ታላቁ የስፖርት መድረክ በአራት ዓመት አንድ ጊዜ በመጣ ቁጥር በኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ውስጥ ባህል እስኪመስል ውዝግብ መፈጠሩ የተለመደ ነው። አሁንም የፓሪስ 2024 ኦሊምፒክ ሊጀመር ከአንድ ወር ያነሰ ጊዜ በቀረው በዚህ ወቅት የተለመደው ውዝግብና ጭቅጭቅ አላጣውም። በእርግጥ ይህ ውዝግብ መፈጠር የጀመረው ከወራት አስቀድሞ ነው። ያም ሆኖ የዘንድሮው ውዝግብ ከዚህ ቀደም እንደተለመደው በአትሌቶች ምርጫና ተያያዥ ጉዳዮችን በተመለከተ አይደለም። የውዝግቡ መሪ ተዋናዮች ግን የተለመዱት የተቋሙ መሪዎች ናቸው።
የዘንድሮው ውዝግብ እንዳለፉት ዓመታት በቀላሉ የሚታይ የግለሰቦች አለመግባባት ብቻ ተደርጎ የሚታለፍ አይደለም። ነገሩ ከዚያም ይሻገራል። መዘዙም ሀገርን ከባድ ዋጋ ሊያስከፍል የሚችል እና በአመራሩ በኩል ብዙ የመርህና የሕግ ጥሰት የተፈፀመበት ነው። እርግጥ ነው ኮሚቴውን ባለፉት ስምንት ዓመታት ገደማ እየመራ የሚገኘው ሥራ አስፈፃሚ ገና ሥልጣኑን ከመጨበጡ አንስቶ በሕግና በመርህ ሳይሆን በአንድ ግለሰብ ፍላጎት ብቻ የሚመራ ስለመሆኑ የማያውቅ የስፖርት ቤተሰብ የለም። ወሎ ሰፈር በሚገኘው የኮሚቴው የተንጣለለ ቅጥር ጊቢ ውስጥ ከተቋሙ መዋቅር እስከ ሠራተኛና ባለሙያዎች ቅጥር፣ ከሚዲያ ጥሪ እስከ ግልጸኝነትና ተጠያቂነት የሚሉ መርሆች ውሃ ከበላቸው ዓመታት ተቆጥረዋል።
አሁን ላይ ለተፈጠረው ውዝግብ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ የፕሬዚዳንትና ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ሕገ ወጥ ምርጫ የሁሉም ነገር መነሻ ነው። ሕገወጡ ምርጫ በድብቅ ከተካሄደ ሁለት ሳምንት አልፎታል። ምርጫውን ከሚዲያና ከአንዳንድ አባል ማኅበራት በመደበቅ ብቸኛ እጩ ፕሬዚዳንቱ በድብቅ ተመርጠዋል። ከአባል ፌዴሬሽኖች አንዳንዶቹ ስለ ጉባዔውና ምርጫው ስለ ተሻሻለው ደንብም ሆነ ስለ እጩዎች መላክ የሚያውቁት ጉዳይ አልነበረም፤ ጥሪም አልደረሳቸውም። አሁን ያለው የኦሊምፒክ ኮሚቴ ገና የ10 ወራት የሥልጣን እድሜ ቢቀረውም ከሕግ ውጭ ራሱን መርጦ በድጋሚ ቆይታውን አራዝሟል፤ ኦሊምፒክ ኮሚቴው ለዚህ የሚሰጠው ምላሽ ባለፈውም ከቶኪዮ ኦሊምፒክ በፊት ነው ያደረግነው የሚል ነው፤ ያኔም ምርጫው ከኦሊምፒኩ በኋላ መስከረም ላይ እንዲደረግ በጠቅላላ ጉባዔው ቢወሰንም አመራሩ ይህንን ችላ ብሎ ከባህርዳርና ከሃዋሳ ምርጫ ማድረግ አትችሉም ተብለው ተሰድደው አዲስ አበባ ላይ በር ዘግተው ምርጫ ማከናወናቸው በወቅቱም ብዙ ጫጫታና ሰልፍ እስርና ወከባ ማስተናገዳቸው ይታወሳል።
