የሰዎች የእለት ተእለት ክዋኔ በውሳኔ የተሞላ ነው:: በእያንዳንዱ የሕይወት እንቅስቃሴያቸው ውስጥም ሰዎች የተለያዩ ውሳኔዎችን ያሳልፋሉ:: ከዚህ አንፃር ውሳኔ የሰው ልጅ አንዱ የሕይወት አካል እንደሆነ ይቆጠራል:: የሰውን ልጅ ከፍና ዝቅ ከሚያደርጉት ነገሮች ውስጥም የመወሰን አቅሙ እንደሆነ ይነገራል:: ለዛም ነው ውሳኔን በራስ፣ በኑሮና በሕይወት ላይ ማስተላለፍ እጅግ ቁልፍ ጉዳይ ነው የሚባለው::
ውሳኔ አንድን ነገር የማድረግና ያለማድረግ ምርጫ ነው:: አንድን ነገር ለማድረግና ላለማድረግ በመምረጥ ሂደት ግን ማመንታት፣ ለመወሰን መቸገር፣ ቸኩሎ አልያም ደግሞ ዘግይቶ መወሰን፣ ለመወሰን ከራስ ጋር ሙግት መግጠምና ሌሎችም መሰል እንቅፋቶች ያጋጥማሉ:: ዋናው ቁም ነገር ግን የተሰላ ውሳኔ መወሰን ውጤቱ ምን ያህል ጠቃሚ እንደሆነ መረዳት ያሻል:: በተለይ ደግሞ ከውሳኔ በፊት የውሳኔውን ውጤት በጥልቀት መረዳት የተሳሳተ ውሳኔ ከማሳለፍ ይታደጋል::
ለምሳሌ አንድ ሰው በቀን አንድ ገፅ መፅሃፍ ለማንበብ ወስኖ ያለውን ካደረገ አእምሮውን ለማሳደግ ቆርጦ ተነስቷል:: በየቀኑ ለተወሰኑ ደቂቃዎች የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ለማድረግ ከወሰነ የአካል ብቃቱን እያሳደገ ነው:: ይህ ሲባል እግረ መንገዱን የሰውነቱን ጤና ከመጠበቅ በዘለለ ትንፋሹን፣ ፅናቱንና ነገሮችን የመቋቋም አቅሙን እያጎለበተ ነው:: ይህ ሁሉ የሚመጣው ታዲያ በውሳኔ ነው::
በጣም ለሚወደው ነገር ትልቅ ትኩረት ለመስጠት የወሰነ ሰው የገነዘብ ስኬት ወደሚሰጠው ነገር ራሱን እየወሰደ ነው:: የማኅበረሰብ ወይም የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ላይ የተወሰነ ግዜ ለመስጠት የወሰነና ያለውን የሚፈፀም ሰው የሕሊና እርካታ ወደሚሰጠው ነገር እየተጓዘ ነው:: ለሚወዳቸው ሰዎች፣ ለቤተሰቦቹ፣ ለጓደኞቹ፣ ለፍቅረኛው ግዜ ለመስጠት የወሰነ ሰው ስሜታዊ እርካታ ለሚሰጠው ነገር እየጣረ ነው:: ታዲያ አንተስ መቼ ነው በአካል፣ በፋይናስ፣ በስነ-ልቦና፣ ለስሜትና ደስተኛ ለሚያደርጉ ነገሮች ግዜ ለመስጠት የምትወስነው መቼ ነው?
