መንግሥት መሠረታዊ ስብራቶችን በመጠገን ገለልተኛ ሲቪል ሰርቪስ ለመገንባት እየሠራ ነው

አዲስ አበባ፦ መንግሥት መሠረታዊ ስብራቶችን በመጠገን ገለልተኛ ሲቪል ሰርቪስ ለመገንባት እየሠራ መሆኑን የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ቦርድ ሰብሳቢ ዶክተር ተመስገን ቡርቃ ገለጹ።

የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሰለጠናቸውን ሁለት ሺህ 269 ተማሪዎች ትናንት አስመርቋል።

የዩኒቨርሲቲው የቦርድ ሰብሳቢ ዶክተር ተመስገን ቡርቃ በምረቃ መርሀ ግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልእክት፤ የሰለጠነና ቀልጣፋ አገልግሎት የሚሰጥ ሲቪል ሰርቪስ ሥርዓት መገንባት ለአንድ ሀገር እድገት ጉልህ አስተዋጽኦ ያበረክታል። በመሆኑም መንግሥት መሠረታዊ ስብራቶችን በመጠገን ገለልተኛ ሲቪል ሰርቪስ ለመገንባት እየሠራ ነው።

የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲም ከተመሰረተበት ጊዜ አንስቶ ከ50 ሺህ በላይ ምሩቃንን አሰልጥኖ በማስመረቅ ለሲቪል ሰርቪስ ሥርዓቱ ግንባታ ትልቅ ሚና ተጫውቷል ብለዋል። በቀጣይነትም ይህን ሥራውን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚኖርበት አመላክተዋል። ምሩቃን ከአድሎ ነጻ ሆነው ሕዝባቸውን እንዲያገለግሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ፍቅሬ ደሳለኝ በበኩላቸው፤ ዩኒቨርሲቲው መንግሥትና ሕዝብ የጣሉበትን የመማር ማስተማር፣ ችግር ፈቺና የፖሊሲ ግብዓት የሚሆን ጥናትና ምርምር ማካሄድ እንዲሁም የማህበረሰብ አገልግሎት መስጠት ኃላፊነት በአግባቡ ለመወጣት እየሠራ ነው።

በዚህም ባለፉት አራት ዓመታት 497 ችግር ፈቺና የፖሊሲ ግብዓት መሆን የሚችሉ ጥናትና ምርምሮችን አከናውኗል።

 

የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራት እያከናወነው ባለው ሥራም በ2016 ሰባት ሺህ 268 ተማሪዎችን ተቀብሎ በማስተማር ላይ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በ2017 የትምህርት ዘመንም ከሰባት ሺህ በላይ ተመሪዎችን ለመቀበል ምዘና ማከናወኑን ገልጸዋል።

ጠንካራ የምርምርና ማማከር ሥርዓት በመገንባት በሚዲናዋ የሚከናወኑ የኮሪደር ልማትን ጨምሮ ለሀገራዊ ሁለንተናዊ ለውጥ እያበረከተ መሆኑን አንስተዋል።

ምርምሮችን በዲጅታል የመረጃ ቋት በማደራጀት ለሕዝብ ተደራሽ እያደረገ ነው ሲሉም ፕሬዚዳንቱ አብራርተዋል፡፡

የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራት እያከናወነው ባለው ሥራም ተማሪዎችን ተቀብሎ በማስተማር ላይ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በትናንትናው ዕለት ከተመረቁት ሁለት ሺህ 269 ተማሪዎች መካከል 122 በመጀመሪያ ዲግሪ፣ ሁለት ሺህ 120 በሁለተኛ ዲግሪ እንዲሁም 27 በሦስተኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን የተከታተሉ መሆናቸው ተጠቁሟል።

ፋንታነሽ ክንዴ

አዲስ ዘመን ሰኔ 30 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You