ሴቶችን ከጥቃት ነጻ የሚያደርገው የ”ዜሮ ፕላን” ማዕከል

ከጥቂት ዓመታት በፊት የዲላ ዩኒቨርሲቲ ያቋቋመውን የ“ዜሮ ፕላን” ማዕከል ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ጎብኝተው ልምድ ይወስዱ ዘንድ እንደጠራቸው ወይዘሮ መሰረት አስራት ያስታውሳሉ። እርሳቸውም በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የሴቶች፣ ሕጻናት፣ ወጣቶችና ኤች.አይቪ/ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር ዳይሬክተር እንደመሆናቸው በወቅቱ ከልምዱ ሊቀምሩ በዲላ ዩኒቨርሲቲ መገኘታቸውን ይገልጻሉ።

ዲላ ዩኒቨርሲቲ ባዘጋጀው መድረክ የተገኙት ወይዘሮ መሰረት፣ የዲላ ዩኒቨርሲቲን ጉብኝት በአግባቡ ካጣጣሙ በኋላ ማዕከሉ በምን ዙሪያ እንደሚሰራ ተረድተዋል። እርሳቸውም “የእኛ ዩኒቨርሲቲ ደግሞ ይህን ማእከል በተሻለ ሁኔታ መሰራት አለበት” በሚል ተነሳሽነት ወደዩኒቨርሲቲያቸው ይመለሳሉ።

በዲላ ዩኒቨርሲቲ መድረክ ላይ የተገኙት ሁሉም የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች የሴቶች፣ ሕጻናት፣ ወጣቶችና ኤች.አይቪ/ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር ዳይሬክተሮች መሆናቸውን የሚያስታውሱት ወይዘሮ መሰረት፣ “እዛ ተገኝቼ ልምድ ከቀሰምኩ በኋላ በቀጥታ ወደ ዩኒቨርሲቲዬ ተመልሼ ምን ባደርግ ይሻላል ስል ከራሴ ጋር ሞገትኩ። የራሴን ስራ ለመስራትም ተነሳሳሁ፤ እንዲያውም ካየሁት በላይ አሻሽዬ ለመስራትም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር መከርኩ፤ ከተማሪዎች ኅብረት ጋርም ተነጋገርኩ፡፡” ሲሉ ያብራራሉ።

በእርግጥ ዳይሬክቶሬቱ የሚሰራው በ”ዜሮ ፕላን” ማዕከል ላይ ብቻ አይደለም፤ ስራው ዘርፈ ብዙ ነው። የሴት መምህራንን አቅም ከመገንባት እስከ ሴት ተማሪዎች፣ ሴት የአስተዳደር ሰራተኞች ጭምር ድጋፍ እስከመስጠት በመስራት ላይ መሆኑን ይገልጻሉ። ማእከሉ በተለይ በአሁኑ ወቅት ለሴት ተማሪዎች ትልቅ እፎይታን ማጎናጸፉንም ያስረዳሉ፡፡

ዘርፉ በተለይ ሴት ተማሪዎች ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራ ዳይሬክተሯ ጠቅሰው፣ ዳይሬክቶሬቱ ዘርፈ ብዙ ስራዎችን እንደሚሰራ፣ የማይነካካቸው ስራዎች እንደሌሉም አክለው ይገልጻሉ። አብነት ጠቅሰው ሲያብራሩ እንዳሉት፤ የሴቶችን ተሳትፎ ከማሳደግ አንጻር የሴት ተመራማሪዎች ብቻ የሚሰሯቸው የምርምር ስራዎች አሉ። እነዚህን መሰል በቅጥር ግቢው ውስጥ ለሚሰሩ ስራዎች ዳይሬክቶሬቱ ድጋፍ ያደርጋል። በጋራ ሆኖም ይሰራል፡፡

ሴት ተማሪዎች ላይ ትኩረት ተደርጎ ከሚሰራው ስራ ውስጥ አንዱ (አንዳንዴ ወንዶችንም ያካትታል) የኢኮኖሚ ችግር ላለባቸው ተማሪዎች ድጋፍ ማድረጉ ነው። በተለይ ሴት ተማሪዎች በኢኮኖሚ ችግር ምክንያት ዩኒቨርሲቲውን ለቅቀው እንዳይወጡ እንደ ፋይናንስ ያሉ መሰረታዊ ድጋፎችን ይደረጋል። ይህ የፋይናንስ ድጋፍ የሚደረገው በዳይሬክቶሬቱ አነሳሽነት ስፖንሰር አድራጊዎች ተፈልገው ነው። ለአብነት ያህልም በዚህ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ለ570 ተማሪዎች (ወንዶችንም ይጨምራል) ድጋፍ ተደርጓል።