አንዳንድ ሰዎች ‹‹ደስተኛ ወይም ስኬታማ ያልሆንኩት የምፈልገው ነገር ስላልተሟላልኝ ነው፤ በቤተሰቦቼ ምክንያት ነው፤ በዙሪያዬ ባሉ ጓደኞቼ ምክንያት ነው ወይ ደግሞ በምኖርበት ሀገር ድህነት ምክንያት ነው›› ሊሉ ይችላሉ:: እነርሱ እነዚህን እንደምክንያት ቢዘረዝሩም ታዲያ ምክንያታቸው ውሃ የሚቋጥር አይደለም:: ምክንያቱም መወሰን ስላልቻሉ ነው:: እነዚህ ሰዎች የሚፈልጉትን ነገር በእጃቸው ለማስገባት ቢወስኑ ኖሮ ለዛ ነገር የሚከፈለውን ዋጋ ሁሉ ከፍለው ማሳካት አያቅታቸውም ነበር::
አንድ ጀልባ ቀዛፊ የልጅነትና አብሮት የተማረ ጓደኛው ከሀገሪቱ ንጉስ ቀጥሎ ትልቅ ስልጣን የሚባለውን ጠቅላይ ሚኒስትርነት እንዴት ሊያገኝ እንደቻለ ሁሌም እንቆቅልሽ ይሆንበታል:: እሱ ከኔ ምን የተለየ ነገር ቢኖረው ነው እኔ እዚህ ውሃ ለውሃ ጀልባ ለመቅዘፍ እየተንከራተትኩ እሱ ጠቅላይ ሚኒስትር የሆነው ብሎ ሁሌም አምርሮ ይቀናና ይናደድ ነበር::
በአንድ አጋጣሚ የሀገሪቱ ንጉስ ከባድ ውሳኔዎችን ለማስተላለፍ የሚያደርጉትን ስብሰባ ለማካሄድ ካቢኔያቸውን ሰብስበው ያንን ወንዝ መሻገር ነበረባቸውና የዚህን ሰው ጀልባ ይሳፈራሉ:: ጀልባውን ተሳፍረው ወንዙን ከተሻገሩ በኋላ ንጉሱና ካቢኔያቸው ማታ ከወንዝ ማዶ ጊዚያዊ ድንኳን አዘጋጅተው ባረፉበት ወቅት ሌሊት ላይ ለቅሶ ያዘለ ከባድ ጩኸት ይሰማሉ:: ከዛም ባለጀልባውን አስጠርተው ጩኸቱ ምን እንደሆነ ይጠይቁታል::
ባለጀልባውም ቆይ አረጋግጬ ልምጣ ብሏቸው ትንሽ ቆይቶ ተመልሶ ይመጣና ድመት እንደጮኸች ይነግራቸዋል:: ‹‹የጫካ ናት ወይስ የቤት ድመት?›› ብለው ሲጠይቁት ‹‹ቆይ እሱንም አረጋግጬ ልምጣ›› ብሎ ተመልሶ ሄዶ አራጋግጦ ይመጣና ‹‹የቤት ድመት ነች ለማዳ ናት›› ብሎ ይመልሳል:: ‹‹አሃ! ምን ሆና ነው ግን የጮኸችው›› ብለው ይጠይቁታል:: አሁንም ‹‹ንጉስ ሆይ አሁንም ሄጄ አረጋግጬ ልምጣ›› ብሎ ተመልሶ ሄዶ ይመጣና ሙጭሊቶች በምትወልድበት ግዜ እንደጮኸች ይነግራቸዋል:: ንጉሱም ‹‹ስንት ልጆች ወለደች?›› ብለው ይጠይቁታል:: ‹‹ቆይ ንጉስ ሆይ እሱንም አረጋግጬ ልምጣ›› ይላቸውና አሁንም ደርሶ ይመለስና አራት ሙጭሊቶች እንደወለደች ይነግራቸዋል::
ንጉሱ አሁንም መልሰው የሙጭሊቶቹ ቀለማቸው ምን አይነት እንደሆነ ይጠይቁታል:: እርሱም አሁንም አረጋግጬ ልመለስ ይላቸውና ደርሶ ይመለሳል:: ሁለት ጥቁር ሁለት ነጭ ሙጭሊቶች እንደወለደች ይነግራቸዋል:: ‹‹እንዴ እናትዬዋስ ቀለሟ ምን ይመስላል›› ብለው ንጉሱ ሲጠይቁት ንጉስ ሆይ እሱንም አረጋግጬ ልምጣ ይላቸውና ተመልሶ መጥቶ የእናትዬዋ ቀለም ነጭ በጥቁር እንደሆነ ይነግራቸዋል::
