አረንጓዴ ዐሻራ- የትውልድ አደራ

ከዛሬ 400 ዓመት በፊት የኢትዮጵያ የደን ሽፋን 40 በመቶ እንደነበርና በተለያዩ ሰው ሠራሽና ተፍጥሯዊ ችግሮች ምክንያት ይህ አሃዝ እስከ ሶስት በመቶ ወርዶ እንደነበር መረጃዎች ያመላክታሉ። ይህ በኢትዮጵያ የተስተዋለው የደን ሽፈን መቀነስ በአንዳንድ የዓለማችን ሀገሮችም ተመሳሳይነት ያለው በመሆኑ ለአየር ንብረት ለውጥ ዐቢይ ምክንያት ሆኗል። ዓለምን ከተጋረጠባት አደጋ ለማዳን ሀገራት ትኩረት ሰጥተው ከሚተገብሩት ጉዳይ አንዱ የደን ሽፋንን ማሳደግ በመሆኑ ኢትዮጵያም ለደን ሀብቷ ትኩረት በመስጠት አሽቆልቁሎ የነበረውን የደን ሽፋኗን እያሳደገች ትገኛለች። በተለይም የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ-ግብርን ከጀመረች ወዲህ የደን ሀብቷ ከዓመት ወደ ዓመት እየጨመረ መምጣቱ በተጨባጭ የሚታይ ሀቅ ነው።

በመጀመሪያው ምዕራፍ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ- ግብር በ2011 ዓ.ም ክረምት ወቅት አንድ ሰው 40 ችግኞችን ይተክላል በሚል ስሌት በድምሩ አራት ቢሊየን ችግኞችን ለመትከል እቅድ ተይዞ ነበር ወደ ሥራ የተገባው። ይህም እቅድ እንዲሁ አልቀረም። ይልቁንም ከታሰበው በላይ ተሳክቷል።

ሐምሌ 22 ቀን 2011 ዓ.ም በአንድ ጀምበር 200 ሚሊየን ችግኞችን የመትከል ዕቅድ ግቡን አልፎ በቀን 354 ሚሊየን ገደማ ችግኞች መተከላቸውን በወቅቱ የሚመለከታቸው የሥራ ኃላፊዎች ገፀዋል። በዚህም ወቅት 20 ሚሊየን ኢትዮጵያውያን በአረንጓዴ ዐሻራ ታሪክ የሚዘክረውን ሥራ ሠርተዋል።

ይህ ጥረትም ውጤት እያፈራ ስለመሆኑ አሃዛዊ መረጃዎች ፍንትው አድርገው ያሳያሉ። መረጃዎች እንደሚያመለክቱት የኢትዮጵያ የደን ሽፋን ከነበረበት 17 ከመቶ ወደ 20 በመቶ አድጓል። ይህ አሃዝ በየጊዜው እያደገ ስለመሄዱም በየዓመቱ የሚከናወኑ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብሮች ጠቋሚ ናቸው።

እኔም እንደ ዜጋ ይህ መርሐ ግብር ይመለከተኛል። የእኔ ብቻ ሳይሆን የቤተሰቤ ጉዳይ፤ የትውልድ አደራ እንደሆነ እገነዘባለሁ። እኔ ይህን የአረንጓዴ መርሐ ግብር የምደግፈውና ከልቤ የምሳተፈውም ስለተባለ እና ስለተነገረ ብቻ ሳይሆን የእኔን እና የቤተሰቦቼን ነገ የሚወስን በመሆኑ፤ ለምለም፤ ነፋሻ አየር እና ለኑሮ ተስማሚ የሆነች ኢትዮጵያን ለመጪው ትውልድ ለማስረከብ ካለኝ ልባዊ መሻት ነው።

በእኔ ግንዛቤ ችግኞች በልጅ ይመሰላሉ። እንክብካቤና ክትትል ያስፈልጋቸዋል። ባላፉት ዓመታት የተከልኳቸው ችግኞች ፈክተውና ለምተው ስመለከታቸው ልፋቴ መና አልቀረም እላለሁ። ችግኞቹ ዘንበል ባሉ ቁጥር ያሳሱኛል፤ ውሃ በጠማቸው ቁጥር እኔም ይጠማኛል። በፀሐይ ሲጠወልጉ ሳይ እኔም ከእነርሱ ቀድሜ እዝላለሁ። በልቤ ውስጥ ልጆቼ እና ቤተሰቦቹ እንዳሉ ሁሉ የነገ ተስፋችንን የሚያለመልሙ ችግኞችም አሉ። እንግዲህ መልካም ሕይወት በለምለም ነገሮች ይመሰላል። እኔም ቤተሰቤም ለምለም የሆነ ነገር እንመኛለን፤ ለም የሆነች ኢትዮጵያን ለትውልድ ለማስተላለፍም እንተጋለን- የትውልድ አደራ አለብንና።

ባለፉት አራት ዓመታት የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ትግበራ ማኅበረሰቡ የችግኝ ተከላና እንክብካቤ ባህልን አዳብሯል። መርሃ- ግብሩ መልከ-ብዙ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትሩፋትም አስገኝቷል። እንደ መንግሥት እቅድና የረጅም ጊዜ ትልም አረንጓዴ ዐሻራ ብዙ ነገሮችን ያቀፈ ነው። የተተከሉ ችግኞችን በቴክኖሎጂ መከታተል የሚያስችል የአሠራር ሥርዓት ተዘርግቶ ክትትል ይደረጋል።

