ለኮንስትራክሽን ዘርፉ የሥራ ላይ ደህንነትና ጤንነት

የኮንስትራክሽን ዘርፉ ለኢኮኖሚ እድገት ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ዘርፉ ከዓለም የሰራተኛ ኃይል ሰባት በመቶ ያህሉንም ይይዛል። ይህ ዘርፍ ከስራ ጋር በተያያዘ በሚከሰቱ አደጋዎችም ዘርፉ ይጠቀሳል፡፡

መረጃዎች እንደጠቆሙት፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከስራ ጋር ተያይዞ በሚያጋጥሙ አደጋዎች በዓመት በአማካይ ሁለት ነጥብ 78 ሚሊዮን ያህል ሰዎች ለሞት ይዳረጋሉ። ከዚህ ውስጥም 17 በመቶ የሚሆነው ሞት የሚከሰተው ከኮንስትራክሽን ጋር በተያያዙ ከባድ አደጋዎች ነው።

በኢትዮጵያም የኮንስትራክሽን ዘርፉ ለኢኮኖሚያዊ ዕድገት የጎላ አስተዋፅኦ የሚያበረክት ሲሆን፣ ከግብርናው ቀጥሎ ከፍተኛ መጠን ያለው የሰው ሀይል እንደሚይዝም መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በዘርፉ በተለያዩ ምክንያቶች ሳቢያ በሚከሰቱ አደጋዎች ጋርም ስሙ ይነሳል፡፡ በዚህም ሰራተኞች፣ በግንባታ አካባቢ የሚንቀሳቀሱ ሰዎች፣— ወዘተ ህይወት ይጠፋል፤ አካል ይጎድላል፤ ሌሎች የጤና ችግሮች ይከሰታሉ፡፡

ግንባታዎች በሚካሄዱባቸው አካባቢዎች ከፍተኛ የግንባታ ተረፈ ምርቶች ተከማችተው ይታያሉ። የግንባታ ጥራት ጉድለት፣ የግንባታ መወጣጫዎች ደረጃቸውን የጠበቁ አለመሆን፣ ወዘተ ሌሎች የአደጋ መንስኤ በመሆን ይጠቀሳሉ፡፡ የዘርፉ አለመዘመንና የተቋራጮች ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት አለማደግ ሌሎች ለአደጋዎቹ መከሰት ምክንያት ተደርገው ይጠቀሳሉ፡፡ይህ ሁሉ በኮንስትራክሽን ባለሙያው ላይ ብቻ ሳይሆን አገልግሎት በሚያገኙ እንዲሁም በግንባታው አካባቢ በሚንቀሳቀሱ ሰዎች ላይ አደጋዎችን ሊያስከትል ይችላል።

በሀገሪቱ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ዘርፉን ለማዘመን እና ጥራቱን ለማስጠበቅ በሙያ ደህንነት እና ጤንነት ላይ መሻሻሎችን ለማምጣት ጥረቶች እየተደረጉ ይገኛሉ። ዜጎችን ከአደጋዎቹ ለመጠበቅ ብቻም ሳይሆን፣ የኮንስትራክሽን ዘርፉን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ለማሳደግ በተለይ የስራ ላይ ደህንነት እና ጤንነት ሰርተፊኬት እንደ አንዱና ዋነኛ መስፈርት ተደርጎም እየተሰራበት ነው። በመንግሥት በኩል አስገዳጅ የሆኑ የሕግ ማዕቀፎች ተግባራዊ ለማድረግ እየተሰራ ይገኛል። ለህንጻ ተቋራጮች የተለያዩ ስልጠናዎች እየተሰጡ ናቸው።

ከሰሞኑም የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራ ተቋራጮች ማህበር እና ከኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር ባዘጋጁት ስልጠና ለ194 የኮንስትራክሽን ሙያተኞች ስልጠና ተሰጥቷል፡፡ ሰልጣኞቹ ከማህበሩ የተለያዩ አባል ድርጅቶች የተውጣጡ ናቸው፡፡

