ኢትዮጵያ የብዙ ደማቅ ታሪክ ሰሪ ሀገር መሆንዋ የታወቀ ነው፤ ይሁንና ታሪካቸው በአግባቡ በወረቀት ላይ የሠፈረው የጥቂቶቹ ብቻ ነው። በተለያዩ የታሪክ አጋጣሚዎችና ባገኟቸው ዕድሎች በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር ዕውቀት ለመቅሰምና የበለጠ ግንዛቤ ለማግኘት የቻሉ አንዳንድ ኢትዮጵያውያ ያገኙትን ዕውቀት ለወገኖቻቸው ለማድረስና አዳዲስ አሠራርንና አስተሳሰብን በሕዝባችን መካከል ለማስረጽ፣ አብዝተው የደከሙና ሕይወታቸውን አሳልፈው እስከ መስጠት የደረሱ ፋና ወጊ ግለሰቦች እንደ ነበሩ ይታወቃል።
ሀገራቸውን ከውጭ ወራሪ ጠላት በመከላከል አኩሪ ታሪክ የሠሩ፣ የሕዝባቸው ደህንነትና አንድነት እንዲጠበቅ ለማድረግ መሥዋዕትነት የከፈሉና አንፀባራቂ ታሪክ የሠሩ ጥቂቶች አልበሩም። በድርሰት፣ በሙዚቃ፣ በሥዕል፣ በስፖርት፣ በታሪክ፣ በሳይንስና በእምነት አስተምሮ፣ በኪነ ጥበብና የምርምር ሥራዎችም ኢትዮጵያን በዓለም የበለጠ እንድትታወቅ ያደረጉ ትናንትናም ዛሬም ደምቀው የሚታዩ ደማቅ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት ብዙዎች ናቸው።
ከእነዚህ የሀገር ባለውለታ ግለሰቦች መካከል ኢትዮጵያ በስፋት በምትታወቅበት የአትሌቲክስ ስፖርት ላይ ያሉ ብዙዎች ናቸው፤ በተለይም በረዥም ርቀት አትሌክስ በኩል ለብዙዎቻችን ደስታን የሰጡ፣ ሀገራችንም ፊተኛውን መስመር እንዳትለቅ ያደረጉ መኖራቸው የሚታወቅ ነው። ከእነዚህ አትሌቶች መካከል በርካታ ውድድሮችን በማሸነፍና እርሳቸውን ተከትለው ለመጡ ስመ-ጥር አትሌቶች ምሳሌ መሆን የቻሉት አትሌት ሀጂ ቡልቡላ በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ።
ትውልድና ዕድገት፦
አትሌት ሀጂ ቡልቡላ ትውልድና ዕድገታቸው በቀድሞ አርሲ ክፍለ ሀገር በአሁኑ አርሲ ዞን ጭላሎ አውራጃ ሊሙና ቢልቢሎ ወረዳ ነው። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በትውልድ ከተማቸው ሊሙ፤ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ በቦቆጂ ከተማ ተከታትለዋል። ሀጂ ቡልቡላ፣ ለትምህርት የነበራቸው ፍቅር ከፍተኛ እንደነበር ከስፖርት ይልቅ ትምህርታቸውን ለመከታተል ፍላጐት እንደነበራቸው ይናገራሉ።
የአትሌቲክስ ጅማሮ፦
አትሌቱ፣ “በትምህርት ቤት በሚደረጉ ስፖርታዊ ውድድሮች ተሳትፎ በማድረግ የማሸንፈው እኔ ቢሆንም ለትምህርቱ እንጂ ለስፖርት ፍቅር አልነበረኝ። በስፖርት እንዲህ ታዋቂ እሆናለሁ ብዬ አስቤ አላውቅም ነበር። ነገር ግን በውድድሩ በማሳየው እንቅስቃሴ ተማሪዎች፣ መምህራንና ቤተሰቦቼ አትሌቲክስ ላይ ያለኝን አቅም አይተው ለስፖርቱ ትኩረት እንዲሰጥ ይወተውቱኝ ነበር ይላሉ።
