ዕንባና እልልታ …

እንደ መነሻ ..

የባልና ሚስት የዓመታት ጥምረት ከጽኑ ፍቅር ጋር ነው። ሁለቱም ከቀድሞ ትዳራቸው ልጆችን አፍርተዋል። ልጆቹ ዛሬ ከእነሱ ጋር አይኖሩም። ለሁሉም ግን የእናት አባት ወግ ሳይነፍጉ ፍቅራቸውን ይለግሳሉ። ወላጆች ከልጆቻቸው፤ ልጆችም ከእነሱ አልራቁም። ጥንዶቹ አጋጣሚ በዓላማ አቆራኝቶ በአንድ መኖር እንደያዙ በብዙ የፈተና መንገዶች ተመላልሰዋል፡፡

ሕይወትን ፤ ለመግፋት ኑሮን ለማሸነፍ፣ ያልሆኑት የለም። በቤት ኪራይ ጣጣ ብዙ አይተዋል። ልጆች ለማሳደግ አበሳ ቆጥረዋል። በህመም በችግር ፣ በማጣትና ማግኘት የከፈሉት ዋጋ ጥቂት ይሉት አይደለም። ከሁሉም ግን በአንዷ ልጃቸው ህመም ሳቢያ ያሳለፉትን መራር ሕይወት በዋዛ አይረሱትም። እሷ ለእነሱ የጥምረታቸው ማገር፣ የፍቅራቸው ገመድ ናት። በማንነቷ ጨለማን ከብርሃን አይተዋል። ለቅሶን ከሳቅ ተጋርተዋል፡፡

ከአስር ዓመት በፊት

ጎልማሳው አብዩ መንግሥቴ ሕይወታቸውን ለማሽነፍ በጉልበታቸው ያድራሉ። በጥበቃ ሥራ የሚያገኙት ገቢ ለአንድ ራሳቸው አንሶ አያውቅም። እንዲያም ሆኖ ኑሯቸውን፣ ጎዶሏቸውን የሚሞላ ሕይወት መመኘታቸው አልቀረም። ይህ እውነት ደግሞ ከትዳር የሚገኝ ጸጋ ብቻ እንደሆነ አሳምረው ያውቃሉ። ሁሌም ከብቸኝነት ተላቀው የግራ ጎናቸውን ለማግኘት ያልማሉ። አብዩ የዘወትር ጸሎታቸው ከቀናት በአንዱ ዕውን ሆነ። የእህል ውሀ ጉዳይ እንደሳቸው መልካም ትዳርን ከሚያስቡ ወይዘሮ ጋር ኮከባቸው ገጠመ። ሁለቱም ሃሳባቸው በእኩል ሰምሮ ጋብቻ ፈጸሙ። አዲሱ ትዳር በመግባባት በመከባበር ዘለቀ። ሁለቱም ጎጇቸውን በጋራ ሊያቆሙ ፣ ቤታቸውን ሊያሟሉ ከልባቸው ጣሩ፡፡

ጥንዶቹ ‹‹የሀገሬ፣ የወንዜ ልጅ›› ይባል ልማድ አልያዛቸውም። ቋንቋቸው ፍቅር ሆኖ በአንድ ሊጣመሩ ቃልኪዳናቸው ጸና። ይህ በጎ አብሮነት ውሎ አድሮ መልካም መሆኑ አልቀረም። ወይዘሮዋ ነፍሰጡር መሆናቸውን አወቁ። የምስራቹ ለጎጇቸው ብስራትን አላብሶ ወራት ተቆጠሩ፡፡

ወይዘሮ ሀረጓ ሽፈራው ቀደም ሲል አራት ወንዶችን ወልደዋል። ልጆቻቸውን ለማሳደግ ደግሞ ብዙ ዋጋ መክፈላቸውን ዛሬም ድረስ አይዘነጉም። የቀድሞ ባለቤታቸው በሞት እንደተለዮዋቸው ወደ አረብ ሀገር ተጉዘው ነበር። ልጆቹ አድገው ራሳቸውን እስኪችሉም በውጣ ውረድ ማለፍ ግድ ብሏቸው ቆይቷል። ከዓመታት በኋላ ወይዘሮዋ ወደ ሀገር ቤት ተመልሰው በብቸኝነት ሲኖሩ ጊዚያትን አሳለፉ።

