በጎ ፈቃድ አገልግሎት ለዘላቂ የልማት መሠረት

የበጎ ፈቃድ ሥራ በገንዘብ የማይገዛ ነገር ግን በርካታ ስራዎች እየተሰሩበት ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ በጎ ተግባር ነው። የበጎ ፍቃድ ሥራ ሰዎችን ያለገንዘብ ክፍያ በመርዳት የህሊና እርካታ የሚሰጥ፣ የሰዎች ጥሩነትና ደግነት የሚገለጽበት በመሆኑ ይህ ባህል በጎለበተባቸው በሌሎች ሀገራት በዚህ ተግባር የሚሳተፉ ወጣቶች ወደር የሌለው እርካታ እንደሚያገኙበት ሲናገሩ ይደመጣል።

በኢትዮጵያ ዜጎች በመልካም ተግባር በመሳተፍ ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣት የሚያስችላቸው አሳታፊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን ከሆነ ወዲህ በርካቶች የተለያዩ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ።

በግልና በቡድን የተደራጁ ግለሰቦችም አረጋውያንን፣ በህመም የሚሰቃዩ ወገኖችን፣ ልዩ ከለላ የሚያስፈልጋቸው የተጎዱ ሴቶችንና ሕፃናትን ያለምንም የልፋት ዋጋ ሙሉ አልያም ትርፍ ጊዜያቸውን በመጠቀም ሲያግዙና ሲረዱ ማየት እየተለመደ መጥቷል።

የክረምት ወቅት ለአብዛኛው የሀገራችን ተማሪዎች የእረፍት ጊዜ ነው፡፡ በዚህ ወቅት ወጣቶች ለማህበረሰቡ ከፍተኛ ዋጋ ያለው ተግባር ለመፈፀም በበጎ ሥራ ላይ የሚሰማሩበትና ይህንንም ባህል ከመለማመድ አልፈው እንዲዳብር የሚተጉበት ሊሆን ይገባል።

በርካታ ወጣቶች የክረምት ጊዜያቸውን የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በሚሰጡ ተቋማትና አደረጃጀቶች አማካኝነት ጊዜያቸውን ለሌሎች ሲሰጡና ወገኖቻቸውን በሚጠቅም ተግባር ላይ ሲያውሉ፣ በሀገራቸው ዕድገት ላይ ገንቢ አስተዋፅኦ ሲያደርጉ ማየት አሁን አሁን እየተለመደ መጥቷል፡፡ በዘንድሮ የክረምት ጊዜያትም በተለያዩ የሀገራችን ክልሎች የሚገኙ ወጣቶች በበጎ ሥራ ላይ እንደሚሰማሩ ይጠበቃል። ችግኝ መትከል፣ ደም መለገስ፣ በከተሞች የትራፊክ ደንብ ማስከበር አገልግሎት፣ ማጠናከሪያ ትምህርት መስጠት እንዲሁም ህሙማንን በመንከባከብ ወዘተ በበጎ ተግባር ላይ የተሰማሩ ወጣቶች የሚያከናውኗቸው የተለመዱ ተግባራት ናቸው፡፡ እነዚህን አጠናክሮ በመቀጠል ወደላቀ ደረጃ ማሸጋገር ያስፈልጋል።

የበጎ ፍቃድ አገልግሎት መስጠት በሀገራዊ የፀረ ድህነት ትግሉ ላይ የማይፋቅ የራስን አሻራ ማኖር ነውና በዋጋ የማይተመን የመንፈስ እርካታንም ያጎናፅፋል። የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ከዚህ በተሻለ መልኩ መጎልበትና ባህል ሊሆን የሚገባ መልካም ተግባር ለማድረግ ደግሞ ወጣቱ አሁን የተጀማመሩ መልካም ተግባራትን ይዞ ለበለጠ ውጤትና ተጠቃሚነት መንቀሳቀስ ይኖርበታል።

ይህ ተግባር ማንኛውንም ዜጋ የሚያሳትፍ ቢሆንም በዋናነት ግን ወጣቶችን በስፋት የሚመለከት ነው፡፡ ይህ እንቅስቃሴ ማህበራዊ ትስስርን፣ አንድነትንና ፍቅርን የበለጠ እንዲጠናከር የማድረግ አቅም አለው። ሃሳቦችን በማንሸራሸርና ብሄራዊ መግባባትን በመፍጠር የሰላም እሴቶችን ለማዳበርም ትልቅ ሚና አለው። የበጎ አድራጎት ሥራ በእርስ በእርስ ትስስር አንድነት እንዲጎለብት ያደርጋልና የሚሰጠው ማህበራዊ መስተጋብርም የጎላ ነው።

ለዚህ ደግሞ በበጎ ፈቃድ ተግባር ላይ የሚሰማሩ ወጣቶች በሚኖሩበት አካባቢ ብቻ እንዳይወሰኑ ባለፉት አመታት የተጀመሩ ጥረቶችን ማጠናከር የግድ ነው። ወጣቶች ወደ ሌሎች አጎራባች ክልሎች በመዘዋወር እግረ መንገዳቸውን አንድነታቸውንና የባህል ዕሴቶቻቸውን የሚያጋሩበትና የሚያጎ ለብቱበት ሁኔታ መስፋት ይኖርበታል። ይህም ቋንቋ፣ ባህል፣ የአሰራር ዘይቤ እንዲሁም የተለያዩ የባህል እሴቶችንና አንድነትን የሚያጠናክር አንዱ መንገድ ስለሆነ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። ይህ እሳቤ ዕውን እንዲሆን ደግሞ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራን በባለቤትነት የሚመራው የመንግሥት አካል በትኩረት ሊሰራበት ይገባል፡፡