የሀገሪቱ የስፖርት ማህበራት ማደራጃ ደንብ በየትኛውም ፌዴሬሽንም ሆነ ማኅበር ውስጥ የሚገኝ አመራር ከሁለት የሥልጣን ጊዜ ወይም ከስምንት ዓመት በላይ መመረጥ እንደማይችል ይደነግጋል፤ ፕሬዚዳንቱ ግን ለሶስተኛ ጊዜ ተመርጠው ለሶስተኛ ጊዜ በአወዛጋቢ ሁኔታ ሥልጣናቸውን በማስቀጠል ሀትሪክ ሲሠሩ ያቆማቸው አካል የለም። አብዛኞቹ የሚመለከታቸው አካላት ምርጫው የጨረባ መሆኑን እያወቁ ዝምታን መርጠዋል። ጥቂቶች ብቻ አደባባይ ወጥተው “በሕግ አምላክ” ብለዋል። ምርጫው ሕገ ወጥ ነው ብለው ድምፃቸውን ካሰሙ ሰዎች አንዱ በምርጫው የኮሚቴው ምክትል ፕሬዚዳንት ተብሎ የተመረጠው ጀግናው አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገ/ስላሴ ነው። ኃይሌ ምክትል ፕሬዚዳንት ተደርጎ ቢመረጥም ስለ ምርጫው ምንም እንደማያውቅና በወቅቱም ሀገር ቤት እንዳልነበረ፣ ሹመቱንም ከሰው መስማቱን በሚዲያ ወጥቶ ተናግሯል። “ከሦስት ዓመት በፊት በሙያህ አገልግል ተብዬ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ውስጥ ገብቼ ነበር፣ ሆኖም የማየው ሁሉ ደስ ስላላኝ ውሳኔዎች በጋራ ሳይሆን በግል ሲወሰኑ ስመለከት ለመራቅ ተገደድኩ፣ ከሶስት ስብሰባ በላይ አልተሳተፍኩም” ብሏል ኃይሌ።
ጉባዔም ሆነ ምርጫ ከኦሊምፒክ በኋላ መደረግ እንዳለበት የሚናገረው ኃይሌ የአሁኑ ምርጫም ሕጋዊ አይደለም ይላል። ይህ ምርጫ ተሽሮ በቀጣይ በሕጋዊ መንገድ ከተካሄደ ለመወዳደር ማሰቡን ጠቁሞም የእሱን ሹመት በተመለከተ ውሳኔውን ለኦሊምፒክ ኮሚቴውና ለባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ማሳወቁን ገልፆ መፍትሄ ጠይቋል። ኃይሌ ተቃውሞውን ካሰማ በኋላ ኦሊምፒክ ኮሚቴው ኃይሌን እንዳልመረጠው ቢገልፅም በዕለቱ የተመረጡት የቦርድ አባላት ለተሳታፊዎቹ ይፋ ሲሆኑ ግን ስሙ መኖሩ የተረጋገጠ ጉዳይ ነው። ይህ በታወቀ ሰአት የኮሚቴው ፕሬዚዳንት በሚዲያ ወጥተው “ኃይሌ ካልፈለገ ይቀራል የሚያስገድደው የለም” ብለው ተናግረዋል።
በሌላ በኩል የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር በማህበራት ጉባዔና ምርጫ ወቅት በታዛቢነት መገኘት ቢኖርበትም በኦሊምፒክ ጉባዔው ላይ ግን እንዳልተጋበዘ ምርጫውንም በሰሚ ሰሚ እንዳወቀ ሚኒስትር ዴኤታው አምባሳደር መስፍን ቸርነት ተናግረዋል። “ምርጫው ሕጉን አልተከተለም” ሲሉም አረጋግጠዋል። ፕሬዚዳንቱ ግን ለሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በደብዳቤ ጥሪ እንዳደረጉና የሀገሪቱን ስፖርት በበላይነት የሚመራው የመንግሥት አካል ባይገኝም ምርጫውን የማድረግ መብት እንዳላቸው ለማስረዳት ሞክረዋል።
