ንባብ ያለፈውን፣ የአሁኑንና የነገን ትውልድ የሚያገናኝ መሳሪያ ነው

አዲስ አበባ፡– ንባብ ያለፈውን፣ የአሁኑንና የነገን ትውልድ የሚያገናኝ መሳሪያ መሆኑን የአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ገለጸ፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ ለ9ኛ ጊዜ ከተማ አቀፍ የንባብ ባህል ፌስቲቫል “ንባብ ለትውልድ ግንባታ” በሚል መሪ ሃሳብ በኤግዚቢሽን ማዕከል መካሄድ ጀምሯል፡፡

የአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ሂሩት ካሳ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ ንባብን ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ቢሮው ከተማ አቀፍ የንባብ ፌስቲቫሎችን እና ውድድሮችን በማካሄድ ህብረተሰቡን ለማነቃቃት ሲሠራ ቆይቷል፡፡

ንባብ ያለፈውን፣ የአሁኑንና የነገውን ትውልድ የሚያገናኝ መሳሪያ ነው ያሉት ዶክተር ሂሩት፤ ቤተ መፃሕፍት ከመገንባትና አንባቢውን ከማነቃቃት ባለፈ የነገዋን ሀገር ለሚረከብ ትውልድ የሚመጥን ድርሰት በመድረስ ትውልድ የሚቀርጽ ሥራ መስራት እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

ትምህርት መንገድ ነው ያሉት ኃላፊዋ፤ ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት ቢልኩም በትምህርት ቤቶቻቸው የሚያገኙትን እውቀት እንዲያዳብሩና አእምሯቸውን ንቁ እንዲያደርጉ የንባብ ባህላቸውን እንዲያዳብሩ ማገዝ እንደሚገባ ኣሳስበዋል፡፡

ፌስቲቫሉ ሰኔ ዛሬ ሰኔ 30 2016 ዓ.ም የሚያበቃ ሲሆን የመፍት አውደ ርዕይ፣ የተማሪዎች የንባብ፣ የግጥምና ሌሎች ውድድሮች ሲካሄድ የሚቆይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ባህልና ኪነጥበብ ቱሪዝም ቢሮ የባህል ዘርፍ ምክትል ኃላፊ አስፋው ኩማ በበኩላቸው፤ ፌስቲቫሉ አንባቢ፣ ተመራማሪና ችግር ፈቺ ትውልድ ለመፍጠር ዓላማ አድርጎ የተዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በከተማዋ ዘመናዊ የሆኑ ቤተመጻሕፍት ከመገንባታቸው ጋር ተያይዞ በርካታ አንባቢዎች ቢፈጠሩም አሁንም በርካታ የሚቀሩ ስራዎች አሉ ያሉ ሲሆን በቀጣይም ቤተመጻሕፍትን ለማዘመንና አማራጮችን ለማስፋት ቢሮው እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡

ፌስቲቫሉ ተማሪዎች የክረምት ጊዜያቸውን በንባብ እንዲያሳልፉና የንባብ ባህላቸውን እንዲያዳብሩ ይረዳል ያሉት ምክትል ኃላፊው፤ ወላጆች ልጆቻቸው የንባብ ጊዜ እንዲኖራቸውና የንባብ ክህሎታቸውን እንዲያዳብሩ ለማድረግ ትኩረት ሰጥተው መሥራት እንደሚኖርባቸው አሳስበዋል፡፡

አቶ አስፋው ፌስቲቫሉ የኅብረተሰቡን የማንበብ ልምድ ከማዳበር በተጨማሪ ደራሲዎች፣ አታሚዎች፣ ቤተመጻሕፍት እና የመጽሐፍ ሻጮች የገበያ ትስስር የሚፈጥሩበት እንደሚሆን ተናግረዋል።

መስከረም ሰይፉ

አዲስ ዘመን ሰኔ 30 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You