ትዮጵያዊነት በአብሮነት የቆነጀ የሕብረብሄራዊነት ውበት እንደሆነ ብዙዎች ይስማሙበታል። ብዝሀነትን እንደውበት እና እንደኃይል ተጠቅመን እልፍ የጋራ ታሪኮችን ጽፈናል። ዛሬ ላይ ከፊት ጎልተው በመታየት የክብርና የሉአላዊነት ቀለም ከሆኑን ውስጥ ቀዳሚዎች እነዚያ የጋራ ትስስሮቻችን ናቸው። ውበት የሚለው ጽንሰ ሀሳብ በአንድ ብቸኛና ነጠላ እውነት በኩል የማይነጸባረቅ ከብዙሀነት ውስጥ የሚፈልቅ የጋራ መልክ ነው፡፡
ብዙሀነት ውስጥ ኢትዮጵያዊነትን ሳንዶል እንዴትም ብናስብ ልክ አንሆንም። ልክነታችን ያለው ኢትዮጵያ ብለን ስንጀምርና ስንጨርስ ነው። ለመግባባትና አብሮነትን ለማስቀጠል የጀመርናቸው የውይይትና የእርቅ መድረኮች በአብሮነት ኢትዮጵያን እንድናስቀጥል፣ በብዙሀነት ውስጥ የሚንጸባረቅን ነጠላ ትርክት ለማስቀረት፣ ልዩነቶችን በኃይል ሳይሆን በምክክር የማርገብ ባህልን በማዳበር ከሁላችን ለሁላችን የሆነን ዓላማ ለመፍጠር ነው፡፡
ከሁላችን ለሁላችን የሆነ ትርክት ቡዳኔ የሌለው፣ ወገንተኝነት የማይንባረቅበት፣ በኢትዮጵያዊነት የወል ስም የሚጠራ የብዙሀነት ቀለም ነው። ማንንም ከኋላና ከፊት ሳያቆም አብረን ጀምረን አብረን እንድንጨርስ የሚያደርግ የእኩል አስተሳሰብ ዝማኔ ነው። የጋራ እውነት አጥተን እየተገፋፋን ያለነው ውስጣችን በገቡ የብሄር አስተሳሰቦች ስለመሆናቸው የሚጠፋን አይደለም። በገዘፈና በገነነ ኢትዮጵያዊነት ውስጥ ብሄር ተኮር ነጣጣይ ትርክት እንዴት ገባ ብለን ስንጠይቅ ብዙ ምክንያቶችን እናገኛለን፡፡
እንደዋነኛ ምክንያት የሚጠቀሱት ግን በፖለቲካው ምህዳር ዙሪያ የሚታዩ የብኩርና ግፊያዎች ናቸው። እኚህ የብኩርና ግፊያዎች በእልህና በማንአለብኝነት ደልበው ኢትዮጵያዊነትን ያወየቡ የእኩይ ትሩፋት ውጤቶች ናቸው። ይሄ ማለት ምክክርና የሀሳብ የበላይነት የሌለባቸው፣ በቂም በቀል የበሰሉ፣ ስልጣንንም ሆነ ፍላጎትን በኃይል ለማሳካት ከሚደረግ ግብግብ የሚወጡ አፍራሽና አምካኝ ሰጣ ገባዎች የሚጠቃለሉበት ነው። ዛሬ ላይ ብሄራዊ ምክክር ብለን ኮሚሽን አቋቁመን፣ በጀት መድበን፣ ቅድመ ዝግጅቶችን አድርገን ዓመታትን በፈጀ እንቅስቃሴ ለውይይት ስንቀመጥ በጥላቻ የተነጠቅናትን ኢትዮጵያ ለማስመለስ፣ በጦርነት የተጎሳቆለ ሕዝባችንን ነጻ ለማውጣት ነው፡፡
