የሆንግ ኮንግ አየር መንገድ ሁከት የፈጠሩ ጥንዶች ድጋሚ በአውሮፕላኖቹ እንዳይበሩ አገደ

የሆንግ ኮንግ አየር መንገድ የሆነው ካቲ ፓሲፊክ በበረራ ወቅት ሁከት የፈጠሩ ሁለት ባልና ሚስት መንገደኞች ድጋሚ በአውሮፕላኖቹ እንዳይበሩ አግዷል፡፡ ጥንዶቹ አንዲት ከቻይና የመጣች መንገደኛ ወንበሯን ወደኋላ በመዘርጋቷ ምክንያት ነው ግርግር የፈጠሩት።

ቻይናዊቷ መንገደኛ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጿ እንደለጠፈችው ከሆነ ጥንዶቹ ከኋላዋ ተቀምጠው ሳለ ወንበሯን ለመደገፍ እንዲመች በመለጠጧ ነው ሁከት የተነሳው።

የሆንግ ኮንግ አየር መንገድ የሆነው ካቲ ፓሲፊክ ባለፈው እሑድ ባወጣው መግለጫ ጥንዶቹ ድጋሚ በአውሮፕላኖቹ ላይ እንዳይጓዙ ጥቁር መዝገብ [ብላክሊስት] ውስጥ ስማቸውን ማስፈሩን አስታውቋል። አየር መንገዱ በመግለጫው “ጥብቅ የሆነ የመቻቻል ፖሊሲ” እንደሚያራምድ ገልፆ፣ ሌሎች መንገደኞችን መረብሽ ፍፁም ተቀባይነት የለውም ብሏል።

ካቲ ፓሲፊክ ሁከት አሊያም ግርግር ፈጥረዋል በሚል መንገደኞችን ያገደ የመጀመሪያው አየር መንገድ አይደለም። በተለይ በአሜሪካ የግል አየር መንገዶች ያልተገባ ባህሪ አሳይተዋል የሚሏቸውን መንገደኞች ድጋሚ ድርሽ እንዳይሉ ያግዳሉ።

ከአሜሪካ የግል አየር መንገዶች አንዱ የሆነው ዴልታ ዋና ሥራ አስኪያጅ በረራ የሚያስተጓጉሉ መንገደኞች በፌዴራል መንግሥት እስከ ወዲያኛው በአውሮፕላን እንዳይጓዙ ሊታገዱ ይገባል ብለው መጠየቃቸው ይታወሳል።

አየር መንገዶች በረራ ላይ ያልተገባ ባሕሪ አሳይተዋል ያሏቸውን መንገደኞች ወንጀል ቢፈፅሙም ባይፈፅሙም የማገድ መብት አላቸው።

ዴልታ አየር መንገድ በአውሮፓውያኑ 2022 ባወጣው መረጃ 1‚900 ሰዎችን ‘ኖ ፍላይ ሊስት’ ውስጥ እንዳስገባ ይናገራል። አብዛኞቹ በኮቪድ ወረርሽኝ ወቅት መመሪያዎችን ባለመከተላቸው ነው ድጋሚ በአየር መንገዱ አውሮፕላኖች እንዳይሳፈሩ የታገዱት።

ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የሚያገለግሉ አየር መንገዶችን ጨምሮ በተለያዩ አገራት ያሉ አየር መንገዶች የየራሳቸው የበረራ ‘ብላክሊስት’ አላቸው። ይህ ማለት አንድ መንገደኛ አውሮፕላን ሲሳፈር አሊያም በረራ ላይ ሳለ የአየር መንገዱን ሕግጋት የሚጥስ ተግባር ከፈፀመ በአየር መንገዱ አውሮፕላኖች ድጋሚ እንዳይሳፈር ይታገዳል ማለት ነው።

አንዳንድ አየር መንገዶች እንደ ተሳፋሪው ድርጊት ክብደት ቅጣቱን በዓመታት ሊገድቡት ቢችሉም አንዳንዶቹ ደግሞ መቼም ቢሆን መንገደኞች ድርሽ እንዲሉ አይፈቅዱም። አንድ መንገደኛ በአንድ አየር መንገድ ታገደ ማለት በሌሎች አየር መንገዶች መሳፈር አይችልም ማለት ግን አይደለም።

ለዚህ ነው የአሜሪካ አየር መንገዶች ‘ኖ ፍላይ ሊስት’ ውስጥ የገቡ ሰዎች የፌዴራል ቅጣት ይጣልባቸው የሚሉት። ይህ ከሆነ በረራ አውኳል የተባለ አንድ መንገደኛ ድጋሚ አውሮፕላን መሳፈር አይችልም ማለት ነው።

በረራ የሚያውክ ባህሪ አሳይተዋል የተባሉ ሰዎች ድጋሚ እንዳይበሩ ከመታገዳቸው በላይ፣ የገንዘብ ቅጣት ሊጣልባቸው እንዲሁም ክስ ሊመሠርትባቸው ይችላል።

ይህ ዕግድ ሁለት ዓይነት ነው። አንደኛው በአየር መንገዶች የሚፈፀም ሲሆን፣ ሌላኛው እና ከባድ የሚባለው ደግሞ በፌዴራል መንግሥት ተግባራዊ የሚደረግ እና መንገደኞች በአውሮፕላን በረራ ከአገር እንዳይወጡ የሚያግድ ነው። ሕጉ በበርካታ አገራት ተመሳሳይ ቢሆንም አፈፃፀሙ ሊለያይ ይችላል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በፖሊሲው መሠረት መንገደኞች በአልኮል መጠጥ አሊያም በአደገኛ ዕፅ ተፅዕኖ ውስጥ ካሉ ከበረራ ሊታገዱ ይችላል ይላል። አልፎም ሌሎች መንገደኞችን ሰላም የሚነሱ ወይም በረራውን አደጋ ላይ የሚጥሉ፤ ከበረራው ክፍል የሚሰጣቸውን ትዕዛዝ የማይቀበሉ፤ ያልተገባ ባህሪ የሚያሳዩ እንዲሁም ሌሎች መንገደኞች ወይም የበረራ ሠራተኞች ላይ አደጋ የሚያመጡ ከበረራ ሊታገዱ ይችላሉ።

