የክረምት ጫንቃዎች

ሕይወት ፈርጀ ብዙ ገጽታዎች አሏት፤ መውጣት እንዳለ ሁሉ መውረድም ይኖራል። ከመውረድ ውስጥም በትጋት መውጣት ይቻላል። አግኝቶ ማጣት እንዳለ ሁሉ አጥቶም ይገኛል። ይህ የሕይወት እውነታ ነው፤ በጥቂቶች የህይወት መውጣትና መውረዶች ውስጥ ብዙዎች ይማራሉ። የህይወትን ፈተናዎችም ያውቃሉ። በከፍታ ውስጥ የሚገኙት ‹‹እንዲህም ይኖራል እንዴ?›› ብለው ራሳቸውን ይጠይቃሉ። ለተቸገሩት ያዝናሉ፤ ካላቸው ቀንሰው የሌሎችን ችግር ይካፈላሉ፤ በተጨማሪም ችግር ብልሃትን ያስተምራል እንዲሉ ከችግር ጋር ተላምዶ ከመኖር ይልቅ ለመፍትሄ የሚታትሩትንም ያበረታታሉ። በመሆኑም ‹‹እንዲህም ይኖራል›› ብለን በከፈትነው አምዳችን ህይወትን በየፈርጁ ታስተውሉበት፤¸አስተውላችሁም ትማሩበት ዘንድ ጋበዝናችሁ። ለአስተያየቶቻችሁ፤ ለመሰል ታሪኮች ጥቆማችሁ እንዲሁም ለድጋፋችሁ የዝግጅት ክፍላችን አድራሻ ትጠቀሙ ዘንድ ጋበዝናችሁ።

ብዙዎች የሰኔን መምጣት በጉጉት ይጠብቃሉ:: ይህ ወር የክረምቱ መግቢያ በር ነውና የቸርነት እጁ ሰፊ ነው:: ወቅቱን ብርቱ ገበሬ ለእርሻው፣ተማሪው ለውጤቱ፣ ሰፊዋ መሬት ደግሞ ለውሃ ጥሟ ይሹታል::

በዚህ ክረምት በርካቶች ለፍሬያቸው ይተጋሉ፣ ጊዜውን ተጠቅመው ጎዶሏቸውን የሚሞሉ፣ ቤታቸውን የሚደጉሙ፣ ኑሯቸውን የሚለውጡ ብዙ ናቸው:: እርግጥ ነው . ክረምት የራሱ የሚባል ችግር አለው፣ ድንገቴው ጎርፍ፣ ብዙ ያጠፋል፣ ጭቃው ማጡ ያሰለቻል፣ ብርድ ቆፈኑም ይከብዳል:: እንዲያም ሆኖ ክረምቱ ጸጋው የበዛ፣ ሲሳይ ቱርፋቱ የበረከተ ነው::

ዘይነባ…

ማለዳውን ሻይ ቡናዋን ይዛ ከመንገድ ዳር የምትገኘው ዘይነባ ያለፉት በርካታ ክረምቶች ለእሷ መልካም ሆነው አልፈዋል:: በነዚህ ጊዜያት የአቅሟን ያህል አላጠችም:: በቀን ውሎዋ የምታገኘው ገቢ ለቤቷ ሙሉ ነበር:: ለትርፍ ባትሰራም፣ለወር ዕቁብ አታጣም:: ካላት ቆጥባ ከእጇ አብቃቅታ እንደራሷ ታድራለች::

ካገሯ ወሊሶ ከወጣች ሁለት አስርት ዓመታት የዘለለችው ወይዘሮ በአዲስ አበባ ኑሮ ያላየችው፣ ያልሞከረችው የለም:: በሰው ቤት ሰራተኝነት ዓመታትን ዘልቃለች:: በቀን ስራ ውሎ ጉልበቷን ከፍላለች፤ክፉ ደግ ያየችበት የትዳር ህይወት በቀላሉ ‹‹እንዲህ ነው›› የሚሉት አይደለም::

በቤት ኪራይ እንግልት፣ልጅ በማሳደግ ግዴታ ፣አብሮ በመኖር ጣጣ የከፈለችው ዋጋ ቀላል አይባልም:: ዛሬም ኑሮን ለማሸነፍ ከጎዳና ውላ ታመሻለች::ከብስኩት፣ ከአምባሻው አምስት፣ አስር ብላ የምትቆጥረው ገቢ አንዳንዴ የመጣበትን በወጉ አይመልስም:: ብክን፣ብትን ይልባታል:: የውሀ ቅዳ መልስ ህይወትን ለመቋቋም ስራ ባለበት መፍጠን፣ መሮጥ ልማዷ ነው::