ዳይሬክቶሬቱ የሚያደርግላቸው የገንዘብ ድጋፍ ብቻ አይደለም፤ የስነ ልቦና ችግር ላለባቸው ተማሪዎችም የማማከር ስራ ይሰራል። ለዚህ ተብሎ የተከፈተ ቢሮ በመኖሩም በዚያም ችግር ያጋጠማቸውን ተማሪዎች ያወያያል። ከእርሱ በላይ ሲሆን ደግሞ የዩኒቨርሲቲው የሳይኮሎጂ ትምህርት ክፍል በመኖሩ ከትምህርት ክፍሉም ጋር በትስስር ይሰራል። የስነ ልቦናው ችግር ከዚያም ትምህርት ክፍል ገዘፍ የሚል ከሆነ ደግሞ ሆስፒታል ድረስ በመሄድ መፍትሔ እንደሚበጅ ዳይሬክተሯ ተናግረዋል፡፡

ዳይሬክቶሬቱ ድጋፍ የሚያደርግላቸው ለ570 ተማሪዎች የገንዘብ ብቻ አይደለም። በተለይ ለሴት ተማሪዎች የንጽሕና መጠበቂያ ያቀርባል። ድጋፉ በዚህም ሳይገታ ለሴት ተማሪዎች የሚያስፈልገው እንደ ቅባት፣ ለትምህርታቸው የሚያስፈልጉ ቁሳቁስና ሌሎች ድጋፎችንም ያደርጋል። ለዚህ አይነት እርዳታ በተለይ መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ድጋፍ እንደሚጠይቅና ከእነርሱም ጋር እንደሚሰራ ወይዘሮ መሰረት ይናገራሉ።

ወይዘሮ መሰረት፣ “ሴቶች በግቢያችን ውስጥ በነጻነት እንዲወያዩና ሐሳባቸውን እንዲገልጹ የሚያስችላቸው ‘ዜሮ ፕላን’ የሚባል ማዕከል ተቋቁሟል ሲሉ ጠቅሰው፣ ዜሮ ፕላን ሲባል ሴት ተማሪዎች ላይ የሚደርሰውን የትኛውንም ተጽዕኖ ዜሮ ለማድረግ መስራት ማለት ነው” ይላሉ። ዜሮ መደረግ አለባቸው ተብለው ከሚሰሩ ስራዎች መካከልም አብነት ጠቅሰው ሲያብራሩ እንዳሉትም፤ አንዱ ጾታዊ ትንኮሳ ነው። በሴት ተማሪዎች ላይ የሚደርሰው ጾታዊ ትንኮሳ እንዳይኖር ወይም ዜሮ እንዲሆን ለማድረግ የሚሰራበት እቅድ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ኤች.አይ.ቪ/ኤድስን በመከላከልና ስርጭቱን በመግታት ረገድ ስራዎች ተሰርተው ምንም አይነት ችግር እንዳይኖር ለማድረግ የታቀደ ስራ ነው።

የ”ዜሮ ፕላን” ስራ በዚህ ብቻ የሚገታ አይደለም የሚሉት ዳይሬክተሯ፣ ሴት ተማሪዎች ከዩኒቨርሲቲ የመባረር እጣ ፈንታ እንዳያጋጥማቸው በጥብቅ እንደሚሰራም ተናግረዋል። በተለይም ሴት ተማሪዎች ትንኮሳ ተካሒዶባቸው ሊያጋጥማቸው የሚችል ያልተፈለገ እርግዝና እንዳይከሰትባቸው በጥብቅ እንደሚሰራም አመልክተዋል።

እንደ እሳቸው ማብራሪያ፤ ማዕከሉ ለሴት ተማሪዎች ዘርፈ ብዙ አገልግሎት የሚሰጥ እንዲሆን ታልሞ የተሰራ ነው። ለምሳሌ አብዛኛውን ጊዜ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የልደት ቀንን ለማክበር ከቅጥር ግቢው ውጭ ይወጣሉ። ከግቢው ውጭ የመውጣታቸው ምስጢር ልደት ለማክበር ቢሆንም፤ ከልደት ቀን በስተጀርባ የሚፈጸሙ ሌሎች አላስፈላጊ ድርጊቶች አሉ። ምንም እንኳን ተማሪዎቹ ከግቢው የወጡት ልደታቸውን ብቻ ለማክበር ቢሆንም፣ በሌሎች ወጥመዶች ውስጥ ሳያውቁ ሊገቡ ይችላሉ፡፡

