የሠራተኛውን የማዘውተሪያ ስፍራ ችግሮች ለመቅረፍ ጥረት እየተደረገ ነው

የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) በየዓመቱ በሚያካሂዳቸው የሠራተኛ ውድድሮች የማዘውተሪያ ስፍራ ችግር አንዱ ፈተናው ነው። ባለፉት ዓመታት የነበሩ የማዘውተሪያ ስፍራዎችን ችግር ዘንድሮ ለመቅረፍ ከወዲሁ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት በተለይም ከአዲስ አበባ እንዲሁም ከኦሮሚያ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ጋር በመነጋገር ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል፡፡

የኢሠማኮ ማህበራዊ ጉዳይ ኃላፊና የስፖርት ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ፍሰሃፂዮን ቢያድግልኝ እንደገለጹት፤ ኢሠማኮ የራሱ የስፖርት ሜዳ እንዲኖረው ለማድረግ ከረጅም ዓመት ጀምሮ በተለይም ከአዲስ አበባ መስተዳድር ቦታ እንዲሰጠው ጠይቆ ነበር። በዚህም ላፍቶ ወይም ቦሌ ክፍለ ከተማ ሜዳዎች ተመርጠውና ፕላን ተዘጋጅቶ መቶ ሚሊዮን ብር የሚያወጣ ሜዳ ለማዘጋጀት አቅዶ ነበር። ይሁን እንጂ የመሬት ልማት ማኔጅመንቶች ሰዎች ሲቀያየሩ ሳይሳካ ቀረ። ኢሠማኮ አሁን ላይ የማዘውተሪያ ስፍራ ለማግኘት ለኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥትና ለስፖርት ቢሮው በሸገር ከተማና አካባቢው ትብብር እንዲደረግ ጥያቄ አቅርቦ እየተከታተለ ይገኛል።

ቦታው ከተገኘም ለጊዜው በቆርቆሮም ቢሆን አጥሮ እየተጠቀመ ማዘውተሪያ ስፍራውን የመስራት ሃሳብ እንዳለው አቶ ፍሰሃፂዮን ይናገራሉ። ኢሠማኮ በርካታ አባል ድርጅቶች አሉት(በአዲስ አበባ እንኳን ከ30-70ሺ ይሆናሉ)፣ እነዚህን በማስተባበር በሂደት ሁሉም የሚችለውን አዋጥቶ ማዘውተሪያውን በመስራት ከአስር ዓመት በላይ ጥረት የተደረገበትን የስፖርት ሜዳ እውን ያደርገዋል የሚል ተስፋ እንዳላቸው አቶ ፍሰሃፂዮን ያስረዳሉ፡፡

እንደ ኃላፊው ገለፃ፣ በአሁኑ ወቅት ወደ 2‚400 ያህል ድርጅቶች በኢሠማኮ ስር ታቅፈው ይገኛሉ። ወደ አንድ ሚሊዮን ሠራተኛ አለ፤ ድርጅቶቹ እነዚህ ብቻ አይደሉም፣ ወደ አራት ሚሊዮን ያህል በኢሠማኮ ስር ያልተደራጀ ሠራተኛ አለ። እነዚህን ማምጣት ያስፈልጋል። ተቋማት መደራጀትና የኢሠማኮ አባል መሆን አለባቸው፤ የመደራጀት ጥቅሙን እየተገነዘቡ ሲሄዱም ስፖርቱ የሚፈጥርላቸው ውጤት ምንድነው የሚለውን ጉዳይ በተለይም ጤንነቱ የተጠበቀ አምራች ዜጋ ከመፍጠር አንፃር ግንዛቤ ማሳደግ ያስፈልጋል ብለው ያምናሉ። ስፖርት ጥቅሙ ለሠራተኛው ብቻ ሳይሆን ለአሰሪውም ጭምር ነው። ሠራተኛው በስፖርት ጤንነቱ የተጠበቀ ሲሆን ምርትና ምርታማነት ይጨምራል፣ ሌላው ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር ወዳጅነትን ለመፍጠር ልምድ ለመለዋወጥ፣ ጥሩ የስራ ከባቢ ለመፍጠርና ወዘተ ግንዛቤው ካደገ ሠራተኛው ስፖርቱን የራሱ ያደርገዋል ይላሉ፡፡