የሚሰማኝ ቢኖርና የእኔን የታናሹን ምክር የሚሰማ ቢኖር ኢትዮጵያን ነጻ እናውጣ ስል እናገራለው። ኢትዮጵያ ነጻ የምትወጣው በጦር መሳሪያ ብዛት፣ በእርስ በርስ ጦርነት፣ በወንድማማኞች መገፋፋት አይደለም። ሕዝባችን ነጻ የሚወጣው በቂምና በቀል፣ በጥላቻና በዘረኝነት አይደለም። ሀገር ነጻ የምትወጣው ምክክርን ባህል ባደረገ ሕዝባዊ ተሞክሮ ነው። ሕዝብ የመከራ ቀንበሩን የሚጥለው ፖለቲካው ካሸከመው የጦርነትና የእርስበርስ ግጭት ሲርቅ ነው። ከሰላሳ ዓመታት ለራቀ ዘመን ሕዝባችን የጦርነት ቀንበርን በጫንቃው ላይ ተሸክሟል። ትውልዱ በዘር ተቧድኖ ኢትዮጵያዊነትን ሰውሮ ሰንብቷል፡፡
የዚህ ዓላማ አትራፊዎች ፖለቲከኞቻችንና ጥቂት ቡድኖች መሆናቸው ሳይታለም የተፈታ ቢሆንም ሲሰነብት ግን እዳው ለሁላችንም የሚተርፍ ነው። ሕዝብ የሌለበት ፖለቲካ፣ ለትውልዱ የማይወግን ፖለቲከኛ ከሰራው በጎ ነገር ይልቅ መታወሻው ያጠፋው ትንሽ ጥፋት ነው። የዘር ፖለቲካ በዓለም ላይ እነማንን ምን እንዳደረገ የምናውቅ ነን። ከአውሮፓ ጀርመንና አይሁዳውያንን ከአፍሪካ ደግሞ ሩዋንዳን ምን ያክል ዋጋ እንዳስከፈለ የቅርብ ዜናችን ነው። በተመሳሳይ መልኩ ብዙሀነትን እንደ ድልና እድል በመውሰድ ሀገራቸውን ያሻገሩ እንደ ህንድና ናይጀሪያ ያሉ በርካታ ሀገራትን ማንሳት ይቻላል፡፡
ሕንድ በዓለም ላይ ከ200 ለራቀ ዓመታት ከማንም ጋር ጦርነት ያልገጠመች ብቸኛዋ ሀገር ናት። ይሄ ሰላም ወዳድ ጥንካሬዋ ብዙሀነት የሌለባት የአንድ ቋንቋና የአንድ ብሄር መገኛ ስለሆነች የሆነ አይደለም። የሚገርመው ነገር ሕንድ ውስጥ ከ700 በላይ የተለያዩ ቋንቋዎች በተለያዩ ብሄሮች ይነገራሉ። እኚህ ሁሉ ቋንቋዎች ግን የበላይና የበታች ሳይሉ ቅድሚያ ለሕንድ በሚል መርህ የጸኑ ስለሆኑ ነው። 700 የሚደርሱ የተለያዩ ቋንቋዎች በባህል፣ በስርዐት፣ በወግ፣ በልማድ ተለያይተው በሀገር ጉዳይ ግን ተመሳስለው ይኖራሉ። ናይጀሪያም እንዲሁ የተለያዩ ብሄረሰቦች በተለያየ ማንነት በኩል እናት ሀገራቸውን ከፊት አድርገው የሚኖሩባት ሀገር ናት፡፡
እኛ ሀገር ሲሆን ነገሮች ለምን እንደሚቀየሩ ባይገባኝም ቅድሚያ ለኢትዮጵያ ማለት በሚያስችል ፖለቲካዊ ስነልቦና ውስጥ ስላልዳበርን እንደሆነ ግን አፌን ሞልቼ መናገር እችላለው። ብሄራዊ ምክክር ይሄን አይነቱን ልምምድ በማስቀረት የሀሳብ የበላይነትን በማስረጽ ትውልዱ ተነጋግሮ የሚግባባበትን፣ ፖለቲከኞች ከጦርነት በፊት ሰላም የሚፈጥሩበትን አዲስ የተሀድሶ አቅጣጫን መቅደድ ነው። እንደሀገር አይደለም እንደግለሰብ እንኳን ልዩነት የማይቀርና የሚፈጠር ጉዳይ ነው። የሀሳብ ልዩነት፣ የፍላጎትና የፖለቲካ ልዩነት እንዲሁም የአመለካከትና ልዩነት በየትም ቦታ ያለ ክስተት ነው። ቁም ነገሩ ግን እነዚህ ልዩነቶቻችን ለጦርነት በር ከፋች እንዳይሆኑ ማድረጉ ላይ ነው። ከተቻለ ለበረከት ካልተቻለ ግን ለመርገምት መንስኤ እንዳይሆኑን በመነጋገር መፍትሄ መስጠት መቻል ይጠበቅብናል፡፡
