ኢትዮጵያውያን በረጅሙ ዘመናቸው ከሚታወቁባቸው እሴቶቻቸው መካከል መረዳዳታቸው በእጅጉ ይጠቀሳል፤ የማንነታቸው አንዱ መለያም እሱው ነው። የእምነቶቻቸው መሰረቶችም ይሁኑ የወጡባቸው ማህበረሰቦች ማንነት ይህን ያደርጉ ዘንድ የግድ የሚሏቸው እንደመሆናቸውም ለቸገራቸው ሲሰጡ የኖሩት ከተረፋቸው አይደለም። ከአፋቸው ከፍለው፣ ለክፉ ቀን ካሉት ላይም አንስተው ይሰጣሉ።
በታክሲ ከመጓዝ ይልቅ በአውቶብስ መጓዝ ወጪን እንደሚቀንስ አምነው አውቶብስ ተሳፍረው እያለ የከፋ ችግር ያለበት እርዳታ የሚጠይቅ ሲገጥማቸው፣ ያቺን ተጠራቅማ ትልቅ ነገር ትሰራለች ብለው የቆጠቧትን ሳንቲም ብቻ ሳይሆን ሌላም ጨምረው ለተቸገረ ሲሰጡ የሚታዩትም ለእዚህ ነው። ከአፋቸው ክፍለው ብቻም ሳይሆን ተበደርው፣ ተለቅተውም የሚለግሱም ናቸው፡፡
ይህ የመረዳዳትና መተሳሰብ እሴታቸው፣ ይህ ለጋስነታቸው ግን ምክንያቱ የተለያየ ሊሆን ይችላል ክፉኛ እየተሸረሸረ መጥቷል። በዚህ የተነሳም በነበረበት ልክ አልገኝ እያለ ነው፤ አንዱ ጠግቦ የሚያደርገውን ሲያጣ፣ ሌላው የሚልስ የሚቀምሰው፣ አንገቱን ያስገባበት፣ ይፈወስበት እያጣ ካለበት ሁኔታ ይህንን መገንዘብ የሚቻለውም ይቻላል፤ በእዚህ አስከፊ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ዜጎች ቁጥር ይህ ሁኔታ ሊያጋጥም ይችላል ከሚያስብለውም በላይ እየገዘፈና እየሰፋ የመጣበት ሁኔታም ያ እሴት እየተሸረሸረ ስለመምጣቱ ያመላክታል።
ለተቸገሩ ሰዎች የሚደረገው ድጋፍ ከቤተሰብ አባል፣ ከእናት፣ አባት የሚዘልበትን ሁኔታ ብዙም ማየት እየተቻለ አይደለም። የመረዳዳቱ ልክ በጠባብ አካባቢ ውስጥ የታጠረ እየሆነ ይገኛል። በእዚህ የተነሳም በአንድ ወቅት ለብዙዎች የዋሉ ወገኖች እድሜ፣ ጤና ማጣትና ሌሎች ምክንያቶች ባመጡት ጣጣ የሰው እጅ ለማየት ሲዳረጉ፣ ልጆችና ቤተሰብ የሌላቸው በመሆናቸው ሳቢያ የሚያስታውሳቸው ሲያጡ፣ ያጎረሱ እጆቻቸው ነጥፈውባቸው ለልመና ሲዳረጉ አይዟችሁ የሚሏቸው፣ ቤታቸው ላያቸው ላይ ሲፈርስ ቀና የሚያደርጉላቸው ሲያጡ ለዚያውም በብዛት እየታየ ባለበት በዚህ ዘመን የመረዳዳት እሴቱ አልተሸረሸረም ብሎ የሚያናግር አይደለም።
በችግር ውስጥ ለሚገኝ የቅርብ ቤተሰብም ሆነ ለሌሎች የሚደረጉ ድጋፎች በዘላቂነት ከችግር የማያወጡ በመሆናቸው ሳቢያ ድጋፍ ፈላጊዎች ዛሬ ድጋፍ አግኝተው ተመስጌን ቢሉም ነገ መልሰው ድጋፍ ሊጠይቁ የሚችሉ ናቸው።
ኢትዮጵያውያን ድጋፍ ለማድረግ ፈጥኖ በመድረስ በኩል ብዙም ባይታሙም፣ የሚታሙት ይህን ድጋፋቸውን በተቀናጀና ከተረጂነት ሊያወጣ በሚችል መልኩ አለማድረጋቸው ላይ ነው። ድጋፉ የተቀናጀ አለመሆኑ ችግሩን በዘላቂነት መፍታት ሳያስችል ቆይቷል፤ ይህ ብቻም ሳይሆን ችግሩን ከሕዝብ እና መንግስት አቅም በላይ የሆነ አስመስሎት ከመኖሩም በተጨማሪ እየተወሳሰበና አየገዘፈ እንዲመጣ አርጎታል። ዜጎች በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እየተገኙ በሩቁ እየታየ ያለበት ሁኔታ፣ ድጋፍ የማድረጉ ስራ የመንግስት ተደርጎ የቆየበት ሁኔታም እንዲሁ የመረዳዳት እሴቱን ዳዋ እንዲበላው እያደረገው ይገኛል።