ይህ ዓይነቱ ሕይወት ለሴት ልጅ ፈታኝ እንደሆነ አላጡትም። በብዙ አጋጣሚ ማንነትን ከችግር እንደሚጥል ያውቃሉ። ሀረጓ ከባለቤታቸው ሞት በኋላ ብቸኝነትን ምርጫ ማድረጋቸው ልጆች ለማሳደግ ኑሮን ለማሸነፍ ነው። በአንድ አጋጣሚ ግን ከአሁኑ ባለቤታቸው ጋር ተዋወቁ። ውስጣቸውን ሲያውቁት፣ ሲረዱት አልዘገዩም። ማንነታቸው ከሳቸው ሕይወት ቢመስል ሊቀርቧቸው ወደዱ። ሁለቱም ሃሳብ ዓላማቸው አንድ ሆኖ ቁም ነገር አሰቡ፤ የጋራ ጎጆ ቀለሱ።

ሌላው ምኞት…

ወይዘሮዋ ከአሁኑ ትዳራቸው ሴት ልጅ እንዲኖራቸው ይመኛሉ። ከሰሞኑ የእርግዝና ክትትል የሰሙት እውነት ደግሞ የጸሎታቸው መልስ ሆኗል። በሆዳቸው ከአንድ አይሉት ሁለት መንታ ሴቶች መኖራቸውን አውቀዋል። ይህ ደስታ ለጥንዶቹ የጋራ ሆኖ ከርሟል። አጋጣሚው ሁለቱን በፍቅር የሚያስርነውና ቀኑ ደርሶ ልጆቻቸውን እስኪስሙ ቸኩለዋል።

አባወራው በጥበቃ ሥራ የሚያገኙት ደሞዝ ብዙ የሚባል አይደለም። ወይዘሮዋ ቤታቸውን ለመደጎም እንጀራ ጋግረው ይሸጣሉ። በአቅማቸውም የሽሮ ቤት ከፍተዋል። ጥረታቸውን ያስተዋሉ ደንበኞች ጠዋት ማታ ከእሳቸው ይጠቀማሉ። የኪራይ ቤት ሕይወት ቢከብድም ጥንዶቹ በመተሳሳብ አቅልለው ይዘውታል። በኑሯቸው ደስተኛ የሆኑት ባልና ሚስት ጠዋት ማታ ፈጣሪያቸውን እያመሰገኑ ነገን በተስፋ ያልማሉ፡፡

ዕልልታና ዕንባ …

ወይዘሮዋ አሁን የመውለጃ ጊዚያቸው ደርሷል። ለዘጠኝ ወራት በእርግዝና ክትትል ቆይተው ተናፋቂዎቹን መንታ ልጆች ሊታቀፉ ነው። ከቀናት በአንዱ የባልና ሚስቱ ህልም ዕውን ሆነ። የሚያማምሩትን መንታ ሴት ሕፃናት በምስጋና ተቀብለው ታቀፉ። ፊታቸው በፈገግታ በራ ደስታቸው በእጥፍ ጨመረ፡፡

ይህ እውነት ግን ብዙ አልቆየም። በአንዷ ሕፃን ላይ የታየው ምልክት አስደንጋጭና አሳሳቢ ነበር ። ሕፃኗ በሰላም ብትወለድም ጀርባዋ ክፍት ሆኖ ውሀ ቋጥሯል። ይህ አጋጣሚ ለሐኪሞች አዲስ አይደለም። በእርግዝና ወቅት ፎሊክ አሲድን በአግባቡ ባለመውሰድ የሚከሰት ችግር ነው።

አስገራሚው ጉዳይ ችግሩ የተከሰተው በአንዷ ላይ ብቻ መሆኑ ነው። በአንድ እናት ማህጸን ካሉ ልጆች ችግሩ የሚመለከተው ሁለቱንም ሊሆን በቻለ ነበር አጋጣሚው ግን አንዷን አልፎ ሌላዋን ነጥሎ አግኝቷታል፡፡

