የሰኔ ወር መጨረሻ አካባቢ እና የሐምሌ ወር መጀመሪያ የተማሪዎች የምርቃት ዜናዎች ይበዙበታል።ቀደም ሲል በነበሩት ዓመታት በከፍተኛ ድምቀት የሚታወቀው የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ምርቃት ነበር።ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የመዋዕለ ሕጻናት ምርቃት የመገናኛ ብዙኃን የዜና ሽፋን ላይ ባይደርስም በሰፈር ግን ከዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ምርቃት በላይ አጀንዳ ሆኗል።ትልቅ መፎካከሪያም ሆኗል።
የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ምርቃት ትኩረት የሚስበው ግን ለተመራቂ ተማሪዎች ብቻ አይደለም።ለተመራቂ ተማሪዎች ወላጆች፣ ለመንግሥት፣ በቀጣይ ዓመት ለሚመረቁ ተማሪዎች፣ ባለፈው ዓመት ለተመረቁ ተማሪዎች (በትዝታ)፣ ባለፈው ዓመት ብቻ ሳይሆን ከዚያ በፊትም ቢሆን የተመረቁ ሰዎች ትዝ ይላቸዋል።ታዲያ ማን ቀረ? ምናልባት ‹‹ትምህርት የፋራ ነው›› ብሎ ወደ ቦዘኔነት የገባ ሰው ነው የሚቀርበት።ምናልባት እሱም ቢሆን ጓደኞቹን በቴሌቭዥን ባየ ቁጥር ትዝ ይለዋል።ስለዚህ የሁሉም ጉዳይ ነው ብለን እንውሰደው፡፡
እንግዲህ ሰሞነኛው የተማሪዎች የምርቃት ሽር ጉድ ነውና ስለምርቃት አንዳንድ ነገሮችን እናስታውስ።
በምረቃ ሰሞን በሬዲዮ ጣቢያዎች የመዝናኛ ፕሮግራሞች ማድመቂያ የሚሆነው የተመራቂ ተማሪዎች መጽሔት ላይ የሚወጣው የስንብት ቃል (በእንግሊዘኛ ነውና የሚጠራ Last Word) ነው።ተማሪዎች የየራሳቸውን ፍልስፍና ያስቀምጡበታል።አንዳንዶቹ ያሳለፉትን ውጣ ውረድ ይጽፋሉ።አንዳንዶቹም ቀልድ ይጽፉበታል።በጣም የሚበዛው ግን ፈጣሪያቸውንና ቤተሰባቸውን የሚያመሰግኑት ናቸው።ወደ ቀልድ ያዘነበለ ጽሑፍ ከሚያስቀምጡት ውስጥ ከሰማሁትና ካየሁት ጥቂቶችን ላካፍላችሁ።
ከሁሉም ይህኛው ይገርማል።መቼም ተማሪ ሆኖ የመምህርን ብቃት መለካት ያለ ነው።መምህር እገሌ ጎበዝ ነው፤ መምህር እገሌ አይችልም ማለት የተለመደ ነው።በማይችሉ መምህራን ሲበሳጭ የቆየ ተማሪ መመረቂያው ላይ ‹‹ሳይማር ላስተማረኝ መመምህሬ አመሰግናለሁ!›› ብሎ ጻፈ።አስቂኝም ቢመስልም የቁም ነገር መልዕክትም ያለው ነው።
