ዶክተር ቶማስ ቸርነት በግብርና ሚኒስቴር የእንስሳትና ዓሳ ሃብት ፕሮጀክት ብሔራዊ አስተባባሪ
በግብርና ሚኒስቴር ሥር የተደራጀው ክፍለ አህጉራዊ የእንሰሳት ዓሳ ሴክተር ልማት ፕሮጀክት መነሻ ሁኔታው የእንሰሳት ዓሳ ሃብትን በሃገር ደረጃ ከቁጥር ያለፈ ፋይዳ እንዲኖረው እና አርሶ አደሩ ከሰብል ምርቱ ጎን ለጎን ተጠቀሚ እንዲሆን ጥር 25 2010 ዓ.ም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መፅደቁ ይታወሳል። በዚህ መሰረትም የእንሰሳት ዓሳ ሃብት ልማት የኢትዮጵያ ፕሮጀክት በሚል ስያሜ ከዓለም ባንክ በተገኘ 170 ሚሊዮን ዶላር የብድር ስምምነት መሰረት ከየካቲት 14 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ ሲተገበር ቆይቷል። ፕሮጀክቱ ላለፉት ስድስት ዓመታት በዋነኝነት እየሠራ ያለው በአራቱ የእንስሳት እሴት ሰንሰለቶች ማለትም በወተት ልማት፣ በዶሮ እርባታ፣ በቀይ ስጋ እና በዓሣ ላይ ምርትና ምርታማነትን እንዲሁም ወደ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን ማሻሻል ላይ አተኩሮ ነበር።
ይህ የልማት መርሃ ግብር የመጀመሪያው ምዕራፍ የተቀመጠለት የጊዜ ገደብ ሊገባደድ በጣት የሚቆጠሩ ወራት ቀርተውታል። በእነዚህ ዓመታት ታዲያ ፕሮጀክቱ ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ የእንስሳት ሃብት ምርታማነት ለማሳደግ ይዞ የተነሳውን ምን ያህል ዓላማውን አሳክቷል? እውን ሕዝብንና ሃገርን በተጨባጭ ተጠቃሚ አድርጓል? ስንል በግብርና ሚኒስቴር የእንስሳትና ዓሳ ሃብት ፕሮጀክት ብሔራዊ አስተባባሪ ዶክተር ቶማስ ቸርነትን ጠይቀናል። በዚህና በሌሎችም የዘርፉ ወሳኝ ጉዳዮች ዙሪያ ከአስተባባሪው ጋር ያደረግነውን ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው ይዘን ቀርበናል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ፕሮጀክቱ ከስድስት ዓመት በፊት ሲነደፍ ምን ዓላማ ይዞ እንደነበር እንዲሁም አተገባበሩ ምን ይመስል እንደነበር ያስታውሱንና ውይይታችን እንጀምር?
ዶክተር ቶማስ፡- የዚህ ፕሮጀክት ዋና ዓላማው በእንስሳት ሃብታችን ላይ ከፍተኛ እምርታ ለማምጣት ነው። የእንሰሳት ዓሳ ሀብት ልማት ዘርፍ ፕሮጀክት በአይነቱ ለየት ያለ፤ እንሰሳትንና የእንሰሳት ሃብት ልማትን ለመደገፍ ብቻ የመጣ ሲሆን 176 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዶላር በዓለም ባንክ በረጅም ጊዜ ወለድ በተገኘ ብድር ሲከናወን የቆየ ነው። ፕሮጀክቱ ሁለት ዓይነት ባህሪ ያለው ሲሆን የመጀመሪያው በስድስት ክልሎች በ58 ወረዳዎች እና በ1ሺ755 ቀበሌዎች እንዲሁም ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ ተጠቀሚዎችን ተሳታፊ አድርጓል። ሁለተኛው ደግሞ በብሔራዊ ደረጃ ሁሉንም ክልሎች መሰረት ያደረገ ድጋፍ ያካሂዳል። አስቀድሜ እንደገለፅኩልሽ ፕሮጀክቱ ከየካቲት 21 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ መተግበር የጀመረ ሲሆን ላለፉት ስድስት ዓመት በዘጠኝ ክልሎች ላይ የሚከናወነው የእንስሳት ሃብት ልማት ስራ ሲደግፍ ቆይተዋል።