እንግዲህ በዚህ ውስጥ የረጅም ጊዜ ሕልም አለ። በዚህ ውስጥ ዘመናትን የሚያሻግር ሃሳብ እና ውጥን አለ። በዚህ እቅድ ውስጥ ነገን መመልከት አለ፡፡

የነገዋ ኢትዮጵያዬ የፈካችና የለመለመች፤ የልጆቼ ወይም የመጪው ትውልድ መኖሪያ እንድትሆን እሻለሁ። በልጆቼ ውስጥ ነገን አሻግሬ አያለሁ። በመሆኑም ለነገ የሚሆን ስንቅ ከወዲሁ መሰነቅ፤ መሰነድ፤ መትከል፤ ማረም፤ መኮትኮት እንዳለብኝ እገነዘባለሁ። ልጆቼ የእኔ የትናንት፣ ዛሬ እና የነገ ነፀብራቆቼ ናቸው፡፡

አንድ ፀሐፊ በማህበራዊ ድረ ገጽ ላይ እንዳስቀመጡት፤ የችግኝ ጣቢያዎች ብዛት፣ ደረጃ፣ ጥራትና አቅም በየጊዜው እያደገ ነው። ከትሩፋታቸው መካከል አረንጓዴ የአኗኗር ዘይቤን መፍጠራቸው፤ የደን

ጭፍጨፋ ምጣኔን በበዙ እንዲቀንስ ማስቻላቸው፣ ወጣቶችና ሴቶችን ጨምሮ ለብዙዎች የገቢ ምንጭና የሥራ ዕድል መፍጠራቸው፤ የተራቆቱ አካባቢዎችና ተፋሰሶች እንዲያገግሙ ማስቻላቸው ይጠቀሳሉ።

ባገገሙ ተፋሰሶችም በርካታ አርሶ እና አርብቶ አደሮች በንብ ማነብና እንስሳት መኖ ልማት ዙሪያ በመሳተፍ ተጨማሪ ገቢ እንዲያገኙ እና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸውን እያረጋገጡ ነው። ለአብነትም የተተከሉ የአቮካዶ ችግኞች ለፍሬ መብቃታቸውን ተከትሎ ለውጭ ገበያ እንዲቀርቡ በመደረጉ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ሁለተኛዋ አቮካዶ አምራች እንድትሆንም ዕድል ከፍቷል።

የአረንጓዴ ዐሻራ የሀገራችንን የዛሬንም ሆነ የነገ ዕጣ ፈንታ የሚወስን፣ ጊዜውን የሚዋጅ ተግባር ነው። ኢትዮጵያ በተፈጥሮ የተቸረችው አየር ንብረትና መልክዓ- ምድር ለዚህ የሚጋብዝ ነው። ደን ልማት ዘላቂ ሥራ መሆን አለበት። ባለቤትነት እንዲጨምርም በወል መሬት ብቻ ሳይሆን በግል ይዞታም አረንጓዴ ዐሻራ መተግበር አለበት። የደን ልማት አካል የሆነው አረንጓዴ ዐሻራ ሀገራዊ ፋይዳው ሁለንተናዊ ነው። ሀገራዊ ፋይዳው ባለፈ ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ በረከቶችን ተሸክሟል። የደን ልማት የቅንጦት ሳይሆን የሕልውና ጉዳይ ነው የሚያሰኘውም ለዚህ ነው።

ይህን ደግሞ ሰፊ ጉልበት ያለውን ሕብረተሰብ በዘመቻ መልክ አስተባብሮ ገቢራዊ ማድረግ ይጠበቃል። እኔ ነገ ለልጆቼ ቅርስ ነው የምላቸው፤ ታሪክ ነው ብዬ የማወሳቸው፤ ሕልውናዬ ነው ብዬ የማወጋቸው ነው- የአረንጓዴ አሻራ። በታሪክ ውስጥ ሀገሬ የምትታወስበት፤ ልጆቼ የሚነግሱበት፤ እኔም አንገቴን ቀና አድርጌ በልበ ምልዑነት የምናገርበት የቤተሰቤ ታሪክ ነው። በመሆኑም እኔም፤ እናንተም በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ-ግብሩ ደማቅ ታሪካችንን መጻፍ ያለብን ዛሬ ነው።

አረንጓዴ ዐሻራ ለእያንዳንዱ ሰው የመኖር ዋስትና የሚሰጥና ሀገራዊ ሕልውናን የሚያረጋገጥ እንጂ ፖለቲካዊ ትርጉም ያለው አይደለም። በዚህ የ2016 ዓ.ም የክረምት ወራት እንደ ሀገር 7ነጥብ9 ቢሊዮን ችግኞችን የመትከል ውጥን ተይዟል። በዚህ ውስጥ የእኔ ድርሻ ምን መሆን አለበት ብሎ ለምላሹ መዘጋጀት ደግሞ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ዜጋ ሀገራዊ ኃላፊነት ሊሆን ይገባል።

ክፍለዮሐንስ አንበርብር

አዲስ ዘመን ሐምሌ 2 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You