ሁሉም የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰጪ ወጣቶች ከፌዴራል እስከ ታችኛው የቀበሌ መዋቅር ድረስ ወደ ሥራው ከመግባታቸው በፊት በባለሙያዎች የታገዘ የግንዛቤ ፈጠራ መድረኮችን በማስፋት ወደ ሥራ እንዲገቡ ማድረግ ያስፈልጋል። ከዚህ ጋር በተያያዘ የተዘጋጀውን ራሱን የቻለ መመሪያና መተዳደሪያ ደንብ ወጣቶች እንዲያውቁ የማድረግ ሥራን ቀደም ብሎ ማከናወን ተገቢ ነው።

በጎ ፍቃድ ማለት የሰዓት፣የገንዘብ ወይም የሌሎች ጉዳይ ሳይሆን ልብን የመስጠት ጉዳይ ነው። ሀገራችን በርካታ የበጎ አድራጎት ባህል ልምምዶች ያላት ቢሆንም አገልግሎቱን የሚሰጡ ባለሙያ እና ተቋማት ቁጥር ያለመታወቅ እንዲሁም በኢኮኖሚው እና በማህበራዊ ዘርፉ ያደረገው አስተዋጽኦ በተደራጀ መረጃ ሊሰነድ ይገባል። ይህም በዘርፉ የሚታዩ ችግሮችን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀረፉ ለመሄድ በጎ ፍቃደኝነትን ባህሉ ያደረገ ማህበረሰብ ለመፍጠር የጎላ ሚና ይኖረዋል።

በጎ ፍቃድ በዘልማድ የሚመራ ሳይሆን ዓለም አቀፍ ደረጃ /standard/ ያለው በመሆኑ በዛ መሰረት መመራት ይገባዋል። የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ስንሰራ ብዙሃነትን እና የሀገሪቱን ህግ ማክበር፣የማህበረሰቡን ጥቅም ማስቀደም፣ቀጣይነት ያለው አገልግሎት ማረጋገጥ፣ግልጽነትና ተጠያቂነት ማስፈን እና ባለቤትነትን ማዳበር የሚሉ የበጎ ፍቃድ ፕሮግራም መርሆችን ማወቅና ተግባራዊ ማድረግ ይገባል፡፡

የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መገለጫው ብዙ ነውና ከተለመዱት የማህበረሰብ አገልግሎቶች የዘለለ አርቆ ማሰብ ተገቢ ነው። ይህም በሀገራችን ላይ የተጀመረውን የለውጥ እንቅስቃሴ ቀጣይነት ይኖረው ዘንድ ወጣቱ ግንባር ቀደም ተዋናይ በመሆን ሚናውን መጫወት ይኖርበታል፡፡ ከነዚህ ሚናዎች መካከል በዋናነት ከበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ በተጓዳኝ በማህበራዊ ሚዲያ ድረ ገፆች አማካኝነት ሰላም ጠፍቶ ግጭት፣ ልማት ጠፍቶ ጥፋት፣ እድገት ሳይሆን ውድቀት እንዲነግስ ለማድረግ ብሔርን ከብሔር፣ ሃይማኖትን ከሃይማኖት በማጋጨት ዕድገቱን ወደ ኋላ ለመቀልበስ የሚጥሩ ኃይሎችን መታገል ይገባል፡፡

ይህን ተግባር ማከናወን የሚቻለው ደግሞ ወጣቱ እኩይ ተግባራትን ተቀብሎ ለማራገብ ከመሞከር ይልቅ ትክክለኛውን ሀገራዊ የፍቅር መስመር እንዲይዙ ስህተታቸውን ነቅሶ በማውጣት ማረም ሲችል ነው፡፡ ስለሆነም ከግጭት፣ ከትርምስ ኪሳራ እንጂ ትርፍ እንደሌለው በአንክሮ መምከር እና ማስተካከልን ወጣቱ እንደ በጎ ፍቃድ አገልግሎት ሊቆጥረው ይገባል። ከሌላው ማህበረሰብ ይልቅ ለመረጃ ቅርብም ነውና በማህበራዊ ሚዲያው በሚነዙ አሉባልታዎች ዙሪያ እውነተኛውን ነገር ፈልፍሎ ማጋለጥ ከወጣቱ የሚጠበቅ ተግባር ነው፡፡

የበጎ ፈቃድ ተግባር የሀገር ዘላቂ ልማት መሠረት እንደመሆኑ ቀጣይነት ባለው መልኩ በበጋውም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም መዘንጋት የለበትም። በመሆኑም የበጎ ፈቃድ ሥራ የአንድ ወቅት ብቻ ሳይሆን ዘላቂነት ኖሮት ወገኖቻቸውን በሁሉም መስክ በማገዝ ወጣቶች በስፋት የሚሳተፉበት ሊሆን ይገባል።

ልኡል ከ 6ኪሎ

አዲስ ዘመን ሰኞ ሐምሌ 1 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You