የፖለቲካ እሳቤ ያልከፋፈለው ሕዝባዊ ተሳትፎ በአረንጓዴ አሻራ ተጨባጭ ውጤት አምጥቷል

– በሐረሪ ዳያስፖራውን በአሳተፈ መርሀ ግብር 500 ሺህ ችግኞች ተተክለዋል

ሐረር:- ሕዝቡ በፖለቲካ እሳቤዎች ሳይከፋፈል በአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር በስፋት በመሳተፉ ተጨባጭ ውጤት ተገኝቷል ሲሉ የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ገለጹ። “የምትተክል ሀገር የሚያጸና ትውልድ” በሚል መሪ ሃሳብ የክረምት ችግኝ ተከላ መርሀ ግብር ትናንት በሀረሪ ክልል ተጀምሯል።

መርሀ ግብሩን ያስጀመሩት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ፣ መርሀ ግብሩ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ በክልል ደረጃ በርካታ ሥራዎች እየተከናወኑ እንዳለና በዚህም አበረታች ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በአረንጓዴ አሻራ ውጤት የመጣው ሕዝቡ በፖለቲካ እሳቤዎችና በርእዮተ ዓለም ሳይከፋፈል የችግኝ ተከላ መርሀ ግብሩን በባለቤትነት በመሳተፉ ነው ብለዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ እንደገለጹት፤ የአየር ንብረት ለውጥና የአፈር መሸርሸር ለዓለም ሕዝብ ከፍተኛ ፈተና ሆኗል። ችግሩን ለመቅረፍ በተደጋጋሚ የተለያዩ ጥረቶች ቢደረጉም ችግሩን ሊመጥኑ የሚችሉ መፍትሔዎች ባለመቀመጣቸውና ተጨባጭ ሥራ ሳይሠራ ቆይቷል። በዚህም ቀድሞ በነበረው ሁኔታ የኢትዮጵያ የደን ሽፋን ከ40 በመቶ ወደ ሦስት በመቶ ወርዶ ነበር።

ከለውጡ ማግስት ጀምሮ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ባስጀመሩት የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር በሀገሪቷ አበረታች፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚደነቅ የተግባር ሥራ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።

ከለውጡ በኋላ በተጀመሩ ጠንካራ ሥራዎች የደን ሽፋኑን ከነበረበት ሦስት በመቶ ወደ 26 ነጥብ ሰባት በመቶ ማሳደግ እንደተቻለም አንስተዋል።

ይህ የሚያበረታታ፣ ተስፋ ሰጪ እና ሲያጋጥሙ የነበሩትን የአየር ንብረትና የአፈር መሸርሸር ችግሮችን ሊቀርፍ የሚችል ነው ብለዋል።

ሥራው የተሟላ ሆኖ እንዲቀጥልና የተጀመሩ የልማት ስራዎች በውጤት እንዲታጀቡ የተጀመረውን የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር አጠናክሮ መቀጠል እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

በዘንድሮ ዓመት በክልሉ ሁለት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል መታቀዱን ገልጸው፤ ከዚህ ውስጥ በተለይም ዓለም አቀፍ የሐረር ቀንን ለማክበር ከመጡ ዳያስፖራዎች ጋር በመሆን 500 ሺህ ችግኞች እንደተተከሉ ተናግረዋል። ይህም በክልሉ ካለው አጠቃላይ ሁኔታ ጋር ሲታይ የሚተከሉ ችግኞች በአንድ በኩል የደን ዛፎች ሲሆኑ፤ ሌሎች ደግሞ ምግብ ነክና ለውበት የሚሆኑ ናቸው ብለዋል።

ከሚተከሉ ችግኞች 70 በመቶ የሚሆኑት ለምግብነት የሚውሉ ሲሆን 30 በመቶዎቹ ደግሞ የደን ዛፎች እንደሚሆኑም አብራርተዋል።

ይህ በሀገር አቀፍም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ እንደ አንድ ስኬት የሚታየው ሥራ በአመራር ቁርጠኝነትና በሕዝቡ ሰፊ ተሳትፎ የመጣ እንደሆነም አስረድተዋል።

በክልሉ 26ኛውን ዓለም አቀፍ የሐረር ቀን ምክንያት በማድረግ የ2016 ዓ.ም ክልል አቀፍ የአረንጓዴ አሻራ ማስጀመሪያ መርሀ ግብር እየተካሄደ ሲሆን፣ በመርሀ ግብሩ ዳያስፖራውን ማህበረሰብ በማሳተፍ 500 ሺህ ችግኞች ተተክለዋል።

አዲሱ ገረመው

አዲስ ዘመን ሰኔ 30 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You