት ሲደረግ ቆይቷል። በዚህም ለውጦች ስለመኖራቸው የማይካድ ቢሆንም አስደሳች ናቸው ብሎ ደፍሮ ለመናገር ግን አስቸጋሪ ነው። ይህ ድክመት ለመለወጥ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የተለያዩ የመፍትሄ አማራጮችን በመከተል እየተሰራም ይገኛል።

የአካባቢ ጥበቃ ውጤታማነትን ለማሳደግ የወጡ ሕግና ደንቦች ተግባራዊ እንዲሆኑ በዘርፉ የባለድርሻ አካላትንና የማኅበረሰቡን ሚና ማጠናከርን ታሳቢ በማድረግ ባሳለፍነው መጋቢት 20 ቀን “ብክለት ይብቃ፤ ውበት ይንቃ” በሚል መሪ ሃሳብ የተጀመረው ሀገር አቀፍ ንቅናቄም የዚሁ አንድ አካል ነው።

ለሚቀጥሉት ስድስት ወራት ተግባራዊ የሚሆን ሀገር አቀፍ የብክለት መግቻ ንቅናቄ፣ በኢፌዲሪ የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን አስተባባሪነትም ከሚያዝያ 1/2016 እስከ መስከረም 30/2017 ዓ.ም የሚዘልቅ ነው። በመርሃ ግብሩም በየወሩ የተለያዩ የብክለት መቆጣጠር ስራዎች ለማከናወን እቅድ ተይዟል። ባሳለፍነው ሚያዝያ ወር ‹‹የፕላስቲክ አጠቃቀም ዘይቤያችንን እናዘምን›› በሚል መሪ ሀሳብ የተጀመረው ንቅናቄ የተለያዩ ስልቶች በመጠቀም በተለያዩ ተግባራት እየተካሄደም ይገኛል። የተለያዩ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮችም ለንቅናቄው ሁለንተናዊ ትግበራና ውጤታማ አፈፃፀም የነቃ ተሳትፎ በማድረግ ላይ ናቸው፡፡

በንቅናቄም ውጤታማ በሆነ መልኩ ቀጣይነት እንዲኖረውና የወቅቱን የህልውና ስጋት ብክለትና ብክነት ለመቀልበስ በተለይ አካባቢን ከብክለት የተፈጥሮ ሀብትን ከብክነት መጠበቅ የመኖርና ያለመኖር ህልውና ጉዳይ መሆኑን በመረዳት መላው ህዝብ ለትውልድ ያማረች አካባቢዋ የተጠበቀ ለሌሎች ምሳሌ የምትሆን ሀገር ለመገንባት መትጋት ይኖርበታል፡፡

ምን ይደረግ

በተፈጥሮ ላይ የተመረኮዘውን የሰው ሕይወት የተሻለ ለማድረግ ስህተቶችን ማረም የግድ ይላል። አካባቢን ከብክለት በመጠበቅ ለሰው ልጅ ተስማሚ የሆነ ስነ ምህዳር ለመፍጠርም በተቀናጀ መንገድ መስራት የግድ ይላል። ሁሉም ማኅበረሰብ ጤናማ አካባቢን ለትውልድ ለማስተላለፍ በእኔነት ስሜት የአካባቢ ብክለት መንስኤዎችን ማስወገድ ይጠበቅበታል፡፡

ከብክለት ነጻ እና ለኑሮ ተስማሚ የሆነ አካባቢን ለመፍጠር በተለይም የፕላስቲክ ቆሻሻ አጠቃቀምና አወጋገድን ማስተካከል የግድ ይላል። በየአካባቢው በዘፈቀደ የሚጣሉ ፕላስቲኮችን ዘወትር በማፅዳት አካባቢን ከብክለት ነፃ የማድረግና ስነ-ምህዳርን በዘላቂነት የመጠበቅ ሥራ የሁሉም ህብረተሰብ ኃላፊነት መሆን ይኖርበታል።

የፕላስቲክ ቆሻሻ ማስወገድ ብቻ ሳይሆን መልሶ ጥቅም ላይ የሚውልበት መንገድ እንዲፈጠር በትኩረት መስራት ያስፈልጋል። በተለይም የፕላስቲክ አምራቾች የሚያመርቷቸውን ምርቶች መልሶ መጠቀም የሚያስችላቸውን አቅም መፍጠርና፣ ጉዳቱን ለመቀነስ ድርጅቶች ለኅብረተሰቡ የሚሸጧቸውን የተለያዩ ምርቶች ለመሸጥ የሚጠቀሙትን የፕላስቲክ ምርቶች ወደ ሌሎች ፕላስቲክ ባልሆኑ ምርቶች የሚቀይሩበትን ሁኔታ መፍጠር ይገባል፡፡