ባልና ሚስት በእጅጉ ግራ ተጋቡ። ከዚህ ቀድሞ እንዲህ ዓይነቱን አጋጣሚ አያውቁትም። ስሜታቸው በሀዘንና ደስታ የተዋጠው ጥንዶች ስለልጃቸው መፍትሔ ዝም አላሉም። ሐኪሞች ዘንድ የነበረው ውሳኔ ደግሞ ፈጣን ነበር። ሕፃኗ ከተወለደችበት ሆስፒታል ህክምና ወደምታገኝበት ስፍራ በአስቸኳይ እንድትላክ ተደረገ። እናት ጤነኛዋን ልጅ ይዘው ከቤት ሲገቡ አባት ታማሚዋን ሕፃን ሆስፒታል አስተኝተው ህክምናውን እንዲከታተሉ ሆነ፡፡

ይህ ጊዜ ለሁለቱም ከባድና አስጨናቂ ነበር። በሞትና ሕይወት መካከል የነበረችውን ጨቅላ ለማዳን ርበርቡ ቀላል አልነበረም። ባለችበት ዕድሜ ቀዶ ህክምና ሊደረግላት ግድ ብሏል። ለአንድ ወር አብረዋት የቆዩት አባወራ ከጭንቀት ባለፈ ጤናቸው ታውኳል። ሥራቸውን ትተው ኩርምት ማለታቸው «ዳነች ሞተች›› ሲሉ መሳቀቃቸው ዋጋ አስከፍሏቸዋል፡፡

በእንቅርት ላይ…

የሆስፒታሉ ቆይታ እንዳበቃ የባልና ሚስት ሕይወት እንደ ቀድሞው ቀጠለ። እንዲያም ሆኖ ደስታቸው ሙሉ አልሆነም። በአንደኛዋ ልጅ ሲደሰቱ በታመመችው መንትያዋ ማዘናቸው አልቀረም። ሁለቱ ልጆች ዕድሜያቸው ከፍ ማለት ሲይዝ ችግሩም በእኩል መጨመሩን ቀጠለ። ይህን ተከትሎ አባወራው ጤናቸው ይታወክ ጀመር፡፡

አቶ አብዩ የሆስፒታሉ ቆይታቸው ጤናማ አልነበረም። ያጋጠማቸው የሳንባ ምች አልጋ አስይዞ አክርሟቸዋል። ይህ ምክንያት ሆኖም ከሥራው ተባረዋል። ውሎ አድሮ ተደራራቢው ችግር ለቤተሰቡ ፈተና መሆኑ አልቀረም። በወይዘሮዋ እጅ የነበረ ወረት ባክኗል። ንግዳቸው ከስሯል፣ ኑሮን ለመደጎም ጥሪታቸውን አሟጠዋል፣ ወርቆቻቸውን ጨምሮ፣ የቤት ዕቃዎችን ሸጠዋል፡፡

አሁን ሕፃንዋ እንደ እህቷ ለመራመድና ለመዳህ እየሞከረች አይደለም። ያጋጠማት የነርቭ ችግርና ተደጋጋሚ ኢንፌክሽን ከወገቧ በታች እንዳትላወስ ይዟታል። በቤቱ የሚቀመስ ዳቦ እስኪጠፋ ተፈትነዋል። የአባወራው ህመም ተባብሶ ሆስፒታል በተኙ ጊዜ ደግሞ ችግሩ የዋዛ አልሆነም። አሁንም አንዳቸው የአንዳቸውን ጎዶሎ እየሞሉ ክፉ ቀንን ማለፍ ነበረባቸው። እንዲያም ሆኖ ስለምን ሲሉ ፈጣሪያቸውን አይወቅሱም። ሁሌም በምስጋና አድረው ነገን ተስፋ ያደርጋሉ፡፡