በአካባቢው ያሉ አብሮ አደግ ጓደኞቻቸው ስፖርት ላይ ያላቸውን ብቃት ሁሌም ይገልጹላቸው ነበር። ሀጂ ቡልቡላ፣ ትምህርታቸውን ከስፖርት ጋር አንድ ላይ ለማስኬድ ጥረት በማድረግ እስከ አስራ አንደኛ ክፍል መከታተል የቻሉ በመሆናቸው፤ የአካባቢው አመራሮች እስከ መኖሪያ ቤታቸው እየመጡ ወደ ስፖርቱ ገብተው ሀገራቸውንና አካባቢያቸውን ማስጠራት እንዳለባቸው ይወተውቷቸው እንደነበር ይናገራሉ። እርሳቸውም በዚያው መሠረት ሙሉ ትኩረታቸውን ስፖርት ላይ እንዳደረጉ ይገልፃሉ።
“ለትምህርቴ ከፍተኛ ፍቅር ስለነበረኝ በአትሌቲክስ እንድወዳደር በትምህርት ቤት ተወክዬ ብላክም ከውድድር ሁሉ እየቀረሁ አስቸግራቸው ነበር። በወቅቱ የወረዳው አስተዳደሪ አቶ ተክለፃድቅ የሚባሉ ግለሰብ ለስፖርት በተለይም ለአትሌቲክስ ልዩ ፍቅር ስለነበራቸው እኔን እስከ ቤት በመምጣት በውድድሮች እንድሳተፍ ያደርጉኝ ነበር” ይላሉ።
ስፖርትን በትምህርት ቤት የጀመሩት ሀጂ ቡልቡላ፣ በመጀመሪያ በአጭር እርቀት ከ 100 እስከ 400 ሜትር፣ በ800 ሜትር እንዲሁም በ 1500 ሜትር ጀምረው እስከ 12 ኪሎ ሜትር ሀገር አቋራጭ ውድድር በብቃት መሳተፍ ችለዋል። መሳተፍ ብቻ ሳይሆን ውድድሮቹን በተደጋጋሚ አሸንፈዋል።
የመጀመሪያ ውድድራቸውን በ1976 ዓ.ም በተደረገው ሀገር አቀፍ የአትሌቲክስ ውድድር የጀመሩት ሀጂ ቡልቡላ፣ በወቅቱ ውድድሩን በማሸነፍ እንደ አርሲ ክፍለ ሀገር ቀድመው በመውጣት አካባቢያቸውን በማስጠራት ተሸላሚ መሆን ችለዋል። ከዚህ ውድድር በኋላ ከአካባቢው በእርሳቸው አርአያነት እነ ደራርቱ ቱሉ፣ ፋጡማ ሮባ፣ በሻቱ ደበሌ፣ ሃይሌ ገብረስላሴ የመሳሰሉት አትሌቶች መውጣት ችለዋል። አትሌቱ፣ የእነዚህ አትሌቶች መውጣት ለአካባቢው አትሌትክስ ምሳሌ መሆን እንደቻሉ ይናገራሉ።
መነሻቸው ሊሙና ቢልቢሎ ትምህርት ቤት የሆነው ሀጂ ቡልቡላ በአርሲ ዞን፣ በቆጂ፣ እስከ ጃንሜዳ ኢንተርናሽናል ሀገር አቋራጭ ውድድር፣ በኢትዮጵያ አትሌክስ ሻምፒዮና፣ በአዲስ አበባ ክለቦች አትሌቲክስ ሻምፒዮና፣ በአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፕዮና በመላው አፍሪካ ጨዋታዎች፣ በተለያዩ የዓለም አቀፍ ሀገር አቋራጭና የዓለም ሻምፒዮናዎች ተሳታፊ ሆነው ውጤት ማስመዝገብ ችለዋል።
ከዚህ በተጨማሪ ሀጂ ቡልቡላ ፣ በተለያዩ የአውሮፓ ሀገራት የአትሌቲክስ ውድድር ኢትዮጵያን በመወከል በግልና በቡድን በተለያዩ ርቀቶች የሜዳልያ ባለቤት ሆነዋል። በዚህም ሀገራቸውን በዓለም አደባባይ ከማስተዋወቃቸው ባሻገር ሠንደቅ ዓላማዋ ከሌሎች የበለፀጉ ሀገራት በላይ ከፍ ብላ እንድትውለበለብ አድርገዋል።
