የሀገር መድህን የሆነው የበጎ ፈቃድ ሥራ

የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰዎች በራሳቸው ተነሳሽነትና መልካም ፈቃድ ለኅብረተሰቡ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ በመሳተፍ ነፃ አገልግሎት የሚያበረክቱበት ተግባር ነው።

የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የሰው ልጅ ምንም አይነት ክፍያ የማያገኝበት ይበጃል፣ ይሆናል፣ ያስደስታልና የህሊና እርካታ ያስገኛል ብሎ ያለምንም ቀስቃሽና ጎትጓች በእራሱ ተነሳሽነት የሚፈፅመው ተግባር ነው።

ይህ ተግባር ማንኛውንም ዜጋ የሚያሳትፍ ቢሆንም በዋናነት ግን ወጣቶችን በስፋት የሚመለከት ተግባር ነው። ይህ እንቅስቃሴ ማህበራዊ ትስስርን፣ አንድነትንና ፍቅርን የበለጠ እንዲጠናከር ማድረግ ማስቻሉ ደግሞ ሌላኛው ፋይዳ ነው።

በጎነት የሚታይ ፍሬ ነው። የሕይወትን ጎተራ የሚሞላ ለግለሰብና ለሀገር የሚተርፍ ተግባር፤ በጎነት ከማሰብ በዘለለ፤ አብዝቶ ከመልካም ሥራዎች ጎን መሰልፍን፣ ሌሎችን ማገዝ ላይ ማትኮርን ከሰው ምላሸ ሳይጠብቁ ከራስ በላይ ለሌሎች ማድረግን የሚጠይቅ የንፁህ ልብ ክዋኔ ነው።

በጎነት ለኢትዮጵያውያን የአብሮነታቸው ድልድይ፣ የትስስራቸው ገመድ ሆኖ ብዙ ፈታኝ ሁኔታዎችን አሻግሮ ዛሬ ላይ ያደረሳቸው ትልቅ እሴት ነው። በጎነት የአእምሮ እርካታ የምናገኝበት፣ ደስታን የምንፈጥርበት፣ ሀገር የምትለማበት በሰውነታችን የታደልነው ስጦታ ነው።

የተትረፈረፈ ሀብት ስላለን ወይም አቅማችን የተለየ ስለሆነ የምንፈፅመው ሳይሆን ሁሉም ሰው የታደለው ፀጋና እምቅ ሃይል ነው። ፀጋውን ወደ ተግባር ስንቀይር የሌሎች ሕይወትን የሚቀይር፣ ችግር ውስጥ ያሉትን እንባ የሚያብስ ስጦታ ነው።

የሌሎች ሕይወትን መቀየርና ከችግር መታደግ ደግሞ ትልቁ የአእምሮ እርካታ ምንጭ ነው። በጎነት ለኢትዮጵያውያን የአብሮነታቸው ድልድይ፣ የትስስራቸው ገመድ ሆኖ ከትናንት እስከ ዛሬ ብዙ ፈታኝ ሁኔታዎችን አሻግሮ ዛሬ ላይ ያደረሳቸው ትልቅ እሴት ስለመሆኑ የሚያጠያይቅ አይደለም። ካለበጎነት ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ብዙ ፈታኝ ጊዜን ተሻግረው በጋራ ደምቀው ችግራቸውን አልፈው ባልቀጠሉ ነበር።

በመሆኑም በጎነት ከትናንት እስከ ዛሬ ካሻገሩን መልካም እሴቶቻችን መካከል አንዱና ዛሬም አጠናክረን ለቀጣዩ ትውልድ ልናሻግረው የሚገባው እሴታችን ነው።

የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ዜጎች በሩቁ የሚሰሙት ሳይሆን የቀን ተቀን የሕይወት ልምምዳቸው እንዲሆን መንግሥት የብሔራዊ የበጎ ፈቃድ ማህበረሰብ አገልግሎት ፕሮግራም ቀርጾ አበይት ተግባራት የተከናወኑ ሲሆን በዚህም ዘርፈ ብዙ ውጤቶች ተመዝገበውበታል።