አንዳንዶች ሕፃኗን ባዩ ጊዜ ችግሩን በባልና ሚስቱ ማላከክ ልማዳቸው ነው። ሁሌም የእሷ ህመም የእነሱ ሀጢያት መሆኑን ሊያስረዷቸው ይሞክራሉ። ጥንዶቹ ስለ ሁኔታው ለመዘርዘር አቅም የላቸውም። እየተከፉ፤ እያዘኑ በይሁንታ ይችሉታል። ችግር ሲከፋ ኑሮ ሲወደድ የቤት ኪራይ ጉዳይ ጭንቅ ሆነ። ገንዘቡ ተገኝቶ ሲከፈል ደግሞ የአከራዮቹ ዓመልና ሰበብ ቅጥ አጣ። አብዛኞቹ ባገኙት አጋጣሚ ተከራዮች መሆናቸውን ይነግሯቸዋል። የሕፃኗን ዳይፐር ምክንያት አድርገው የሚወቅሷቸውም አይጠፉም። ‹‹ግቢያችን ቆሸሸ፣ ዝንብ አመጣብን›› ያሉትም ያለ አንዳች ማስጠንቀቂያ ያስወጧቸዋል፡፡

አቶ አብዩ ከተከራዩበት ቤት በዚሁ ምክንያት ለአራት ጊዜ መባረራቸውን ያስታውሳሉ። ከሁሉም ግን በወርሀ ሐምሌ በዶፍ ዝናብና ጎርፍ ሕፃናቱን ይዘው ከቤት የተባረሩበትን ጊዜ ፈጽሞ አይረሱትም። ድንገቴው አጋጣሚ መላውን ቤተሰብ በደራሽ ወንዝ ሊወስድባቸው ነበር፡፡

በየጊዜው አከራዮቻቸው ቤቱን እንዲለቁ ሲያስገድዷቸው ሁሌም ሰበብ የሚያደርጉት ህመምተኛዋን ልጅ ነው። ባለባት ችግር ራሷን መቆጣጠር ያለመቻሏን ያውቃሉና ምክንያታቸው ትሆናለች።

ልጆቹ ከፍ ባሉ ጊዜ መዋደዳቸው የተለየ ሆኗል። አንዷ ሲከፋት ሌላዋ ማልቀሷ የፍቅራቸውን ጽናት ያሳያል። መንታ ናቸውና እርስ በርስ ስሜትና ሃሳብን ይጋራሉ። እናት ሀረጓ የትናንትናውን ሕይወት አይረሱትም። ራሳቸውን ለማሸነፍ፣ ቤታቸውን ለማቆም ሲሮጡ፣ ሲጥሩ ነበር። ዛሬ ግን የሚሰሩባቸው ጠንካራ እጆች በተለየ ኃላፊነት ታስረዋል። ሁሌም አንዷን ታቅፈው፣ ሌላዋን አዝለው ይጓዛሉ፡፡

ብርሃኔ …

‹‹ብርሃኔ›› ሲሉ የሰየሟት ልጅ ለእነሱ ልክ እንደ መብራት ነች። ሀዘን ደስታቸውን ከፊታቸው ለይታ ታውቃለች። አመላካከቷ፣ ሳቅ ጨዋታዋ ለየት ይላል። ርቆ ለመሄድ ዊልቸር አይመችምና ዛሬም ከእናቷ ትከሻ አልወረደችም። ‹‹ለላም ቀንዷ አይከብዳት›› ሆኖ የእናት ሀረጓ ትከሻ ሁሌም ለልጃቸው ምቹ እንደሆነ ነው። አሁን ላይ ግን ዕድሜዋ ሲጨምር፣ ሰውነቷ ሲከብድ ያስቡ ይዘዋል። መላው እስኪገኝ ነገን እንዴት ትሆናለች? ይሉት ጭንቀት ሲያስተክዛቸው ይውላል፡፡

ለልጅቷ በየቀኑ የሚያስፈልጋት ዳይፐር ቀላል የሚባል አይደለም። ዓይነቱና ቁጥሩ ከተለመደው ይለያልና እንዳሻ ከሱቅ መርጠው አይገዙትም። እሱም ቢሆን ዋጋው ከፍ ያለ በመሆኑ በእነሱ አቅም የሚሞከር አልሆነም። ይህ ይሆን ዘንድ ግን ለልጃቸው መኖርና ህልውና ከአቅማቸው በላይ ሮጠው ግዴታቸውን ይወጣሉ፡፡