አንዳንዴ ብስኩት አምባሻውን ተወት አድርጋ ከልብስ አጠባው ትገኛለች:: ድግስ ባለበት ሰፈር ሁሌም የወጥ ሰሪዎች ረዳት መሆን ብርቋ አይደለም:: ይህኛው ክፍያ ወዲያው ስለሚሰጣት ከሰራው መገኘት ምርጫዋ ነው:: የልብስ አጠባው ብር ቢዘገይም ባንክ እንዳለ ገንዘብ ትቆጥረዋለች::

የአጠባው ገንዘብ ጠርቀም ብሎ ሲደርስ ቀዳዳዎች ይሸፍናል::እንዲያም ሆኖ ስራው በቶሎ ላይገኝ ይችላል:: ሲገኝ ደግሞ ፈተና አያጣውም.ጉልበት ይጠይቃል፤ አቅምን ይፈትናል::በዚህ ስራ ሁሉም ጥሩና መጥፎ አይደለም:: አንዳንዶች ሲያሰሯት ከርመው ገንዘቧን ሊያዘገዩ፣አልያም ላይሰጡ ይችላሉ:: እንዲህ ሲገጥማት ሆድ ይብሳታል፣ ሀዘኗ ይልቃል::

አብዛኞች ግን እንዲህ አይደሉም:: ኑሮዋን ይረዳሉ፣ሸክሟን ያቀላሉ:: ካለችው በላይ ሰጥተው፣ለቤት ለልጇ የሚበጀውን ቋጥረው ይሸኟታል::ለእንዲህ አይነቶቹ ዘይነባ በእጅ በእግሯ ብትሰራ ቅር አይላትም፣ከተባለችው በላይ ፣ ስትታዘዝ ከልቧ ደስ እያላት ነው::

ብዙ ደንበኞቿ በእሷ ላይ ዕምነት ጥለዋል:: ልብስ ስታጥብ ከኪስ የምታገኘውን ገንዘብና ውድ ዕቃዎች ወደ ጉያዋ አትደብቅም:: በታማኝነት ይዛ ለባለቤቶቹ ትሰጣለች:: ይህ ማንነቷ መልካም ስም አሸልሟት ከደንበኞቿ አዝልቋታል::

ዘይነብ ከአንድ ዓመት በፊት መኖሪያዋ ከከተማው ወጣ ይል ነበር :: አካባቢው ከሌሎች ቦታዎች ለቤት ኪራይ የተሻለ ነው::ለእሷ አቅም ቀላል ባይሆንም ኑሮን በጉልበቷ ፣ በላቧ ወዝ ለማሸነፍ አስችሏታል:: የመንደሩ በረከት ለእሷና ለአንድዬ ልጇ ጉሮሮ አሳጥቷት አያውቅም:: ባላት ገዝታ ፣ ቤቷን ሞልታ ለማደር አቅም ሆኗት ዘልቋል::

ከአንድ ዓመት ወዲህ የዘይነባ ህይወት ካለፉት ዓመታት የተለየ ሆኗል:: የኖረችበት ሰፈር በልማት ምክንያት ከፈረሰ ወዲህ ወደመሀል ከተማ ልትመጣ ተገዳለች:: እንዲህ መሆኑ ለእሷ ቀላል አልሆነም:: በአቅሟ የቤት ኪራይ ማግኘት ፣ለስራዋ ቦታ መፈለግ ገቢዋን ማመጣጠን ሁሉ ፈትኗታል::

ከሁሉም በላይ የአንዲት ልጇ ጉዳይ ዕንቅልፍ ይነሳታል::ከአባቷ ጋር እሷ ከተወለደች ጥቂት ጊዜያት በኋላ ተለያይተዋል:: ጥሏት ከሄደ ወዲህ ለአንዲትም ቀን ዓይኗን አላየም:: በእሷ ትከሻ ብቻ የምታድገው ህጻን አሁን ሰድስት ዓመት አልፏታል:: እናት ለስራ በየሄደችበት ይዛት ትዞራለች:: ልብስ ስታጥብ፣እንጀራ ስትጋግር፣ብስኩትና ሻይ ስትሸጥ ሁሉ ከጉያዋ አትርቅም::

