“ባህላዊና ትውፊታዊ ቅርሶቻችን የሀገር ግንባታ መሣሪያ ሆነው እንዲያገለግሉ አበክረን እንሠራለን”- አቶ አደም ፋራህየብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት

አዲስ አበባ፡- ባህላዊና ትውፊታዊ ቅርሶቻችን የሀገር ግንባታ መሣሪያ ሆነው እንዲያገለግሉ አበክረን እንሰራለን ሲሉ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ሃላፊ እና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ ገለጹ። አቶ አደም ፋራህ ለኢሬቻ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

አቶ አደም እንደገለጹት፤ ሕዝባዊ በዓላት በሕዝቡ ባለቤትነት ለመጪው ትውልድ እንዲተላለፉ፣ ማህበራዊ ትስስር እንዲፈጥሩ፣ የሀገር ግንባታ መሣሪያ ሆነው እንዲያገለግሉና ህብረ ብሔራዊ አንድነታችንን እንዲያጠናክሩ ብልፅግና ፓርቲ ባለፉት ዓመታት ሰፊ ትኩረት ሰጥቶ ሲሰራ ቆይቷል።

በሁሉም የሀገራችን ክፍሎች ያሉ የሕዝብ ሀብት የሆኑ የጋራ እሴቶችና ባህሎች የሚንፀባረቅባቸውን በዓላት ተገቢውን ክብርና ትኩረት እንዲያገኙ በማድረግ በሠራነው ሥራም የሀገራችንን ህብረ ቀለማዊ ሀምራዊነት ከሀገር ውስጥ አልፎ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሊያሳዩ የሚችሉ ውጤቶች ተመዝግበዋል ብለዋል።

በዚህም መንግሥት ሚናውን መርህንና ሕዝብ የሰጠውን ኃላፊነት መሠረት በማድረግ ባደረገው ድጋፍ በርካታ ሕዝባዊ ባህላዊና ትውፊታዊ ቅርሶቻችን በዩኔስኮ የተመዘገቡ ሲሆን ሕዝብ ይበልጥ ባለቤት ሆኖ እንዲጠብቃቸው፣ እንዲንከባከባቸውና ብሔራዊ ኩራትን እንዲጎናፀፍባቸው ተጨማሪ እድሎችን ፈጥሮልናል ሲሉም አክለዋል።

አቶ አደም፤ ይህንንም ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት በቀጣይም በሁሉም የሀገራችን ክፍሎች ዘመን ተሻጋሪ የትውልድ ዐሻራ ከማኖር በተጨማሪ ከሕዝብ የተቀዱና ለሀገር ግንባታ የሚውሉ እንደ ኢሬቻ ያሉ ሕዝባዊ በዓላት ተገቢውን እውቅና እና ክብር እንዲያገኙ ልዩ ትኩረት ሰጥተን እንንቀሳቀሳለን ብለዋል፡፡

በተያያዘ የሐረሪ ክልላዊ መንግሥት የሰላም፣ የፍቅር፣ የእርቅ፣ የወንድማማችነት፣ የእህትማማችነትና የአንድነት ማሳያ ለሆነው የኢሬቻ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላልፏል።

በመልዕክቱም በኦሮሞ ሕዝብ ዘንድ በታላቅ ድምቀት የሚከበረው የኢሬቻ በዓል በመስከረም ወር ከክረምት ወደ በጋ፣ ከጭለማ ወደ ብርሃን መሸጋገርን በማሰብ ለፈጣሪ ምስጋና ለማቅረብ የሚከበር የአደባባይ በዓል ነው ብሏል።

ኢሬቻ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ሀብት ከመሆኑም ባሻገር አንድነትን፣ አብሮነትንና መተባበርን የሚያጎለብት ታላቅ በዓል መሆኑንም ገልጿል። የኢሬቻ በዓል የሕዝቦችን ትስስር የሚያጠናክር እና የሀገር ውስጥ ቱሪዝምን ለማስፋፋት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለውም እንዲሁ።

የክልሉ መንግሥትም ካለፉት ዓመታት የኦሮሞን ባህል፣ እሴትና ታሪክን ለማስተዋወቅና ለማሳደግ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ ጠቅሶ በተለይም ኢሬቻን በሚመለከት ግንዛቤ ለማሳደግ የሚያስችል ሥራ በትኩረት እየሠራ እንደሚገኝ አስታውቋል።

የክልሉ መንግሥት ዘንድሮ የሚከበረው የኢሬቻ በዓል ሌሎች ብሄር ብሄረሰቦችን ባሳተፈ መልኩ በሰላም እና ባማረ መልኩ እንደሚከበር ሙሉ እምነት እንዳለውም ገልጿል።

በመሆኑም የኢሬቻ በዓልን ስናከብር ባህልና ወጉን በጠበቀና በሚያጠናክር መልኩ ለቀጣዩ ትውልድ እንዲተላለፉ በማድረግ ሊሆን ይገባልም ብሏል።

የኢሬቻ በዓል ተሳታፊዎችም ወንድማማችነትንና እህትማማችነትን እንዲሁም አንድነትን በማጎልበት ሰላም በሚያረጋገጥ መልኩ እንዲጠናቀቅ የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡም ጥሪ አቅርቧል።

የኢሬቻ በዓል እንደወትሮው ሁሉ የሰላም፣ የፍቅር፣ የወንድማማችነት፣ የእህትማማችነትና የአብሮነት በዓል እንዲሆን የክልሉ መንግሥት ያለውን ልባዊ ምኞት መግለጹን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ ያመላክታል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን መስከረም 25/2017 ዓ.ም

 

 

Recommended For You