አንዳንዶች የልዩነትን በየትም ቦታ መኖር ሲገልጹ፤ ‘ሰው ከሰው አይደለም እግር ከእግር ራሱ ይጋጫል’ ይላሉ። ልዩነት የትም አለ። የትም መኖሩ አንዳችን ከአንዳችን በሀሳብ፣ በአረዳድ፣ በእውቀት የተለያየን መሆኑን የሚያመላክት እንጂ እኔ ያልኩት ካልሆነ በሚል ለጦርነት የምንነሳበት አይደለም። ልዩነቶቻችንን በስክነት ካየናቸው ብዙ ዋጋ የሚያወጡ የልማትና የእድገት ምንጭ መሆን የሚችሉ ናቸው። በስክነት ስለማናያቸው ግን ለጦርነትና ለግጭት በር ከፋች ሆነው ዋጋ እያስከፈሉን ይገኛሉ፡፡
ግጭት ሳይሆን ፍጭት ነው የሚያስፈልገን። የሀሳብ ፍጭት ከመቼውም ጊዜ በላይ የመከራዎቻችን ማስታገሻ ሆኖ የሚመጣ ነው። በሀሳብ ተፋጭተን የጋራ ቤት ካልሰራን በግጭት የምናተርፈው ትርፍ አይኖርም። ኢፒክፌተስ የተባለ ፈላስፋና ደራሲ ‹ወሳኙ ነገር የገጠመን ነገር ሳይሆን ለገጠመን ነገር ምላሽ የምንሰጥበት መንገድ ነው› ይለናል። ከዚህ የፈላስፋ እይታ ተነስተን የሀገራችንን ነባርና አሁናዊ ሁኔታዎቻችን ብንቃኝ ችግር ፈቺ በሆኑ የመፍትሄ ሀሳቦች ላይ ከማተኮር ይልቅ ችግሩ ላይ ማተኮራችን ልቆ ይገኛል፡፡
ያለፉት ጊዜዎች በጦርነት ላይ ጦርነት የሆኑብን ጦርነትን የሚሽር አስታራቂና አግባቢ ሀሳብ ማመንጨት ተስኖን ችግር ፈጣሪ ሆነን ስለሰነበትን ነው። ችግርን ማሰብ ችግር ከመፍጠር ባለፈ መፍትሄ አያመጣም። ትላልቆቹን የስነ ልቦና ጠበብቶች ጨምሮ ስለሕይወትና ፖለቲካ ጥልቅ መረዳት ያላቸው አዋቂዎች ሰላምን ከችግር ርቆ በተቀመጠ የእርቅና የተግባቦት አእምሮና ልብ በኩል ይገልጹታል። ሲያክሉም ችግሩን በፈጠረ ጭንቅላት መፍትሄ እንደማይመጣ በመናገር ራስን ለእርቅና ለጋራ ሰላም ባዘጋጀ መንፈስ ለመተቃቀፍ መጠጋጋት አዋጪ እንደሆነ ይናገራሉ።
እንደባለሙያዎቹ ገለጻም ሆነ እንደግል እይታ ሰላም ሰላማዊ አካባቢ ይፈልጋል። ጦርነት በቃን፣ ቂምና በቀል በቃን፣ ጥላቻና መገፋፋት ይብቃን፣ እኛ ወንድማማቾች ነን፣ እኛ ኢትዮጵያዊ ነን፣ እኛ በጋራ ታሪክ ያበብን የብዙሀነት ዘሮች ነን ብለን የተነሳን እለት የሚመጣ ከሁላችን ለሁላችን የሆነ መንፈስ ነው። እዚህ ሰላም ፈልገን፣ እዚያ እልህ ይዘን፣ ፖለቲካው ሳይጠራ፣ ፖለቲከኞቻችን ሰላም ሰባኪ ሳይሆኑ ሰላም አይመጣም። ሰላምን የምንፈልግ ከሆነ በአብሮነት ወደድሮነት መጓዝ አለብን። ድሮነት በአንድ ስም የተጠራንበት፣ በአንድ ሽክና የጠጣንበት፣ በዋርካዎቻችን ጥላ ስለኢትዮጵያ የመከርንበት የትዝታ ሰነዳችን ነው። በአብሮነት ወደድሮነት ስል መምጣቴም ለዚያ ነው፡፡