በዚህ ግዜ ንጉሱ ታዲያ ለድመቷ ምን አደረክላት ብለው ጀልባ ቀዛፊውን ይጠይቁታል:: እርሱም ንጉስ ሆይ ቆይ አንድ ነገር አድርጌላት ልምጣ ብሎ ሊሄድ ሲል ቆይ ቆይ አንተ እዚሁ ጋር ቆየኝ ብለው እዛው በቆመበት የሀገሪቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ካረፈበት ድንኳን አስጠርተው ‹‹የሆነ ጩኸት ሰምቼ ነበር እስኪ ምን እንደሆነ አጣራ›› ብለው ይልኩታል:: ጠቅላይ ሚኒስትሩም እሺ ብሎ ከአፍታ ቆይታ በኋላ ይመለሳል::
ጩኸቱ የተሰማው አንድ ጥቁር በነጭ ቀለም ያላት የቤት ድመት አራት ሙጭሊቶች በወለደች ቅፅበት እንደሆነና የወለደቻቸው ሙጭሊቶችም ሁለት ነጭ ሁለት ጥቁር ሲሆኑ ለእናትዬዋ ምግብና ወተት እንደተሰጣት እርሷና ሙጭሊቶቿ ለማዳ የቤት ድመት በመሆናቸው የዱር አውሬ እንዳያጠቃቸው አስተማማኝ በሆነ አጥር እንደከለሏቸው ይናገራል::
ንጉሱም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ላቀረበላቸው ሪፖርት አመስግነው ካሰናበቱት በኋላ ወደጀልባ ቀዛፊው ዞረው እንዲህ አሉት:: ‹‹ጀልባህን ተሳፍረን ስንመጣ ጠቅላይ ሚኒስትሩን እያየህ ሲሰማህ የነበረውን የቅናት ስሜት አስተውዬው ነበር:: የኔና የእርሱ ልዩነት ምንድን ነው ብለህ ለራስህ ስጠይቅ እንደነበረም እገምታለሁ:: አንተ ብዙ ግዜ ተመላልሰህ ሁኔታውን ተመልክተህ ያልወሰንከውን ውሳኔ እርሱ በአንድ ምልታ ወጥቶ ወስኖ ነገሮችን አስተካክሎ መጣ::››
እንግዲህ በሕይወታችን ውስጥ ወደተለያየ አቅጣጫ የእኛን በሳል ውሳኔዎች ሊጠይቁ የሚችሉ ወቅቶች ይመጣሉ:: እነዛን ወቅቶች ግን የምናልፋቸው ወይም የምንወስናቸው በየትኛው ጥበባችን ነው? በሕይወታቸው ላይ አስገራሚ ለውጥ ያመጡ ሰዎች ከባድ ውሳኔዎችን ወስነው እዛ እንደደረሱ አስብ:: አንተ ራሱ አሁን የደረስክበትን ደረጃ የወሰነልህ ከዛሬ አምስትና አስር ዓመት በፊት ታደርጋቸው የነበሩ ነገሮች ናቸው:: ታነባቸው የነበሩ መፅሃፍት፣ ታያቸው የነበሩ የቴሌቪዥን ሾዎችና ፊልሞች፣ ትሰማቸው የነበሩ ዘፈኖች፣ በዙሪያህ ይሰበሰቡ የነበሩ ጓደኞችህ፣ አብረሃቸው የምትውላቸው ሰዎች ናቸው ዛሬ የቆምክበትን የወሰኑልህ::
ታዲያ አንድ ነገር አስተውል:: የዛሬ አምስት ዓመት የሚኖርህንም ሁኔታ የሚወስኑት አሁን የምታደርጋቸው ነገሮች ናቸው:: ስለዚህ በቶሎ ወስን:: ሚዛን ወደምትፈልገው አቅጣጫ እንድታጋድል ከፈለክ ያን አቅጣጫ ጫን አድርገህ መያዝ ብቻ ነው የሚጠበቅብህ:: ስለዚህ አንተም የዛሬ አምስትና አስር ዓመት መሄድ ወደምትፈልግበት አቅጣጫ ሚዛን እንድታጋድል አሁኑኑ ወስንና ውሳኔህን ተግባራዊ ለማድረግ ወስን:: ውሳኔ ከዚህ በላይ ምንም አይጠይቅም:: ሕይወት ቀያሪ ነገር ነው ተጠቀምበት:: ነገር ግን ደግሞ ትክለኛ ውሳኔ በትክክለኛው ቦታና ሰዓት ለመወሰን ከፈለክ የሚከተሉትን ስድስት ነጥቦች ተከተል::
