ባለሀብቶችን የሚገቱ የቢሮክራሲ ማነቆዎች

የኢትዮጵያ መንግሥት የውጭ አገር ባለሀብቶችን ለመሳብ በብዙ መንገድ ጥረቱን ቀጥሏል፡፡ ወሳኝ የሆኑ ሕጎችንም ከማርቀቅ እስከማጸደቅ ደርሷል፡፡

በተለይም ባለሀብቶቹ ከፋይናንስ ዘርፉ ጀምሮ እስከ ተለያዩ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ላይ ተሰማርተው ውጤት እንዲያስመዘግቡ በተቻለው ፍጥነት ሁሉ በመጓዝ ላይ ይገኛል፡፡ ይህ ሁሉ የመንገድ ጥርጊያ፤ የውጭ አገር ባለሀብቶችን ብቻ በመሳብ ለማሽሞንሞን ሳይሆን ለአገር ውስጥ ባለሀብቱም ምቹ የስራ መደላድል ለመፍጠርና አገሪቱም ከዘርፉ መጠቀም እንድትችል ታስቦ መሆኑ ይታመናል፡፡

መንግስት፣ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚው ፈጣን እድገት እንዲያስመዘግብ አቅዶ ከፍተኛ እንቅስቃሴ እያደረገ ባለበት በዚህ ጊዜ፤ እቅዱ ግቡን እንዳይመታ የሚያደርጉ አሰራሮች ግን አይጠፉም፡፡ አንድ አገልግሎት ፈላጊ ኢንቬስተር አገልግሎት ወደሚሰጡ ተቋማት በሚሔድበት ወቅት የሚያጋጥመው የሚያረካ፣ የሚያማርር አሊያም መካከለኛ የሆነ መስተንግዶ ሊሆን እንደሚችል ይታሰባል፡፡

በኢትዮጵያ በአብዛኛው የሚንጸባረቀው ከውስን ተቋማት በስተቀር አብዛኞቹ አገልግሎት አሰጣጣቸው የተጓተተና የሚያማርር እንደሆነ የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ መንግስት በብዙ ጥረትና ማግባባት ጥሪ እያደረገ ወደአገር ውስጥ ገብተው እንዲያለሙ የሚጋብዛቸው ባለሀብቶችን በአግባቡና በመልካም መስተንግዶ በመቀበል ለጥያቄያቸው ተገቢ ምላሽ መስጠት ካልተቻለ ደግሞ የሚፈለገው የኢኮኖሚ እድገት እንደሚቀጭጭ ይታመናል፡፡ ስለዚህም አገልግሎት አሰጣጡ ቀልጣፋና ግልጽ መሆን አማራጭ ሳይሆን የግድ እንደሚል ይነገራሉ፡ ፡

አገልግሎት የሚሰጡ ጥቂት የማይባሉ ተቋማት ግን ይህን ሲያደርጉ አይስተዋልም፡፡ ይልቁኑ ቢሮክራሲያዊ አሰራርን በማንሻፈፍ ባለሀብቱ እንዲማረር በማድረጉ በኩል የተካኑ ስለመሆናቸው ትችት ይሰነዘርባቸዋል፡፡ ለመሆኑ ቢሮክራሲ ሲባል ምን ማለት ነው? ተቋማት ለደንበኞቻቸው የሚሰጡት አገልግሎት ቢሮክራሲያዊ ማነቆዎች የበዛበት ነው ማለትስ ምን ማለት ነው? መገለጫውና መፍትሔ ምንድን ነው? ስንል ለዘርፉ ቅርበት ያላቸውን ምሁራን አነጋግረናል፡፡ ካነገጋገርናቸው ምሁራን መካከል በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የሶሻል ሳይንስና ሂዩማኒቲ ኮሌጅ መምህር ዓለምሰገድ ደበሌ (ዶ/ር) አንዱ ናቸው፡፡

