ለዛሬ ሃሳብ ልንቆነጥር ያሰብነው ‹‹ልሳነ ፍጥረት›› ከተባለ መሐፍ ነው። መጽሐፉ ዘ-ልዑል በተባለ ተርጓሚ የተተረጎመ ሲሆን ዋና ደራሲው ግን ታዋቂው ሳይንቲስት ፍራንሲስ ኮሊንስ ነው። ተርጓሚውን ዘ-ልዑልን እያመሠገንን ጥቂት ሃሳቦቹን ዘግነን በመውሰድ ሃሳቦቻችንን እናቀርባለን።
የመጽሐፉ ዋና ትኩረት ሳይንስና ሃይማኖት የተዛመዱ እንጂ ጠላት የሆኑ እንዳልሆኑ አበክሮ የሚገልፅ ነው። መጽሐፉ ሳይንስና ሃይማኖትን የሚያስታርቁ መረጃዎችን አጭቆ ይዟል። ብዙዎች የሳይንስ ተከታይ የሆኑ ሃይማኖትን ሲያወግዙ እናያለን። እንደዚሁም የሃይማኖት አክራሪ ሆነው ሳይንስን ሲረግሙ ውለው ሲረግሙ የሚያድሩም ብዙ ናቸው። ይሄ መጽሐፍ በሁለቱም ጥግ ላሉ ፅንፈኞች ጥሩ መረዳትን የሚያጎናጽፍ ነው። በተለይ በሳይንስና ሃይማኖት ዙሪያ የእያንዳንዳቸውን ሚና ማወቅ ለሚፈልግ አንባቢ ጥሩ መረጃ የሚያስጨብጥ መጽሐፍ ነው።
አንዳንድ ለሃይማኖት ደግ ምልከታ የሌላቸው ሰዎች ወይም አክራሪ ኢአማንያን ሃይማኖትን ጥሩ ባልሆኑ ሃይማኖተኞች ሲበይኑ እናያለን። ይሄ መጽሐፍ ይሄን በተመለከተ በገጽ 39 ላይ እንዲህ ይላል‹‹ግንዱ ምሣር ስለተሠራበት ዋርካን ታወግዛላችሁ? ውሸት በውስጡ ስለሚያሳልፍ አየርን ታወግዛላችሁ? የሞዛርትን The Magic Flute የተሰኘ ሙዚቃ በቅጡ ያልተለማመዱ ብላቴናዎችን አቀራረብ በማድመጥ ትመዝናላችሁ? በሠላማዊ ውቅያኖስ ላይ የምትጠልቀውን ፀሐይ በእውን ካላያችሁ የቱሪስት በራሪ ፅሁፎችን እንደምትክ ትወስዳላችሁ? የፆታዊ ፍቅርን ጉልበት ጎረቤታችሁ ባለው የንትርክ ጋብቻ አማካይነት ብቻ ትገመግማላችሁ? አይሆንም! የእምነትን ውለታ በተጨባጭ መገመት የሚቻለው ንፁሁንና የጠራውን ውሃ በመመልከት እንጂ በማስቀመጫው ዝጋታምነት አይደለም።››መንፈሳዊ እውነታን መንፈሳዊ ነን በሚሉ አስመሳዮች መካድ እውነታን መካድ እንደሆነ መፅሐፉ በገፅ 194 ላይም በመድገም እንዲህ ሲል ይገልጻል ‹‹የመንፈሳዊ እውነታ ንፁህ ውሃ በእነዚያ ሰብዓዊ ፍጡራን በሚባሉ የዛጉ ማድጋዎች እንደሚኖርና ከአለፍ አገደምም እነዚያ መሠረታዊ እምነቶች በከፋ ሁኔታ ሊወላገዱ መቻላቸው ሊያስደንቅ እንደማይገባ ነው። ስለዚህ የእምነት ግምገማዎን በግለሰቦች ወይም በተደራጁ ሃይማኖቶች በሚታዘቡት ባህሪያት ላይ አይመስርቱ። በምትኩ ልዕልናን በሚያጎናጽፉን፣ ጊዜ በማያነትባቸው መንፈሳዊ እውነታዎች ላይ ይመስርቱ።››
ሌላው ከሳይንስ የምንጠቀመውና የምናገኘው ነገር እንዳለ ሁሉ ሳይንስ የማይመልሰውም ብዙ ጥያቄዎች አሉ። ሃይማኖት የማይመልሰውን ሳይንስ ይመልሰዋል፤ ሳይንስ የማይመልሰውን ሃይማኖት ይመልሰዋል። ይሄን በተመለከተ መጽሐፉ በገፅ 76 ላይ ‹‹ከሳይንስ …ህይወት እንዴት ይሠራል? … ለሚለው ጥያቄ አጓጊ ምላሾችን ልናገኝ እንችላለን። ከሳይንስ ብቻ ልናገኝ ከማንችለው መልሶች ውስጥ …..ህይወት ለምን ኖረ? ለምንድነው የተፈጠርኩት?… ለሚሉት ጥያቄዎች ነው።›› ይላል።
