ተመራቂዎች የቀሰሙትን ዕውቀት በመጠቀም መላውን ሕዝብ በቅንነት ማገልገል አለባቸው

አዲስ አበባ:- ተማሪዎች ከዩኒቨርሲቲው የቀሰሙትን ዕውቀትና ክህሎት በመጠቀም መላውን ሕዝብ ያለምንም ልዩነት በታማኝነትና በቅንነት ማገልገል እንዳለባቸው ተገለጸ።

ኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ ያሰለጠናቸውን አንድ ሺህ 688 ተማሪዎችን ትናንት አስመርቋል። የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ሚኒስትርና የኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ ቦርድ ሰብሳቢ ለገሠ ቱሉ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ መንግሥት የትምህርት ጥራትን ማረጋገጥ የሚያስችል የትምህርት ሥርዓት ማሻሻያ ሪፎርም እያካሄደ ነው ብለዋል።

ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው የሀገርና የህዝብን አደራ የሚተገብሩና ብቁ ዜጋ እንዲሆኑ የሚያስችላቸውን እውቀት መጨበጣቸውን በመግለጽ፤ ተመራቂዎች የትውልድ ህልም መሐንዲሶች፤ የቀመር የባህሪ ገንቢዎችና የተስፋ ችቦ ተሸካሚዎች መሆናቸውን ተናግረዋል።

ሁልጊዜም ለተራማጅና ሁለንተናዊ ብልጽግና መትጋት አስፈላጊ መሆኑን በመግለጽ፤ ተመራቂዎች የኢትዮጵያ የወደፊት መሐንዲሶች ናችሁ ብለዋል።

ተመራቂዎች በምክንያታዊነት በሰላም ወዳድነትና በመቻቻል ስሜት የተገነባ ትውልድና ምርታማ ማህበረሰብ ለመፍጠር የራሻቸውን አሻራ ማኖር እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ብርሃነመስቀል ጠና (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ ጥራትና ብቃት ያላቸውን መምህራንና ተማሪዎችን ለማፍራት እየሰራ ነው፡፡

በዩኒቨርሲቲው በመደበኛ፤ በማታና በተከታታይ መርሐ ግብር አንድ ሺህ 688 ዕጩ ምሩቃን ለምረቃ በቅተዋል ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ ከነዚህም ተመራቂዎች መካከል 876 ወንዶች ሲሆኑ 812 ሴቶች ናቸው ብለዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው ካሉት ዲፖርትመንቶች መካከል ስምንቱ በሀገር አቀፍ የመውጫ ፈተና ተማሪዎቻቸውን 100 በመቶ ማሳተፋቸውን ጠቅሰው፤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲው የዘንድሮውን ተመራቂዎች ጨምሮ ከመቶ ሺህ በላይ የትምህርት ባለሙያዎችን ማፍራቱን ተናግረዋል።

በትምህርት ዘርፍ አንጋፋና ቀዳሚው የትምህርት ዩኒቨርሲቲው ሀገሪቱ የምትፈልገውን የተማረ የሰው ኃይል ፍላጎት ለማሟላት የበኩሉን ድርሻ ሲወጣ መቆየቱን ገልጸው፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ የትምህርት ስብራትን ለመጠገን ኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ መመስረቱን አስረድተዋል።

በሀገሪቱ ብቸኛ የሆነው የትምህርት ዩኒቨርሲቲው ጥረቱን በአዲስ መልክ አጠናክሮ መቀጠሉን የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፤ ለሀገሪቱ የልማትና የብልፅግና ጉዞ ትምህርት ቁልፍ ሚና እየተጫወተ ነው ብለዋል፡፡

በትምህርት ዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ፕሮግራሞችን የማሻሻልና በአዲስ ምዕራፍ የማስቀጠል ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል፡፡

የትምህርት ዩኒቨርሲቲው የሀገሪቱን የትምህርት ስብራት ችግር በጥናትና ምርምር በመለየት፣ ሁለት ዓለም አቀፍና ሀገር አቀፍ የምርምር ጉባኤ ማካሄዱን ገልጸው፤ ከትምህርት ጥራት ችግር የሚወጣበትን የመፍትሔ ሃሳቦች ማዘጋጀታቸውን ጠቁመዋል፡፡

ተማሪዎች ከዩኒቨርሲቲው የቀሰሙትን እውቀትና ክህሎት በመጠቀም መላውን ሕዝብ ያለምንም ልዩነት በታማኝነትና በቅንነት ማገልገል እንዳለባቸው ጠቁመው፤ ሥራ ጠባቂ ሳይሆን ሥራ ፈጣሪ በመሆን ውድድር በበዛበት በዚህ ፈጣን የለውጥ ዓለም ውስጥ ሁሌም ራሳቸውን ሊያበቁ እንደሚገባ አሳስበዋል።

በምርቃቱ ሥነ-ሥርዓት ላይ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቋሚ ኮሚቴ አባላትን ጨምሮ የተመራቂ ቤተሰቦች ተገኝተዋል::

ማርቆስ በላይ

አዲስ ዘመን  ሰኔ 30 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You