ይህ በግብርና ሚኒሰቴር የእንሰሳት ዓሳ ዘርፍ ልማት ዘርፉ ሥር የሚከናወነው ፕሮጀክት እንደሃገር በእንስሳት ሃብት ልማት ረገድ የታቀደውን ዕቅድ በማሳካት፤ ብሎም ሀገራችን የያዘችውን የልማት አቅጣጫ፤ እንዲሁም የልማት ቱሩፋት እቅድ እውን በማድረግ የበኩሉን አስተዋፅኦ አበርክቷል፤ እያበረከተም ይገኛል። ይህንንም ውጤት በሚያመጣ መልኩ ስራ ላይ በማዋልና የእንሰሳት ዓሳ ዘርፍ ልማት ፕሮጀክትም የያዛቸውን ግቦች፣ ስትራቴጂዎች፣ እንዲሁም ከአሁን ቀደም በነበሩት ፕሮጀክቶች የመፈጸም አቅም ክፍተትን በመሙላት ሁሉም ባለ ድርሻ አካልና ፈፃሚው በጋራ እና በቅንጅት በመተባበር የእንሰሳት ዓሳ ዘርፍ ልማት ፕሮጀክት እቅድና ተልዕኮ በማሳካት ላይ ይገኛል፡፡
በነገራችን ላይ ከግብርና አኳያ እንደሃገር እስከአሁን ድረስ በርካታ ፕሮጀክቶች ተከናውነዋል፤ ሆኖም ግን በሰብልና በተፈጥሮ ሃብት ልማት ላይ ያተኮሩ ናቸው። በእንስሳት ሃብታችን ላይ የተለየ ፕሮጀክት ሲነደፍ ይሄ የመጀመሪያው ነው። አስቀድሜ እንደገለፁት የፕሮጀክቱ ዓላማ በእንስሳት ሃብታችን ላይ ለውጥ ለማምጣት ነው። ከዚህ አንፃር ፕሮጀክቱ ሶስት አንኳር ጉዳዮችን የያዘ ሲሆን እነዚህም ምርትና ምርታማነትን ማሻሻል፣ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ለአርሶአደሩ ተደራሽ ማድረግና አርሶአደሩን ከገበያ ጋር ማስተሳሰር ናቸው፡፡
አዲስ ዘመን፡- የፕሮጀክቱ መተግበር በሀገርም ሆነ በክፈለአህጉር ደረጃ ያስገኛቸዋል ተብለው የሚጠበቁ ውጤቶች ምን ነበሩ?
ዶክተር ቶማስ፡- ፕሮጀክቱ ሲቀረፅ እንዳልሽው በሃገርም ሆነ እንደአህጉር ያሳካል ተብሎ የታለሙ የልማት አጀንዳዎች አሉት። በዋናነትም አርሶ አደሩን፣ ወጣቱን እና ሴቶችን ተጠቃሚ ማድረግ የታለመ ሲሆን፤ በእንሰሳትና ዓሳ ዘርፍ ለሚሰማሩ አርሶ አደሮች እንዲሁም የእንሰሳት ምርት አቀናባሪዎች ተገቢውን አገልገሎት መስጠት ሌላው አንኳር ጉዳይ ነበር። በተጨማሪም ለአርሶ አደሮች እና ነጋዴዎች የተሻሻለ የገበያ ተደራሽነትን ማጎልበትም ቁልፍ ሥራዎች ነበሩ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ታዲያ ከዚህ አንፃር ምን ያህል ስኬታማ ሥራ ተከናውኗል ተብሎ ይታመናል?
ዶክተር ቶማስ፡- አስቀድሜ ለመግለፅ እንደሞከርኩት ይህንን ፕሮጀክት መተግበር ያስፈለገበት ዋነኛ ምክንያት የኢትዮጵያ ያላትን የእንስሳት ሃብት ልማትን በማሻሻል ለኢኮኖሚው እድገት አወንታዊ ሚና እንዲጫወት በማለም ነው። እንደሚታወቀው ደግሞ ኢትዮጵያ በእንስሳት ሃብቷ ከአፍሪካ ቀዳሚ ብትሆንም ይህንን ሃብት ይዛ ተጠቃሚ አልነበረችም። ከኢትዮጵያ ይልቅ እነ ቦትስዋና ከፍተኛ ወተት እያመረቱ ወደ አውሮፓ ገበያ ጭምር ይልካሉ። እኛ ግን በእንስሳት ሃብት ቁጥር ይዞ ከመቀመጥ ባለፈ ሕዝቡም ሆነ ሃገር በሚገባ ተጠቃሚ አልሆነም። አይደለም አዋቂው ሕፃናት ጭምር የሚገባውን ወተት አያገኙም። በመሆኑም ይህንን ታሪክ ለመቀየር ያስችል ዘንድ በዚህ ፕሮጀክት አማካኝነት የተለያዩ ስራዎች ተከናውነዋል። በተለይም በአራት የእሴት ሰንሰለቶች ማለትም በስጋ፣ በወተት፣ በዓሳና በዶሮ ምርት ላይ ከፍተኛ እምርታ ለማምጣት ርብርብ ሲደረግ የነበረው። ምርታማነታቸው ከፍተኛ የሆነ እንስሳት ዝርያዎችን በማዳቀልና ዝርያዎችን በማሻሻል ምርታማነት እንዲጨምር ትኩረት ተደርጎ ተሰርቷል።
በሁለተኛ ልማት ትኩረት የነበረው ደግሞ በተቋማት የሚሰራውን ሥራ የማሳደግና አቅማቸውን ከፍ የማድረግ ሥራ ነው።