እርሳቸው እንደሚሉት፤ ቢሮክራሲ ሲባል በመጀመሪያ የስራ ክፍፍልን መሰረት ያደረገ፣ ውሳኔ መስጠትንና አገልግሎት መስጠትን የሚያመለክት ነው፡፡ ቢሮክራሲ ትርጉሙ አዎንታዊ የሆነ ነው፡፡ ነገር ግን በጊዜ ሒደት አሉታዊ ትርጉም እንዲኖረው ያደረገው የስራ መንዛዛቱ ነው፡፡ በስራ ሒደቱ ላይ እክሎች ሲመጡ አሉታዊ የሆነ ትርጉም እንዲኖረው አድርጎታል፡፡

ሌላው ያነጋገርናቸው በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ በስነ ዜጋና ስነ ምግባር ትምህርት ክፍል የመልካም አስተዳደርና ልማት መምህር አዳፍረው አዳነ ናቸው፡፡ እርሳቸውም፤ ቢሮክራሲ የሚለው ቃል በስርዓት የተዋቀረ፣ በልዩ ቦታ የሚተገበር፣ የተዋረድ የአስተዳደር ስርዓት እና የኃላፊነት እርከንን ያመለክታል ይላሉ፡፡ ግሪካዊው ፈላስፋ “አርስቶትል”ን ጠቅሰው እንደተናገሩትም፤ ቢሮክራሲ የተሳለጠ አስተዳደራዊና ማህበራዊ ስርዓትን እንዲሁም ፍትህን ለማስጠበቅ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን ያስረዳሉ።

አሁን ባለንበት ዘመን ቢሮክራሲ በሁሉም ቦታዎች የሚገኝ የዘመናዊው ማህበረሰብ አካል ነው የሚሉት መምህር አዳፍረው፣ የመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ኮርፖሬሽኖችና ሌሎች ድርጅቶች በቢሮክራሲያዊ መዋቅሮች ላይ በመመስረት እየሰሩ እንደሚገኙም ይናገራሉ፡፡ ቢሮክራሲ እየተባለ የሚጠራው ጉዳይ ብዙ ጊዜ በቀርፋፋነት ወይም ቀልጣፋ አለመሆን እና በውጤታማነት ማነስ ትችት የሚሰነዘርበት ቢሆንም የዘመናዊ አስተዳደር መሰረታዊ ገጽታ ሆኖ መቀጠሉን አስረድተዋል፡፡

መምህሩ፣ የዘርፉ ተመራማሪ የሆኑትን ማክስ ዌበርን ጠቅሰው እንደገለጹት፤ የቢሮክራሲ ፅንሰ[1]ሀሳብ ተዋረዳዊ መዋቅርን፣ በግልጽ የተለዩ ሚናዎችንና ኃላፊነቶችን፣ መደበኛ ህጎችንና ሂደቶችን እንዲሁም ግላዊ ያልሆኑ ግንኙነቶችንና መስተጋብሮችን ያካትታል። ፖለቲካና ወቅታዊ ወቅታዊ ትንታኔ ገጽ 8 አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሐምሌ 2 ቀን 2016 ዓ.ም ባለሀብቶችን የሚገቱ የቢሮክራሲ ማነቆዎች ዓለምሰገድ (ዶ/ር) እንደሚሉት ደግሞ፤ በኢትዮጵያ የቢሮክራሲ ማነቆዎች አሉ፡ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ በእድገት ላይ ያለች አገር ናት፡፡

ለዚህ እድገቷ ደግሞ የአገር ውስጥ ኢንቨስትመንት ወሳኝ እንደሆነው ሁሉ የውጭ ኢንቨስትመንትም ወሳኙ ጉዳይ ነው፡፡ በተለይ የውጭ ኢንቨስትመንት፤ የውጭ ምንዛሬን በማምጣቱም ሆነ የስራ እድል በመፍጠሩ ረገድ የራሱ ድርሻ ያለው ነው፡ ፡ ኢትዮጵያ፣ የውጭ ኢንቨስትመንትን ውጤታማ ሊያደርግ የሚያስችል የተፈጥሮ ሀብታም ናት፤ ከዚህ በተጨማሪ የጂኦፖለቲካዊ ጠቀሜታዋም ትልቅ የሚባል ነው፡፡

