መጤ ተምችን የመከላከል ሁሉን አቀፍ ጥረት

መነሻውን መካከለኛው አሜሪካ ያደረገው መጤ ተምች እ.ኤአ 2016 ላይ አፍሪካ መድረሱን መረጃዎች ይጠቁማሉ። ተምቹ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ በኩል ገብቶ በስድስት ወራት ውስጥ መላ ሃገሪቱን ማዳረሱ ይታወሳል።

ተምቹ በተለይም ምድር ወገብ አካባቢ ያሉ አካባቢዎችን በስፋት አጥቅቷል። በእነዚህ አካባቢዎች ዓመቱን ሙሉ ዝናብ የማይቋረጥ መሆኑ ለተምቹ መስፋፋት ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረለትም የግብርና ባለሙያዎች ያስረዳሉ።

የግብርና ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያመለክተው፤ መጤ ተምቹ ከ25 እስከ 30 ባሉት ቀናት ውስጥ ብቻ ከእንቁላል ተነስቶ ቢራቢሮ መሆን ይችላል። በመሆኑም በተለይ እንደበቆሎ ያሉና በሶስት ወር የሚደርሱ ሰብሎች ቶሎ በተምቹ የሚመቱ በመሆኑ ሙሉ ለሙሉ የመውደም እድላቸው ሰፊ ነው።

ባለፉት ሶስት ዓመታት ግብርና ሚኒስቴር፣ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ከዓለምቀፍ ኢንሴክት ፊዚዮሎጂና ኢኮሎጂ ማዕከል (ኢሲፔ) ጋር በመተባበር ተምቹን የመከላከል ዘመቻ አካሂደዋል። ይኸው ከአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ድርጅት (US­AID) በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ አማካኝነት ሲተገበር የነበረው ፕሮጀክት የጊዜ ገደቡን አጠናቆ ከሰሞኑ የመዝጊያ መርሃ ግብር በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ተካሂዷል።

የፕሮጀክቱ አስተባባሪና በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የሆለታ ማዕከል የነፍሳት ተባይ ተመራማሪ ዶክተር ግርማ ደምሴ በተለይ ለ‹‹አዲስ ዘመን ጋዜጣ›› በሰጡት ማብራሪያ፤ መጤ ተምቹ ወደ ኢትዮጵያ ሲገባ መጀመሪያ ላይ የደቡብ ኢትዮጵያ ክፍልን ነው ያጠቃው፤ ስምንት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ደግሞ መላ ሃገሪቱ ላይ ተስፋፍቷል።

የጉዳት መጠኑ በተወሰነ መልኩ ደጋ አካባቢ ላይ አነስ ቢልም አጠቃላይ በሃገሪቱ የበቆሎ ምርት ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል። በሃገሪቱ ወይና ደጋና ቆላ አካባቢዎች ላይ ከፍተኛ ጥፋት ያስከተለ ሲሆን፣ በተለይም በበቆሎ ምርት ላይ መጠነ ሰፊ ጉዳት አምጥቷል።

ይህን አደገኛ ተምች (ትል) ለመከላከል ባለፉት ሶስት ዓመታት መንግስት ሰፊ ርብርብ ሲያደርግ መቆየቱን ዶክተር ግርማ አመልክተው፤ ‹‹ ለእዚህም የኢትዮጵያ መንግስት ከአራት ቢሊዮን ዶላር በላይ ወጪ አድርጓል፤ ያም ቢሆን 36 በመቶ የሚሆን ምርት ብክነት አጋጥሟል፤ ይህም ሃገሪቱ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በምታደርገው ጥረት ላይ ጫና ፈጥሯል›› ሲሉ ያብራራሉ። ይህም መሆኑም የአርሶ አደሩ የምርት ወጪ ከፍ እንዲል ማድረጉን ጠቁመው፤ መንግስት የመጤ ተምቹን አደገኛነት በመገንዘብ ፀረ- ተምች መድሃኒቶችን ለአርሶ አደሮቹ በነፃ እስከመስጠት የደረሰበት ሁኔታ መኖሩን ያብራራሉ።