1ኛ. ችግሩን ጠንቅቆ ማወቅ
ምንም ሰው አንድ ውሳኔ ከማሳለፉ በፊት መሰብሰብ ያለበትን መረጃዎች ሁሉ መሰብሰብ ይኖርበታል:: ማወቅ ያለበትን ነገር ሁሉ ማወቅ አለበት:: ይሁንና ስለሚወስነው ነገር በቂ መረጃ ከሌለው ግራ ይጋባል:: ይሁንና መረጃ መሰብሰብ ሲጀምር በቂ እውቀት ኖሮት እርገጠኝነትና ልበ ሙሉነት ይሰማዋል:: እንዲያም ሆኖ ከመጠን በላይ መረጃ ከተሰበሰበ ደግሞ መልሶ ግራ መጋባት ይመጣል:: ስለዚህ በቂ መረጃ ሲኖር መወሰን የግድ ይላል::
እዚህ ጋር በቂ መረጃ እንዳለ እንዴት ሊታወቅ ይችላል የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል:: ለዚህ መልስ ባይኖርም በቂ መረጃ ሲኖር እርገጥኝነት ይሰማል:: ለእርግጠኝነት የቀረበ ስሜት ሲሰማ ደግሞ መወሰን ያስፈልጋል:: ምክንያቱም ያኔ በቂ መረጃ ተይዟል ማለት ነው::
2ኛ. የሚወሰነው ውሳኔ ከሕይወት ዓላማ ጋር አብሮ መሄድ አለበት
ለዛሬ ወይም ለግዚያዊ ጥቅም ብለን ቀላል ውሳኔ መወሰን የለብንም:: ዘላቂውን ጥቅም ማስቀደም አለብን:: ነገ ምን ሊፈጠር ይችላል፤ ምን ላገኝ እችላለሁ፤ ምን ልጎዳ እችላለሁ ብለን ማሰብ አለብን:: ምንም ነገር ከመወሰናችን በፊት ነገን ማሰብ ይኖርብናል:: ውሳኔያችን ከሕይወት አላማችን፣ ከነገው ፍላጎታችን፣ ከመዳረሻችን፣ ከማንነታችን ጋር አብሮ እንደሚሄድ እርግጠኛ መሆን አለብን::
3ኛ. ሌላ ሰው እንደምንመክር አስበን መወሰን
እንደምታውቁት ለሌሎች ሰዎች መምከር እንችልበታለን:: ሰዎች ምን ቢያደርጉ ምን እንደሚሳካላቸው እናውቅበታለን:: ለራሳችን ነው የማናውቀው:: ጠንቋይ ለራሱ አያውቅም ይባላል:: እኛም ብንሆን ብዙ ግዜ ለሰው እንጂ ለራሳችን አናውቅም:: ስለዚህ ራሳችን የገጠመን ችግር ሌላ ሰው እንደገጠመው አስበን ራሳችንን መምከር ያስፈልጋል:: እንደሁለተኛና ሶስተኛ ወገን አይተን ራሳችንን ‹‹እንዲህ ብታደርግ እንዲህ ይፈጠራል፤ እንዲህ ብታደርግ ይሄ ነው መፍትሄው›› እያልን ራሳችንን መምከር ይገባል:: ያኔ ከጫና እንውጣለን:: ምክንያቱም እኔ አይደለውም ችግር ውስጥ የገባሁት እንላለን:: ያኔ ብዙ መፍትሄ ይመጣል:: ከመፍትሄዎቹ መካከል ጥሩውን መርጠን መወሰን ነው::
4ኛ. ውጤቱን ማነፃፀር
አንድ ነገር ከመወሰናችን በፊት ‹‹ያ የምንወስነው ውሳኔ ምን ሊያስከትል ይችላል፤ እንዲህ ብማር ነገ ደስተኛ ላልሆን እችላለሁ፤ እንዲህ ብሰራ ስራው ላያድግ ይችላል፤ ይህን ቢዝነስ ብጀምር እኮ መጨረሻ ላይ ሄዶ ሄዶ እዚህ ጋር ሊያቆም ይችላል›› ብለን ብዙ ነገር አስበን ውጤቱን አሰላስለንና አወዳድረን መወሰን ያስፈልጋል:: እንደዛ ካላደረግን መጨረሻ ላይ የሚመጠው ውጤት ከባድ ይሆናል:: ምክንያቱም አሁን ያለንበት ጋር ቆመን ብቻ ማየት የለንበትም:: ስለዚህ አንድ ነገር ከመወሰናችን በፊት ውጤቱን ማሰብና አስቀድሞ መተንበይ አለብን:: ከዛ በኋላ የሚጎዳ ከሆነ መተው፤ የሚጠቅም ከሆነ ደግሞ መቀጠል ነው::