የአርሲ ክፍለ ሀገር አትሌቲክስ ፈር ቀዳጅ የሆኑት ሀጂ ቡልቡላ፤ እሳቸውን በመከተል ለወጡት የዝነኛው አትሌት ሃይሌ ገብረሥላሴ ታላቅ ወንድም ተኪዬ ገብረሥላሴ፣ ለሚ ጨንገሬ፣ ለገሠ ጽጌ፣ ወርቁ ቢቂላ፣ ሃይሌ ገብረሥላሴ፤ ሃይሉ መኮንን፣ ተስፋዬ ቶላ፣ ገዛኸኝ አበራ፣ ምክትል ኮሚሽነር ሁሴን ሽቦ፣ ሀጂ አዴሎን የመሳሰሉ ብርቱ የኢትዮጵያ አትሌትክስ ስፖርት ጀግኖች አዋሽን ተሻግረው ዓለምን ማንቀጥቀጥ እንዲችሉ ምሳሌ ሆነዋል።
ሀጂ ቡልቡላ፣ በሴቶችም እንዲሁ፤ እንደ አየለች ወርቁ፣ መሬማ ደንቦባ፣ ደራርቱ ቱሉ፣ ፋጡማ ሮባ፣ እልፍነሽ ዓለሙ፣ የመሳሰሉ በኢትዮጵያ አትሌትክስ በወርቃማ ቀለም የተፃፈ ታሪክ መሥራት የቻሉ አናብስት እንዲወጡ አርአዓያ መሆን ችለዋል።
“በወቅቱ በኢትዮጵያ ደረጃ ተወዳዳሪ ያልነበረኝ ሰው ስለሆንኩኝ በጉዳት በአንዳንድ ምክንያቶች ከስፖርቱ ዓለም ስርቅ ከፍተኛ ሃዘን ተሰምቶኝ ነበር። ነገር ግን በነበረኝ ጊዜ ለሀገሬ በሰራሁት ሥራ ኩራት የሚሰማኝና ቀን በሰጠኝ ጊዜ ማድረግ የምችለውንና ማድረግ ያለብኝን ሥራ በመስራቴ እንድኮራ ያደርገኛል’’ ይላሉ።
ሀጂ ቡልቡላ ፣ “ከስፖርት ለመገለሌ በወቅቱ የነበረው የስፖርት ፌዴሬሽን ያደረሰብኝ በደል አንዱ ምክንያት ነበር” የሚሉት ሀጂ ቡልቡላ አንድ አትሌት ውድድር ሲያደርግ ከሁለት ዓመት በላይ ከቆየ ይዳከማል፤ ከዚህ አንፃር በነበረው ትክክለኛ ያልሆነ አሠራር በዓለም አቀፍ ደረጃ ውድድሮች ሲደረጉ እንዳልሳተፍ መደረጌ ትልቅ የሞራል ጉዳት አድርሶብኝ ነበር ይላሉ።
በስፖርቱ ያሉ ስዎች የራሳቸውን ጥቅም በማስቀደም ስፖርተኛው ላይ በደል ይፈፅማሉ የሚሉት ሀጂ ቡልቡላ፤ “እኔን ብዙዎች በኦሎምፒክና በተለያዩ ውድድሮች ውጤት ያመጣል ብለው ቢጠብቁም በተደጋጋሚ በአሠልጣኞች ምክንያት ከውድድር ውጪ እየተደረኩ ያሳልፍኳቸው ጊዜያት ብዙ ነበሩ’’ ይላሉ።
በአትሌቲክስ ያስመዘገቡት ውጤት፦
በ1986 በፈረንሳይ በተደረገው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና፣ በአፍሪካ ደረጃ ደግሞ በአልጄሪያ በተደረገው የመላው አፍሪካ ጨዋታዎች በ5000 እና በ 10,000 ሜትር ሁለተኛ ደረጃ በመያዝ ያጠናቀቁት ሀጂ ቡልቡላ፣ በተለይ በአልጄሪያ በነበረው ውድድር ስለነበረው የአየር ሁኔታ ሲናገሩ፤ ከ40 ዲግሪ ሴንትግሬድ በላይ የሆነ ከፍተኛ ሙቀት ስለነበር በአካባቢው የሰደድ እሳት ተነስቶ በአውሮፕላን ውሃ እየተረጨ እሳት ለማጥፋት ጥረት እየተደረገ እያየን ነበር ውድድር ያደረግነው ይላሉ።