የአብስራ የብርሃኔ መንትያ እህት ናት። ዕድሜዋ ሲደርስ በጊዜዋ ትምህርት ጀምራለች። ብርሃኔ ልክ እንደ ግማሽ አካሏ ሁሉ መማርና ፣ ዕውቀት መቅሰምን ትሻለች። ይህ ደግሞ ለሁሉም ዜጋ የተሰጠ መብት ነው። ይሁን እንጂ እንደ እህቷ ማለዳ ተነስታ ራሷን አታዘጋጅም። ደብተሯን በቦርሳዋ ይዛ ፈጥና አትሮጥም። እህቷን ጨምሮ እኩዮቿ ወደ ትምህርት ቤት ሲሄዱ በዝምታ እያ ስተዋለች ነው፡፡

እሷ ይህን ላድርግ ብትል ደግሞ ፈጽሞ አይቻላትም። ከወገቧ በታች ያለው አካሏ እየታዘዛት አይደለም። ወላጆቿ ግን ልጃቸው ‹‹አትችልም›› ሲሉ ዝም አላሉም። እናት ሀረጓ በትከሻቸው አዝለው፣ አባትዬው ከኋላ ተከትለው የትምህርት ቤቶችን በሮች አንኳኩ።

ያልተከፈቱ በሮች…

ሁሉም ትምህርት ቤቶች በእናቷ ጀርባ ላይ የታዘለችውን ሕፃን ባዩ ጊዜ ‹‹አስተምሩልን›› ይሉትን ጥያቄ ሊቀበሉት አልወደዱም። በተለይ ብርሃኔ የዳይፐር ተጠቃሚ መሆኗን ሲረዱ ፊታቸውን አዙረው በራቸውን ዘጉ። ይህ እውነት የገባቸው ወላጆች ውስጣቸው አዝኖ ብቻ አልተመለሱም። በሚመለከታቸው አካላት ፊት ቀርበው የመማር ዕድል ስለተነፈጋት ዕንቦቃቅላ ልጃቸው ‹‹ፍረዱኝ›› ሲሉ አቤት አሉ፡፡

እውነታውን የሰሙ የመንግሥት አካላት ትኩረት አልነፈጓቸውም። ሕፃን ብርሃኔ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ የመማር ዕድል እንድታገኝ አስገዳጅ ትዕዛዝ አስተላለፉ። የሕፃኗና የወላጆቿ ልብ በሀሴት ሞላ። እሷም እንደ እህቷና መሰል እኩዮቿ በትምህርት ገበታ ዕውቀትን ልትቀስም መብቱን አገኘች። እናቷ ጠዋት አዝለው ያደርሷታል። ጥቂት ቆይተውም ዳይፐር ቀይረው ደህንነቷን አረጋግጠው ይመለሳሉ። አባት በተራቸው ወደቤት ይመልሷታል። ውሎዋ ከእህቷ ጋር በመሆኑ ደስተኛ ነች፡፡

ሕፃን ብርሃኔ ሁሌም ስለወላጆቿ ከልብ ታዝናለች። በተለይ እናቷ እሷን አዝለው ሲጓዙ እንዳይደክማቸው፣ እንዳይሰለቻቸው ስጋቱ አላት። በቻለችው አቅም በፍቅር እየጠራች የውስጧን ታወጋቸዋለች። ‹‹አይዞሽ እናቴ በርቺልኝ›› ትላቸዋለች። እናቷ ፈጽሞ አያማርሩም። የእሷ ችግር አለመራመድ ብቻ በመሆኑ ደስተኛ ናቸው፡፡

የእሷን መሰል ህመም ያለባቸው ሕፃናት፣ አብዛኞቹ የማይናገሩ፣ የማይሰሙና የማያዩ መሆናቸውን አስተውለዋል። ይህን አጋጣሚ ማወቃቸው ታዲያ ስለ ብርሃኔ ለፈጣሪ ደጋግመው ምስጋና እንዲያቀርቡ ምክንያት ሆኗል። ሁሌም አስተዋይ ልጃቸውን ያደንቋታል። እንዳይከፋት፣ እንዳታዝን ይጠነቀቃሉ፡፡