ዘይነባ ለአዲስ ኑሮ መሀል ከተማ ከገባች ጀምሮ ለልጇም ሆነ ለእሷ ህይወት አልቀለለም::ስለመኖር ብዙ ሞክራለች:: ድንች ቅቀላ፣በሚጥሚጣ ለመሸጥ ተቀምጣለች:: ስራውን ቀድመው ሌሎች መያዛቸው ግን ለገበያዋ አላመቸም:: እንደነሱ ጥሩ ቦታ ማግኘት፣ ደንበኞችን ማበራከት አልሆነላትም::

እሱን ትታ ደግሞ ብስኩትና አምባሻ፣ መሸጥ ጀመረች ::ሻይና ቡና በፔርሙስ ሞልታ ተጠቃሚውን ናፈቀች:: ለጥቂት ቀን ብትቸገርም ከሌላው ስራ የተሻለ ሆነላት::ለሊት ተነስታ የውሎዋን ለመሙላት ተፍ ተፍ ትላለች:: ዘይነባ እንዲህ ስታደርግ በየዕለቱ መሳቃቋ አልቀረም::ያለሰአቱ የምታበራው የአከራዮቿ አምፖል ፣ በየጊዜው የምታቀጣጥለው የከሰል ጭስ ከቀናት በአንዱ ጥያቄ እንዳያስነሳ ትሰጋለች:: ለመኖር ምርጫዋ ይህ ሆኗል:: ምንአልባት የእሷ ኑሮ ለሌሎች ከጎረበጠ ቀጣይ ዕጣ ፈንታዋን አታውቅም::

ባለሻይ…

አሁን ዘይነባ ሻይ ቡናዋን ይዛ ብስኩት አምባሽ ትሸጣለች:: ልክ እንደእሷ መተዳደሪያቸውን በዚህ ስራ ያደረጉ ቀድመው ለመሸጥ ይፎካከሯታል:: እንደእነሱ ቀድማ ለመገኘት መሮጥ፣መፍጠን አለባት::ይህ እንዳይሆን የትንሽ ልጇ አቅም የሚፈቅድ አይሆንም::

እሷ በተጠራችበት ስትሮጥ ህጻኗ ከኋላዋ ትከተላለች:: እናት ልጄን ‹‹አደራ››ብላ የምተውበት ምቹ ቦታ የለም:: ልጅቷ ግን ስለእሷ ህይወት የሚከፈለው ዋጋ የገባት ይመስላል:: እንደልጅ አትረብሽም፣አትቀብጥም::ቢርብ ፣ ቢጠማት ‹‹ስጭኝ›› ብላ አትጠይቅም:: የተሰጣትን ቀምሳ ውላ ታመሻለች:: ከማለዳ እስከምሽት ከእሷው ጋር ውላ ስትገባ ከበዛ ድካም ጋር ነው:: ጎዳና ውላ ማምሸቱን የለመደችው ህጻን ይህን ኑሮ እንደ ውዴታ ተቀብላ መኖርም ይዛለች::

አሁን የሰኔ ወር ሊሰናበት ጥቂት ቀናት ቀርተውታል:: እስካሁን ጅማሬው ለእሷ እንደ ክረምት አልጨከነባትም:: ጥቂት ዘንቦ ብልጭ የምትለው ጸሀይ ተስፋዋን እየሆነች ቀን አሻግራታለች:: ክረምቱ ሲገፋ፣ ውርጩ ሲበረታ ግን ሁሉም ያሳስባል ፣ጭቃ ማጡ ፈተና ይሆናል:: በተለይ እንደ ዘይነባ ቋሚ የስራ ቦታ ለሌለው ፣ሮጦ ተባሮ ለሚያድር ተስፈኛ ክረምት ዝናብ ብቻ አይደለም::

ዘይነባ ጓዘ ብዙ ነች::ስራ ለመሄድ ስታስብ ልጇን ጨም ሮ በርካታ ዕቃዎችን ተሸክማ ነው::ሳንቲም ለመቆጠብ ስትል በጋሪና በባጃጅ መሄድ ያለባትን መንገድ በእግሯ ትጓዛለች::እንዲህ ባደረገች ቁጥር ሰአት ይረፍዳል:: ድካምና ዝለትን ይዛ ስራ ቦታዋ ስትደርስ አዲስ ጉልበት ትጨምራለች:: የእጇን ለመሸጥ፣ እዚህም እዚያም መሮጥ ግዴታዋ ነው::