“ሁለተኛ መውጣት የቻልኩት ለመተንፈስ እንኳ አስቸጋሪ በሆነ የአየር ሁኔታ ውስጥ በመሮጥ ነበር። በወቅቱ ሌሎች የአፍሪካ አትሌቶችን ጨምሮ ከእኔ ጋር ኢትዮጵያን የወከሉት ጫላ ከልሌና ደበበ ደምሴ በነበረው የአየር ጠባይ ምክንያት እራሳቸውን ስተው ወድቀው ነበር። በወቅቱ ከውድድር በኋላ ብዙ አትሌቶች የህክምና ድጋፍ እየተደረገላቸው ተመልክቻለሁ። ያንን ሁሉ በመቋቋም ነው ለሀገሬ የብር ሜዳልያ ማሸነፍ የቻልኩት’’ ሲሉም ያስረዳሉ።
በዚያን ወቅት ውድድሩን ከአሸነፈው ሞሮኮአዊው አትሌት በጥቂት ሴኮንዶች ዘግይቼ ነው ሁለተኛ የወጣሁት የሚሉት ሀጂ ቡልቡላ፤ እንዲያውም በ5000 ሜትር ውድድር ለማሸነፍ ተቃርቤ ከአንድ አትሌት ጋር በውድድር መሃል በተፈጠረ ምክንያት ከመሮጫ መስመር በመውጣቴ ነው የአንደኝነት ሥፍራውን የተነጠቅኩት ይላሉ።
“ከዚህ የአፍሪካ ውድድር በኋላ የኦሎምፒክ ውድድር ስለነበር የተለያዩ የመጠሪያ ውድድሮችን አድርገን የተዘጋጀን ቢሆንም፤ በወቅቱ የስፖርት ፌዴሬሽን ከነበረው የፖለቲካ አሰላለፍ ጋር ተያይዞ በነበረው ውጥረት ምክንያት ኢትዮጵያ በውድድሩ ተሳትፎ እንዳይኖራት አደረገ። በኦሎምፒክ ተሳትፌ ቢሆን በአፍሪካ ውድድሮች ላይ የነበረኝን ጉድለት በማሻሸል የወርቅ ሜዳልያ ለሀገሬ ማምጣት እችል ነበር” በማለትም ይቆጫሉ።
ኢትዮጵያ ባልተሳተፈችበት በዚህ የኦሎምፒክ ውድድር በአልጄሪያ የአፍሪካ ጨዋታ ከእኔ ጋር ተፎካካሮ አንደኛ የወጣው የሞሮኮው አትሌት ፣ በከፍተኛ ልዩነት ነበር የሚሉት ሀጂ ቡልቡላ፤ ወርቅ አመጣለሁ የምልበት ምክንያት ውድድሩ ካለው የአየር ሁኔታ አንፃር ለኢትዮጵያ አትሌቶች የተሻለ ስለሚሆን ነው ይላሉ።
“ከዚህ ውድድር በኋላ እኔም ሆንኩ ሀገሪቷ በኦሎምፒኩ ባለመካፈሏ የኢትዮጵያ መንግሥት ጨምሮ የስፖርት ፌዴሬሽን ሰዎች በጣም አዝነው እንደነበር
አስታውሳለሁ። የ5000 እና 10,000 ሜትር ውድድር የማሸነፍ አቅም ነበረ በሚል ፀፀት እንደተሰማቸው የስፖርት አመራሮች ነግረውኛል የሚሉት ሀጂ ቡልቡላ፣ አንድ ነገር ካለፈ በኋላ መቆጨት ምንም ትርጉም የለውም በሚል ምላሸ እንደሰጧቸው ያስታውሳሉ።
ሀጂ ቡልቡላ በዓለም አቀፍ ውድድሮች፦
በአንጎላ በተካሄደው ውድድር ለተከታታይ ሶስት ዓመታት በአምስትና አስር ሺህ ሜትር አንደኛ ደረጃ መያዝ ቻልኩ የሚሉት ሀጂ ቡልቡላ፤ ከዚህ በተጨማሪ በርቀቱ ብርሃኑ ግርማ በተባለ አትሌት ተይዞ የነበረውን ሰዓት በማሻሸል/ ሪከርድ በመስበር ማሸነፍ ቻልኩ ይላሉ። በዚህም ለተከታታይ ሶስት ዓመታት ውድድር በማሸነፍ አዲስ ክብረ ወሰን ያዝኩ። በወቅቱ ይህ ክስተት ትልቅ መነጋገሪያና ለእኔም ኩረት የሆነ ነበር ሲሉ ያስረዳሉ።