ስለዚህ የልደት ቀንን ለማክበር ሲባል ከግቢው እንዳይወጡ ለማድረግ የልደት ቀናቸውን ሊያከብሩ የሚችሉበት ቦታ ማመቻቸት አንዱ መፍትሔ ነው በሚል ስራዎች መስራታቸውን ዳይሬክተሯ ገልጸዋል። ይህን ተከትሎ ክፍል የተዘጋጀላቸው ሲሆን፣ የልደት ቀኗን ለማክበር ፍላጎት ያላት ተማሪ ያለምንም ችግር በተዘጋጀው ክፍል ውስጥ ማክበር እንድትችል መደረጉን ያስረዳሉ።

በአሁኑ ሰዓት በጣም ጥሩ የሆነው ነገር ማዕከሉ መኖሪያ ቤት እየመሰላቸው እስከመምጣት ደርሷል። አገልግሎቱ ከማወያያ፣ የልደት ቀን ከማክበሪያም በላይ ከፍ ብሎ ማጥኛም ጭምር እየሆነ ነው። ተግባረ ብዙ ማዕከል መሆኑን ለመረዳት ሌሊት ላይ ተማሪዎች እያጠኑበት መቆየቱም አንዱ ማሳያ ነው። ተማሪዎቹ በዩኒቨርሲቲው ማደሪያ ክፍላቸውና በቤተ መጻሐፍት ውስጥ ከሚያሳልፉ ይልቅ በማዕከሉ በነጻነት እየተነጋገሩ እና እየተወያዩ እውቀታቸውን ማዳበር እየመረጡ ነው። የቤት ያህል ቅልል ስለሚላቸው ለሌቱን ሙሉ ያነቡበታል። ከዚህም የተነሳ የማጥኛ ቦታቸው ሆኗል ማለት ይቻላል።

ይህ የማዕከሉ አገልግሎት እንደተጠበቀ ሆኖ በየአስራ አምስት ቀኑ ግን መደበኛ የሆነ አገልግሎት ይሰጣል። ለምሳሌ ሴቶች ይመካከሩበታል፤ ይወያዩበታል፤ ስልጠናም ይወስዱበታል። ለአብነት ያህል ችግራቸውን በግልጽ በመወያየት ወደ መፍትሔ ለመምጣት ይጠቀሙበታል። ከመማር ማስተማሩ ጋር ተያይዞ ያጋጠማቸው እክል ካለም በጉዳዩ ዙሪያ መክረው መፍትሔ ለማበጀት ይተጋሉ።

ወይዘሮ መሰረት፣ “በግቢያችን ያለው የተማሪዎች ኅብረት የጠነከረ ነው” ይላሉ። በሴት ተማሪዎች ኅብረት ፕሬዚዳንት መሪነት ሁሌም የመወያያ ርዕስ እየተዘጋጀ ውይይት እንደሚደረግም ያመለክታሉ። በዚህ ውይይት ውስጥ የሚገኘው ዘርፈ ብዙ ጥቅም እንዳለ ሆኖ ሴቶቹ ሰው ፊት ቀርበው እንዴት ንግግር ማድረግ እንደሚችሉና የሐሳብ ፍሰትን እንደሚጠብቁ የሚለማመዱበት መድረክም ነው ሲሉ ያብራራሉ።

እርሳቸው እንደሚሉት “የዜሮ ፕላን” ማዕከል የተቋቋመው ከዲላ ዩኒቨርሲቲ ልምድ ከተቀሰመ በኋላ በ2014 ዓ.ም ነው። ግንባታው ተጠናቅቆ ሙሉ በሙሉ ወደስራ የገባው ደግሞ በ2015 ዓ.ም ነው። ዩኒቨርሲቲዎች የራሳቸው የሆኑ መመሪያዎች አሏቸው። ይህን መመሪያ በመከተል ስራ ለመስራት ደግሞ ቅድመ ሁኔታዎች አስፈላጊ ነበሩና ያንን ቅድመ ሁኔታ የማመቻቸቱ ተግባር ሲፈጸም ቆይቷል፤ አንዱ መመሪያም የ”ዜሮ ፕላን” ማዕከል ነው።

በዚህም ምክንያት በማዕከል መፍትሔ ሊያገኝ የሚችል ልክ እንደ ጾታዊ ትንኮሳ አይነት ችግር በምን አግባብ ሊፈታ እንደሚችል በመመሪያው ተቀምጧል የሚሉት ዳይሬክተሯ፣ ያንን መመሪያ በማዕከሉ ለሚሰበሰቡ ሴት ተማሪዎች ማስገንዘብ አንዱ ተግባር ነው ይላሉ። ለተማሪዎቹ የሚደረገው ገለጻ እና ማወያየት ተማሪዎቹ እውቀታቸው እንዲጨምር ያደርጋቸዋል። ስለዚህም ጾታዊ ትንኮሳ በሚያጋጥማቸው ጊዜ ወዴት መሔድ እና ለማን ጉዳዩን መናገር እንዳለባቸው ግንዛቤው ይኖራቸዋል ሲሉ ያመለክታሉ።