አየር መንገዱ ‘ኖ ፋላይ ሊስት’ ወይም ላልተወሰነ ጊዜ በኢትዮጵያ አየር መንገድ እንዳይበሩ ስለማገድ በድረ-ገፁ በግልፅ ያስቀመጠው መመሪያ የለም። በቅርቡ ዮሐንስ ዳንኤል የተባለ ቲክቶከርን ጨምሮ ስድስት ግለሰቦች ወደ መቀለ በሚደረግ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ላይ በፈጠሩት ግርግር ምክንያት በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ይታወሳል።

በዕለቱ አውሮፕላኑ በነበረው ጭጋጋማ የአየር ሁኔታ መብረር እንደማይችል ቢገለጽም፤ አውሮፕላን ላይ ተሳፍረው የነበሩት ግለሰቦች ከአውሮፕላን “አንወርድም” በማለት ከአየር መንገዱ ሠራተኞች ጋር እሰጥ አገባ ውስጥ ሲገቡ ማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ በተለቀቁ ተንቀሳቃሽ ምሥሎች ታይተዋል።

ዘ ትራቭል የተሰኘው የጉዞ ምክር ሰጪ ድረ-ገፅ ‘ኖ ፍላይ ሊስት’ ውስጥ የሚያስገቡ ያላቸውን 7 ድርጊቶች ይፋ አድርጓል። አብዛኞቹ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ድረ-ገፅ ላይ ከተቀመጡት መመሪያዎች ጋር ተመሳሳይነት አላቸው።

የበረራ አስተናጋጆች የሚሰጡትን መመሪያ አለመቀበል እና የአውሮፕላኑን ሠራተኞችን መተናኮስ ሊያስቀጣ ይችላል። ሰክሮ መገኘት እና የአደጋ ጊዜ መውጫ በርን ለመክፈት መሞከር ለዕግድ ሊዳርግ ይችላል።

መንገደኞችን ከበረራ ማገድ የሚባለው ሐሳብ በጣም እየተስፋፋ የመጣው እንዲሁም ሕጉ ጠበቅ ማለት የጀመረው ከመስከረም 11 በአሜሪካው ላይ ከተፈጸመወው የሽብር ጥቃት በኋላ ነው።

አሜሪካን ጨምሮ ሌሎች ምዕራባዊያን አገራት በሽብርተኝነት የፈረጇቸውን ቡድኖች አባላት ‘ኖ ፍላይ ሊስት’ ውስጥ ያስገቧቸዋል። ይህም ማለት ግለሰቦቹ ዕግድ ወደተጣለባቸው አገራት አየር ክልል መግባት አይችሉም ማለት ነው።

የአሜሪካው ፌዴራል ቢሮ ኦፍ ኢንቬስቲጌሽን (ኤፍቢአይ) እንዳይበሩ የታገዱ ሰዎችን የሚከታተልበት መዝገብ አለው።

በሌላ በኩል በዓለማችን ያሉ አየር መንገዶች የራሳቸውን ዕግድ ማስተላለፍ እንዲችሉ ሥልጣን ተሰጥተቸዋል። አየር መንገዶች ሁከት ፈጥረዋል አሊያም ሕግጋት አልተከተሉም ያሏቸውን መንገደኞች በራሳቸው የማገድ መብት አላቸው ማለት ነው።

ያልተገባ ባህሪ ማሳየት የሚለው ዝርዝር ሰፋ ያለ ሲሆን፣ ከመጠን ያለፈ አልኮል ከመጠጣት ጀምሮ እስከ የበረራ አስተናጋጆችን መተናኮል የሚለው ተካቶበታል።

የአሜሪካው ፌዴራል አቪየሽን አስተዳዳሪ እንደሚለው መንገደኞች ድጋሚ እንዳይበሩ ከመታገድ ባለፈ እስከ 37 ሺህ ዶላር የሚደርስ ቅጣት ሊከናነቡ እና የወንጀል ክስ ሊመሠርትባቸው ይችላል።

ከሆንግ ኮንግ የመጡት ጥንዶች ከዚህ በኋላ በካቲ ፓሲፊክ አየር መንገድ መብረር አይችሉም ማለት ነው። ይህ ማለት በሌሎች አየር መንገዶች መጠቀም አይችሉም ማለት ግን አይደለም።

አብዛኛውን ጊዜ መንገደኞች አላስፈላጊ ባህሪ አሳይተዋል ተብለው ከበረራ የሚታገዱት በስካር ምክንያት እንደሆነ አንድ ጥናት ይጠቁማል።

የአሜሪካ ሕግ መንገደኞች በአየር መንገዱ አስተናጋጆች ካልቀረበላቸው በቀር ከበረራ በፊትም ሆነ በረራ ላይ አልኮል መጠጥ መጠቀምን ይከለክላል።

በአንዳንድ አገራት ድጋሚ እንዳይበሩ ዕግድ የተጣለባቸው ሰዎች ለፍርድ ቤት ይግባኝ ብለው ጉዳያቸው እንዲታይ እና ድጋሚ መብረር እንዲችሉ መጠየቅ ይችላሉ።

በጋዜጣው ሪፖርተር

 አዲስ ዘመን መስከረም 25/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You