ነገር ግን ኢትዮጵያ ያላትን የተፈጥሮ ሀብቷን ለመጠቀምም ሆነ የጂኦፖለቲካዊ ተፈላጊነቷን በአግባቡ ለመገልገል እንዳያስችላት አንዳንድ አሉታዊ ተጽዕኖዎችን የሚያሳዩ ቢሮክራሲዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ በተለያዩ ተቋማት የሚስተዋለው የስራ መጓተት ተጠቃሽ ነው ይላሉ፡፡

እንደ ዓለምሰገድ (ዶ/ር) ገለጻ፤ እሱ ማለት ግን ኢትዮጵያ ውስጥ ለውጭ ኢንቨስትመንት የማይሆን ነገር አለ ማለት አይደለም፡፡ ለውጭ ኢንቨስትመንት የሚሆኑ ሕጎች እየወጡም ምቹ ሁኔታ እየተፈጠረም እንደሆነ የሚታይ ሐቅ ነው፡፡ ለምሳሌ የፕራቬታይዜሽን ሕግ ተሻሽሏል፡፡ እሱም በመሻሻሉ እንደሳፋሪኮም አይነት ኩባንያዎች መግባታቸው አንዱ ምልክት ነው፡ ፡

በሪልስቴት የተሰማሩ ባለሀብቶችም አሉ፡፡ ነገር ግን እነዚህ በቂ አይደሉም፡፡ ሌሎችም ይከተሉ ዘንድ መሻሻል የተገባቸው አሰራሮች አሉ፡፡ በአገራችን ካሉ የቢሮክራሲ ችግሮች ለምሳሌ አንደኛውና ዋንኛው ሙስናን ነው የሚሉት ዓለምሰገድ (ዶ/ር)፣ ሙስና ለልማትም ለእድገትም ትልቅ ማነቆ የሚሆን ነው ይላሉ፡፡ ባለሀብቶች በየሔዱበት አካባቢ ገንዘብ የሚጠየቁ በመሆናቸው እንደዚያ አይነቱ አሰራር የሚያማርረውና ተስፋ የሚያስቆርጠው የውጭ ባለሀብቶችን ብቻ ሳይሆን የአገር ውስጥ ባለሀብቱንም ጭምር ነው፡፡

ሙስና ሲኖር ባለሀብቱ ለማልማት ያለውን መነቃቃት ይገድላል ሲሉ ያስረዳሉ፡፡ ሌላው የቢሮክራሲ ማነቆ ስራ ማጓተታችን ነው የሚሉት ዓለምሰገድ (ዶ/ር)፣ በእያንዳንዱ ሲቪል ሰርቪስ ውስጥ ስራ ማጓተት እንዳለ ይጠቅሳሉ፡፡ ስራ የማጓተት አንዱ ምልክት ከሙስና ጋር በተያያዘ የሚመጣ ነው፡ ፡

በአሁኑ ወቅት አገልግሎቶች እየተሰጡ ያሉት በገንዘብ ኃይል በመሆኑ ገንዘብ የማይሰጥ አካል አገልግሎቱ የሚጓተት እንደሆነም ይናገራሉ፡፡ መምህር አዳፍረው እንደሚሉት ከሆነ ደግሞ፤ ቢሮክራሲ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ የሚኖረው ተፅዕኖ አሉታዊ ወይንም አዎንታዊ ሊሆን ይችላል። ይህም ተፅዕኖ ሊወሰን የሚችለው በቢሮክራቲክ አሰራር መኖር አለመኖር ሳይሆን ቢሮክራሲው በተዋቀረበትና በሚተገበርበት ሁኔታ ላይ ነው።