‹‹ዓለም አንድ መንደር ሆናለች፤ በዚህ የተነሳ ከፍተኛ የንግድ እንቅስቃሴና የሰዎች ከቦታ ቦታ ዝውውር በመኖሩ መጤ ተምቹ ከደቡብ አሜሪካ ተነስቶ መላ ዓለምን አዳርሷል›› የሚሉት ዶክተር ግርማ፣ መጤ ተምቹ በባህሪው በፍጥነት የሚዛመት መሆኑን አስታውቀዋል፤ በዚህ የተነሳም ጎረቤት ሃገራት ቢቆጣጠሩትም እንኳ አንዴ ከገባ በኋላ ሙሉ ለሙሉ ማጥፋቱ አዳጋች መሆኑን ያመለክታሉ። ‹‹በተለይ አዲሱ መጤ ተምች ድንበር ዘለልና ብዙ ኪሎ ሜትሮችን የመብረር አቅም እንዳለው ጠቅሰው፣ ‹‹ኢትዮጵያ ብቻዋን የመከላከልና የመቆጣጠር ስራ ብትሰራም ጎረቤት ሃገራት ካልተከላከሉ ሙሉ ለሙሉ ማጥፋት አይቻልም›› ይላሉ።

የመከላከል ስራው በትብብር መስራትን እንደሚጠይቅ አስታውቀው፣ ለእዚህም የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ከአገር በቀልና ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር በትብብር እንደሚሰራ ይገልፃሉ። የተቀናጀ ስራ ካልተሰራ ተምቹን መከላከልም ሆነ የሚያደርሰውን ጉዳት መቆጣጠር አይቻልም ብለዋል። በተለይ በዘርፉ የሚወጡ የምርምር ወጤቶችን፤ ቴክኖሎጂዎችንና መረጃዎችን ለሌሎች ሃገራትም የሚጠቅም መሆን አለበት ሲሉም ጠቅሰው፣ በዚህ መሰረት ፕሮጀክቱ ከአምስት ባላነሱ የአፍሪካ ሃገራት ላይ ተግባራዊ በማድረግ ተምቹን የመከላከል ስራ ሲከናወን መቆየቱን አስታውቀዋል።

እሳቸው እንዳሉት፤ ኢንስቲትዩቱ ባለፉት ሶስት ዓመታት ተምቹን መከላከል በሚያስችሉ ምርምሮች ላይ አተኩሮ ሲሰራ ቆይቷል። ከዚህ ቀደም በነበረው ተሞክሮ ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ ተምቹ በኬሚካል /ፀረ-ተባይ መድሃኒቶች/ ለማጥፋት ጥረት ይደረግ ነበር። ይሄ ኬሚካል በሰው፤ በከርሰ ምድርና በአየር ንብረት ላይ የሚያመጣው ጉዳት በመኖሩ የጥቅሙን ያህል ጉዳትም ያስከትላል። በመሆኑም የሰውንም ሆነ የአካባቢውን ደህንነት መጠበቅ የሚያስችል የተቀናጀ ተምች የመከላከልና የመቆጠጠር ስርዓት ተዘርግቷል። በከፊል ፀረ-ተምች ኬሚካሉን በመጠቀም በከፊል ደግሞ በተፈጥሮ የመከላከል ሥራ መስራት ወሳኝ ይሆናል።

ይህም የተቀናጀ የመከላከልና የመቆጣጠር ስራ በዋናነትም ተፈጥሮዊ በሆነ መንገድ ማለትም ፀረ ተምች የሆነ የሳር ዝርያን በማሰራጨትና ኬሚካል በመጠቀም ሲሰራ መቆየቱን ጠቅሰው፤ በተለይ የኬንያን ተሞክሮ በመውሰድ ደህንነቱ የተጠበቀ የመከላከልና ቁጥጥር ሥርዓት መዘርጋት መቻሉን ይጠቅሳሉ። በአሁኑ ወቅት ሙሉ ለሙሉ ተምቹን ማጥፋት ባይቻልም የመከላከል አቅም ግን ማጎልበት መቻሉን አስታውቀዋል። በቀጣይ ቴክኖሎጂውን በስፋት የማድረስ ስራ እንደሚሰራ ዶክተር ግርማ አመልክተው፤ ለእዚህም የአጋር ተቋማትና ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