ከዚህ አንፃር በዚህ ፕሮጀክት አማካኝነት በስድስት ዓመታት ውስጥ የተሰሩት ስራዎች በርካታ ለውጦችን አጥቷል። የራሱ የእድገት ሂደት ያለው ሲሆን የመጀመሪያው ሥራ ገበሬውን ማደራጀትና የስራ እድል መፍጠር ነው። የስራ እድል የሚፈጠረው ደግሞ በእንስሳት ሃብታችን ነው። ይሄ ፕሮጀክት በተከናወነባቸው ዘጠኝ ክልሎች ውስጥ በሚገኙ 58 ወረዳዎች 1ሺ 755 ቀበሌ ገበሬ ማህበራት እንዲደራጁ ተደርጎ ነው ወደ ሥራ የተገባው። በእነዚህ ማህበራት ውስጥ የሚገኙ 1ነጥብ 2 ሚሊዮን የሕብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ተችሏል። እነዚህም የተለዩት ሥራአጥ የሆኑ የአርሶአደሩ ልጆች፣ ሴቶችን ነው። በተለይ ለሴቶች የእንስሳት ሃብት ምርቱን በጓሮ ስለሚሰሩት የተሻለ ድጋፍና ክትትል ይደረግላቸዋል። በጥቅሉ 10 ሺ 53 ማህበራትን የገበሬ ማህበራትን ያደራጀን ሲሆን፤ ገበሬዎቹ እንዲደራጁ የተደረጉት በግል ፍላጎታቸው ሲሆን እያንዳንዱ ማህበራትም 25 ዓባላት እንዲኖሩት ተደርጓል። የተደራጁትም በአራቱም የእዝ ሰንሰለት (ወተት እና ስጋ፣ በዶሮ፣ ዓሳ እና በማር) በማምረት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ድጋፍ ሲደረግላቸው ቆይቷል፡፡
እንደሚታወቀው ደግሞ ኢትዮጵያ ትንሽም ቢሆን ወደ አረብ ሃገራት ስጋ ትልካለች፤ በዚህ ሂደትም በፕሮጀክቱ ተካተው ምርት የሚያመርቱ አካላትን የገበያ ትስስር በመፍጠር ተጠቃሚ እንዲሆን አድርገናል። ስራው በጥሩ ሁኔታ ሲከናወን ነው የቆየው። አብዛኞቹ ገበሬዎች እኛ ለዚህ ፕሮጀክት ማስፈፀሚያ ከተበደርነው በላይ ነው ትርፋማ የሆኑት። ይህም የሚያሳየው የእንስሳት ሃብታችን ከተሰራበት በጣም የሚያኮራ መሆኑን ነው። ከዚህ ባሻገር የአየር ፀባያችን ምቹ ነው፤ በተለይ የመኖ አቅርቦት እንደልብ ቢሆን በእንስሳት ሃብታችን በብዙ ሺ እጥፍ በተገኘ ነበር፡፡፡
በዓሳ ምርት በኩል ባሉን የውሃ አካላት እና አኳካልቸ (ሰው ሰራሽ ኩሬ አማካኝነት) ዓሳ እናረባለን። ዓሳ የማያውቁ አካባቢዎች ሁሉ ኩሬ ቆፍረው ማምረት ብሎም ለገበያ ማቅረብ ጀምረዋል። መካከለኛ እና የላቀ ደረጃ ላይ ያሉ የዓሣ ሀብት ኅብረት ስራ ማህበራት የመደገፍ ሥራም በስፋት ሲከናወን ቆይቷል። በዋናነት አስፈላጊ ቁሳቁሶችን ማድረስ እና እንደ የዓሣ ማቀነባበሪያ ቤት፣ ሱቅ እና የዓሣ መሸጫ ያሉ መገልገያዎችን በመገንባት ዘርፉ እንዲጠናከር ጥረት ተደርጓል። በተጨማሪም የዓሣ ጫጩት ማምረቻ ማዕከላትን የማጠናከር ሥራ ተሰርቷል፡፡
ከዚህ አንፃር ለአብነት ብንጠቅስ በመጠናቀቅ ላይ ባለው በጀት ዓመት በዘጠኝ ወራት ብቻ አምስት የዓሣ ጫጩት ማምረቻ ማዕከላትን በተለያዩ ቁሳቁሶችና ግንባታዎች የማጠናከር ስራ የተሰራ ሲሆን የዓሣ ኩሬ ጥገናና አዲስ ግንባታ፣ የቤት ውስጥ ዘመናዊ የዓሣ ጫጩት ማባዣ ማዕከል ግንባታና የውስጥ ቁሳቁስ
አቅርቦት፣ ሰርቶ ማሳያ የዓሣ ኩሬዎች ግንባታና የስልጠና አዳራሽ ማሻሻልና የዓሣ መኖና ሌሎች መሳሪያዎች አቅርቦትን ማሻሻል ተችሏል። እንዲሁም የዓሣ ጫጩት ብዜትና ስርጭትን በሚመለከት የቆሮሶ፣ አምባዛና ካርፕ የዓሣ ዝርያዎችን ማምረትና ማከፋፈል ተችሏል። ዘንድሮ ብቻ 21 ሺ,302 የዓሣ ዘርን ለገበሬዎች ማከፋፈል እና በውሃ አካላት ውስጥ ተጨምሯል።
አዲስ ዘመን፡-ባለፉት ስድስት ዓመታት ትኩረት ተደርጎ ከተሰራባቸው ጉዳዮች አንዱ ዝርያ የማሻሻል ስራ እንደሆነ ጠቅሰዋል፤ በዚህ ረገድ የታየውን እምርታ ያስረዱን?
