የሰኔ ወር የሰማይን ፈገግታ ይነጥቃል። የአዲስ አበባ ሰማይ አኩርፏል። ድምፁን አውጥቶ ማስገምገም፤ ማንባት ጀምሯል። የጫነውን ዝናብ ቅዝቃዜን በቀላቀለ ነፋስ አጃቢነት ማውረዱን ተያይዞታል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቲያትር መግቢያ ላይ ቁጥሩ እጅግ የበዛ ሰው ግጥም ብሏል። የተሰበሰበው ሰው ዝናቡን ለመሸሽ በስፍራው ስለነበር ተጠልሎ እስኪያቆም የሚጠባበቅ አልነበረም። ይልቁንም ከነበረበት ቦታ በጥበብ ጥሪ ዝናቡን ተጋፍጦ ወደ ጥበብ ቤት የመጣ እንጂ። የጥበብ ጉልበት የገዘፈ ነውና አፍቃሪውን ብርድና ቁር ሳይበግረው ከያለበት ሰብስቦ በረከቱን ይመግባል።
በኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር አዘጋጅነት በብሔራዊ ቲያትር በሚቀርበው “ብሌን የኪነ ጥበብ ምሽት 6” ላይ ለመታደም በሩ እስኪከፈት በትዕግስት በመጠባበቅ ላይ ይገኛል።
የዝግጅቱ ጅማሮ ይሆናል ከተባለበት 25 ደቂቃ ዘግይቶ የትያትር ቤቱ በሮች ተከፍተው ታዳሚውን መቀበል ጀመሩ። በመብራት ከተዋበው መድረክ አካባቢ ካለ የድምፅ ማጉያ (ስፒከር) የሚወጣው ለስለስ ያለ በመሳሪያ የተቀነባበረ ሙዚቃ ጥሩ መንፈስ አላብሶ አዳራሹን ያላምዳል።
ባለፈው ሰኔ 3 ምሽት 6ኛው ብሌን የኪነ ጥበብ ምሽት በኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር አዘጋጅነት በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቲያትር በደመቀ መልኩ ተካሂዷል። በዚህ የኪነ ጥበብ ምሽት አንጋፋና ወጣት የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ሥራዎቻቸውን በተለያየ ይዘትና ቅርፅ ለታዳሚው አቅርበዋል። እኛም በቦታው ተገኝተን ምሽቱን ያደመቁትን ሥራዎች በዚህ መልክ አሰናድተናል።
የኪነ ጥበብ ምሽቱ አላማ ወጣትና አንጋፋ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ሥራዎቻቸውን ለህዝብ እንዲያቀርቡ ከማድረግ ባለፈ በሀገራችን ሰላም፣ አንድነት፣ ፍቅርና ሀገራዊ መግባባት ይሰፍን ዘንድ በማዝናናት ለህዝብ ግንዛቤ ማስጨበጥና መልዕክት ማስተላለፍ መሆኑን የመርሀ ግብሩ ደጋሽ የሆነው የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር አስታውቋል።
በአርቲስት ያለለት አዱኛ በባህላዊ ማሲንቆ ጨዋታ ደምቆ የጀመረው የኪነ ጥበብ መድረኩ በተከታታይ ኪነ ጥበባዊ መሰናዶዎች ማለትም በግጥም፣ ወግ፣ ቅኔና መነባነብ ታዳሚውን እያዝናና ሲያስተምር አምሽቷል።