ይህም ማለት የቢሮክራሲ አወቃቀር ስራዎችን ሊያቀሉ የሚችሉ ዘመናዊ ስልቶችንና ቴክኖሎጂዎችን የሚጠቀም ከሆነ የሰው ኃይልንና የቁሳቁስ ብክነትን በመቀነስ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ አዎንታዊ ተፅዕኖ ሊያስከትል ይችላል። ይሁንና ለአንድ ሀገር ኢኮኖሚያዊ እድገት የባለሃብቱ ሚና የጎላ እንደሆነ እየታወቀ ባለሀብቱ አግባብ ባለው መንገድ ኢንቨስት እንዲያደርግ በዘርፉ ያሉ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የአሰራር ስርዓታቸውን ቀልጣፋና ግልጸኝነት የተሞላበት ለማድረግ እምብዛም ሲነሳሱ አይስተዋልም፡፡ እርሳቸውም ልክ እንደ ዓለምሰገድ (ዶ/ር) ሁሉ የቢሮክራሲ ማነቆ የሆኑ እንደ ሙስና እና ብልሹ አሰራር ሲንጸባረቁ የሚታይ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡

እርሳቸው እንደሚያስረዱት፤ ቢሮክራሲ በጣም የተንዛዛና ኋላቀር ከሆነ የሀገርን ኢኮኖሚ ክፉኛ ሊጎዳ ይችላል። በሌላ መልኩ ደግሞ የቢሮክራሲ አተገባበር ከአድልዎ፤ ከስርቆትና ከሙስና ጽዱ በሆነ መልኩ ተግባራዊ ማድረግ ካልተቻለ የሀገርን ሀብት በቢሮክራሲ ስም የመበዝበዝ ሁኔታ ስለሚፈጠር በዚህ ረገድ ከፍተኛ የሆነ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል።

የቢሮክራሲ አሰራር በብቃት፣ በግልፀኝነት እና ተጠያቂነት ላይ የተመሰረተ ከሆነ የተረጋጋ የስራ ከባቢን በመፍጠር፣ የግለሰቦችን ሀብት የማፍራት መብት በማስከበርና ፍትሀዊ የሆነ ፉክክርን በመፍጠር ለሀገር ኢኮኖሚ አዎንታዊ ሚና ይኖረዋል። ከዚህም በተጨማሪ የተሻለ የቢሮክራሲ አሰራርን መዘርጋት በግለሰቦችም ሆነ በተቋም ደረጃ ኮንትራቶችን ለማስፈጸም፣ አዕምሯዊ ንብረቶችንና መብቶችን ለማስጠበቅ እንዲሁም የንግድ ምዝገባንና ፈቃድን በማሳለጥ ውጤታማ የሆኑ የስራ ፈጠራዎችንና ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት ይረዳል።

በዋናነት ብቃትን መሰረት ያደረጉና ከሙስና የጸዱ ቢሮክራሲዎች ጥሩ ችሎታ ያላቸውን ግለሰቦች ወደ ፐብሊክ ሰርቪስ እና የተለያዩ አስፈጻሚ ተቋማት በመሳብ የተሻለ ፖሊሲዎችን ለማውጣትና ለመተግበር ያስችላል።

ከዚህ በተቃራኒው ቢሮክራሲ የኢኮኖሚ እድገትን ሊያደናቅፍ የሚችልባቸው ሁኒታዎችም አሉ። ቢሮክራሲ በውጤታማነት እጦት፣ በሙስና፣ በጣም በተጓተተ የስራ ሂደት እና ኃላፊነትን በአግባቡ ባለመወጣት ምክንያት የአገርን ኢኮኖሚ ወደኋላ ሊጎትትና ሊጎዳ ይችላል ይላሉ።

በተቋማት ውስጥ ቢሮክራሲያዊ ብልሽቶች ሲፈጠሩ ሙስናን ያስከትላሉ የሚሉት መምህር አዳፍረው፣ ይህ ደግሞ ገበያን ያዛባል፤ የውጪ ኢንቨስትመንቶችን ያደናቅፋል፤ ሕዝብ በመንግስት ተቋማት ላይ ያለውን አመኔታ ያሳጣል ሲሉ ያስረዳሉ።