ዶክተር ቶማስ፡- አንቺም እንደገለፅሽው ፕሮጀክቱ በተከናወነባቸው ዓመታት ሌላኛውና ዋነኛው ሥራችን የነበረው ዝርያ ማሻሻል ስራ ሲሆን፤ ይህም የሚደረግበት ምክንያት እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ላሞች በቀን ከአንድ ተኩል ሌትር በላይ አይሰጡም። ዝርያዎቹን ማሻሻል ከተጀመረ ወዲህ በቀን ከስድስት ሌትር በላይ ወተት በየቀኑ እየተገኘ ነው ያለው። የመኖ አቅርቦታችንና ማኔጅመንታችን ገና ያላደገ በመሆኑ ከዚያ በላይ ከፍ ማድረግ አልተቻለም። በሰለጠኑት ሃገራት ግን ከ50 ሌትር በላይ የሚያገኙ ዝርያዎች አሉ። ዝርያ ባሻሻልንባቸው ወረዳዎች በተለይ ሴቶች ተደራጅተው በማምረት ከቤት ፍጆታቸው አልፈው ወተት እርጎና መሰል የተወተት ተዋፅኦችን በመሸጥ ተጠቃሚ እየሆኑ ነው ያለው።
ለውጭ ገበያ የሚቀርበው የስጋ ከብትንም ዝርያ ማሻሻል ስራ ተሰርቷል። ምክንያቱም ደግሞ በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ መሆን የሚቻለው የተሻሻሉ ዝርያ ሲሆኑና በጥሩ ሁኔታ ማደጋቸው ሲረጋገጥ ብቻ ነው። ከዚህ ባሻገር መኖ ማሻሻል ስራም ሌላው የፕሮጀክቱ አካል ነው። የቁም እንስሳት ሃብታችን ጥቅም ላይ ማዋል ከፈለግን በዚያው ልክ የመኖ አቅርቦታችንንም ማሻሻል ያስፈልጋል። ጥሩ ምርት ለማግኘት መጀመሪያ ጥሩ መኖ ማቅረብ አለብን። በመሆኑም ከእንስሳት ሃብት ልማቱ ጎን ለጎን የመኖ ልማቱም አብሮ በመስራት ተመጋጋቢ ሆነው እንዲቀጥሉ ጥረት ተደርጓል፡፡
አዲስ ዘመን፡- በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ የተሻሻሉ እንስሳቶችን ለማዳቀል የሚያግዘው ‘ናይትሮጅን’ የተባለው ንጥረ ነገር እጥረት መኖሩን አይተናል። ከዚህ አኳያ የእናንተ ድጋፍ እንዴት ይገለፃል?