በተለይ በኢትዮጵያ በክረምት ወራት በሚከናወኑ የበጎ አድራጎት ሥራዎች የብዙ አቅመ ደካማ ግለሰቦች የዘመመ ጎጆ ተቃንቶና እንደ አዲስ ተሠርቶ ከክረምት ዝናብ ከበጋ ደግሞ ከፀሀይ ተርፈው ሕይወታቸውን መምራት ችለዋል። በደም ልገሳ እንዲሁ የብዙ እናቶችን ብሎም በተለያየ ህመም ለሚሰቃዩ ወገኖች ደም በመለገስ ሕይወት አድን ሥራ መሥራት እንደተቻለ አይተናል።

ዘንድሮም በሀገር አቀፍ የክረምት ወራት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ለማከናወን “በጎነት እና አብሮነት ለኢትዮጵያ ከፍታ” በሚል መሪ ቃል ወደ ሥራ ተገብቷል። በዘንድሮው የክረምት በጎ አድራጎት ሥራ የማስጀመሪያ መድረክ ላይ የተገኙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፤ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በተደመረ ጉልበት፣ እውቀትና ክህሎት ሀገር የመገንባት ሂደት ነው። ከዚህ ቀደም በበጎ ፍቃድ በተሰጡ አገልግሎቶች የማህበረሰቡ አንገብጋቢ ችግሮች መፍታት ተችሏል። በዘንድሮው ክረምትም ሚሊዮኖች ይደገፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልፀዋል ።

ለዚህም የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን በተቀናጀ አግባብ ለመምራትና ዜጎች የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን ባህል ማድረግ እንዲችሉ የተለያዩ ፖሊሲዎችን እና አሠራር ሥርዓት መዘርጋት በማስፈለጉ የፖሊሲ ዝግጅት ረቂቅ ተዘጋጅቶ ለሚመለከተው የመንግሥት አካል ቀርቧል። ይህ ፖሊሲ እስኪጸድቅም ከ2002 ዓ.ም ጀምሮ የተቀረጸው የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች ስታንዳርድ ተግባራዊ እየተደረገ ነው።

በ2016 ዓ.ም የክረምት ወራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የስምሪት መርሐ-ግብር 34ሚሊዮን 27ሺ 197 በጎ ፈቃደኞችን በ14 የስምሪት መስኮች በማሠማራት 49 ሚሊዮን 598ሺ 406 የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው። በዚህም 26,051,064,875 ብር የሚገመት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በመስጠት፣ ማህበራዊ ትስስር እና ህብረ ብሔራዊ አንድነት የሚጠናከርበት እንደሚሆን በመድረኩ ተገልጿል።

ሀገር ማለት ሰው እንደመሆኑ ሀገር የሚለውጥ መልካም ሃሳብ ያላቸው ግለሰቦች ሀገራቸውን ለማቅናት መንገድ ስለሚሆን በበጎ አድራጎት ሥራዎች ላይ ንቁ ተሳታፊ መሆን ይኖርባቸዋል።

የወጣትነት ትኩስ ጉልበት ለበጎነት ሲውል ደግሞ እንደ ሀገር ትርጉሙ ብዙ በመሆኑ በተለይ ወጣቶች በዚህ የክረምት የበጎ አድራጎት ሥራ በንቃት መሳተፍ አለባቸው።

ለመልካም ሥራ ረፍዶ አያውቅም ፤ በጎነትን ዛሬ መጀመር ይቻላል። ካለን ነገር ለማካፈል የግድ ሀብታም መሆን አያስፈልገንም። ማንኛውም ሰው በጎ ነገር ማድረግ ይችላል። ስለዚህ የወደቁትን ለማንሳትና ጠያቂና አጋዥ የሌላቸውን ሰዎች አለንላችሁ ለማለት ሁሉም ሰው በተለይ ወጣቱ በበጎ ፈቃድ ሥራ ውስጥ መሳተፍ ይኖርበታል።

ይህ ሲሆን የሀገር ሸክም ይቀላል፤ የአቅመ ደካሞች መንፈስ ይታደሳል፣ ያዘዘመው ይቃናል፤ የደፈረሰው ይጠራል። የአረጋውያን እንባ ይታበሳል፤ የተራቡ ይጠግባሉ፤ መንፈሳቸው የታወከ የፈወሳሉ። እንደሀገርም ድህነት ይመጣል።

ክብረአብ

አዲስ ዘመን  ሰኔ 30 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You