መረዳዳት ብዙ ችግሮችን እንደሚፈታ እየታወቀ ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን በቅጡ ባይታወቅም፣ በመረዳዳት ሊወገዱ የሚችሉ ችግሮች በሀገሪቱ ተንሰራፍተው ይታያሉ። ዛሬ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ባለሀብቶችንና ሌሎች በጎ ፈቃደኞችን በማስተባበር መኖሪያ ቤታቸው ላያቸው ላይ ለወደቀባቸው አቅመ ደካሞችና ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ነዋሪዎች መኖሪያ ቤቶች እየታደሱ እና በአዲስ መልክ እየተገነቡ ያሉበት /ለእዚያም ብዙ ሺ መኖሪያ ቤቶች/ ሁኔታ፣ በብዙ ሺ ለሚቆጠሩ ዜጎች ደግሞ የምገባ መርሀ ግብር መፈጠሩ፣ ወዘተ ሲታሰብ ችግሩን በጋራ መፍታት እንደሚቻል መረዳት ይቻላል፤ ይህ ርብርብ ችግሩ ምን ያህል ሰፊና ምን ያህል ሰፊ ርብርብም እንደሚፈልግ ያመለክታል።
በሀገሪቱ ድጋፍ ሊደረግላቸው የሚገባ ሰዎች አሁን ድጋፍ እየተደረገላቸው የሚገኙና በአይን ሲታዩም ሆነ ሲናገሩ ከሚሰሙት በመነሳት ሊደገፉ የሚገባቸውን ይዘን ብቻ መሆን የለበትም፤ ጸጉራም ውሻ አለ ሲሉት በራብ ይሞታል እንዲሉ በየቤታቸው ሆነው በችግር ውስጥ ተቆራምደው የሚገኙትም ቁጥር ስፍር የላቸውምና ችግሩ ግዙፍ ነው።
በአዲስ አበባና በሌሎች ከተሞች እየተካሄዱ የሚገኙ ድጋፍ የሚፈልጉ አቅመ ደካሞችንና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን የሕብረተሰብ ከፍሎች ለመደገፍ እየተከናወኑ ያሉት ተግባሮች ችግሩ የቱንም ያህል ሰፊ ቢሆን በዚያው ልክ ርብርቡን በማጠናከር በሂደት ችግሩን መፍታት እንዲሁም ለመፍታት የሚያስችል ዘላቂ መፍትሄ ማስቀመጥ እንደሚቻል ያመላክታሉ።
በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በመረዳዳት ግዙፍ የተባሉ ችግሮች እየተፈቱ ያሉበት ሁኔታ በርካቶችን መታደግ እየተቻለ ያለበትን ሁኔታ ከማመላከቱም በላይ ችግሩ ምን ያህል ግዙፍና ለመፍታትም ርብርብ ማድረግ ወሳኝ ስለመሆኑ ሌላ ሰፊ ኃላፊነት የሚወሰድበትም ነው። በመረዳዳት ሊቃለሉ የሚችሉ ችግሮች መንግስትን ወይም የውጭ በጎ አድራጊዎችን እጅ ሲጠብቁ መቆየታቸው ችግሩን ለመፍታት በቁጭት መነሳት እንደሚገባም ያስገነዝባሉ።
መንግስት ሁሉንም ዘርፎች በሚጠበቅበት ልክ ሊደርስ እንደማይችል ይታወቃል። ለቀጣይ ልማት የሚያስፈልጉ ግዙፍ ስራዎች ላይ የተጠመደ እንደመሆኑ አቅመ ደካሞችንና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ዜጎችን ከችግር በማውጣት በኩል በሚፈለገው ልክ ሊሰራ አይችልም። ይህንንም ተገንዝቦ የሕዝቡን፣ የባለሀብቶችን፣ ወዘተ ንቁ ተሳትፎ በመጠየቅ ችግሩን ደረጃ በደረጃ ለመፍታት ወደ መስራት ገብቷል።
አዎን፤ ማንም ቀና አሳቢ ሊገነዘብ እንደሚችለውም መንግስት ካለው ውስን አቅም አኳያ ሲታይ ሁሉንም የሕዝቡን ጥያቄዎች መመለስ አይችልም። መፍታት እየቻለ የሚያቆየው የሚዘነጋው ችግርም አይኖርም፤ ችግሮች ገንግነው እየወጡ ያሉት መንግስት ማድረግ አቅም በማጣቱ ብቻም አይደለም፤ የመንግስት የምንጊዜም አጋር እንደሆኑ የሚታመንባቸው መላው ሕዝብ፣ ባለሀብቶች፣ ወዘተ ይህን ክፍተት ለመድፈን ከተፎ ሆነው ባለመገኘታቸውም ነው።