ሀጂ ቡልቡላ፣ በ1988 ዓ.ም በሌላኛዋ አፍሪካዊት ሀገር ሴኔጋል ዳከር ላይ በተደረገው የአምስትና የአስር ኪሎ ሜትር ውድድሮች ላይ በመሳተፍ በሁለቱም ርቀት የሁለተኛ ደረጃ ይዞ በማጠናቀቅ ለሀገራቸው የብር ሜዳልያ ማስገኘት ችለዋል።
በስፔን የነበረው ዓለም አቀፍ ውድድር ፈታኝ ነበር የሚሉት ሀጂ ቡልቡላ፤ “በውድድሩ ከምስራቅ አፍሪካ በተለይ ከታንዛኒያ ተፎካካሪ አትሌቶች ነበሩ፤ በዚህ ፈታኝ ውድድር ሁለተኛ ደረጃ በመያዝ ማጠናቀቅ እንደቻሉና በወቅቱ ውድድሩን ለማሸነፍ ከፍተኛ ተጋድሎ ስለማድረጋቸው ይናገራሉ።
ሀጂ ቡልቡላ እንደሚናገሩት፤ በ1979 ዓ.ም አዲሱን የፈረንጆች ዓመት ምክንያት በማድረግ አንጎላ ሉሃንደ ከተማ ላይ በተካሄደው ውድድር በሌላኛው ኢትዮጵያዊ አትሌት ብርሃኑ ግርማ ለአራት ዓመታት የተያዘውን የአምስትና የአስር ሺህ ርቀት ክብረወሰን መሻሸል መቻላቸው ከአትሌቲክስ ሕይወታቸው የማይረሱት በውጤታማነታቸውም ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሱበት ወቅት እንደነበር ጊዜውን አስታውሰው ይናገራሉ።
በ1987 እንደ አውሮፓ ዘመን አቆጣጠር ፖላንድ ዋርሶ ከተማ ላይ በተካሄደው የሀገር አቋራጭ ውድድር ኢትዮጵያ በቡድን እንድታሸንፍ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ካደረጉ አትሌቶች መካከል አንዱ እንደነበሩም ይገልፃሉ።
በተጨማሪም በጣሊያን ሮም በተመሳሳይ ዓመት በተካሄደው ውድድር ከፍተኛ ተጋድሎ በማድረግ ኢትዮጵያ በቡድን ሁለተኛ ደረጃ ይዛ ማጠናቀቅ እንድትችል ሀጂ ቡልቡላ የራሳቸውን የላቀ አስተዋጽኦ ማበርከት ችለዋል።
በዚሁ ሀገር በተካሄደው ውድድር በአምስት ኪሎ ሜትር 13 ደቂቃ ከ31 ሰከንድ በሆነ ሰዓት በመግባት አንደኛ ደረጃ መያዝ የቻሉት ሀጂ ቡልቡላ፤ በውድድር አንደኛ ከመውጣታቸውም በላይ በርቀቱ የቦታውን ሰዓት ማሻሸል ችለዋል።
ፊንላንድ ሄልሲንኪ ከተማ በተካሄደው የአስር ኪሎ ሜትር ውድድር 27 ደቂቃ ከ43 ሰከንድ ከ 4 ማይክሮ ሰከንድ በመግባት ማሸነፍ የቻሉት ሀጂ ቡልቡላ፤ ይህ ሰዓታቸው በወቅቱ የቦታው ክብረወሰን ሆኖ ተመዝግቧል።
በሀገር ውስጥ የተሳተፉባቸው ውድድሮች፦
የጃንሜዳ ኢንተርናሽናል ሀገር አቋራጭ ውድድር በ1976 ዓ.ም የተጀመረ ሲሆን፣ ሀጂ ቡልቡላ ኢትዮጵያን በመወከል የተካፈሉት በ1978 ዓ.ም ነበር። በአዋቂ ወንዶች 12 ኪሎ ሜትር 36 ደቂቃ ከሃያ ሰባት ሰከንድ በመግባት በውድድሩ ለኢትዮጵያ የወርቅ ሜዳልያ አስገኝተዋል። በዚህ ውድድር ላይ ኢትዮጵያን ጨምሮ ኬንያ፣ ጅቡቲ፣ የመን፣ ሶቪየት ህብረትና ቡልጋሪያ ተካፍለው ነበር።