ክረምቱን…

ዘይነባ ክረምቱ አምርሮ የሚገባበትን የሀምሌ ነሀሴን ወር አስቀድማ ፈርታዋለች:: አምና ላይ በስራዋ መቀጠል ቢከብዳት እሸት በቆሎ እየቀቀለች፣ለመሸጥ ሞክራለች:: በቆሎውን ለመረከብ ፣ ጉልበት መክፈል ግድ ይላታል:: ጅማሬዋ እንዳሰበችው ባልሆነ ጊዜ ሁሉን ትታ ልብስ ማጠብ ጀምራ ነበር::

ዘንድሮ ደግሞ ከመጪው ክረምት ልትጋፈጥ፣ከብርድ ከጭቃው ልትታገል ቀን መቁጠር ይዛለች::እንደ አምናው ሁሉ ፈተና እንደሚገጥማት አልጠፋትም:: ከጀመረችው ስራ ‹‹ይብቃኝ›› ብላ አልቆመችም::አሁንም አማራጭን ፍለጋ ትተጋለች:: ዛሬም ስለመኖሯ ትሮጣለች::

ሁሌም በመንገዱ ዳርቻ ስለመኖር፣ የሚተጉ ፣ስለነጋቸው የሚያልሙ ነፍሶች ቀን ተሌት ንቁ ናቸው ::እነሱ በየግዜው መስራት መሮጥ ካልቻሉ ኑሮን አይገፉትም:: አብዛኞቹ ራሳቸውን የሚስተዳድሩ ወጣቶች መሆናቸው ሁኔታቸው ይለያል::

ሁሉም በሚባል መልኩ የተሻለ ህይወትን ፍለጋ ከትውልድ ሀገራቸው ወጥተዋል::እንዲህ ከሆነ በኋላ የእናት አባትን ምርቃት እንጂ ጥቅምን ማግኘት ዘበት ነው:: እንደውም ሰርተው ከሚያገኙት ለቤተሰብ መርዳት፣ማገዝ ግዳታቸው መሆኑን አውቀዋል::

ጫማ አሳማሪው…

ወጣት ማቲዎስ ዓለም ከትውልድ ሀገሩ ወላይታ አዲስ አበባ የገባው በዕድሜ ትንሽ ሳለ ነበር:: ገና ህጻን ሆኖ ከሰፈሩ ልጆች በዛ የሚሉት ወደከተማ እንደሚተሙ ሲሰማ ቆይቷል:: የልጅነት አእምሮው የእነሱን ለውጥና ዕድገት አበክሮ ይከታተል ነበር::

ጥቂት ከፍ እንዳለ በዕድሜ የሚያንሱት ጭምር አዲስ አበባ እየሄዱ መኖራቸውን አረጋገጠ:: ማቲዎስ በየቀኑ የሚሰማው የእናቶቻቸው ጨዋታ ለጆሮው ተለየበት:: ሁሌም የሚያወሩት ስለልጆቻቸው ጥሩ መኖር ፣ መብላትና መልበስ ነው::አንዳንዴ የሚታዘበው እውነትም ይህን ሀቅ ሲያረጋግጥለት ቆይቷል::

ማቲዎስ አንድ የዘመድ ልጅ ቤተሰቦቹን ጥየቃ ከሰፈራቸው ከርሞ መሄዱን ካየ ወዲህ ልቡ ይበልጥ ተነስቷል:: ዕድሜው ከእሱ የሚያንስ ቢሆንም ካሰበው ሲደርስ ምንም እንደማያቅተው ለውስጡ ነግሮታል:: እንደ እኩዮቹ አለመማሩ ከወላጆቹ አላራቀውምና :: ከእርሻና ከቤት ይውላል::

የልብ ሃሳብ…

አንድ ቀን ማቲዎስ የልቡ ሞላለት::በድንገት ከሰፈር ልጆች ተቀላቅሎ ከአካባቢው ራቀ:: የመንገዱ ፍጻሜ መዳረሻውን አዲስአበባ አደረገው:: ከማቲዎስ ጋር የነበሩ ልጆች መሀል ከተማ ሲገቡ በየአቅጣጫው ተበተኑ :: አብዛኞቹ ተቀባይ ዘመድ ነበራቸው::ከቆይታ በኋላ እሱና ሌላ አንድ ልጅ ብቻቸውን እንደሆኑ አወቁ::