ሌላው የሠራተኛው ስፖርት ችግር በጀት ነው። በ1970ዎቹ ሠራተኛው ከራሱ ኪስ እያወጣ ትግል ፍሬ፣ እርምጃችንና የመሳሰሉት መፈጠራቸውን ያስታወሱት አቶ ፍሰሃፂዮን፣ በወቅቱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም ከ70 በመቶ በላይ ከነዚሁ የተገኘ ነበር ይላሉ። ያንን ወርቃማ ዘመን ለመመለስ አሁን ላይ መስራት ያስፈልጋል። ይህ ደግሞ እውን የሚሆነው ሠራተኛው ስፖርቱን የራሱ ሲያደርገው ነው። ‹‹አሁን ላይ ስፖርቱ እየተካሄደ የሚገኘው ኢሠማኮና ሌሎች ባለድርሻ አካላት እንዲሁም ድርጅቶችና ሀገር አቀፍ የስፖርት ማህበራት ድጋፍ እያደረጉለት ነው። ኢሠማኮ አሁን ባለው የአቅም ውስንነት የተወሰነ በጀት ይመድባል፣ ግን በቂ አይደለም፤ በዚህ ረገድ ሠራተኛው ራሱ አስተዋፅኦ ማድረግ ይጠበቅበታል፣ ኢሠማኮ ኃይሉ ሰራተኛው ነው፣ የሚተዳደረው ሠራተኛው በሚያዋጣው አንድ ፐርሰንት ነው፣ ስፖርት በባህሪው ወጪ ይጠይቃል፣ ኢሠማኮ ኃይሉን እያጠናከረ የፋይናንስ ችግሩን ለመቅረፍ ሠራተኛው ለስፖርቱ ማዋጣት አለበት፣ ይህም ስፖርቱ የራሱ እንደሆነ እንዲሰማው ያደርጋል፡፡›› ብለዋል።

አቶ ፍሰሃፂዮን አክለውም፣ ‹‹ተቋማትና የሠራተኛው ቁጥር እየጨመረ ነው የሚሄደው፤ ይህን ወጥ በሆነ መንገድ አደራጅቶ ለመምራት ኢሰማኮ ለወደፊቱ በባለ ድርሻ አካላት የሚዋቀር እንደ ቦርድ የማቋቋም ሃሳብ አለው፤ በዚህ የሀገሪቱን ትልልቅ ተቋማት በማካተት ከበጀት ጀምሮ ድጋፍ እያደረጉ በራሳቸው እንዲመሩት ማድረግ፣ ስፖርቱ በስራ ቦታዎች ጭምር እንዲደረግ እቅዶች አሉን፡፡›› ሲሉም አብራርተዋል።

ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ግንኙነቶችን በማጠናከርም ሀገር አቀፍ የስፖርት ማህበራትና ሌሎችም የሚያደርጉትን ድጋፍ ማስቀጠል የእቅድ አካል ነው። በዚህ ረገድ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኢሠማኮ በኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ጠቅላላ ጉባዔ ድምፅ እንዳይኖረው መደረጉ ይታወቃል። አቶ ፍሰሃፂዮን በዚህ ጉዳይ ላይ ማብራሪያ ሲሰጡ ‹‹ይሄ መሆን የለበትም፤ ሠራተኛው የማህበረሰቡ ትልቅ አካል ነውና ኮሚቴው ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። ይህን ለባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ጭምር በደብዳቤ ገልጸን መልስ እየጠበቅን ነው። በየዓመቱ የበጀትና የስፖርት ትጥቆች ድጋፍ እየተደረገልን ነበር፣ በዚህም ስፖርተኞችን እየሸለምንና እያበረታታን ነበር፣ ስፖርትን ማስፋፋት አላማው ያደረገው ኦሊምፒክ ኮሚቴ ይበልጥ መደገፍ እንጂ እኛን ማግለል የለበትም፡፡›› ብለዋል፡፡

አቶ ፍሰሃፂዮን የ2017 ዓ.ም የሠራተኛው ስፖርታዊ ውድድሮችን በተመለከተ ሲናገሩም፣ ህዳር መጀመሪያ አካባቢ ሊጀመር በታቀደው የበጋ ወራት ውድድሮች ቅርጫት ኳስን አንዱ የፉክክር አካል ከማድረግ በተጨማሪ የሴቶች የስፖርት ተሳትፎም በከፍተኛ ሁኔታ እንዲጨምርና ድርጅቶችም ለዚህ ልዩ ትኩረት እንዲሰጡበት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል። ለዚህም ከሁለት መቶ በላይ ድርጅቶች በውድድሮች እንዲሳተፉ በደብዳቤ ጥሪ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመው፤ ከ9ኙ የኢሠማኮ ኢንዱስትሪ ፌዴሬሽኖች የትኞቹ የስፖርት ማህበራት እንደሚሳተፉ ዝርዝሩ በቀረበላቸው መሰረት በደብዳቤ እየጠየቁ እንደሚገኙ አስረድተዋል። በዚህም ዘንድሮ በተለይም በአዲስ አበባና ዙሪያዋ የሚገኙ ማህበራት ጥሩ ተሳትፎ ይኖራቸዋል የሚል ተስፋ አላቸው፡፡

ቦጋለ አበበ

አዲስ ዘመን መስከረም 25/2017 ዓ.ም

Recommended For You