አርቲስት እንዳለ ጌታ ከበደ፣ አገኘው ኪዳኔ፣ ትዕግስት ማሞ፣ ፍሬዘር አድማሱ፣ አሳዬ ገነነ፣ ኤልያስ ዘርይሁን እና ሌሎች የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች በዝግጅቱ ላይ ሥራዎቻቸውን አቅርበዋል።
የራሱን የአጻጻፍ ስልት በመከተል በተለይ በግጥሞቹ ዘመን ተሻጋሪ ሥራዎችን አበርክቶ ያለፈው አይረሴው የጥበብ ሰው ሰለሞን ደሬሳ የዘከረው የኪነ ጥበብ ምሽቱ የደራሲውን ልዩ ልዩ ጽሑፎች፣ ግጥሞች፣ የህይወት ተሞክሮ፣ ፍልስፍናውና ልዩ የአጻጻፍ ስልቱ የተመለከቱ ዳሰሳዊ ጽሑፎች የቀረቡ ሲሆን፤ በተለይ በደራሲ እንዳለጌታ ከበደ ስለ ደራሲ ሰለሞን ደሬሳ ሥራዎችና ፍልስፍና የተመለከተ አጠር ያለ ጽሑፍ የተዘካሪው ሰው ማንነት ለታዳሚው ቁልጭ አድርጎ ያሳየ ነበር።
ደራሲ እንዳለጌታ ሰለሞን ደሬሳን ባወሳበት ጽሑፉ ዘርፈ ብዙ ክህሎትን የተላበሰ የስነ ጽሑፍ ሰው እንደነበረ ገልፃል። ደራሲ፣ ገጣሚ ጋዜጠኛ፣ የስነ ጥበብ ሐያሲ፣ ተፈላሳፊ፣ መምህርና አማካሪ የነበረው ሰለሞን ደሬሳ በ1964 ባወጣው “ልጅነት” በተሰኘውና አፈንጋጭ ዘይቤ በነበረው የመጀመሪያ የግጥም መድብሉ ለብዙዎች የተለየ ተስጥዖ ያለው ምርጥ የኪነ ጥበብ ሰው መሆኑ ያሳየበት እንደነበር ተገልጿል።
ሦስት መጽሐፎችን ለንባብ ያበቃው አርቲስት ሰለሞን ደሬሳ በፃፋቸው ልዩ ልዩ መጣጥፎች ግጥሞችና የሥነ ጽሑፍ ሥራዎች ለኢትዮጵያ ኪነ ጥበብ እድገት ትልቅ አሻራ ያኖሩ ዘመን ተሸሻጋሪ ሥራዎች መሆናቸውን በጽሑፉ አቅራቢ ተገልጿል።
ዘርፈ ብዙው የኪነጥበብ ሰው አርቲስት ሰለሞን ደሬሳ በአሜሪካ ሚኔሶታ ግዛት ባለፈው ዓመት ጥቅምት 23/2010 ዓ.ም ህይወቱ ማለፉ ይታወሳል።
ሀገራዊ የፍቅር ስሜት በተላበሱ በኪነ ጥበብ ሥራዎች ደምቀው ባመሹበት መድረክ የታዳሚው ቀልብ የሳበውና የቲያትር ባለሙያ በሆነው አሳዬ ገነነ “ተጓዡ መምህር” በሚል ርዕስ ያቀረበው አንድ ሰው የሚቀርብ አጭር ተውኔት ነበር።
ተውኔቱ በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ ተማሪዎች እያደረጉት ያለው ያልተገባ ግጭት የሚተች እና ተማሪዎች ትምህርታቸው ላይ በማተኮር ለሀገር ግንባታና እድገት ምሁራዊ አስተዋጽኦ ማድረግ እንዳለባቸው የሚመክር ነበር። በተጨማሪም በተውኔቱ ሀገራዊ ስሜትን የተላበሰ ዜጋ ለማፍራት መደረግ ያለበትን መሰረታዊ ጉዳይ ምን እንደሆነ በጥበባዊ ስልት ለመጠቆም ሞክሯል።
በገጣሚ እንድሪያስ ተረፈ ተፅፎ የቀረበው “ባህር ሳለን ኩሬ” የተሰኘ ግጥም ለሀገር ማሰብን፣ ከመነጠል ይልቅ አንደነት የተሻለ ሃይል የሚሰጥ መሆኑን፣ የሚያለያዩን ጉዳዮች እንደ ሀገር ውይይት በማድረግ ሊፈቱ እንደሚገባና ትውልዱን ሀገራዊ አስተሳሰብ እንዲላበስ መሥራት ተገቢ መሆኑን የሚመክር ነበር። የገጣሚ እንዲሪያስ ግጥም ይዘትና ጥበባዊ ገለፃ ታዳሚው እንዲወደው ትልቅ አስተዋፅዖ አበርክቶለታል።