መምህር አዳፍረው፣ የኢትዮጵያ መንግስት የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ያነቃቃል እንዲሁም የተሻለ ተወዳዳሪ ኢኮኖሚ ለመፍጠር የተሻሉ እድሎችን ያመጣል ብሎ ያመነበትን ኢኮኖሚያዊ ሪፎርም እያደረገ እንደሚገኝ ጠቅሰው፤ ከእነዚህ ሪፎርሞች ወስጥ አንደኛው የውጪ ባለሀብቶችን ወደ ሀገር ውስጥ በመሳብ ተሳታፊ ማድረግ ነው ብለዋል።

ከዚህ ጋር ተያይዞ ቢሮክራሲው ውስብስብና የተንዛዛ ነው የሚል ትችት እንዳለበት ተናግረው፤ ይህ ስጋትና ትችት በራሱ ጥናት የሚያስፈልገው ቢሆንም ችግሩ እንዳለ ለመናገር ግን ብዙ ማሳያዎች ይስተዋላሉ ሲሉ ገልጸዋል። ለአብነትም የተለያዩ አገልግሎት ፈላጊዎች በብዙ መንገድ ሲማረሩ ማዳመጥ የተለመደ ጉዳይ ነው፤ በግለሰብ ደረጃ እንኳን ትንሽ ጉዳይ ለማስፈጸም የሚፈጀው ጊዜና ጉልበት እለፍ ሲልም የሚጠየቀው ገንዘብ የቢሮክራሲውን ቀልጣፋ አለመሆንና ለብልሹ አሰራሮች የተጋለጠ መሆኑን አመላካች ነው ሲሉ ተናግረዋል።

እርሳቸው እንደሚሉት፤ ስለዚህ ሀገሪቱ ለውጪ ባለሀብቶች ያደረገችው ጥሪ በአንድም ይሁን በሌላ በኩል ቢሮክራሲውን ተንተርሶ ሊደርስበት የሚችለው ተጽዕኖ ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችል ተገማች ነው። በመሆኑም ይህንን ስጋት ለማስቀረት ከወዲሁ እልባት ስለሚያሻ መንግስትም ሆነ ፖሊሲዎችን ለማስፈጸም ስልጣን የተሰጣቸው ተቋማት ውስጣዊ አሰራራቸውን በመፈተሽ ዘመናዊና ከዓለም ነባራዊ ሁኔታዎች ጋር በተወዳዳሪነት ለመራመድ የሚችል የቢሮክራሲ ስርዓት መዘርጋት ይኖርባቸዋል።

ዓለምሰገድ (ዶ/ር) በበኩላቸው እንደሚሉት፤ ሌላው በዘመናዊ መልክ የስራ ባህልን ማዳበር፤ የስራ ጊዜ አጠቃቀምን በማስተካከል የስራ ባህላችንን መቀየር ተገቢ ነው፡፡ ሌላው አስፈላጊው ሰራተኛ በተፈለገበት ቦታ መመደብ ወሳኝ ነው፡፡ ባለሙያዊነትን ማዳበርም አስፈላጊ ነው፡፡ በተጨማሪ ትክክለኛ እውቀት ያለው ሰው ኢንቨስትመንት አካባቢ ተመድቦ ቢሰራ የተሻለ ኢንቨስትመንትን መሳብ ይችላል፡፡ ዋናው ነገር የተሻለና የተቀላጠፈ አገልግሎት መስጠት ነው፡፡

ስራ ማጓተቱን በመተውና እንደ አገር በማሰብ አገርና ሕዝብ መቀየር የሚችልበት ነገር ላይ ትኩረት መስጠት ያሻል ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ ተቋማት ውስጥ ጥሩ አገልግሎት የሚሰጡ አሉ፡፡ የእነዚያን ተቋማት ልምድ መቀመር ተገቢ ነው የሚሉት ዓለምሰገድ (ዶ/ር)፣ ለምሳሌ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በመልካም አርዓያነቱ የሚጠቀስ ነው ይላሉ፡፡