ዶክተር ቶማስ፡- ዋናው ዝርያ ለማሻሻል የሚያግዘው ናይትሮጂን እጥረት አለብን ላሉ አካባቢዎች ይረዳ ዘንድ አራት ሊኩዩድ ናይትሮጂን ገዝተን አስቀምጠናል። አሁን ላይ እጥረት አለ የሚል አካባቢ አልገጠመንም። ግን ደግሞ በዚያኑ መጠን ደግሞ አርቴፊሻል ኢንሱሚሌሽን (ሰው ሰራሽ የማዳቀል ዘዴ) የሚሰሩ ባለሙያዎች እጥረት አለ። ግብዓት ማቅረብ ብቻ ሳይሆን ዘመኑን የሚዋጅ ባለሙያ ሊኖር ይገባል። ከዚህ አኳያ በተለይ የወተት ምርታማነት ማሳደግ ስለሚገባ ጊደሮችን ብቻ በስፋት የሚያባዛ 30 ሺ ዘረመል አሰራጭተናል። በተለይ ከንባታ፣ ሲዳማና ደቡብ ኢትዮጵያ አካባቢዎች ላይ የወተት በርካታ የወተት መንደሮችን በመመስረት ምርቱ በከፍተኛ መጠን እንዲጨምር እያደረግን ነው ያለ ነው። ፕሮጀክቱ በጥቅሉ አየር ላይ የሚነገርለት ሳይሆን በተጨባጭ መሬት ላይ የወረደና የሰውን ሕይወት እየለወጠ ያለ ነው። በአንዳንድ ፕሮጀክት ወረዳዎች የተመረተው ወተት የሚሰበሰብባቸው ትላልቅ ማዕከላት አቋቁመናል። ያ ግን በፕሮጀክት ወረዳ መወሰን የለበትም። ችግሩ ያለው እንደሃገር አቀፍ ነው። የወተት ማዕከላቱ በተለይ በከተሞች ቅርብ ሊሆን ይገባል፤ ምክንያቱም የገበያ ትስስሩ እንዲጠናከርና አምራቹ ኃይል ተጠቃሚ እንዲሆን ነው። በአጠቃላይ በዘርፉ ያለውን ችግር መፍታት ባለሃብቶችን ወደ እንስሳት ሃብት ልማት መግባት አለባቸው የሚል እምነት አለኝ። ገበሬዎችንም የብድር አቅርቦት ከተመቻቸላቸው ጥሩ ዝርያ ያላቸውን ከብቶች በማራባት ምርታማነታቸውን ማሳደግ ይገባቸዋል። ይህንን ማድረግ ካልቻልን ግን ቁጥሩ እያደገ የመጣውን የኢትዮጵያን ሕዝብ በአግባቡ መመገብ አንችልም፡፡
አዲስ ዘመን፡- በተለይም በአርብቶአደር አካባቢዎች በቀንድ ከብቶች ላይ የሚከሰት ተላላፊ በሽታዎችን በመከላከል ረገድ የፕሮጀክቱ ሚና ምን ነበር?
ዶክተር ቶማስ፡- ፕሮክቱ በዋናነት በእንስሳት ላይ የሚከሰቱ በሽታዎችን ከመከላከሉ ጎን ለጎን ተቋማትን በማጠናከሩ ሥራ ላይ ትኩረት ያደርጋል። ከምንሰራባቸው 58 ወረዳዎች በተጨማሪ በብሔራዊ ፕሮግራሞቹ በሽታ የመከላከል ሥራ የሚሰሩ ተቋማትን ይደግፋል። ምክንያቱም ወረርሽኝ በሽታን በተወሰኑ አካበቢዎች ብቻ በመስራት ልንከላከለው ስለማንችል የእንስሳት መከላከል ሥራ ሁሉም የሃገሪቱ አካባቢዎች ያማከለ ሥራ ይሰራል። ሃገር አቀፍ የበሽታ ቁጥር ካልተካሄደ በተወሰኑ ቦታዎች ብቻ ቢደረግ ትርጉም የለውም። በመሆኑም በሁሉም አካባቢዎች በተለይም በግና ፍየልን የሚያጠቁ በሽታዎችን ለመከላከል በስፋት ክትባት እያደረግን ነው፡፡
ከዚህ አንፃር የበጎችና ፍየሎች ደስታ መሰል በሽታን ከሀገራችን እ.ኤ.አ በ2027 እንዲሁም ከዓለም በ2030 ለማጥፋት በመንግስት በከፍተኛ ደረጃ ትኩረት ተሰጥቶበት እየተሰራ ሲሆን፤ ይህም ስኬት ተግባራዊ እንዲሆን በወረዳ ደረጃ ያሉትን የእንስሳት ጤና ባለሙያዎችን ስለ በሽታው ስለሚያስከትለው ጉዳትና በሽታውን በቀላሉ ለይቶ እንዴት መከላከል እንደሚቻል፤ የደም ናሙና በተግባር እንዴት እንደሚሰበሰብ ስልጠና ተሰጥቷል። በተጨማሪ በምንሰራባቸው ወረዳዎች ሁሉ የእንስሳት ክትባት ሥራ በየዓመቱ ይሰራል፤ ዘንድሮ በዘጠኝ ወራት ብቻ ወር ለበጎችና ፍየል የደስታ መሰል በሽታ ክትባት የተሰጠ ሲሆን ይህም 5 ሚሊዮን 811ሺ 366 በግና ፍየል ተከትበዋል፤ በዚህም 478 ሺ 952 አርብቶ አደር ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡
በሌላ በኩል የእንስሳት አያያዝ ስልጠና በፕሮጀክቱ ተሳታፊ ለሆኑ አካላት ተሰጥቷል። ፕሮጀክቱ ዋና ዓላማው እንዳውም ግንዛቤ ማሳደግ ነው። አርሶ አደሩም ሆነ አርብቶ አደሩ ዘመናዊ አመራረት ዘዴ እንዲከተሉ የተለያዩ ድጋፍ ስናደርግላቸው ቆይተናል። በነገራችን ላይ ጥሬ ገንዘብ ለገበሬ አንሰጥም፤ የተሻሻሉ ዝርያ ያላቸውን እንስሳቶችንና ግብዓት በማቅረብ እንዲሁም ስልጠና በመስጠት ነው የምንደግፋቸው። በአጠቃላይ ፕሮጀክቱ በተተገበረባቸው ስድስት ዓመታት ውጤታማ ሥራ መስራት ተችሏል። ለሚኒስቴሩ የእንስሳት ሀብት ዘርፉ የበጀት ምንጭ ሆኖ እያገለገለ የሚገኘው ይኸው ፕሮጀክት ነው። በተለይ የእንስሳት በሽታ ቁጥጥር ስራው ዋነኛ ምንጭ ሆኖ እያገለገለ ነው፤ በሽታ ከተከሰተ በኋላ ከማከም ይልቅም አስቀድሞ መከላከሉ ላይ ትኩረት ያደርጋል። ፕሮጀክቱ ብዙውን የመንግስት ስራ እየደገፈ ሲሆን በእንስሳት ሃብቱ ላይም ለውጥ እንዲመጣ አስተዋፅኦው የላቀ ነው። በጠቅላላው ትልቅ ቁጥር ላለው የእንስሳት ሃብት ጥራት ላይ ማተኮር ይገባል። ለዚህ ደግሞ በዋናነት ኤክስቴንሽኑ ላይ መሰራት አለበት።
አዲስ ዘመን፡-እርሶም እንዳሉት ኢትዮጵያ በቀንድ ከብት ሃብት ቀዳሚ ሃገር ብትሆንም የሚገባትን ያህል ተጠቃሚ አልሆነችም፤ ይህንን ታሪክ ከመቀየር አኳያ ምን መሰራት አለበት ብለው ያምናሉ ?
ዶክተር ቶማስ፡- ልክ ነው፤ የእንስሳት ሃብታችን ቁጥር ከአፍሪካም ሆነ በዓለም ደረጃ የላቀ የሚባል ነው። ሆኖም በዚያው ልክ ለኢኮኖሚያችን የጀርባ አጥንት ሆኖ እያገለገለገለ አይደለም። እንዳው ወደ ውጭ የመላኩን ነገር እንተወውና ሕዝቡ ባለው የእንስሳት ሃብት የሚገባውን ያህል የተመጣጣነ ምግብ እያገኘ አይደለም፤ እየጠቀመም አይደለም። ጎረቤታችን ኬኒኛ ከእኛ በተሻለ መልኩ 37 በመቶ የእንስሳት ተዋፅኦ ተጠቃሚ ነች። ሌሎች ጎረቤት ሃገራትም አጠቃቀም ከእኛ የተሻለ ነው። ምክንያቱም ደግሞ በቀኝ ግዛት ጊዜ የውጭ ዝርያዎችን አምጥተው የወተት ምርታቸውን ከፍ አድርገዋል። እኛ ግን ሕዝብ ቁጥራችን በየቀኑ እየጨመረ ቢሆንም በራሳችን የዝርያ ማሻሻሉ ፍጥነት እንደተፈለገው አልመጣም። ቁጥሩ ትልቅ ቢሆንም ምርታማ አይደለም፡፡
ይህንን ሁኔታ ለመቀየር ጥሩ የመኖ እና የከብት ዝርያ ሊኖረን ይገባል፤ የአረባብ ዘዴዎችንንም ማሻሻል ይገባናል። ጥሩ ዝርያ ካመጣን የወተት ምርቱ ይጨምራል፤ አሁን ያለብን የተመጣጣነ ምግብ እጥረትም እንፈታለን። አሁን በበግና ፍየል ችግር የለብንም። ምክንያም የሚፈልጉት ትንሽ ቦታና መኖ በመሆኑ ነው። ከብት ግን ለግጦሽ ብንለቀው ከእርሻ ጋር መሬት ይሻማል፤ ገበሬውም ቢሆን መኖ ከማምረት ይልቅ ሰብል ማምረትን ስለሚመርጥ ምርታማ የሆነ የቀንድ ሃብት ሊኖረን አይችልም። ያለንን ምቹ የአየር ንብረት ተጠቅመን ዝርያ ማሻሻል አለብን። በሌላ በኩል አስቀድሜ እንደተናገርኩት ሀገሪቱ በቀንድ ከብት ሃብቷ ተጠቃሚ እንድትሆን ባላሃብቶች ዘርፉን መቀላቀል አለባቸው። ወይም የእኛ ገበሬዎች ወደ ኢንቨስተርነት ማደግ አለባቸው።
ከዚሁ ጎን ለጎንም እንደ ሌማት ቱርፋት ያሉ የልማት ስትራቴጂዎች መስፋፋት አለባቸው የሚል እምነት አለኝ። ይህንን ማድረግ ከቻልን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለውጥ ማምጣት እንችላለን። ግን አሁን በያዝነው አካሄድ ግን ያደገውን የኢትዮጵያ የሕዝብ ቁጥር መግበን የውጭ ገበያ ማማተር አንችልም። ስለዚህ በተለይ ኢንቨስተሮች ወደ ዘርፉ እንዲገቡ ማበረታትና ምቹ ሁኔታ መፍጠር መቻል አለበት፡፡
አዲስ ዘመን፡- የእንስሳት ሃብት ልማቱን ማሳደግ ለምግብ ዋስትና መረጋገጥ የሚኖረው ድርሻ እንዴት ይገለፃል?