የኮንስትራክሽን ሥራ ተቋራጮች ማህበር ፕሬዚዳንት ኢንጂነር ግርማ ሀብተማርያም በዚህ ወቅት እንዳስታወቁት፤ የሀገሪቱ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት እንዲኖረው ለማድረግ ከሚጠበቅበት መስፈርቶች አንዱ የኮንስትራክሽን የሙያ ደህንነት እና ጤንነት ጉዳይ ነው። በዚህ ጉዳይ ላይ በመንግሥት በኩል እርምጃ መጀመሩ፣ መንግሥት ዘርፉ ደረጃ በደረጃ እያደገ እንዲሄድና ዓለም አቀፋዊ ደረጃውን የጠበቀ ለማድረግ ያለውን ጥረት ያሳየ ነው ሲሉ ፕሬዚዳንቱ አስታውቀዋል።

በሀገሪቱ በተለይ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ እድገት አሳይቷል የሚሉት ኢንጂነር ግርማ፤ ይሁንና ሀገር በቀሉ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ከዘርፉ እድገት አልተቋደሰም ሲሉ ያመለክታሉ። እሳቸው እንዳሉት፤ ለዚህም ከሚጠቀሱት ምክንያቶች አንዱ እና በበርካታ የዘርፉ ተዋናዮች የሚታመንበት ምክንያት ግልፅ የሆነ የእድገት ፍኖተ ካርታ አለመኖሩ ነው።

ይህም በመንግሥት በኩል ትኩረት እንደሚሰጠው እና ወደ ተግባር ሊገባ እንደሚችል ተናግረው፣ ለተግባራዊነቱም እንቅስቃሴ እንደሚጀመር ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴዎች እየታዩ ነው ብለዋል። ማህበሩም እንደ አንድ የኢኮኖሚው ባለድርሻ አካል ለአሰራር ስርዓቱ ተግባራዊነት የበኩሉን በማበረከት ሀገራዊ ኃላፊነቱን እንደሚወጣም አረጋግጠዋል።

በኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት፣ በኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለሥልጣን እና በኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራ ተቋራጮች ማህበር በኩል የሶስትዮሽ የመግባቢያ ስምምነት ሰነድ መደረጉን አስታውሰው፣ በዚህ ስልጠናም የኮንስትራክሸን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት የላቀ የባለቤትነት ድርሻ እንደነበረው ጠቁመዋል። ፕሬዚዳንቱ ስልጠናውን በአምስት ዙር አጠናክሮ በማስቀጠል የኮንስትራክሽን የሙያ ላይ ደህንነት እና ጤንነትን በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ውስጥ ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጠው አሰራር ስርዓት እንዲሆን የበኩሉን ሚና እንደሚወጣ አስታውቀዋል።

የኮንስትራክሽን የሙያ ላይ ደህንነት እና ጤንነት በአሁኑ ወቅት በስራ ላይ እንዲውል እየተደረገ ባለው የሙያ ብቃት እና ማረጋገጫ መመሪያ ላይም እንደ አንድ አስገዳጅነት ያለው መስፈርት ሆኖ መቀመጡ፣ ጉዳዩ ከፍተኛ ትኩረት እንደተሰጠው እና አቢይ አጀንዳ መደረጉን ማየት ችለናል ብለዋል። በኮንስትራክሽን ስራ ተቋራጮች ማህበር በኩልም ሙያተኞቹን ለስልጠና በመላክ እና ለተግባራዊነቱ ከፍተኛ እንቅስቃሴ ማድረግ መጀመሩን አመላክተዋል። በመንግሥት በኩልም አስገዳጅ መመሪያ እንዲወጣ ከመደረጉ ቀደም ብሎ የሶስት ዓመታት የዝግጅት ጊዜ እንዲኖር መደረጉ መንግሥት በኃላፊነት ስሜት ሊመራው ማቀዱን ያሳየ መሆኑን ገልጸዋል።

የኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ታምራት ሙሉ በበኩላቸው የኮንስትራክሽን የሙያ ደህንነት እና ጤነነት ስልጠና እና አጠቃላይ የአሰራር ስርዓቱን አስመልክተው ሲያብራሩ እንደገለጹት፤ ሀገሪቱ ለካፒታል በጀት ከምትመድበው ትልቅ ሀብት 60 በመቶ ያህል ለኮንስትራክሽን ዘርፍ የሚመደብ ነው። በሀገሪቱ በርካታ የሚታዩ የልማት ስራዎችም የዘርፉ ውጤቶች ናቸው። የኮንስትራክሽን ዘርፉን አቅም ማሳደግ ሀገርን ማልማት ነው በሚል እየተሰራ ነው። በዚህ መሰረት የኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት የተለያዩ የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎችን ይሰጣል።

የኮንስትራክሽን የሙያ ላይ ደህንነት እና ጤንነት ጉዳይም በዓለም አቀፍ ደረጃ ትኩረት የሚስብ ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰው፣ ኢንስቲትዩቱም በዚህ ላይ ስልጠናዎችን በትኩረት እየሰጠ መሆኑን ገልጸዋል። በሙያ ደህንነት እና ጤንነት ላይ ተሰራ ማለት አምራች ኃይሉን መጠበቅ ማለት ነው ሲሉም አስገንዝበዋል።

ኢንጂነር ታምራት እንደተናገሩት፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከስራ ጋር ተያይዞ በሚያጋጥሙ የደህንነት እና ጤንነት አደጋዎች በአማካይ በዓመት ሁለት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን አካባቢ ሰዎች ለሞት ይዳረጋሉ። ከዚህ ውስጥ የ17 በመቶው ሞት ምክንያት የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው መሆኑን የዓለም የሰራተኞች ድርጅት መረጃ ያመለክታል።

የስራ ላይ ደህንነትና ጤንነት ላይ ከተሰራ ይሄንን አምራች ኃይል መጠበቅ ይቻላል። አደጋው በሰው ላይ ከሚያደርሰው ጉዳት በተጨማሪ በሀብት እና በገፅታ ላይ የሚያሳድረው ጉዳት ከፍተኛ ነው ሲሉም አስታውቀው፣ ይህን ችግር ለመፍታት ኢንዱስትሪው በደህንነት እና ጤንነት ላይ በትኩረት መስራቱ ተገቢ መሆኑን አመላክተዋል።

የኮንስትራክሽን ማኔጀመንት ኢንስቲትዩትም ከዚህ አንፃር ለደህንነት እና ጤንነት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው። በዚህ ላይ ዋነኛ የፊት ተዋናይ የሆኑትም የስራ ተቋራጮች መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ስልጠናውን ለስራ ተቋራጮች ለመስጠት ጥረት ሲደረግ መቆየቱን አስታውሰዋል።

እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ስልጠናውን አስመልክቶ አነስተኛ ፍላጎት እንደነበር ጠቅሰው፣ ከተወሰነ ጊዜ ወዲህም ግን በተለይ አሁን ያለው የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራ ተቋራጮች ማህበር ከኢንስቲትዩቱ ጋር ለመስራት ባለው ቁርጠኝነት የተነሳ ስልጠናዎችን በስፋት ለመስጠት ተችሏል ብለዋል። በአምስት ዙርም 194 ባለሙያዎችን ለማሰልጠን መቻሉን ተናግረዋል።