የተምቹ በጥፍነትና በስፋት መሰራጨት ችግሩ በኢትዮጵያ አቅም ብቻ እንደማይፈታ እንደሚያመላክትም ጠቅሰው፣ እንደ የአሜሪካ የበጎ አድራጎት ድርጅት፣ የአውሮፓ ሕብረት፣ የደቡብ ኮሪያ መንግስትና የዓለም አቀፍ የምግብና እርሻ ድርጅት (ፋኦ) ከመሳሰሉ ጋር እየተሰራ መሆኑን ያስረዳሉ። ‹‹በዚህ የተቀናጀ የመከላከል ሥራ አርሶ አደሩን በማንቃት፣ በማሰልጠን፤ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን በማውጣት፤ የክትትልና የቅድመ ትንበያ መረጃ ዲጂታል በሆነ መልኩ በአስቸኳይ እስከ ቀበሌ ድረስ እንዲደርስ የማድረግ ሰራ መከናወኑን ጠቅሰዋል፤ ‹‹በዚህም ጥሩ ውጤት እየተገኘ ነው፤ ጉዳቱንም እየቀነስን ነው›› ይላሉ።

‹‹ይሄ ማለት ግን ሙሉ ለሙሉ ማጥፋት የሚቻልበት ደረጃ ተደርሷል ማለት አይደለም›› ሲሉ ተናግረው፣ ‹‹በአሜሪካ እንኳ ሶስት ዓመት ቆይቷል፤ እኛ ሃገር ደግሞ የአየር ሁኔታው ለተምቹ መስፋፋት የሚመች በመሆኑ እየተከላከሉ መኖር ነው የሚያዋጣው›› ሲሉም ያክላሉ። መንግስት በያዘው መንገድ የመከላከሉን ሥራ አጠናክሮ መቀጠል እንደሚጠበቅበት አሳስበው፤ ተመራማሪውም የተሻለ ቴክኖሎጂ በማውጣት ላይ ርብርቡን ማጠናከር እንደሚገባው ያስገነዝባሉ፡፡

ዶክተር ግርማ እንዳብራሩት፤ ኢንስቲዩቱ ቴክኖሎጂዎችን በማፍለቅ ረገድ ትልቅ ኃላፊነት አለበት፤ ቴክሎጂዎቹን ከሼልፍ አውርዶ ለአርሶ አደሩ ተደራሽ በማድረግ ረገድ የባለድርሻ አካላት ያልተቋረጠ ርብርብ ማድረግ ያስፈልጋል። የመከላከሉ ስራ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት የሚጠይቅ በመሆኑና ከሃገሪቱም የቆዳ ስፋት አንፃር በመንግስት አቅም ብቻ የማይቻል በመሆኑ ቴክኖሎጂውን የማባዛትና ለአርሶአደሩ የማሰራጨት ሥራው የሁሉንም እገዛ ይሻል።

በግብርና ሚኒስቴር የተምች አሰሳ ጥናትና ክትትል ባለሙያ አቶ አስቻለው ጀማነ እንደሚገልፁት፤ የመጤ ተምች ወረርሽኙን በመከላከል ረገድ ሚኒስቴሩ ለቀበሌና ወረዳ ባለሙያዎች ስልጠና በመስጠት፤ የግብርና ባለሙያዎች ከአርሶ አደሩ ጋር በመሆን መረጃዎችን የማጠናከር ሥራዎች እየተሰሩ ናቸው። አሁን ባለው ሁኔታ ከሁለት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ሄክታር በላይ ከሆነው የበቆሎ ማሳ ውስጥ ወደ አንድ ነጥብ ስድስት ሚሊዮኑ ላይ የዳሰሳ ጥናት ተደርጓል። በዚህ ጥናት መሰረት 450 ሺ የሚሆነው ሄክታር በመጤ ተምቹ መጠቃቱን ለማወቅ ተችሏል።

ከዚህ ውስጥ በ309 ሺ ሄክታር ላይ ያለውን ተምች በሁለት መንገዶች የመከላከል ሥራ መሰራቱን ገልጸዋል፤ የመከላከል ስራው አንደኛው በባህላዊ መንገድ፣ ሁለተኛው ደግሞ በኬሚካል ርጭት መካሄዱን ጠቅሰዋል። በባህላዊ ዘዴ አርሶ አደሩ በራሱ ያካበተውን እውቀት በመጠቀም እንዲሁም ሰብልን ከሌላ አዝዕርት ጋር አሰባጥሮ በመዝራት መጤ ተምቹ እንዳይዛመት ጥረት መደረጉንም ይጠቁማሉ። አርሶ አደሩ በልምድ አሸዋ፣ አፈር፣ ውሃ የመሳሰሉትን የተክሉ ሙሽራ አካል ላይ በማስቀመጥ ተምቹ ሕልውና እንዲያጣ የሚደረግበት ባሕላዊ ዘዴ እንዳለውም ገልጸዋል።