ዶክተር ቶማስ፡- አስቀድሜ እንደገለፅኩት በቀንድ ከብት ሃብታም ብንሆነም የከብቱ ተዋፅኦ የሆኑ ምርቶችን የመጠቀም ባህላችን በጣም ደካማ ነው። አርሶአደሩ ከብቶችን ቢያረባም ወተት የመጠጣትም ሆነ ስጋ የመመገብ ልምድ የለውም። እንደው ወደ አፋርና ሱማሌ ባሉ አርብቶአደር አካባቢዎች ወተት የመጠጣት ባህል በተወሰነ ደረጃ አለ ቢባልም አብዛኛው አርሶ አደር ባመረተው ምርት ተጠቃሚ አይደለም። በዚህ ምክያንት ተደጋጋሚ የሆነ የምግብ ዋስትና እና የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ይስተዋላል። ይህንን ችግር ከመቅረፍ አቋያ አስቀድሜ እንደገለፅኩት ዝርያ በማሻሻል ምርታማነትን የማሳደጉ ነገር እንደተጠበቀ ሆኖ የአርሶ አደሩን አስተሳሰብ መቀየር ትልቅ የቤት ስራ ነው የሚሆነው። በተጓዳኝ ደግሞ ባለሃብቶች በዘርፉ በስፋት በተሰማሩ ቁጥር ምርቱ እንደልብ ስለሚገኝ የማህበረሰቡም የተመጣጠነ ምግብ ችግር ይፈታል የሚል እምነት አለኝ። ለዚህ ደግሞ መሳካት ከስር ከስር ቴክኖሎጂ የሚያቀርብ የምርምር አካል ሊኖር ይገባል። ሁለቱ ተመጋጋቢ በመሆናቸው አንድ ላይ መሄድ አለባቸው፡፡
አዲስ ዘመን፡- የቴክኖሎጂና የቴክኒክ ድጋፍ ከማድረግ አኳያ ከምርምር ተቋማት ጋር በምን መልኩ ነው የምትሰሩት?
ዶክተር ቶማስ፡- ለእንስሳት ሃብታችን ምርታማነት መጨመር ዝርያ ማሻሻል ይገባል ካልን ከምርምር ተቋማት ጋር ተቀናጅቶ መስራት ደግሞ የግድ ይላል። አባላዘር ወስዶ የማዳቀል ሂደትም የተቋማቱ ሚና ወሳኝ ነው። አሁን ላይ እንደውም የሽል (ኢምብሪዮ) ንቅለ-ተከላ ሁሉ ጀምረናል። ይህንን ቴክኖሎጂ ማስተዋወወቅ የተቻለውም ከምርምር አካላት ጋር ባለን ቁርኝት ነው። ግን ደግሞ በጣም ውድ ቴክኖሎጂ ነው። በመሆኑም ተደራሽ ለመሆንና ማስፋፋት አልቻልንም። በስፋት ለመስራት ኢንቨስትመንት ይፈልጋል። ይህም ደግሞ በመንግስት አቅም ብቻ የሚቻል አይደለም። በመሆኑም አሁንም የግሉ ዘርፍ ድጋፍ ሊያደርግና በልማት ስራውም ሊሳተፍ ይገባል። በርካታ አርሶ አደሮች ዝርያ ለማሻሻል ከፍተኛ ፍላጎት አላቸው፤ ሆኖም የአቅም ውስንነት ይገድባል። በእኛ አቅም ፍላጎቱን ለማርካት የበኩላችንን ጥረት እያደረግን ነው። ስለዚህ ያለ ምርምር ቴክኖሎጂ ማሻሻል አይቻልም።
አዲስ ዘመን፡- በተፈጠሩ የወተት፤ የዶሮ መሰል መንደሮች ምርት በስፋት እየተመረተ ቢሆንም ምርቱን የሚቀበል አግሮ ኢንዱስትሪ ባለመኖሩ፤ እንዲሁም የገበያ ትስስሩ ጠንካራ ባለመሆኑ በአምራቹ ላይ ስጋት የሚፈጠርበት ሁኔታ አለ። ከዚህ አኳያ ይህ ፕሮጀክት ምን አስተዋፅኦ አበርክቷል?