ተቋሙ፣ ስመጥር ከመሆኑም በተጨማሪ ደንበኞችን እንዴት እንደሚያስተናግድ የተመሰከረለት ነው፡፡ ኢንቨስተሮችም ቢሆኑ ወደ አገር የሚገቡት በዚህ ትልቅ ተቋም አማካይነት ነውና የእነርሱን ልምድ በመውሰድ የተሻለ ሆኖ ለመገኘት መስራት ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡

እርሳቸው እንደሚሉት፤ ሌላው ተጠቃሹ ቴሌኮሙኒኬሽን ተቋም ነው፡፡ ተቋሙ ከሚያስፋፋቸው መሰረተ ልማቶች ጀምሮ ያለውን የስራ ባህል መውሰድ መልካም ነው፡፡ እነዚህ ተቋማት የወሰዱትን ሪፎርም ተግባራዊ ማድረግ ያሻል፡፡

የእነርሱም ተሞክሮ መውሰድ አንዱ የኢንቨስትመንት እድልን መሳቢያ ከመሆኑ በተጨማሪ የቢሮክራሲ ማነቆ የሆነውን አካሔድ ሊገታ የሚችል ነው፡፡ ምሁራኑ እንደሚሉት፤ ቢሮክራሲያዊ ማነቆ እየበዛ የሚሄድ ከሆነና የሚመጡ ባለሀብቶችም በሚፈልጉት ልክ መስተናገድ የማይችሉ ከሆነ ለሚመጣው ባለሀብት ብቻ ሳይሆን አገር ውስጥ ላለው ዜጋም ጭምር ስጋት ይፈጠራል፡፡

ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ከሌለ የውጭ ምንዛሬ አይኖርም፡፡ እንደዚያ ከሆነ ደግሞ ለአገር ትልቅ ስጋት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ብዙ ሀብትና በቂ የሰው ጉልበት አላት፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን በአፍሪካ ቀንድና በምስራቅ አፍሪካ ስለምትገኝ የገበያ ማዕከል ናት፡፡ የጂኦፖለቲካ አቀማመጧም ጥሩ የሚባል ነው። ይህንን ለኢንቨስተሮቹ በማሳየት ወደአገራችን እንዲመጡ ማድረግ ይቻላል፡፡

ይኼንን ለማድረግ ግን ማነቆዎቹ መፈታት አለባቸው፡፡ ሙስናው፣ ስራን ማጎተቱ፣ የሰላሙ መደፍረሱና መሰል ነገሮች ላይ በደንብ መስራት የግድ ይላል፡፡ ባለሀብቱ አግባብ ባለው መንገድ ኢንቨስት እንዲያደርግ በዘርፉ ያሉ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የአሰራር ስርዓታቸውን ቀልጣፋ፣ ግልጸኝነት የተሞላበት ማድረግ እንዲሁም ከሙስና እና ከብልሹ አሰራር በፀዳ መልኩ መተግበር ይኖርባቸዋል።

በዋናነት ትኩረት ማድረግ ያለባቸው የግለሰቦች ትውውቅና ግንኙነት ላይ ሳይሆን ሙያዊ ብቃትና ዝግጅት ላይ መሆን አለበት። በአንድ አገር ውስጥ የቢሮክራሲ ማነቆ እየጠነከረ ከመጣ ችግሩ እየተባበሰና ጉልበተኛው እየበረታ ስለሚመጣ ኢኮኖሚ እየተዳከመ ይሔዳል፤ በኢኮኖሚ ጠንካራ ያልሆነ አገር የጊዜውን ፈተና መቋቋም ስለማይችል በጊዜ ሒደት ሊፈርስና ዜጋውም ሊበተን ይችላል፡፡

አስቴር ኤልያስ

አዲስ ዘመን ሐምሌ 2/2016 ዓ.ም

Recommended For You