እንዲሁ በ1978 ዓ.ም በተመሳሳይ ውድድር በአዋቂ ወንዶች 12 ኪሎ ሜትር አበበ መኮንን የተባለ አትሌት 36 ደቂቃ ከ40 ሰከንድ አንደኛ ሲወጣ ሀጂ ቡልቡለ 36 ደቂቃ ከ50 ሰከንድ በመግባት ለኢትዮጵያ የብር ሜዳልያ ማስገኘት ችለዋል።
በ1980 ዓ.ም ደግሞ በተመሳሳይ ውድድር ለሁለተኛ ጊዜ አበበ መኮንን የቀዳሚነቱን ሥፍራ ሲይዝ ሌላኛው የወቅቱ ድንቅ አትሌት በቀለ ደበሌ ሁለተኛ ሲወጣ ሀጂ ቡልቡላ ደግሞ ሶስተኛ በመውጣት የነሀስ ሜዳልያ አስገኝተዋል።
ለአራተኛ ጊዜ በ1981 ዓ.ም በተደረገውና ስድስት ሀገራት በተካፈሉበት የ 12 ኪሎ ሜትር ሀገር አቋራጭ ውድድር የወቅቱ ኮከብ አበበ መኮንን ለሶስተኛ ጊዜ የውድድሩ አሸናፊ ሆኖ አንደኛ ሲወጣ፤ ሀጂ ቡልቡላ ደግሞ ሁለተኛ ደረጃ በመያዝ የብር ሜዳልያ ለኢትዮጵያ አስገኝተዋል።
በተጨማሪም በ1982 ዓ.ም ኢትዮጵያ፣ ታንዛኒያ፣ ኬንያና ዝንባቡዌ በተካፈሉበት የጃንሜዳ ሀገር አቋራጭ የአትሌቲክስ ሻምፒዮና አበበ መኮንን ለአራተኛ ጊዜ በማሸነፍ የወርቅ ሜዳልያ ሲያገኝ፤ ሀጂ ቡልቡላ ደግሞ ሁለተኛ ደረጃን ይዘው በማጠናቀቅ የብር ሜዳልያ ለሀገራቸው አስገኝተዋል።
በሀገር ውሰጥ የተደረጉ ውድድሮችን በተለይ የሀገር አቋራጭ ውድድሮችን በተደጋጋሚ በመሳተፍ በተለያየ ጊዜ ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ደረጃ በመያዝ ያጠናቀቁት ሀጂ ቡልቡላ፤ ሁለተኛና ሶስተኛ በመያዝ ከጨረሱት ይልቅ አንደኛ ደረጃ በመያዝ አያሌ ውድድሮችን እንዳጠናቀቁ ይገልፃሉ።
“እኔ ውድድር በማደርግበት ወቅት በሀገር ውስጥ ሆነ በውጭ ሀገር እኔን ቀድመው ያጠናቀቁ አትሌቶች ጥቂት ናቸው። ” የሚሉት ሀጂ ቡልቡለ፤ በአትሌቲክስ ዘርፍ በወቅቱ ለነበሩ አትሌቶች እንደ አርአዓያ የሚታዩ የዘመኑ ፈርጥ እንደነበሩ ወደ ኋላ ተመልሰው ያስታውሳሉ።
ሌላው የአዲስ አበባ ከተማ የመቶኛ ዓመት የምስረታ በዓል ምክንያት በማድረግ በተደረገው ውድድር የመጀመሪያ ደረጃ በመያዝ ያጠናቀቁት ሀጂ ቡልቡላ፤ በዚህ ውድድር እንደ አበበ መኮንን፣ በቀለ ደበሌ፣ አይነት ታላላቅ አትሌቶች ተሳታፊ እንደነበሩ ገልፀው፤ ይህንን ውድድር በቀዳሚነት በመጨረሳቸው የክብረ በዓሉን ችቦ የመለኮስ ዕድል እንዳገኙና በክብረ በዓሉ በክብር እንግድነት ተገኝተው እንደነበር ያስታውሳሉ።
ሀጂ ቡልቡላ፣ በክለብ ደረጃ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ አትሌት ነበሩ። ብዙ አትሌቶች እርሳቸውን በመከተል ለኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ በአትሌቲክስ ዘርፍ ተሳታፊ ለመሆን በቅተዋል።
አብሯቸው የሮጡ ታላላቅ አትሌቶችና የልጅነት ገጠመኞቻቸው፦