መጤ አረሙ በገባባቸው ሶስት ዓመታት ማለትም ከ2009 እስከ 2011 ዓ.ም በተከታታይ በተካሄደ ጥናት ተምቹ 36 በመቶ የምርት ቅነሳ እንዲመጣ ምክንያት መሆኑን ለማወቅ ተችሏል ሲሉ አቶ አስቻለው ይናገራሉ። በመንግስት በኩል ተምቹን ለመከላከል ከፍተኛ ጥረት ቢደረግም ሊቀንስ ያልቻለው በተምቹ ባህሪ እንደሆነ ያስረዳሉ።

ዓለም አቀፍ ጥናቶች ጠቅሰው እንደተናገሩትም፤ ተምቹ ሊመገባቸው የሚችሉ ከ353 በላይ እፅዋቶች አሉ፤ በኢትዮጵያ ረገድ ደግሞ በቆሎ፣ ማሽላ፣ ስንዴና ጥቅል ጎመን ላይ ነው እየተከሰተ ያለው። ተምቹ በበጋ ስንዴ እና አትክልትና ፍራፍሬ በሚያለሙ አካባቢዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያስከተለ ስለመሆኑም ጠቁመዋል።

በቅርቡ የተሰራ የቅድመ ትንበያ ጥናትን መሰረት አድርገውም ሲያብራሩ እ.ኤአ እስከ 2080 ተምቹን ከዓለም ሙሉ ለሙሉ መጥፋት እንደማይችል አስታውቀዋል። ‹‹የፈለገውን ያህል ጥረት ቢደረግ የሃገሪቱ የአየር ንብረትና ምቹ ሁኔታ ለተምቹ መስፋፋት ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል፤ በዚህም የተነሳም ተምቹን ሙሉ ለሙሉ ማጥፋት አይቻልም፤ በመሆኑም ተምቹ እያለ ጉዳቱን እየተከላከልን፤ ምርቱ እንዳይቀንስ በምናደርግባቸው ሁኔታዎች ላይ ትኩረት አድርገን እየሰራን ነው ያለነው›› ሲሉ ያስረዳሉ። የተለያዩ የመከላከያ ዘዴዎችን በአንድ ላይ በማቀናጀትና በመተግበር ጉዳቱ የከፋ እንዳይሆን እየተደረገ ያለው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ያመለክታሉ።

ናይሮቢ የሚገኘው ዓለምቀፍ ኢንሴክት ፊዚዮሎጂና ኢኮሎጂ ማዕከል (ኢሲፔ) ተወካይ ሪቾ ኦቪኖ እንደሚናገሩት፤ ማዕከሉ በተምችና መሰል ዕፅዋትን የሚያጠቁ ነፍሳት ላይ ምርምር ያደርጋል። በኢትዮጵያ ላለፉት ሶስት ዓመታት ሲተገበር የቆየው ፕሮጀከት ማህበረሰቡን በማስተባበር ይህን በቆሎና የመሳሰሉትን የአገዳ ሰብሎች በስፋት የሚያጠቃ ተምች አስቀድሞ የመከላከልና ከተከሰተ በኋላ እንዳይሳተፉ የመቆጣጠር ሥራ ሲያከናውን ቆይቷል።

ፕሮጀክቱ በዋናነት ሰብል አምራች የሆኑ የኢትዮጵያ አርሶ አደሮችን አቅም ማጎልበት ላይ ትኩረት አድርጎ ሲሰራ መቆየቱን ጠቅሰው፣ ‹‹ፎላሚ›› የተባለው ይህ መጤ ተምች በሰብሎቻቸው ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት ከወዲሁ አውቀውና የመከላከል ዘዴውን እንዲቀስሙ ሰፊ ጥረት ሲደረግ ነበር ብለዋል።

እንደ ተወካይዋ ማብራሪያ፤ አርሶ አደሩ የመሬቱን ምርታማነት ለማጎልበት ከፍተኛ ወጪ በማውጣት ማዳበሪያ ይገዛል፤ የአየር ንብረት ለውጡንም ለመቋቋም ሲል ቀን ከሌሊት ይደክማል። ይህ በሆነበት ሁኔታ ተምቹ የሚያመጣውን ጉዳት መቋቋም ስለሚያቅታቸው ወደ ተስፋ መቁረጥ ውስጥ የሚገቡበት ሁኔታ አለ።