አንዳንድ ጊዜ ሴት ተማሪዎች የደረሰባቸውን ጥቃት መግለጽም ሆነ ማሳወቅ ላይፈልጉ ይችላሉ የሚሉት ዳይሬክተሯ፣ ለዚህ ምክንያታቸው ደግሞ ጉዳያቸውን አሳልፈው ቢያወሩ የሚመጣ መፍትሔ የማይኖር ስለሚመስላቸው ይሆናል ይላሉ። በደላቸውን በሆዳቸው ይዘው መፍትሔ ለሌለው ነገር ለማንም አልናገርም በሚል ከነችግራቸው ሲቀመጡ ደግሞ ችግሩ እየከፋ በትምህርታቸውም ወደኋላ እየቀሩ እንዲሄዱ ሊያደርጋቸው እንደሚችልም ተናግረዋል።

እሳቸው እንዳሉት፤ ማእከሉ እውን ከሆነ በኋላ ግን በዚህ ዙሪያ ዩኒቨርሲቲው ግልጽ መመሪያ ስላስቀመጠ ጾታዊ ትንኮሳ ቢደርስባቸው ዩኒቨርሲቲው ይቆማል። እንደዚያ አይነት ችግር በሚያጋጥማቸው ጊዜም ዩኒቨርሲቲው የራሱ ዲስፒሊን ያለው እንደመሆኑ በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ያለው የዲስፒሊን ኮሚቴ መፍትሔ ይሰጣል።

የዩኒቨርሲቲው የ”ዜሮ ፕላን” ማዕከል የተለያየ አገልግሎት መስጠት ከሚያስችሉት 11 ክፍሎች በተጨማሪ ስልጠና የሚሰጥበት ሰፋ ያለ ሌላ ክፍልም አለው። ማዕከሉ የራሱ ተጠሪ ያለው ነው። በማዕከሉ ሁሉም ሴት ተማሪዎች ሊጠቀሙበት ይችላሉ። ለሴት ተማሪዎች የተለያየ አገልግሎት መስጠት የሚችል እንደሆነና ሁሉም ሴት ተማሪዎች መጥተው ሊገለገሉበት እንደሚችሉ በተገኘው መድረክ ሁሉ የማስገንዘብ ስራ እንደሚሰራም ዳይሬክተሯ ሁሌም ከመናገር አለመቆጠባቸውን አስረድተዋል።

እርሳቸው እንደሚሉትም፤ ምንም እንኳ የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ በ2015 ዓ.ም “ዜሮ ፕላን” ማዕከልን የሴት ተማሪዎችን ጥቃት “ዜሮ” ማድረግ ነው በሚል መርህ ስራ ቢያስጀምርም፣ በአሁኑ ወቅት ግን ምን ያህል ውጤት ተመዘገበ የሚለውን ለመለየት የዳሰሳ ጥናት ማድረግ እንደሚጠይቅ ዳይሬክተሯ ተናግረዋል።

አንድ በግልጽ መናገር የሚቻለው ነገር ሴት ተማሪዎች ሙሉ አቅማቸውን ተጠቅመው በማዕከሉ ማጥናታቸውና በሚያጋጥሟቸው ችግሮች ላይ በመወያየት ችግሮቹን ለመፍታት እርስ በእርስ መረዳዳት መቻላቸው የማእከሉ ውጤት ተብሎ ሊወሰድ እንደሚችል ጠቅሰዋል። ይህ ብቻ ሳይሆን በማዕከሉ በመገኘት ስለሚያጠኑም ለትንኮሳ የሚጋለጡበትን እድል እየዘጉም ጭምር መሆናቸውም ሌላው ማእከሉ ያስገኘው ጥቅም መሆኑን ተናግረው፣ ማዕከሉ ሌሊቱን ሁሉ ሴቶቹ እያጠኑበት የሚቆዩበት መሆኑም ሌላው ያስገኘው ጥቅም ነው ብለዋል።

ዳይሬክተሯ እንደሚሉት፤ ማዕከሉ ሲገነባ የራሱ የሆነ ዓላማ ሰንቆ ቢሆንም፣ አሁን ላይ ዘርፈ ብዙ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል። አስቀድሞ የታሰበው በየ15 ቀኑ ሴት ተማሪዎችን ማወያየት እና ስልጠና መስጠት ቢሆንም፣ ከዚያ ያለፈ ፋይዳ እንዳለው ማወቅ ችሏል።

አስቴር ኤልያስ

አዲስ ዘመን ሐምሌ 2/2016 ዓ.ም

Recommended For You