በሌላ በኩል በምርጫው ጀግናው አትሌት ቀነኒሳ በቀለና ወጣቷ አትሌት ጉዳፍ ፀጋዬ የአትሌቶች ተወካዮች ተብለው ተመርጠዋል፤ የአትሌቶች ማህበር ግን አትሌቶቹ በመመረጣቸው ደስተኞች ቢሆንም ስለ ምርጫው ማኅበሩ ምንም እንደማያውቅና አትሌቶቹንም እንዳልወከላቸው በማረጋገጥ ሕጉን ያልጠበቀ አካሄድ ነው ሲል ኮንኗል።
ከተጠቀሱት አካላት ውጪ ሌሎች የጉዳዩ ባለቤቶች ዝምታን የመረጡበት ምክንያት አጠያያቂ ነው። ኦሊምፒክ ኮሚቴው አሻሻልኩት ባለው ደንብ የምክትል ፕሬዚዳንትነት ቦታን በቀጥታ ያገኘው አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ዝምታን ከመረጡት አንዱ ነው። ከሶስት ዓመት በፊት በተካሄደው ምርጫ የተቃውሞ መሪና አሰላፊ የነበረው አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በዚህ ጉባዔ ተወካይ ልኳል። ይሁንና ከባለፈው ከተቃወመው ምርጫ የማያንስ የሕግ ጥሰት በዚህኛውም የጨረባ ምርጫ በግልፅ እየታየ ፌዴሬሽኑና መሪዎቹ ዝም ማለታቸው አስገራሚና በብዙዎች ዘንድ ጥያቄ የተነሳበት ነው።
ዝምታን የመረጠው የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ኦሊምፒክ ኮሚቴው ከወር በፊት የደንብ ማሻሻያ ሲያደርግ እንዲሁም አወዛጋቢውን ምርጫ ሲያከናውን ምንም ጥሪ እንዳልቀረበለት የአደባባይ ሀቅ ነው። በምርጫው ላይም ተወካይ አልላከም። ሆኖም ይህንን ሕገወጥ ምርጫ በተመለከተ ተቃውሞም ሆነ ድጋፍ ሲያሰማ አለመታየቱ አስገራሚ ነው።
በምርጫው የተገኙና ያልተገኙ አባል ማኅበራት፣ ስማቸው ምርጫው ውስጥ የገባ አመራሮችና ስፖርተኞች እንዲሁም መንግሥት ጉዳዩን አይተው እንዳላዩ ማለፋቸው ጥያቄን ያጭራል። አንዳንዶቹ የፓሪስ ኦሊምፒክ ይለፍና እንናገራለን የሚል ሃሳብ ውስጥ ይገኛሉ። ይሁንና ይህንን ታላቅ ስህተት ለማረም የታሪክ ተወቃሽም ላለመሆን ትክክለኛው ጊዜ አሁን መሆኑን ግን ማስታወስ ይኖርባቸዋል። በርካታ የመንግስትና የግል መገናኛ ብዙሀን በተመሳሳይ ዝምታን መምረጣቸውም ያስተዛዝባል። እውነትን ፈልጎ ሸፍጥን አጋልጦ ሕዝቡ እንዲፈርድ የማድረግ ሙያዊ ኃላፊነት አለባቸው።