ይህም ስራ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በምስራቅ አፍሪካ ባሉ ሃገራትና በደቡብ አፍሪካ፤ ዛምቢያና ማላዊ እየተከናወነ መሆኑን ተወካይዋ ጠቅሰው፣ በኢትዮጵያም አምቦ፣ ባኮ፣ መልካሳና ሃዋሳን ጨምሮ በሰባት የተለያዩ አካባቢዎች ላይ እየተተገበረ መሆኑን አመልክተዋል። በእነዚህ ዓመታት በተለይ በቆሎ አምራች የሆኑ አርሶአደሮች በተምቹ እያደረሰባቸው የነበረውን ጉዳት ለመቀነስ ሰፊ ርብርብ መደረጉን ያስረዳሉ፡፡

ከኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር ‘ዲስሞዲየም’ና ‘ብራኬሪያ’ የተሰኙ የሳር ዝርያዎችን አርሶአደሩ በማሳው ከሰብሉ ጎን በመትከል ተምቹ እንዳይራባ የማድረግ ሥራ ሲሰራ መቆቱን ይጠቁማሉ።

እሳቸው እንዳሉት፤ በተለይም ሞዴል አርሶአደሮች ማሳ ላይ ሳሩን በመትከል ለሌሎች ተሞክሮ እንዲያካፍሉ ተደርጓል። ይህ ማለት ግን አርሶአደሩ ተምቹን የሚከላከልበት ነባርና ባህላዊ ዘዴ እንዲተው አይገደደም፤ ይልቁንም ጎን ለጎን ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን እንዲጠቀም ነው የተደረገው።

ስለ ተምቹ ባህሪና ስለመከላከያ ዘዴው ግንዛቤ የማስጨበጡ ሥራ በቀጣይም መሰራት እንደሚገባው ያስገነዝባሉ። ‹‹ከአርሶአደሩ ጀምሮ እስከ ፖሊሲ አውጪው ድረስ የተምቹን አደገኛነት እንዲገነዘቡ ማድረግ ያስፈልጋል፤ ግንዛቤው ሲኖር ነው የመከላከል ሥራው ውጤታማ ይሆናል›› በማለት ነው የተናገሩት።

የወለጋ ነዋሪው ሞዴል አርሶአደር አስፋው ረታ፤ በቆሎ በአካባቢያቸው በስፋት ከሚመረቱ ሰብሎች መካከል ዋነኛው እንደሆነ ጠቅሰው፤ ከአራት ዓመታት ወዲህ ግን በመጤ ወረርሽኙ ምክንያት ምርቱ በከፍተኛ መጠን መቀነሱን ያመለክታሉ። ‹‹ፕሮጀክቱ በአካባቢያችን መተግበር ከመጀመሩ በፊት በተምቹ ምክንያት ብዙ የደከምንበት የበቆሎ ማሳ ውድመት ደርሶበት ነበር›› ሲሉ አስታውሰው፣ ይሁንና ፕሮጀክቱ መተግበር ከጀመረ ወዲህ በተምቹ ዙሪያ የነበራቸው ግንዛቤ በመጨመሩና የመከላከል ስራውም በባለሙያ የታገዘ እንዲሆን በመደረጉ የምርቱ መጠን ከፍ እያለ መምጣቱን አስታውቀዋል።

በተለይም የተምቹን እድገት የሚያጨናግፉ የሳር ዝርያዎችን በማሳቸው ላይ መትከል ከጀመሩ ወዲህ ምርታማነት መጨመሩን፤ የእርሳቸውን ተሞክሮ ለሌሎች አርሶአደሮች በማካፈልና የሳር ዝርያውን በማባዛት ተምቹ ከአካባቢው እስኪጠፋ ድረስ የበኩላቸውን ጥረት እያደረጉ ስለመሆኑ ሞዴል አርሶአደሩ ተናግረዋል። የሳር ዝርያውን በግላቸው እያባዙ ለግብርና ሚኒስቴር በመሸጥ እንዲሁም ለከብት መኖ በማዋል ተጠቃሚ መሆናቸውንም ተናግረዋል። የሳር ዝርያ እጥረት መኖሩን ጠቅሰው፤ በተለይ አባዥ ተቋማት ድጋፍ እንዲያደርጉ አርሶ አደሩ ጠይቀዋል።

ማህሌት አብዱል

አዲስ ዘመን ሰኞ ሐምሌ 1 ቀን 2016 ዓ.ም

 

Recommended For You