በበጎ ፈቃድ አገልግሎት እየተመለሱ ያሉትን አይነት ችግሮች መፍታት የሚቻለው ሕዝቡ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት እየተሰማራ በሚያከናውናቸው ተግባሮች ጭምር ነው። ይህንን ደግሞ ባለፉት ጥቂት የለውጡ ዓመታት የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ በተለይ በክረምት ወቅት ባከናወናቸው ተግባሮች የተመዘገቡ ስኬቶች በሚገባ አመላክተዋል። በክረምት ለዚያም በጥቂት ወራት የተከናወኑትና እየተከናወኑ ያሉት የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች ተዳክሞ የነበረውን የኢትዮጵያውያን የመረዳዳት እሴት በእጅጉ እየተነቃቃ እንዲመጣ እያስቻሉት መሆናቸውን እያየን ነው።
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባለፈው ዓመት ብቻ የአቅመ ደካሞችን መኖሪያ ቤቶች በማደስ፣ በአዲስ መልክ በመገንባት እንዲሁም ከከተማዋ መታደስ ጋር በሚራመድ መልኩ ባለ ብዙወለል መኖሪያ ቤቶችን ዘመናዊ መኖሪያ ቤቶችን በመገንባት ለተጠቃሚዎቹ ማስተላለፍ እየታቻለ ያለበት ሁኔታም ይህንኑ በሚገባ ያስገነዝባል።
በከተማ አስተዳደሩ ባለፈው 2015 ዓ.ም ብቻ የተከናወነውን ለእዚህ በአብነት መጥቀስ ይቻላል። በዓመቱ ስድስት ሺ 730 መኖሪያ ቤቶች ተገንብተው ለአቅመ ደካሞችና ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ወገኖች ተላልፈዋል። ይህ አሀዝ እንደ አሀዝ ብቻ ሲታይም በእጅጉ ትልቅ ነው። ከዚያ ባሻገር ደግሞ ምን ያህል አቅመ ደካሞችንና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን የሕብረተሰብ ክፍሎችንና ቤተሰቦቻቸውን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ሲታሰብ ደግሞ ስራው እጅግ እጅግ ግዙፍ መሆኑን ይጠቁማል። በእነዚህ ሁሉ ቤቶች የገባው ደስታና ፈንጠዚያ ሲታሰብ፣ ይህ ሁሉ በመሆኑ በመላ ኢትዮጵያውያን ቤት ጭምር የገባው የደስታ ስሜት ሲታሰብም እንዲሁ በመንግስት አስተባባሪነት፣ በዜጎችና ባለሀብቶች አማካይነት የተከናወነው ይህ ተግባር በእርግጥም ታላቅ ነው።
አስተዳደሩ በበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ አማካይነት የቤት እድሳትና መልሶ ግንባታውን የከተማዋን ገጽታ በሚገነባ መልኩ ወደ መገንባትም ገብቷል። ለእዚህም ባለበርካታ ወለል ሕንጻዎችን በመገንባት ለእነዚህ የኅብረተሰብ ክፍሎች ማስተላለፉን ቀጥሏል። በ2016 የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎትም አስተዳደሩ ባለሀብቶችን በማስተባበር ሶስት ባለዘጠኝ ወለል ሕንጸዎችን ለአቅመ ደካሞችና ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው የከተማዋ ነዋሪዎች እያስገነባ ይገኛል።
ተቀዛቅዞ የቆየውን የኢትዮጵያውያን የመረዳዳት እሴት በእጅጉ እያነቃቃ የመጣው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በተለይ በአዲስ አበባ የአቅመ ደካሞችን መኖሪያ ቤት በማደስ፣ በአዲስ በመገንባት፣ አዳዲስ ዘመናዊ የመኖሪያ ግዙፍ ሕንጻዎችን በመገንባት እየተከናወኑ ያሉ ተግባሮች፣ በበዓል ወቅቶች የሚደረጉ የማእድ ማጋራት ስራዎች፣ የምግባ መርሀ ግብሮችና የመሳሰሉት ተግባሮች ኢትዮጵያውያን የሚያስተባብራቸውና የሚመራቸው ካገኙ ምን ያህል በችግር ላይ የሚገኙ ወገኖችን መታደግ እንደሚችሉ ሁነኛ ማሳያ ሆኖል።
የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ በደም ልገሳ፣ በአካባቢ ጽዳትና ማስዋብ፣ በትራፊክ ማስተናበር፣ ለተማሪዎች የማጠናከሪያ ትምህርት በመስጠትና በመሳሰሉት በአጠቃላይ ከ15 በላይ በሆኑ መርሀ ግብሮች እያበረከተ ያለው አስተዋጽኦም ሲታሰብ የአገልግሎቱ ፋይዳ ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ በማድረግና የመንግስትን ሸክም በማቃለል በኩል ምን ያህል እጅግ ከፍተኛ መሆኑን ያመለክታል።
እንደ መቄዶኒያ፣ አበበች ጎበና ያሉ ግዙፍ ተቋማት በበጎ አድራጎት ተግባር እያከናወኑ የሚገኙት እጅግ ታላቅ ተግባር፣ ለእነዚህ ተቋማት ኅብረተሰቡ በተደራጀም ይሁን በግሉ በበጎ ፈቃድ እያከናወነ ያለው ሰፊ ተግባር እንደሀገር ይበልጥ እየጎለበተ እንዲመጣ የበኩሉን ሚናም ይወጣል። በተለይ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት በሀገሪቱ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እንዲጎለብት በመኖሪያ ቤት እድሳትና በመሳሰሉት ኅብረተሰቡ ዘንድ ወርደው እያከናወኑት ያለው ዘርፈ ብዙ ተግባር በችግር ውስጥ ያሉ ኢትዮጵያውያን ወገንና ሀገር እንዳላቸው በእጅጉ እንዲሰማቸው ያደረገ መሆን ችሏል።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን ለማነቃቃት እየተከናወነ ያለውን ተግባር ተክትሎ እየታዩ ያሉ ውጤቶች፣ ሀገሪቱ በሚገባ ሳትጠቀምበት የኖረችውን ትልቅ የልማት አቅም፣ በቀጣይ በሚገባ በመጠቀም መንግስት ብቻውን በሚፈልገው ልክ ሊደርስባቸው ያልቻላቸውን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ለመፍታት እንዲጠቀምባቸው ያስችላል። በዚህም ዜጎችን በብዙ መልኩ መታደግ የሚችል የኢትዮጵያውያንን የመረዳዳት እሴትን ወደ ቀድሞ ቦታው ለመመለስም ይጠቅማል።
ለበጎ ፈቃዱ አገልግሎቱ እየሰፋ መምጣት በአገልግሎቱ የተሰማሩት ወገኖች ርብርብ ትልቁን ስፍራ ቢይዝም፣ አገልግሎቱ ካሸለበበት እንዲነቃና እንዲስፈነጠር በማድረግ በኩል ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አበቤ እያከናወኑ ያሉት ተግባር ትልቁን ስፍራ ይይዛል።
የአቅመ ደካሞችን የዘመሙ ቤቶች በማፈርስና በአዲስ እንዲገነቡ ስራውን በማስጀመር፣ የግንባታውን ሂደት በመከታተል፣ ግንባታው ሲጠናቀቅም ቁልፍ በመስጠትና ቤቶቹን በማስረከብ፣ ቤቶቹን ያገኙ ነዋሪዎችን የደስታ ስሜት ያዳመጡት እነዚህ መሪዎች ይህ ስራ ሳያሰልስ እንዲከናወን እንዲሁም ስራው የመላ ኢትዮጵያውያን እንዲሆን በማድረግ ላይም ይገኛሉ። ይህን ስራ ባለሀብቶች በስፋት እንዲቀላቀሉት ማድረግ ተችሏል። መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ ወጣቶች፣ ወዘተ የስራቸው አካል ጭምር እስከ ማድረግ ደርሰዋል።
ዛሬ ቤት ማደስ ላይ ብቻ አይደለም እየተሰራ ያለው። ግንባታው ከፍ እንዲል እየተደረገ ነው። ባለበርካታ ወለል ሕንጻዎችን ወደ መገንባት እስከ መሸጋገር ደርሷል። ለእዚህም በአሁኑ ወቅት በአዋሬና በልደታ የተገነቡና እየተገኑቡ ያሉት ባለብዙ ወለል መኖሪያ ቤቶች ለእዚህ በአብነት ይጠቀሳሉ። የቤቶች እድሳትና ግንባታው የማያመላልስ፣ የከተማዋን ገጽታ በሚገነባ መልኩ ወደ መካሄድ እየተሸጋገረ ይገኛል፤ ይህም ትልቅ እምርታ ሊባል ይችላል።
ዘካርያስ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 2 ቀን 2016 ዓ.ም