አንዳንዱ ደግሞ በራሱ ስንፍና ላይ ይቀልዳል።ለምሳሌ ሰሞኑን ‹‹ስለምን ከወደቁት መሃል ትፈልጉኛላችሁ?›› የሚል የስንብት ቃል (ላስት ወርድ) ሲዘዋወር ነበር።እንደምንም ተንቀጥቅጦ ያለፈ ሌላኛው ሰነፍ ደግሞ ‹‹ ማለፌን ለ‹‹A›› ንገሯት›› የሚል ቃል ጽፌ እንደነበር አስታውሳለሁ።
አንዳንዱ ደግሞ የተለመዱ አባባሎችን ጠምዘዝ በማድረግ ወደቀልድነት ያመጣቸዋል።ለምሳሌ ‹‹የተማረ ይግደለኝ›› የሚለው አባባል የተለመደ ነው። አንዱ ተመራቂም እንዲህ አለ።‹‹ሰፊው ሕዝብ ሆይ! የተማረ ይግደለኝ ብለሃልና መጣሁልህ!›› ሌሎችንም እንጨምር።‹‹የሚረዳኝ የለምና ሥራ ፈልጉልኝ፣ ሳልሸከመው የከበደኝ ነገር ቢኖር ሰው ብቻ ነው፣ ለአንድ ባርኔጣ ይሄ ሁሉ ጣጣ!፣ ሳይጨርሰኝ ጨረስኩት(ትምህርቱን መሆኑ ነው)..›› የሚሉ የስንብት ቃላት ፈገግታን ይፈጥራሉ።ይሄ በዩኒቨርሲቲዎች ብቻ ሳይሆን በኮሌጆችም ጭምር ያለ ነው።እዚህ ላይ አንድ የሰማሁት የስንብት ቃል አለ።አንድ ከ10ኛ ክፍል ውጤት ያልመጣለት ተማሪ ኮሌጅ ገብቶ በዲፕሎማ ሲመረቅ መመረቂያው ላይ ‹‹ይብላኝ ለማትሪክ እኔስ ተመረቅኩ!›› ብሏል።
የምርቃት ሰሞን በዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆች ሽር ጉዱ ይበዛል።‹‹የእገሌ እንዲህ ነው፣ የእገሌ አምሮበታል…›› ወሬዎች ሁሉ ሱፍ ሱፍ ይላሉ። በተለይም ማታ ማታ እንደየ ትምህርት ክፍሉ በቡድን በቡድን ሆኖ መጓዝ የተለመደ ነው።በተለይም የእራት ግብዣ (ፓርቲ ይሉታል) የሚኖር ዕለት ሽርጉዱ ይጦፋል።የሽኝት ፕሮግራም የሚባልም አለ።ምንም እንኳን የእኔ ትዝታ ከ9 ዓመታት በፊት የነበረ ቢሆንም ከነበርኩበት ተነስቼ እንደማስታውሰው የ1ኛና የ2ኛ ዓመት ተማሪዎች የትምህርት ክፍላቸውን ተመራቂዎች ለመሸኘት የሚያዘጋጁት ዝግጅት ነው።እዚህ ላይም የሚታየው የሱፍ ትርዒት ነው።
ይህ የምርቃት ሰሞን ለተመራቂዎች ብቻ ሳይሆን ባለፈው ዓመትም ሆነ ከዚያ በፊት ለተመረቁ ሁሉ ትዝታ ነው።እንዲያውም አንዳንዶቹ ዳግም ምርቃት ሁሉ ይመስላቸዋል።ለዚህም ነው ትዝታቸውን በፎቶ የሚያጋሩት።
ለዚህ ትዝብት መነሻ የሆነኝ ግን የዳግም ምረቃ ነገር ነው።ይሄውም በቤት ውስጥ ትልቅ ድግስ ተደግሶ የሚደረገው ምርቃት ማለት ነው።ተማሪው ግቢ ውስጥ ከተመረቀው በተጨማሪ ቤተሰብ ጋ ሲሄድ ድግስ ይዘጋጃል።በእርግጥ እንደየተማሪው ፍላጎትና የቤተሰብ ሁኔታ ይለያያል።የቤተሰብ ሁኔታ ሲባል እንግዲህ የሀብታም ልጅ ብቻ ያዘጋጃል ማለት አይደለም።የድሃ ልጅ ቢሆንም የሚዘጋጅለት አለ።