በመጨረሻም

የበለጸገች፣ ጽዱና አረንጓዴ ኢትዮጵያን ለመፍጠር የተጀመሩ ዘርፈ ብዙ ጥረቶችም ውጤታማ በሆነ መልኩ ለማስቀጠል በተለይም አካባቢን ከብክለት የተፈጥሮ ሀብትን ከብክነት መጠበቅ የመኖርና ያለመኖር ህልውና ጉዳይ መሆኑን በመረዳት መላው ህዝብ የጀመረውን ሁለንተናዊ ጥረት ይበልጡን አጠናክሮ ሊቀጥልም ይገባል።

የአካባቢ ብክለትን መከላከል ለአንድ አካል ብቻ የሚተው ባለመሆኑ አጠቃላይ ነዋሪው፣ ግለሰቦችና ተቋማት አስተዋጽዖ ሊያደርጉ ይገባል። ለዚህም የሚዲያና ኪነ-ጥበብ ሰዎች የግንዛቤ መፍጠርና የጉዳቱን ልክ በማሳየት ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ሁነኛ አጋዥ ሊሆኑም ይገባል። በአሁን ወቅት የአየር ንብረት ለውጥ እያስከተለ የሚገኘውን ሁለንተናዊ ተፅዕኖን ለመቋቋም ሁሉም ሊረባረብ የግድ ይላል፡፡

የአየር ንብረት ለውጥ ለመመከት የሚከወኑ ተግባራትንም ሀገራዊ የእድገት አቅጣጫና ራእይ ጋር አጣጥሞ መከወን እንደ አማራጭ የሚወሰድ ሳይሆን እንደ ዋነኛ ስልት ሆኖ መወሰድ ያለበት ነው። የመፍትሄ እርምጃዎችም ከድህነት ቅነሳ፣ ከምግብ ዋስትና እና ከአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ስራዎች ጋር ሊዋህዱና ሊቀናጁ ይገባል። በየአካባቢው ማህበረሰቦች የሚገኙ ጠቃሚ ልምዶችና እውቀቶችን ከግምት ውስጥ ማስገባትም መዘንጋት አይኖርበትም፡፡

በጥናትና ምርምር በታገዘ መልኩ ለአየር ንብረት ለውጥና የተፈጥሮ አደጋዎች ይበልጥ ተጋላጭ ለሆኑ የኢኮኖሚ አውታሮችና የማህበረሰብ ክፍሎች ልዩ ትኩረት ማድረግም ያስፈልጋል። ብዝሃ ሕይወትንና ሥነ-ምህዳርን መሠረት ያደረገና ዘላቂነት ያለው የተፈጥሮ ሀብት አያያዝና(በተለይ የመሬት፣ የውሃና የሃይል) አጠቃቀምን መተግበር ያስፈልጋል፡፡

በሀገሪቱ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ማህበረሰብና ኢኮኖሚን ለመገንባትና የተለያዩ ከብክለት የፀዱ የልማት ስራዎችን ለማከናወን የሚያግዝ የቴክኒክ፣ የገንዘብና የተስማሚ ቴክኖሎጂ ድጋፍ ለማሰባሰብ በተቀናጀና ቀጣይነት ባለው መልኩ ተግቶ መስራትም የግድ ነው፡፡

የልማትና የአቅም ግንባታ ስራዎች ከጊዜያዊነት ባለፈ በአብዛኛው በአካባቢው ህብረተሰብ ሙሉ ፍላጎትና ተሳትፎ በመመስረት በዘላቂነትና በወጥነት የረዥም ጊዜ ግቦችን ከማሳካትና የአደጋ ስጋቶችን ከመቀነስ አንፃር ሊቃኙም ይገባል። በአጠቃላይ በሁሉም አቅጣጫ በመከናወን ላይ የሚገኙ ተግባራት በሙሉ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ማህበረሰብንና ኢኮኖሚን ከመገንባት አንፃር መቃኘት ይኖርባቸዋል፡፡

ታምራት ተስፋዬ

 አዲስ ዘመን ሐምሌ 3/2016

 

 

Recommended For You