ሳይንስ በቁሳዊ ምርምሩ ብዙ ተራምዷል። ይሄ የማይካድ ሃቅ ነው። ነገር ግን ሳይንስ ሁሉንም ያውቃል ማለት አይቻልም። ሳይንስ ተፈጥሯዊውን ዓለም ይመረምራል፤ ከተፈጥሮ በስተጀርባ ያለውን መንፈሳዊ እውነታ ግን ለመመርመር አቅም ያንሰዋል። ትዕይንተ ዓለሙንና የተፈጥሮ ሕጉን በማይናወጥ ለውጥ እየተለዋወጠ እንዲሠራ የሚያደርገውን ሚስጥር ለማወቅ ሳይንስ ብቁ አይደለም። ለዚህም ነው በመጽሐፉ በገፅ 191 ላይ ከዚህ በታች ያለውን ሃሳብ የምናገኘው ‹‹ሳይንስ ተፈጥሯዊውን ዓለም የመመርመሪያ ብቸኛ አግባብ ያለው መንገድ ነው። የአቶምን መዋቅር በመፈተሸ ይሁን የትዕይንተ ዓለሙን ተፈጥሮ ወይም የሰውን ዘረመል ድርድር ሳይንሳዊ ዘዴ የተፈጥሮ ክስተቶችን የመረጃ ፍቱንና አስተማማኝ መንገድ ነው። በእርግጥ ሙከራዎች በከፍተኛ ሁኔታ ይከሽፋሉ። የሙከራዎች አተረጓጎሞች የተሳሳቱ ሊሆኑ ይችላሉ። እናም ሳይንስ ስህተት ሊሠራ ይችላል። ነገር ግን በተፈጥሮው ሳይንስ ራሱን የሚያርም ነው። በእውቀት ዕድገት እርምጃ ፊት ሊቆም የሚችል አብይ ግድፈት አይኖርም። ቢሆንም ቅሉ ወሳኝ ጥያቄዎችን ሁሉ ለመመለስ ሳይንስ ብቻውን በቂ አይደለም።›› በማለት ይገልፃል።
እውነት ነው! የሃይማኖት ሊቃውንት፣ መንፈሳዊ የጥበብ ሰዎች በስነ ፈለግ፣ በትዕንተ ዓለሙና በራሱ የሰው ልጅ አፈጣጠርና ዕጣ ፋንታ ላይ ብዙ ተመራምረዋል። መጽሐፉ የታዋቂውን ሳይንቲስት የሮበርት ጃስትሮን ሃሳብ ተውሶ እንዲህ ይለናል ‹‹በዚህ ቅጽበት በሚመስለው ሳይንስ መቼም ቢሆን የፍጥረትን መጋረጃ ሊገልጥ እንደማይቻለው ነው። በአመክንዮ ኃይል ሲመካ ለኖረ ሳይንቲስት ታሪኩ የሚያበቃው እንደክፉ ቅዥት ነው። የድንቁርናን ተራራ ቧጥጦ ከፍተኛውን አናት ለመቀዳጀት ደርሷል። የመጨረሻውን ዓለት ተሻግሮ ብቅ እንዳለም አቀባበል ያደረጉለት በስፍራው ለዘመናት የከረሙ የሃይማኖት ሊቃውንት ነበሩ።››
መጽሐፉ በአጠቃላይ ስለዓብይ ፍንዳታ (Big Bang theory)፣ ስለዓብይ ስምዳታ (Big crunch theory)፣ ስለዲኤንኤ እና ስለአርኤንኤ ድርድሮች፣ ስለፍካሬ ልቦና (Psycho-analysis) ወዘተ ጉዳዮችን በማንሳት እንዲሁም የተለያዩ የዘርፉ ምሁራንን በመጥቀስ የሃይማኖትና የሣይንስን የማታረቅ ሃሳብ፣ አንድነትና ልዩነት በደንብ የተነተነ መጽሐፍ እንደሆነ የመጽሐፍ ሃያሲ አቶ እሸቱ ብሩ ይናገራሉ።
ይህ አጭር ጽሑፍ የመጽሐፍት አስተውሎት እንጂ ሙያዊ አስተያየት አይደለም። እኛም ተዝቆ የማያልቀውን የመጽሐፉን መሉ ሐሳብ በሙላት ታገኙት ዘንድ መጽሐፉን እንድታነቡት እንጋብዛለን ።
አዲስ ዘመን ሰኔ 16/2011
አብርሃም ተወልደ