ኢንጂነር ታምራት እንዳስታወቁት፤ የኮንስትራክሽን ተቋራጮች የሙያ ላይ ደህንነት እና የጤንነት ሰርተፊኬት ለሀገር ውስጥ ገበያ ብቻ ሳይሆን ለዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትም ወሳኝ ነው። አሁን ባሉ ዓለም አቀፍ ጨረታዎች ላይ እንደ አንድ መስፈርት የሚታይም ነው። ደህንነት እና ጤንነት ላይ ሰርቲፋይድ መሆን፣ በአይኤስኦ ሰርቲፋይድ መሆን፣ ዓለም አቀፍ መስፈርት ናቸው። አሁን ያለው ፍላጎት ደግሞ የኛ ስራ ተቋራጮች በሀገር ውስጥ ብቻ እንዲቆዩ ሳይሆን፤ በአስር ዓመቱ የዘርፉ እቅድ ቢያንስ 25 በመቶ ገበያው ላይ ተወዳዳሪ ሆነው እንዲቀርቡ ነው ብለዋል።

የሀገር ውስጥ ስራ ተቋራጮችም ተወዳዳሪ እንዲሆኑ የውስጥ አሰራር ስርዓታቸውን ማዘመን አለባቸው ሲሉ ገልጸው፤ ለዚህም ሲባል ዓለም አቀፍ ደረጃዎችን የጠበቀ የአሰራር ሥርዓትን መጠበቅ የሚያስችሉ ስልጠናዎች ለተለያዩ ስራ ተቋራጮች መሰጠቱን አስታውቀዋል።

የኮንስትራክሽን ዘርፉን ተወዳዳሪነት ለማሳደግ የፕሮጀክት ማናጀሮችን በማብዛት እንደሚያስፈልግ ጠቁመው፣ ፕሮፌሽናል ማናጀሮች በስፋት ሲኖሩም ፕሮጀክቶችን በአግባቡ የመምራት አቅም ይኖራል፤ ብክነቶች ይቀንሳሉ፤ የስራ ላይ ደህንነትና ጤንነት እንዲሁም ሌሎች የሚፈለጉ መስፈርቶችን በአግባቡ መምራትም ይችላሉ ሲሉ አብራርተዋል።

እሳቸው እንዳሉት፤ መንግሥት በያዘው አቅጣጫ መሰረት የኮንስትራክሽን ዘርፉን ፍትሃዊ ከማድረግ አንፃር ዲጂታል ኢኮኖሚ ለመገንባት እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው። ለዚህም ችግሮችን አስቀድሞ ለመለየት የሚያስችሉት እንደ ቢም ቴክኖሎጂ በመሳሰሉት ላይ ስልጠናዎች በስፋት እየተሰጡ ናቸው፡፡ የፕሮጀክት ማኔጅመንት ስልጠናዎች፣ በጥራት፣ በደህንነት፣ በባለሙያ ቅጥር፣ በኮንትራት አስተዳደር፣ በዋጋ አስተዳደር፣ በፋይናንስ አስተዳደር፣ ስልጠናዎች እየተሰጡ ይገኛሉ። በኢንዱስትሪው ውስጥ ተወዳዳሪ ሆኖ መቀጠል ከተፈለገም እነዚህን ስልጠናዎች መውሰድ የተሰጠውንም ነፃ የስልጠና እድል መጠቀም እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ለኢኮኖሚው በአጠቃላይ ለሀገር እድገት በየትኛውም መስክ ካሉት ኢንዱስትሪዎች ይልቅ በጣም ተወዳዳሪ እና ተጨባጭ ውጤት መምጣት የሚያስችል ኢንዱስትሪ ነው።

ኢንዱስትሪው ጊዜያዊ የሆኑ ፈተናዎች በተለይም ከሙያ ክፍተት ጋር የተያያዙ ማነቆዎች ይታዩበታል፡፡ በተለይ ከትምህርት ስርአቱ ጋር ተያይዞ ያለው እና ንድፈ ሀሳብ ላይ ብቻ ያተኮረ ትምህርት ወደ ተግባር ሲወጣ መደነጋገር ሲፈጥር በየቀኑ የስራ ውሎ ላይ በግልጽ ይታያል።