አንዳንዴ ግን ብርሃኔ ከአጠገቧ ሰው ሲጠፋ ይከፋታል። ከጎኗ ማንም እንዲርቅ አትፈልግም። አጋጣሚ ሆኖ ጫማ ለእህቷ ሲገዛ ለእሷም በልኳ ሊገዛላት ግድ ነው። እሷን አትሄድም፣ አትራመድም ብሎ ማለፍ ታላቅ ስህተት ነው። ብርሃኔ አሁን ዊልቸር ላይ መቀመጥ ችላለች። ወደፊት ደግሞ በሰው ሠራሽ አካል እንድትጠቀም ዕቅድ ተይዟል፡፡

ይህ ተስፋ ለወላጆቿ ታላቅ ብርሃን ሆኗል። አንድ ቀን ተራምዳ እንደምትሄድ ውስጣቸው ያምኗል። ብርሃኔ ዛሬ ላይ እግሮቿ ስሜት አልባ ናቸው። ቢመቱ፣ ቢቆነጠጡ፣ እሳት ቢያገኛቸው፣ አንዳች መልዕክት የላቸውም። ይህ ታሪክ ግን አንድ ቀን እንደሚለወጥ የሁሉም ተስፋና ዕምነት ነው፡፡

ዛሬን…

ዛሬ ላይ መንትዮቹ ስምንተኛ ዓመታቸውን እየተሻገሩ ነው። በቅርብ ጊዜ የብርሃኔን ችግር ያስተዋለው የአካባቢው ወረዳ አስተዳደር ለቤተሰቡ ይበጃል ያለውን የቀበሌ መኖሪያ ቤት ሰጥቷቸዋል። ከአንደበታቸው ሁሌም ምስጋና የማይጠፋው ባልና ሚስት በሆነላቸው ሁሉ ተደስተው መልካም ሕይወትን ቀጥለዋል፡፡

ማንነታቸውን ያስተዋሉ፣ ጥረታቸውን ያዩ ልበ መልካሞች ታዲያ ‹‹አይዟችሁ›› ማለታቸውን አልተውም። እማወራዋ የደረቅ እንጀራ ንግዳቸውን ቀጥለዋል። የጎደለውን ባሟሉላቸው ወዳጆቻው ምስጋናቸው የላቀ ነው። እነሱ ሸክማቸውን አቅልለው ድካማቸውን ተካፍለዋል፡፡

በእሳቸውና በባለቤታቸው እምነት እንዲህ ዓይነቱ በረከት የተገኘው ‹‹ብርሃኔ›› ሲሉ በሰየሟት፣ ብዙዎች ‹‹አትበጅም፣ አትረባም›› ባሏት ልጃቸው ሰበብ ነው። አሁን ባልና ሚስቱ ሕይወታቸው በበረከት ታጅቦ ሰላማዊ ሕይወትን ይዘዋል። ‹‹አንተ ትብስ፣ አንቺ›› ይሉት መተሳሰብ በፍቅር ታጅቦም ኑሯቸው ትርጉም አግኝቷል።

ሁለቱም ዛሬ ስለሆነላቸው መልካም ነገር ምስጋናቸው የላቀ ነው። ትናንት በእነሱ ላይ የሆነውን ክፉ አጋጣሚ ዛሬ ፈጽሞ አያስቡትም። ሁሌም በመንትዮቹ ልጆቻቸው ማንነት ነገን አሻግረው እያዩ ብሩህ ተስፋን ያልማሉ። እናት ሀረጓ ልጃቸው ብርሃኔ አንድ ቀን ቆማ እንደምትሄድ ሙሉ እምነት አላቸው። ይህ ይሆን ዘንድ የሰው ሠራሽ አካል መደገፊያው ወሳኝነት አለው። ይህን ድጋፍ ለማግኘት እስከ አስራ ስምንት ሺህ ብር ተጠይቀዋል።

‹‹ከአንድ ብርቱ ሁለት መድኃኒቱ›› እንዲሉ ዛሬ የልጃቸውን ተስፋ ለማለምለም ‹‹አለናችሁ›› ባይ ወገን ያሻቸዋል። እኛም ባለ ብሩህ አይምሮዋን ታዳጊ ብቁ ዜጋ አድርጎ ለውጤት ለማብቃት የመልካም ሰዎች እጆችና ልቦና አይጥፋ እንላለን፡፡

መልካምሥራ አፈወርቅ

 አዲስ ዘመን መስከረም 25/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You