ሀጂ ቡልቡላ፣ ኢትዮጵያን በዓለም መድረክ ማስጠራት ከቻሉ ስመ ጥር አትሌቶች ጋር የተለያዩ ውድድሮችን ስለማድረጋቸው ይናገራሉ። ለአብነት አትሌት ወዳጆ ቡልቲ፣ አበበ መኮንን፣ በቀለ ደበሌ ጋር የተለያዩ ውድድሮችን አድርገዋል፤ በወቅቱ ሁላችንም ተመሳሳይ የብቃት ደረጃ ላይ ነበርን። ከዚህ ባሻገር በአንድ አሠልጣኝ ስር አንድ አይነት ሥልጠና ነበር የሚሰጠው። በዚህ ምክንያት በዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ ውጤታማ ለመሆን አስቸጋሪ እንደማይሆን ይናገራሉ።
ሀጂ ቡልቡላ እንደሚናገሩት፤ በወቅቱ አንድ ውድድር ሲኖር በተደጋጋሚ የማጣሪያ ውድድሮች ተደርገው ነበር። ለውድድር የምንለካው በዚህን ጊዜ የነበሩ ጠንካራ አትሌቶችን ማሸነፍ በራሱ ሌላ ፈተና ነገር ነበር። ግን በቀዳሚነት በማጠናቀቅ ነበር የሚታወቀው።
“የኢትዮጵያ ሀገር አቋራጭ ውድድር ሲካሄድ በተደጋጋሚ በማሸነፍ የምታወቀው እኔ ነኝ። ” የሚሉት ሀጂ ቡልቡላ፤ “እነወዳጆ ቡልቲን የመሳሰሉ ጠንካራ አትሌቶች የሚፎካከሩኝ ቢሆንም የቀዳሚነቱን ሥፍራ አልሰጠውም። ለእያንዳንዱ ውድድር ከፍተኛ ዝግጅት አድርጌ ስለምመጣ ውጤታማ ሆኜ ለማጠናቀቅ አልቸገርም ነበር’’ ይላሉ።
“በወቅቱ በተለይ በአትሌቲክስ ስፖርት ከፍተኛ ስምና ዝና ነበረኝ። ” የሚሉት ሀጂ ቡልቡላ፤ ጠንካራ ተፎካካሪ ሆኖ ውድድሮችን በማሸነፍ የሚታወቁ አትሌቶች ይህንን መመስከር እንደሚችሉ ይናገራሉ።
በልጅነታቸው ሀጂ ቡልቡላ፣ ከትምህርት ቤት ወደ መኖሪያ ቤት በሚመለሱበት ሰዓት ሃይለኛ የጭላሎ ዝናብ ሲመጣ ሌሎች ጓደኞቻቸውን በመቅደም እየሮጡ ዝናቡ ሳይደርስባቸው እቤት ይገቡ እንደነበር ይነገርላቸዋል።
በዚህ የተነሳ እንኳን ሰው ዝናብ አይደርስበትም የተባለላቸው ሀጂ፣ በፍጥነታቸው የሚያውቋቸው የአካባቢው ሽማግሌዎች አንድ ነገር ሲፈልጉ “ያንን በፍጥነቱ ወደር የማይገኝለትን ልጅ ጥሩና ቶሎ መልዕክት አድርሶ እንዲመጣ ላኩት ይሏቸው እንደነበር የልጅነት ጊዜያቸውን ወደኋላ ተመልሰው በማስታወስ ይናገራሉ። ይህ ብቻ አይደለም ሀጂ ቡልቡላ፣ የአካባቢው ከብቶች ሲያመልጡ እንኳን አባርሮ አረፋ በማስደፈቅ አድክሞ ወደ ቤት ይመልሱ እንደነበር ያስታውሳሉ።
ሀጂ ቡልቡላ ፣ ከአንድ ቦታ ወደሌላ ቦታ መልዕክት ለማድረስ ሲሄዱ በፍጹም ቀስ ብሎ መሄድ የማይወዱ በሩጫ ወደ ተላኩበት መሄድ የሚመርጡ በመሆናቸው በአካባቢው ሰዎች “አላቲ” ወይም በራሪ ወፍ የሚል ቅፅል ስም ተሰጥቷቸው ነበር።
በሀጂ ቡልቡላ ዘመን የነበሩት ስመ-ጥር የኢትዮጵያ አትሌቶች አበበ መኮንን፣ ወዳጆ ቡልቲ፣ በቀለ ደበሌ፣ ወልደሥላሴ ሚልኬሣ፣ ደበበ ደምሴ፣ ተስፋዬ ጣፋ፣ አዲሱ አበበ፣ ተክዬ ገብረሥላሴ፣ በድሉ ክብረትና ንጉሡ ኡርጌ፣ ነጋሽ ሀብቴ የመሣሠሉ እንደነበር ይናገራሉ።