ዶክተር ቶማስ፡- ልክ ነው፤ በተፈጠሩ የወተትም ሆነ የሌሎች የእንስሳት ልማት መንደሮች የሚመረቱ ምርቶችን የሚሰበሰብ ተቋም ያለመኖሩ አምራቾቹ ላይ የሚፈጥረው ጫና አለ። አምራቹ ኃይል ተጠቃሚ እንዲሆን ከተፈለገ ገበያ ትስስር ልንፈጥርለት ይገባል። በተለይ ምርቱ ላይ አተኩሮ እንዲሰራና ውጤታማ እንዲሆን የገበያ ትስስር የሚፈጥር አካል መኖር አለበት። የተመረተው ምርት ገበያ ካላገኘ ባይመረት ይመረጣል። ዋናውና ቁልፉ ጉዳይ ደግሞ የእንስሳት ምርት ሁሉም በሚባል ደረጃ ቶሎ የሚበላሽ በመሆኑ አምራቹ በወቅቱ ምርቱን የሚወስድለት ካላገኘ ለኪሳራ ይዳረጋል። ይህም ደግሞ በቀጣይ እንዳያመርት ያደርገዋል፤ ተስፋም ሊያስቆርጠው ይችላል። ለምሳሌ ዓሳ ከኩሬው አውጥተን ቶሎ ወደ ማቀዝቀዣ ካላስገባነው፤ ወተትም እንዲሁ ወደ ተጠቃሚው ካላደረስነው የመበላሸቱ እድል ሰፊ ነው። ከተበለሸ በኋላ ወደገበያ ብናስገባው ከፍተኛ የጤና ጠንቅ ያመጣል። ስለዚህ ማንኛውም የእንስሳት ተዋፅኦ ልክ እንደሌላው ምርት መጋዘን ውስጥ የምናስቀምጠው አይደለም።
ስለዚህ ገበያና አምራቹን ማገኛኘት የመንግስትም ሆነ የሚመለከተው አካል ኃላፊነት ነው። የዚህ ፕሮጀክት ዋና ስራው ይኸው ነው። ፕሮጀክቱ ተግባራዊ በሆነባቸው አካባቢዎች የሚመረተውን የወተት ምርት የምንሰበስባቸው ማቀዝቀዣ ያላቸው ትልልቅ 15 ቦቲ መኪናዎች ገዝተን አቅርበናል። በየእለቱ አነስተኛ ገበሬዎች የሚያመርቱትን ወተት እየተሰበሰቡ ወደ ገበያ የሚሰራጭበት ሁኔታ ፈጥረናል። የእኛ ሚና የነበረውም አምራቹን ከገበያው ጋር የማስተሳሰርና ግብዓት ማቅረብ ነው። እንደሃገር በርካታ ተመሳሳይ ተሽከርካሪዎችን ማዘጋጀት ይገባል፤ ሆኖም የኢኮኖሚ አቅማችን ውስን በመሆኑ እንደሚፈለገው ማቅረብ አልተቻለም። እኛ ባገኘናት ብድር የተመሰረተውን ወተት ወደ ገበያ የምናደርስበት ሁኔታ ፈጥረናል። በእርግጥ አንዳንድ ክልሎች ላይ ለዚህ ዓላማ የተገዛውን ተሽከርካሪ ለሌላ ስራ ሲያውሉት ይስተዋላል። ይህንን የሚቆጣጠር አካል ያስፈልጋል። ሲጀመርም በቂ ባለመሆኑ ተጨማሪ መኪኖች ሊኖሩ ይገባል።
አዲስ ዘመን፡- የፕሮጀክቱ የመጀመሪያ ምዕራፍ ወደ መጠናቀቁ ደርሷል፤ ቀጣዩ ሥራ ምን እንደሆነ ይግለፁልንና ውይይታችንን እናብቃ?
ዶክተር ቶማስ፡- እንዳልሽው የእንስሳትና ዓሳ ሃብታችንን ምርታማነት ለማጎልበት በዓለም ባንክ ድጋፍ ላለፉት ስድስት ዓመታት ሲተገበር የቆየው ይህ ፕሮጀክት የመጀመሪያው ምዕራፍ ሊጠናቀቅ የቀናት እድሜ ነው ያለው። ሁለተኛው ምዕራፍ ለመጀመር ፕሮፖዛል ነድፈን አቅርበናል፤ አስፈላጊው ቅድመ ሁኔታዎችም ተመቻችተዋል። ስለዚህ ፕሮጀክቱ ከፀደቀና ብድሩ ከተገኘ ዘርፉን አሁን ካለበት በላቀ ደረጃ በማሳደግ ሃገሪቱ ባላት ሃብት በተጨባጭ ተጠቃሚ የሚያደርጋት ስራ ይሰራል የሚል እምነት አለኝ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ለሰጡን ማብራሪያ በዝግጅት ክፍሉ ስም ከልን አመሰግናለሁ፡፡
ዶክተር ቶማስ፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ሰኞ ሐምሌ 1 ቀን 2016 ዓ.ም