ዘመን የድሮነት ቀለም ከሌለው፣ ትውልድ የአባቶቹን የወዳጅነት ፈለግ ካልተከተለ ምን ቢሰለጥን ስይጥንና አያጣውም። በስልጣኔ ውስጥ ሰይጥነን የቆምነው የድሮ የፍቅር ኮቴዎቻችንን ስለሻርን፣ የመጣንባቸውን የአብሮነት ሰርጦች ስለተውን ነው። የኋላው ከሌለ የለም የፊቱ እንዲሉ…መነሻዎቻችን ለመድረሻዎቻን ፈርቀዳጆች ሆነው የሚወሱ ናቸው። ዛሬ ላይ የለመለመው የብሄርተኝነት ቀንበጥ እንዴት መጣ? ለምን መጣ? በማን መጣ? ስንል ድሮነትን በሻሩ አእምሮና ልቦች እንደሚሆን እናምናለን፡፡
በአብሮነት ወደድሮነት ኢትዮጵያዊነትን የሚመልስ፣ ወንድማማችነትን የሚከልስ የመከራዎቻችን ማብቂያ ተደርጎ የሚወሰድ ነው። አለመደማመጥና አለመከባበር ይዞን እንጂ ለብዙዎች የጸሀይ መውጫ ምስራቆች ነበርን። ትዕቢትና እልኸኝነት ባይከልለን ኖሮ ዛሬም እንደትናንት አይኖች ሁሉ ወደእኛ ባማተሩ ነበር። የገጠሙን ችግሮች በምክክርና በውይይት ካየናቸው እዚህ ግቡ የማይባሉ ስለመሆናቸው እናምናለን። ፋፍተውና ፈርጥመው ከአቅማችን በላይ እስኪሆኑ ስለምንጠብቅ ግን ብዙ ዋጋ ያስከፍሉናል፡፡
ትርፍ በሌለው ጦርነት፣ እሴት በማይጨምር ብሄርተኝነት፣ አሸናፊ በሌለው ሰጣ ገባ፣ ክብር በማይጨምር መገፋፋት ከድጡ ወደማጡ ሆነን የከረምነው የውይይት ባህል ስላላዳበርን ነው። የውይይት ባህል በአንድ ሀገር ላይ እጅ የጠበቀ ማህበራዊ እሴት ነው። ጨዋ ትውልድ ከመቅረጽ፣ ግብረገብ ማህበረሰብ ከመፍጠርና ቅድሚያ ለሀገር የሚል ሕገመንግስት ከማርቀቅ ረገድ የማይተካ ሚና ያለው ነው። ትናንትን በርብረን ኢትዮጵያዊነት ፍቅርና አንድነት ነው የምንለው በወረስነው የአባቶቻችን የሰጥቶ መቀበል ባህላዊ ውርስ አማካኝነት ነው። ዛሬም ሰላማችንን የምናጸናበት፣ አንድነታችንን የምንመልስበት የውይይት ባህል ያስፈልገናል፡፡
