ማንበብ አስደሳች ጊዜ ማሳለፊያ ብቻ ሳይሆን ሌሎችን ለመረዳትም ጠቃሚ መሣሪያ ነው

ዲላ:- ማንበብ አስደሳች ጊዜ ማሳለፊያ ብቻ ሳይሆን የሌሎችን ባህል፣ እምነትና አስተሳሰብ ለመረዳት የሚያስችል መሣሪያ ነው ሲሉ የዲላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ኤሊያስ አለሙ (ዶ/ር) ገለጹ።

በጌዴኦ ዞን ዲላ ከተማ “የንባብ ባህል ለትምህርት ጥራት” በሚል መሪ ሃሳብ የንባብ ሳምንት ማስጀመሪያ መርሀ ግብር ትናንት ተካሂዷል።

በመርሃ ግብሩ የዲላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ኤሊያስ አለሙ (ዶ/ር) እንደተናገሩት፤ ማንበብ አስደሳች ጊዜ ማሳለፊያ ብቻ ሳይሆን የሌሎችን ባህል፣ እምነትና አስተሳሰብ ለመረዳት የሚያስችል መሣሪያ ነው።

የማንበብ ፍቅርን በማዳበር በዙሪያችን ስላለው ዓለም ሰፋ ያለ እይታን ማዳበር እንችላለን ያሉት ኤሊያስ አለሙ (ዶ/ር)፤ አዘውትረው የሚያነቡ ግለሰቦች ርህራሄን፣ አመለካከትን እና ማህበራዊ ግንዛቤን የመረዳት ችሎታቸው ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።

ማንበብ ለተለያዩ አመለካከቶች እና ባህሎች ያጋልጣል። ይህም ያሰብነውን ሃሳብ ጥንካሬና ድክመት እንድንለይ ከማስቻሉም በላይ የዓለም እይታችንን ያሰፋል ያሉት ኤሊያስ አለሙ (ዶ/ር)፤ ከዚህ አንፃር መፅሐፎች ስለ ሰው ስሜቶች፣ ተነሳሽነቶች እና ልምዶች ጥልቅ ግንዛቤን የምንረዳባቸው መሣሪያ ናቸው ሲሉም ተናግረዋል።

የጌዴኦ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ዘማች ክፍሌ በበኩላቸው፤ አንባቢ ትውልድ የተለያዩ አመለካከቶችን እና ልምዶችን በጥልቀት መረዳት ይችላል። በዚህም ሀገርን ያለማል፣ ራሱን ያሳድጋል፣ ከሌሎች ጋር መግባባት ይችላል ብለዋል።

ይህም በሰዎች መካከል ያለውን ልዩነት እንድናውቅ እና እንድናከብር ከማድረጉም በላይ ይበልጥ የሚያቀራርብ እና የሚስማሙ ግንኙነቶችን ያመጣል ያሉት አቶ ዘማች ክፍሌ፤ የንባብ ሳምንቱ በጌዴኦ ዞን የተካሄደበት ዓላማም ነዋሪዎች የማንበብ ጠቀሜታን ተረድተው የትሩፋቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል መሆኑን ገልጸዋል።

ማንበብ መቻል የእውቀት መሠረት እና የፈጠራ ምንጭ ሆኖ ሳለ ማህበራዊ ሚዲያ የማንበብ ባህል ላይ ተፅዕኖ እያሳደረ ይገኛል ያሉት ደግሞ የዲላ ከተማ ከንቲባ አቶ ዳንኤል ሽፈራው ናቸው።

የንባብ ሳምንቱ የኢትዮጵያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት ከጌዲዮ ዞን ትምህርት መምሪያና ከዲላ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር የተዘጋጀ ሲሆን፤ ይህም ወጣቶች ለንባብና ለምርምር ያላቸውን ክህሎት ለማጎልበት እንዲቻል የልምድ ልውውጥ ለማድረግ ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የኢትዮጵያ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጻሕፍት አገልግሎትና የዲላ ዩኒቨርሲቲ፣ የዲላ ከተማ አመራር አባላት፣ ደራሲ ዘነበ ወላና ሌሎችም ደራሲያን እንዲሁም ነዋሪዎች ተገኝተዋል።

ሳሙኤል ወንደሰን

አዲስ ዘመን መስከረም 25/2017 ዓ.ም

 

 

Recommended For You