ከግብዓት ጋር የሚያያዙ ጉዳዮች የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ፖሊሲ ፍኖተ ካርታ ማህበረሰቡን እና ጉዳዩ የሚመለከታቸውን በማሳተፍ ወደ ማፅደቅ ሂደት እየተገባ መሆኑን ጠቁመዋል። ዘርፉ በሁለንተናዊነት ከየት ወዴት እንደሚደረስ ፍኖተ ካርታው ያሳየናል ሲሉም ጠቅሰው፤ ይህ ብቻውን ግን በቂ እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡ ለተግባራዊነቱም ሁሉም በኃላፊነት ስሜት መስራት እንደሚገባው አመላክተዋል።

ሚኒስትሯ እንዳስገነዘቡት፤ በተለይ የስራ ላይ ደህንነትና ጤንነት ከኮንስትራክሽን ዘርፍ ጋር በቀጥታ የሚያያዝ ስለሆነ እያንዳንዱ ስራ ተቋራጭ እና የዘርፉ ባለሙያ ወደሚሰራባቸው ሳይቶች ተመልሶ ማየት ይገባዋል። ጥንቃቄ አድርጉ የሚል ፅሁፍ መጻፍ ብቻ በቂ አይደለም። ሄልሜት ብቻ ካለው በቂ ነው ብሎም የሚያስብ አለ።

መንግሥት አሁንም አንድ እርምጃ ወደፊት እየሄደ በዓለም አቀፍ ደረጃ አድናቆት የሚሰጣቸውን እንደ ቢም ቴክኖሎጂ ባሉት ላይ ጨምሮ በነፃ ስልጠና እየሰጠ መሆኑን አስታውቀዋል። ዜጎች በስራ ቦታቸው ላይ አደጋ እየደረሰባቸው መሆኑን ጠቅሰው፣ በስራው ላይ በቀጥታ የሚሳተፉት ብቻ ሳይሆኑ የአገልግሎት ተጠቃሚውም ጭምር አደጋ እየደረሰበት ነው ሲሉም አመልክተዋል፡፡ ለዚህም በተለይ አስገዳጅ የሆኑ የሕግ ማዕቀፎችን በቅርቡ ተግባራዊ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ይህም ዘርፉ በሀገር ውስጥ ተወዳዳሪ መሆን ብቻ ሳይሆን ወደ ሌሎች ጎረቤት ሀገራት ከተሳካም በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ዘርፍ መሆን አለበት ሲሉ ጠቁመው፣ በሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታት ውስጥ የሚፀድቀው የኮንስትራክሽን የስራ ላይ ደህንነት አስገዳጅ ህግ ሆኖ እንደሚወጣም ጠቁመዋል። እሳቸው እንዳሉት፤ በአንድ ስፍራ ላይ ኮንስትራክሽን አለ ከተባለ የግንባታው ብቻ ሳይሆን አካባቢው በሙሉ በግንባታ ተረፈ ምርት እየተጥለቀለቀ ከፍተኛ ጉዳትም እየደረሰ ነው። በከተሞች በሚሰሩ ሜጋ ፕሮጀክቶች፣ አረንጋዴ ስፍራዎች፣ የውሃ መፍሰሻ ቱቦዎች፣ በእያንዳንዱ በኮንስትራክሽን ግብዓት ተረፈ ምርቶች እየተሞሉ ናቸው። እነዚህን ዘርፉን የማይመጥኑ ብልሽቶች በሕግ ማዕቀፍ ማስተካከል ያስፈልጋል፡፡

ፈተናዎች ቢኖሩም ከተማንም ከተማ ለማድረግ ሀገርንም ሀገር ለማድረግ እና የሀገርን የኢኮኖሚ እድገት ለማረጋገጥ የኮንስትራክሽን ዘርፍ ትልቅ ሚና እንዳለው ጠቅሰው፣ ተቋራጮች ተወዳዳሪነታቸውን እንዲያሳድጉ የሚሰራው የግንባታ ስራ ሁሉ ቀጣዩን ትውልድ ታሳቢ ማድረግ እንደሚገባው ጠቅሰው፣ ለዚህም መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።

በኃይሉ አበራ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 29 ቀን 2016 ዓ.ም

 

Recommended For You