ምሽቱ ገፍቶ ጨለማው ሲበረታ ሁለቱ እንግዳ ልጆች በጭንቀት ተዋጡ:: በዚህ ሥፍራ የሚጠሩት ዘመድ፣ የሚገቡበት ቤት የለም::በመፋጠጥ ሰአታት ተቆጠሩ ::አጋጣሚ ሆኖ ቋንቋቸውን የሰማ አንድ የሀገራቸው ልጅ ጠጋ ብሎ አዋያቸው:: እውነቱን ሳይደብቁ ከቤት ጠፍተው መምጣታቸውን ተናገሩ:: ልጁ ስሜታቸውን ለመጋራት አልዘገየም:: እሱም ከወራት በፊት ካገሩ የወጣው በተመሳሳይ አጋጣሚ ነበር::

የዕድል ጉዳይ ሆኖ የልጁ ኑሮ ከአንድ የጎዳና ጥግ ነው::ቀን ሲሮጥ ውሎ ማታ ጎኑ የሚያርፍበት ስፍራ አለው:: ዛሬ ደግሞ ከጓዳው፣ እንግዶችን ተቀብሎ ሊያስተናግድ ነው:: በዚህ መልኩ የጀመረው የአዲስ አበባ ህይወት እንደዋዛ ከወራት ተሻገረ::

እንግድነትን በብርታት …

ማቲዎስ ከተማውን ሲያውቅ፣መውጫ መግቢያው አልጠፋውም:: ለግዜው ለዕለት ጉርሱ ከመንገድ ቆሞ ሳንቲም መለመን ጀመረ:: ልጅነቱን ያዩ አልጨከኑበትም:: በሚያገኘው ገንዘብ ርሀብ ጥማቱን እያስታገሰ ቆየ:: በኋላ ግን የእሱ እኩዮች ጥንካሬ ውሰጡን ማረከው::

ያገኘውን እየሰራ ለብዙዎች እየታዘዘ ሳንቲም መያዝ የጀመረው ማቲዎስ :: ከሆቴል የሚያገኘውን ትራፊ እየጎረሰ የሊስትሮ ዕቃዎች ገዝቶ ያዘ:: ይህን ብርታት ያዩ አንዳንዶች የጎደለውን ሞልተው ‹‹አለንልህ›› አሉት::ደንበኞችን አብዝቶ ለማግኘት አፍታ አልዘገየም::ትናንትናን በልመና የሚያውቁት በርካቶች ስራውን በይሁንታ መረቁለት::

ትንሹ ልጅ ካገሩ የወጣበትን ምክንያት ዘንግቶት አያውቅም:: አገሩ ሳለ አዲስ አበባ ቆይተው በየመንደሩ የሚዘልቁ ሰዎች ገጽታ ትዝ ይለዋል:: እሱ ዛሬ ከቦታው ደርሶ ይህን ታሪክ ፈጥኖ አላገኘውም:: ትዝታው ግን አብዛኞቹ ራሳቸውን ለውጠውና በአለባበስ ዘንጠው ሲንጎማለሉ ያሳየዋል::

ይህ እውነት አብሮት ቢዘልቅ ያሰበውን ከማድረግ ወደ ኋላ አላለም:: የአቅሙን አጠራቅሞ ወላጆቹን ለማገዝ፣ራሱን ለማስደሰት ሞክሯል::ከጎዳና ኑሮ ወጥቶ ቤት መከራየት ከጀመረ ወዲህ ስለነገ ያላው ምኞት በእጅጉ በርትቷል::ቀለም ቡሩሹን ይዞ ጫማ ሊያሳምር ሲወጣ ደንበኞቹን ያከብራል:: ከብዙዎች ይግባባል::

ከዓመታት በኋላ…

እነሆ ! ዓመታት ነጉዱ::ማቲዎስ ልጅነቱ አልፎ ጉርምስናው ተተካ::ይህኔ የግራ ጎኑ አጋርነት አስፈለገው:: እንዳሰበው ሆነለት ::አቻውን አላጣም:: ሚስት አግብቶ ባለ ትዳር ሆነ:: ጥንዶቹ ዓላማቸው አንድ ቢሆን ጎጇቸው ሞቀ፣ደመቀ:: የሶስት ጉልቻን ወግ ሲጀምሩ መተሳሰባቸው ትርጉም ኖረው::