ሕገወጡን ምርጫ በይፋ የተቃወሙት ሻለቃ ኃይሌ እንዲሁም የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር በቀጣይ የራሳቸውን ርምጃ ለመውሰድ በመወሰናቸው ሌሎችም የሚመለከታቸው አካላት ከጎናቸው ሊቆሙ ይገባል። ኃይሌ ይህ ምርጫ ካልተሰረዘ እስከ ዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ድረስ እንደሚሄድ አረጋግጧል። ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱም ለመንግሥት አሳውቆ መፍትሄ እፈልጋለሁ ብሏል። መቀመጫውን ስዊዘርላንድ ያደረገው ዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ስለ ምርጫው የሚወስነው አልያም የሚያነሳው ጥያቄም በቀጣይነት ይጠበቃል። በኦሊምፒክ ኮሚቴው በኩል ደግሞ ይህንን ምርጫ በይፋ የተቃወሙትን በተለይ ኃይሌና ባህልና ስፖርት ሚኒስቴርን እንዲሁም ሌሎች የሚመጡ ካሉ ምን ሊያደርግባቸው እንደሚችል ወደፊት የሚታይ ይሆናል።
የክልል ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነሮችና የፌዴሬሽን የጽሕፈት ቤት ኃላፊዎች በማኅበራት ጉባኤዎች ላይ መመረጥና በድምፅ መሳተፍ እንደማይችሉ ገለልተኛ ሆነው ብቻ እንዲሳተፉ የስፖርት ማኅበራት ሕጉ ይደነግጋል፤ አሁን ግን የክልል ኦሊምፒክ ቅርንጫፎች በሚል በቦርድ አባልነት ገብተዋል፤ የአዲስ አበባ አስተዳደር እንዲሁም የሐረሪና የአማራ ስፖርት ኮሚሽኖች የኦሊምፒክ ኮሚቴ የቦርድ አባል ሆነው ተመርጠዋል፤ የኦሊምፒክ ቻርተሩ የማይፈቅደው መንግሥታዊ ተቋማት በኮሚቴው ውስጥ ማካተት ተሽሯል። የኦሊምፒክ ስፖርት ያልሆኑ ማህበራት በኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ውስጥ ድምፅ ሰጪ ተመራጭ አባል ወይም መሪ ሆነው መሥራት እንደማይችሉ ሀገራዊው ሕግ ያዛል፤ አሁን ግን ከኦሊምፒክ ጋር ምንም ግንኙነት የሌለው የባህል ስፖርቶች የቦርድ አባል ሆኖ ተመርጧል፤ ሌሎችም ሕጎች ተጥሰዋል።
ምርጫው በዚህ ወቅት በድብቅ የተካሄደበት ምክንያት ለማንም የተደበቀ አይደለም። የፓሪስ ኦሊምፒክ ውጤት ሳይታይ የኦሊምፒክ የኮሚቴው ሥራ ሳይገመገም ተቻኩሎ ምርጫ መደረጉ ምናልባትም ፓሪስ ላይ የሚመዘገበው ውጤት ጥሩ ካልሆነ አንመረጥም የሚል ስጋት ስላለ ሳይቀድሙን እንቅደማቸው በሚል ብልጣብልጥ አካሄድ ነው። ይህ ባለፈው ቶኪዮ ኦሊምፒክ ላይ የታየና ጀግናው አትሌታችን ሻለቃ ኃይሌም በጽኑ የሚያምንበት ጉዳይ ነው። ኮሚቴው ግን የኮቪድ ወረርሽኝ ብዙ መርሀግብሮችን እንዲራዘሙ በማድረጉ ያለፈውም የአሁኑም ምርጫ ከኦሊምፒክ በፊት እንዲካሄድ ተደርጓል ባይ ነው። ያለፈው ምርጫ ይሁን ብለን እንቀበል፣ ዘንድሮም ተመሳሳይ ምክንያት ማቅረብ ግን “ጨፍንና ላሞኝህ” ካልሆነ ምን ሊባል ይችላል?
የስፖርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታው በኦሊምፒክ ኮሚቴው ጥርስ ካስነከሰባቸው ምክንያቶች አንዱ መንግሥት ለቶኪዮ ኦሊምፒክ የሰጠው 156 ሚሊዮን ብር ኦዲት እንዲደረግ ለኦሊምፒክ ኮሚቴ ጥያቄ ቢያቀርቡም እምቢ መባሉን መግለፃቸው ነው። በዚህም ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ከኦሊምፒክ ኮሚቴ ጋር ያለው የሥራ ግንኙነት እየተቋረጠ መምጣቱን ሚኒስትር ዲኤታው ቃል በቃል ተናግረዋል። የኮሚቴው ፕሬዚዳንት ግን ኮሚቴው ከዚህ ቀደም በነበረው መንገድ ኦዲት መደረጉን ነው የሚናገሩት። በተለመደው መንገድ ኦዲት ሲደረግም የኮሚቴው አጠቃላይ ወጪና ገቢ አንድ ላይ ኦዲት ተደረገ እንጂ ለቶኪዮ ኦሊምፒክ መንግሥት የሰጠው ከ150 ሚሊዮን ብር በላይ ምን ላይ ዋለ የሚለው ጉዳይ አልተወራረደም። ይህ ገንዘብ ለብቻው በውጭ ኦዲት እንዲደረግ ፍቃደኛ አይደለም። የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ጥያቄም ይህ ለአንድ ኦሊምፒክ ከሕዝብ መቀነት ተፈትቶ የተሰጠ ገንዘብ ምን ምን ላይ እንደዋለ ይጣራ የሚል ነው። ምክንያቱም ከኮሚቴው አጠቃላይ ገቢና ወጪ ጋር ኦዲት መደረጉ በትክክል ምን ላይ እንደዋለ አያሳይምና።
አስገራሚው ነገር ከቶኪዮ ኦሊምፒክ በፊት በተካሄዱት ሦስት ኦሊምፒኮች በአጠቃላይ ይህን ያህል ገንዘብ አልወጣም። በቶኪዮ ኦሊምፒክ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ይህ ሁሉ ገንዘብ ፈሶ ግን የተመዘገበው አንድ የወርቅ ሜዳሊያ ነው። ይህን ለምን ብሎ የጠየቀና እንዲመረመር ያደረገ አካል አለመኖሩ ሲያስገርመን ኮሚቴው ዘንድሮም ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ ለፓሪስ ኦሊምፒክ ያስፈልጋል ብሎ ከመንግሥት ካዝና እስኪሰጠው እየተጠባበቀ ይገኛል። ይህ የፀረ ሙስና ተቋም ጭምር ሊመለከተው የሚገባ ሰፊ ጉዳይ መሆኑን በዚሁ አጋጣሚ መጠቆሙ ተገቢ ነው።
ኮሚቴው ከምርጫ ዘመን ማራዘም ጀምሮ ያሻሻላቸውን አብዛኞቹን ሕግና ደንቦች በረቀቀና ለትርጉም እንዲሁም መከራከሪያ ነጥብ ክፍት በሆነ መንገድ በጉባዔ ሕግና ደንብ አፀድቆ ተብትቦ አስቀምጧቸዋል። ይህም ነገ ጉዳዩ እየከረረ ሲሄድ መንግሥት ጣልቃ ገብቶ እንዳያስተካክል ሀገርን ከኦሊምፒክ ሊያሳግድ ይችላል በሚል ስጋት እግር ከወርች አስሮ የሚያስቀምጥ አይነት ነው። ኢትዮጵያ በፊፋ ውድድሮች የታገደችበት ጊዜ የሩቅ ዘመን ታሪክ አይደለም። አሁንም ኦሊምፒክ ኮሚቴውን በፕሬዚዳንትነት እየመሩ የሚገኙት ግለሰብ ያኔ ኢትዮጵያ በፊፋ ስትታገድ የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት እንደነበሩ ልብ ይሏል። አሁንም ተመሳሳይ ካርድ መምዘዝ የሚያስችላቸውን መንገድ ሊከተሉ ስለሚችሉም እዚህ ሁሉ አዘቅጥ ውስጥ ከመገባቱ አስቀድሞ ግን ለኢትዮጵያ ኦሊምፒክ የሚቆረቆር ሁሉ ድምፁን ሊያሰማ ይገባል!
ሚዛን ስሜ
አዲስ ዘመን ሰኔ 30 ቀን 2016 ዓ.ም