የሀብታም ልጅ ሆኖም ‹‹እኔ አልፈልግም›› ብሎ የሚከለክል ይኖራል።ብቻ ያም ሆነ ይህ እንደየሁኔታው ለዳግም ምረቃ ከፍተኛ ድግስ የሚያዘጋጁ አሉ።አግባብ ነው አግባብ አይደለም ብዙ ሲያከራክር የቆየ ጉዳይ ነው።የሚገርመው ግን ነገሩ ትክክል አለመሆኑን የሚያወግዙ ወላጆች ሁሉ ሳይቀር የራሳቸው ላይ ሲደርስ ግን ይደግሳሉ።በባህላችን ‹‹ምን ይሉኛል›› የሚባል ነገር ስላለ በእኔ ሲሆን ሊቀር አይችልም በሚል ስሜት ነው።
ለመሆኑ በዚህ የኑሮ ውድነት፣ በዚህ የሥራ አጥነት ሁኔታ፣ ሰፊ ድግስ ደግሶ ማጥለቅለቅ ተማሪውንስ ማሳቀቅ አይሆንም? እንዲያ ተደግሶ፣ አሼሼ ገዳሜ ተብሎ፤ ተመራቂው በነጋታው የትምህርት ማስረጃውን ይዞ ዝናብና ፀሐይ ሲፈራረቅበት የድግሱ ታዳሚዎች ምን ይላሉ? የሥራ ፍለጋን ነገር እያሰበ እሱስ እንዴት ይጨፈርለታል? እንዲያውም ከተቻለ ሥራ ሲያገኝ ቢደገስ ሳይሻል አይቀርም።
ሌላው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በጣም የተለመደው ደግሞ የመዋዕለ ሕጻናት ምርቃት ድግስ ነው።ባለፈው ዓመት ከአንድ የዘመድ ቤት ተጠራሁ።ምን እንደሆነ አልተነገረኝም።በደፈናው ‹‹ፀበል ነገር…›› ተብየ ነው የተጠራሁ።በኋላ ነገሩን ሳጣራ በሐበሻ ልማድ ትንሽ ናት ለማለት መሆኑ ነው፤ ሲቀጥል የሚመጣው ሰው ምንም ነገር እንዳያስብ መሆኑ ነው።በተባልኩት ሰዓት ስሄድ ግቢው ተጥለቅልቆ ሽር ጉድ ሆኗል።በጌጣጌጦችና በልብሶች ምርቃት መሆኑን አወቅኩ።ምንም እንኳን እኔን ባያገባኝም ‹‹ምንድነው አሁን ይሄ ሁሉ ድካም?›› ብየ ስጠይቅ፤ ‹‹ሁሉም እያደረገ ታዲያ እኛ ብቻ ለምን እንቀራለን?›› በማለት ነው።
ነገርየው ልማድ ስለሆነ ልጆችም በእነርሱ ብቻ ሲቀር ቅር ሊላቸው ይችላል።እንዲህ በፉክክር እየተደረገ ጭራሽ መደበኛ ባህል ሆኖ አረፈው።የትምህርት ቤት ክፍያ ሲገፈግፈው የከረመ ወላጅ ለመዋዕለ ሕጻናት ምርቃትም ሊደግስ ነው ማለት ነው።12ኛ ክፍል ላይም ተጀምሯል ተብሏል።እንግዲህ አንድ ድሃ ወላጅ ከትምህርት ቤት ክፍያ ጀምሮ ልጆቹ ከዩኒቨርሲቲ እስከሚመረቁ ድረስ የሚያወጣው ወጪ በአግባቡና ለሚፈለገው ብቻ ቢሆን ለልጆቹ አንድ ንግድ ቤት ይከፍት ነበር ማለት ነው።
‹‹ጩኸቱ ከፍየሏ በላይ ሆነ›› እንደሚባለው የምርቃት ድግሱ ከትምህርቱ እና ከሚያገኙት ሥራ በላይ እንዳይሆን!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ሰኞ ሐምሌ 1 ቀን 2016 ዓ.ም