ማቲዎስ ለዓመታት እሱን ከመሰሉ ወጣቶች ጋር በአንድ ሆኖ ጫማ ሲያሳምር ቆይቷል:: እግረ መንገዱን የሚያገኘው ድለላም ገቢ ሲያስገኝለት፣አቅሙን ሲደጉምለት ነበር:: አሁን እንደ ቀድሞ ብቻውን አይደለም:: ሚስቱን ጨምሮ ሁለት ልጆችና አንድ ራሱን በኃላፊነት ይመራል::

ክረምትን በፍራቻ…

ማቲዎስ የዘንድሮውን ክረምት የፈራው ይመስላል::ቀድሞ ክረምት ‹‹መጣሁ ባለ ጊዜ ደስታው ልዩ ነበር:: ከበጋው በተለየ ደንበኞቹ ይጎበኙታል፣ጉርሻና ገበያው ይደራል፣አንገቱን ደፍቶ ጫማውን ሲጠርግ፣ሲያስምር ምሳ ለመቅመስ ጊዜ አልነበረውም::ይህ ወቅት ለድሀ ጎጆው በረከት የሚሰጠው ተናፋቂ ጊዜ ነበር::

ሊስትሮው ማቲዎስ አሁን ያለበት የስራ ቦታ የቀድሞው አይነት አይደለም::ፒያሳና አካባቢው በልማት ከተነሳ በኋላ ከደንበኞቹ ተለያይቶ አካባቢን ቀይሯል::ዛሬ ቋሚ ቦታ ማጣቱ ስራውን አዳክሞታል::እንደበፊቱ ጊዜና ሰአት አንሶት አያውቅም ::እንደምንም ተባርሮ የሚያገኘው ስራ ከሌሎች እያጋፋ ሲያገላምጠው ይውላል::

ልክ እንደዘይነባ ሁሉ ክረምቱን እያሰበ የሚጨነቀው ወጣት በመጪው ጊዜ ምን ማድረግ እንዳለበት አላቀደም:: እንደበፊቱ ቢሆን የክረምቱ መድረስ እንደዝናቡ በረከቱ ነበር:: ደንበኞችን ያፈራል፣ ስራውን አብዝቶ፣ ገቢውን ይጨምራል::

አሁን ማቲዎስ ‹‹ሊስትሮ›› ነኝ ቢልም ስለሚሆነው ሁሉ እርግጠኛ አይደለም:: በፍቅር የሚወደውን የሊስትሮ ሙያ እንደዋዛ መተው ባይሻም አሁን ውስጡ ከሌላ ዕቅድ እያደረሰው ነው:: ያገኘውን ለመስራት ወደኋላ አይልም::ከእሱ ልፋት በስተጀርባ እጁን የሚጠብቁ ሚስትና ልጆቹ በእሱ ጫንቃ ሲያድሩ ቆይተዋል::

ዛሬ ደግሞ የክረምቱ ጫና ከጫንቃው የተጫነ ያህል ቢሰማው ዛሬን ለመኖር ከሸክሙ፣ከጥበቃው፣ ከመላላኩ ስራ ተገኝቷል:: ጥሩው ነገር ተግባቢውን ማቲዎስ ፊት የሚነሳው የለም:: ለአዲሶቹ ስራዎችና ለአካባቢው እንግዳ ቢሆንም መልካምነቱን የሚያውቁ ሁሉ ‹‹አለንህ›› ይሉታል::

ተመሳስሎን በመፍትሄ …

ዘይነባንና ማቲዎስን የመሰሉ፣ህይወት እንጀራቸው ከጎዳናው ሲሳይ የተጣመረ ነፍሶች በአንዳንድ አጋጣሚ ከኑሯቸው ሸርተት የሚሉበት ሰበብ አይጠፋም:: እንዲህ አይነቶቹ ብርቱዎች ከራሳቸው አልፈው ሌሎችን የሚያኖሩ ናቸውና የመልካም ሰዎች በጎ ዓይኖች ሊያዩ ፣ሊጎበኙዋቸው ይገባል::

መልካምሥራ አፈወርቅ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 29 ቀን 2016 ዓ.ም

 

Recommended For You