ከአትሌቲክስ የራቁበት ምክንያት፦
“እኔ ከአትሌቲክስ የመራቄ ምክንያት አሠልጣኞች የፈጠሩት ችግር ነው። ” የሚሉት ሀጂ ቡልቡላ፤ “ከስፖርት እንድገለል ያደረጉ አሁንም በሕይወት ያሉ የቀድሞ አሠልጣኞች ናቸው፤ አሁን እከሌ እንዲህ አደረገኝ ማለት ትርጉም የለውም ። ነገር ግን በወቅቱ የነበሩ አሠልጣኞች ከሀገር ብሔራዊ ጥቅምና ከውጤት አንፃር መዝነው ሳይሆን የራሳቸውን ጥቅም ለማግኘት በማሰብ አትሌት ስለሚመርጡ ብቃቱ እያለው ከውድድር የሚገለለው አትሌት ሞራሉ ስለሚጎዳ ብቃቱን ማስቀጠል ሳይችል ይቀርና ከስፖርቱ ይወጣል። በእኔ ላይ የደረሰውም ይህ ነው። ” ይላሉ።
“አንድን አትሌት ሁለት ዓመት ሙሉ ከውድድር ዓለም እንዲርቅ መቅጣት ማለት እጅግ ልብ የሚሰብር ነው። ” የሚሉት ሀጂ ቡልቡላ፤ “እኔ ላይ የደረሰው ነገር በወቅቱ ከነበረኝ ብቃት አንፃር ለእኔ የማይገባ ስለነበር በከፍተኛ ደረጃ ያሳዘነኝ ከመሆኑ በላይ ተስፋ በመቁረጥ ከአትሌቲክሱ እንዲገለል ምክንያት ሆኖኛል። ” ይላሉ።
“ይህ አድሏዊ አሠራር በእኔም ሆነ በሀገሪቱ ላይ በዘርፉ ውጤት እንዳይመጣ በማድረግ የፈጠረው ችግር በቀላሉ የማይታይ ነው። ” የሚሉት ሀጂ ቡልቡላ፤ ይህ የራስን ጥቅም ከሀገር ፍላጐት የማስቀደም አካሄደ በተለይ በስፖርቱ ከእኛ ዘመን ጀምሮ እስከዛሬ የቀጠለ ችግር ነው። ” ይላሉ።
አሁን ያሉበት ሁኔታ፦
“ከአትሌቲክሱ አስቀድሜ በጠቀስኩት ምክንያት ከተለየሁ በኋላ በብዙ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ አልፌያለሁ፤ ህመም አጋጥሞኝ ህክምና እየተከታተልኩ እገኛለሁ። ህክምና በማደርግበት ወቅት አትሌት ደራርቱ ቱሉ አልፎ አልፎ በመጠየቅ እገዛ አድርጋልኛለች። ለዚህ ችሮታዋ አመሰግናታለሁ”። ይላሉ።
ተተኪ አትሌቶችን የማሠለጥንበት ዕድል ባገኝ ሙያውን በደንብ የማውቀው በመሆኑ፤ በተለይ በረዥም ርቀት ኢትዮጵያ የነበራትን ስም እያጣች በምትገኝበት በዚህ ወቅት ጠንካራ አትሌቶችን የማፍራት አቅም አለኝ፤ ስለዚህ ዕድሉን አግኝቼ የነበረኝን ልምድ በመጠቀም እንድሠራ መንገድ ቢመቻች መልካም ነው። ” በማለት ይገልጻሉ።
“ሀገሬን በተለያዩ የዓለም መድረኮች ወክዬ ብዙ ታሪክ መሥራት የቻልኩ ሰው ብሆንም ትክክለኛ ባልሆነና ኢ-ፍትሀዊ በሆነ አሠራር ከአትሌቲክስ ስፖርት እርቄ እትብቴ በተቀበረበት ሊሙ ቢልቢሎ በአንዲት ደሳሳ የገጠር ቤት ውስጥ ተጥዬ መኖር እጣ ፈንታዬ ሆኗል።” ሲሉ ኢትዮጵያን በተለያዩ መድረኮች ከፍ ያደረጋት አትሌት ይናገራሉ።
ክብረአብ በላቸው
አዲስ ዘመን ሰኔ 30 ቀን 2016 ዓ.ም