አዲስ አበባ፡- የአሜሪካ መንግሥት ለኢትዮጵያ በከፍተኛ ትምህርት ተደራሽነትን ለማሻሻል እና ለማስፋት እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚያስቀጥል አስታወቀ፡፡
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከአሜሪካ ኤምባሲ ጋር በመተባበር የአሜሪካ መንግሥት ለኢትዮጵያ በፖይንት ፎር ፕሮግራም አማካኝነት ያደረጋቸውን ድጋፎች መነሻ በማድረግ የፕሬዝዴሻል ሲሚናር ያካሄደ ሲሆን፤ በሳይንስ ዘርፍ የአሜሪካ ብሔራዊ የክብር ሜዳሊያ ተሸላሚው ፕሮፌሰር ገቢሳ ኢጄታ ፅሁፍ አቅርበዋል።
በሴሚናሩ ላይ የተገኙት በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኢርቪን ማሲንጋ፤ የአሜሪካ መንግሥት ከኢትዮጵያ ጋር በመተባበር የትምህርት ተደራሽነትን ለማሻሻል እና ለማስፋት የበኩሉን አስተዋፅኦ እያበረከተ መሆኑን በመግለጽ፤ እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ፤ ፕሮግራሙ በዋናነት አሜሪካ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በመተባበር የትምህርት ተደራሽነትን ለማሻሻልና ለማስፋት በሚደረገው ጥረት ለተለያዩ ዘርፎች የቴክኒክ ድጋፍ በማድረግ ለኢትዮጵያ የልማት ጉዞ ትልቅ ሚና መጫወቱን ተናግረዋል።
የአሜሪካና የኢትዮጵያ ግንኙነት 120 ዓመታትን ያስቆጠረ እንደሆነና በተለይ የፖይንት ፎር ፕሮግራም በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የቆየ ትብብር እንዲጠናከር አስተዋጽኦ ማድረጉን የጠቆሙት አምባሳደር ኢርቪን ማሲንጋ፤ በአሁኑ ወቅት የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች አስተዳደርንና የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል እገዛ እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡
ይህ ፕሮግራም ለሁለቱ ሀገራት ዩኒቨርሲቲዎች በትምህርት እድለኞች፣ በጥናትና ምርምር ዘርፎች አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት ነው። ፕሮፌሰር ገቢሳ ኢጄታም የዚህ ፕሮግራም ተጠቃሚ ሲሆኑ በሠሯቸው በርካታ የጥናትና ምርምር ሥራዎችና ባገኟቸው ውጤቶች እጅግ የሚደነቁ መሆናቸውን አምባሳደሩ ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) እንደገለፁት፤ የሰው ልጅ ከምንም አይነት ሁኔታ ቢነሳ ባህሪው ካልገደበው በየትኛውም የዓለም ጫፍ መድረስ እንደሚችል ፕሮፌሰር ገቢሳ ኢጄታ ማሳያ ናቸው።
እንዲሁም ፕሮፌሰር ገቢሳ የዓለም የምግብ ድርጅትና በሳይንስ ዘርፍ የአሜሪካ ብሔራዊ የክብር ሜዳሊያ ተሸላሚ ነው። እንዲሁም ድርቅን የሚቋቋም ማሽላ ያገኘ ዓለም አቀፍ ሳይንቲስት ነው ያሉት ተጠባባቂ ፕሬዚዳንቱ፤ ይህም ለኢትዮጵያውያን ታዳጊዎችና ተማሪዎች ትልቅ አርአያ እንዲሆኑ ያስችላቸዋል ብለዋል፡፡
በትምህርት የማይጣስ ተራራ የማይወጣ ዳገት የለም፤ አሁን ያለው ትውልድ ከፕሮፌሰር ገቢሳ ኢጄታ መማር ይችላል። የኢትዮጵያ መንግሥት እንደ ፕሮፌሰር ገቢሳ ሌሎችም ዜጎቹ በተለያዩ ሀገራት ቢኖሩም ሀገራቸውን እንዲያገለግሉ ከፍተኛ ፍላጎት አለው ብለዋል።
እንደ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንቱ ገለጻ፤ ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ጋር የጠበቀ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ያላት ሲሆን የፖይንት ፎር ፕሮግራም በኢትዮጵያ ተግባራዊ መደረግ ከተጀመረ ዘንድሮ 75 ሆኖታል። ፕሮፌሰር ገቢሳ ኢጄታም የፕሮግራሙ ተጠቃሚ ናቸው፡፡
በዚህ ፕሮግራም አማካኝነትም ከፍተኛ ትምህርት በኢትዮጵያ ጅማሮውን ያገኘ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ደረጃ ትምህርት ዛሬ ለመድረሱ የፖይንት ፎር ፕሮግራም የራሱ አስተዋጽኦ እንዳለው ተጠባባቂ ፕሬዚዳንቱ ጠቁመዋል፡፡
ፕሮፌሰር ገቢሳ ኢጄታ በበኩላቸው፤ የፖይንት ፎር ፕሮግራም እ.አ.አ በ1949 ተግባራዊ መደረግ የጀመረ ሲሆን ለፕሮግራሙ ተግባራዊነትም 45 ሚሊዮን ዶላር ተመድቦ እንደነበር ገልጸዋል፡፡
በፕሬዚዳንት ሀሪ ትሩማንና ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ባደረጉት ስምምነት መሠረት በኢትዮጵያ የከፍተኛ ትምህርት ጅማሮ መሠረት የተጣለበትና ግብርናን ለማዘመን የተደረገ እንቅስቃሴ ሲሆን፤ በዚህ መነሻም ዛሬ ላይ በርካታ የግብርና ኮሌጆች መገንባት ተችሏል።
ይህ ፕሮግራም በኢትዮጵያ በርካታ ጠንካራ ተቋማትን ለመፍጠር ያስቻለ መሆኑን የገለጹት ፕሮፌሰር ገቢሳ ኢጄታ፤ የጅማ፣ የጎንደር፣ የዛኔው አለማያ የአሁኑ ሀሮማያ ዩኒቨርሲቲዎች፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድና ሌሎችም ተቋማት ዛሬ ላይ እንዲደርሱ የፖይንት ፎር ፕሮግራም ጥንስስ ሆኖ ያገለገለ ሲሆን፤ የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ካበቃ በኋላ ዓለም ሰላም እንድትሆንና በዓለም ዙሪያ ያሉ ትብብሮች እንዲያድጉ የተጀመረ ፕሮግራም መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በሴሚናሩ ላይም የጅማ፣ የጎንደር፣ የሀሮማያና የሌሎችም የሀገር ውስጥ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንቶች ተገኝተዋል።
ቃልኪዳን አሳዬ
አዲስ ዘመን መስከረም 25/2017 ዓ.ም