በግጥም መነባንብና ወግ መሀል አልፎ አልፎ በአርቲስት ያለለት አዱኛ ይቀርብ የነበረው የባህል ጨዋታ (የማሲንቆ ጫዋታ) የዝግጅቱ ታዳሚ በ “ተቀበል” ግጥም ያሳተፈና የጥበብ ሁለንተናዊ አሳታፊነት በጉልህ ያሳየ መድረኩንም ያደመቀ ትዕይንት ነበር።
በገጣሚ ኤልያስ ዘርይሁን “ንጉሥ ሆይ” በገጣሚ ትዕግስት ማሞ “ትዕዛዝ” በሚል ርዕስ የቀረቡ ተከታታይ ግጥሞች ማህበራዊና ወቅታዊ ብርቱ ጉዳዮችን አንስተው የሚሞግቱ በሳል ሥራዎች ናቸው። በግጥሞቹ የአብሮነትና መተሳሰብ ጠቀሜታ፣ የፍቅርን ሃያልነት፣ የእውነትን አሸናፊነት፣ የማስመሰልና የሀሰት ፍፃሜ ውድቀት መሆኑን አሳይተዋል።
ሌሎች በመድረኩ ላይ የቀረቡ የኪነ ጥበብ ሥራዎች የአዘጋጁን አላማ በሚያሳካ መልኩ ታዳሚውን እያዝናኑ ጥበባዊ በሆነ መልኩ መልካሙን ነገር አወድሰዋል። ስህተት ያሉትን ለማረቅ መክረዋል፤ አስተምረዋል፤ አለፍ ብለውም መጥፎን ልማድና ተግባር ነው ያሉትን አንስተው ኮንነዋል።
በጥበብ ሥራዎች ደምቆ የነበረው ምሽት የኪነ ጥበብ ባለሙያው ከታዳሚው ጋር አገናኝቶ አዝናንቶና አስተምሮ ባማረ መልኩ ተጠናቋል። በመድረኩ ላይ ያየነው አንድ መልካም ነገር መጥቀሱ እዚህ ላይ ተገቢ ይመስላል።
በኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ደጋሽነት በቀረበው በዚህ ደማቅ የኪነ ጥበብ ምሽት ተሳታፊ የነበሩ ወጣት የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ከነባርና በሙያው ላይ ሰፊ ልምድ ካላቸው መሰል ሙያተኞች በጋራ እንዲያቀርቡና ልምድ እንዲለዋወጡ ዕድል መፍጠሩ በራሱ የአዘጋጁ መልካም ጅማሮ የሚበረታታ መሆኑን መግለፅ እንወዳለን።
በሙያው ወደፊት ለመቀጠልና መድረክ አግኝቶ ለህዝብ ሥራን ለማቅረብ በተለይ አዲስ ለሆነ ሰው ከባድ መሆኑን በዚሁ 6ኛው ብሌን የኪነ ጥበብ ምሽት ላይ ተጋብዞ “ተጓዡ መምህር” የተሰኘውን የአንድ ሰው አጭር ተውኔት ያቀረበው የትያትር ባለሙያው አሳዬ ገነነ ይገልፃል።
አሳዬ እሱን ለመሰሉ ወጣትና ጀማሪ የሥነ ጽሑፍ ባለሙያዎች ከአንጋፋ የጥበብ ባለሙያዎች ትልቅ ልምድ እንዲቀስሙ በዚህ መሰል መርሐ ግብሮች እንዲሳተፉ ዕድል መሰጠቱ መልካም ጅምር መሆኑን ገልፆ ተመሳሳይ መድረኮች ላይ ቢመቻቹ መልካም እንደሆነ አስተያየቱን ሰቷል።
እኛም መሰል የኪነ ጥበብ መድረኮች ሲዘጋጁ ወደ ጥበብ ሙያ የተቀላቀሉ አዳዲስ የዘርፉ ባለሙያዎችን ሥራዎች የሚያቀርቡበት መድረክ ቢመቻች ለጥበቡ ዕድገት የጎላ አስተዋጽኦ ይኖረዋልና የኢትዮጵያን ደራሲያን ማህበር መልካም ጅምር ሌሎች የኪነ ጥበብ ማህበራትና ተቋማት ትኩረት ሰጠው ቢሠሩበት መልዕክታችን ነው። መልካም ሳምንት።
አዲስ ዘመን ሰኔ 18/2011
ተገኝ ብሩ