በነገራችን ላይ ኢትዮጵያዊነትን ያወየቡ፣ ትናንት ላይ የሌሉ ዛሬ ላይ በዝተውና ሰፍተው የምናያቸው የሰላም ጥያቄዎች፣ የእርስበርስ ፍጅቶች፣ የዘረኝነት ነቀርሳዎች ባፈነገጡ ወይም ደግሞ ክብር ባልሰጠናቸው እሴቶቻችን መውደቅ የመጡ ናቸው። የትኛውም ነገር ችግር ለመፍጠር የራሱ መነሻ አለው። አሁን ለብዙ ዋጋ መክፈል መንስኤ የሆኑን ችግሮች በእኩይ ፖለቲካው ልምምድ የወረስናቸው መርዘኛ ልምምዶች ናቸው። እኚህን ከኢትዮጵያዊነት ያፈነገጡ ለማንም የማይበጁ ችግር ፈጣሪ ልምምዶች ለማስቀረት ሰላም መር ውይይት፣ አስታራቂና አቀራራቢ ንግግሮች እጅግ አዋጪዎች ናቸው። ከትናንት ወደዛሬ ይዘናቸው የመጣናቸውን ነውሮች በመልካም ለመቀየር ነው። ሕዝብ የሌለበት፣ ሀገርና ትውልድ የመከኑበት የብቻ ሀሳብ ችግሮቻችን ፈርጥመው እንዲያጠቁን እድል ከመስጠት ባለፈ ድል አያመጡም፡፡
በኢትዮጵያዊነት ካልደመቅን በምንም ብንደምቅ አናምርም። ያማርነው፣ አፍሪካን ነጻ ያወጣነው፣ በዓለም አደባባይ አንቱታን ያገኘነው በኢትዮጵያዊነት ስለቆምን ነው። እንግሊዞች ራሳቸውን ‘ኤንጅል ላንድ’ (የመላእክት ሀገር) ብለው የሚጠሩ ሕዝቦች ናቸው። እንግሊዝ ግን በኢትዮጵያ ያፈረች ሀገር ናት። ጣሊያኖች ራሳቸውን የስልጣኔና የዘመናዊነት ፊታውራሪ አድርገው ያወጁ ናቸው። በምድር ላይ ብቸኛ አንገት ያስደፋቻቸው ሀገር ኢትዮጵያ ናት። ከማንም በፊት ሀገርና ሕዝብ፣ ባለታሪክና ሉአላዊ ተብለን ሌላው ቀርቶ ራሳችንን በኢትዮጵያዊነት ለመጥራት እየቸገረን እንገኛለን። የሰላም ሀገር፣ የነጻነትና የፍትህ ምድር የሚል ቅጽል ስም ወጥቶልን ከወንድሞቻችን ጋር በሰላም መኖር ጠፍቶናል፡፡
በፍቅርና በውይይት ከተገመደ ብዙሀነት እጅግ አትራፊ የድልና እድል መገኛ ነው። ባለፉ ታሪኮቻችን በኩል የተንጸባረቁ ገድሎች በብዙሀነታችን በኩል የተገለጡ ስለመሆናቸው ተጠራጣሪ አይኖርም። ከዛ ዘመን የአድዋ ድልን ከዚህ ዘመን ደግሞ የሕዳሴ ግድብን ብንወስድ መነሻና መድረሻቸው ብዙሀነት እንደሆነ እናምናለን። ሰላም መር በሆነ የውይይት ባህልና ፖለቲካ ውስጥ ብዙሀነት እንከን ሆኖ አያውቅም፡፡
በክብርና በሕብረት የመጣንባቸው ዳናዎች የብኩርና ጌጥን ከትበው በነጻነት ቢያቆሙንም በጦርነትና በዘረኝነት ስም እያደበዘዝናቸው እንገኛለን። ወደፊት ለመሄድ በሚደረግ ትግል ውስጥ እንደሰላም አዋጪ መንገድ የለም። ሰላም ከሌለ ሁሉም ነገር እንዳይሆንና እንዳይረባ ሆኖ የተቀመጠ ነው። ከምንም በላይ በውይይት የዳበረ አስተማማኝ ሰላም ያስፈልገናል። ለሰላም ቅድሚያ በሚሰጥ፣ ለአብሮነትና ለብዙሀነት በሚወግን ፖለቲካና የንግግር ባህል ውስጥ ሀገርና ሕዝብ እንሁን።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵያ)
አዲስ ዘመን ሰኞ ሐምሌ 1 ቀን 2016 ዓ.ም