5ኛ. በየቀኑ የምንወስናቸው ትናንሽ ውሳኔዎች ላይ መለማመድ
በቀን ውስጥ በጣም ብዙ ውሳኔዎችን እንወስናለን:: ጠዋት ስንት ሰዓት ልነሳ፣ ስራ ልግባ አልግባ፤ ምን ልብላ፤ ከማጋር ልዋል፤ ምን ሳደርግ ልዋል፤ ምን ላድርግ፤ በምን ልዝናና፤ ምን ስሰራ ላምሽ፤ ምን ልጠጣ፤ ምን ልብላ …. ወዘተ ብዙ ውሳኔ አለ:: እነዚህ ውሳኔዎች ግን ሕይወታችንን እስከመጨረሻ ድረስ ሊቀይሩት ይችላሉ:: ምክንያቱም የዛሬ አምስት ዓመት በፊት ታደርጋቸው የነበሩ ነገሮች፣ አብርሃቸው ትውላቸው የነበሩ ሰዎች፣ ታያቸው የነበሩ የቴሌቪዥን ፊልሞች፣ ድራማዎች፣ ታነባቸው የነበሩ መፅሃፍቶች፣ አብራሀቸው ትሰበስባቸው የነበሩ ሰዎች በሙሉ ዛሬ የደረስክበትን ደረጃ ወስነዋል:: ዛሬ የምታደርጋቸውም ነገሮች የዛሬ አምስትና አስር ዓመት የምትደርስበትን ይወስናሉ:: የዛሬ አምስት ዓመት ያደረከው ከዛሬው ጋር ተመሳሳይ ከሆነ የዛሬም አምስት ዓመት አሁን ያለህበት ቦታ ነው የምትኖረው::
ስለዚህ በየቀኑ የምታደርጋቸው ትናንሽ ውሳኔዎች ሕይወትህን እስከመጨረሻው ይቀይሩታል:: አስተውል ትልቁን መርከብ የሚያሰምጠው ማእበል ብቻ አይደለም:: ከታች በትንሽዬ ቀዳዳ ውሃ መግባት ከጀመረ የግዜ ጉዳይ ነው እንጂ መርከቡ መስጠሙ አይቀርም:: ስለዚህ አንተም የምትወስናቸው ውሳኔዎች በሙሉ ሕይወትህን ሊቀይሩት ይችላሉ:: እነዚህ ትናንሽ ውሳኔዎች ላይ ብልጥ ከሆንክ፣ ጥበበኛ ከሆንክ ትላልቆቹ ውሳኔዎች ሲመጡ መወሰን አይከብድህም:: ምክንያቱም በትናንሾቹ ጥሩ በራስ መተማመን ይሰማህልና::
6ኛ. ከውሳኔ በኋላ ማመንታት የለብንም
ይህ ወሳኝ ነጥብ ነው:: ከውሳኔ በኋላ ማመንታት የለብንም:: አንዳንድ ግዜ ጥሩ ውሳኔ እንወስንና ቆይ እስኪ ይህን ነገር ባደርገው ብለን ማመንታት ከጀመርን ሌላ የማይረባ ውሳኔ ይከተልና እሱን ወስነን የማይረባ ነገር ይፈጠራል:: ስለዚህ በደምብ አስበን ከወሰንን በኋላ ወደ ድርጊት መግባት አለብን:: እርግጥ ወሰንን ማለት ወደ ድርጊት ገባን ማለት አይደለም::
ስለዚህ ከላይ የተቀመጡት አምስት ትክክለኛ ውሳኔ ለማሳለፍ የሚረዱ ነጥቦችን ከተጠቀማችሁ መወሰን አለባችሁ:: መወሰን ግን ብቻውን በቂ አይደለም ወደገደለው ወደ ድርጊት መግባት ይኖርባችኋል:: ያ ማለት ስድስተኛውን ነጥብ ልብ ማለት ይገባል::
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 29 ቀን 2016 ዓ.ም